top of page

ለልጅ ስልክ መስጠት ኦቲዝም ያመጣ ይሆን?

በብዙዎቻችን ቤቶች ውስጥ ህጻናት እና ስልክ ያላቸው ቁርኝት እየጨመረ መጥቷል። ከአንድ ስፍራ ተቀምጦ ለሰአታት በስልክ ስክሪኖች ላይ ተተክሎ የሚያሳልፍ ህጻን ጥቂት አይደለም

ክፍሉ በድምጾች ተሞልተው፤ እናት ስትጠራ፣ ወንድም እና እህቶች ሲስቁ ፤ ስልኩ ላይ ተደፍቶ ህጻኑ ዘወር አይልም። እንደዚህ አይነት ትዕይንት በከተሞች ከተለመደ ሰንበትበት ብሏል።


በአለም አቀፍ ደረጃ እንኳን 2 አመት ያልሞላቸው ህጻናት መካከል ከ60% በላይ የሚሆኑት በየቀኑ ስክሪን ይጠቀማሉ። ይህ አሳሳቢ ነው!


ወላጆችማ በረዥም ጊዜ ውስጥ የለመዱትን ቴክኖሎጂ ፤ በስርአት ማውራት ያልቻሉ ህጻናት አቀላጥፈው ሲጠቀሙ ይገረማሉ። ጠቋሚ ሳያስፈልጋቸው የህጻናት መዝሙሮችን፣ የካርቶን ቪድዮዎች እንዲሁም አስቂ ቪድዮዎች በራሳቸው እየቀያየሩ ሲያዩ "ከእኛ በላይ ዘመናዊ ናቸው" ብለው አድናቆት ይቸራሉ። አንዳንድ ወላጆች ይህንን የአእምሮ ብሩህነት አድርገው ይወሰዳሉ።


በተለይ ደግሞ ስራ ለበዛባቸው ፣ የቤት ውስጥ ኃላፊነት ላጨናነቃቸው ወላጆች ስልኩን ሰጥቶ እርፍ ማለት ይመርጣሉ። ስልኩ እንደ "ነጻ ሞግዚት" ሆኖ ያገለግላል። ህጻኑ ሳይረብሽ፣ ሳያለቅስ፣ ከቤት ሳይወጣ ባለበት ተተክሎ ለሰዓታት ሲቆይ ፤ ወላጅ የራሱን ስራ ለመከወን ትልቅ እረፍት ያገኛል። ስልኩ የልጁን ትኩረት ሰርቆ በማቆየቱ ወላጅነትን የቀለለ ያደርገዋል።


ለመሆኑ ይህ ለወደፊት ዕድገታቸው ጠቃሚ ነው ወይስ ዋጋ ያስከፍላል? በአንዳንድ ማህበራዊ ድህረ ገጾች እንደሚነሳው ፤ ገና በለጋ ዕድሜ ስክሪን/ስልክ አብዝቶ መጠቀም ለኦቲዝም (ASD) ይዳርግ ይሆን?" 


በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እነዚህን ጥያቄዎች በጥልቀት እንመረምራለን። ስለ ስክሪኑ ተፅዕኖ ከማውራታችን በፊት ስለ ኦቲዝም መረዳት አለብን።


ኦቲዝም ምንድን ነው?

ምስሉ ላይ እንደተመለከተው ኦቲዝም ያለባቸው ህጻናት ከማህበራዊ ቁርኝት ርቀው ብቻችውን መሆን ይመርጣሉ።
ምስሉ ላይ እንደተመለከተው ኦቲዝም ያለባቸው ህጻናት ከማህበራዊ ቁርኝት ርቀው ብቻችውን መሆን ይመርጣሉ።

ኦቲዝም ከአንጎል እድገት ጋር የተያያዘ የጤና እክል ነው። ይህም በዘላቂነት አንድ ህጻን ዓለምን የሚረዳበትን መንገድ የሚቀይር ነው። በሽታው ያለባቸው ህጻናት የሚከተሉትን ባህሪያት ይስተዋልባቸዋል።


