top of page

ዳማከሴ ወይስ ጤና አዳም ፡ የቱ ይሻላል?

በኢትዮጵያ ብዙ ቤቶች ውስጥ ድንገተኛ ራስ ምታት፣ ምች፣ አስቸጋሪ ጉንፋን አልያም የሆድ ህመም ሲጀምር፤ ብዙዎች ወደ ፋርማሲ ከመሄድ ይልቅ ወደ ጓሮአቸው ዞር ማለት ይመርጣሉ። ከብዙ ቤቶች ጓሮም ጤና አዳም እና ዳማከሴ አይጠፉም!


ለዚህም ነው በየመኖሪያ ቤቱ ....

“ጤና አዳም አምጡ!” አልያም ፤

“ዳማከሴ አለ?” የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ የሚሰሙት።

ከጉንፋን እስከ ራስ ምታት፣ ከትኩሳት እስከ አፍንጫ መደፈን — እነዚህ ሁለት ቅጠሎች በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዋነኛ “የመጀመሪያ እርዳታ” ናቸው። ውጤታቸውንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተግባር ይመሰክራሉ።


በሳይንስ በኩል እያንዳንዱ ቅጠል ስላለው አስደናቂ የጤና ጠቀሜታ ከዚህ በፊት በነበሩ ጽሁፎቻችን በሰፊው ዳሰናቸዋል። (ጽሁፎቹን እዚህ ያገኟቸዋል፦ የጤና አዳም ሳይንሳዊ ጠቀሜታዎች እና የዳማከሴ ሳይንሳዊ ጠቀሜታዎች)። ዛሬ ግን ሁለቱን ቅጠሎች እናነጻጽራለን ።


ታድያ ከሁለቱ ተመራጭ የቱ ይመስልዎታል?
አንድ ላይስ መጠቀም ይቻላልን?

ለእነኝህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት እያንዳንዱን በጥልቀት እንመልከት።


ዳማከሴ

በኢትዮጵያ ባህላዊ ሕክምና ውስጥ ዳማከሴ (Ocimum lamiifolium) እንደ ተራ ቅጠል ሳይሆን እንደ ድንገተኛ በሽታ መከላከያ ነው ። ዝርያው በሳይንስ ከበሶ ብላ (Basil) እና ከስጋ መጥበሻ (Rosemary) ጋር የተቀራረበ ነው። ለዘመናት ለሚንቀለቀል ትኩሳት፣ ለጭንቅላት ምታት እና ለ'ምች' ማስታገሻነትም ሲያገለግል ኖሯል። 



ዛሬ ግን ይህ የጓሮ ፈውስ በባህል ብቻ አልቀረም። በርካታ የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የሳይንስ ጥናቶች የዳማከሴን ቅጠል በላብራቶሪ በመመርመር፣ ከበስተጀርባው ስላሉት አስደናቂ ኬሚካላዊ እና ፋርማኮሎጂካዊ ሚስጥሮች የሚከተሉትን ሳይንሳዊ እውነታዎች አረጋግጠዋል።


የዳማከሴ ቅጠል ሲታሽ የሚሰጠው ጠንካራ መዓዛ ዝም ብሎ የተፈጠረ አይደለም። በላብራቶሪ የጋዝ ክሮማቶግራፊ (GC-MS) በጥናት እንደተረጋገጠው፤ ቅጠሉን በእጃችን አሽተን ስናሸት ወይም በሙቅ ውሃ/ቡና ውስጥ አድርገን እንፋሎቱን ወደ ውስጥ ስንስብ፤ ውስጡ ያሉ ውህዶች (ለምሳሌ "ቦርኒል አሴቴት" እና "ፒ-ሳይሜን" የተባሉ አስፈላጊ ዘይቶች (essential oils) ) በቀጥታ ወደ ትንፋሽ ቱቦአችን ይገባሉ። ንጥረ ነገሮቹ በአፍንጫ እና በሳይነስ አካባቢ ያሉ የደም ስሮች ላይ ባላችው አዎንታዊ ተጽእኖ ፤ የታፈነ አፍንጫን ወዲያውኑ የመክፈት እና የመተንፈሻ አካላትን የማረጋጋት ከፍተኛ ሳይንሳዊ አቅም አላቸው።



በጥናት እንደተረጋገጠው ዳማከሴ በውስጡ የያዛቸው ፌኖሊክ ውህዶች (Phenolic compounds)፣ ፍላቮኖይዶች (Flavonoids) እና ታኒን (Tannins) ባክቴሪያዎችን የማጥፋት ከፍተኛ አቅም አላቸው። የተክሉ ይዘቶች የባክቴሪያዎችን የውጭ ሽፋን (Cell membrane) በመበጣጠስ እንዳይራቡ እና እንዳይኖሩ ያግዳቸዋል። ይህም በባህል ለቁስል፣ ለጉሮሮ ህመም እና ለኢንፌክሽኖች ለምን ፍቱን እንደሆነ ማረጋገጫ ነው።


