ከባድ የወር አበባ ህመም ባይሆንስ?
- Zebeaman Tibebu
- Mar 8
- 5 min read
ጸሀይ ብርሀኗን ከፈነጠቀች ሰአታት ተቆጥረዋል። ስራ ለመሄድ ጓጉታ በጠዋት የተነሳች ቢሆንም ፤ አልቻለችም። በታችኛው የሆድ ክፍሏ ላይ እንደ ስለት የሚቆርጥና የሚጠዘጥዝ ህመም ቀስፎ ይዟታል።
ከቤት ለመውጣት ህመሙን ማስታመም ጀመረች። ብርቱ ቢሆንም ፤ "የወር አበባ ህመም ነው" ብላ ለራሷ ነገረችው። ወር አበባዋ ከመጣ ሁለተኛ ቀኗ ነው። ህመሙ ከባሰባት ግን አመታት ተቆጥረዋል። ሆኖም ማንም ሊረዳት አልቻለም።
"ይሄ የሴት ልጅ እዳ ነው! አይዞሽ ጠንከር በይ" የሚላት እንጂ ፤ ምናልባት ሌላ ችግር ይኖራል ብሎ የጠረጠረም የለም። ህመሙን አሸንፎ ለመውጣት ትግሉን ተያያዘችው።

ለመጠርጠርስ የሚያበቃ ምን አለ?
ሁሉም ሴት አንድአይነት ወርሃዊ ኡደት ያካሂድ እንጂ ህመሙ ለየቅል ነው። ብዙም ህመም ሳይሰማቸው የሚያሳልፉ ጓደኞች አሏት። በየቀኑ ሁለት ህመም ማስታገሻ ካልዋጡ ህመሙን የማይችሉም ታውቃለች። የሷንም በተፈጥሮ ጸና ከሚልባቸው መሀል አድርጋ አስባለች።
ህመሙ አቅም የሚያሳጣ ነው። ፊቷ በላብ ተጥለቅልቋል። የድካም ሸክም እየተጫጫናት ነው። ስራ ካልሄደች ልትባረር ትችላለች።
እናስ ምን ተሻላት?
እሷን ያጋጠማት ተራ ምቾት ማጣት አይደለም፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን በዝምታ የሚያሰቃየው፣ ነገር ግን ብዙም የማይነገርለት “ኢንዶሜትሪዮሲስ” የተሰኘው በሽታ ነው።
ኢንዶሜትሪዮሲስ ምንድን ነው?
በተፈጥሮ በሴት ልጆች ላይ የማህጸን ግድግዳ የተለያዩ ለውጦችን ያካሂዳል። የወርሃዊ ኡደቱ የሚያልቀው ፤ ጽንስን ለመቀበል ተዘጋጅቶ የነበረው የማህጸን ግድግዳ ፈርሶ ፤ በወር አበባ መልክ ሲወጣ ነው። ሂደቱም መልሶ እንደ አዲስ በቀጣይ ወር ይጀምራል።
የማህጸን ግድግዳ ህዋሳት ከማህጸን ውጭ ቢያድጉስ ምን ይፈጠራል?

