top of page

የመርከብ ላይ ወረርሽኝ ፡ አለምን ያሳሰበው የሃንታ ቫይረስ (Hantavirus)

በፈረጆቹ የሜይ ወር መጀመሪያ አከባቢ ላይ ፤ በአዘቦት ጠዋት ላይ ኤም.ቪ ሆንድየስ (MV Hondius) የተባለችው የቅንጦት መዝናኛ መርከብ በኬፕ ቨርዴ የባህር ዳርቻ ላይ መልሕቋን ለመጣል ተገደደች።


ይህ በጉዞ ፕሮግራሟ ላይ አልነበረም። ከአርጀንቲና ተነስታ ወደ ካናሪ ደሴቶች 147 ተሳፋሪ ይዛ ፤ በመጓዝ ላይ የነበረችው የዚህች መርከብ ጉዞ፤ ባልታሰበ የህክምና ቀውስ ምክንያት ቅዠት ሆኖ አረፈው!



በመርከቧ ላይ አንድ ተሳፋሪ በድንገት ታመመ! ቀጥሎም ሌላኛው... ብዙም ሳይቆይ የታመሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጣ።


ያልታወቀ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የመተንፈስ ችግር እና ድንገተኛ የሞት ዜናዎች በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በስፋት መዘገብ ጀመሩ። በጥቂት ቀናት ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የበርካታ አገራት የጤና ተቋማት ቫይረሱ ያለባቸውን ተሳፋሪዎችና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት ደፋ ቀና ማለት ተያያዙት።


ይህ ድንገተኛ የህክምና አደጋ በኋላ ላይ የሃንታ ቫይረስ (Hantavirus) ወረርሽኝ መሆኑ ተረጋገጠ። በዚህም መርከቧና ተሳፋሪዎቿ የዓለም አቀፍ የጤና ምርመራ ማዕከል ሆኑ።



እስከ ዛሬዋ ግንቦት 2 2018 ዓ.ም ድረስ ፤ የዓለም ጤና ድርጅት እና የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ከዚሁ መርከብ ጋር የተያያዙ ቢያንስ ስምንት ታማሚዎችን( 6 የተረጋገጡ እና 2 የተጠረጠሩ) እና ሶስት አሳዛኝ የሞት አደጋዎችን በቅርበት እየተከታተሉ ይገኛሉ።


የመርከቧን ተሳፋሪዎች ከመርከቧ የማወረድ ሥራ እየተከናወነ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አንድ ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም፦


ለመሆኑ ሃንታ ቫይረስ ምንድን ነው? ልንሰጋስ ይገባናል?

ለመሆኑ ሃንታ ቫይረስ ምንድን ነው?


ሃንታ ቫይረስ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ወይም ኮቪድ-19 አይደለም፤ የሃንታ ቫይረሶች በተለምዶ በሰዎች መካከል በስፋት አይሰራጩም። ይህ የቫይረስ ዝርያ በዋነኝነት እንደ አይጥ ባሉ አጥቢ እንስሳት የሚተላለፍ ሲሆን፤ ከሌሎች ቫይረሶች የሚለየውም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ "ዙኖቲክ" (zoonotic) በሽታ በመሆኑ ነው።



በሳይንሳዊው ዓለም የሃንታ ቫይረሶች በሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ይከፈላሉ፦

  • የድሮው ዓለም (Old World) ሃንታ ቫይረሶች፦ በአብዛኛው በአውሮፓ እና በእስያ የሚገኙ ሲሆኑ፤ ኩላሊትን የሚያጠቃ ከባድ የጤና እክል (HFRS) ያስከትላሉ።

  • የአዲሱ ዓለም (New World) ሃንታ ቫይረሶች፦ በአሜሪካ አህጉር የሚገኙ ሲሆን፤ ሳምባን በፈሳሽ እንዲሞላ በማድረግ የመተንፈሻ አካላትን ክፉኛ የሚያጠቁ (HCPS) ናቸው።


