top of page

ሙዚቃ እና ጤና

ሙዚቃ የሚወዱ ሰዎችን “ለምን ትወዳላችሁ?” ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? ምናልባት መልሱ በቃላት የሚገለጽ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ገና አፉን ያልፈታ ሕፃን ልጅ የሚመስጥ ዜማ ሲሰማ በደስታ ሲወዛወዝ ካስተዋሉ፣ ነገሩ ከፍላጎት በላይ የሆነ የተፈጥሮ ምስጢር እንዳለው ይረዱታል።

ለመሆኑ ይህ ስሜት ከየት የመጣ ነው?

በመንገድ ሲጓዙ መኪናዎች ጩኸትና በሰዎች ጨዋታ ፣ በእለት ተእለት ሁካታ መካከል፣ ከሩቅ የሚሰማ የሙዚቃ ድምጽ ድንገት ጆርዎ ውስጥ ጥልቅ ይላል። በዚያች ቅጽበት ሳይታወቅዎት የልብ ትርታዎ ይረጋጋል፣ ትከሻዎ ይላላል፣ እናም አንድ ዓይነት የሰላም ስሜት በሰውነትዎ ላይ ይሰፍናል። አንዳንዴም ውስጥዎ ብዙ ስሜትን ይቀሰቅሳል።

ይህ ዝም ብሎ የፈጠራ “ስሜት” ብቻ እንዳይመስልዎት። ይህ ከጆሮዎ አልፎ በጠቅላላው የባዮሎጂ ሥርዓትዎ ውስጥ የሚከናወን ውስብስብ ሳይንሳዊ ሂደት ነው።

እስቲ በጥልቀት እንመልከተው።


ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው የተቀናጁ ድምጾች (Rhythm and Melody) በሰውነታችን ላይ ስለሚያመጡት ቀጥተኛ ባዮሎጂያዊ ለውጥ እንጂ፣ ዓለማዊ ሙዚቃን ወይም መንፈሳዊ መዝሙርን ለመደገፍ ወይም ለመቃወም የቀረበ አይደለም። 

አእምሮዎ ለሙዚቃ ለምን "ይጓጓል"?


የሙዚቃ ጉዞ የሚጀምረው በጆሮዎ ቢሆንም፣ መጨረሻው ግን እዚያ አይደለም። የዜማው ድምፅ የአንጎልዎ የድምፅ መቀበያ ክፍል (Auditory Cortex) እንደደረሰ፣ በፍጥነት ወደ ቀሪው የአንጎልዎ ክፍል በፍጥነት ይሰራጫል።


ታድያ የሚወዱትን የሙዚቃ ምት ሲሰሙ የአንጎልዎ የደስታ ማዕከል (Ventral Striatal Network) በድንገት በ "ዶፓሚን ማዕበል" ይሞላል። ዶፓሚን ማለት አእምሯችን በስኬታችን ወቅት የሚያመርተው መልካም ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ የተፈጥሮ ሽልማት ነው።


ኔቸር ኒውሮሳይንስ የተባለው ታዋቂ የሳይንስ መጽሔት የተለቀቀ አንድ ጥናትዊ ጽሁፍ ሙዚቃ እንደ ምግብ ወይም እንደ ጥልቅ የፍቅር ቅርርብ ያሉ ለሰው ልጅ መትረፍ (Survival) አስፈላጊ የሆኑ ስሜቶች የሚመነጩበትን ያአእምሮ ክፍል ያነቃቃክ። ይህም ሙዚቃ ለሰው ልጅ ዝም ብሎ መዝናኛ ሳይሆን፣ ለአእምሮአችን መልካም ፋይዳ ያለው አስፈላጊው ግብዓት መሆኑን ይጠቁማል።


ከዚህም በላይ፣ ሙዚቃ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የጭንቀት ሆርሞን (Cortisol) እስከ 25% ድረስ የመቀነስ አቅም አለው። በዚህ ፈጣንና ውጥረት በበዛበት ዓለም ውስጥ፣ ሙዚቃ ለአእምሯችን እንደ "ማደሻ ቁልፍ" (Reset Button) በመሆን ውስጣዊ ሰላማችንን ይመልስልናል።


ሙዚቃ የልብ ትርታን ይቃኝ ይሆን?