በማህፀን ውስጥ የሚገኘው ህብረ ህዋስ (Endometrium) ከማህጸን ውጭያለቦታው በኦቫሪ (እንቁላል ማቀፊያ)፣ በማህፀን ቱቦዎች፣ በአንጀት ወይም በሽንት ፊኛ ላይ ሊያድግ/ሊጣበቅ ይችላል። ይህም ያለቦታው ያደገ የማህጸን ህዋስ በየወሩ የሴት ልጅ ሰውነት ኡደትን ተከትሎ ለውጥ ያካሄዳል።
ታድያ ችግር የሚፈጥረው የወር አበባ ሲታይ ነው። ያለቦታው ስላደገ ፤ ይህ የማህጸን ህዋስ ሲፈርስ በወር አበባ መልክ ወደ ውጭ አይወጣም። አጠገብ ያሉ አካላት ላይ ደሙ ይፈሳል። ይህም ስር ለሰደደ ሰውነት መቆጣት ፣ ለኢንፌክሽን ፣ እና ለጠባሳ ህመም ይዳርጋል። ህመሙም ከወር አበባ እጅጉን ያየለ ነው።
ስርጭቱ ምን ይመስላል?
እንደ ዓለም አቀፍ የጤና መረጃዎች ከሆነ፣ በመውለጃ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ 10 ሴቶች መካከል አንዷ በዚህ ስውር በሽታ ትጠቃለች። ይህ ማለት በዓለም ዙሪያ ወደ 190 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች እንደ ባለታሪኳ በዝምታ ይማቅቃሉ።
በኢትዮጵያ ደግሞ ፈተናው ይበልጥ ይበረታል። በሀገራችን ካለው ማህበራዊ እይታ አንጻር፣ ከባድ የወር አበባ ህመም እንደ “ተፈጥሯዊ” ወይም “የሴትነት እጣ ፈንታ” ተደርጎ ብቻ ነው የሚወሰደው። ህመሙ ቢበረታም ብዙዎች በዝምታ እንዲታገሱት ይገፋፋሉ። በዚህም ምክንያት አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት ትክክለኛውን የህክምና ምርመራ ለማግኘት ከ5 እስከ 10 ዓመታት ሊፈጅባት ይችላል።
በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግሩት ምልክቶቹ

ኢንዶሜትሪዮሲስ ህመም ብቻ አይደለም ፤ ሕይወትን በማይታዩ መንገዶች ያውካል። ሰውነታችን ይህ ችግር እንዳለ የሚገልጽባቸው ቁልፍ ምልክቶች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ የሚሄድና በተራ ማስታገሻ የማይታገስ የወር አበባ ህመም።
ከወር አበባ ውጭ ያለ የዳሌ ህመም — በእንቁላል መውጫ (ovulation) ወቅት የሚብስ አልያም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጊዜ በዳሌ አከባቢ የሚሰማ ህመም።
በግንኙነት ወቅት የሚሰማ ህመም።
ለመውለድ መቸገር፦ ያለ ምንም ግልጽ ምክንያት ለማርገዝ መቸገር ወይም መካንነት።
ከፍተኛ ድካም፦ ከህመሙ ጋር ተያይዞ የሚመጣ አቅም የማጣት ስሜት፣ ማቅለሽለሽ ወይም የምግብ መፈጨት ችግር ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ እንደ "ተራ የወር አበባ ህመም" ወይም እንደ ጭንቀት ተቆጥረው ችላ ይባላሉ። ህመሙም ከወር አበባ ህመም ሊያይል ይችላል።
አስተውይ! ህመሙ የድክመት ምልክት ሳይሆን የጤና እክል ነው።
በምን ምክንያት ይከሰታል?

ምንም እንኳን የኢንዶሜትሪዮሲስ ትክክለኛ መንስኤ አሁንም ድረስ ጥናት እየተደረገበት ያለ ምስጢር ቢሆንም፣ ለበሽታው መከሰት የሚከተሉትን አራት መላምቶች ይሰጣሉ።
የወር አበባ ወደ ኋላ መመለስ (Retrograde menstruation)፦ ይህ በጣም የታወቀው መላምት ነው። በወር አበባ ወቅት ደም በማህፀን በኩል ወደ ውጭ ከመወጣት ይልቅ ፤ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሄዶ ይህን ችግር ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል። በዚህ ደም ውስጥ የሚገኙ ህዋሳት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ በመጣበቅ ማደግ ይጀምራሉ።
በሽታ የመከላከል ሥርዓት መዳከም፦ በተለምዶ ሰውነታችን የተሳሳተ ቦታ ላይ ያሉ ህዋሳትን ቢያስወግድም ፤ ይህን በሽታ የሚያመጡትን ህዋሳት ለማስወገድ ይሳነዋል።
ጄኔቲክስ (ዘረመል)፦ እናታቸው ወይም እህታቸው ኢንዶሜትሪዮሲስ ያለባቸው ሴቶች በችግሩ የመያዝ ዕድላቸው ከ7-10 እጥፍ ይጨምራል።
ሆርሞኖች፦ ኢንዶሜትሪዮሲስ በኤስትሮጅን ሆርሞን ላይ ጥገኛ የሆነ በሽታ ነው። ይህ ሆርሞን ለህብረ ህዋሱ እድገትና ለመቆጣት ምክንያት ይሆናል።
ምርመራ፡ እንዴት ማወቅ ይቻላል?
ኢንዶሜትሪዮሲስ ከሰውነት እይታ ውጭ ተደብቆ የሚቆይ "ስውር በሽታ" በመሆኑ፣ ትክክለኛውን ምርመራ ለማግኘት ከፍተኛ ጥንቃቄና የባለሙያ ክትትል ይጠይቃል። ባለሙያዎች በሽታውን ለመለየት የሚከተሉትን ዋና ዋና መንገዶች ይጠቀማሉ፦