እንደ ሮይተርስ (Reuters) ዘገባ ከሆነ፤ በኤም.ቪ ሆንድየስ መርከብ ላይ የተከሰተው ወረርሽኝ "አንዴስ ቫይረስ" (Andes virus) የተባለው የአዲሱ ዓለም የቫይረስ ቡድን አባል ነው። በአንዳንድ ጥናቶች እና የCDC መረጃዎች መሰረት ፤ ይህ አስፈሪ የቫይረስ ዝርያ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 50% የሚደርሱ ታማሚዎችን ለሞት ይዳርጋል።

ቫይረሱ እንዴት ይሰራጫል?



ለሃንታ ቫይረስ ለመጋለጥ የግድ በመርከብ ላይ መሆን አያስፈልግዎትም፤ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በሚተነፍሱት አየር አማካኝነት ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ። የቫይረሱ ዋነኛ የመተላለፊያ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፦


  • በአየር መበከል (Aerosolization)፦ የአይጥ ሽንት፣ እዳሪ፣ ወይም የአይጥ መኖሪያ ስፍራዎች በሚነኩበት ጊዜ፤ ቫይረሱ በአይን በማይታዩ ብናኞች አማካኝነት ወደ አየር ይገባል። እነዚህ በአየር ላይ የሚንሳፈፉ ጥቃቅን ጠብታዎች ወደ ውስጥ ሲተነፈሱ ቫይረሱን ያስተላልፋሉ።

  • አካባቢን በማጽዳት ወቅት፦ አቧራማ የሆኑና አይጥ የሚኖርባቸውን ስፍራዎች ሲጠርጉ ወይም ሲያጸዱ የሚፈጠረው ብናኝ፤ ቫይረሱን በአጋጣሚ ወደ ውስጥ ለመተንፈስ ሰፊ ዕድል ይሰጣል፤ በዚህም ቫይረሱ በትንፋሽ አማካኝነት ወደ ሰውነት ይገባል።

  • ቀጥተኛ ንክኪ፦ ምንም እንኳን አልፎ አልፎ የሚከሰት ቢሆንም፤ በአይጥ ንክሻ አልያም በአይጥ እዳሪና ሽንት የተበከሉ ነገሮችን ነክቶ አፍን፣ አፍንጫን፣ ወይም አይንን በመንካት ሊተላለፍ ይችላል።


ታድያ የአሁኑን ወረርሽኝ የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው?

አብዛኞቹ የሃንታ ቫይረሶች በሰዎች መካከል በቀላሉ አይተላለፉም፤ ወረርሽኞች በታሪክ ተወስነው የቆዩትም በዚህ ምክንያት ነው።



ነገር ግን የአሁኑ ወረርሽኝ መነሻ የሆነው የአንዴስ ቫይረስ (Andes virus)፤ ለረጅም ጊዜ በሚቆይ የቅርብ ንክኪ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ውስን ችሎታ አለው። ይህ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድል፤ ለቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት ተጨማሪ አቅም ሰጥቶታል።


ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ደጋግመው እንደሚያሳስቡት፤ ይህ ቫይረስ እንደ ኮቪድ-19 በአየር ላይ በቀላሉ አይተላለፍም። ይልቁንም ስርጭቱ ጥብቅና የቅርብ ንክኪን ይጠይቃል። ይህንን ልዩነት በሚገባ መገንዘብ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ተገቢውን ጥንቃቄ እንድናደርግ ይረዳናል።


በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ምን ዓይነት ምልክቶችን መከታተል አለብን?