በላብራቶሪ የእንስሳት ሙከራዎች (In vivo studies) እንደተረጋገጠው፣ የዳማከሴ ቅጠል ውህዶች በሰውነታችን ውስጥ ህመም እና ከፍተኛ ትኩሳት የሚቀሰቅሱትን ፕሮስታግላንዲን (Prostaglandins) የተባሉ ኬሚካሎች እንዳይመረቱ የማገድ (Cox-inhibitory) ባህሪ አላቸው። በዚህም የተነሳ በተወሰነ ደረጃ ከአስፒሪን ወይም ከፓራሲታሞል ጋር የሚመሳሰል ፤ የትኩሳት ማስታገሻ ባህሪ (Antipyretic) ሊኖረው እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ።

ይህ ግን አስፕሪን እና ፓራሴታሞልን ይተካል ማለት አይደለም!

ጤና አዳም


በኢትዮጵያ ባህላዊ ማህበረሰብ ውስጥ የጤና አዳም (Ruta chalepensis) እና የቡና ትስስር እጅግ ጥብቅ ነው። ማለዳ ላይ ቡና ሆነ ወተት ሲፈላ፤ አንድ የጤና አዳም ቅጠል ተቆርጦ ሲገባ የሚፈጥረው ልዩ መዓዛና ጣዕም ይማርካል። ነገር ግን የዚህ ተክል ስያሜ “የአዳም ጤና” መሆኑ፤ ጥቅሙ ከማዕድ ማድመቂያነት አልፎ እጅግ የላቀ የሕክምና ሚና አለውን?


ከዳማከሴ ፈጽሞ የተለየ ኬሚካላዊ ይዘት ያለው ጤና አዳም ፤ በላብራቶሪ ምርምሮች ውስጥ ሲፈተሽ የሚከተሉትን ጥልቅ የሳይንስ እውነታዎች አሳይቷል።


ጤና አዳም ለሆድ ህመም እና ለቁርጠት ማስታገሻነት ሊውል ይችላል። ይህም በውስጡ የያዛቸው ፍላቮኖይዶች (እንደ ሩቲን/Rutin ያሉ) እና አልካሎይዶች የተሰኙ ውህዶች ፤የሆድ አካላት ጡንቻዎችን የማረጋጋት/ የማላላት አቅም አላቸው። ለዚህም የምግብ መፈጨት ሥርዓት ሲታወክ ወይም ሆድ መወጠር ሲኖር ፤ ውስጡ አሉት ውህዶች የሆድ ጡንቻዎች እንዳይኮማተሩ በማድረግ ድንገተኛውን የሆድ ቁርጠት (Cramps) ወዲያውኑ ያረጋጋሉ። 


ሳይንሳዊ ንጽጽር ፡ ዳማከሴ ወይስ ጤና አዳም?

በሳይንሳዊው ዓለም “ከሁለቱ የቱ ይበልጣል?” ለሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ሁለቱም እፅዋት ሙሉ ለሙሉ የተለያየ ውህዶች ያሏቸው ፤ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችንን ለይተው የሚያክሙ የተፈጥሮ ልዩ ስጦታዎች ናቸው። አንዱ ለአየር መንገድ ሲደርስ፣ ሌላኛው ደግሞ ለሆድ ዕቃ መታወክ ፍቱን መድኃኒት ነው።


 የእነርሱን ሳይንሳዊ ልዩነትና ጥንካሬ በተሟላ ሁኔታ ለመረዳት የሚከተለውን ንፅፅራዊ ሰንጠረዥ ይመልከቱ፦

የንጽጽር መስፈርት

ዳማከሴ (Ocimum lamiifolium) 🌿

ጤና አዳም (Ruta chalepensis) ☕

በዋነኝነት የሚያገለግለው

ለመተንፈሻ አካላት ችግሮች እና ለትኩሳት

ለምግብ መፈጨት ችግሮች እና ለትላትል ችግሮች

የሚያክማቸው ህመሞች

ጉንፋን፣ ሳል፣ የአፍንጫ መታፈን፣ ትኩሳት እና ምች

የሆድ ቁርጠት፣ የጋዝ መብዛት፣ የሆድ ትላትል እና ድንገተኛ የራስ ምታት

ዋና የኬሚካል ይዘት

ቦርኒል አሴቴት፣ ፒ-ሳይሜን እና ዩጂኖል (essential oils)፣ወ.ዘ.ተ...

ሩቲን (ፍላቮኖይድ)፣ ሻሌፒን እና አልካሎይዶች፣ወ.ዘ.ተ...

