top of page

117 results found with an empty search

  • ዳማከሴ ወይስ ጤና አዳም ፡ የቱ ይሻላል?

    በኢትዮጵያ ብዙ ቤቶች ውስጥ ድንገተኛ ራስ ምታት፣ ምች፣ አስቸጋሪ ጉንፋን አልያም የሆድ ህመም ሲጀምር፤ ብዙዎች ወደ ፋርማሲ ከመሄድ ይልቅ ወደ ጓሮአቸው ዞር ማለት ይመርጣሉ። ከብዙ ቤቶች ጓሮም ጤና አዳም እና ዳማከሴ አይጠፉም! ለዚህም ነው በየመኖሪያ ቤቱ .... “ጤና አዳም አምጡ!” አልያም ፤ “ዳማከሴ አለ?” የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ የሚሰሙት። ከጉንፋን እስከ ራስ ምታት፣ ከትኩሳት እስከ አፍንጫ መደፈን — እነዚህ ሁለት ቅጠሎች በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዋነኛ “የመጀመሪያ እርዳታ” ናቸው። ውጤታቸውንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተግባር ይመሰክራሉ። በሳይንስ በኩል እያንዳንዱ ቅጠል ስላለው አስደናቂ የጤና ጠቀሜታ ከዚህ በፊት በነበሩ ጽሁፎቻችን በሰፊው ዳሰናቸዋል። (ጽሁፎቹን እዚህ ያገኟቸዋል፦ የጤና አዳም ሳይንሳዊ ጠቀሜታዎች እና የዳማከሴ ሳይንሳዊ ጠቀሜታዎች)። ዛሬ ግን ሁለቱን ቅጠሎች እናነጻጽራለን ። ታድያ ከሁለቱ ተመራጭ የቱ ይመስልዎታል? አንድ ላይስ መጠቀም ይቻላልን? ለእነኝህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት እያንዳንዱን በጥልቀት እንመልከት። ዳማከሴ በኢትዮጵያ ባህላዊ ሕክምና ውስጥ ዳማከሴ (Ocimum lamiifolium) እንደ ተራ ቅጠል ሳይሆን እንደ ድንገተኛ በሽታ መከላከያ ነው ። ዝርያው በሳይንስ ከበሶ ብላ (Basil) እና ከስጋ መጥበሻ (Rosemary) ጋር የተቀራረበ ነው። ለዘመናት ለሚንቀለቀል ትኩሳት፣ ለጭንቅላት ምታት እና ለ'ምች' ማስታገሻነትም ሲያገለግል ኖሯል። ዛሬ ግን ይህ የጓሮ ፈውስ በባህል ብቻ አልቀረም። በርካታ የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የሳይንስ ጥናቶች የዳማከሴን ቅጠል በላብራቶሪ በመመርመር፣ ከበስተጀርባው ስላሉት አስደናቂ ኬሚካላዊ እና ፋርማኮሎጂካዊ ሚስጥሮች የሚከተሉትን ሳይንሳዊ እውነታዎች አረጋግጠዋል። የዳማከሴ ቅጠል ሲታሽ የሚሰጠው ጠንካራ መዓዛ ዝም ብሎ የተፈጠረ አይደለም። በላብራቶሪ የጋዝ ክሮማቶግራፊ (GC-MS) በጥናት እንደተረጋገጠው፤ ቅጠሉን በእጃችን አሽተን ስናሸት ወይም በሙቅ ውሃ/ቡና ውስጥ አድርገን እንፋሎቱን ወደ ውስጥ ስንስብ፤ ውስጡ ያሉ ውህዶች (ለምሳሌ "ቦርኒል አሴቴት" እና "ፒ-ሳይሜን" የተባሉ አስፈላጊ ዘይቶች (essential oils) ) በቀጥታ ወደ ትንፋሽ ቱቦአችን ይገባሉ። ንጥረ ነገሮቹ በአፍንጫ እና በሳይነስ አካባቢ ያሉ የደም ስሮች ላይ ባላችው አዎንታዊ ተጽእኖ ፤ የታፈነ አፍንጫን ወዲያውኑ የመክፈት እና የመተንፈሻ አካላትን የማረጋጋት ከፍተኛ ሳይንሳዊ አቅም አላቸው። በጥናት እንደተረጋገጠው ዳማከሴ በውስጡ የያዛቸው ፌኖሊክ ውህዶች (Phenolic compounds)፣ ፍላቮኖይዶች (Flavonoids) እና ታኒን (Tannins) ባክቴሪያዎችን የማጥፋት ከፍተኛ አቅም አላቸው። የተክሉ ይዘቶች የባክቴሪያዎችን የውጭ ሽፋን (Cell membrane) በመበጣጠስ እንዳይራቡ እና እንዳይኖሩ ያግዳቸዋል። ይህም በባህል ለቁስል፣ ለጉሮሮ ህመም እና ለኢንፌክሽኖች ለምን ፍቱን እንደሆነ ማረጋገጫ ነው። በላብራቶሪ የእንስሳት ሙከራዎች (In vivo studies) እንደተረጋገጠው፣ የዳማከሴ ቅጠል ውህዶች በሰውነታችን ውስጥ ህመም እና ከፍተኛ ትኩሳት የሚቀሰቅሱትን ፕሮስታግላንዲን (Prostaglandins) የተባሉ ኬሚካሎች እንዳይመረቱ የማገድ (Cox-inhibitory) ባህሪ አላቸው። በዚህም የተነሳ በተወሰነ ደረጃ ከአስፒሪን ወይም ከፓራሲታሞል ጋር የሚመሳሰል ፤ የትኩሳት ማስታገሻ ባህሪ (Antipyretic) ሊኖረው እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ ግን አስፕሪን እና ፓራሴታሞልን ይተካል ማለት አይደለም! ጤና አዳም በኢትዮጵያ ባህላዊ ማህበረሰብ ውስጥ የጤና አዳም (Ruta chalepensis) እና የቡና ትስስር እጅግ ጥብቅ ነው። ማለዳ ላይ ቡና ሆነ ወተት ሲፈላ፤ አንድ የጤና አዳም ቅጠል ተቆርጦ ሲገባ የሚፈጥረው ልዩ መዓዛና ጣዕም ይማርካል። ነገር ግን የዚህ ተክል ስያሜ “የአዳም ጤና” መሆኑ፤ ጥቅሙ ከማዕድ ማድመቂያነት አልፎ እጅግ የላቀ የሕክምና ሚና አለውን? ከዳማከሴ ፈጽሞ የተለየ ኬሚካላዊ ይዘት ያለው ጤና አዳም ፤ በላብራቶሪ ምርምሮች ውስጥ ሲፈተሽ የሚከተሉትን ጥልቅ የሳይንስ እውነታዎች አሳይቷል። ጤና አዳም ለሆድ ህመም እና ለቁርጠት ማስታገሻነት ሊውል ይችላል። ይህም በውስጡ የያዛቸው ፍላቮኖይዶች (እንደ ሩቲን/Rutin ያሉ) እና አልካሎይዶች የተሰኙ ውህዶች ፤የሆድ አካላት ጡንቻዎችን የማረጋጋት/ የማላላት አቅም አላቸው። ለዚህም የምግብ መፈጨት ሥርዓት ሲታወክ ወይም ሆድ መወጠር ሲኖር ፤ ውስጡ አሉት ውህዶች የሆድ ጡንቻዎች እንዳይኮማተሩ በማድረግ ድንገተኛውን የሆድ ቁርጠት (Cramps) ወዲያውኑ ያረጋጋሉ። ሳይንሳዊ ንጽጽር ፡ ዳማከሴ ወይስ ጤና አዳም? በሳይንሳዊው ዓለም “ከሁለቱ የቱ ይበልጣል?” ለሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ሁለቱም እፅዋት ሙሉ ለሙሉ የተለያየ ውህዶች ያሏቸው ፤ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችንን ለይተው የሚያክሙ የተፈጥሮ ልዩ ስጦታዎች ናቸው። አንዱ ለአየር መንገድ ሲደርስ፣ ሌላኛው ደግሞ ለሆድ ዕቃ መታወክ ፍቱን መድኃኒት ነው። የእነርሱን ሳይንሳዊ ልዩነትና ጥንካሬ በተሟላ ሁኔታ ለመረዳት የሚከተለውን ንፅፅራዊ ሰንጠረዥ ይመልከቱ፦ የንጽጽር መስፈርት ዳማከሴ (Ocimum lamiifolium) 🌿 ጤና አዳም (Ruta chalepensis) ☕ በዋነኝነት የሚያገለግለው ለመተንፈሻ አካላት ችግሮች እና ለትኩሳት ለምግብ መፈጨት ችግሮች እና ለትላትል ችግሮች የሚያክማቸው ህመሞች ጉንፋን፣ ሳል፣ የአፍንጫ መታፈን፣ ትኩሳት እና ምች የሆድ ቁርጠት፣ የጋዝ መብዛት፣ የሆድ ትላትል እና ድንገተኛ የራስ ምታት ዋና የኬሚካል ይዘት ቦርኒል አሴቴት፣ ፒ-ሳይሜን እና ዩጂኖል (essential oils)፣ወ.ዘ.ተ... ሩቲን (ፍላቮኖይድ)፣ ሻሌፒን እና አልካሎይዶች፣ወ.ዘ.ተ... አሰራሩ በትንፉሽ ቧንቧ ዙሪያ ያሉ የደም ስሮችን ያላላል፤ ንፍጥን ያቀጥናል፤ ባክቴሪያን ይገድላል በሆድ ዕቃ ውስጥ ያሉ ለስላሳ ጡንቻዎች እንዳይኮማተሩ የካልሲየም ፍሰትን ያግዳል ደህንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀም በእንፋሎት መታጠንን (Inhalation) ማዘውተር (ጉበትን በቀጥታ አይነካም) በሻይ፣ በቡና ወይም በቅመማ ቅመም ውስጥ በጥቂቱ መውሰድ በአጠቃላይ እነዚህ ሁለት እፅዋት የአሠራር ስልታቸውም ሆነ የሚሰጡት የጤና ውጤት ፍጹም የተለያዩ ናቸው። ለዚህም ነው ጥያቄያችን መሆን ያለበት “የትኛው ይበልጣል?” ሳይሆን “መቼ የቱን እንጠቀም?” የሚለው ነው። የመተንፈሻ አካላት እና ትኩሳት ሲኖር፦ ዳማከሴ ተመራጭ ነው። በውስጡ የያዛቸው ልዩ ተለዋዋጭ ዘይቶች የአየር ማስተላለፊያ መንገዶችን በፍጥነት የመክፈትና ትኩሳትን የመቀነስ ከፍተኛ ሳይንሳዊ አቅም አላቸው። የሆድ እና የምግብ መፈጨት ችግር ሲኖር፦ ጤና አዳም ቀዳሚ ምርጫ ነው። የሆድ ዕቃ ጡንቻዎችን በማዝናናት ድንገተኛና አስቸጋሪ የቁርጠት ስሜትን ወዲያውኑ የማጥፋት አስደናቂ ብቃት አለው። አብሮ መውሰድ ይቻላል? ⚠️ አዎ! በባህላዊው አጠቃቀም ሁለቱን ቅጠሎች አንድ ላይ አፍልቶ መጠጣት ወይም መውሰድ ይችላል። ይሁን እንጂ ሁለቱም እፅዋት በውስጣቸው እጅግ ጠንካራ የኬሚካል ይዘት እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም። በመሆኑም አጠቃቀማቸው ጥንቃቄን ይሻል! በተለይም ጤና አዳም በከፍተኛ መጠን ከተወሰደ ለሰውነት መርዛማ ሊሆን ስለሚችል ፤በጥቂቱ እና በልክ መጠቀም ይመረጣል። እንዲሁም ሁለቱም ቅጠሎች (በተለይ ጤና አዳም) ማህጸን ላይ ባላቸው ተጽእኖ ለነፍሰ ጡር እናቶች ፈጽሞ አይመከሩም። ከዚህም ባሻገር የጉበት እና የኩላሊት ችግር ያለባችው ሰዎች ላይ እጅግ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። እዚህ ጋር ያስተውሉ ፤ እነዚህ ቅጠሎች ዋነኛ የህመም ማስታገሻን ፈጽሞ አይተኩም። የዘመናዊ ህክምና መተኪያ ሆነው አገልግሎት ላይ መዋል አይችሉም። ከፍተኛ የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው በሽታዎች ዘላቂ መፍትሄ አይደሉም። ትልቁ ስህተት! “ተፈጥሯዊ ከሆነ አይጎዳም” የሚል እምነት በተፈጥሮ ሕክምና ዙሪያ ያለው ትልቁ እና በጣም አደገኛው የተሳሳተ ግንዛቤ “ተፈጥሯዊ እስከሆነ ድረስ ምንም ዓይነት ጉዳት የለውም” ብሎ ማሰብ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ጥቅም ላይ የዋሉ ዘመናዊ መድኃኒቶች የተቀመሙት ከዕፅዋት መሆኑን መዘንጋት የለብንም! ዕፅዋት በውስጣቸው ኃይለኛ የሆኑ ኬሚካላዊ ውህዶችን ይዘዋል። እነዚህ ኬሚካሎች ልካቸውን ጠብቀው ከተወሰዱ፤ ፈዋሽ ሊሆኑ ቢችሉም፤ መጠናቸው ሲያልፍ ወይም ከተገቢው ውጭ ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ሲቀላቀሉ ግን መርዛማ ሊሆኑ ይችላሉ። የዘመናዊ ሳይንስ ዋና ጥቅሙም ይህንን የዕፅዋቱን ምስጢራዊ ባህሪ በመመርመር “ልኩን” ማሳወቁ ላይ ነው። በዚህም መሠረት የሕክምና ጥናቶች በዳማከሴ እና በጤና አዳም አጠቃቀም ላይ የሚከተሉትን ጥብቅ የሳይንስ ማስጠንቀቂያዎች ይሰጣሉ፦ ዳማከሴ ሲወስዱ ማድረግ ያለብዎ ጥንቃቄዎች ዳማከሴ ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ቢሆንም፣ የረጅም ጊዜ አጠቃቀሙ ላይ ጥንቃቄ ይሻል። የዳማከሴን ጭማቂ በየቀኑ እና ከሁለት ሳምንት በላይ በተከታታይ በከፍተኛ መጠን መውሰድ፤ በውስጡ ያሉት ውህዶች ጉበት እና ኩላሊት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ያደርጋል። በመሆኑም ለአጭር ጊዜ (ለ3 ወይም ለ5 ቀናት) ለትኩሳት እና ለጉንፋን ማስታገሻነት ብቻ መጠቀም ይመረጣል። ለዚህም ሌላኛው መፍትሔው ፤ ቅጠሉን በእጅ አሽቶ ጭማቂውን በጥቂት ጠብታ በውሃ ወይም በቡና መውሰድ፤ አልያም አፍልቶ መታጠን (Inhalation) ይመከራል። የእንፋሎት ትንፋሹ በቀጥታ ከአየር መንገድ ጋር እንጂ ከጉበት ስራ ጋር ስለማይገናኝ ይህ አጠቃቀም እጅጉን ይመክራል። የጤና አዳም ሲጠቀሙ ማድረግ ያለብዎ ጥንቃቄዎች፡ ጤና አዳም እጅግ ኃይለኛ የኬሚካል ውህዶች ስብስብ በመሆኑ፣ አጠቃቀሙ የላቀ ጥንቃቄን ይፈልጋል። ጤና አዳም ለነፍሰ ጡር ሴቶች ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ጤና አዳም በማህፀን ጡንቻዎች ላይ ከፍተኛ የመኮማተር እና የማህፀን ደም ፍሰትን የመጨመር ባህሪ አለው። በመሆኑም ፅንስን የማጨናገፍ አደጋ ስላለው ነፍሰ ጡር እናቶች በምንም መልክ ፈጽሞ ሊጠቀሙበት አይገባም። ውስጡ ያሉት ፉራኖኩማሪኖች ከቆዳ ጋር ንክኪ ፈጥረው ለፀሐይ ብርሃን (UV Rays) ሲጋለጡ፣ ቆዳን ለከፍተኛ ማቃጠል፣ ለሽፍታ እና ለቆዳ ቀለም መለወጥ (Phytophotodermatitis) ይዳርጋሉ። ስለዚህ ቅጠሉን ከነኩ በኋላ ቆዳን በውሃና በሳሙና በሚገባ መታጠብ ያሻል። ልክ እንደ ዳማከሴ ሁሉ፣ የጤና አዳም ዘይትን ወይም ጭማቂን ከልክ በላይ መውሰድ የጉበት መመረዝ (Toxic hepatitis) እና የኩላሊት መቁሰል ሊያስከትል ይችላል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ባህል በቡና ውስጥ የሚገባው የቅጠል መጠን እጅግ አነስተኛ በመሆኑ፣ ለጤናማ ሰው ለአጠቃላይ አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። ማጠቃለያ ዳማከሴ እና ጤና አዳም በኢትዮጵያውያን ጓሮዎች ውስጥ ለዘመናት የቆዩ፣ የትውልድ ዕውቀት እና የባህል መገለጫ የሆኑ ውድ ሀብቶቻችን ናቸው። ዛሬ ላይ የሕክምና ሳይንስ ላብራቶሪዎች በሰፊው መርምረው ያረጋገጡት እውነትም ይሄንኑ ነው፤ እነዚህ ቅጠሎች እንዲሁ በልማድ የሚቀጠፉ ሳይሆኑ፣ እያንዳንዳቸው የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎችን ለይተው የሚያክሙ የተፈጥሮ መድሀኒቶች ናቸው። ሆኖም ግን፣ ተፈጥሯዊ መሆናቸው ብቻውን ከአደጋ ነፃ አያደርጋቸውም። ልክ እንደ ማናቸውም ዘመናዊ መድኃኒቶች ሁሉ፣ የእነዚህም ዕፅዋት ፈዋሽነት የሚረጋገጠው አጠቃቀማቸውን፣ መጠናቸውን (ልክን) እና የሚሰጡበትን ጊዜ አውቀን በጥንቃቄ ስንጠቀምባቸው ብቻ ነው። በመጨረሻም፣ እነዚህ ቅጠሎች የዘመናዊ ሕክምናን ሚና ፈጽሞ ሊተኩ እንደማይችሉ ማስታወስ ይገባል። በዕውቀት እና በኃላፊነት እንጠቀም!

  • የመርከብ ላይ ወረርሽኝ ፡ አለምን ያሳሰበው የሃንታ ቫይረስ (Hantavirus)