የሃንታ ቫይረስ ፈታኝነቱ መጀመሪያ ላይ እንደ ተራ ጉንፋን መምሰሉ ነው። ምልክቶቹ ከቫይረሱ ጋር ከተገናኙ ከ1 እስከ 8 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ። በሽታው ሁለት ደረጃዎች አሉት፦


  • የመጀመሪያ ደረጃ (ከ1-5 ቀናት)፦ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የጡንቻ ሕመም (በተለይ በጭን፣ በወገብ፣ እና በጀርባ ጡንቻዎች)፣ ድካም፣ እና ራስ ምታት ሊሰማ ይችላል።

  • በሽታው እየጸና ሲሄድ፦ ቫይረሱ እየገፋ ሲሄድ ታካሚዎች ድንገተኛ የትንፋሽ እጥረት እና የማያቋርጥ ሳል ያጋጥማቸዋል። ይህም የአዲሱ ዓለም የሃንታ ቫይረስ የሳምባ ሕመም (Pulmonary Syndrome) ዋና መለያ ምልክት ነው።


እንደ ሲ.ዲ.ሲ (CDC) መረጃ፤ ለዚህ የሳምባ ችግር ከሚጋለጡ 10 ሰዎች መካከል እስከ 4 የሚሆኑት ፈጣን የሕክምና እርዳታ ካላገኙ ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል።


ሕክምናውስ ምንድን ነው?

ለሃንታ ቫይረስ እስካሁን ድረስ የተለየ ክትባት ወይም መድኃኒት የለም። ሕክምናው ሙሉ በሙሉ በሆስፒታል ውስጥ በሚደረግ የድጋፍ ክትትል ላይ የተመሠረተ ነው። ለዚህም መከላከል የተሻለው የህክምና አማራጭ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።



ለዚህም ወረርሽኝ ፤ እጅጉን ውጤታማ የሆኑት የመከላከያ መንገዶችም እጅጉን ቀላል ናቸው።


  • አይጦች ካሉባቸው አካባቢዎች ራስዎን ያርቁ።

  • አይጦች ወደ ቤትዎ ወይም መጋዘንዎ የሚገቡባቸውን ቀዳዳዎች በሽቦ ወይም በሲሚንቶ ይዝጉ።

  • አቧራማ መጋዘኖችን ወይም የተተዉ ክፍሎችን ሲያጸዱ፤ መስኮት ይክፈቱ። አየር እንዲገባ ያድርጉ። ብናኝ እንዳይተነፍሱ የመከላከያ ማስኮችን(ቁሶችን) መጠቀም አስፈላጊ ነው።

  • ደረቅ የአይጥ እዳሪን በፍጹም አይጥረጉ። ይልቁንም አካባቢውን በበረኪና ለ5 ደቂቃ ያርጥቡትና ከዚያ በእርጥብ ጨርቅ ያጽዱት።

  • ለረጅም ጊዜ ተዘግቶ የቆየ ክፍል ውስጥ ከመግባትዎ በፊት ለ30 ደቂቃ ያህል መስኮትና በሮችን ከፍቶ አየር እንዲገባ ያድርጉ!


የጤና መረጃዎችን ይከታተሉ!



የኤም.ቪ ሆንድየስ መርከብ በካናሪ ደሴቶች በለይቶ ማቆያ ስር በምትገኝበት በዚህ ወቅት፤ የጤና ተቋማት ወረርሽኙ በሰፊው ሕዝብ ላይ ስጋት የመፍጠር ዕድሉ አነስተኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።


ሆኖም ጉዞና እንቅስቃሴ ባልተገደበባት ዓለማችን፤ አዳዲስ ዜናዎችን በንቃት መከታተልና ስለመከላከያ እርምጃዎች የሚወጡ መረጃዎችን መከተል የመጀመሪያው የመከላከያ እርምጃ ነው።


አቧራማ ቦታዎችን ካጸዱ በኋላ፤ ከአይጦች ጋር ንክኪ ኖሮዎት ድንገተኛ ትኩሳት ወይም የመተንፈስ ችግር ካጋጠመዎት፤ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ይሂዱ።


ዘወትር የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን መመሪያ ይከተሉ!

Comments


bottom of page