ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና : ጥሩ ወይስ መጥፎ
- Zebeaman Tibebu
- 2 days ago
- 5 min read
“ያቺን ዝነኛ ሰው አየሃት? ፊቷ ምን እንደሆነ?”
ይህ አብዝተን የምንሰማው አረፍተ ነገር እየሆነ መጥቷል። በኢትዮጵያም ጥቂት የማይባሉ ታዋቂ ግለሰቦች ከንፈር ከማስተካከል፣ ወገብ ከማጥበብ ፣ ውፍረት ከማጥፋት እስከ ዳሌ ማሳደጊያ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና እንዳደረጉ በገሀድ ይታወቃል።

ታድያ ግን ድንገት ከታሰበው ይልቅ መልክ ሲቀይር ወይም.... አንዳንዴም በሚያስደነግጥ መልኩ ሲለወጥ... ወዲያውኑ አንድ መደምደሚያ ላይ ይደረሳል፦
👉 “የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና አደገኛ ነው።”
👉 “ሰውነትን ያበላሻል።”
ግን እውነቱ ይሄ ብቻ ነው?
ወይስ በጥቂት የሚታዩ ውጤቶች ላይ በመመስረት አንድን ሙሉ የሕክምና ዘርፍ እየፈረድን ነው?
እስቲ ረጋ ብለን ከፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ጀርባ ያለውን ሳይንስ፣ ቁጥሮች እና እውነታውን እንመርምር።
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ታሪክ
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ታሪክ ከ4,000 ዓመታት በፊት የጀመረ መሆኑን ያውቃሉ?
ታሪኩ የሚጀምረው በጥንታዊት ህንድ (በ600 ዓመተ ዓለም ገደማ) ሲሆን፣ በወቅቱ "የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አባት" ተብሎ የሚጠራው ሱሽሩታ (Sushruta) የተባለ ሐኪም በአደጋ ወይም በቅጣት ምክንያት አፍንጫቸው ለተቆረጠ ሰዎች አዲስ አፍንጫ ለመስራት የሚያስችል ብልህ ዘዴ ፈጠረ። ይህም ዘዴ ከታካሚው ግንባር ላይ ቆዳን በመቁረጥና ወደ አፍንጫው አካባቢ በማዞር አዲስ ቅርጽ መስጠት ሲሆን፤ ይህ የ"ቆዳ ንቅለ ተከላ" (Skin Grafting) መሠረታዊ መርህ ዛሬም ድረስ በዘመናዊ የሕክምና ክፍሎች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል።

ይሁን እንጂ በመካከለኛው ዘመን አከባቢ ፤ በአውሮፓ የሰውን አካል መለወጥ እንደ "ኃጢአት" ተቆጥሮ ፤ ዘርፉ ለዘመናት ተዳክሞ ነበር። በኋላ ግን እንደ ጋስፓሬ ታግሊያኮዚ ያሉ ሐኪሞች የፕላስቲክ ስርጀሪን ምህዳር ሊለውጡ ችለዋል።
የዚህ ዘርፍ እውነተኛው "ወርቃማ ዘመን" የመጣው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በነበረው አስከፊ ሁኔታ ነው። በጦርነቱ ወቅት በከባድ መሣሪያዎች ፊታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ፤ገጽታቸው የተለወጠባቸው ወታደሮች ነበሩ። እነኝህ ወታደሮች ቢተርፉም ፤ መልካቸው የጦርነቱ ሰለባ ነበር። አብሮም ማንነታቸውና ሰብዓዊ ክብራቸው ፈርሶ ነበር። በዚህ ወቅት ሰር ሃሮልድ ጊሊስ (Sir Harold Gillies) የተባሉ አርቆ አሳቢ ሐኪም የሺዎችን ፊትና ማንነት መልሶ መገንባት ጀመሩ።