  1. በማህበራዊ ግንኙነት እና ተግባቦት ላይ ይቸገራሉ።

  2. ተደጋጋሚ ድርጊቶችን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። የለመዱትን የዕለት ተዕለት ተግባር የመምረጥ ዝንባሌ አላቸው።


እነዚህ ህጻናት አካባቢያቸውን የሚያዩበት፣ የሚሰሙበት እና የሚያስተውሉበት መንገድ የተለየ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ100 ሕፃናት መካከል አንዱ የኦቲዝም ምልክት ይታይበታል ተብሎ ይገመታል። ምልክቶቹ አብዛኛውን ጊዜ ከ2 እስከ 3 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ መታየት ይጀምራሉ። በቂ ድጋፍ እና ክትትል ከተደረገላቸው ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ውጤታማ ሕይወት መምራት ይችላሉ።


ስልኩ ኦቲዝም አምጥቶበት ይሆን?

እንደ The Lancet እና JAMA Pediatrics ያሉ የሕክምና መጽሔቶች ያወጧቸው ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፣ ኦቲዝም ከዘረመል (genetics) እና በጽንስ ወቅት ከነበረ የጭንቅላት ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው። ይህም ማለት ኦቲዝም ህጻኑ ስልክ ከመንካቱ ከረጅም ጊዜ በፊት የሚወሰን ነው። ለዚህም ከዩቲዩብ /ቲክቶክ ቪድዮ አጋር ኦቲዝም አይያዝም።

ዲጂታል ሚዲያ ኦቲዝምን አያመጣም።

ታድያ ይህ እውነት ከሆነ ታድያ ኦቲዝም እና ስልክን የሚያቆራኙ ጥናቶች ከየት መጡ?

እዚህ ጋር ያስተውሉ ፤ ስልክ መጠቀሙ ኦቲዝም ባያስከትልም ፤ ከመጠን ያለፈ የስልክ አጠቃቀም የኦቲዝምን ምልክቶች "ሊመስል" ይችላል። ይህንንም መመሳሰሉን አስከትሎ ስልክ አጠቃቀምን ተከትሎ የሚመጣው ለውጥ የዲጂታል ኦቲዝም ይሰኛል። ሆኖም ግን ይህ እንደ ትክክለኛው ኦቲዝም ከዘረመል/ከባዮሎጂ ግንኙነት የለውም። ፈጽሞ የተለያየ ነው! 

ምልክቶቹ ለምን ከኦቲዝም ጋር ተመሳሰሉ?

የሕፃን አእምሮ በመጀመሪያዎቹ 1,000 ቀናት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ያድጋል። ይህ ዕድገት የሚፋጠነው ህጻን ልጅ ከአከባቢው ጋር በሚያደርገው መስተጋብር/ግንኙነት ነው። ይህም ከእናት እና ከቤተሰብ ጋር የሚኖር የአይን ለአይን ግንኙነት፣ የእናት ፈገግታ , የሚያደርገው ንግግር እንዲሁም ከእድሜ እኩዮቹ ጋር የሚኖረው ቁርኝት እድገቱን ይወስናል።

በቤተሰብ ፋንታ ልጁ ከስልክ ጋር ብዙ ሰአት ሲያሳልፍ ይህ ወሳኝ ግንኙነት ይቋረጣል።  የስልክ ስክሪን የህጻኑ ዋነኛ ጓደኛ ይሆናል። ከሰው ፊት ይልቅ ህጻኑ በፍጥነት የሚንቀሳቀሱ ምስሎችን እና ተደጋጋሚ ሰው ሰራሽ ድምጾችን ያያል/ይሰማል። ይህም እድገቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል።