    በፈረጆቹ የሜይ ወር መጀመሪያ አከባቢ ላይ ፤ በአዘቦት ጠዋት ላይ ኤም.ቪ ሆንድየስ (MV Hondius) የተባለችው የቅንጦት መዝናኛ መርከብ በኬፕ ቨርዴ የባህር ዳርቻ ላይ መልሕቋን ለመጣል ተገደደች። ይህ በጉዞ ፕሮግራሟ ላይ አልነበረም። ከአርጀንቲና ተነስታ ወደ ካናሪ ደሴቶች 147 ተሳፋሪ ይዛ ፤ በመጓዝ ላይ የነበረችው የዚህች መርከብ ጉዞ፤ ባልታሰበ የህክምና ቀውስ ምክንያት ቅዠት ሆኖ አረፈው! በመርከቧ ላይ አንድ ተሳፋሪ በድንገት ታመመ! ቀጥሎም ሌላኛው... ብዙም ሳይቆይ የታመሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጣ። ያልታወቀ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የመተንፈስ ችግር እና ድንገተኛ የሞት ዜናዎች በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በስፋት መዘገብ ጀመሩ። በጥቂት ቀናት ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የበርካታ አገራት የጤና ተቋማት ቫይረሱ ያለባቸውን ተሳፋሪዎችና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት ደፋ ቀና ማለት ተያያዙት። ይህ ድንገተኛ የህክምና አደጋ በኋላ ላይ የሃንታ ቫይረስ (Hantavirus) ወረርሽኝ መሆኑ ተረጋገጠ። በዚህም መርከቧና ተሳፋሪዎቿ የዓለም አቀፍ የጤና ምርመራ ማዕከል ሆኑ። እስከ ዛሬዋ ግንቦት 2 2018 ዓ.ም ድረስ ፤ የዓለም ጤና ድርጅት እና የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ከዚሁ መርከብ ጋር የተያያዙ ቢያንስ ስምንት ታማሚዎችን( 6 የተረጋገጡ እና 2 የተጠረጠሩ) እና ሶስት አሳዛኝ የሞት አደጋዎችን በቅርበት እየተከታተሉ ይገኛሉ። የመርከቧን ተሳፋሪዎች ከመርከቧ የማወረድ ሥራ እየተከናወነ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አንድ ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም፦ ለመሆኑ ሃንታ ቫይረስ ምንድን ነው? ልንሰጋስ ይገባናል? ለመሆኑ ሃንታ ቫይረስ ምንድን ነው? ሃንታ ቫይረስ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ወይም ኮቪድ-19 አይደለም፤ የሃንታ ቫይረሶች በተለምዶ በሰዎች መካከል በስፋት አይሰራጩም። ይህ የቫይረስ ዝርያ በዋነኝነት እንደ አይጥ ባሉ አጥቢ እንስሳት የሚተላለፍ ሲሆን፤ ከሌሎች ቫይረሶች የሚለየውም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ "ዙኖቲክ" (zoonotic) በሽታ በመሆኑ ነው። በሳይንሳዊው ዓለም የሃንታ ቫይረሶች በሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ይከፈላሉ፦ የድሮው ዓለም (Old World) ሃንታ ቫይረሶች፦ በአብዛኛው በአውሮፓ እና በእስያ የሚገኙ ሲሆኑ፤ ኩላሊትን የሚያጠቃ ከባድ የጤና እክል (HFRS) ያስከትላሉ። የአዲሱ ዓለም (New World) ሃንታ ቫይረሶች፦ በአሜሪካ አህጉር የሚገኙ ሲሆን፤ ሳምባን በፈሳሽ እንዲሞላ በማድረግ የመተንፈሻ አካላትን ክፉኛ የሚያጠቁ (HCPS) ናቸው። እንደ ሮይተርስ (Reuters) ዘገባ ከሆነ፤ በኤም.ቪ ሆንድየስ መርከብ ላይ የተከሰተው ወረርሽኝ "አንዴስ ቫይረስ" (Andes virus) የተባለው የአዲሱ ዓለም የቫይረስ ቡድን አባል ነው። በአንዳንድ ጥናቶች እና የCDC መረጃዎች መሰረት ፤ ይህ አስፈሪ የቫይረስ ዝርያ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 50% የሚደርሱ ታማሚዎችን ለሞት ይዳርጋል። ቫይረሱ እንዴት ይሰራጫል? ለሃንታ ቫይረስ ለመጋለጥ የግድ በመርከብ ላይ መሆን አያስፈልግዎትም፤ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በሚተነፍሱት አየር አማካኝነት ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ። የቫይረሱ ዋነኛ የመተላለፊያ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፦ በአየር መበከል (Aerosolization)፦ የአይጥ ሽንት፣ እዳሪ፣ ወይም የአይጥ መኖሪያ ስፍራዎች በሚነኩበት ጊዜ፤ ቫይረሱ በአይን በማይታዩ ብናኞች አማካኝነት ወደ አየር ይገባል። እነዚህ በአየር ላይ የሚንሳፈፉ ጥቃቅን ጠብታዎች ወደ ውስጥ ሲተነፈሱ ቫይረሱን ያስተላልፋሉ። አካባቢን በማጽዳት ወቅት፦ አቧራማ የሆኑና አይጥ የሚኖርባቸውን ስፍራዎች ሲጠርጉ ወይም ሲያጸዱ የሚፈጠረው ብናኝ፤ ቫይረሱን በአጋጣሚ ወደ ውስጥ ለመተንፈስ ሰፊ ዕድል ይሰጣል፤ በዚህም ቫይረሱ በትንፋሽ አማካኝነት ወደ ሰውነት ይገባል። ቀጥተኛ ንክኪ፦ ምንም እንኳን አልፎ አልፎ የሚከሰት ቢሆንም፤ በአይጥ ንክሻ አልያም በአይጥ እዳሪና ሽንት የተበከሉ ነገሮችን ነክቶ አፍን፣ አፍንጫን፣ ወይም አይንን በመንካት ሊተላለፍ ይችላል። ታድያ የአሁኑን ወረርሽኝ የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? አብዛኞቹ የሃንታ ቫይረሶች በሰዎች መካከል በቀላሉ አይተላለፉም፤ ወረርሽኞች በታሪክ ተወስነው የቆዩትም በዚህ ምክንያት ነው። ነገር ግን የአሁኑ ወረርሽኝ መነሻ የሆነው የአንዴስ ቫይረስ (Andes virus)፤ ለረጅም ጊዜ በሚቆይ የቅርብ ንክኪ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ውስን ችሎታ አለው። ይህ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድል፤ ለቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት ተጨማሪ አቅም ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ደጋግመው እንደሚያሳስቡት፤ ይህ ቫይረስ እንደ ኮቪድ-19 በአየር ላይ በቀላሉ አይተላለፍም። ይልቁንም ስርጭቱ ጥብቅና የቅርብ ንክኪን ይጠይቃል። ይህንን ልዩነት በሚገባ መገንዘብ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ተገቢውን ጥንቃቄ እንድናደርግ ይረዳናል። በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ምን ዓይነት ምልክቶችን መከታተል አለብን? የሃንታ ቫይረስ ፈታኝነቱ መጀመሪያ ላይ እንደ ተራ ጉንፋን መምሰሉ ነው። ምልክቶቹ ከቫይረሱ ጋር ከተገናኙ ከ1 እስከ 8 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ። በሽታው ሁለት ደረጃዎች አሉት፦ የመጀመሪያ ደረጃ (ከ1-5 ቀናት)፦ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የጡንቻ ሕመም (በተለይ በጭን፣ በወገብ፣ እና በጀርባ ጡንቻዎች)፣ ድካም፣ እና ራስ ምታት ሊሰማ ይችላል። በሽታው እየጸና ሲሄድ፦ ቫይረሱ እየገፋ ሲሄድ ታካሚዎች ድንገተኛ የትንፋሽ እጥረት እና የማያቋርጥ ሳል ያጋጥማቸዋል። ይህም የአዲሱ ዓለም የሃንታ ቫይረስ የሳምባ ሕመም (Pulmonary Syndrome) ዋና መለያ ምልክት ነው። እንደ ሲ.ዲ.ሲ (CDC) መረጃ፤ ለዚህ የሳምባ ችግር ከሚጋለጡ 10 ሰዎች መካከል እስከ 4 የሚሆኑት ፈጣን የሕክምና እርዳታ ካላገኙ ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል። ሕክምናውስ ምንድን ነው? ለሃንታ ቫይረስ እስካሁን ድረስ የተለየ ክትባት ወይም መድኃኒት የለም። ሕክምናው ሙሉ በሙሉ በሆስፒታል ውስጥ በሚደረግ የድጋፍ ክትትል ላይ የተመሠረተ ነው። ለዚህም መከላከል የተሻለው የህክምና አማራጭ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ለዚህም ወረርሽኝ ፤ እጅጉን ውጤታማ የሆኑት የመከላከያ መንገዶችም እጅጉን ቀላል ናቸው። አይጦች ካሉባቸው አካባቢዎች ራስዎን ያርቁ። አይጦች ወደ ቤትዎ ወይም መጋዘንዎ የሚገቡባቸውን ቀዳዳዎች በሽቦ ወይም በሲሚንቶ ይዝጉ። አቧራማ መጋዘኖችን ወይም የተተዉ ክፍሎችን ሲያጸዱ፤ መስኮት ይክፈቱ። አየር እንዲገባ ያድርጉ። ብናኝ እንዳይተነፍሱ የመከላከያ ማስኮችን(ቁሶችን) መጠቀም አስፈላጊ ነው። ደረቅ የአይጥ እዳሪን በፍጹም አይጥረጉ። ይልቁንም አካባቢውን በበረኪና ለ5 ደቂቃ ያርጥቡትና ከዚያ በእርጥብ ጨርቅ ያጽዱት። ለረጅም ጊዜ ተዘግቶ የቆየ ክፍል ውስጥ ከመግባትዎ በፊት ለ30 ደቂቃ ያህል መስኮትና በሮችን ከፍቶ አየር እንዲገባ ያድርጉ! የጤና መረጃዎችን ይከታተሉ! የኤም.ቪ ሆንድየስ መርከብ በካናሪ ደሴቶች በለይቶ ማቆያ ስር በምትገኝበት በዚህ ወቅት፤ የጤና ተቋማት ወረርሽኙ በሰፊው ሕዝብ ላይ ስጋት የመፍጠር ዕድሉ አነስተኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ሆኖም ጉዞና እንቅስቃሴ ባልተገደበባት ዓለማችን፤ አዳዲስ ዜናዎችን በንቃት መከታተልና ስለመከላከያ እርምጃዎች የሚወጡ መረጃዎችን መከተል የመጀመሪያው የመከላከያ እርምጃ ነው። አቧራማ ቦታዎችን ካጸዱ በኋላ፤ ከአይጦች ጋር ንክኪ ኖሮዎት ድንገተኛ ትኩሳት ወይም የመተንፈስ ችግር ካጋጠመዎት፤ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ይሂዱ። ዘወትር የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን መመሪያ ይከተሉ!

  • ከ 8000 ኪሎ ሜትር ርቀት የተደረገው ቀዶ ጥገና

    ወቅቱ መጋቢት 2026 ነው። በጂብራልታር! አንድ ታካሚ የቀዶ ጥገና ጠረጴዛ ላይ ተኝቷል። ክፍሉ ውስጥ ያለው ሮቦት እጆች በሰውነቱ ውስጥ ያለውን የፕሮስቴት ካንሰር በከፍተኛ ጥንቃቄ እየለዩ ያወጣሉ። ክፍሉ ውስጥ የሚሰማው የሞኒተሩ ድምፅ ብቻ ነው። የታካሚው ልብ ትርታ በዲጂታል ስክሪን ላይ ይታያል። በታካሚው ራስጌ ቆሞ መመሪያ የሚሰጥ ሐኪም የለም፤ የሐኪሙ እጆች እንደውም በሌላ አገር ናቸው። እንደውም ቀዶ ጥገና ሐኪሙ ያለው ለንደን ውስጥ ባለ አንድ ክሊኒክ ውስጥ ነው። በሐኪሙ ጣቶች እና በታካሚው ልብ ትርታ መካከል 1,500 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕርና የየብስ ርቀት ቢኖርም ፤ በለንደን የሚንቀሳቀሱት የሐኪሙ ጣቶች በጂብራልታር ካሉት የሮቦት እጆች ጋር በፍጹም ቅንጅት ይሰራሉ። በዶክተሩ ጣቶች እና በሮቦቱ እጆች መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት አንድ ሰከንድ አንድ ሰከንድ እንኳን አይሞላም (ስድስት መቶኛ ስከንድ)። ይህም ቴሌሰርጀሪ የቀዶ ጥገና ክፍልን ግድግዳ ማፍረሱን ያሳያል። አዲሱ ዘመን ለብዙ አስርት ዓመታት የቀዶ ጥገና ሕክምና የማይጣስ አንድ ሕግ ነበረው፦ ሐኪሙና ታካሚው በቀዶ ጥገና ክፍል መገናኘት አለባቸው። የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት እጥረት ባለበት አከባቢ ለሚኖር ታካሚ ፤ ይህ ሕግ ብዙውን ጊዜ የሞት ፍርድ ነበር። ዛሬ ግን ይህ ሕግ በቴሌ-ሰርጀሪ (Telesurgery) አማካኝነት ታሪክ መሆን ችሏል። ፈጣን የፋይበር ኦፕቲክስ ግንኙነት ፤ የ5ጂ ቴክኖሎጂ እና የዘመናችን ሳይንስ ያገኛው ግኝቶች ተጣምረው በአለም ዙሪያ የዲጂታል የመረጃ መረብ ገንብተዋል። አሁን አንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም ልክ እንደ ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪ በመቆጣጠሪያ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኝን ታካሚን በስክሪን እያየ የቀዶ ጥገና ማከናወን ይችላል። ይህ ደግሞ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቱን ተደራሽነት ለአለም ህዝብ በሙሉ ያደርገዋል። የሕክምና ዓለምን ያስገረሙ 4 ድንቅ የርቀት ቀዶ ጥገናዎች 1. ከለንደን እስከ ጂብራልታር (2026) በቀዶ ጥገናው ጊዜ የተነሳ ምስ፡ ከቢቢሲ ድህረ ገጽ የተወሰደ ይህ ተራ የሕክምና ሙከራ ሳይሆን የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ ምጥቀት የታየበት ታላቅ ድል ነበር። ፕሮፌሰር ፕሮካር ዳስጉፕታ በለንደን ክሊኒክ ሆነው "ቱማይ" (Toumai) የተባለውን የሮቦት ሥርዓት በመምራት በጂብራልታር የሚገኝን ታካሚ በስኬት አከሙ። የሚገርመው የመረጃ ልውውጥ መዘግየቱ (Latency) 0.06 ሰከንድ ብቻ መሆኑ ነው። ይህም ለሐኪሙ አእምሮ ምንም ዓይነት መዘግየት እንዳይሰማውና ልክ እዚያው ታካሚው አጠገብ እንዳለ ሆኖ በልበ ሙሉነት እንዲሠራ አስችሎታል። 2. ከሮም እስከ ቤጂንግ (8,000 ኪ.ሜ) ይህ ክንውን ልክ እንደ ሳይንስ ልብ-ወለድ ፊልሞች አስደናቂ ነው። ሐኪሙ ዣንግ ሹ ጣሊያን (ሮም) ተቀምጦ፣ በቻይና (ቤጂንግ) የሚገኝን ታካሚ የፕሮስቴት ቀዶ ጥገና አከናወነ። በመካከላቸው የ8,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ቢኖርም፤ የመረጃ ፍጥነቱ ግን 135 ሚሊ ሰከንድ ብቻ ነበር። ይህ ፍጥነት የሰው ልጅ ዓይኑን ከሚከድንበት ቅጽበት (300 ሚሊ ሰከንድ) በሁለት እጥፍ የፈጠነ በመሆኑ፣ የምድር ስፋት ሕይወት ለማዳን እንቅፋት አለመሆኑን በተግባር አረጋግጧል። 3. በሳተላይት የታገዘ ቀዶ ጥገና (2025) ክላሳ ወደ ቤጂንግ የተደረገው ቀዶ ህክምና፡ "የኢንተርኔት ገመድ ባይኖር ወይም ቢቋረጥ ምን ይከሰታል?" ለሚለው ስጋት በ2025 ቻይናውያን ሐኪሞች በሰማይ ላይ መልስ አግኝተዋል። በምድር ላይ ካለ የኬብል መስመር ይልቅ በሳተላይት ግንኙነት በመታገዝ ከ5,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ ቀዶ ጥገና አደረጉ። ይህ ስኬት ወደፊት በጦር ሜዳ፣ በውቅያኖስ ላይ ወይም ገለልተኛ በሆኑ በረሃማ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች የሰለጠነ የሕክምና እርዳታን ከከተማ ሆኖ ለማድረስ ትልቅ ተስፋን ሰንቋል። 4. ከታይላንድ እስከ ቻይና፦ የሕክምና እኩልነት ዶክተሩ ከቻይና እስክሪን እያየ የሀሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና ሲያደርግ። ከባንጎክ ፖስት የተወሰደ በሚያዝያ 2026 በባንኮክና በምዕራብ ቻይና መካከል በ2,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሐሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና ተከናወነ። ቴክኖሎጂው የሕክምና እውቀት ከሐኪሙ አእምሮ ወጥቶ በዲጂታል መስመር አማካኝነት ወደ ማንኛውም የዓለም ጥግ ማድረስ እንደሚቻል አሳይቷል። ታድያ ግን በቴክኖሎጂው ላይ ሕይወትን መጣል ይቻላል? ቴሌ-ሰርጀሪ (Telesurgery) የሕክምናውን ዓለም ድንበር ቢሰብርም ፤ አንድ ትልቅ ጥያቄ ግን ያጭራል፦ ቴክኖሎጂው ችግር ቢያጋጥመው ፤ እንደተጠበቀው ባይሰራ ሕይወትስ ምን ይሆናል? ይህንን የቴክኖሎጂ እመርታን ጥያቄ ላይ የሚያሳድሩ አንዳንድ ፈተናዎች አሉ። ለምሳሌ፡- መዳሰስ አለመቻል አንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም የሚሠራው በአይኑ ብቻ ሳይሆን በጣቶቹም ጭምር ነው። የደም ሥር ትርታን፣ የስጋን መደደር እና መለስለስ በእጅ ዳስሶ የመለየት ጥበብ (Haptics) ለስኬታማ ቀዶ ጥገና ወሳኝ ነው። በቴሌ-ሰርጀሪ ግን ይህ የለም። የሐኪሙ ጣቶች ያዛሉ እንጂ መዳሰስ አይችሉም። ሐኪሙ የሰውን አካል የሚነካው በብረት እንጂ በጓንት አይደለም። ይህ የ መዳሰስ ስሜት መቋረጥ በሐኪሙና በታካሚው መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ወደ ቴክኒካዊ ትዕዛዝ ብቻ ይቀንሰዋል። ይህም ቀዶ ጥገናው ላይ ጫና ማሳደሩ የማይቀር ነው። ግንኙነት ቢቋረጥ ተጠያቂው ማን ነው? የሕግና የሞራል ፈተና ሌላ ትልቁ ጥያቄ ነው። በተለመደ ቪዲዮ ጥሪ ላይ የኢንተርኔት መቆራረጥ ቢያስከፋ ነው፤ ሆኖም ግን በቀዶ ጥገና መሃል ግን ሕይወት ሊያልፍ ይችላል። በቀዶ ጥገና ጊዜ የዶክተሩ ትእዛዝ ሮቦቱ ጋር ባይደርስ ፤ የኢንተርኔት መቆራረጥ ቢከሰት ወይም ግንኙነቱ ቢዘገይ (Lag) ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂው ማን ነው? ኢንተርኔት አቅራቢው የቴሌኮም ድርጅት? የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ችግር ስላጋጠመ ሆስፒታሉ? የቴክኖሎጂው ዝግጅት ስለሌለው ወይንስ ሐኪሙ? ቀዶ ጥገናውን እያደረገው ያለው በመሆኑ ፤ በቅጽበት የሚደማ ደምስርን መቋጠር ባለመቻሉ። ተጠያቂው ማን ነው? የ ኢንተርኔት መረብ ደህንነት ሕይወት በዳታ መልክ በኢንተርኔት ሲጓዝ፤ ሌላው ስጋት የሳይበር ጠለፋ ነው። አንድ ታካሚ በቀዶ ጥገና ጠረጴዛ ላይ እንዳለ ፤ የግንኙነት መረቡ ቢጠለፍ ውጤቱ አስከፊ ነው። በመሆኑም ሆስፒታሎች አሁን የቀዶ ጥገና ክፍሉን ብቻ ሳይሆን፣ መረጃው የሚጓዝበትን የዲጂታል መስመርም መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ጋዜጣ ላይ የማይወጣው የማይታየው ቡድን በሺዎች ኪሎ ሜትሮች ርቆ ያለው ሐኪም ላይ ብናተኩርም፤ የታካሚው ሕይወት ግን በእርግጥ ያለው በቅርቡ ያሉ የቀዶ ጥገና ህክምና ቡድን ላይ ነው። ኢንተርኔት ቢቋረጥ ወይም ሮቦቱ ሥራ ቢያቆም፣ የክፍሉ የሕክምና ቡድን በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ቀዶ ጥገናውን ተረክበው ለማስቀጠል ዝግጁ መሆን አለባቸው። ቴሌ-ሰርጀሪ ስኬታማ የሚሆነው ሮቦቱ ሲሠራ ብቻ ሳይሆን፤ ሮቦቱ ሲበላሽ የሰው ልጅ ተክቶት ለመሥራት ሲችል ነው። ተግባራዊነቱ ለኢትዮጵያ ምን ያህል ነው? ዓለም ለንደንና ሮም ያሉ ሐኪሞችን በአድናቆት ሲመለከት፤ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ የራቀ ነው። የሐኪምና የሕዝብ ብዛት ጥምርታ ከ100,000 ሰው ከአንድ ስፔሻሊስት በታች በሆነበት አገራችን ፤ ርቀት ችግር የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። ለዚህ እውነት ተግባራዊ ቢሆን ፤ ቴሌ ሰርጀሪ የሚያመጣቸው መልካም ጎኖች አሉ። ሆኖም ግን የሚከተሉት መታሰብ አለባቸው። ትልቁ ፈተና "የሁለትዮሽ ቡድን" ወጪና ድካም ነው። ቴሌ-ሰርጀሪ "አንድ ታካሚ ግን ሁለት የሕክምና ቡድን" ይጠይቃል፤ አንደኛው ከሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በስክሪን የሚያክም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሽተኛው አጠገብ ሆኖ የኢንተርኔት መቆራረጥን ወይም የመብራት መጥፋትን በተጠንቀቅ የሚጠብቅ ነው። የሰው ኃይል እጥረት ባለባት አገር፤ አንድን ሙሉ የባለሙያ ቡድን ለጥንቃቄ ብቻ "ተጠባባቂ" አድርጎ ማስቀመጥ የሰው ኃይል ብክነትን ብቻ ሳይሆን፤ ለሆስፒታሎችና ለታካሚዎች የማይቀመስ የሕክምና ወጪን ይዞ ይመጣል። ከዚህም በላይ የመበራት መጥፋት በተለመደበትና የኔትወርክ መቆራረጥ እጅጉን አስቸጋሪ በሆነበት በሀገራችን ፤ ቀዶ ጥገና መሃል የሮቦት እጅ መቆሙ አልያም አርፍዶ መስራቱ፤ የምናልባት ጉዳይ ሳይሆን ፤ የሚያጋጥም አደጋ ነው ። እንደ ሀገርስ፦ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በአንድ የሮቦት ሲስተም ላይ ማዋል ይሻላል ወይስ ያንን ገንዘብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሐኪሞችን ለማሰልጠንና የገጠር ክሊኒኮችን ለማጠናከር? ለጊዜው በኢትዮጵያ ያለው እውነተኛ "ዲጂታል አብዮት" በሮቦቱ ቀዶ ጥገና ማድረጉ ሳይሆን ቴሌ-ሜንቶሪንግ (Telementoring) ሊሆን ይችላል። ይህም የዓለም ስፔሻሊስቶች በኢንተርኔት አማካኝነት የኢትዮጵያ ሐኪሞችን "በጆሮአቸው" እየመከሩ ቀዶ ጥገናው ላይ ማገዙ ነው። እንደ ሀገር እያደግን ስንሄድ ግን በሙሉ ደረጃ መተግበር ይችላል። ባጠቃላይ ሲታይ፤ ቴሌ-ሰርጀሪ ለኢትዮጵያ የሕክምና ዘርፍ ብሩህ ተስፋን ሰንቆ የመጣ "የነገ ተአምር" መሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ፣ ያለንበት ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ቴክኖሎጂውን ዛሬውኑ በሙሉ አቅም ለመተግበር ገና መሆናችንን ያሳየናል።