1. በዶክተር የሚወሰድ የህክምና ታሪክ
ምርመራው የሚጀምረው በንግግር ነው። ዶክተር ስለ የወር አበባ ዑደት ፣ ስለ ህመሙ ጽኑነት እና በቤተሰብ ውስጥ (ለምሳሌ እናት ወይም እህት ላይ) ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ይጠይቃል። ህመምዎን ደብቀሽ ሳይሆን በዝርዝር ማስረዳትሽ ለትክክለኛው ምርመራ ቁልፍ እርምጃ ነው።
2. የላቀ የምስል ምርመራ (Imaging)
በሽታው በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማየት ዶክተሮች የሚከተሉትን ሊጠቀሙ ይችላሉ፦
አልትራሳውንድ (Ultrasound)፦ በተለይ በማህፀን በኩል የሚደረግ አልትራሳውንድ በእንቁላል ማምረቻ ላይ ያሉ እድገቶችን/መቆጣቶችን ለመለየት ይረዳል።
ኤምአርአይ (MRI)፦ በሽታው ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ተሰራጭቶ እንደሆነ ለማወቅ ጥልቅና ዝርዝር ምስል ይሰጣል።
3. የላፓሮስኮፒ ምርመራ “የመጨረሻው ማረጋገጫ”
እስከ ዛሬ ድረስ ኢንዶሜትሪዮሲስ መኖሩን 100% ለማረጋገጥ የሚረዳው ዋነኛው መንገድ ይሄ ነው። ይህ በሆድ ውስጥ ትንሽ ቀዳዳ ፈጥሮ ፤ በዛ ካሜራ በማስገባት በቀጥታ የሚደረግ ምርመራ ነው። ዶክተሩም በሽታውን በአይኑ ከማየት ባለፈ፣ ያለ ቦታው ያደገውን ህዋስ/አካል ለማስወገድ ይችላል። ለዚህም ህክምናውንም ጭምር እንዲያከናውን ያስችላል።
ሕክምና አማራጮቹስ ምንድን ናቸው?

ኢንዶሜትሪዮሲስ በአሁኑ ጊዜ ፍጹም መፍትሄ የለውም። ሙሉ በሙሉ አይድንም። ግን በሽታው ሕይወትዎን እንዳይቆጣጠረው የሚያደርጉ ውጤታማ የህክምና አማራጮች አሉ። የህክምናውም ዋነኛ ዓላማ ህመምን መቀነስ፣ የመውለድ ዕድልን መጨመር እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን እንዳይሰናከል ማድረግ ነው። ዋነኛ የህክምና አማራጮቹም የሚከተሉት ናቸው።
1. የመድኃኒት ህክምና
ሁለት አይነት የመድሀኒት አማራጮች አሉት። የህመሙን ብርታት ለመቀነስ ፤ ስሜቱን ለማስታገስ ፤ የህመም ማስታገሻዎችን መውሰድ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር በኪኒን ወይም በመርፌ የሚሰጡ የሆርሞን መድኃኒቶች የወር አበባ ዑደትን በማስተካከል በሽታውን ያክማሉ።
2. ቀዶ ጥገና፦
ይህን መፍትሔ እላይ በምርመራ ስር አንስተነዋል።
3.የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ
በሽታውን ለመቆጣጠር መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይመከራል። በሳምንት ጥቂት ቀናት ቀለል ያለ እርምጃ ወይም ስፖርት መስራት ህመሙን ይቀንሳል። እላይ በምስሉ እንደሚታየው የሞቀ ውሃ በእቃ አድርጎ ሆድ ላይ (ከእንብርት በታች) ማድረግ ፤ ህመሙን እንዲቀንስ ያደርጋል።
አመጋገብስ ለውጥ ያመጣል?