ከጦርነቱ በኋላ የጸረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶችና ማደንዘዣዎች መዘመን ሕክምናውን ይበልጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን አደረገው። ወታደሮችን ለመጠገን ይውሉ የነበሩት እነኛ ዘዴዎችም ወደ ተራው ሕዝብ በመሸጋገራቸው የዛሬው የውበት ቀዶ ሕክምና እንዲፈጠር ምክንያት ሆኑ። በአሁኑ ጊዜ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና በጥንታዊ ጥበብና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተመስርቶ በሳይንስ ተደግፎ የብዙዎችን ህይወት እየለወጠ ይገኛል ።
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ስለ ውበት ብቻ አይደለም
ብዙ ጊዜ ሲነሳ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከውበት ጋር ተያያዥነት አለው። እርሶም ፕላስቲክ ስርጀሪ ሲባል የሚመጣልዎት የሆሊውድ አርቲስት ይሆናል። የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ግን ይህ ብቻ አይደለም።ይህ ዘርፍ በአንድ የሰውነት ክፍል ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ድረስ ያለውን ማንኛውንም የሰውነት ክፍል ሊያካትት ይችላል።
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና የሰውን አካል መልሶ ለመገንባት፣ ለመጠገን ወይም ቅርፅን ለማስተካከል የሚረዳ የሕክምና ዘርፍ ነው። "ፕላስቲክ" የሚለው ቃል የመጣውም "መቅረጽ" ወይም "ማስተካከል" ከሚለው የግሪክ ቃል ነው። ዋና ዓላማው ከአደጋ፣ ከበሽታ ወይም ከተፈጥሮ ጉድለት የተነሳ የተጎዱ የሰውነት ክፍሎችን ወደ ነበሩበት መመለስ ነው።

ይህ የሕክምና ዘርፍ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል። እነሱም መልሶ የመገንባት (Reconstructive) እና የውበት (Cosmetic) ቀዶ ሕክምና ናቸው። መልሶ የመገንባት ቀዶ ሕክምና የሚደረገው በተፈጥሮ ጉድለት (ለምሳሌ እንደ ከንፈር መሰንጠቅ አይነት)፣ በአደጋ፣ በቃጠሎ ወይም በካንሰር ምክንያት የተጎዱ የሰውነት ክፍሎችን ተግባር እና ገጽታ ለማስተካከል ነው። ይህ ዓይነቱ ሕክምና የታካሚውን ጤና እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማሻሻል የሚደረግ ነው።
በሌላ በኩል የውበት ቀዶ ሕክምና የሚከናወነው፤ የአንድን ሰው ውጫዊ ገጽታ ይበልጥ ለማሳመር ነው። ይህ የሚደረገው በትክክል በሚሰሩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ነው። ዓላማውም አፍንጫን ለማስተካከል፣ የፊት መጨማደድን ለማስወገድ ወይም የሰውነት ቅርጽን ለማስተካከል፣ ወ.ዘ.ተ... ነው። ይህ በርካታ ዓይነቶች ያሉት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እንደ የዳሌ ቅርጽ ማስተካከያ (BBL) እና የጡት ማሳደግ (Breast Augmentation) ያሉ የውበት ማሻሻያዎች በስፋት ከሚከናወኑት መካከል ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ የተለመዱ ሂደቶች ባለፈ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች እጅግ በጣም ልቅ እና ያልተለመዱ የሰውነት ለውጦችም ሊደረጉ ይችላሉ።

ቁጥሮቹ ምን ይናገራሉ?
በአሁኑ ወቅት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ዘርፍ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ሲሆን፤ በ2024 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 38 ሚሊዮን የሚሆኑ የሕክምና ሂደቶች ተከናውነዋል። ከታካሚዎች መካከል 85.5% የሚሆኑት ሴቶች ቢሆኑም፣ የወንዶችም ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። በተለይም ከ18-34 ዓመት ያሉ ወጣቶች ለአፍንጫ እና ለጡት ቅርጽ ማስተካከል ቅድሚያ ሲሰጡ፤ ዕድሜያቸው ከ35 በላይ የሆኑት ደግሞ እንደ ቦቶክስ ያሉ የፊት ማደስ ሕክምናዎችን በስፋት ይመርጣሉ።