  • ስለ ሪህ ማወቅ ያለብዎ

    ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በዝምታ ነው! ሪህ ያለበት ሰው ቀኑን ደህና ሆኖ ውሎ ፤ ሌሊት ሲሰቃይ ሊያሳልፍ ይችላል። አንሶላ ሲነካው እንኳን የሚያሳብድ ፤ የሚመዘምዝ/ የሚለበልብ/ የሚቆረጥም ከባድ ህመም አለው። ህመሙ እጅጉን ከባድ ነው። የሆነ ባዕድ ነገር መገጣጠሚያ ውስጥ ገብቶ የሚወጋና የሚቆረጥምም ይመስላል። በመገጣጠሚያ ላይ ሰፍሮ የሪህ ህመም የሚያመጣው ርኩስ መንፈስ ምስል (ይህ የድሮ አስተሳሰብ ነበር!) ከዘመናዊው ሕክምና ዕውቀት በፊት፤ ይህ ድንገተኛና ክፉ ስቃይ "በመገጣጠሚያ ውስጥ በሰፈረ ርኩስ መንፈስ" የሚመጣ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ይህም ሕመሙ ካለው ኃይል የተነሳ ነበር። በወቅቱም አንድ የማይታይ ክፉ ኃይል መገጣጠሚያን ቆንጥጦ ይዞ / እየቀጠቀጠ ያሳምማል ተብሎ ይታሰብ ነበር (እላይ ያለውን ምስል ይመልከቱ)። ለዚህም ብዙዎች መንፈሳዊ መፍትሔዎች ይፈልጉት ነበር። ቆየት ብሎም በሽታው "የነገሥታት በሽታ" የሚል ስያሜ አገኘ። ይህ የሆነው በሽታው የላቀ ክብር ኖሮት ሳይሆን፤ ከቅንጦት አመጋገብ፣ ከሥጋ ብዛትና፣ ከመጠን ካለፈ መጠጥ ጋር ተያይዞ ስለሚከሰት፤ በወቅቱ ድሎት ያላቸው ወገኖች ብቻ የሚያስተናግዱት በመሆኑ ነበር። ዛሬ ግን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ በሽታ ሆኗል። በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ የአኗኗር ዘይቤ መለወጥን ተከትሎ የሪህ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም፤ አሁንም ድረስ በበሽታው ዙሪያ ባለ የግንዛቤ ክፍተት ፤ እንደ ተራ ቁርጥማት ታይቶ በአግባቡ ሳይታከም ረዥም ጊዜ ይቆያል። ይህም በሽታው እንዲባባስ እድልን ይከፍታል። በደንብ ለመረዳት ስለ ሪህ በጥልቀት እንመልከት... ሪህ በትክክል ምንድን ነው? ሪህ በዋናነት የመገጣጠሚያ ሕመም ብቻ ሳይሆን ፤ የሰውነት ባዮኬሚካላዊ ኡደት (Metabolism) መዛባት ውጤት ነው። ይህ ችግር የሚከሰተው ዩሪክ አሲድ (Uric acid) የተባለ ዝቃጭ በመገጣጠሚያዎች ውስጥ ሲከማች በሚፈጠር የመቆጣት (Inflammation) ዓይነት ነው። ዩሪክ አሲድ ደግሞ ሰውነታችን ፒዩሪን (Purines) የተባሉ ውህዶችን ሰባብሮ ወደ ጥቅም ሲቀይር የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ተረፈ ምርት ነው። በስተቀኝ የሚታየው ቢጫ ክምችት፤ በአውራ ጣት መገጣጠሚያ ላይ የተከማቸና ለሪህ ሕመም ምክንያት የሚሆን የዩሪክ አሲድ ዝቃጭ ነው። በጤናማ ሰውነት ውስጥ የተመረተው ዩሪክ አሲድ በደም ውስጥ ይሟሟል። ደም ውስጥ ያለው ዩሪክ አሲድም ኩላሊት ጋር ሲደርስ ተጣርቶ በሽንት መልክ ከሰውነት ይወገዳል። ይህ ኡድት ሲስተጓጎል ሪህ ይፈጠራል። ይህም የሚፈጠረው ሰውነታችን ከመጠን በላይ ዩሪክ አሲድ ሲያመርት (ስጋ በመብላት፣ ወ.ዘ.ተ....) ወይም ኩላሊታችን ዝቃጩን በአግባቡ ማስወገድ ሲያቅተው(የኩላሊት ችግር ሲኖር) በደማችን ውስጥ ያለው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ዋናው ችግር የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው። በደም ውስጥ ያለው የዩሪክ አሲድ መጠን እጅጉን ሲበዛ ፤ የዩሪክ አሲድ ዝቃጩ ወደ ክምችት ይቀየራል። ይህም ክምችት እንደ መርፌ የሾሉ ክሪስታሎች በውስጡ ያሉት ሲሆን ፤ በመገጣጠሚያዎች ውስጥ ይሰበሰባል። ይህም መውጋትና መቆርጠም ይጀምራል። ይህም ለከፍተኛ ስቃይ፤ ለመገጣጠሚያ መቆጣትና ለድንገተኛ እብጠት ዋነኛው ምክንያት ይሆናል። ሪህ ለምን በጣም ያማል? ሪህ ዝምተኛ አይደለም። ዋናው መለያው በድንገት የሚመጣ ከፍተኛ ህመም ነው። ህመሙ ከባድ ከሆኑ የመገጣጠሚያ ህመሞች ተርታ ይመደባል። የሚሰማውም ብዙውን ጊዜ በሌሊት ወይም በማለዳ ላይ ነው። ብዙውን ጊዜ የሚጠቃው መገጣጠሚያ የእግር ትልቁ ጣት ስርን(ኳሱን)ነው። ይህም ህመም ፖዳግራ/Podagra ይባላል። ይህ የተለመደው ቦታ ይሆን እንጂ ፤ ሪህ ቁርጭምጭሚትን፣ ጉልበትን፣ የእጅ ጣቶችን እና ክርንን ሊያጠቃ ይችላል። ታድያ ህመሙ ለምን ይበረታል? የሕመሙ ግዝፈትና የጥቃቱ ድንገተኛነት የሚያያዘው ፤ የሰውነታችን የበሽታ መከላከል ሥርዓት ከሚሰጠው ምላሽ ነው። የሰውነታችን መከላከያ ሰራዊት እነዚህን በመገጣጠሚያ ውስጥ የተከማቹ መርፌ መሰል ክሪስታሎች እንደ ባዕድ ወራሪ ይመለከታቸዋል። ለዚህም ነጭ የደም ህዋሳት ወደ ተጠቂው ቦታ በከፍተኛ ሁኔታ ይዘምታሉ። እነኝህ ህዋሳት በሚያደርጉት ጥቃት (የሰውነታችን የተጋነነ ምላሽ) የሪህ ምልክቶች ይታያሉ። መገጣጠሚያው ያብጣል ፤ ይቀላል ፤ሙቀት ይኖረዋል/ለንክኪ ያተኩሳል እንዲሁም ሥሥ ነገር እንኳን ሲነካው እጅጉን ያማል። ይህ ሂደት ሰውነታችን ራሱን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ቢሆንም፤ ውጤቱ ግን ልብስ ሲነካው የሚብስ ጽኑ ስቃይ ይሆናል። 💡 ያስተውሉ፦ ድንገተኛ የሆነ የመገጣጠሚያ ሙቀት እና እብጠት ለመጀመሪያ ጊዜ ካጋጠመዎት ወደ ሕክምና ባለሙያ መሄድ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ምልክቶቹ ከሪህ ጋር የሚመሳሰል ግን አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልገው ሌላ የመገጣጠሚያ ኢንፌክሽን (septic arthritis) ሊሆን ስለሚችል ነው። ለዚህም በቤት ውስጥ በሚደረግ ህክምና ብቻ ማለፍ አደጋ አለው። የሪህ በሽታ ለምን እየጨመረ መጣ? በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሪህ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ይህ ለውጥ በግልጽ እየታየ ይገኛል። ለዚህ መባባስ ዋነኛው ምክንያት የከተማ ነዋሪ መሆን ያስከተለው የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ነው። በተለይም የስጋ፣ የለስላሳ ስኳር መጠጦች እና የተቀነባበሩ ምግቦች ፍጆታ መጨመር፤ ከሰውነት እንቅስቃሴ መቀነስ ጋር ተዳምሮ ለዩሪክ አሲድ መከማቸት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።በመሆኑም ሪህ የአንድ መገጣጠሚያ ሕመም ብቻ ሳይሆን፤ አጠቃላይ የጤና ሁኔታችንና የአኗኗር ዘይቤያችን ነጸብራቅ ነው። ለሪህ ተጋላጭ ማነው? ከአኗኗር ዘይቤ ባሻገር፤ ለሪህ በሽታ ተጋላጭነትን የሚጨምሩ የተፈጥሮ እና የግል ሁኔታዎች አሉ። እነዚህም በሽታው በማን ላይ በብዛት ሊከሰት እንደሚችል ፍንጭ ይሰጡናል። ጾታ እና እድሜ፦ ሪህ በብዛት በወንዶች ላይ የሚታይ በሽታ ሲሆን፤ በተለይም ከ30 እስከ 50 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ በስፋት ይከሰታል። ሴቶች ደግሞ የመውለጃ እድሜያቸው እስኪያልፍ (Menopause) ድረስ ባለው ጊዜ በሰውነታቸው ውስጥ በሚመነጨው የኢስትሮጅን ሆርሞን ጥበቃ ስለሚያገኙ ተጋላጭነታቸው አነስተኛ ነው። ነገር ግን ከዚያ በኋላ በሴቶች ላይም ተጋላጭነቱ እየጨመረ ይሄዳል። የቤተሰብ ታሪክ (ዘረመል)፦ በቤተሰብዎ ውስጥ የሪህ ተጠቂ ካለ፤ እርስዎም የመያዝ ዕድልዎ ከፍተኛ ነው። ይህም የሰውነታችን የሜታቦሊዝም ኡደትና ዩሪክ አሲድን የማስወገድ ብቃት በከፊል በዘር የሚወረስ በመሆኑ ነው። የጤና ሁኔታዎች፦ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የደም ግፊት፣ ስኳር፣ የልብ እና የኩላሊት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ለሪህ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም አንዳንድ የደም ግፊት መድኃኒቶች በደማችን ውስጥ የዩሪክ አሲድ መጠንን ሊጨምሩ ይችላሉ። የበሽታውም መጭመር በአንድ በኩል ከዚህ ጋር ተያያዥነት አለው። የምግብ ጥያቄ፦ ሪህን በትክክል የሚያመጣው ምንድን ነው? ሪህ የሚመጣው "ብዙ ስጋ በመብላት" ብቻ ነው የሚል የተሳሳተ እምነት በማህበረሰባችን ውስጥ ይታያል። ይህ አመለካከት በከፊል እውነት ቢሆንም፤ ሙሉውን ምስል ግን አይገልጽም። እርግጥ ነው፤ እንደ ጥሬ ስጋ (ክትፎ ወይም ቁርጥ)፤ እንደ ጉበት እና ኩላሊት ያሉ አካላትን መመገብ እና የተወሰኑ የባህር ምግቦች በውስጣቸው ባለው ከፍተኛ የፒዩሪን መጠን አላቸው። ለዚህም የዩሪክ አሲድን ክምችት ይጨምራሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ቢራ እና ጠጅ ያሉ የአልኮል መጠጦች በሰውነታችን ውስጥ ዩሪክ አሲድ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመረት በማድረግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኩላሊት ዝቃጩን እንዳያስወግድ በማሰናከል ለሕመሙ መባባስ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ከስጋ ባልተናነሰ ሁኔታ የስኳር መጠጦችም (በተለይም ፍሩክቶስ ያላቸው ለስላሳዎችና የታሸጉ ጭማቂዎች) ለሪህ ተጋላጭነትን በእጅጉ ይጨምራሉ። በአንጻሩ ደግሞ እንደ ወተትና እርጎ ያሉ የምግብ አይነቶች የዩሪክ አሲድ መጠንን የመቀነስ ባህሪ አላቸው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የጾም ምግቦች (አትክልትና ጥራጥሬዎች) ለሪህ ህመምተኞች እጅግ ተስማሚና ጤናማ አማራጮች ናቸው። ህመሙ ከመጀመሩ በፊት አንድ ሰው ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ሳይታይበት ለዓመታት በደሙ ውስጥ ከፍተኛ የዩሪክ አሲድ መጠን (Hyperuricemia) ሊኖረው ይችላል። ይህ ወቅት በሽታው በሰውነት ውስጥ ጫና የሚያሳድርበት ፤ ነገር ግን ገና ያልጀመረበት ረቂቅ ምዕራፍ ነው። እዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ ፤ የሕመም ምልክቶች እስካልታዩ ወይም ሌሎች ለከፋ ችግር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እስካልኖሩ ድረስ ወዲያውኑ መድኃኒት ላለመጀመር ይመከራል። ይሁን እንጂ ምልክቶቹ አንዴ ከታዩና ሕመሙ ከቀሰቀሰ፤ በሽታው ወደ አዲስና አስቸጋሪ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ማለት ነው። ይህም ማለት ሰውነታችን ውስጥ ያሉት ክሪስታሎች መከማቸት ብቻ ሳይሆን፤ መገጣጠሚያችንን ማጥቃት መጀመራቸውን የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ ምልክት ነው። በመሆኑም በዚህ ወቅት ወደ ሕክምና በመሄድ ተገቢውን ክትትል ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። የሕክምና ዘዴዎች የሪህ ሕክምና ዋና ግብ ሕመምን ማስታገስ ብቻ ሳይሆን፤ መሠረታዊ የሆነውን የሰውነት ባዮኬሚካላዊ ኡደት (Metabolism) መቆጣጠር ነው። ሕክምናው እና የመከላከያ እርምጃዎቹ በሚከተሉት ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ይጠቃለላሉ፦ ፩. አፋጣኝ ሕክምና ማድረግ፦ ድንገተኛ ሕመም በሚቀሰቅስበት ወቅት ዋነኛው ግብ እብጠትንና ስቃይን መቀነስ ነው። ለዚህም የሕክምና ባለሙያዎች የተለያዩ መድሐኒቶችን ያዝዛሉ። ፪. የአኗኗር ዘይቤና የምግብ ምርጫ፦ ሪህን ለመከላከልና የዩሪክ አሲድ መጠንን ለማመጣጠን የሚከተሉት እርምጃዎች ወሳኝ ናቸው፦ ውህ አብዝቶ መጠጣት ይመከራል። በቂ ውኃ መጠጣት ኩላሊታችን ዩሪክ አሲድን በቀላሉ አጥልቶ እንዲያስወግድ ይረዳዋል። የምግብ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርብዎታል። ከፍተኛ ፒዩሪን ያላቸውን ምግቦች (ቀይ ሥጋና የውስጥ አካላት) መቀነስ፤ እንዲሁም በስኳር የበለፀጉ ለስላሳዎችንና አልኮልን ማስወገድ። ክብደትን ይቆጣጠሩ። ከልክ ያለፈ ውፍረት ለሪህ ተጋላጭነትን ስለሚጨምር፤ ጤናማ የሰውነት ክብደትን መጠበቅና መጠነኛ እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ፫. የረዥም ጊዜ ክትትል ሪህ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ በየጊዜው የሚመላለስ በሽታ ነው። በመሆኑም የሕመሙ ጥቃት ተደጋጋሚ ከሆነ፤ የዩሪክ አሲድ መጠንን በቋሚነት የሚቀንሱ መድኃኒቶችን መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል። በየጊዜው የዩሪክ አሲድ መጠንን በደም ምርመራ መከታተልና ከሐኪም ጋር መመካከር በሽታው ወደ ከፋ ደረጃ (የመገጣጠሚያ እብጠትና የኩላሊት ጠጠር) እንዳይሸጋገር ይረዳል።ረጅም ጊዜ ህክምና ደግሞ የዩሪክ አሲድ መጠንን የሚቀንሱ መድሃኒቶችን መውሰድን ያካትታል። ⚠️ ጠቃሚ ጥንቃቄ፦ የረጅም ጊዜ መድሃኒቶች ከፍተኛ ህመም ባለበት ወቅት መጀመር የለባቸውም! ምክንያቱም ድንገተኛ የዩሪክ አሲድ መጠን ለውጥ ፤ ህመሙን ሊያባብሰው ይችላል። ህመሙ ጋብ ሲል መጀመር ይመረጣል። ሪህ ችላ ቢባል ምን ይከሰታል? ሪህ የ"ህመም" ጉዳይ ብቻ አይደለም። ካልታከመ ወደ ስር የሰደደ እና ከባድ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል። በሪህ ምክንያት የመጣ የእጅ ጣቶች መገጣጠሚያ ለውጥ ሪህ የ"ሕመም" ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ካልታከመ ወደ ስር የሰደደ እና አውዳሚ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል። በሽታው በወቅቱ ካልተገታ መገጣጠሚያን ደጋግሞ ያጠቃል። ይህም በጊዜ ውስጥ ብዙ የዩሪክ አሲድ ክምችት መጋጠሚያ ላይ እንዲኖር ከማድረጉ ባሻገር ፤ እላይ በምስሉ እንደሚታየው የመገጣጠሚያን ቅርጽ በቋሚነት ሊለውጥ ይችላል። ይህ ክምችት በህክምናው ቶፋይ (Tophi) ይባላል። በመገጣጠሚያዎች ዙሪያ ስለሚገኝ ከመልክ ባሻገር ፤ የመገጣጠሚያን እንቅስቃሴ ይገድባሉ። ኩላሊት ላይም ዩሪክ አሲድ ከተከማቸ ፤ ለኩላሊት ጠጠር እንዲሁም ለኩላሊት ችግር ሊያጋልጥ ይችላል። ያስተውሉ! ሪህ የመገጣጠሚያ ህመም ብቻ አይደለም። የበሽታው ስቃይ እጃችን ላይ እንደሆነው ሁሉ መፍትሄውም በእጃችን ላይ ይገኛል። ዛሬ የምናደርገው የአመጋገብ ምርጫ፤ የምንወስደው የውሃ መጠን እና ለጤናችን የምንሰጠው ትኩረት የነገውን ጤንነት ይወስነዋል። ሕመሙ እስኪቀሰቅስ አይጠብቁ። ምልክቱ ከታየዎት ወደ ሕክምና በመሄድ ተገቢውን ምርመራ ያድርጉ፤ የአኗኗር ዘይቤዎን ያስተካክሉ፤ ጤናዎን በንቃት ይጠብቁ።

  • ስኳር ማቆም ከ ስኳር በሽታ ይታደጋልን?

    ጣፋጭ ፍራቻ እና ውስብስብ እውነታው ብዙውን ጊዜ ማስጠንቀቂያው የሚጀምረው እንዲህ በሚል ነው፦ “ስኳር መብላትን አቁም፤ አለበለዚያ ስኳር ይይዝሃል።” በብዙዎች ዘንድ ይህ መልዕክት በስፋት ይነገራል። ስኳር እንደ ዋነኛ ጠላት ይታያል። ያለ ስኳር የሚጠጣ ሻይ እንደ መድኃኒት ይቆጠራል። ዳቦ፣ ሩዝ እና ፍራፍሬዎች እንኳን ሳይቀር በጥርጣሬ ዓይን ይታያሉ። ግን ነገሩ እንደዚህ ቀላል ነውን? ስኳርን ማቆም ብቻውን ከስኳር ህመም ይጠብቀናል? ወይስ እውነታው ከባዮሎጂ፣ ከአኗኗር ዘይቤ እና ከጊዜ ጋር የተቆራኘ ከዚህ የበለጠ ውስብስብ ነው? ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ከፍርሃት ወጥተን ወደ ሳይንስ መግባት ይኖርብናል። የሰውነታችን እና የስኳር ግንኙነት እንደ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ፍራፍሬ ወይም ስኳር ያሉ ምግቦችን ስንመገብ ሁል ጊዜ ሰውነታችን ካርቦሃይድሬቱን ወደ ግሉኮስ (Glucose) ይቀይረዋል። ይህ ግሉኮስ ወደ ደም ዝውውራችን ይገባል። በዚህ ጊዜ ኢንሱሊን (Insulin) የተባለ ሀይለኛ ሆርሞን ስራውን ይጀምራል። ኢንሱሊን እንደ ቁልፍ በማገልገል ግሉኮስ ወደ ህዋሳት ገብቶ ለኃይል ምንጭነት እንዲውል ያደርጋል። ጤናማ በሆነ ሰውነት ውስጥ ይህ ሂደት ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል። ነገር ግን በስኳር ህመም (በተለይም ሁለትኛው አይነት ስኳር ውስጥ) ይህ ስርአት መታወክ ይጀምራል። ሰውነታችን በቂ ኢንሱሊን ማምረት ያቅተዋል ወይም ሴሎቻችን ለኢንሱሊኑ ምላሽ መስጠት ያቆማሉ። ይህም የኢንሱሊን መቋቋም (Insulin Resistance) ይባላል። እውነተኛው ችግር የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው። ለምን ስኳር ያላቸው ምግቦች ከስኳር ህመም ጋር ይያያዛሉ? ይህንን በግልጽ እንረዳው። ስኳር በቀጥታ በአንድ እርምጃ ብቻ የስኳር ህመምን አያመጣም። ነገር ግን የተጨመረ ስኳር የበዛባቸው ምግቦች (በተለይም ለስላሳ መጠጦች) ለበሽታው የመጋለጥ እድልን በእጅጉ ይጨምራሉ። ለምን? ስኳር ያለባቸው ምግቦች በሚመገቡበት ጊዜ የሚከተሉትን ሂደቶች በሰውነትዎ ውስጥ ይፈጠራሉ። ከመጠን በላይ ኃይል ያገኛሉ (ካሎሪ )→ይህም የክብደት መጨመር ያመጣል። የክብደት መጨመር በበኩሉ → የኢንሱሊን መቋቋም መጨመርን ያስከትላል። የኢንሱሊን መቋቋም ደግሞ → በጊዜ ሂደት የደም ስኳር መጠን ከፍ እንዲል ያደርጋል። ስለዚህ ዋናው ችግር ስኳሩ ብቻ ሳይሆን፤የአመጋገብ ዘይቤው፣ ከፍተኛ የካሎሪ ፍጆታ፣ የቃጫ (Fiber) እጥረት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ድምር ውጤት ነው። ስኳር ብቻ ፈጽሞ አይደለም። ችግሩ ስኳር ብቻ አይደለም ብዙዎቻችን ትኩረታችን ያለው ሻይ ውስጥ በምንጨምረው ስኳር ወይም በምንጠጣው ለስላሳ መጠጥ ላይ ነው። እርግጥ ነው፣ እነሱን መጠንቀቅ መልካም ነው፤ ግን ችግሩ እዚህ ጋር ብቻ አያበቃም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በነጭ ዱቄት የተጋገረ ዳቦ፣ የተቀነባበረ ነጭ ሩዝ እና የታሸጉ ፋብሪካ ስራ ምግቦች በደማችን ውስጥ የሚያስከትሉት ውጤት ልክ እንደ ስኳር ነው። እነዚህ ምግቦች በደም ውስጥ ያለ የስኳር መጠንን በፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራሉ። 'ከፍተኛ የሆነ ግላይሴሚክ ኢንዴክስ (Glycemic Index) አላቸው። ስለዚህ 'ስኳር አቆምኩ' ብለን ፤ ነጭ ዳቦ ወይም ሩዝ ላይ ካልተጠነቀቅን፤ ግማሽ መንገድ ላይ ብቻ ነን ያለነው። ምክንያቱም ለሰውነታችን ስኳር ተመገብን ፤ ዳቦ ሆነ ሩዝ በሰውነትዎ ላይ የሚያሳድሩት ተጸእኖ ተቀራራቢ ነው። በስኳር ህመምተኞች ላይ ስኳር ለምን ይከለከላል? አንድ ሰው በስኳር ህመም ተያዘ ማለት ሰውነቱ በደሙ ውስጥ ያለውን ስኳር የማስተናገድ አቅሙ ተዳክሟል ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ ጣፋጭ ነገሮችን መመገብ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል። እንዴት ቢሉ? በመጀመሪያ፣ ጣፋጩ ምግብ እንደተበላ በደማችን ውስጥ ያለው ስኳር በድንገት በጣም ይጨምራል። ይህ ደግሞ ቀድሞውኑ ዝልፍልፍ ላለውና ለተዳከመው የኢንሱሊን ስርአታችን የማይሸከመውን ተጨማሪ ጫና ይሳድራል። ነገሩ እዚህ ላይ ብቻ አያበቃም፤ ይሄ በደም ውስጥ የበዛው ስኳር በጊዜ ሂደት ሰውነትን ይጎዳል። ቀስ እያለ የአይን ብርሃንን ይነጥቃል፤ ኩላሊትን ያዳክማል፤ እንዲሁም የነርቭ ስርአትን በማጥቃት ለከባድ መዘዞች ይዳርጋል። ትልቁ ስህተት! “ስኳር ካቆምኩ በሽታው ይጠፋል” ይህ በጣም የተለመደ እና አደገኛ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። ስኳርን ማቆም የደም ስኳርን ለመቆጣጠር ይረዳል፣ ክብደት ለመቀነስም ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ስኳር መቀነስ በራሱ በሽታውን ወዲያውኑ አያጠፋውም። ምክንያቱም የስኳር ህመም የኢንሱሊን መቋቋምን፣ የጣፊያ ስራን እና የዘር ውርስን ጋር ቁርኝት ያለው ቋሚ የሰውነት ኡደት መዛባት ነው። አንዳንድ ሰዎች በአኗኗር ለውጥ የደም ስኳራቸውን ወደ ጤናማ ደረጃ ሊመልሱ ይችላሉ። ይህ ሪሚሽን (Remission) እንጂ ፈውስ (Cure) አይደለም፤ ምክንያቱም የአኗኗር ዘይቤው ከተቀየረ ምልክቶቹ ሊመለሱ ይችላሉ። ስኳርን ለመቀነስ ፤ የታሸጉ ምግቦች ሲገዙ ምን ይዩ? በሱፐርማርኬቶች ውስጥ “ጤናማ” ተብለው የሚሸጡ ብዙ ምግቦች የተደበቁ ስኳሮች ሊኖሯቸው ይችላል። ሰውነትዎን ለመጠበቅ የግድ የምርቱን ይዘት (Ingredients) እና የአመጋገብ መረጃ (Nutrition Facts) መመልከት አለብዎት። ስኳር ብዙ ጊዜ ስሙን ቀይሮ ይደበቃል። በሚገዙት ዕቃ ላይ ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ይዘቶች ውስጥ እነዚህን ስሞች ካዩ፣ ዕቃውን መልሰው ያስቀምጡት! ሀይ ፍሩክቶስ ኮርን ሲረፕ (High Fructose Corn Syrup) ማልቶዴክስትሪን ወይም ዴክስትሮስ (Maltodextrin/Dextrose) ኢንቨርት ሹገር ወይም ሞላሰስ (Invert Sugar/Molasses) የፍራፍሬ ጭማቂ ክምችት (Fruit Juice Concentrates) እነዚህ ስሞች ካሉ ስኳር መኖሩን ይወቁ። የ"4-ግራም" ህግ በምርቱ ማሸጊያ ላይ "Total Sugars" የሚለውን ይመልከቱ። ይህንን ቀመር ሁልጊዜ ያስታውሱ፦ 4 ግራም ስኳር = 1 የሻይ ማንኪያ ስኳር። ለምን ይሄ አስፈላጊ ሆነ? ምክንያቱም በፋብሪካ በተዘጋጁ ምግቦች ውስጥ ያለው ስኳር እንደ ፍራፍሬ ካሉ ተፈጥሯዊ ነገሮች የሚገኝ ሳይሆን "ፈጣን ስኳር" በመሆኑ ነው። በፋብሪካ የሚጨመር ስኳር በውስጡ ምንም አይነት ቃጫ (Fiber) ስለሌለው፣ እንደተመገብነው በቀጥታ ወደ ደም በመግባት የስኳር መጠንን በድንገት ያንራል። ለምሳሌ የምትበሉት አንድ ትንሽ እርጎ 20 ግራም ስኳር ካለው ፤ በአንድ ጊዜ 5 የሻይ ማንኪያ ስኳር እየበላችሁ ነው ማለት ነው። ይህም ጣፊያዎ (Pancreas) ድንገት ለሚመጣበት ከፍተኛ ስኳር ተብሎ ያልተዘጋጀ ኢንሱሊን እንዲያመርት በማስገደድ ለከፍተኛ ድካም እና ለኢንሱሊን መቋቋም (Insulin Resistance) ይዳርጋል። ለዚህም በማሸጊያው ላይ 4 ግራም ስኳር ካዩና በይዘቱ (Ingredients) ዝርዝር ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት ቃላት ከመጀመሪያዎቹ ሶስት ዝርዝሮች ውስጥ ከሉ ፤ ያ ምግብ ለጤናዎ ምንም ፋይዳ የሌለውና ለስኳር ህመም ተጋላጭ የሚያደርግ መሆኑን ይረዱ። እነኝህን ካዩ ከመግዛት ቢቆጠቡ ይመከራል! ከፍርሃት ወደ ግንዛቤ የስኳር ህመም በአንድ ማንኪያ ስኳር የሚመጣ ሳይሆን የረጅም ጊዜ የአኗኗር ዘይቤ እና የሰውነት ኡደት መዛባት ውጤት ነው። ስኳርን ማቆም ትልቅ እርምጃ ነው፤ ነገር ግን መፍትሄው እዛ ላይ አያበቃም። እውነተኛ ጥበቃ የሚመጣው ሰውነታችንን በማዳመጥ፣ ፋይበር (ቃጫ) ያላቸውን እንደ እንጀራ እና ጥራጥሬ ያሉ ምግቦችን በማዘውተር እና እንቅስቃሴ በማድረግ ነው። ጤና በአንድ ውሳኔ የሚገነባ ሳይሆን፣ በየቀኑ በምናደርጋቸው ጥቃቅን ምርጫዎች ድምር ውጤት የሚገኝ ስጦታ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ስኳርን ብቻ ሳይሆን አኗኗርዎን ይቀይሩ!