ምንም እንኳን አመጋገብ በሽታውን ሙሉ በሙሉ ባይፈውስም፣ በሰውነት ውስጥ ያለውን የኤስትሮጅን መጠን በመቀነስ እና ቁስለትን (inflammation) በመከላከል ህመሙን በእጅጉ ሊያቃልል ይችላል። ለዚህም የሚከተሉትን ይመገቡ።
ኤስትሮጅንን የሚቀንሱ ምግቦችን ተመገቢ። ለዚህ ከፍተኛ ፋይበር ያላቸው ምግቦች ተመራጭ ናቸው። ትርፍ ኤስትሮጅን ከሰውነት እንዲወጣ ያግዛሉ ። እንደ ባቄላ፣ አተር፣ ገብስ ፣ አጃ እና አረንጓዴ ቅጠላቅጠሎችን መመገብ ይመከራል።
የሰውነት መቆጣትን/ ቁስለትን የሚቀንሱ ምግቦችን ተመገቢ። እንደ ተልባ እና ለውዝ ያሉ ቅባታማ ምግቦች እንዲሁም አሳ ውስጣቸው ሰውነት መቆጣት የሚቃወም ውህድ ስላላቸው ህመሙን ሊቀንሱ ይችላሉ።
እነዚህን ምግቦች ቀንሺ። አኩሪ አተር ፣ ቀይ ስጋ፣ አልኮል እና ካፊን ያሉ ምግቦች በአንድ ሆነ በሌላ መንገድ በሽታውን ስለሚያባብሱ መቀነስ ይመረጣል።
ባይታከምስ ምን ችግር አለው?

ብዙ ሴቶች ህመሙን “የሴትነት ጽናት” አድርገው በዝምታ ለመጋፈጥ ቢመርጡም፣ ሳይታከም ከቆየ የከፋ ዋጋ ያስከፍላል። ችላ ማለቱ የሚያስከትላቸው ዋና ዋና አደጋዎች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦
1. መካንነት ያመጣል። በሽታው ካለባቸው ሴቶች መካከል ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት ለማርገዝ ይቸገራሉ። በሽታው በማህፀን ቱቦዎች እና በእንቁላል ማምረቻዎች ላይ በሚፈጥረው ጠባሳ ምክንያት፣ የፅንስ መፈጠርንና እድገትን ያደናቅፋል።
2. የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሕይወት ያቃውሳል። ስር የሰደደው ህመም ሴቶችን ከመደበኛ ትምህርታቸው እንዲስተጓጎሉ ፤ ከሥራ ገበታቸው በተደጋጋሚ እንዲቀሩ ያደርጋል። ማህበራዊ ቁርኝታቸው ላይም ተጽእኖ ያሳድራል።
3. የስነ-ልቦና ጫና ያሳድራል። ለዓመታት የሚዘልቅ ማንም የማይረዳው ህመም ከመሆኑም በላይ በዙሪያ ያሉ የሰዎች አለመረዳት፣ ለጭንቀትና ለድብርት ያጋልጣል።
ቀደም ብሎ ማወቅ ግን ያድናል!
አትታገሽ ! ተመርመሪ
የወር አበባ ህመምሽ እየባሰ ከመጣ አሁኑኑ ወደ ማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት በመሄድ መፍትሄ ፈልጊ።
ቀደም ብሎ ሕክምና ማግኘት ህመምን ይቀንሳል፣ የአካል ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳትን ይከላከላል እንዲሁም የመውለድ ዕድልን ያሻሽላል።
እና ምን ትጠብቂያለሽ?




Comments