ስለ ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ማወቅ ያለብሽ?
- Zebeaman Tibebu
- Mar 22
- 3 min read
Updated: 2 days ago
ይህንን ሁኔታ በልቦናሽ አስቢው...
ምሽት ነው። ከፍቅረኛሽ ጋር መልካም ጊዜ እያሳልፈሽ ፤ ድንገት ኮንዶም ተቀደደ። ሁልጊዜ የምትወስጂውን የእርግዝና መከላከያ ኪኒን ዛሬ አልወሰድሽም ነበር። ድንገት ያላሰብሽው እና ያልተዘጋጀሽበት ክስተት ተፈጠረ!

ምን ተሻለሽ?
ፖስት ፒል መውሰድ አልያስ....?
እሱንስ መቼ እና እንዴት መውሰድ እንዳለበሽ ታውቂያለሽ?
ዛሬ በብዙዎች ዘንድ ፖስት ፒል በመባል ስለሚታወቀው የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ መንገድ እናነሳለን። ፖስት ፒል የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ መድሀኒቶች ውስጥ የአንዱ የብራንድ (የፋብሪክ ምርት) ስም ስለሆነ ፤ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ የሚለውን ስያሜ ብቻ እንጠቀማለን።
ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ምንድን ነው?
ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ደህንነቱ ያልተጠበቀ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ተከትሎ የሚመጣ እርግዝናን ይከላከላል።ለዘወትር አገልግሎት የሚውል ሳይሆን እንደ “ተጠባባቂ እቅድ” የሚያገለግል ነው።

እንዴት ይሠራል?
ድንገተኛ መከላከያ የሚሠራው እርግዝና ከመጀመሩ በፊት ነው። እርግዝና እንዳይፈጠር ይከላከላል እንጂ ፤ እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ ጥቅም አይኖረውም።እርግዝናን የሚከላከለው በሚከተሉት መንገድ ነው።
1️⃣ የእንቁላል መውጣትን ያዘገያል፦ ድንገተኛ መከላከያው ሲወሰድ በመደበኛ ሁኔታ የሚወጣውን የሴት ልጅ እንቁላል ዘግይቶ እንዲወጣ ያደርገዋል። እንቁላል በጊዜ ካልወጣ ደግም የወንድ ዘር ፈሳሽ የሚያገኘው ነገር ስለሌለ እርግዝና አይፈጠርም።
2️⃣ የወንድ ዘር ከእንቁላል ጋር እንዳይገናኝ እንቅፋት ይሆናል፦ የወንድ ዘር በሴት አካል ውስጥ እስከ 5 ቀናት ሊቆይ ይችላል። ድንገተኛ መከላከያው ደግም የማህፀን በርን በወፍራም ፈሳሽ በመዝጋት የወንድ ዘር እንቁላል ጋር እንዳይደርስ ያሰናክላል። እንዲሁም የወንድ ዘር እንቅስቃሴን በመቀነስ ጽንስ እንዳይፈጠር ያደርጋል።

🚫 ይህ ሲሆን ግን ያስተውሉ! ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ የሚከተሉትን አያደርግም።
❌ በማህፀን ግድግዳ ላይ ያረፈን እርግዝና አያሰናክልም።
❌ ውርጃ አያስከትልም።
❌ ነባር እርግዝናን አይጎዳም።
የሚሰራው እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት እንጂ በኋላ አይደለም!
ሦስቱ ዋና ዋና ዓይነቶች (አማራጮችሽን እወቂ)
እንደ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያነት የሚያገለግሉ ሦስት አማራጮች አሉ። እያንዳንዱን በዝርዝር እንመልከት፦
1️⃣ ሌቮኖርጀስትሬል (Levonorgestrel) ኪኒኖች -
ይህ በብዛት በኢትዮጵያ የሚገኝ አማራጭ ሲሆን እንደ ፓስት ፒል ፣ ላና እና ፒል 72 በሚባሉ ስሞች ሊገኝ ይችላል። ይህ መድሀኒት
በ72 ሰዓታት (በ3 ቀናት) ውስጥ ቢወሰድ ይመረጣል። ውጤታማነቱም በመጀመሪያ 3 ቀናት ላይ ከፍ ያለ ነው። ሆኖም ግን እስከ 5 ቀን ቢወሰድ ሊሰራ ይችላል።
2️⃣ ዩሊፕሪስታል አሴቴት (Ulipristal Acetate) ኪኒኖች
ይህ እስከ 120 ሰዓታት (5 ቀናት) ድረስ ውጤታማ የሆነ አማራጭ ነው። ውጤታማነቱ ከሌቮኖርጀስትሬል የላቀ ነው። ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ፋርማሲዎች በስፋት አይገኝም።
3️⃣ ሉፕ /የመዳብ አዩዲ (Copper IUD - ሉፕ)
ይህ የረጅም ጊዜ የወሊድ መከላከያነት የሚያገለግል ሲሆን ፤ እስከ 5 ቀናት ከተደረገ ውጤታማ ይሆናል። ማህጸን ላይ ካለው ተጽእኖ ባሻገር ፤ ለወንድ ዘር መርዛማ የሆነ ከባቢን በመፍጠር እርግዝና እንዳይፈጠር ያደርጋል። ሴት ልጅ ማህጸን ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን ፤ እስከ 10 አመት ድረስ ሊያገለግል ይችላል።
ውጤትማነቱስ ምን ያህል ነው?
ውጤታማነቱ እንደ አወሳሰድ ሰዓቱ ይወሰናል፦
በ1 ቀን ውስጥ ከተወሰደ → እስከ 95% ውጤታማ ሊሆን ይችላል።
በ 3 ቀን ውስጥ ከተወሰደ → ከ 75–89% ውጤታማ ነው።
ከ 3 ቀን በኋላ ግን → ውጤታማነቱ ዝቅተኛ ነው። ነገር ግን እስከ 5 ቀን ድረስ የመከላከል ዕድል ሊኖረው ይችላል።
⚠️ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንደ ፖስትፒል ያሉ ኪኒኖች የሰውነት ክብደታቸው ከፍተኛ በሆኑ ሴቶች (BMI ከ30 kg/m² በላይ) ላይ ውጤታማነታቸው ሊቀንስ ይችላል።
ለዚህም የሰውነት ክብደታቸው ከፍ ያሉስ ሴቶች እላይ የጠቀስነውን የመዳብ መከላከያ (Copper IUD) ቢወስዱ ይመረጣል።