ጥናቶች እንደሚያሳዩት በታዳጊ ህጻናት ላይ በቀን ከ2-3 ሰዓት በላይ ስክሪን መጠቀም የሚከተሉትን ሊያስከትል ይችላል፦

  • የንግግር መዘግየት፤

  • የአይን ለአይን ግንኙነት መቀነስ፤

  • ከሌሎች ልጆች ጋር ለመጫወት ፍላጎት ማጣት ፤ ያስከትላል።


እነኝህ ባህሪያት ደግሞ ኦቲዝም ካለባቸው ህጻናት ባህሪያት ጋር ይመሳሰላሉ። ለዚህም አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ላይ "ኦቲዝም መሰል" ባህሪያትን አይተው ይደነግጣሉ። ይህ ግን ህጻኑ ኦቲዝም ኖሮበት አይደለም። ይልቁንም ማህበራዊ ክህሎትን ለማዳበር የሚያስፈልገውን የሰው ልጅ ግንኙነት በስክሪን በመተካቱ የመጣ ነው።

ከመጠን ያለፈ አጠቃቀም የሚያስከተለው ችግር፡

ችግሩ ቴክኖሎጂው ሳይሆን የሰው ልጅ ግንኙነት መተካቱ ላይ ነው። ከመጠን ያለፈ ተጋላጭነት (በተለይ ከ3 ዓመት በታች) የህጻን ልጅ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል።


ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ከ1 አመት እስከ 2 አመት እድሜ ያሉ ህፃናት በቀን 30 ደቂቃ ተጨማሪ የስክሪን ጊዜ ካሳለፉ የንግግር መዘግየት እድላቸው በ 49% ከፍ ይላል። ይህ ደግሞ ሊያሳስበን ይገባል።

ከዚህም ባሻገር አብዝቶ ስልክ/ስክሪን መጠቀም የሚከተሉትን ችግሮች ያስከትላል፦

  • የወላጅ እና የልጅ ትስስር ያዳክማል፦ ስክሪን በልጁ እና በወላጆቹ መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ ግንኙነት እና የመጫወቻ ጊዜን ይቀንሳል። ለዚህም ከወላጅ ጋር ያለ ቅርበትን ይቀንሳል።

  • የእንቅልፍ መዛባት ያመጣል፦ ከስክሪን የሚወጣው ብርሃን እና የሚያነቃቁ ምስሎች ህፃናት በቀላሉ እንቅልፍ እንዳይወስዳቸው ወይም ጥራት ያለው እንቅልፍ እንዳያገኙ ያደርጋል።

  • ከፍተኛ ብስጭት እና ባህሪ መለዋወጥ ያመጣል፦ ከመጠን ያለፈ ተጋላጭነት ለብስጭት፣ ለትኩረት ማጣት፣ እና ለባህሪ መለዋወጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል።


ለዚህም በሳይንስ የሚከተሉት ገደቦች ይመከራሉ።

  • የልጅዎ ዕድሜ ከ0-18 ወራት ከሆነ ፤ ምንም አይነት ስክሪን አይፈቀድም። ቢበዛ የሚፈቀደው የቪድዮ ስልክ ጥሪ ብቻ ነው።

  • የልጅዎ እድሜ ከ 2-5 ዓመት ከሆነ ፤ በቀን የሚፈቀደው ቢበዛ አንድ ሰዓት ነው። ያውም ትምህርታዊ መሆን ይኖርበታል። ይህንንም የስልክ አጠቃቀም ጥራቱ እና በውስጡ ያለው ይዘትን ለማረጋገጥ ወላጅ መከታተል/መቆጣጠር ይኖርበታል።

የእርስዎ ልጅ አጠቃቀምስ ምን ይመስላል?

እውቀት በተግባር ሲታገዝ ነው ጤና መጠበቅ የሚቻለው። እናስ ምን አሰቡ!?