  • ቤተሰብዎን ከአየር ብክለት እንዴት ይጠብቃሉ?

    አዲስ አበባ ነቅታለች! እንደወትሮው ሁሉ የትራፊክ ጫጫታው ከተማዋን ሞልቶታል። የሞተሮች ድምፅ ይነሳል፤ የመኪና ጥሩምባዎች በህንፃዎች መካከል ይስተጋባሉ። ሰዎች ወደ ስራ፤ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ይጣደፋሉ። ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ከፍተው ደንበኛ ይጠብቃሉ። ሁሉም ነገር የተለመደ ይመስላል። ሆኖም ግን አንድ ችላ የሚባል ስጋት አለ.... በእያንዳንዱ ትንፋሻችን ውስጥ በዝምታ የሚገባ ጠላት እርሱም የአየር ብክለት ነው። ይህ ጠላት ወዲያውኑ አያስደነግጥም። ነገር ግን ቀስ እያለ በጤናችን ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። የሚያስደነግጠው እውነታ ግን ይሄ ነው፦ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2021 ብቻ በአየር ብክለት ምክንያት ከ 76,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል። በተለይም እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት፤ የአየር ብክለት ከምግብ እጥረት ቀጥሎ ዋነኛው የሞት መንስኤ ነው። እናስ በቀላሉ የምንተነፍሰው አየር፤ በዝምታ ህይወታችንን እያሳጠረው ይሆን? ይሄ ጉዳይ "ለነገ" የሚባል አይደለም፤ ዛሬውኑ ልናስብበት የሚገባ የህልውና ጉዳይ ነው። 🏙️ የማይታየው የከተማ እውነታ እንደ አለም ጤና ድርጅት (WHO) መረጃ፤ የአየር ብክለት የሚፈጠረው ከተሽከርካሪ ጭስ፣ ከፋብሪካዎች እና ከከሰል ወይም ከቆሻሻ መቃጠል በሚወጡ መርዛማ ቁሶች ነው። አደገኛ የሚያደርገው ይዘቱ ብቻ ሳይሆን አለመታየቱ ነው። የአየር ብክለት ከሚያመጡት ውህዶች ውስጥ እጅጉን ጥቃቅን የሆኑ ቅንጣቶች ይገኙበታል። እነዚህ በተለይ መጠናቸው አንድ አንድሚሊየነኛ አከባቢ ያሉት(በተለይ PM2.5 ተብለው የሚጠሩ እጅግ ጥቃቅን ቅንጣቶች) በሰውነታችን የተፈጥሮ መከላከያን በቀላሉ አልፈው ወደ ሳምባ በቀላሉ ይገባሉ። አልፎ ተርፎም ወደ ደም ዝውውር ይገባሉ። እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የነዚህ ቅንጣቶች መጠን ከአለም ጤና ድርጅት የደህንነት መስፈርት ከ4 እስከ 7 እጥፍ ብልጫ እንዳለው ተመዝግቧል። 🫁 የአየር ብክለት በሰውነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የመተንፈሻ አካላት የዚህ ስውር ጥቃት የመጀመሪያ ሰለባዎች ናቸው። ለተበከለ አየር መጋለጥ የአስም በሽታን ያባብሳል፤ ለከባድ የሳምባ መቆጣት (Bronchitis) ያጋልጣል እንዲሁም የሳምባን ኦክስጅን የመቀበል አቅም በእጅጉ ያዳክማል። ነገር ግን ጉዳቱ እዚህ ላይ አያበቃም። ረጅም ጊዜ ለብክለት መጋለጥ ከልብ እና የደም ዝውውር በሽታዎች፣ ከደም ግፊት እና ከስትሮክ (Stroke) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ። ሳይንሳዊ እውነታው እንደሚጠቁመው፤ ጥቃቅን የብክለት ቅንጣቶች ወደ ደም ዝውውር በመግባት የደም ቧንቧዎችን ያጠባሉ። ይህም ልብን ለከፍተኛ ጫና ይዳርገዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአዲስ አበባ ከተማዋ የጤና ጣቢያዎች የሚመዘገቡ የሳምባ ምች ታካሚዎች ቁጥር በአምስት ዓመት ውስጥ ብቻ ከ500 ወደ 29,000 በላይ ማደጉ ተመዝግቧል። ይህ አስገራሚ ጭማሪ ከከተማዋ የአየር ብክለት መጠን መጨመር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአየር ውስጥ የጥቃቅን ቅንጣቶች መጠን በጨመረ ቁጥር (በተለይ መጠናቸው ከ2.5 ማይክሮሜትር በታች) ፤ በድንገተኛ ክፍል የሚታከሙ የልብ ህመምተኞች ቁጥርም አብሮ ይጨምራል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በሲጋራ ማጨስ የማያውቁ ሰዎችን ጨምሮ፤ በሳምባ መጥበብና መዘጋት (COPD) የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። ይህ ማለት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ስንጓዝ የምንተነፍሰው አየር፤ በውስጣችን የማይታይ የጤና ቀውስ እየፈጠረ ነው ማለት ነው። እያንዳንዱ ትንፋሽ ሳምባችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም ጭምር አደጋ ላይ እየጣለው ይገኛል። 🌍 የአየር ብክለት ምንጮች ምንድን ናቸው? የአዲስ አበባን አየር የሚበክሉ ምክንያቶች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም፤ በዋናነት ግን የሚከተሉት አምስት ዋነኛ መንስኤዎች እንመለከታለን። 1. አሮጌ ተሽከርካሪዎች "ወረራ" በከተማ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች መካከል ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑት የሚተፉት ጥቁር ጪስ ከዘመናዊ መኪኖች በብዙ እጥፍ ይበልጣል። በተለይ በከባድ ጭነት መኪኖችና በአሮጌ ታክሲዎች የሚወጣው የተሽከርካሪ ጪስ (28%) ዋነኛው የአየር መመረዝ ምክንያት እንደሆነ የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ። 2. የቤት ውስጥ የባዮማስ ቃጠሎ (18%) የአየር ብክለት ከቤት ውጭ ብቻ ሳይሆን በቤታችን ውስጥም አለ። አብዛኛው ነዋሪ ለምግብ ማብሰያነት የሚጠቀመው እንጨት፣ ከሰል እና ኩበት ከፍተኛ የሆነ መርዛማ ጭስ ይፈጥራሉ። በተለይ ደካማ የአየር ዝውውር ባለባቸው ቤቶች ውስጥ ምግብ ማብሰል እና እንጀራ መጋገር የቤት ውስጥ አየርን እጅጉን እንዲበከል ያደርጉታል። ለዚህም ብዙ እናቶችን ለሳንባ ካንሰር እና ለትንፋሽ ቧንቧ ህመሞች እየዳረገ ይገኛል። በዚህም ዙሪያ የጻፍነውን ጽሁፍ ይመልከቱ። 3. የመንገድና የህንፃ ግንባታ አቧራ (17%) አዲስ አበባ በግንባታ ላይ ያለች ከተማ እንደመሆኗ፤ ያልተጠረጉ መንገዶችና የግንባታ ቦታዎች የሚፈጥሩት አቧራ ሌላኛው የብክለት ምንጭ ነው። መኪኖች ባልተጠረጉ መንገዶች ላይ ሲጓዙ የሚነሳው ደቃቅ ብናኝ በቀጥታ ወደ መተንፈሻ አካላችን በመግባት ሳንባን ያቆስላል። 4. በክፍት ቆሻሻ ማቃጠል ቆሻሻን በሜዳ ላይ የማቃጠል ልምድ ፤ በተለይም ፕላስቲኮችንና ጎማዎችን ማቃጠል እጅግ መርዛማ የሆኑ ኬሚካሎችን ወደ አየር ይለቀቃል። እንደ "ህዳር ሲታጠን" ያሉ ባህላዊ ድርጊቶች በአንድ ጀምበር የከተማዋን የአየር ብክለት መጠን እንዲጨምር ሊያድርጉ ይችላሉ። 5. የኢንዱስትሪ ልቀቶች ፋብሪካዎች (ለምሳሌ የጨርቃጨርቅ፣ የሲሚንቶና የምግብ ማቀነባበሪያዎች) ለአየር ብክለት የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚለቁት ሰልፈር ዳይኦክሳይድ እና ናይትሮጅን ኦክሳይድ የአየሩን ጥራት ይበልጥ ያበላሹታል። በይበልጥ ተጎጂ ማነው? ብክለቱ ሁሉንም ቢነካም፤ በስራ መደባቸው የተነሳ በይበልጥ ተጋላጭ ነት ያላቸው አሉ። ለምሳሌ፦ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች፦ ቀኑን ሙሉ በመኪና ጪስና በአቧራ ታፍነው የሚውሉ እናቶችና ወጣቶች። አሽከርካሪዎችና ትራፊክ ፖሊሶች፦ በትራፊክ መጨናነቅ ውስጥ ረጅም ሰዓት የሚያሳልፉና አየሩን በቀጥታ የሚጋፈጡ የከተማዋ ዘብ ጠባቂዎች። 🏠 እርስዎ ምን ማድረግ ይቻላሉ? የአየር ብክለትን ለመከላከል የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልገው ፤ ሳይታለም የተፈታ ነው። ሆኖም ግን እርስዎ እንደ ግለሰብ በቤትዎ የሚከተሉትን ቢያደርጉ ተጋላጭነትዎን መቀነስ ይችላሉ። በአከባቢዎ ትራፊክ የሚበዛበት ፤ብዙ ጎረቤቶዎችዎ ምግብ የሚያበስሉበት ሰዓታት ላይ መስኮቶችውን ይዝጉ። ይህም የአየር ብክለቱ ወደቤትዎ እንዳይገባ ይከላከልልዎታል። ግድ ካልሆነብዎ በቀር በእግር ሲጓዙ ከዋና ዋና መንገዶች የቻሉትን ያህል ቢርቁ ፤ ለብክለት የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል። ቤትዎ ውስጥ እንጨት ወይም ከሰል የሚጠቀሙ ከሆነ ፤ የጭስ ማውጫ መጠቀም ወይም ማብሰያ ቤትዎ በቂ አየር እንዲያገኝ ያድርጉ። በተለይ በተለይ የህፃናት የመተንፈሻ አካላት ገና በማደግ ላይ ስለሆኑ ለብክለት እጅጉን ተጋላጭ ነው። ገና በልጅነት ለብክለት መጋለጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የሳምባ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም ልጆችዎ ከፍተኛ ብክለት ባለባቸው ሰዓታት ከቤት ባይወጡና ንጹህ አየር ባለባቸው ቦታዎች ቢጫወቱ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። የአመለካከት ለውጥ ያስፈልግዎታል! ምናልባትም ከሁሉ በላይ አስፈላጊው ለውጥ የተግባር ብቻ ሳይሆን የሐሳብም ጭምር ነው። የአየር ብክለት ብዙ ጊዜ ከቁጥጥርዎ ውጭ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ነገር ግን የሕዝብ ጤና ሳይንስ በተለየ መንገድ ይተረጉመዋል፦ የአየር ብክለት መሻሻል እንደሚችል የጤና ስጋት (Modifiable Risk Factor) እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ማለት ግለሰቦች የብክለቱን ምንጭ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይችሉም፤ ግንዛቤ በመያዝ ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እና ጤናቸውን መጠበቅ ይችላሉ ማለት ነው። አዎ! ከእርሶዎ ግንዛቤ ጋር ተያይዞ ፤ የተሻሉ የከተማ ፖሊሲዎች ፤ ንፁህ የትራንስፖርት ሥርዓቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ደንቦች መኖራቸው ያስፈልጋል። እርስዎ ግን እስከዛ የድርሻዎን ይወጡ። ጤናዎን ይጠብቁ!

