ቡና ለጤናችን መርዝ ወይስ መድሐኒት? ሳይንሱ ምን ይላል?
- Zebeaman Tibebu
- 1 day ago
- 4 min read
ለኢትዮጵያ ህዝብ ቡና መጠጥ ብቻ አይደለም።
ባህል ነው!
ሥርዓት ነው!
መጨዋወቻ ፤ መተዋወቂያ እና መግባቢያ ነው!
ከዚህም አልፎ የቡና ኤክስፖርት የኢኮኖሚያችን መሰረት በመሆኑ " የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ብና የሚሉ.... " ዜማዎችም አሉን። የቡና ስርአታችንም ለየት ያለ ነው።

ታድያ ግን አንዳንድ ጥናቶች ቡና ለጤና ጠቃሚ ነው ሲሉ ፤ ሌሎች ቡና ያለውን የጤና አደጋ ያነሳሉ። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ግራ ያጋባል። አንዳንዶች " የጤና ጠንቅ ስላለው ባልጠጣስ" ሲሉ ፤ ሌሎች ደም ግፊት እያለባቸው እንኳን ቡና አብዝተው ይጠጣሉ።
ታድያ የትኛው ትክክል ነው? እነኝህ ጥናቶች ተሳስተው ይሆን?
ይህን ለመመለስ መጀመሪያ ቡና በውስጡ ካፊን (caffeine) ጨምሮ ብዙ ንጥረ ነገሮች እንዳሉት ማወቅ አለብዎ። ቡና አንቲኦክሲዳንትስ (Antioxidants) እና ፖሊፊኖልስ (Polyphenols) የተባሉ ለጤና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ይዟል።
ይህንን በጥልቀት እንመልከት!
ከቡና መጠጣት ጀርባ ያለው ስሌት
የኢትዮጵያ ቡና እንብለው እንጂ አብዛኛው በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚበቅለው የቡና ዝርያ ኮፊ አረቢካ (Coffee Arabica) ይሰኛል። የላብራቶሪ ምርመራዎች እንደሚያሳዩት፦
አረቢካ ቡና ዝርያ በደረቅ ክብደቱ ከ1.2%–1.5% ካፊን ይይዛል። ይህ ማለት በአንድ ግራም ቡና ውስጥ ከ12–15 ሚሊግራም (mg) ካፊን ማለት ነው።

አሁን ይህንን ወደ ሲኒ እንለውጠው። አንድ በባህላዊ መንገድ የሚፈላ ቡና በአንድ ጊዜ ከ10–14 ግራም ቡና ሊጠቀም ይችላል።
ይህ ማለት፦
የኢትዮጵያ ቡና አፈላል ስርአት ለየት ያለ በመሆኑ ፤ ሶስት ጊዜ ስለሚጠጣ ፤ እንዲሁም ለረዥም ጊዜ ስለሚፈላ ፤ አንድ በባህላዊ መንገድ የሚፈላ የቡና ሲኒ ጠንከር ያለ ተጽእኖ ያሳድራል። ለዚህም ከፍተኛውን መጠን ብንወስድ በአንድ ሲኒ ጠንካራ የኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ከ120–210 mg ካፊን ይገኛል።
ይህ ግምት አይደለም ፤ የኬሚስትሪ ሳይንስ ነው።
ይህ ለጤና ከሚቀመጡ ገደቦች ጋር ሲነጻጸር እንዴት ይታያል?
የሕክምና ሳይንስ እንደሚጠቁመው፦
✅ ለጤናማ አዋቂ ሰው በቀን የሚፈቀደው ከፍተኛ መጠን በቀን 400 mg ማለፍ የለበትም።
✅ ለነፍሰ ጡር ሴቶች ደግሞ ከ 200 mg ቢያንስ ይመከራል።

አሁን በጥንቃቄ እናስብ።
አንድ ባህላዊ ሲኒ ከ120–210 mg ካን ከያዘ ፤ ከአንድ እስከ ሁለት ሲኒ (እንደ ቡናው ጥንካሬ) ለአብዛኛው አዋቂ ሰው ጤናማ ነው። ከዛ በላይ ከጠጡ ግን ገደቡን ሊያልፉ ይችላሉ።
ሆኖም ግን በባህላችን መሰረት ቤት ውስጥ የሚፈላ ቡና ፤ እስከ ሶስተኛ ነው የሚጠጣው። አቦል ጦና በረካን ሳይደርስ መሄድ አይወደድም። ምንም እንኳን የኋለኞቹ ዙሮች ቢቀጥኑም፣ ድምር ውጤቱ ለጤናማ ሰው ከሚፈቀደው ሊበልጥ ይችላል።
ሳይንስ ከባህል ጋር የሚገናኘው እዚህ ጋር ነው።
ይህ የካፊን መጠን ለምን ተቀመጠ ?
አንጎላችን ውስጥ በተፈጥሮ እንቅልፍ እንዲመጣ የሚያደርጉ አዴኖሲን (adenosine) የተሰኙ ውህዶች አሉ። ቡና ውስጥ ያለው ካፊንም በአንጎል ውስጥ አዴኖሲኖች እንዳይሰሩ ይዘጋባቸዋል። ይህም ንቁ እንዲሆኑ ያደርጋል። ለዚህም ደምዎ ውስጥ ያለው የካፊን መጠን ያለውን ተጽእኖ ይወስናል።