ለመሆኑ አንድ ዜማ እንደ ማረጋጊያ መድኃኒት ሊያገለግል ይችላል? ለብዙዎቻችን ጥያቄው የሚከብድ ቢመስልም፣ የሕክምና ሳይንስ ግን ምላሹን በአጭር ቃል “አዎ!” ብሎታል።



ጃማ ኢንተርናል ሜዲሲን (JAMA Internal Medicine) የተባለው የሕክምና መጽሔት ባወጣው ጥናት መሠረት፣ በደቂቃ ከ60 እስከ 80 የሚመታ (BPM) ሙዚቃ በአካላችን ላይ አስደናቂ ተጽዕኖ አለው። ይህ የሙዚቃ ምት ካረፈ የሰው ልጅ የልብ ትርታ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ፣ ልባችን ራሱን ከዜማው ጋር ለማመሳሰል ይሞክራል።


ይህ “ተፈጥሯዊ ቅኝት” በሰውነታችን ውስጥ የሚከተሉትን ለውጦች ያመጣል፦

  • የደም ግፊት መረጋጋት፦ የሙዚቃው ምት የላይኛውን የደም ግፊት (Systolic) ዝቅ እንዲል በማድረግ የደም ሥሮችን ውጥረት ያላላል።

  • የልብ ምት ስምምነት፦ ልብዎ ቃል በቃል ከሚሰሙት ዜማ ጋር አብሮ ለመራመድ ይሞክራል፤ ሙዚቃው ሲረጋጋ ልብዎም አብሮ ይረጋጋል።

  • ውጤቱ፦ ይህ ሂደት በልብ ላይ የሚደርሰውን አላስፈላጊ ጫና ይቀንሳል። ይህም በተለይ የደም ግፊት ላለባቸው ወይም ከልብ ሕመም ለሚያገግሙ ወገኖቻችን ሙዚቃን ታማኝ የጤና አጋር ያደርገዋል።

ባጭሩ፣ ሙዚቃ ለጆሮ የሚቀርብ ድምፅ ብቻ ሳይሆን፣ ለልባችን መልካም ጠቀሜታ ያለው ነው ማለት ነው።


ተፈጥሯዊ የህመም ማስታገሻ

በሕክምና ሳይንስ ውስጥ ካሉት እጅግ አስደናቂ ግኝቶች አንዱ “በሙዚቃ የሚመጣ የህመም ማስታገሻ” (Music-Induced Analgesia) ነው። ይህ ዝም ብሎ የሰዎች ግምት አይደለም፤ ዘ ላንሴት (The Lancet) የተባለው ታዋቂ የሕክምና መጽሔት ከ70 በላይ ጥናቶችን አጠቃሎ ባቀረበው ማስረጃ መሠረት፣ ከቀዶ ጥገና በፊትም ሆነ በኋላ ሙዚቃ ያዳመጡ ታካሚዎች ከሌሎቹ በበለጠ የህመም ስሜታቸው እንደቀነሰና ፈጣን ማገገም እንዳሳዩ አረጋግጧል።

ለመሆኑ ሙዚቃ እንዴት ነው ህመምን የሚያታግሰው?

ምስጢሩ “የህመም ቁጥጥር በር” (Gate Control Theory) በሚባለው ሳይንሳዊ ሂደት ውስጥ ይገኛል። አእምሯችን ወደ እሱ የሚመጡትን መረጃዎች የሚያስተናግድበት ውስን አቅም አለው። የሚመስጥ ዜማ ስንሰማ፣ አእምሯችን በሚያስደስት የድምፅ ማነቃቂያ ይሞላል። በዚህ ጊዜ ህመምን ወደ አእምሮ የሚወስዱት የነርቭ መንገዶች “ይጨናነቃሉ”። የዚህን ጊዜ የትኩረት ሽሚያ ይኖራል። አእምሮዎም በህመሙ ፋንታ በዜማው ላይ እንዲያተኩር ይገደዳል። ደስ የሚለው ድምፅ የአንጎልዎን የትኩረት በር ስለሚቆጣጠረው፣ የህመም ምልክቶች በቀላሉ ሰርገው መግባት አይችሉም።


ለዚህም ለተለያየ ህመም ጊዜ የሚወዱትን ሙዚቃ መክፈት የህመም ማስታገሻ የመውሰድ ፍላጎትዎን በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስልዎት ይችላል።

ሙዚቃ ያለ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት፣ አእምሮዎ ህመምን በራሱ መንገድ እንዲቋቋም የሚያደርግ ተፈጥሯዊ ስጦታ ነው።

የትዝታ ካዝና

ሙዚቃ በሕክምና ረገድ ትልቁን ተአምር የሚሠራው እንደ አልዛይመር ባሉ የመርሳት በሽታዎች ላይ ነው። እስቲ ያስቡት...አንድ የሚወዱት ቤተሰብዎ ፤ በጊዜው ውስጥ ማንነትዎንና የቆዩ ትዝታዎችን ሲረሳ ማየት እንዴት ይከብዳል?ለአንዳንዶችም የሚሰብር ነው።

ሆኖም ሳይንስ አንድ ተስፋ ሰጪ ምስጢር ይነግረናል!

