top of page

በአመጋገብ የስኳር በሽታ ይፈወሳልን?

“በአመጋገብ የስኳር በሽታዬን ተፈውሷል…”


በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይህ ንግግር በኢትዮጵያ እንደ ተስፋ ሰጪ ብስራት ፤ በየማህበራዊ ሚዲያም እንደ ትልቅ ዜና በስፋት እየተሰማ ይገኛል። አንዳንዶች እንደውም "ድህነት ያገኘሁት ፤ እከሌ/እከሊት የተሰኘ/ች የስነምግብ አማካሪ ጋር ሄጄ ነው" ሲሉም ይስተዋላሉ።

በዚህም ምስክርነት ላይ ተመስርቶ ብዙ የስኳር ታማሚዎች ፤ ወደ እነኝህ ስፍራዎች እየጎረፉ ፤ ተመሳሳይ ውጤቶች እያስተዋሉ ፤ ጥቂት የማይባሉትም የስኳር መድሐኒት መውሰድ እያቆሙም ይገኛሉ።


የስኳር በሽታን ሙሉ በሙሉ እንደሚፈውሱ ፤ በድፍረት የሚናገር ባለሙያ እምብዛም ባይገኙም ፤ እነኝህ ታካሚዎች ይህን ምስክርነት ሲሰጡላቸው ግን፤ በዝምታ የሚያልፉ አሉ።


ለመሆኑ ግን እውነታው ምንድን ነው?


የሰለጠነው አለም ያልደረሰበት ተአምራዊ የሳይንስ ልህቀት ፤ ወይስ ስለ ስኳር በሽታ ያለ የግንዛቤ ክፍተት?

እያንዳንዱን በጥልቀት እንመልከተው፡


ሰዎች እያዩት ያለው ፈውስ ምንድን ነው?

ጥብቅ የምግብ ቁጥጥር የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች በጤናቸው ላይ አስገራሚ ለውጦችን ይመለከታሉ፤ የደም ስኳር መጠናቸው ይቀንሳል፣ የዕለት ተዕለት መድኃኒት ፍላጎታቸውም ይወርዳል። በተለይም ከአመጋገብ ለውጥ ጋር ክብደትን መቀነስ ከተቻለ፣ የሰውነት ህዋሳት ለኢንሱሊን ሆርሞን የተሻለ ምላሽ እንዲሰጡ በማድረግ የስኳር በሽታ ምልክቶችን ሊያጠፋ ይችላል። ይህ በተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች የተረጋገጠ በሕክምናው ዓለም የሚታወቅ እውነታ ነው።



በዚህ ሂደት የታካሚው የላቦራቶሪ ምርመራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ይሻሻላሉ። በተለይም ባለፉት ሶስት ወራት በደም ህዋሳት ላይ የነበረውን ከፍተኛ የስኳር ጫና የሚለካው የ HbA1c ምርመራ ወደ "ጤናማ" ደረጃ ይመለሳል። ይህን አስደሳች ውጤት ያየ ታካሚ ታዲያ በተፈጥሮ የሚደርስበት አንድ መደምደሚያ አለ፦

"በሽታው ጠፍቷል!"

እንደዚህ ቢያስቡም አይፈረድባቸውም!


አንድ ወሳኝ ጥያቄ ግን ማንሳት ያስፈልጋል፦


እሳት ውስጥ ማገዶ መጨመር ብናቆምና ፤ ወላፈኑ ባይታየን ፤ እሳቱ በእርግጥ ጠፍቷል ማለት ነውን?


በሽታው እንዴት ይከሰታል?

የደም ስኳር ምርመራ ውጤታችን "ጤናማ" ስለመጣ ብቻ በሽታው ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ማለት እንዳልሆነ ለመረዳት፤ የቆሽትን እና የኢንሱሊን ሆርሞንን ሳይንሳዊ ሂደት በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል። በቆሽታችን ውስጥ አይሌትስ ኦፍ ላንገርሃንስ (Islets of Langerhans) የተባሉ ጥቃቅን ህዋሳት አሉ። እነዚህ ህዋሳት የደም ስኳርን የሚቆጣጠረውን ኢንሱሊን የማምረት ኃላፊነት አለባቸው።


በዚህ ምስል ውስጥ 3ኛው ቁጥር ያለባቸው ህዋሳት የቆሽት ኢንሱሊን አምራች ህዋሳት ናቸው።
በዚህ ምስል ውስጥ 3ኛው ቁጥር ያለባቸው ህዋሳት የቆሽት ኢንሱሊን አምራች ህዋሳት ናቸው።

እነዚህን ህዋሳት በአንድ ፋብሪካ ውስጥ እንደሚሰሩ ሰራተኞች አድርገው ያስቧቸው። በህይወት ዘመናችን አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰሩ ሲሆን ፤ ያለ እረፈት ለ 24 ሰዓታት እስከ እለተ ሞታችን ይተጋሉ። እነኝህ ህዋሳት ለረጅም ዓመታት በሚደርስባቸው ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት ጫና እና የሰውነት ኢንሱሊንን የመቋቋም ባህሪ (Insulin Resistance) ምክንያት፣ በእነዚህ ህዋሳት ላይ እጅግ ከፍተኛ የስራ ጫና ይፈጠራል።