ከውበት ማሻሻያ ጎን ለጎን፣ የመልሶ ግንባታ ቀዶ ሕክምናም በብዛት እየተከናወነ ይገኛል። በየዓመቱ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ዕጢ/ካንሰር ማስወገድ ሂደቶች ይከናወናሉ። እነኚህም በተለይ የቆዳ ካንሰርን ለማከም የሚደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ናቸው። ከ150,000 በላይ ሴቶች ደግሞ ከካንሰር በኋላ የጡት መልሶ ግንባታ ሕክምና ያገኛሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትም በተፈጥሮ የሚከሰተውን የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ለማስተካከል በሚደረግ ቀዶ ሕክምና ተጠቃሚ ይሆናሉ።
አብዛኞቹ ውጤቶችም አስተማማኝ ፣ አስቀድሞ የሚገመቱ እና አርኪ ናቸው።
ታድያ ለምንድነው ፍርሃት ውይይቱን የሚቆጣጠረው?
ምክንያቱም አብዛኞቻችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተሳኩ ሕክምናዎችን አንመለከትም። የምናየው ጥቂት የተበላሹትን ብቻ ነው። በተለይም ዝነኛ ሰዎች ላይ የተደረጉትን ነው የምናስተውለው።
ለምንድነው አንዳንድ ውጤቶች የሚበላሹት?
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ሁልጊዜ ስኬታማ ላይሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ውጤቱ ሳይሳካ የሚቀረው በግልጽ በሚታወቁ ስህተቶች ምክንያት ነው። ዋነኛ ምክንያቱ የባለሙያ ብቃት ማነስ ነው። ቀዶ ሕክምናው እውቅና በሌላቸው ቦታዎችና ልምድ በሌላቸው ሰዎች ሲከናወን አደጋው ከፍ ያለ ይሆናል። በተጨማሪም በአንድ የሰውነት ክፍል ላይ ደጋግሞ ቀዶ ሕክምና ማድረግ የሰውነት ሕብረ ሕዋሳትን (Tissue) ስለሚጎዳ፣ መልክን ከተፈጥሮአዊነት ውጭ እንዲዛባ ሊያደርገው ይችላል።

ከዚህም ባለፈ፣ የታካሚው የግል ሁኔታ ለውጤቱ መበላሸት ትልቅ ድርሻ አለው። ለምሳሌ ፦ እንደ ሲጋራ ማጨስ ያሉ ልማዶችና ስር የሰደዱ በሽታዎች ቁስሉ ቶሎ እንዳይድን እንቅፋት ይሆናሉ። እንዲሁም ከቀዶ ሕክምና በኋላ ሐኪሞች የሚሰጡትን የጥንቃቄ መመሪያ አለማክበር ለኢንፌክሽንና ለሌሎች ችግሮች ይዳርጋል። ይህም የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ያደርጋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ከመጠን ያለፈ "ፍጹምነትን" ከሕክምናው መጠበቅ ለብስጭት ይዳርጋል። ምክንያቱም የሕክምናው ዓላማ ማሻሻል እንጂ ተአምር መፍጠር አይደለም።
የስነ-ልቦናው ተጽዕኖ ምንድነው?
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከአካላዊ ለውጥ ባለፈ ጥልቅ የሆነ የስነ-ልቦና ፋይዳ አለው። ብዙ ታካሚዎች ከቀዶ ሕክምና በኋላ የተሻለ በራስ መተማመን እንደሚሰማቸውና በሰውነት ገጽታቸው ላይ ከፍተኛ እርካታ እንደሚያገኙ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ በዕለት ተዕለት ግንኙነታቸውና በሥራ ሕይወታቸው ላይ ደስተኛ እንዲሆኑና ጥራት ያለው ሕይወት እንዲመሩ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።

ይሁን እንጂ ሕክምናው ሌላም ገጽታ አለው። አንዳንድ ጊዜ የቀዶ ሕክምናው መነሻ ምክንያት ከውስጣዊ ፍላጎት ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያና በሌሎች ተጽዕኖዎች የሚመጣ "የውበት መስፈርት" ሊሆን ይችላል። በተለይም የሰውነት ገጽታ ችግር (BDD) ያለባቸው ሰዎች፤ በሰውነታቸው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ቢደረግላቸው ሊረኩ አይችሉም። ስለዚህ ውጤቱ በቀዶ ሕክምናው ላይ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው ባለው አመለካከት ላይም ይወሰናል።
ጥቅሞቹና ስጋቶቹ
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከውበት ማማር ባለፈ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት በእጅጉ ያሻሽላል። በሕክምናው ረገድ ግልጽ የሆኑ ተግባራዊ ጥቅሞች አሉት፤ ለምሳሌ የአፍንጫ ቀዶ ሕክምና የተሻለ አተነፋፈስን ሲሰጥ፣ የጡት መቀነስ ቀዶ ሕክምና ደግሞ ለዓመታት የቆየን የጀርባ ሕመም በማቃለል የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲኖር ይረዳል።