የሰው ልጅ ትዝታዎች ሁሉ ቢጠፉም፣ የሙዚቃ ትዝታ ግን በአእምሮአችን ውስጥ “ባለቤት” የለውም። የነርቭ ሳይንስ መጽሐፍት እንደሚያረጋግጡት፣ የሙዚቃ ትዝታ የሚቀመጠው “ሂፖካምፓስ” (Hippocampus) በሚባለውና በመርሳት በሽታ የመጨረሻ ደረጃ ላይ በሚጠቁት የአንጎል ክፍሎች ውስጥ ነው።


ይህም ሁለት ታላላቅ መልካም ጎኖች አሉት፦

  • ድንገተኛው መንቃት፦ ለብዙ ጊዜ መናገር ያልቻሉ ወይም ለአካባቢያቸው ምላሽ መስጠት ያቆሙ አባቶችና እናቶች፣ የልጅነት ዘፈኖቻቸውን ወይም የድሮ መዝሙሮቻቸውን ሲሰሙ ድንገት አብረው መዘመር ሲጀምሩ ይታያሉ። ሙዚቃ በመርሳት በሽታ የተዘጋውን የአእምሮ በር የሚከፍት ብቸኛ ቁልፍ ይሆን?


  • የአእምሮ ጥንካሬ፦ አንድ የሙዚቃ መሣሪያ መለማመድ ወይም በዝማሬ ውስጥ መሳተፍ የአንጎል ራሱን የማደስ ብቃት (Neural Plasticity) ያሳድጋል። ይህም እርጅና በአእምሯችን ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚችል ጠንካራና “ወጣት” አእምሮ እንዲኖረን ያደርጋል።


በአጭሩ፣ ዜማዎች በአእምሮአችን ውስጥ የታተሙ የትዝታ አሻራዎች ናቸው፤ ዕድሜም ሆነ በሽታ በቀላሉ ሊያጠፋቸው የማይችሉ ታማኝ ምስክሮች ይሆናሉ።


ሙዚቃ ለበሽታ መከላከል አቅም

ሙዚቃ በእርግጥ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም ሊያጠናክር ይችላል?

ሳይንሱ ያለ ምንም ማመንታት ምላሹን "አዎ" ብሎታል። በክሊኒካዊ ጥናቶች እንደተረጋገጠው፣ አንድ ሰው በሙዚቃ ውስጥ ሲቆይ ሰውነቱ ቫይረሶችን የሚከላከሉትን እንደ "ሳይቶኪንስ" (Cytokines) እና "ኢሚውኖግሎቡሊን ኤ" (IgA) ያሉ ጋሻዎችን በከፍተኛ መጠን ማምረት ይጀምራል።

ኢሚውኖግሎቡሊን ኤ በሰውነታችን ውስጥ ባሉ እንደ አፍና አፍንጫ ባሉ አካላት ውስጥ የሚገኝ የመጀመሪያው የሰውነት መከላከያ መስመር ነው። ይህ ፕሮቲን ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነታችን እንዳይገቡ “የድንበር ጠባቂ” ሆኖ ያገለግላል። ክሊኒካዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ለ50 ደቂቃ ብቻ የሚያረጋጋ ሙዚቃ ማዳመጥ የዚህን ተከላካይ ፕሮቲን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።


የተፈጥሮ ኮማንዶዎች (Natural Killer Cells) መጠንንም ይጨምራል። እነዚህ ህዋሳት በደማችን ውስጥ የሚዘዋወሩና በቫይረስ የተጠቁ ሴሎችን ወይም የካንሰር ሴሎችን ለይተው የሚያጠቁ “የሰውነት ወታደሮች” ናቸው። ሙዚቃ እነዚህ ሴሎች ይበልጥ ንቁና ቀልጣፋ እንዲሆኑ በማድረግ የሰውነትን የማጥቃት አቅም ያሳድጋል።


ከዚህም ባሻገር ሙዚቃ የሰውነትን ሚዛን በመጠበቅ፣ አላስፈላጊ የሰውነት እብጠትን (Chronic Inflammation) የሚቀንሱ ሳይቶኪኖችን እንዲመረቱ ያደርጋል። ይህ በተለይ ከጭንቀት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል ወሳኝ ነው።


እንዳይሳሳቱ ሙዚቃ ሊቅ አያደርግም!