  • ሙዚቃ እና ጤና

    ሙዚቃ የሚወዱ ሰዎችን “ለምን ትወዳላችሁ?” ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? ምናልባት መልሱ በቃላት የሚገለጽ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ገና አፉን ያልፈታ ሕፃን ልጅ የሚመስጥ ዜማ ሲሰማ በደስታ ሲወዛወዝ ካስተዋሉ፣ ነገሩ ከፍላጎት በላይ የሆነ የተፈጥሮ ምስጢር እንዳለው ይረዱታል። ለመሆኑ ይህ ስሜት ከየት የመጣ ነው? በመንገድ ሲጓዙ መኪናዎች ጩኸትና በሰዎች ጨዋታ ፣ በእለት ተእለት ሁካታ መካከል፣ ከሩቅ የሚሰማ የሙዚቃ ድምጽ ድንገት ጆርዎ ውስጥ ጥልቅ ይላል። በዚያች ቅጽበት ሳይታወቅዎት የልብ ትርታዎ ይረጋጋል፣ ትከሻዎ ይላላል፣ እናም አንድ ዓይነት የሰላም ስሜት በሰውነትዎ ላይ ይሰፍናል። አንዳንዴም ውስጥዎ ብዙ ስሜትን ይቀሰቅሳል። ይህ ዝም ብሎ የፈጠራ “ስሜት” ብቻ እንዳይመስልዎት። ይህ ከጆሮዎ አልፎ በጠቅላላው የባዮሎጂ ሥርዓትዎ ውስጥ የሚከናወን ውስብስብ ሳይንሳዊ ሂደት ነው። እስቲ በጥልቀት እንመልከተው። ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው የተቀናጁ ድምጾች (Rhythm and Melody) በሰውነታችን ላይ ስለሚያመጡት ቀጥተኛ ባዮሎጂያዊ ለውጥ እንጂ፣ ዓለማዊ ሙዚቃን ወይም መንፈሳዊ መዝሙርን ለመደገፍ ወይም ለመቃወም የቀረበ አይደለም። አእምሮዎ ለሙዚቃ ለምን "ይጓጓል"? የሙዚቃ ጉዞ የሚጀምረው በጆሮዎ ቢሆንም፣ መጨረሻው ግን እዚያ አይደለም። የዜማው ድምፅ የአንጎልዎ የድምፅ መቀበያ ክፍል (Auditory Cortex) እንደደረሰ፣ በፍጥነት ወደ ቀሪው የአንጎልዎ ክፍል በፍጥነት ይሰራጫል። ታድያ የሚወዱትን የሙዚቃ ምት ሲሰሙ የአንጎልዎ የደስታ ማዕከል (Ventral Striatal Network) በድንገት በ "ዶፓሚን ማዕበል" ይሞላል። ዶፓሚን ማለት አእምሯችን በስኬታችን ወቅት የሚያመርተው መልካም ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ የተፈጥሮ ሽልማት ነው። ኔቸር ኒውሮሳይንስ የተባለው ታዋቂ የሳይንስ መጽሔት የተለቀቀ አንድ ጥናትዊ ጽሁፍ ሙዚቃ እንደ ምግብ ወይም እንደ ጥልቅ የፍቅር ቅርርብ ያሉ ለሰው ልጅ መትረፍ (Survival) አስፈላጊ የሆኑ ስሜቶች የሚመነጩበትን ያአእምሮ ክፍል ያነቃቃክ። ይህም ሙዚቃ ለሰው ልጅ ዝም ብሎ መዝናኛ ሳይሆን፣ ለአእምሮአችን መልካም ፋይዳ ያለው አስፈላጊው ግብዓት መሆኑን ይጠቁማል። ከዚህም በላይ፣ ሙዚቃ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የጭንቀት ሆርሞን (Cortisol) እስከ 25% ድረስ የመቀነስ አቅም አለው። በዚህ ፈጣንና ውጥረት በበዛበት ዓለም ውስጥ፣ ሙዚቃ ለአእምሯችን እንደ "ማደሻ ቁልፍ" (Reset Button) በመሆን ውስጣዊ ሰላማችንን ይመልስልናል። ሙዚቃ የልብ ትርታን ይቃኝ ይሆን? ለመሆኑ አንድ ዜማ እንደ ማረጋጊያ መድኃኒት ሊያገለግል ይችላል? ለብዙዎቻችን ጥያቄው የሚከብድ ቢመስልም፣ የሕክምና ሳይንስ ግን ምላሹን በአጭር ቃል “አዎ!” ብሎታል። ጃማ ኢንተርናል ሜዲሲን (JAMA Internal Medicine) የተባለው የሕክምና መጽሔት ባወጣው ጥናት መሠረት፣ በደቂቃ ከ60 እስከ 80 የሚመታ (BPM) ሙዚቃ በአካላችን ላይ አስደናቂ ተጽዕኖ አለው። ይህ የሙዚቃ ምት ካረፈ የሰው ልጅ የልብ ትርታ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ፣ ልባችን ራሱን ከዜማው ጋር ለማመሳሰል ይሞክራል። ይህ “ተፈጥሯዊ ቅኝት” በሰውነታችን ውስጥ የሚከተሉትን ለውጦች ያመጣል፦ የደም ግፊት መረጋጋት፦ የሙዚቃው ምት የላይኛውን የደም ግፊት (Systolic) ዝቅ እንዲል በማድረግ የደም ሥሮችን ውጥረት ያላላል። የልብ ምት ስምምነት፦ ልብዎ ቃል በቃል ከሚሰሙት ዜማ ጋር አብሮ ለመራመድ ይሞክራል፤ ሙዚቃው ሲረጋጋ ልብዎም አብሮ ይረጋጋል። ውጤቱ፦ ይህ ሂደት በልብ ላይ የሚደርሰውን አላስፈላጊ ጫና ይቀንሳል። ይህም በተለይ የደም ግፊት ላለባቸው ወይም ከልብ ሕመም ለሚያገግሙ ወገኖቻችን ሙዚቃን ታማኝ የጤና አጋር ያደርገዋል። ባጭሩ፣ ሙዚቃ ለጆሮ የሚቀርብ ድምፅ ብቻ ሳይሆን፣ ለልባችን መልካም ጠቀሜታ ያለው ነው ማለት ነው። ተፈጥሯዊ የህመም ማስታገሻ በሕክምና ሳይንስ ውስጥ ካሉት እጅግ አስደናቂ ግኝቶች አንዱ “በሙዚቃ የሚመጣ የህመም ማስታገሻ” (Music-Induced Analgesia) ነው። ይህ ዝም ብሎ የሰዎች ግምት አይደለም፤ ዘ ላንሴት (The Lancet) የተባለው ታዋቂ የሕክምና መጽሔት ከ70 በላይ ጥናቶችን አጠቃሎ ባቀረበው ማስረጃ መሠረት፣ ከቀዶ ጥገና በፊትም ሆነ በኋላ ሙዚቃ ያዳመጡ ታካሚዎች ከሌሎቹ በበለጠ የህመም ስሜታቸው እንደቀነሰና ፈጣን ማገገም እንዳሳዩ አረጋግጧል። ለመሆኑ ሙዚቃ እንዴት ነው ህመምን የሚያታግሰው? ምስጢሩ “የህመም ቁጥጥር በር” (Gate Control Theory) በሚባለው ሳይንሳዊ ሂደት ውስጥ ይገኛል። አእምሯችን ወደ እሱ የሚመጡትን መረጃዎች የሚያስተናግድበት ውስን አቅም አለው። የሚመስጥ ዜማ ስንሰማ፣ አእምሯችን በሚያስደስት የድምፅ ማነቃቂያ ይሞላል። በዚህ ጊዜ ህመምን ወደ አእምሮ የሚወስዱት የነርቭ መንገዶች “ይጨናነቃሉ”። የዚህን ጊዜ የትኩረት ሽሚያ ይኖራል። አእምሮዎም በህመሙ ፋንታ በዜማው ላይ እንዲያተኩር ይገደዳል። ደስ የሚለው ድምፅ የአንጎልዎን የትኩረት በር ስለሚቆጣጠረው፣ የህመም ምልክቶች በቀላሉ ሰርገው መግባት አይችሉም። ለዚህም ለተለያየ ህመም ጊዜ የሚወዱትን ሙዚቃ መክፈት የህመም ማስታገሻ የመውሰድ ፍላጎትዎን በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስልዎት ይችላል። ሙዚቃ ያለ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት፣ አእምሮዎ ህመምን በራሱ መንገድ እንዲቋቋም የሚያደርግ ተፈጥሯዊ ስጦታ ነው። የትዝታ ካዝና ሙዚቃ በሕክምና ረገድ ትልቁን ተአምር የሚሠራው እንደ አልዛይመር ባሉ የመርሳት በሽታዎች ላይ ነው። እስቲ ያስቡት...አንድ የሚወዱት ቤተሰብዎ ፤ በጊዜው ውስጥ ማንነትዎንና የቆዩ ትዝታዎችን ሲረሳ ማየት እንዴት ይከብዳል?ለአንዳንዶችም የሚሰብር ነው። ሆኖም ሳይንስ አንድ ተስፋ ሰጪ ምስጢር ይነግረናል! የሰው ልጅ ትዝታዎች ሁሉ ቢጠፉም፣ የሙዚቃ ትዝታ ግን በአእምሮአችን ውስጥ “ባለቤት” የለውም። የነርቭ ሳይንስ መጽሐፍት እንደሚያረጋግጡት፣ የሙዚቃ ትዝታ የሚቀመጠው “ሂፖካምፓስ” (Hippocampus) በሚባለውና በመርሳት በሽታ የመጨረሻ ደረጃ ላይ በሚጠቁት የአንጎል ክፍሎች ውስጥ ነው። ይህም ሁለት ታላላቅ መልካም ጎኖች አሉት፦ ድንገተኛው መንቃት፦ ለብዙ ጊዜ መናገር ያልቻሉ ወይም ለአካባቢያቸው ምላሽ መስጠት ያቆሙ አባቶችና እናቶች፣ የልጅነት ዘፈኖቻቸውን ወይም የድሮ መዝሙሮቻቸውን ሲሰሙ ድንገት አብረው መዘመር ሲጀምሩ ይታያሉ። ሙዚቃ በመርሳት በሽታ የተዘጋውን የአእምሮ በር የሚከፍት ብቸኛ ቁልፍ ይሆን? የአእምሮ ጥንካሬ፦ አንድ የሙዚቃ መሣሪያ መለማመድ ወይም በዝማሬ ውስጥ መሳተፍ የአንጎል ራሱን የማደስ ብቃት (Neural Plasticity) ያሳድጋል። ይህም እርጅና በአእምሯችን ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚችል ጠንካራና “ወጣት” አእምሮ እንዲኖረን ያደርጋል። በአጭሩ፣ ዜማዎች በአእምሮአችን ውስጥ የታተሙ የትዝታ አሻራዎች ናቸው፤ ዕድሜም ሆነ በሽታ በቀላሉ ሊያጠፋቸው የማይችሉ ታማኝ ምስክሮች ይሆናሉ። ሙዚቃ ለበሽታ መከላከል አቅም ሙዚቃ በእርግጥ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም ሊያጠናክር ይችላል? ሳይንሱ ያለ ምንም ማመንታት ምላሹን "አዎ" ብሎታል። በክሊኒካዊ ጥናቶች እንደተረጋገጠው፣ አንድ ሰው በሙዚቃ ውስጥ ሲቆይ ሰውነቱ ቫይረሶችን የሚከላከሉትን እንደ "ሳይቶኪንስ" (Cytokines) እና "ኢሚውኖግሎቡሊን ኤ" (IgA) ያሉ ጋሻዎችን በከፍተኛ መጠን ማምረት ይጀምራል። ኢሚውኖግሎቡሊን ኤ በሰውነታችን ውስጥ ባሉ እንደ አፍና አፍንጫ ባሉ አካላት ውስጥ የሚገኝ የመጀመሪያው የሰውነት መከላከያ መስመር ነው። ይህ ፕሮቲን ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነታችን እንዳይገቡ “የድንበር ጠባቂ” ሆኖ ያገለግላል። ክሊኒካዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ለ50 ደቂቃ ብቻ የሚያረጋጋ ሙዚቃ ማዳመጥ የዚህን ተከላካይ ፕሮቲን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። የተፈጥሮ ኮማንዶዎች (Natural Killer Cells) መጠንንም ይጨምራል። እነዚህ ህዋሳት በደማችን ውስጥ የሚዘዋወሩና በቫይረስ የተጠቁ ሴሎችን ወይም የካንሰር ሴሎችን ለይተው የሚያጠቁ “የሰውነት ወታደሮች” ናቸው። ሙዚቃ እነዚህ ሴሎች ይበልጥ ንቁና ቀልጣፋ እንዲሆኑ በማድረግ የሰውነትን የማጥቃት አቅም ያሳድጋል። ከዚህም ባሻገር ሙዚቃ የሰውነትን ሚዛን በመጠበቅ፣ አላስፈላጊ የሰውነት እብጠትን (Chronic Inflammation) የሚቀንሱ ሳይቶኪኖችን እንዲመረቱ ያደርጋል። ይህ በተለይ ከጭንቀት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል ወሳኝ ነው። እንዳይሳሳቱ ሙዚቃ ሊቅ አያደርግም! ስለ ሙዚቃ አቅም ስናወራ ብዙ ጊዜ የሚነሳ አንድ ዝነኛ ተረት አለ፤ እርሱም "የሞዛርት ውጤት" (The Mozart Effect) ይባላል። ክላሲካል ሙዚቃን ማዳመጥ ብቻውን ሕፃናትን ወደ ሊቅነት ይቀይራል የሚለው ይሄ አስተሳሰብ ለዓመታት እንደ ትልቅ ግኝት ሲነገር ቆይቷል። ነገር ግን ሳይንሳዊ ሐቁን መረዳት ለጤናማ አጠቃቀም ወሳኝ ነው። በታዋቂ የሳይንስ መጽሔቶች የወጡ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፣ ሙዚቃ የአንድን ሰው የአእምሮ ብቃት (IQ) በቋሚነት የመጨመር "አስማታዊ" ኃይል የለውም። ይልቁንም ሙዚቃ የሚያደርገው አእምሮን ወደ ተሻለ የንቃት ደረጃ ማምጣት ነው። ሙዚቃ አእምሮን ወደ ተሻለ ዝግጁነትና ደስታ ስለሚያመጣው፣ ችግሮችን የመፍታትና የማሰብ ብቃታችን ለተወሰነ ጊዜ ይጨምራል። ይህም ለአጭር ጊዜ መሆኑ መስተዋል ይኖርበታል። እንዲሁም ሙዚቃ አእምሯችን ምስሎችን እንዲያቀናጅና ውስብስብ ነገሮችን እንዲረዳ መንገድ ይከፍታል። ስለዚህ ሙዚቃ ሰውን "ሊቅ" አያደርግም፤ ነገር ግን አእምሮ ያለውን የላቀ ብቃት እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል። ማወቅ ያለብዎት አራቱ ዋና ጥያቄዎች ጥያቄ 1፦ የሙዚቃው ዓይነት (Genre) በፈውሱ ላይ ተጽዕኖ አለው? መልስ፦ ሳይንሱ የሚነግረን ትልቁ ሚስጥር "የግል ምርጫ" ወሳኝ መሆኑን ነው። የሕክምናው ጥቅሙ የሚገኘው ሙዚቃው በውስጣችሁ በሚፈጥረው ጥልቅ ስሜት ነው። ክላሲካል ሙዚቃ በሳይንሳዊ ጥናቶች በብዛት ቢጠቀስም፣ እርስዎ የሚወዱት ኢትዮ-ጃዝ (Ethio-Jazz) ከሆነ፣ አእምሮዎ ዶፓሚን የሚያመነጨው በዚያው ሙዚቃ ነው። ስለዚህ ለእርስዎ የሚስማማውን ይምረጡ። ጥያቄ 2፦ ሙዚቃ ለእንቅልፍ ጥራት አስተዋጽኦ ያደርጋል? መልስ፦ አዎ፣ ያውም በከፍተኛ ሁኔታ! ከመተኛትዎ በፊት ለ45 ደቂቃ ያህል ረጋ ያለ ሙዚቃ ማዳመጥ አእምሮዎ በፍጥነት ወደ "አልፋ" እና "ዴልታ" ሞገዶች እንዲሸጋገር ያደርገዋል። ይህ ሂደት ወደ ጥልቅ እንቅልፍ እንዲገቡና ጠዋት ሲነቁም ሙሉ እረፍት አግኝተው እንዲነሱ ይረዳዎታል። ጥያቄ 3፦ ሙዚቃን ማዳመጥ ይሻላል ወይስ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት? መልስ፦ ሁለቱም የየራሳቸው በረከት አላቸው። ማዳመጥ ለጭንቀት መቀነስና ለህመም ማስታገሻነት እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት እንቅስቃሴ ስላለው ለአእምሮ እንደ ስፖርትነት ያገለግላል። መሣሪያ መጫወት ከሙዚቃው ባሻገር ፤ የማሰብን ነገሮችን የማቀናጀትንና ትኩረትን የመሰብሰብ ብቃትን (Executive Function) በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል። ጥያቄ 4፦ ከፍተኛ ድምፅ ያለው ሙዚቃ በጤና ላይ ጉዳት አለው? መልስ፦ አዎ! ከ85 ዴሲቤል በላይ ለሆነ ድምፅ ለረጅም ጊዜ መጋለጥ ጆሮ ላይ ጉዳት አለው። ታምቡር ላይ ካለው አሉታዊ ተጽእኖ ባሻገር ፤ ጆሮዎት ላይ የሚጮህ ድምጽ እንዲሰማዎ (Tinnitus) ያደርጋል። ዘላቂ የመስማት ችግርም ሊያስከትል ይችላል። ታድያ ግን ያስተውሉ! ሙዚቃ የልብ ትርታን ማረጋጋት ፤ ህመምን የማስታገስ እና በሽታ የመከላከያ አቅምን የማጠናከር ልዩ አቅም ቢኖረውም ፤ አጠቃቀምዎ በልክ መሆን አለበት። አልያ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል!

  • ልጅዎን ያመመው ቀላል ሕመም ነው ወይስ ሌላ?

    ትላንት በደስታ ሲቦርቅ፤ ሳቁ ቤቱን ሲሞላው የዋለ ልጅ፤ ዛሬ ጠዋት ግን ከአልጋው መነሳት አቅቶት ይደፋል። ከሰዓት በኋላ ደረቅ ሳል ይጀምረዋል። ምሽት ላይ ደግሞ ተቅማጥ ይጨመርበታል። ይህ ትዕይንት በብዙ ቤቶች የተለመደ ነው። እንዲህ ያሉ ድንገተኛ መታመሞች ሲከሰቱ፤ ቤተሰብ "ምን ይሻላል?" ብሎ መጨነቁ አይቀሬ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ ምክሮች ከያሉበት ይዘንባሉ፦ “ፈሳሽ አጠጡትና ይተኛው፤ ይለቀዋል” “ብርድ እንዳይገባው ደርብቡለት። ሙቅ ነገር ስጡት።” “ትንሽ ታሞ ነው። ነገ ይነሳል...” በአብዛኛው ሁኔታዎች ይህ የቤት ውስጥ ጥበብ ይሰራል። ህፃኑ አገግሞ ወደ ጨዋታው ይመለሳል፤ ህይወትም በለመደችው መስመር ትቀጥላለች። ነገር ግን... ነገሮች ሁልጊዜ እንዲህ ቀላል አይሆኑም። አንዳንዴ ያ ቀላል የመሰለው ሳል ሳይታወቅ ወደ ፈጣንና አጣዳፊ አተነፋፈስ ይቀየራል። ያ ተራ ተቅማጥ ሰውነትን የሚያፈዝ አደገኛ የፈሳሽ እጥረት (Dehydration) ይወልዳል። "ትንሽ ትኩሳት ነው" ያልነው ጉዳይ ህፃኑን ራሱን እስከማሳት ሊያደርሰው ይችላል። በእነዚህ ወሳኝ ሰከንዶች ውስጥ በልበ ሙሉነት የምንሰጣቸው የቤት ውስጥ ምክሮች ብቻቸውን በቂ አይደሉም። እንዲያውም አንዳንዴ በህይወትና በሞት መካከል ያለውን ጠባብ መስመር ሊያጠፉት ይችላሉ። ታዲያ ልዩነቱን እንዴት እንወቀው? ይህ ጥያቄ ስለ ፍርሃት ሳይሆን ስለ ንቃት ነው። "አልጋው ላይ ይዋል" በሚባለው ህመም እና "አሁኑኑ ሆስፒታል!" በሚያስባለው አደገኛ ምልክት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል። የልጅዎ የነገ ሳቅ የሚመሰረተው ይህንን በመለየትዎ ላይ ተመስርቶ ነው። የልጅነት ሕመሞች ተፈጥሮአዊነት የልጅነት ሕመም እንግዳ ነገር አይደለም፤ እንዲያውም የማደግ አንዱ አካል ነው። የሕክምና መጽሐፍት እንደሚነግሩን፤ ትናንሽ ልጆች በዓመት ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት በመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ሊያጠቁ ይችላሉ። ይህ ሂደት በራሱ አንድ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፤ የበሽታ መከላከል አቅማቸው ገና በማደግ ላይ ስለሆነ፤ ሰውነታቸው አዳዲስ ረቂቅ ተህዋሲያንን መለየትና መቋቋም እየተለማመደበት ያለ መንገድ ነው። ልጅዎ ከአካባቢው ጋር በተገናኘ ቁጥር የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል። እያንዳንዱ ትኩሳት፤ እያንዳንዱ ሳል፤ እና እያንዳንዱ ጉንፋን የሰውነቱ የመከላከያ ሰራዊት እየተገነባ መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። ስለዚህ ትኩሳት፣ ሳል ፣እና ተቅማጥ ያልተለመዱ ክስተቶች አይደሉም፤ የሚጠበቁ ናቸው። እንዲያውም አብዛኛዎቹ እነዚህ ሕመሞች ቀለል ያሉና በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥንቃቄ የሚሻገሩ ናቸው። ሆኖም ግን፤ ይህ “ተራነት” አታላይ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም አደገኛና ከባድ ሕመሞች መጀመሪያ ላይ ማንነታቸውን በግልጽ አያሳውቁም። እንደ ቀላል ህመም መስለው፤ በኋላ ላይ እየተባባሱ ሊመጡ ይችላሉ። ውስጣዊ አጥፊነታቸውን በቀላል ምልክቶች ጀርባ ሊደበቅ ይችላል። ምልክቶቻቸው ተመሳሳይ ሲሆኑ—ግን ሕመሙ ሲለያይ ለወላጆች ትልቁ ፈተና ይሄ ነው። ሕመሞች መጀመሪያ “ተመሳሳይ ፊት” ይዘው ብቅ ማለታቸው ያሳስባቸዋል። ቀላል ጉንፋን እና ሳንባ ምች (Pneumonia) መጀመሪያ ተመሳሳይ ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ። ሁለቱም ትኩሳት ይላቸዋል፤ ያስላቸዋል፤ ድካምም ይታይባቸዋል። በተመሳሳይ ተራ የሆድ መረበሽ እና ለሕይወት አስጊ የሆነ ተቅማጥ መነሻቸው አንድ ዓይነት ሊሆን ይችላል። ይህም የሆነው ሰውነታችን ጉዳቱን መግለጽ የሚችልበት ምልክቶች የተገደቡ ስለሆኑ ነው። እንደምሳሌ ትኩሳት፣ ሕመም መሰማት (pain)፣ ድካም እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ብዙ በሽታዎች ላይ ይስተዋላሉ። በበሽታዎች መሀል ለመለየት ግን የእነዚህ ምልክቶች መኖር ብቻ ሳይሆን፤ ከሰዓት ወደ ሰዓት የሚያሳዩት የባሕሪ ለውጥና አብረዋቸው ያሉ ምልክቶችን ማየት ያስፈልጋል። እውነተኛውን ታሪክ የሚነግረን ያ የለውጥ ሂደት ነው። ትኩሳትን እንደምሳሌ እንውሰድ። ትኩሳት ሰውነት በሽታን እየተከላከለ መሆኑን የሚያሳይ የበሽታ መከላከያ ስርአታችን የመታገል ምልክት ነው። በቫይረስ የሚመጡ ሕመሞች ላይ ትኩሳት ቢኖርም፣ ሰውነት ራሱ ሊያስወግደው ይችላል ። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ከትኩሳቱ መጠን (ቁጥር) ባሻገር የልጁ አጠቃላይ ሁኔታ ነው። ትኩሳት ኖሮትም የሚጠጣ፣ የሚጫወትና፣ ንቁ የሆነ ልጅ፤ ትኩሳት ኖሮት ዝልፍልፍ ከሚል ከሚነጫነጭ ወይም ጭልጥ ያለ ዝምታ ውስጥ ከሚሰምጥ ልጅ ጋር ፈጽሞ እኩል አይደለም። ይህ ትኩሳት ያለበት ልጅ የሚኖረው የወባ በሽታ የተስፋፋበት አከባቢ ከሆነ ደግሞ፤ ማንኛውም ትኩሳት እንደ ድንገተኛ አደጋ ታይቶ ወዲያውኑ ምርመራ መደረግ አለበት። ሕመሙ መልክ ሲቀይር አብዛኛዎቹ የተለመዱ ሕመሞች የሚታወቅ ጉዞ አላቸው፦ ምልክቶች ይታያሉ፤ ይበረታሉ ከዚያም ቀስ በቀስ ይሻላሉ። ነገር ግን ያ ሂደት ሲስተጓጎል ትኩረት ይሻል። ለምሳሌ፡ ወደ ፈጣን ወይም አስቸጋሪ አተነፋፈስ የተቀየረ ሳል ከእንግዲህ ተራ ጉንፋን አይደለም። ፈጣን አተነፋፈስ የምንለው ዕድሜያቸው ከ2-11 ወር ለሆኑ ህፃናት በደቂቃ 50 እና ከዚያ በላይ ሲሆን፤ ከ1 እስከ 5 ዓመት ለሆኑ ደግሞ በደቂቃ 40 እና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው። ከ 6 እስከ 12 እድሜ ላሉ ህጻናት ደግሞ ከ30 በላይ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር (IMNCI) መመሪያዎች፤ አንድ ሕመም ከተለመደው መስመር ወጥቶ ወደ አደገኛ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳዩ "ቀይ መስመሮችን" በግልጽ ያስቀምጣሉ። እነዚህ ምልክቶች የታዩበት ሕፃን በቤት ውስጥ ሊታከም የሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም፤ ይልቁንም አስቸኳይ የሕክምና ዕርዳታ ይሻል። ልጅዎ ላይ የሚከተሉትን ምልክቶች ካዩ በሽታው ቀላል እንዳልሆነ ተረድተው ሳይዘገዩ እርምጃ ይውሰዱ፦ የአተነፋፈስ ለውጥ፦ መተንፈስ መቸገር (የደረት መጎዝጎዝ) ወይም ያልተለመደ ፈጣን አተነፋፈስ። የቆየ ትኩሳት፦ ዕድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች ትኩሳቱ ከ1 ቀን በላይ፤ ከ2 ዓመት በላይ ለሆኑ ደግሞ ከ2 ቀናት በላይ ከቆየ። ከፍተኛ ሙቀት፦ የሙቀት መጠኑ ከ38.5 ዲግሪ ሴልሺየስ (በብብት ሲለካ) በላይ ከሆነ። የአቅም ማጣት፦ ጡት መጥባት ወይም ምግብ መውሰድ በፍጹም አለመቻል። የማያቋርጥ ትውከት፦ የወሰዱትን ማንኛውንም ነገር ወዲያውኑ መመለስ። የንቃት መቀነስ፦ ከመጠን ያለፈ እንቅልፍ ወይም በፍጹም መንቃት አለመቻል። የአንገት መገተር፦ የአንገት መድረቅ ወይም መደደር (Stiff neck) ካለ። መንቀጥቀጥ (Convulsions)፦ ድንገተኛና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የሰውነት መንቀጥቀጥ። አደገኛ የፈሳሽ እጥረት፦ የዓይን መሰርጎድ፣ የከንፈርና የምላስ መድረቅ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ድካም ወይም ዝልፍልፍ ማለት። እነዚህ ምልክቶች ካዩ በሽታው ቀላል አይደልም። መጠበቅ አደጋ አለው። አቅራቢያዎ ያለ የጤና ተቋም ይሂዱ። መዘግየት የሚያስከትለው ጉዳት በሕፃናት ሕክምና ውስጥ "ጊዜ" ቁጥር ብቻ አይደለም፤ የሕይወት መትረፊያ ዕድል እንጂ። አደገኛ ምልክቶች ታይተው ሆስፒታል ለመድረስ የሚባክን እያንዳንዱ ደቂቃ፤ በሕፃኑ ሰውነት ውስጥ ያለውን የሕመም ኃይል ያበረታዋል። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ወደ ሕክምና ለመሄድ የሚዘገዩት በቸልተኝነት ሳይሆን "ይሻለዋል" በሚል ተስፋ ወይም ነገሮችን ባለመረዳት ነው። ሆኖም ይህ መዘግየት ከባድ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። ለምሳሌ፦ የበሽታው መሰራጨት፦ እንደ ሳንባ ምች ያሉ ሕመሞች በሰዓታት ውስጥ ከአንድ የሳንባ ክፍል ወደ ሌላው በመዛመት አተነፋፈስን ሙሉ በሙሉ ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ። የሰውነት መዛል፦ ህፃናት እንደ ትልቅ ሰው መጠባበቂያ ኃይል የላቸውም። ተቅማጥና ትውከት የሚያስከትሉት የፈሳሽ እጥረት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የልብና የኩላሊት ሥራ ላይ ከባድ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ። የሕክምናው መወሳሰብ፦ ቀድሞ ቢደረስ በቀላል መድኃኒት ሊድን የሚችል ሕመም፤ ሲዘገይ ግን ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ወይም የፅኑ ሕክምና ክትትል (ICU) ሊያስፈልገው ይችላል። በሕይወት እና በሞት መካከል ያለው ልዩነት ብዙ ጊዜ ሆስፒታል መድረሳችን ሳይሆን፤ መቼ ደረስን የሚለው ነው። ልጅዎ ላይ ከላይ የተጠቀሱትን አደገኛ ምልክቶች ካዩ፤ "እስቲ ልይ" የሚለው ውሳኔ ለነገ የማይባል የሕይወት መስዋዕትነት እንዳያስከፍልዎት አሁኑኑ እርምጃ ይውሰዱ። ትክክለኛ የቤት ውስጥ እንክብካቤ ምንድነው? ሁሉም የልጅነት ሕመሞች ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል መሄድን ላይጠይቁ ይችላሉ።  እንደውም አንዳንድ ሕመሞች ቀለል ያሉ በመሆናቸው በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥንቃቄ ሊታለፉ ይችላሉ። ምናልባትም በተለያየ ምክንያት አቅራቢያዎ ያለ ጤና ተቋም መሄድ ተቸግረው ሊሆን ይችላል። በእርስዎ ዘንድ ቆራጥ ውሳኔ የሚያስፈልገው የአደጋ ምልክቶችን ለይቶ በማወቅ እንጂ፤ ሁሉንም ሕመም በመፍራት መሆን የለበትም። ልጅዎ ከላይ የጠቀስናቸውን የከፋ አደጋ ምልክት ሳይታይበት ከታመመ፤ የሚከተሉት እርምጃዎችን ቢያደርጉ በፈጣን እንዲያገግም ያግዙታል። ትኩሳት ወይም ተቅማጥ ካለ በቂ ፈሳሽ መስጠት የሕክምናው ቀዳሚ ተግባር ነው። የኦአርኤስ (ORS) ጨው የፈሳሽ እጥረትን በመከላከል ረገድ ሕይወት አዳኝ ነው። በኢትዮጵያ የጤና መመሪያ መሠረት፤ ተቅማጥ ላለባቸው ሕፃናት ከኦአርኤስ ባሻገር የዚንክ ኪኒን መስጠት፤ የሕመሙን ቆይታና ጥንካሬ በእጅጉ ይቀንሳል። ሕፃኑ በሕመም ወቅት የምግብ ፍላጎቱ ቢቀንስም፤ በተደጋጋሚ ትንሽ ትንሽ ምግብ እንዲወስድ ማድረግ ኃይል እንዲያገኝና ማገገሙ እንዲፋጠን ይረዳል። ትኩሳት ካስተዋሉ የሕፃኑን ምቾት ለመጠበቅ እንደ ፓራሴታሞል ያሉ መድኃኒቶችን በሐኪም ወይም በፋርማሲ ባለሙያ በሚታዘዘው ትክክለኛ መጠን መጠቀም ይቻላል። እዚህ ጋር ሊያስተውሉ የሚገባው፦ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ አንቲባዮቲክ (Antibiotics) መጠቀም ጉዳት አለው። ሰውነት ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ጎንዮሽ ጉዳት ባሻገር፤ በሽታውንም ላያክም ይችላል። ለምሳሌ ለቫይረስ ሕመሞች አንቲባዮቲክ ምንም ዓይነት ጠቀሜታ የለውም። እንዲያውም ለወደፊት መድኃኒት የመላመድ (Resistance) ችግርን ሊፈጥር ይችላል። ሁሉንም ነገር የሚቀይረው አንድ ጥያቄ በመጨረሻም፤ ዋናውና ወሳኙ ጥያቄ “ይህ ምን ዓይነት ሕመም ነው?” የሚለው ሳይሆን ይልቁንም፦ “ልጄ እየተሻለው ነው ወይስ እየባሰበት?” የሚለው ነው። ንቁ የሆነ፤ ፈሳሽ የሚወስድና ቀስ በቀስ የሚሻለው ልጅ በቤት ውስጥ ሊከታተሉት ይችላሉ። እየዛለ የሚሄድ፤ ስሜቱ የማይታወቅ ወይም አዳዲስ አሳሳቢ ምልክቶች የታዩበት ልጅ ግን በአስቸኳይ መታየት አለበት። አብዛኛዎቹ የልጅነት ሕመሞች ቀላል ቢሆኑም፤ ጥቂቶቹ በወቅቱ ትኩረት ይሻሉ። የልጅዎ ሕይወት የሚተርፈው በሰዓቱ በሚያደርጉት ውሳኔ ነው። ምልክቶቹን ያስተውሉ። በአፋጣኝ ይወስኑ።