ውሎ አድሮ ሰራተኞቹ (ህዋሳቱ) ይዝላሉ፤ ይደክማሉ። ጫናው ሲበዛባቸው ደግሞ መሞት ይጀምራሉ። የተቀሩት ህዋሳት የሞቱትን ስራ ተክተው ለመስራት ቢጥሩም፣ አቅማቸው በጊዜ ሂደት እየመነመነ ይመጣል። አቅማቸው እጅጉን ሲዳከም ተራውን የደም ስኳር እንኳን ማስተናገድ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ይህ ባዮሎጂያዊ ድካም የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ (Type 2 Diabetes) መነሻ ነው።


ምግባችንን ስናስተካክል ለእነዚህ ህዋሳት የስራ ጫና  ይቀንስላቸዋል። ሆኖም የአመጋገብ ለውጥ የሞቱትን ህዋሳት መልሶ ሊተካ ወይም የመጨረሻው የድካም ደረጃ ላይ የደረሰን ህዋስ እንደ አዲስ ሊያድስ አይችልም።



ደክሞት 20 ኪሎ ማንሳት ለከበደው ሰው ፤ 2 ኪሎ ሰጥቶ ፤ 'ድካም ቀንሷል' ማለት ፈጽሞ አይቻልም። ኪሎ እንጂ ድካም አልቀነሰም!

የምግብ ስርዓት ምን ሊያደርግ ይችላል?


እዚህ ጋር እንዳይሳሳቱ! የአመጋገብ ስርአትን ማስተካከል ለስኳር በሽታ ህክምና ካሉት መፍትሔዎች ውስጥ ቀዳሚው እና ዋነኛው ነው። እንደውም በህክምናው አለም "ምግብ ዋነኛው መድኃኒት ነው" (Food is Medicine) እንደሚባለው፣ የስኳር መድኃኒትን ያለ አመጋገብ ማስተካከል ትርጉም የለሽ ድካም ነው።


በጥንቃቄ መመገብ እና የአበላል ስርአትን ማሻሻል ማለት፤ እነዚያን ለዓመታት ሲለፉ ለቆዩት እና ለደከሙት የቆሽት ህዋሳት እጅግ አስፈላጊ የሆነ "የዕረፍት ጊዜ" መስጠት ማለት ነው። በምግብ የሚመጣውን ጫና በመቀነስ፤ የተዳከሙት "ሰራተኞች" ቢያንስ የዕለት ተዕለት ስራቸውን እንዲከውኑ እና የሰውነትዎን ጤና እንዲጠብቁ እያገዟቸው ነው። ይህ በራሱ ለጤና ጉዞዎ ትልቅ ድል እና ስኬት ነው።


ሆኖም ግን አንድ ወሳኝ ጥንቃቄ ሊኖር ይገባል።

የአመጋገብ ለውጥ ብቻውን ያለ ህክምና ክትትል እና ያለ መድኃኒት እገዛ ውጤታማነቱ ሊስተጓጎል ይችላል።

መድኃኒት እና አመጋገብ ተደጋግፈው ሲሰሩ ብቻ ነው ዘላቂ እና አስተማማኝ ጤና ማግኘት የሚቻለው።


በሽታውን መቆጣጠር ከፈውስ ጋር አንድ አይደለም

በሕክምና ሳይንስ ውስጥ በሽታን መቆጣጠር እና በሽታው ሙሉ በሙሉ መዳኑ (Cure) መካከል ግዙፍ ልዩነት አለ። በዚህ ረገድ የቃላት አጠቃቀማችን እጅግ ጥንቃቄ ሊታከልበት ይገባል።


ያስተውሉ!

"ወላፈኑ ቢቆምም ረመጡ እስካለ እሳቱ ጠፋ ማለት አንችልም።"

ይህ ምሳሌ እንጂ የስኳር በሽታን እንደ እሳት ነው ማለት አይደለም። አመጋገብዎን ሲያስተካክሉ በሽታውን የሚያባብሰውን "ማገዶ" መክተት አቁመው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከጀርባ ያለው የበሽታው ባህሪ አይለወጥም። የደከሙት ህዋሳት እዚያው ናቸው፤ የሞቱትም አይመለሱም። የቀሩት ህዋሳት መስራት የሚችሉትን ያህል ጫና ብቻ እንዲያስተናግዱ ስለተደረገ፣ የላቦራቶሪ ውጤቶችዎ "ጤናማ" መስለው ይታያሉ።


እውነታው ግን ይህ ነው፦

አመጋገብዎን በማስተካከል ስኳርዎን ተቆጣጠሩት እንጂ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ አልዳኑም።

አሁን ዘመኑ በደረሰበት ከስኳር በሽታ የዳኑ ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ይህም ህክምና በቀጣይ አመታት ውስጥ ለአብዛኛው የአለም ህዝብ ይዳረሳል ተብሎ ይታሰባል። እስከዛ ግን የስኳር በሽታዎን መቆጣጠር የእርስዎ ቀዳሚ ድርሻ ነው።


"ድኛለው" የማለት አደጋው ምንድነው?