መቼስ ጥቅም ላይ መዋል አለበት?
ድንገተኛ መከላከያ በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ይመከራል፦
ያለ ምንም መከላከያ ግንኙነት ሲደረግ፤
ግንኙነት ላይ ኮንዶም ሲቀደድ ወይም ሲወልቅ ፤
መደበኛ የእርግዝና መከላከያ ኪኒን ሲረሳ፤
የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሲደርስ፤
መደበኛ መከላከያዎችን በተሳሳተ መንገድ ሲጠቀሙ፤
ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ በ 72 ሰዓታት ውስጥ እንዲወስዱ ይመከራል።
ይህ የመጨረሻ አማራጭ እንጂ የሁልጊዜ ዘዴ አይደለም።
የተለመዱት የጎንዮሽ ጉዳቶች የትኞቹ ናቸው?
ድንገተኛ መከላከያዎች በአጠቃላይ ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው። ይህ ማለት ግን የጎንዮሽ ጉዳት የላቸውም ማለት አይደለም። መድሀኒቱን ሲወሰድ የሚከተሉት የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊስተዋሉ ይችላሉ፦

ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ
ኪኒኑን እንደወሰድሽ በ2 ሰዓት ውስጥ ካስመለሰሽ ሌላ ተጨማሪ መውሰድ ይኖርብሻል።
የድካም ስሜት እና
የጡት ህመም
ከዚህም ባሻገር የወር አበባ ኡደት ላይ ባለው ተጽእኖ ፤ የሚቀጥለው የወር አበባሽ፦
ቀድሞ ሊመጣ ወይም ሊዘገይ ይችላል።
መጠኑ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል።
👉 አስተውይ! እነዚህ ምልክቶች ጊዜያዊ እንጂ አሳሳቢ አይደሉም።
ፈጽሞ ማድረግ የማይችላቸው ነገሮች
ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ብዙ መልካም ጎኖች ቢኖሩትም የሚከተሉትን አስተውይ።
❌ ለዘወትር አገልግሎት አይሆንም፦ ከመደበኛ መከላከያዎች ያነሰ ውጤታማነት ስላለው ፤ ለዕለት ተዕለት ጥቅም እንዲውል አይመከርም።
❌ በጊዜ ይወሰናል፦ውጤታማ የሚሆነው እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት ሲወሰድ ስለሆነ ፤ በመጀመሪያዎቹ ቀናት/ሰአታት ውስጥ ቢወሰድ ይመከራል። መዘግየት ውጤታማነቱን ይቀንሳል።
❌ ከአባላዘር በሽታ አይከላከልም፦ እርግዝናን ብቻ ነው የሚከላከለው። ከኤችአይቪ (HIV) ወይም ከሌሎች የአባላዘር በሽታዎች የመከላከል አቅም የለውም።
መታረም ያለባቸው አመለካከቶች

በኢትዮጵያ ስለ ድንገተኛ መከላከያ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ ቢመጣም ፤ አሁንም የግንዛቤ ክፍተት ይስተዋላል። አወሳሰዱ ወጥ አይደለም። ብዙ ሴቶች ዘግይተው ይወስዳሉ። በተሳስተ አስተሳሰብ የተነሳ ፤ ያልታሰበ እርግዝና የሚያጋጥማቸው ጥቂቶች አይደሉም። እዚህ ጋር ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የተለመዱ የግንዛቤ ክፍተቶች የሚከተሉት ናቸው።
ስህተት፦ “ውርጃ ያስከትላል።” → እርማት ፦ የሚሠራው እርግዝና ከመጀመሩ በፊት ነው። ስለዚህ ውርጃን አያመጣም።
ስህተት፦ “መሃንነት ያመጣል።” → እርማት፦ ይህንን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም። ያለው ተጽእኖ ጊዜያዊ ነው።
ስህተት፦ “አደገኛ ነው።/ከፍተኛ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል። ” → እርማት፦ የዓለም ጤና ድርጅት ለማንኛውም ሴት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን አረጋግጧል።
ስህተት፦ “የዘወትር መከላከያን ይተካል።” → እውነት፦ እንደ ድንገተኛ አማራጭ እንጂ እንደ መደበኛ አይወሰድም።ለዚያ ሌሎች አማራጮች አሉ።
ከተወሰደስ በኋላ?

የድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ከወሰድሽ በኋላ የሚከተሉትን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይመከራል።
መደበኛ የእርግዝና መከላከያሽን ወዲያውኑ ጀምሪ ወይም ቀጥዪ።
እስከሚቀጥለው የወር አበባሽ ድረስ ግንኙነት ስታደርጊ ኮንዶም ተጠቀሚ።
የወር አበባሽ ከአንድ ሳምንት በላይ ከዘገየ የእርግዝና ምርመራ አድርጊ።
ከፍተኛ የሆድ ህመም ካጋጠመሽ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም ሂጂ።
አስተውይ!
የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ውጤታማነቱ በአወሳሰድሽም ላይ የተመሰረተ ነው። ዛሬውኑ ግንዛቤሽን አስተካክይ።










Comments