  • በአመጋገብ የስኳር በሽታ ይፈወሳልን?

    “በአመጋገብ የስኳር በሽታዬን ተፈውሷል…” በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይህ ንግግር በኢትዮጵያ እንደ ተስፋ ሰጪ ብስራት ፤ በየማህበራዊ ሚዲያም እንደ ትልቅ ዜና በስፋት እየተሰማ ይገኛል። አንዳንዶች እንደውም "ድህነት ያገኘሁት ፤ እከሌ/እከሊት የተሰኘ/ች የስነምግብ አማካሪ ጋር ሄጄ ነው" ሲሉም ይስተዋላሉ። በዚህም ምስክርነት ላይ ተመስርቶ ብዙ የስኳር ታማሚዎች ፤ ወደ እነኝህ ስፍራዎች እየጎረፉ ፤ ተመሳሳይ ውጤቶች እያስተዋሉ ፤ ጥቂት የማይባሉትም የስኳር መድሐኒት መውሰድ እያቆሙም ይገኛሉ። የስኳር በሽታን ሙሉ በሙሉ እንደሚፈውሱ ፤ በድፍረት የሚናገር ባለሙያ እምብዛም ባይገኙም ፤ እነኝህ ታካሚዎች ይህን ምስክርነት ሲሰጡላቸው ግን፤ በዝምታ የሚያልፉ አሉ። ለመሆኑ ግን እውነታው ምንድን ነው? የሰለጠነው አለም ያልደረሰበት ተአምራዊ የሳይንስ ልህቀት ፤ ወይስ ስለ ስኳር በሽታ ያለ የግንዛቤ ክፍተት? እያንዳንዱን በጥልቀት እንመልከተው፡ ሰዎች እያዩት ያለው ፈውስ ምንድን ነው? ጥብቅ የምግብ ቁጥጥር የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች በጤናቸው ላይ አስገራሚ ለውጦችን ይመለከታሉ፤ የደም ስኳር መጠናቸው ይቀንሳል፣ የዕለት ተዕለት መድኃኒት ፍላጎታቸውም ይወርዳል። በተለይም ከአመጋገብ ለውጥ ጋር ክብደትን መቀነስ ከተቻለ፣ የሰውነት ህዋሳት ለኢንሱሊን ሆርሞን የተሻለ ምላሽ እንዲሰጡ በማድረግ የስኳር በሽታ ምልክቶችን ሊያጠፋ ይችላል። ይህ በተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች የተረጋገጠ በሕክምናው ዓለም የሚታወቅ እውነታ ነው። በዚህ ሂደት የታካሚው የላቦራቶሪ ምርመራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ይሻሻላሉ። በተለይም ባለፉት ሶስት ወራት በደም ህዋሳት ላይ የነበረውን ከፍተኛ የስኳር ጫና የሚለካው የ HbA1c ምርመራ ወደ "ጤናማ" ደረጃ ይመለሳል። ይህን አስደሳች ውጤት ያየ ታካሚ ታዲያ በተፈጥሮ የሚደርስበት አንድ መደምደሚያ አለ፦ "በሽታው ጠፍቷል!" እንደዚህ ቢያስቡም አይፈረድባቸውም! አንድ ወሳኝ ጥያቄ ግን ማንሳት ያስፈልጋል፦ እሳት ውስጥ ማገዶ መጨመር ብናቆምና ፤ ወላፈኑ ባይታየን ፤ እሳቱ በእርግጥ ጠፍቷል ማለት ነውን? በሽታው እንዴት ይከሰታል? የደም ስኳር ምርመራ ውጤታችን "ጤናማ" ስለመጣ ብቻ በሽታው ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ማለት እንዳልሆነ ለመረዳት፤ የቆሽትን እና የኢንሱሊን ሆርሞንን ሳይንሳዊ ሂደት በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል። በቆሽታችን ውስጥ አይሌትስ ኦፍ ላንገርሃንስ (Islets of Langerhans) የተባሉ ጥቃቅን ህዋሳት አሉ። እነዚህ ህዋሳት የደም ስኳርን የሚቆጣጠረውን ኢንሱሊን የማምረት ኃላፊነት አለባቸው። በዚህ ምስል ውስጥ 3ኛው ቁጥር ያለባቸው ህዋሳት የቆሽት ኢንሱሊን አምራች ህዋሳት ናቸው። እነዚህን ህዋሳት በአንድ ፋብሪካ ውስጥ እንደሚሰሩ ሰራተኞች አድርገው ያስቧቸው። በህይወት ዘመናችን አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰሩ ሲሆን ፤ ያለ እረፈት ለ 24 ሰዓታት እስከ እለተ ሞታችን ይተጋሉ። እነኝህ ህዋሳት ለረጅም ዓመታት በሚደርስባቸው ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት ጫና እና የሰውነት ኢንሱሊንን የመቋቋም ባህሪ (Insulin Resistance) ምክንያት፣ በእነዚህ ህዋሳት ላይ እጅግ ከፍተኛ የስራ ጫና ይፈጠራል። ውሎ አድሮ ሰራተኞቹ (ህዋሳቱ) ይዝላሉ፤ ይደክማሉ። ጫናው ሲበዛባቸው ደግሞ መሞት ይጀምራሉ። የተቀሩት ህዋሳት የሞቱትን ስራ ተክተው ለመስራት ቢጥሩም፣ አቅማቸው በጊዜ ሂደት እየመነመነ ይመጣል። አቅማቸው እጅጉን ሲዳከም ተራውን የደም ስኳር እንኳን ማስተናገድ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ይህ ባዮሎጂያዊ ድካም የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ (Type 2 Diabetes) መነሻ ነው። ምግባችንን ስናስተካክል ለእነዚህ ህዋሳት የስራ ጫና  ይቀንስላቸዋል። ሆኖም የአመጋገብ ለውጥ የሞቱትን ህዋሳት መልሶ ሊተካ ወይም የመጨረሻው የድካም ደረጃ ላይ የደረሰን ህዋስ እንደ አዲስ ሊያድስ አይችልም። ደክሞት 20 ኪሎ ማንሳት ለከበደው ሰው ፤ 2 ኪሎ ሰጥቶ ፤ 'ድካም ቀንሷል' ማለት ፈጽሞ አይቻልም። ኪሎ እንጂ ድካም አልቀነሰም! የምግብ ስርዓት ምን ሊያደርግ ይችላል? እዚህ ጋር እንዳይሳሳቱ! የ አመጋገብ ስርአትን ማስተካከል ለስኳር በሽታ ህክምና ካሉት መፍትሔዎች ውስጥ ቀዳሚው እና ዋነኛው ነው። እንደውም በህክምናው አለም "ምግብ ዋነኛው መድኃኒት ነው" (Food is Medicine) እንደሚባለው፣ የስኳር መድኃኒትን ያለ አመጋገብ ማስተካከል ትርጉም የለሽ ድካም ነው። በጥንቃቄ መመገብ እና የአበላል ስርአትን ማሻሻል ማለት፤ እነዚያን ለዓመታት ሲለፉ ለቆዩት እና ለደከሙት የቆሽት ህዋሳት እጅግ አስፈላጊ የሆነ "የዕረፍት ጊዜ" መስጠት ማለት ነው። በምግብ የሚመጣውን ጫና በመቀነስ፤ የተዳከሙት "ሰራተኞች" ቢያንስ የዕለት ተዕለት ስራቸውን እንዲከውኑ እና የሰውነትዎን ጤና እንዲጠብቁ እያገዟቸው ነው። ይህ በራሱ ለጤና ጉዞዎ ትልቅ ድል እና ስኬት ነው። ሆኖም ግን አንድ ወሳኝ ጥንቃቄ ሊኖር ይገባል። የአመጋገብ ለውጥ ብቻውን ያለ ህክምና ክትትል እና ያለ መድኃኒት እገዛ ውጤታማነቱ ሊስተጓጎል ይችላል። መድኃኒት እና አመጋገብ ተደጋግፈው ሲሰሩ ብቻ ነው ዘላቂ እና አስተማማኝ ጤና ማግኘት የሚቻለው። በሽታውን መቆጣጠር ከፈውስ ጋር አንድ አይደለም በሕክምና ሳይንስ ውስጥ በሽታን መቆጣጠር እና በሽታው ሙሉ በሙሉ መዳኑ (Cure) መካከል ግዙፍ ልዩነት አለ። በዚህ ረገድ የቃላት አጠቃቀማችን እጅግ ጥንቃቄ ሊታከልበት ይገባል። ያስተውሉ! "ወላፈኑ ቢቆምም ረመጡ እስካለ እሳቱ ጠፋ ማለት አንችልም።" ይህ ምሳሌ እንጂ የስኳር በሽታን እንደ እሳት ነው ማለት አይደለም። አመጋገብዎን ሲያስተካክሉ በሽታውን የሚያባብሰውን "ማገዶ" መክተት አቁመው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከጀርባ ያለው የበሽታው ባህሪ አይለወጥም። የደከሙት ህዋሳት እዚያው ናቸው፤ የሞቱትም አይመለሱም። የቀሩት ህዋሳት መስራት የሚችሉትን ያህል ጫና ብቻ እንዲያስተናግዱ ስለተደረገ፣ የላቦራቶሪ ውጤቶችዎ "ጤናማ" መስለው ይታያሉ። እውነታው ግን ይህ ነው፦ አመጋገብዎን በማስተካከል ስኳርዎን ተቆጣጠሩት እንጂ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ አልዳኑም። አሁን ዘመኑ በደረሰበት ከስኳር በሽታ የዳኑ ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ይህም ህክምና በቀጣይ አመታት ውስጥ ለአብዛኛው የአለም ህዝብ ይዳረሳል ተብሎ ይታሰባል። እስከዛ ግን የስኳር በሽታዎን መቆጣጠር የእርስዎ ቀዳሚ ድርሻ ነው። "ድኛለው" የማለት አደጋው ምንድነው? "ድኛለሁ" ብሎ ማሰብ አዎንታዊ ስሜት ቢፈጥርም፣ ይህ አስተሳሰብ ለከፋ አደጋ ሊዳርገን ይችላል። በተለይ እንደ ስኳር ባሉ ስር የሰደዱ ህመሞች ላይ ይህ የ"ሀሰተኛ ደህንነት" ስሜት የሚከተሉትን ስውር አደጋዎች ይዞ ይመጣል፦ 1. የመድኃኒት መቋረጥና የውስጥ አካላት መጎዳት ብዙዎች "ደህና ነኝ" ብለው በማሰብ ብቻ ያለ ባለሙያ ምክር መድኃኒት ያቆማሉ። ነገር ግን የመድኃኒት ለውጥ መደረግ ያለበት በስኳር ስፔሻሊስት (Endocrinologist) እና በህክምና መመሪያዎች ላይ ተመስርቶ ብቻ መሆን አለበት። መድኃኒት በራስ ፍቃድ ማቆም የደም ስኳር በድንገት እንዲጨምር ከማድረጉም ባለፈ፣ በሂደት ለኩላሊት ድክመት፣ ለልብ በሽታ እና ለስትሮክ የመጋለጥ እድልን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። 2. የ"ሀሰተኛ ደህንነት" ስሜትና መዘናጋት "ተፈውሻለሁ" የሚለው እምነት የደም ስኳርን የመከታተል ፍላጎትን ያጠፋል። ይህ መዘናጋት ስኳር "በዝምታ" (Silent killer) የውስጥ አካላትን እንዲጎዳ ሰፊ ዕድል ይሰጠዋል። መከታተል ሲቆም፣ ህመሙም በስውር ስራውን ይቀጥላል። ክትትሉም እቤት በሚደረግ የስኳር ምርመራ ሳይሆን ፤ በህክምና ባለሙያ መሆን ይኖርበታል። 3. የስነ-ልቦና ቀውስ እና ተስፋ መቁረጥ የአመጋገብ ስርዓት ሲለወጥ ወይም የኢንሱሊን አምራች ህዋሳት አቅም ይበልጡኑ እየተዳከመ ሲመጣ ፤ ስኳሩ መልሶ መጨመሩ አይቀሬ ነው። በዚህ ወቅት "ድኛለሁ" ብሎ ሲያስብ የነበረ ሰው የመሸነፍ እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይወርሰዋል። ይህ ስነ-ልቦናዊ ጫና ደግሞ ለቀጣይ ህክምና ያለውን ተነሳሽነት በእጅጉ ይገላል። ምግብ ወይስ መድሐኒት? የተሳሳተው ምርጫ በሀገራችን በኢትዮጵያ ብዙዎቻችን ወደ ተፈጥሯዊ ፈውስ የማዘንበል ልምድ አለን። ይህ ለጤና ጥንቃቄ ማድረግ መልካም ቢሆንም፣ ትክክለኛውን መረጃ ካልያዝን ግን ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል። ጤናማ አመጋገብ እና ዘመናዊ ህክምና ተቃራኒ ሳይሆኑ አጋዥ መሆናቸውን መረዳት የጤና ጉዟችን ስኬት ወሳኝ ነጥብ ነው። ምግብን እንደ መድኃኒት ስንቀበል የበሽታውን ተፈጥሮ ክደን መሆን የለበትም። እንደ ስኳር ያሉ ህመሞች በባህሪያቸው የረጅም ጊዜ ክትትልና ጥንቃቄ የሚሹ መሆናቸውን መረዳት ቀዳሚው እርምጃ ነው። ምግብ በሰውነታችን ላይ ያለውን ጫና ሲቀንስ፣ መድኃኒቶች ደግሞ የኢንሱሊንን ስራ ያግዛሉ። እነዚህ ሁለት ወሳኝ ሀይሎች ተባብረው ሲሰሩ ስኳርን በይበልጥ መቆጣጠር ይቻላል። አንዱን መርጦ ሌላውን እርግፍ አድርጎ መተው ግን ሰውነታችንን ያለ መከላከያ ለጥቃት ማጋለጥ ነው። ያስተውሉ! እውነተኛ ጤና የሚገኘው በአመጋገብ ስርአት እና በህክምና ክትትል መካከል ያለውን ሚዛን ጠብቆ በመጓዝ ነው። አንዱ የሌላው ምትክ ሳይሆን፣ ሁለቱም ለተሻለ ህይወት አስፈላጊ የሆኑ የጤና ምሶሶዎች ናቸው። ተስፋ እውነትን ሊተካ አይገባም፤ ይልቁንም እውነት ለተስፋችን መሠረት መሆን አለበት። ፈውስን ብቻ አይመኙ፤ ይልቁንም ጤናዎን የመቆጣጠር ጥበብን ይገንቡ።

  • “ብርድ መታኝ…” — በእርግጥ “የብርድ በሽታ” አለ?