ስለ ሙዚቃ አቅም ስናወራ ብዙ ጊዜ የሚነሳ አንድ ዝነኛ ተረት አለ፤ እርሱም "የሞዛርት ውጤት" (The Mozart Effect) ይባላል። ክላሲካል ሙዚቃን ማዳመጥ ብቻውን ሕፃናትን ወደ ሊቅነት ይቀይራል የሚለው ይሄ አስተሳሰብ ለዓመታት እንደ ትልቅ ግኝት ሲነገር ቆይቷል። ነገር ግን ሳይንሳዊ ሐቁን መረዳት ለጤናማ አጠቃቀም ወሳኝ ነው።



በታዋቂ የሳይንስ መጽሔቶች የወጡ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፣ ሙዚቃ የአንድን ሰው የአእምሮ ብቃት (IQ) በቋሚነት የመጨመር "አስማታዊ" ኃይል የለውም። ይልቁንም ሙዚቃ የሚያደርገው አእምሮን ወደ ተሻለ የንቃት ደረጃ ማምጣት ነው። ሙዚቃ አእምሮን ወደ ተሻለ ዝግጁነትና ደስታ ስለሚያመጣው፣ ችግሮችን የመፍታትና የማሰብ ብቃታችን ለተወሰነ ጊዜ ይጨምራል። ይህም ለአጭር ጊዜ መሆኑ መስተዋል ይኖርበታል። እንዲሁም ሙዚቃ አእምሯችን ምስሎችን እንዲያቀናጅና ውስብስብ ነገሮችን እንዲረዳ መንገድ ይከፍታል። ስለዚህ ሙዚቃ ሰውን "ሊቅ" አያደርግም፤ ነገር ግን አእምሮ ያለውን የላቀ ብቃት እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል።


ማወቅ ያለብዎት አራቱ ዋና ጥያቄዎች


ጥያቄ 1፦ የሙዚቃው ዓይነት (Genre) በፈውሱ ላይ ተጽዕኖ አለው?

መልስ፦ ሳይንሱ የሚነግረን ትልቁ ሚስጥር "የግል ምርጫ" ወሳኝ መሆኑን ነው። የሕክምናው ጥቅሙ የሚገኘው ሙዚቃው በውስጣችሁ በሚፈጥረው ጥልቅ ስሜት ነው። ክላሲካል ሙዚቃ በሳይንሳዊ ጥናቶች በብዛት ቢጠቀስም፣ እርስዎ የሚወዱት ኢትዮ-ጃዝ (Ethio-Jazz) ከሆነ፣ አእምሮዎ ዶፓሚን የሚያመነጨው በዚያው ሙዚቃ ነው። ስለዚህ ለእርስዎ የሚስማማውን ይምረጡ።


ጥያቄ 2፦ ሙዚቃ ለእንቅልፍ ጥራት አስተዋጽኦ ያደርጋል?

መልስ፦ አዎ፣ ያውም በከፍተኛ ሁኔታ! ከመተኛትዎ በፊት ለ45 ደቂቃ ያህል ረጋ ያለ ሙዚቃ ማዳመጥ አእምሮዎ በፍጥነት ወደ "አልፋ" እና "ዴልታ" ሞገዶች እንዲሸጋገር ያደርገዋል። ይህ ሂደት ወደ ጥልቅ እንቅልፍ እንዲገቡና ጠዋት ሲነቁም ሙሉ እረፍት አግኝተው እንዲነሱ ይረዳዎታል።


ጥያቄ 3፦ ሙዚቃን ማዳመጥ ይሻላል ወይስ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት?

መልስ፦ ሁለቱም የየራሳቸው በረከት አላቸው። ማዳመጥ ለጭንቀት መቀነስና ለህመም ማስታገሻነት እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት እንቅስቃሴ ስላለው ለአእምሮ እንደ ስፖርትነት ያገለግላል። መሣሪያ መጫወት ከሙዚቃው ባሻገር ፤ የማሰብን ነገሮችን የማቀናጀትንና ትኩረትን የመሰብሰብ ብቃትን (Executive Function) በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል።


ጥያቄ 4፦ ከፍተኛ ድምፅ ያለው ሙዚቃ በጤና ላይ ጉዳት አለው?

መልስ፦ አዎ! ከ85 ዴሲቤል በላይ ለሆነ ድምፅ ለረጅም ጊዜ መጋለጥ ጆሮ ላይ ጉዳት አለው። ታምቡር ላይ ካለው አሉታዊ ተጽእኖ ባሻገር ፤ ጆሮዎት ላይ የሚጮህ ድምጽ እንዲሰማዎ (Tinnitus) ያደርጋል። ዘላቂ የመስማት ችግርም ሊያስከትል ይችላል።


ታድያ ግን ያስተውሉ!

ሙዚቃ የልብ ትርታን ማረጋጋት ፤ ህመምን የማስታገስ እና በሽታ የመከላከያ አቅምን የማጠናከር ልዩ አቅም ቢኖረውም ፤ አጠቃቀምዎ በልክ መሆን አለበት።


አልያ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል!

Comments


bottom of page