በ100–200 mg መጠን ካፊን ከጠጡ ፤ ንቁ ይሆናሉ። ፈጣን ምላሽ መስጠት ይችላሉ። በመጠነኛ ደረጃ የልብ ምትዎ ይጨምራል። የደም ግፊትዎ በመጠኑ ከፍ ይላል።
በ300–400 mg መጠን ካፊን ከጠጡ ፤ ከፍተኛ መነቃቃት ይኖርዎታል። አድሬናሊን የሚሰኘው የአደጋ ጊዜ ሆርሞን እና ኮርቲሶል የተሰኘው ከጭንቀት ጋር የሚያያዘው ሆርሞኖች መጠን እንዲጨምር ያደርጋሉ። ለዚህም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ላይ ጭንቀት ይፈጥራል።
ከ400–500 mg በላይ ካፊን ከጠጡ ፤ የልብ ትርታዎ በደንብ ይጨምራል። መቅበዝበዝ እና እንቅልፍ ማጣት ሊኖርዎት ይችላል። የደም ግፊትዎ በከፍተኛ መጠን ይጨምራል። የጨጓራ መቆጣትም ሊያመጣ ይችላል።
ይህ ገደብ የተቀመጠውም ከማንቃቱ ይልቅ ጉዳቱ እንዳይብስ ለማድረግ ነው።
እዚህ ጋር ያስተውሉ! ቡና ላይ የሚደረጉ ጥናቶች በሲኒ ሲገልጹ ለብዙዎች አሳሳች ይሆናል። ቀጭን ቡና 3 ሲኒ እና አንድ ጠንካራ ቡና 1 ሲኒ ውስጣቸው ያለው ውህድ መጠን እኩል ሊሆን ይችላል። ለዚህም አንዳንድ ጥናቶች 3 ሲኒ ቡና ሲሉ ፤ እስከአሁን ያነሳነውን ስሌት ክደው ሳይሆን ፤ ቡናው ቀጭን ሆኖ ሊሆን እንደሚችል ማስተዋል አለብዎ። በባህላዊ መንገድ የተዘጋጀ ቡና አንድ ሲኒ በቂ ሊሆን ይችላል። ❤️ መልካሙ ዜና፡ ቡና ለብዙ ሰዎች ጤናማ ነው
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቀን መጠነኛ ቡና መጠጣት ከሚከተሉት ጥቅሞች ጋር የተያያዘ ነው፦

✅ እድሜን ማራዘም፦ አዘውትረው ቡና የሚጠጡ ሰዎች ካልጠጡት ጋር ሲነጻጸሩ ያለጊዜው የመሞት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ።
✅ የልብ ጤና፦ መጠነኛ ቡና ጠጪዎች ለልብ ሕመም እና ለስትሮክ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው።
✅ የስኳር በሽታ፦ መጠነኛ ቡና መጠጣት ፤ ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን ላይ ባለው ተጽእኖ ፤ ለ ስኳር በሽታ የመጋለጥ እድልን እንደሚቀንስም የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ።
✅ የአንጎል ጤና፦ ቡና አንጎል ላይ ባለውም ተጽእኖ ፤ እንደ ፓርኪንሰን (Parkinson’s) እና አልዛይመር (Alzheimer’s) ያሉ በሽታዎችን የመከላከል አቅም እንዳለውም አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
✅የጉበት መድኃኒት፦ ቡና ውስጥ ያሉት አንቲ አክሲዳንት እና ፌኖልስ የጉበትን ጤና ይደግፋሉ። ጉበት በስብ እንዳይወረርና ለካንሰር እንዳይጋለጥ የመከላከል አቅም አላቸው።
⚠️አሳሳቢው ጉዳይ፡ ቡና ለብዙዎች ጎጂ ሊሆን ይችላል
"ከመጠን ያለፈ ማር ይመራል" እንደሚባለው ሁሉ፣ ቡናም መጠኑ ሲበዛ ወይም አጠጣጡ ሲዛባ አደገኛ ይሆናል። ለዚህም