ይሁን እንጂ የራሱ የሆኑ ስጋቶች እንዳሉትም መዘንጋት የለብንም። በጣም ጎበዝ በሚባሉ ሐኪሞች እጅ እንኳ እንደ ኢንፌክሽን፣ ደም መፍሰስ ወይም ከማደንዘዣ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ስጋቶች ቀድሞ ጥናት የተደረገባቸውና የሚታወቁ በመሆናቸው፤ ትክክለኛ የሕክምና መስፈርቶች በመከተልና ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል ይችላል።
የኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ይመስላል?
በኢትዮጵያም የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ዘርፍ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለና ትኩረት እየሳበ የመጣ የሕክምና ክፍል ነው። እስካሁን ድረስ ዘርፉ በብዛት የሚያተኩረው በመልሶ ግንባታ (Reconstructive) ሕክምናዎች ላይ ሲሆን፣ ይህም በአደጋ፣ በቃጠሎ ወይም በተፈጥሮ ችግሮች ለተጎዱ ወገኖች ትልቅ ተስፋ እየሆነ ይገኛል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ምክንያት ስለ መልክ ማሳመሪያ (Cosmetic) ቀዶ ሕክምና ያለው ግንዛቤና ፍላጎት በከተሞች አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።

ጥቂት የማይባሉ ታዋቂ ሰዎችም ውበት የማሳመሪያ ሕክምናዎችን (ቦቶክስ፣ ብራዚሊያን በት ሊፍት፣ ወ.ዘ.ተ...) ከሀገር ውጭ ወጥተውም እያሰሩ ይገኛሉ። ሆኖም ግን አንዳንዶች የተሟላ መረጃ ስለሌላቸው ወይም አማራጭ በማጣታቸው ምክንያት፤ ውጭ አገርም ሄደው እንኳን እውቅና በሌላቸውና ደህንነታቸው ባልተረጋገጠ ቦታዎች ሕክምናን ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ብዙ ችግር አለው።
እና... የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ጥሩ ነው ወይስ መጥፎ?
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናን "ጥሩ" ወይም "መጥፎ" ብሎ በአንድ ወገን መፈረጅ አይቻልም። ይልቁንም የሕክምናው ውጤትና ፋይዳ የሚወሰነው በታካሚው ፍላጎት፣ በባለሙያው ብቃት እና በሂደቱ ደህንነት ላይ ነው።

በትክክልና አስፈላጊ ሆኖ ሲከናወን፣ የተጎዱ አካላትን በመጠገን ወይም በራስ መተማመንን በመጨመር የታካሚውን የሕይወት ጥራት በእጅጉ የሚያሻሽል ጠቃሚ ዘርፍ ነው። በአንፃሩ፣ ያለ በቂ ዝግጅት፣ ያለ ኃላፊነት ወይም አስፈላጊ ባልሆነ ሁኔታ በብቃት በሌላቸው ሰዎች ሲከናወን ግን ለከፋ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት የሚዳርግ ጎጂ ሂደት ሊሆን ይችላል።
ዋናው ቁልፍ ነጥብ የቀዶ ሕክምናውን ዓላማ በግልጽ ማወቅ እና ብቁ የሆነ ባለሙያ መምረጥ ላይ ነው።
ከሕክምናው በፊት መጠየቅ የሚገባዎት 5 ጥያቄዎች
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ከመወሰንዎ በፊት፣ ሌላ ነገር ባያስታውሱ እንኳ እነዚህን አምስት ጥያቄዎች ራስዎን ይጠይቁ።
ይህ በሕክምና ወይም በስነ-ልቦና ረገድ አስፈላጊ ነው?
ሐኪሙ እውቅና ያለው እና ልምድ ያለው ነው?
ተቋሙ በቂ ቁሳቁስ የተሟላለት ነው?
ስጋቶቹን እና ገደቦቹን ተረድቻለሁ?
ይህንን የማደርገው ለራሴ ነው ወይስ በውጫዊ ተጽዕኖ?
ውሳኔዎት በፍርሃት ሳይሆን በእውቀት ላይ መመስረት አለበት።





Comments