    “ነፋስ መታኝ… አንገቴን ጨመደደኝ…ቀስፎ ብርዱ አጥንቴ ውስጥ ገባ…” ይህን ንግግር በኢትዮጵያ ምድር ያልሰማ ጆሮ፣ ያልተናገረ አንደበት የለም ለማለት ይቻላል። በብዙዎቻችን ዘንድ “የብርድ በሽታ” እንደ ተራ ስሜት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድ ትልቅ የሕክምና ምርመራ (Diagnosis) ተቀባይነት አግኝቷል። በባህልም ይህ በሽታ በሚከተሉት ምክንያቶች እንደሚመጣ ይታመናል፦ ቀዝቃዛ አየር ወይም ነፋስ ሰውነትን ሲመታ/ ከሰውነት ጋር ሲጋጭ ሰውነትዎ ሞቆ ልብሶችን ቀዝቃዛ ቦታ ሲያወልቁ "ይሄን ጊዜ ብርድ ይመታዎታል!" ተብሎ ይታሰባል። ብርድ ሲመታዎትም ፤ አንገትዎ ጋር ፣ ጀርባዎ አልያም ደረትዎ ጋር ህመም ሊሰማዎት ይችላል። የ ሳል ምልክት ሊያዩ ይችላል። በአጠቃላይ ሰውነትዎ ላይ ደስ የማይል የህመም ስሜት ይሰማዎታል። ይህ በባህላዊው ነው። ግን ጥያቄው፦ ❓ ይህ በሽታ እውነት ነውን? ቀዝቃዛ አየር በራሱ በሽታ ነው? ወይስ ከበስተጀርባ ሌላ የህክምና ምስጢር አለ? 🧠የህክምና ሳይንስ ምን ይላል? ዘመናዊ ህክምና አንድ ነገር ላይ በደንብ ይስማማል፦ 👉 ቀዝቃዛ አየር በራሱ በሽታ አያመጣም። በህክምና ሳይንስ ውስጥ ነፋስ፣ ለቅዝቃዜ መጋለጥ ወይም የሙቀት መጠን መቀነስ ብቻውን ኢንፌክሽን ወይም በሽታ እንደሚፈጥር የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ የለም። ይልቁንም ሰዎች “የብርድ በሽታ” ብለው የሚጠሩዋቸው ምልክቶች በህክምናው እንደሚከተለው ይብራራሉ፦ 1. የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ብዙውን ጊዜ የጉንፋን ምልክቶች የሚታዩብን ከቅዝቃዜ በኋላ ስለሚሆን፣ ተጠያቂው ብርዱ ይመስለናል። ነገር ግን እውነተኛው ወንጀለኛ ቫይረስ ነው። ብርድና ንፋስ ለቫይረሶች ስርጭት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ እንጂ ኢንፌክሽን አያመጡም። ቀዝቃዛ አየር የአፍንጫችንን የውስጥ እርጥበት ሲያደርቀው፣ ቫይረሶችን አጣብቆ የሚያስቀረውና የሚያጠፋው ተፈጥሯዊ “ንፍጥ” (Mucus) ስራውን ያቆማል። በዚህ ጊዜ ቫይረሶች/በሽታ አምጪ ተህዋሳት በቀላሉ ወደ ሰውነታችን ሰርገው ይገባሉ። ለዚህም የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ያስከትላሉ። እንዲሁም በብርድ ጊዜ ሰዎች ቤት ውስጥ ይቆያሉ፣ የቅርብ ንክኪ ይጨምራል። ይህ ደግሞ ቫይረሱ ከአንዱ ወደ ሌላው እንዲዘዋወር ሰፊ እድል ይሰጠዋል። 2. የጡንቻና የአጥንት ህመም “ንፋስ ገባብኝ” ስንል የምንገልጸው የጀርባ ወይም የአንገት ህመም፣ የሰውነታችን የተፈጥሮ የመከላከያ ስልት ውጤት ነው። ሰውነት ቅዝቃዜ ሲሰማው ሙቀት ለማመንጨት ሲል ጡንቻዎችን በሃይል እንዲኮማተሩ ያደርጋል። ይህ ድንገተኛ መኮማተር (Spasm) ጡንቻው እንዲዝልና ከፍተኛ ህመም እንዲሰማን ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዝቃዜ የደም ስሮችን ስለሚያጠብ፣ ወደ ጡንቻዎች የሚደርሰው ደም ይቀንሳል። ለዚህም በብርድ ጊዜ ጡንቻዎች ይወጠራሉ፣ የደም ቧንቧዎች ይኮማተራሉ፤ ይህም ህመም በይበልጥ እንዲሰማን ያደርጋል። ችግሩ ያለው ከውጭ በመጣ ንፋስ ሳይሆን በሰውነታችን የውስጥ ምላሽ ላይ ነው። 3. ለቀዝቃዛ አየር ሳንባችን የሚሰጥ ስሜታዊ ምላሽ አንዳንዴ ብርድ ራሱን የሚችል በሽታ ሳይሆን የሰውነት “ቁጣ” (Irritation) ሊሆን ይችላል። ቀዝቃዛና ደረቅ አየር በቀጥታ ወደ ሳንባ ሲገባ፣ የመተንፈሻ ቱቦዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ይጠብባሉ። ይህ ሁኔታ እንደ አስም ያሉ ችግሮች ባሉባቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ትንፋሽ ማጠርና ሳል ይፈጥራል። ከዚህም ባሻገር አፍንጫችን ቀዝቃዛውን አየር ለማሞቅ ሲሞክር ተጨማሪ ፈሳሽ (ንፍጥ)ያመነጫል። ይህ ፈሳሽ በራሱ የኢንፌክሽን ምልክት ሳይሆን፣ አፍንጫችን ስራውን በትክክል እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው። 🔍 ለዚህም ነው “የብርድ በሽታ” እውነት የሚመስለን! 📊ጥናቶች ምን ይጠቁማሉ? በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ሰፊ የሕክምና ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ቀዳሚ ምክንያቶች አንዱ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (CDC) መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአማካይ አንድ አዋቂ ሰው በዓመት ከ2 እስከ 4 ጊዜ በጉንፋን የሚጠቃ ሲሆን፣ ሕፃናት ደግሞ የመከላከል አቅማቸው ገና በማደግ ላይ በመሆኑና በትምህርት ቤቶች ባለው የቅርብ ንክኪ ምክንያት በዓመት ከ6 እስከ 8 ጊዜ ለዚህ ሕመም ይጋለጣሉ። በሀገራችን ኢትዮጵያም በተለይ በክረምት ወቅት፣ በበጋው ቅዝቃዜ እና በደጋማ አካባቢዎች የመተንፈሻ አካላት ችግር ዋነኛው የጤና ስጋት ሆኖ ይታያል. 🤧 የብርድ በሽታ ምልክቶች ሰዎች የሚከተሉትን ምልክቶች በሙሉ “የብርድ በሽታ” በሚል ስም ይሰበስቧቸዋል። "የብርድ በሽታ" ተብለው በአንድ ጥቅል ስም ቢጠሩም ፣ ምልክቶቹ እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ የተለየ ምክንያትና ትርጉም አላቸው። አንድ በአንድ እንመልከት፡ የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት (ምክንያቱ፦ የቫይረስ ኢንፌክሽን ምልክት) የአንገት፣ የትከሻ ፣ የደረት/ጀርባ ህመም (ምክንያቱ፦ የጡንቻ መቆጣት ምልክት) መንቀጥቀጥ /ብርድ ብርድ ማለት/ የትኩሳት (ምክንያቱ፦ የሰውነት መቆጣት/ የኢንፌክሽን ምልክት) ሳል (ምክንያቱ፦ የመተንፈሻ አካል መቆጣት ምልክት) የራስ ምታትና የድካም ስሜት  (ምክንያቱ፦ የሰውነት መቆጣት/ የኢንፌክሽን ምልክት) ❄️ የ“ብርድ” እና “ብርድ ብርድ ማለት” ልዩነት ይህ ብዙዎች የሚያሳስቱትት ነው። እላይ ያነሳነው ቢሆንም ፤ በይበልጥ እንዘርዝረው። ብርድ ብርድ ማለት (Chills)፦  ይህ የኢንፌክሽን/የሰወነት መቆጣት ምልክት ነው። ይህ ብዙውን ጊዜ ትኩሳትን ያመለክታል። ሰውነታችን ሙቀቱን ለመጨመር የሚያደርገው ጥረት ነው። ጡንቻዎቻችንም ሙቀት ለማመንጨት ሲሉ ይንዘፈዘፋሉ። ይሄን ጊዜ የማንቀጥቀጥ ምልክት ይስተዋላል። እርስዎ “ብርድ አነቀጠቀጠኝ” ብለው ልብስ ይደርባሉ። “የብርድ በሽታ”፦  ለቅዝቃዜ በመጋለጥ የሚመጣ ተብሎ የሚታመን ፤ በሕክምና የተለያዩ በሽታዎች ምልክት ነው። 🧣 በተለምዶ ምን ይመከራል? ብዙ ጊዜ ሰው "ብርድ እንዳይመታው" የሚከተሉት ምክሮች ይሰጣሉ። "ቅዝቃዜ ቦታ ልብስ አታውልቅ!" "ወፍራም ልብስ ልበስ!" "ትኩስ ነገር ጠጣ!" "ቅዝቃዜ ቦታ ላይ አትውጣ!" ለመሆኑ እነኝህ ምክሮች ትክክል ናቸው? 👉 አዎ!  ነገር ግን የተሟሉ አይደሉም! እንዴት? እርግጥ ነው! ሙቅ ልብስ መልበስ ሰውነት ምቾት እንዲሰማው፣ ከመጠን በላይ መቀዝቀዝንና የጡንቻ መኮማተርን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ አለው። ነገር ግን በሽታን ለመከላከል ብቻውን በቂ አይደለም። ትክክለኛው እና ሳይንሳዊው የመከላከያ መንገድ ትኩረት ማድረግ ያለበት ተላላፊ ተህዋሲያን ላይ ሲሆን፣ ይህም የእጅ ንፅህናን በመጠበቅ፣ ከታመሙ ሰዎች በመራቅ፣ በተዘጉ ክፍሎች ውስጥ በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር በማድረግ እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚገነቡ የተመጣጠነ ምግቦችን በመመገብ መተግበር አለበት። ማስተዋል ያለብዎት ጉዳይ! ሁሉንም የጤና መታወክ “ብርድ ነው” በሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ስር መሰብሰብ ደግሞ የራሱ የሆነ ከፍተኛ የጤና አደጋ አለው። ይህ አመለካከት ሰዎች ትክክለኛውን የህክምና እርዳታ እንዲያዘገዩ፣ እንደ የሳምባ ምች (Pneumonia) ያሉ ለህይወት አስጊ የሆኑ ከባድ ህመሞችን እንደ ተራ “የብርድ በሽታ” አይተው ቸል እንዲሉ እና ተገቢ ያልሆኑ መድኃኒቶችን እንዲጠቀሙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ስለዚህ ቅዝቃዜው ለበሽታው መንገድ የሚያመቻች “አጋዥ” እንጂ ዋናው “መንስኤ” አለመሆኑን ተገንዝቦ፣ ከጥንቃቄዎች ሁሉ የላቀውን ሳይንሳዊ ጥበቃ ማድረግ ለጤናችን ዋስትና ነው። 🧭 እንግዲህ… “የብርድ በሽታ” እውነት ነው? 👉 እንደ ስሜት — አዎ! 👉 እንደ ህክምና ምርመራ — አይደለም!

  • ጋንግሪን፦ ምልክቶች፣ መንስኤዎች እና መከላከያ መንገዶች

    ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በዝምታ ነው። በድንገት ሳይታሰብ ፤ ያለምንም ማስጠንቀቂያ። ሲጀምር ጥቃቅን ጥቁር ነጠብጣቦች በጣት ጫፍ ላይ ይታያሉ። ቀጥሎም የማይድን፤ እረፍት የማይሰጥ ቁስል ይከተላል። ቀጥሎም እጅግ የሚከብድ ፤ ነፍስን የሚረብሽ መጥፎ ሽታ ቤቱን ይሞላዋል። ጋንግሪን የሰውነት ህዋሳት (tissues) ሲሞቱ  የሚከሰት ሁኔታ ነው። በሰውነት ውስጥ የሚካሄድ የድብቅ ጦርነት ውጤት! እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የስኳር በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባቸው እና የደም ስር ሕክምና ገና ባልተስፋፋባቸው አገራት ፤ ጋንግሪን ብርቅ አይደለም። አውዳሚ ነው፤ አካልን ይበላል ፤ ሕይወትን ያናጋል። ጋንግሪን ከጊዜ ጋር የሚደረግ ሩጫ ነው። በሀገራችን ብዙዎች በትናንሽ ቁስሎች ይዘናጋሉ። "ይድናል" በሚል ተስፋ በባህላዊ መድኃኒቶች ወርቃማውን የሕክምና ጊዜ ያባክናሉ። "አካል ይቆረጣል" የሚለው ፍርሃት ራሱ ፤ ታካሚዎች ወደ ሆስፒታል ዘግይተው እንዲመጡ ያደርጋል። መፈራት የነበረበት ቀዶ ጥገናውን ሳይሆን ፤ ዘግይቶ መድረስ የሚያስከትለውን የማይመለስ ጥፋት ነበር። ዛሬ ስለ ጋንግሪን በግልጽ እንነጋገራለን። ጋንግሪን ምንድን ነው? በቀላል አነጋገር ጋንግሪን ማለት በበቂ የደም ዝውውር እጥረት ወይም በከባድ ባክቴሪያ ወረራ ምክንያት የሰውነት ህዋሳት (tissues) ሲሞቱ የሚከሰት ሁኔታ ነው። ደም ለሰውነታችን የህልውና መሰረት ነው። ለእያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ኦክስጅንን ፤ አልሚ ምግቦችን እና በሽታን የሚከላከሉ ነጭ የደም ሴሎችን ያቀርባል። ልክ የአንድ ተክል የውሃ መስመር ሲዘጋ እንደሚጠወልገው ሁሉ ፤ የደም ዝውውር ሲቋረጥም የሰውነት ክፍሎቻችን መኖር አይችሉም። ጋንግሪን አከሳሰት ደረጃዎች ፡ መጀመሪያ የቆዳ መልክ ይለወጣል (ግራ) ፤ ሲቀጥል ቁስል ይኖራል (መሀል) ፤ መጨረሻ ላይ ጋንግሪን ይከሰታል። ሕዋሳቱ አንዴ መሞት ከጀመሩ ደግሞ ሥጋው መበስበስ ይጀምራል። ያ የሚከረፋና ነፍስን የሚረብሽ ሽታ የሚመጣውም ከዚሁ የሞተ ሥጋ ነው። ነገር ግን ትልቁ አደጋ ሞቱ መጀመሪያ በተጠቁት ሕዋሳት ላይ አለመቆሙ ነው። ለዚህ መበስበስ ምክንያት የሆነው ባክቴሪያ እንደ ሰደድ እሳት አጠገብ ወዳሉ ጤናማ አካላት በፍጥነት ይስፋፋል። እነሱንም እየገደለ ጉዞውን ይቀጥላል። ጋንግሪን "ተላላፊ" የሚመስለውም ለዚህ ነው፤ ሳይቆርጡት የማይቆም ፤ ሳይገቱት የማይገታ የጥፋት ጉዞ! የሕዋሳት መሞት ሂደት ጀርባ ያለው ባዮሎጂ ነገሩን በቀላል ቀመር እንመልከተው። የሰውነታችን ጤንነት በዚህ ሚዛን ላይ የተመሰረተ ነው፦ ደም = ኦክስጅን + አልሚ ምግብ + የበሽታ መከላከያ ይህ የሕይወት መስመር ከአንድ የሰውነት ክፍል ላይ ለረጅም ጊዜ ሲርቅ ፤ ያ አካል ቀስ በቀስ ወደ ሞት ይጓዛል። ሂደቱም እንዲህ ነው፦ የኃይል መቋረጥ፦ መጀመሪያ ሕዋሳቱ ነዳጅ እንደጨረሰ ሞተር ኃይል ማመንጨት ያቆማሉ። የመዋቅር መፈራረስ፦ ቀጥሎም የሕዋሳቱ ሽፋን ጥንካሬውን ያጣና መፈራረስ ይጀምራል። የማይመለስ ጥፋት (Necrosis)፦ በመጨረሻም ሕዋሳቱ ሙሉ በሙሉ ይሞታሉ። ይህ "ኔክሮሲስ" ወይም የማይመለስ የሥጋ መበስበስ የምንለው አስፈሪ ደረጃ ነው። ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም። ባክቴሪያዎች ይህንን የሞተ ሥጋ እንደ መራቢያ ካገኙት ጥፋቱ እንደ ሰደድ እሳት ይፋጠናል! ውጤቱም የሚታይና የሚሰማ ይሆናል። የጠቆረ ፤ የሰለለ ፤ ያበጠ ወይም የሚገማ ሥጋ። ይህ የማይታይ ጦርነት ውጤት ነው። ደም ለሕዋሳቱ መድረስ ሲያቅተው ፤ ባክቴሪያዎች በሞተው ሥጋ ላይ አስፍተው ይሰፍራሉ። አራቱ ዋና ዋና የጋንግሪን ዓይነቶች ጋንግሪን እንደየመጣበት መንገድ እና እንደ ጥፋት ፍጥነቱ በአራት ዋና ዋና ዓይነቶች ይከፈላል። እያንዳንዱ ዓይነት የራሱ የሆነ የጥፋት ምልክት አለው፦ እርጥብ ጋንግሪን ያለባት ግለሰብ የመጀመሪያ ደረጃ ደረቅ ጋንግሪን (Dry Gangrene) — "ዝምተኛው ገዳይ" ይህ በአብዛኛው ያለ ኢንፌክሽን ፤ በደም ዝውውር እጥረት ብቻ የሚከሰት ነው። በስኳር በሽተኞች እና በደም ስር በሽታ ተጠቂዎች ላይ በብዛት ይታያል። ሥጋው ቀስ በቀስ ይደርቃል። ይጠቁራል። በመጨረሻም ልክ እንደ ደረቅ እንጨት ይረግፋል። ሂደቱ ዝግተኛ በመሆኑ ብዙዎች ሳይረዱት ጊዜ ያባክናሉ። እርጥብ ጋንግሪን (Wet Gangrene) — "ድንገተኛው ወራሪ" የደም ዝውውር መቋረጥ ከባክቴሪያ ኢንፌክሽን ጋር ሲቀላቀል የሚፈጠር እጅግ አደገኛ ሁኔታ ነው። እዚህ ጋር ሥጋው አይደርቅም። ይልቁንም ያብጣል ፤ ይረጥባል። እንዲሁም የሚረብሽ የመበስበስ ጠረን ያመጣል። ይህ ዓይነቱ ጋንግሪን በሰዓታት ውስጥ ስለሚስፋፋ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ይሻል። የጋዝ ጋንግሪን (Gas Gangrene) — "ውስጣዊው ቦምብ" ይህ ዓይነቱ ጋንግሪን መርዛማ ጋዝ በሚያመነጩ ባክቴሪያዎች የሚመጣ ሲሆን ፤ በብዛት ከባድ ቁስል ባለባቸው ሰዎች ላይ ይታያል። ባክቴሪያዎቹ በቆዳ ስር አየር ስለሚረጩ ፤ ሲነካ አየር እንዳለ ሆኖ "ጠር-ጠር" የሚል ድምፅ ይሰማል። በፍጥነት ወደ ደም በመቀላቀል ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ገዳይ ዓይነት ነው። ፎርኒየርስ ጋንግሪን (Fournier’s Gangrene) — "ፈጣኑ አጥፊ" በብልት እና አካባቢው ላይ የሚከሰት ፤ እጅግ ፈጣን እና አስከፊ ኢንፌክሽን ነው። ይህ ዓይነቱ ጋንግሪን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ጤናማ ሕዋሳትን የማውደም አቅም ስላለው ፤ከፍተኛ ትኩረትና ፈጣን ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል። ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው? ጋንግሪን በድንገት የሚከሰት ክስተት ሳይሆን ፤ የሰውነታችን የተፈጥሮ ጥበቃ መስመሮች ሲዳከሙ የሚመጣ የጤና ቀውስ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ፤ በተለይም በኢትዮጵያ ለዚህ አደገኛ ሕመም ዋነኛ መንስኤ የሚሆኑት የሚከተሉት ናቸው፦ የስኳር በሽታ ፦ በኢትዮጵያ የጋንግሪን ቁጥር እንዲጨምር ያደረገው ቀዳሚ ምክንያት ነው ይህ ነው። በኢትዮጵያ ካሉ የስኳር በሽተኞች ውስጥ ከ15% እስከ 25% የሚሆኑት በእድሜ ዘመናቸው የከፋ የእግር ቁስል (Foot Ulcer) ያጋጥማቸዋል። ይህ ቁስል በወቅቱ ካልታከመ በቀጥታ ወደ ጋንግሪንና ወደ አካል መቆረጥ (Amputation) ያመራል። የደም ስር መጥበብ (PAD)፦ የደም ስሮች በስብ ወይም በሌላ ምክንያት ሲጠቡ ፤ ሕዋሳቱ የሚፈልጉትን ኦክስጅን አያገኙም። ይህም ለጋንግሪን ያጋልጣል። ከባድ አደጋዎችና ቁስሎች፦ ድንገተኛ አደጋዎች፣ ቃጠሎዎች ፣ ወይም ጥልቅ የሆኑ የመኪና አደጋ ቁስሎች ለባክቴሪያዎች መግቢያ በር በመሆን የጋዝ ጋንግሪን (Gas Gangrene) ሊያስከትሉ ይችላሉ። የሰውነት በሽታ መከላከያ አቅም መቀነስ፦ እንደ ኤች.አይ.ቪ (HIV) ፤ ካንሰር ወይም በኬሞቴራፒ ምክንያት የመከላከል አቅማቸው የደከመ ሰዎች ፤ ትናንሽ ኢንፌክሽኖችን እንኳ መቋቋም ስለማይችሉ ለጋንግሪን ተጋላጭ ናቸው። በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አሳሳቢ የሚያደርገው ምንድነው? በአገራችን የስኳር በሽታ ስርጭት እየጨመረ እየመጣ ነው።  በቅርብ የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የደም ግፊትና ስኳር ባለባቸው ታካሚዎች ላይ   የደም ስር መጥበብ (Peripheral Arterial Disease)  በከፍተኛ ሁኔታ እየታየ ይገኛል። ከዚህም በላይ ፤ ብዙ ታካሚዎች የሕመሙ ምልክት ሳይታይባቸው ለረጅም ጊዜ ስለሚቆዩ ፤ ሆስፒታል የሚደርሱት ጋንግሪኑ ሥር ሰዶ አካል መቆረጥ የግድ በሚሆንበት ደረጃ ላይ ነው። የጋንግሪን ምልክቶች ያስተውሉ መደንዘዝ የመሻል ምልክት አይደለም የቆዳ ቀለም መለወጥ (ከቀይ → ወደ ሐምራዊ/ጥቁር ሰማያዊ → ወደ ጥቁር (ሕዋሳቶቹ ሲሞቱ) ) መጀመሪያ ላይ  የማይታገስ ከፍተኛ ህመም ይሰማል። ሕዋሳቱና ነርቮቹ መሞት ሲጀምሩ ሕመሙ ይጠፋና አካባቢው ይደነዝዛል።(ሕመሙ መጥፋቱ "ዳኑ" ማለት ሳይሆን ፤ አደገኛ ምልክት መሆኑን ልብ ይበሉ) በተለይ በእርጥብ ጋንግሪን ወቅት ፤ ቆዳው ይወጥራል ፤ ያብጣል እንዲሁም መግል ወይም ደም የቀላቀለ ፈሳሽ ይወጣል። ሕዋሳቱ/ስጋው ሲሞት ከባድ ሽታ ይኖረዋል። ኢንፌክሽኑ ወደ ደም ከተቀላቀለ ከፍተኛ ትኩሳት ፤ ብርድ ብርድ ማለት እና የልብ ምት መጨመር ይከሰታል። (ይህ አደገኛ ነው) አ ደገኛ ምልክቶች (አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው) ጋንግሪን ጊዜ አይሰጥም። "ነገ እሄዳለሁ" የሚባልለት ሕመምም አይደለም። የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩዎት ፤ ሕይወት የመጥፋት አደጋ ስለተጋረጥዎ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል መሄድ ይኖርብዎታል፦ የጣት መጥቆር ፦ የእግር ወይም የእጅ ጣትዎ ቀለሙን ቀይሮ ወደ ጥቁርነት ካዘነበለ ፤ ያ አካል ኦክስጅን አጥቶ እየሞተ መሆኑን የሚያሳይ የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ ነው። የሰደድ እሳት ስርጭት፦ የቆዳ መቅላትና እብጠቱ በዓይንዎ እያዩት በፈጣን ሁኔታ ወደ ላይ የሚሰራጭ ከሆነ ፤ ባክቴሪያው በከፍተኛ ፍጥነት ጤናማ ሕዋሳትን እየወረረ መሆኑን ያሳያል። የበሰበሰ ሥጋ ሽታ፦ ከቁስልዎ የሚወጣው ሽታ የሚረብሽ ከሆነ ፤ በሰውነትዎ ውስጥ የሞቱ/እየበሰበሱ ያሉ ሕዋሳት መኖራቸውን ይጠቁማል። ድንገተኛ ግራ መጋባት፣ የሰውነት መዛል፣ ወይም ከፍተኛ ድካም ከተሰማዎት፣ ኢንፌክሽኑ ወደ ደምዎ ውስጥ ገብቶ ሊሆን ይችላል። ይህ በሰዓታት ውስጥ ለሞት ሊያደርስ የሚችል አደገኛ ደረጃ ነው። እነዚህን ምልክቶች ሲያዩ ፈጽሞ የባህል ሐኪም ጋር እንዳይሄዱ። በሕይወትዎ ይፈርዳሉ! ምርመራ እና ሕክምና ጋንግሪንንን ለመለየት ዶክተሮች በአካላዊ ምርመራ ብቻ አይወሰኑም። ሐኪሞች የኢንፌክሽኑን ጥልቅነት በደም ምርመራ ፤ የደም ስሮችን ስራ በዶፕለር (Doppler) አልትራሳውንድ እና የጋዝ መኖርን በራጅ (X-ray) ያረጋግጣሉ። በሽታው ከተረጋገጠ በኋላ የመጀመሪያውና ዋናው ተግባር የጠፋውን የደም ዝውውር መመለስ ነው። የሞተ ሥጋ ለባክቴሪያዎች ምርጥ መራቢያ ስለሆነ ፤ ሐኪሞች የሞተውንና የተበከለውን ሥጋ በጥንቃቄ ያስወግዳሉ። አንዳንዴ ኢንፌክሽኑ ወደ መላ ሰውነት ተሰራጭቶ ሕይወትን እንዳይቀጥፍ ሲባል "አካልን መቁረጥ" (Amputation) እንደ የመጨረሻ አማራጭ ሊወሰድ ይችላል። ታድያ ለምንድነው ኢትዮጵያ ላይ አብዛኛውን ጊዜ አካል የሚቆረጠው? ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ታካሚዎች ሆስፒታል የሚደርሱት ጋንግሪኑ አጥንት ደርሶና ሥጋው በስብሶ ካበቃ በኋላ ነው። ቀድሞ ምልክቶቹን እንዳዩ አይመጡም። የታካሚን ሕይወት በትንሹ አካል ለመለወጥ ሲባል፤ ዶክተሮች ይህን መራራ ግን አስፈላጊ ውሳኔ ይወስናሉ። ኢንፌክሽኑንም ለመቆጣጠር የኢንፌክሽን መቃወሚያ አንቲባዮቲክ ይሰጣል። ከዚህም ባሻገር ከጀርባ ያለ ህመም (ደምግፊት ወይም ስኳር) ለመቆጣጠር ይሞከራል። ህመሙን ለማስታገስም የህመም ማስታገሻ ይሰጣል። ጋንግሪን ዕጣ ፈንታ አይደለም፦ መከላከል ይችላሉ! ትልቁ የምስራች ይህ ነው፦ አብዛኛው ጋንግሪን መከላከል ይቻላል! በተለይ የስኳር ሕመም ያለባችሁ ወገኖቻችን ፤ ጥቂት ቀላል ጥንቃቄዎችን በማድረግ አካልንና ሕይወትን መታደግ ይቻላል። ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ። በየቀኑ እግርን መመርመር ትክክለኛ ጫማ ማድረግ የስኳር መጠንን በጥብቅ መቆጣጠር ሲጋራ አለማጨስ ቁስል ሲፈጠር ወዲያው መታከም የጋንግሪን ህክምና ከጊዜ ጋር የሚደረግ ሩጫ ነው። ጋንግሪን አንድ ከባድ እውነት ያስተምረናል፦ ሕይወት በደም ዝውውር ላይ የተመሰረተች ናት። ደም ቀይ ፈሳሽ ብቻ አይደለም። ኦክስጅን ነው፤ መከላከያ ነው፤ ፈውስ ነው ፤ ሕልውና ነው። ጋንግሪን ከመጮኹ በፊት በለሆሳስ ምልክት ያሳያል። በጊዜ መታከም ማለት ጣትን ከማጣትና እግርን ከማጣት መካከል ያለው ልዩነት ነው። በጋንግሪን ውስጥ ጊዜ ማለት አካል ነው፤ አካል ደግሞ ሕይወት ነው። ምን ይጠብቃሉ!? ዛሬውኑ እግርዎን ይመርምሩ! ዛሬውኑ ስኳርዎን ይቆጣጠሩ! ዛሬውኑ ለጤናዎ ይቁሙ!

  • ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና : ጥሩ ወይስ መጥፎ

    “ያቺን ዝነኛ ሰው አየሃት? ፊቷ ምን እንደሆነ?” ይህ አብዝተን የምንሰማው አረፍተ ነገር እየሆነ መጥቷል። በኢትዮጵያም ጥቂት የማይባሉ ታዋቂ ግለሰቦች ከንፈር ከማስተካከል፣ ወገብ ከማጥበብ ፣ ውፍረት ከማጥፋት እስከ ዳሌ ማሳደጊያ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና እንዳደረጉ በገሀድ ይታወቃል። ታድያ ግን ድንገት ከታሰበው ይልቅ መልክ ሲቀይር ወይም.... አንዳንዴም በሚያስደነግጥ መልኩ ሲለወጥ... ወዲያውኑ አንድ መደምደሚያ ላይ ይደረሳል፦ 👉 “የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና አደገኛ ነው።” 👉 “ሰውነትን ያበላሻል።” ግን እውነቱ ይሄ ብቻ ነው? ወይስ በጥቂት የሚታዩ ውጤቶች ላይ በመመስረት አንድን ሙሉ የሕክምና ዘርፍ እየፈረድን ነው? እስቲ ረጋ ብለን ከፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ጀርባ ያለውን ሳይንስ፣ ቁጥሮች እና እውነታውን እንመርምር። የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ታሪክ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ታሪክ ከ4,000 ዓመታት በፊት የጀመረ መሆኑን ያውቃሉ? ታሪኩ የሚጀምረው በጥንታዊት ህንድ (በ600 ዓመተ ዓለም ገደማ) ሲሆን፣ በወቅቱ "የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አባት" ተብሎ የሚጠራው ሱሽሩታ (Sushruta) የተባለ ሐኪም በአደጋ ወይም በቅጣት ምክንያት አፍንጫቸው ለተቆረጠ ሰዎች አዲስ አፍንጫ ለመስራት የሚያስችል ብልህ ዘዴ ፈጠረ። ይህም ዘዴ ከታካሚው ግንባር ላይ ቆዳን በመቁረጥና ወደ አፍንጫው አካባቢ በማዞር አዲስ ቅርጽ መስጠት ሲሆን፤ ይህ የ"ቆዳ ንቅለ ተከላ" (Skin Grafting) መሠረታዊ መርህ ዛሬም ድረስ በዘመናዊ የሕክምና ክፍሎች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል። ህንዳዊው ዶክተር ሱሽሩታ ይሁን እንጂ በመካከለኛው ዘመን አከባቢ ፤ በአውሮፓ የሰውን አካል መለወጥ እንደ "ኃጢአት" ተቆጥሮ ፤ ዘርፉ ለዘመናት ተዳክሞ ነበር። በኋላ ግን እንደ ጋስፓሬ ታግሊያኮዚ ያሉ ሐኪሞች የፕላስቲክ ስርጀሪን ምህዳር ሊለውጡ ችለዋል። የዚህ ዘርፍ እውነተኛው "ወርቃማ ዘመን" የመጣው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በነበረው አስከፊ ሁኔታ ነው። በጦርነቱ ወቅት በከባድ መሣሪያዎች ፊታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ፤ገጽታቸው የተለወጠባቸው ወታደሮች ነበሩ። እነኝህ ወታደሮች ቢተርፉም ፤ መልካቸው የጦርነቱ ሰለባ ነበር። አብሮም ማንነታቸውና ሰብዓዊ ክብራቸው ፈርሶ ነበር። በዚህ ወቅት ሰር ሃሮልድ ጊሊስ (Sir Harold Gillies) የተባሉ አርቆ አሳቢ ሐኪም የሺዎችን ፊትና ማንነት መልሶ መገንባት ጀመሩ። የህንዳዊው ዶክተር ሱሽሩታ ይጠቀም የነበረው የአፍንጫ ማስተካከል ሕክምና ከጦርነቱ በኋላ የጸረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶችና ማደንዘዣዎች መዘመን ሕክምናውን ይበልጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን አደረገው። ወታደሮችን ለመጠገን ይውሉ የነበሩት እነኛ ዘዴዎችም ወደ ተራው ሕዝብ በመሸጋገራቸው የዛሬው የ ውበት ቀዶ ሕክምና እንዲፈጠር ምክንያት ሆኑ። በአሁኑ ጊዜ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና በጥንታዊ ጥበብና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተመስርቶ በሳይንስ ተደግፎ የብዙዎችን ህይወት እየለወጠ ይገኛል ። የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ስለ ውበት ብቻ አይደለም ብዙ ጊዜ ሲነሳ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከውበት ጋር ተያያዥነት አለው። እርሶም ፕላስቲክ ስርጀሪ ሲባል የሚመጣልዎት የሆሊውድ አርቲስት ይሆናል። የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ግን ይህ ብቻ አይደለም።ይህ ዘርፍ በአንድ የሰውነት ክፍል ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ድረስ ያለውን ማንኛውንም የሰውነት ክፍል ሊያካትት ይችላል። የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና የሰውን አካል መልሶ ለመገንባት፣ ለመጠገን ወይም ቅርፅን ለማስተካከል የሚረዳ የሕክምና ዘርፍ ነው። "ፕላስቲክ" የሚለው ቃል የመጣውም "መቅረጽ" ወይም "ማስተካከል" ከሚለው የግሪክ ቃል ነው። ዋና ዓላማው ከአደጋ፣ ከበሽታ ወይም ከተፈጥሮ ጉድለት የተነሳ የተጎዱ የሰውነት ክፍሎችን ወደ ነበሩበት መመለስ ነው። ይህ የሕክምና ዘርፍ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል። እነሱም መልሶ የመገንባት (Reconstructive) እና የውበት (Cosmetic) ቀዶ ሕክምና ናቸው። መልሶ የመገንባት ቀዶ ሕክምና የሚደረገው በተፈጥሮ ጉድለት (ለምሳሌ እንደ ከንፈር መሰንጠቅ አይነት)፣ በአደጋ፣ በቃጠሎ ወይም በካንሰር ምክንያት የተጎዱ የሰውነት ክፍሎችን ተግባር እና ገጽታ ለማስተካከል ነው። ይህ ዓይነቱ ሕክምና የታካሚውን ጤና እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማሻሻል የሚደረግ ነው። በሌላ በኩል የውበት ቀዶ ሕክምና የሚከናወነው፤ የአንድን ሰው ውጫዊ ገጽታ ይበልጥ ለማሳመር ነው። ይህ የሚደረገው በትክክል በሚሰሩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ነው። ዓላማውም አፍንጫን ለማስተካከል፣ የፊት መጨማደድን ለማስወገድ ወይም የሰውነት ቅርጽን ለማስተካከል፣ ወ.ዘ.ተ... ነው። ይህ በርካታ ዓይነቶች ያሉት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እንደ የዳሌ ቅርጽ ማስተካከያ (BBL) እና የጡት ማሳደግ (Breast Augmentation) ያሉ የውበት ማሻሻያዎች በስፋት ከሚከናወኑት መካከል ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ የተለመዱ ሂደቶች ባለፈ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች እጅግ በጣም ልቅ እና ያልተለመዱ የሰውነት ለውጦችም ሊደረጉ ይችላሉ። ቁጥሮቹ ምን ይናገራሉ? በአሁኑ ወቅት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ዘርፍ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ሲሆን፤ በ2024 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 38 ሚሊዮን የሚሆኑ የሕክምና ሂደቶች ተከናውነዋል። ከታካሚዎች መካከል 85.5% የሚሆኑት ሴቶች ቢሆኑም፣ የወንዶችም ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። በተለይም ከ18-34 ዓመት ያሉ ወጣቶች ለአፍንጫ እና ለጡት ቅርጽ ማስተካከል ቅድሚያ ሲሰጡ፤ ዕድሜያቸው ከ35 በላይ የሆኑት ደግሞ እንደ ቦቶክስ ያሉ የፊት ማደስ ሕክምናዎችን በስፋት ይመርጣሉ። ከውበት ማሻሻያ ጎን ለጎን፣ የመልሶ ግንባታ ቀዶ ሕክምናም በብዛት እየተከናወነ ይገኛል። በየዓመቱ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ዕጢ/ካንሰር ማስወገድ ሂደቶች ይከናወናሉ። እነኚህም በተለይ የቆዳ ካንሰርን ለማከም የሚደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ናቸው። ከ150,000 በላይ ሴቶች ደግሞ ከካንሰር በኋላ የጡት መልሶ ግንባታ ሕክምና ያገኛሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትም በተፈጥሮ የሚከሰተውን የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ለማስተካከል በሚደረግ ቀዶ ሕክምና ተጠቃሚ ይሆናሉ። አብዛኞቹ ውጤቶችም አስተማማኝ ፣ አስቀድሞ የሚገመቱ እና አርኪ ናቸው። ታድያ ለምንድነው ፍርሃት ውይይቱን የሚቆጣጠረው? ምክንያቱም አብዛኞቻችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተሳኩ ሕክምናዎችን አንመለከትም። የምናየው ጥቂት የተበላሹትን ብቻ ነው። በተለይም ዝነኛ ሰዎች ላይ የተደረጉትን ነው የምናስተውለው። ለምንድነው አንዳንድ ውጤቶች የሚበላሹት? የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ሁልጊዜ ስኬታማ ላይሆን ይችላል።  አብዛኛውን ጊዜ ውጤቱ ሳይሳካ የሚቀረው በግልጽ በሚታወቁ ስህተቶች ምክንያት ነው። ዋነኛ ምክንያቱ የባለሙያ ብቃት ማነስ ነው። ቀዶ ሕክምናው እውቅና በሌላቸው ቦታዎችና ልምድ በሌላቸው ሰዎች ሲከናወን አደጋው ከፍ ያለ ይሆናል። በተጨማሪም በአንድ የሰውነት ክፍል ላይ ደጋግሞ ቀዶ ሕክምና ማድረግ የሰውነት ሕብረ ሕዋሳትን (Tissue) ስለሚጎዳ፣ መልክን ከተፈጥሮአዊነት ውጭ እንዲዛባ ሊያደርገው ይችላል። የሆሊውድ ተዋናዩዋ አንጀሊና ጁሊን ለመምሰል ስትጣጣር የነበረችዋ ግለሰብ ከዚህም ባለፈ፣ የታካሚው የግል ሁኔታ ለውጤቱ መበላሸት ትልቅ ድርሻ አለው። ለምሳሌ ፦ እንደ ሲጋራ ማጨስ ያሉ ልማዶችና ስር የሰደዱ በሽታዎች ቁስሉ ቶሎ እንዳይድን እንቅፋት ይሆናሉ። እንዲሁም ከቀዶ ሕክምና በኋላ ሐኪሞች የሚሰጡትን የጥንቃቄ መመሪያ አለማክበር ለኢንፌክሽንና ለሌሎች ችግሮች ይዳርጋል። ይህም የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ከመጠን ያለፈ "ፍጹምነትን" ከሕክምናው መጠበቅ ለብስጭት ይዳርጋል። ምክንያቱም የሕክምናው ዓላማ ማሻሻል እንጂ ተአምር መፍጠር አይደለም። የስነ-ልቦናው ተጽዕኖ ምንድነው? የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከአካላዊ ለውጥ ባለፈ ጥልቅ የሆነ የስነ-ልቦና ፋይዳ አለው። ብዙ ታካሚዎች ከቀዶ ሕክምና በኋላ የተሻለ በራስ መተማመን እንደሚሰማቸውና በሰውነት ገጽታቸው ላይ ከፍተኛ እርካታ እንደሚያገኙ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ በዕለት ተዕለት ግንኙነታቸውና በሥራ ሕይወታቸው ላይ ደስተኛ እንዲሆኑና ጥራት ያለው ሕይወት እንዲመሩ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ሕክምና ው ሌላም ገጽታ አለው። አንዳንድ ጊዜ የቀዶ ሕክምናው መነሻ ምክንያት ከውስጣዊ ፍላጎት ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያና በሌሎች ተጽዕኖዎች የሚመጣ "የውበት መስፈርት" ሊሆን ይችላል። በተለይም የሰውነት ገጽታ ችግር (BDD) ያለባቸው ሰዎች፤ በሰውነታቸው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ቢደረግላቸው ሊረኩ አይችሉም። ስለዚህ ውጤቱ በቀዶ ሕክምና ው ላይ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው ባለው አመለካከት  ላይም ይወሰናል። ጥቅሞቹና ስጋቶቹ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከውበት ማማር ባለፈ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት በእጅጉ ያሻሽላል። በሕክምናው ረገድ ግልጽ የሆኑ ተግባራዊ ጥቅሞች አሉት፤ ለምሳሌ የአፍንጫ ቀዶ ሕክምና የተሻለ አተነፋፈስን ሲሰጥ፣ የጡት መቀነስ ቀዶ ሕክምና ደግሞ ለዓመታት የቆየን የጀርባ ሕመም በማቃለል የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲኖር ይረዳል። የአፍንጫ ማስተካከል ሕክምና ይሁን እንጂ የራሱ የሆኑ ስጋቶች እንዳሉትም መዘንጋት የለብንም። በጣም ጎበዝ በሚባሉ ሐኪሞች እጅ እንኳ እንደ ኢንፌክሽን፣ ደም መፍሰስ ወይም ከማደንዘዣ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ስጋቶች ቀድሞ ጥናት የተደረገባቸውና የሚታወቁ በመሆናቸው፤ ትክክለኛ የሕክምና መስፈርቶች በመከተልና ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል ይችላል። የኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ይመስላል? በኢትዮጵያም የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ዘርፍ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለና ትኩረት እየሳበ የመጣ የሕክምና ክፍል ነው። እስካሁን ድረስ ዘርፉ በብዛት የሚያተኩረው በመልሶ ግንባታ (Reconstructive) ሕክምናዎች ላይ ሲሆን፣ ይህም በአደጋ፣ በቃጠሎ ወይም በተፈጥሮ ችግሮች ለተጎዱ ወገኖች ትልቅ ተስፋ እየሆነ ይገኛል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ምክንያት ስለ መልክ ማሳመሪያ (Cosmetic) ቀዶ ሕክምና ያለው ግንዛቤና ፍላጎት በከተሞች አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። የዳሌ ማስተከከል ሕክምና ጥቂት የማይባሉ ታዋቂ ሰዎችም ውበት የማሳመሪያ ሕክምና ዎችን (ቦቶክስ፣ ብራዚሊያን በት ሊፍት፣ ወ.ዘ.ተ...) ከሀገር ውጭ ወጥተውም እያሰሩ ይገኛሉ። ሆኖም ግን አንዳንዶች የተሟላ መረጃ ስለሌላቸው ወይም አማራጭ በማጣታቸው ምክንያት፤ ውጭ አገርም ሄደው እንኳን እውቅና በሌላቸውና ደህንነታቸው ባልተረጋገጠ ቦታዎች ሕክምናን ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ብዙ ችግር አለው። እና... የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ጥሩ ነው ወይስ መጥፎ? የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ን "ጥሩ" ወይም "መጥፎ" ብሎ በአንድ ወገን መፈረጅ አይቻልም። ይልቁንም የሕክምናው ውጤትና ፋይዳ የሚወሰነው በታካሚው ፍላጎት፣ በባለሙያው ብቃት እና በሂደቱ ደህንነት ላይ ነው። በትክክልና አስፈላጊ ሆኖ ሲከናወን፣ የተጎዱ አካላትን በመጠገን ወይም በራስ መተማመንን በመጨመር የታካሚውን የሕይወት ጥራት በእጅጉ የሚያሻሽል ጠቃሚ ዘርፍ ነው። በአንፃሩ፣ ያለ በቂ ዝግጅት፣ ያለ ኃላፊነት ወይም አስፈላጊ ባልሆነ ሁኔታ በብቃት በሌላቸው ሰዎች ሲከናወን ግን ለከፋ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት የሚዳርግ ጎጂ ሂደት ሊሆን ይችላል። ዋናው ቁልፍ ነጥብ የቀዶ ሕክምና ውን ዓላማ በግልጽ ማወቅ እና ብቁ የሆነ ባለሙያ መምረጥ ላይ ነው። ከሕክምናው በፊት መጠየቅ የሚገባዎት 5 ጥያቄዎች የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ከመወሰንዎ በፊት፣ ሌላ ነገር ባያስታውሱ እንኳ እነዚህን አምስት ጥያቄዎች ራስዎን ይጠይቁ። ይህ በሕክምና ወይም በስነ-ልቦና ረገድ አስፈላጊ ነው? ሐኪሙ እውቅና ያለው እና ልምድ ያለው ነው? ተቋሙ በቂ ቁሳቁስ የተሟላለት ነው? ስጋቶቹን እና ገደቦቹን ተረድቻለሁ? ይህንን የማደርገው ለራሴ ነው ወይስ በውጫዊ ተጽዕኖ? ውሳኔዎት በፍርሃት ሳይሆን በእውቀት ላይ መመስረት አለበት።

bottom of page