"ድኛለሁ" ብሎ ማሰብ አዎንታዊ ስሜት ቢፈጥርም፣ ይህ አስተሳሰብ ለከፋ አደጋ ሊዳርገን ይችላል። በተለይ እንደ ስኳር ባሉ ስር የሰደዱ ህመሞች ላይ ይህ የ"ሀሰተኛ ደህንነት" ስሜት የሚከተሉትን ስውር አደጋዎች ይዞ ይመጣል፦


1. የመድኃኒት መቋረጥና የውስጥ አካላት መጎዳት

ብዙዎች "ደህና ነኝ" ብለው በማሰብ ብቻ ያለ ባለሙያ ምክር መድኃኒት ያቆማሉ። ነገር ግን የመድኃኒት ለውጥ መደረግ ያለበት በስኳር ስፔሻሊስት (Endocrinologist) እና በህክምና መመሪያዎች ላይ ተመስርቶ ብቻ መሆን አለበት። መድኃኒት በራስ ፍቃድ ማቆም የደም ስኳር በድንገት እንዲጨምር ከማድረጉም ባለፈ፣ በሂደት ለኩላሊት ድክመት፣ ለልብ በሽታ እና ለስትሮክ የመጋለጥ እድልን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።


2. የ"ሀሰተኛ ደህንነት" ስሜትና መዘናጋት

"ተፈውሻለሁ" የሚለው እምነት የደም ስኳርን የመከታተል ፍላጎትን ያጠፋል። ይህ መዘናጋት ስኳር "በዝምታ" (Silent killer) የውስጥ አካላትን እንዲጎዳ ሰፊ ዕድል ይሰጠዋል። መከታተል ሲቆም፣ ህመሙም በስውር ስራውን ይቀጥላል። ክትትሉም እቤት በሚደረግ የስኳር ምርመራ ሳይሆን ፤ በህክምና ባለሙያ መሆን ይኖርበታል።


3. የስነ-ልቦና ቀውስ እና ተስፋ መቁረጥ

የአመጋገብ ስርዓት ሲለወጥ ወይም የኢንሱሊን አምራች ህዋሳት አቅም ይበልጡኑ እየተዳከመ ሲመጣ ፤ ስኳሩ መልሶ መጨመሩ አይቀሬ ነው። በዚህ ወቅት "ድኛለሁ" ብሎ ሲያስብ የነበረ ሰው የመሸነፍ እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይወርሰዋል። ይህ ስነ-ልቦናዊ ጫና ደግሞ ለቀጣይ ህክምና ያለውን ተነሳሽነት በእጅጉ ይገላል።


ምግብ ወይስ መድሐኒት? የተሳሳተው ምርጫ

በሀገራችን በኢትዮጵያ ብዙዎቻችን ወደ ተፈጥሯዊ ፈውስ የማዘንበል ልምድ አለን። ይህ ለጤና ጥንቃቄ ማድረግ መልካም ቢሆንም፣ ትክክለኛውን መረጃ ካልያዝን ግን ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል። ጤናማ አመጋገብ እና ዘመናዊ ህክምና ተቃራኒ ሳይሆኑ አጋዥ መሆናቸውን መረዳት የጤና ጉዟችን ስኬት ወሳኝ ነጥብ ነው።


ምግብን እንደ መድኃኒት ስንቀበል የበሽታውን ተፈጥሮ ክደን መሆን የለበትም። እንደ ስኳር ያሉ ህመሞች በባህሪያቸው የረጅም ጊዜ ክትትልና ጥንቃቄ የሚሹ መሆናቸውን መረዳት ቀዳሚው እርምጃ ነው። ምግብ በሰውነታችን ላይ ያለውን ጫና ሲቀንስ፣ መድኃኒቶች ደግሞ የኢንሱሊንን ስራ ያግዛሉ። እነዚህ ሁለት ወሳኝ ሀይሎች ተባብረው ሲሰሩ ስኳርን በይበልጥ መቆጣጠር ይቻላል። አንዱን መርጦ ሌላውን እርግፍ አድርጎ መተው ግን ሰውነታችንን ያለ መከላከያ ለጥቃት ማጋለጥ ነው።


ያስተውሉ!

እውነተኛ ጤና የሚገኘው በአመጋገብ ስርአት እና በህክምና ክትትል መካከል ያለውን ሚዛን ጠብቆ በመጓዝ ነው። አንዱ የሌላው ምትክ ሳይሆን፣ ሁለቱም ለተሻለ ህይወት አስፈላጊ የሆኑ የጤና ምሶሶዎች ናቸው።


ተስፋ እውነትን ሊተካ አይገባም፤ ይልቁንም እውነት ለተስፋችን መሠረት መሆን አለበት።


ፈውስን ብቻ አይመኙ፤ ይልቁንም ጤናዎን የመቆጣጠር ጥበብን ይገንቡ።


Comments


bottom of page