አሰራሩ

በትንፉሽ ቧንቧ ዙሪያ ያሉ የደም ስሮችን ያላላል፤ ንፍጥን ያቀጥናል፤ ባክቴሪያን ይገድላል

በሆድ ዕቃ ውስጥ ያሉ ለስላሳ ጡንቻዎች እንዳይኮማተሩ የካልሲየም ፍሰትን ያግዳል

ደህንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀም

በእንፋሎት መታጠንን (Inhalation) ማዘውተር (ጉበትን በቀጥታ አይነካም)

በሻይ፣ በቡና ወይም በቅመማ ቅመም ውስጥ በጥቂቱ መውሰድ

በአጠቃላይ እነዚህ ሁለት እፅዋት የአሠራር ስልታቸውም ሆነ የሚሰጡት የጤና ውጤት ፍጹም የተለያዩ ናቸው። ለዚህም ነው ጥያቄያችን መሆን ያለበት “የትኛው ይበልጣል?” ሳይሆን “መቼ የቱን እንጠቀም?” የሚለው ነው።


  • የመተንፈሻ አካላት እና ትኩሳት ሲኖር፦ ዳማከሴ ተመራጭ ነው። በውስጡ የያዛቸው ልዩ ተለዋዋጭ ዘይቶች የአየር ማስተላለፊያ መንገዶችን በፍጥነት የመክፈትና ትኩሳትን የመቀነስ ከፍተኛ ሳይንሳዊ አቅም አላቸው።

  • የሆድ እና የምግብ መፈጨት ችግር ሲኖር፦ ጤና አዳም ቀዳሚ ምርጫ ነው። የሆድ ዕቃ ጡንቻዎችን በማዝናናት ድንገተኛና አስቸጋሪ የቁርጠት ስሜትን ወዲያውኑ የማጥፋት አስደናቂ ብቃት አለው።

 

አብሮ መውሰድ ይቻላል? ⚠️


አዎ!

በባህላዊው አጠቃቀም ሁለቱን ቅጠሎች አንድ ላይ አፍልቶ መጠጣት ወይም መውሰድ ይችላል። ይሁን እንጂ ሁለቱም እፅዋት በውስጣቸው እጅግ ጠንካራ የኬሚካል ይዘት እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም። በመሆኑም አጠቃቀማቸው ጥንቃቄን ይሻል!

  • በተለይም ጤና አዳም በከፍተኛ መጠን ከተወሰደ ለሰውነት መርዛማ ሊሆን ስለሚችል ፤በጥቂቱ እና በልክ መጠቀም ይመረጣል።

  • እንዲሁም ሁለቱም ቅጠሎች (በተለይ ጤና አዳም) ማህጸን ላይ ባላቸው ተጽእኖ ለነፍሰ ጡር እናቶች ፈጽሞ አይመከሩም

  • ከዚህም ባሻገር የጉበት እና የኩላሊት ችግር ያለባችው ሰዎች ላይ እጅግ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።


እዚህ ጋር ያስተውሉ ፤ እነዚህ ቅጠሎች ዋነኛ የህመም ማስታገሻን ፈጽሞ አይተኩም። የዘመናዊ ህክምና መተኪያ ሆነው አገልግሎት ላይ መዋል አይችሉም።  ከፍተኛ የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው በሽታዎች ዘላቂ መፍትሄ አይደሉም።


ትልቁ ስህተት! “ተፈጥሯዊ ከሆነ አይጎዳም” የሚል እምነት



በተፈጥሮ ሕክምና ዙሪያ ያለው ትልቁ እና በጣም አደገኛው የተሳሳተ ግንዛቤ “ተፈጥሯዊ እስከሆነ ድረስ ምንም ዓይነት ጉዳት የለውም” ብሎ ማሰብ ነው።


ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ጥቅም ላይ የዋሉ ዘመናዊ መድኃኒቶች የተቀመሙት ከዕፅዋት መሆኑን መዘንጋት የለብንም!

ዕፅዋት በውስጣቸው ኃይለኛ የሆኑ ኬሚካላዊ ውህዶችን ይዘዋል። እነዚህ ኬሚካሎች ልካቸውን ጠብቀው ከተወሰዱ፤ ፈዋሽ ሊሆኑ ቢችሉም፤ መጠናቸው ሲያልፍ ወይም ከተገቢው ውጭ ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ሲቀላቀሉ ግን መርዛማ ሊሆኑ ይችላሉ።