የተሳሳተ አስተሳስብ

እዚህ ጋር ቴክኖሎጂን እንደ ጠላት ብቻ ማየት ስህተት ነው! ቴክኖሎጂ ለህጻናትም ሆነ ለአዋቂዎች ብዙ መልካም ጎኖች አሉት። ኦቲዝም ላለባቸው ልጆች እንደ ድልድይ ሊያገለግል ይችላል። ዲጂታል መሳሪያዎች ዓለምን የሚያዩበት መስኮት ሊሆኑ ይችላሉ።



ብዙ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በምስል በመማር ጎበዝ ናቸው። ለዚህም በምስል አማካኝነት ሃሳባቸውን የሚገልጹባቸው አፕሊኬሽኖች ወይም ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ የሚረዱ ጨዋታዎች ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ። በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለም የህጻናትን ምህዳር የማስፋት ፣ ከቋንቋ ጀምሮ ብዙ መልካም ነገሮች የማስተማር አቅም አለው።


መፍትሔው ምንድን ነው?

የመፍትሄው ቁልፍ ቴክኖሎጂውን መከልከል አይደለም። ስልክን የልጅዎን እድገት በሚደግፍ መልኩ መጠቀም ላይ ነው። ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ።

1. ከልጅዎ ጋር ላሎት ግንኙነት ቅድሚያ ይስጡ።

ማንኛውም አፕሊኬሽን የማህበራዊ ግንኙነት ክህሎትን ሊያስተምር አይችልም። ከልጅዎ ጋር አብረው ያውሩ፣ ይዝፈኑ፣ ፊት ለፊት ይተያዩና ይጫወቱ። እነዚህ አፍታዎች የልጅዎን ማህበራዊ የአእምሮ እድገት ለመገንባት ከማንኛውም የስልክ ስክሪን በላይ ይረዳሉ።


2. ልጅዎን ትተው አይሂዱ።

ልጅዎ ስክሪን የሚጠቀም ከሆነ ብቻውን አይተዉት። አብረው ይቀመጡ፤ የሚያየውን ነገር አብረው ይጠቁሙ፤ ድምፆችን አብረው ይከተሉ። ይህ ብዙ ጠቀሜታ አለው። በአንድ በኩል ልጅዎ ብቻውን የሚያደርገውን ድርጊት ወደ ማህበራዊ ግንኙነት ይለውጠዋል። በሌላ በኩል ልጅዎ የሚያየውን ነገር ትምህርታዊነቱን፣ ጥራቱን እና መልካምነቱን እንዲያረጋግጡ ያስችልዎታል።


3. ሳይንሳዊ የጊዜ ገደቦችን ያክብሩ

እላይ የተጠቀሱትን የህፃናት ህክምና ባለሙያዎች ምክር ይከተሉ!


4. ቀድሞ መድረስ ትልቁ መሳሪያ ነው

ልጅዎ ማንኛውንም የእድገት መዘግየት ካሳየ ፈጽመው አይጠብቁ። እድገቱ ከእድሜ እኩዮቹ አንጻር ከዘገየ ፣ ቃላት ለማውጣት፣ ለመራመድ እንዲሁም አንዳንድ ድርጊቶችን ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ ከወሰደ፤ የጤና ባለሙያ ያማክሩ። ቀድሞ የሚደረግ ድጋፍ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።


እወነታው ይህ ነው!

አእምሮ የሚገነባው በስልክ ላይ በሚታዩ ምስሎች ሳይሆን በሰዎች ነው። አንድ ህጻን ኦቲዝም ይኑርበትም አይኑርበትም፣ የሚፈልገው አንድ አይነት ነገር ነው፦ የሰው ድምጽ፣ በፍቅር የተሞላ እንክብካቤ እና ወደ እሱ የሚመለከቱ የፍቅር አይኖች።

ዛሬውኑ ልጅዎ ዝም እንዲል ስልክ መስጠት ያቁሙ።


በልጅዎ እድገት ዙሪያ የሚያሳስብዎት ነገር አለ? ወይም በአካባቢዎ የሚገኙ የልዩ ፍላጎት ድጋፍ ሰጪ ማዕከላትን ለማወቅ ይፈልጋሉ?

Comments


bottom of page