የጭንቀት ቀስቃሽ (Anxiety Trigger) ነው። ካፊን አድሬናሊንና ኮርቲሶል ሆርሞን ላይ ባለው ተጽእኖ ጭንቀት ሊቀሰቅስ ይችላል። ከመጠን በላይ ሲሆን የልብ ትርታን ያፋጥናል፣ እጅን ያንቀጥቅጣል፣ እንዲሁም ለከፍተኛ መረበሽና ጭንቀት ይዳርጋል።
የእንቅልፍ ሌባ ነው። ካፊን በደም ውስጥ እስከ 6 ሰዓት ይቆያል። ከሰዓት በኋላ የሚጠጣ ቡና የሌሊት እንቅልፍዎን ጥራት ይዘርፈዋል። ጥልቅ እንቅልፍ ማጣት ደግሞ ለደም ግፊትና ለሰውነት መቆጣት (Inflammation) መንስኤ ይሆናል። ለዚህም ከ ቀኑ 9 ሰአት በኋላ ቡና ባይጠጡ መልካም ነው።
የጨጓራ ጠላት ነው። ቡና የጨጓራ አሲድ እንዲመነጭ ያግዛል። የጨጓራ ቁስል ወይም ቃር ያለባቸው ሰዎች ቡና ሲጠጡ ህመሙ እንዲባባስ ያደርጋል።
ለነፍሰ ጡር ሴቶች ስጋት ነው። ከፍተኛ ካፊን በፅንሱ እድገት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ስለዚህ ነፍሰ ጡር እናቶች በቀን ከ1 ሲኒ በላይ እንዳይጠጡ በጥብቅ ይመከራሉ።
❗ቡና አብዝቶ መጠጣት ለስኳር በሽታም ይዳርጋል!
ይህ እላይ ካልነው ጋር ፈጽሞ አይቃረንም!

ለምን?
ብዙዎች ቡና በስኳር አጣፍጠው ነው የሚጠጡት። በአማካይ በአንድ ሲኒ 2 የሻይ ማንኪያ ስኳር ሲጨምሩ ወደ 8 ግራም ስኳር ከቡናው ጋር አብረው ይጠጣሉ። በቀን 3 ሲኒ ቡና ከጠጡ፣ 24 ግራም ስኳር እያገኙ ነው። ይህ በጊዜ ሂደት ሰውነት ኡደትን ያሰናክላል። ለስኳር በሽታም ይዳርጋል።
ሰዎች "ቡና ለስኳር ህመም ያጋልጣል" ሲሉ ፤ ብዙ ጊዜ የሚጠጡት በስኳር የጣፈጠ ቡናን መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም።
ይህ ልዩነት በህክምናው ረገድ እጅግ አስፈላጊ ነው።
ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው እነማን ናቸው?
የሚከተሉት ሁኔታዎች ካሉብዎት ቡና ሲጠጡ ጥንቃቄ ያድርጉ፦
ነፍሰ ጡር ከሆኑ ፤ በቀን ከ200 ሚ.ግ ካፊን (1 ሲኒ) አይለፉ።
ቁጥጥር ያልተደረገበት የደም ግፊት ካለብዎት ፤ ቡና ባይጠጡ ይመከራል።
የጭንቀት (Anxiety) ወይም ድንገተኛ ፍርሃት (Panic) ችግር ካለብዎት ፤ ዶክተርዎን ያማክሩ።
ከፍተኛ የቃር (Reflux) ችግር ካለብዎት ቡና አይጠጡ።
የልብ ምት መዛባት ካለብዎት ቡና አይጠጡ።
ቡና ለሁሉም ሰው እኩል ጠቃሚ ወይም ጉዳት የሌለው ላይሆን ይችላል።
ለማጠቃለል… ቡና ጥሩ ነው ወይስ መጥፎ?
ትክክለኛው መልስ — ያለ ስሜት እና ያለ ማጋነን — እንደሚከተለው ነው፦
ለአብዛኛው ጤነኛ አዋቂ ሰው በቀን ከ አንድ እስከ ሁለት ሲኒ ባህላዊ ቡና የጤና ጉዳት የለውም። በጥናት መሰረትም ለረጅም ጊዜ ጤንነት ጠቀሜታ አለው።
ቁልፉ ነጥብ መፍራት ሳይሆን ፤ መረዳት ነው።
ቡናዎን በእውቀት ይጠጡ።
ቡናዎን በመጠን ይጠጡ ።





Comments