የዘመናዊ ሳይንስ ዋና ጥቅሙም ይህንን የዕፅዋቱን ምስጢራዊ ባህሪ በመመርመር “ልኩን” ማሳወቁ ላይ ነው።


በዚህም መሠረት የሕክምና ጥናቶች በዳማከሴ እና በጤና አዳም አጠቃቀም ላይ የሚከተሉትን ጥብቅ የሳይንስ ማስጠንቀቂያዎች ይሰጣሉ


ዳማከሴ ሲወስዱ ማድረግ ያለብዎ ጥንቃቄዎች



ዳማከሴ ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ቢሆንም፣ የረጅም ጊዜ አጠቃቀሙ ላይ ጥንቃቄ ይሻል።  የዳማከሴን ጭማቂ በየቀኑ እና ከሁለት ሳምንት በላይ በተከታታይ በከፍተኛ መጠን መውሰድ፤ በውስጡ ያሉት ውህዶች ጉበት እና ኩላሊት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ያደርጋል። በመሆኑም ለአጭር ጊዜ (ለ3 ወይም ለ5 ቀናት) ለትኩሳት እና ለጉንፋን ማስታገሻነት ብቻ መጠቀም ይመረጣል። ለዚህም ሌላኛው መፍትሔው ፤ ቅጠሉን በእጅ አሽቶ ጭማቂውን በጥቂት ጠብታ በውሃ ወይም በቡና መውሰድ፤ አልያም አፍልቶ መታጠን (Inhalation) ይመከራል። የእንፋሎት ትንፋሹ በቀጥታ ከአየር መንገድ ጋር እንጂ ከጉበት ስራ ጋር ስለማይገናኝ ይህ አጠቃቀም እጅጉን ይመክራል።


የጤና አዳም ሲጠቀሙ ማድረግ ያለብዎ ጥንቃቄዎች፡



ጤና አዳም እጅግ ኃይለኛ የኬሚካል ውህዶች ስብስብ በመሆኑ፣ አጠቃቀሙ የላቀ ጥንቃቄን ይፈልጋል። ጤና አዳም ለነፍሰ ጡር ሴቶች ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ጤና አዳም በማህፀን ጡንቻዎች ላይ ከፍተኛ የመኮማተር እና የማህፀን ደም ፍሰትን የመጨመር ባህሪ አለው። በመሆኑም ፅንስን የማጨናገፍ አደጋ ስላለው ነፍሰ ጡር እናቶች በምንም መልክ ፈጽሞ ሊጠቀሙበት አይገባም።


ውስጡ ያሉት ፉራኖኩማሪኖች ከቆዳ ጋር ንክኪ ፈጥረው ለፀሐይ ብርሃን (UV Rays) ሲጋለጡ፣ ቆዳን ለከፍተኛ ማቃጠል፣ ለሽፍታ እና ለቆዳ ቀለም መለወጥ (Phytophotodermatitis) ይዳርጋሉ። ስለዚህ ቅጠሉን ከነኩ በኋላ ቆዳን በውሃና በሳሙና በሚገባ መታጠብ ያሻል።


ልክ እንደ ዳማከሴ ሁሉ፣ የጤና አዳም ዘይትን ወይም ጭማቂን ከልክ በላይ መውሰድ የጉበት መመረዝ (Toxic hepatitis) እና የኩላሊት መቁሰል ሊያስከትል ይችላል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ባህል በቡና ውስጥ የሚገባው የቅጠል መጠን እጅግ አነስተኛ በመሆኑ፣ ለጤናማ ሰው ለአጠቃላይ አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው።


ማጠቃለያ

ዳማከሴ እና ጤና አዳም በኢትዮጵያውያን ጓሮዎች ውስጥ ለዘመናት የቆዩ፣ የትውልድ ዕውቀት እና የባህል መገለጫ የሆኑ ውድ ሀብቶቻችን ናቸው። ዛሬ ላይ የሕክምና ሳይንስ ላብራቶሪዎች በሰፊው መርምረው ያረጋገጡት እውነትም ይሄንኑ ነው፤ እነዚህ ቅጠሎች እንዲሁ በልማድ የሚቀጠፉ ሳይሆኑ፣ እያንዳንዳቸው የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎችን ለይተው የሚያክሙ የተፈጥሮ መድሀኒቶች ናቸው።


ሆኖም ግን፣ ተፈጥሯዊ መሆናቸው ብቻውን ከአደጋ ነፃ አያደርጋቸውም። ልክ እንደ ማናቸውም ዘመናዊ መድኃኒቶች ሁሉ፣ የእነዚህም ዕፅዋት ፈዋሽነት የሚረጋገጠው አጠቃቀማቸውን፣ መጠናቸውን (ልክን) እና የሚሰጡበትን ጊዜ አውቀን በጥንቃቄ ስንጠቀምባቸው ብቻ ነው።


በመጨረሻም፣ እነዚህ ቅጠሎች የዘመናዊ ሕክምናን ሚና ፈጽሞ ሊተኩ እንደማይችሉ ማስታወስ ይገባል።


በዕውቀት እና በኃላፊነት እንጠቀም!



Comments


bottom of page