“ብርድ መታኝ…” — በእርግጥ “የብርድ በሽታ” አለ?
- Zebeaman Tibebu
- 5 days ago
- 3 min read
“ነፋስ መታኝ… አንገቴን ጨመደደኝ…ቀስፎ ብርዱ አጥንቴ ውስጥ ገባ…”
ይህን ንግግር በኢትዮጵያ ምድር ያልሰማ ጆሮ፣ ያልተናገረ አንደበት የለም ለማለት ይቻላል።
በብዙዎቻችን ዘንድ “የብርድ በሽታ” እንደ ተራ ስሜት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድ ትልቅ የሕክምና ምርመራ (Diagnosis) ተቀባይነት አግኝቷል።
በባህልም ይህ በሽታ በሚከተሉት ምክንያቶች እንደሚመጣ ይታመናል፦
ቀዝቃዛ አየር ወይም ነፋስ ሰውነትን ሲመታ/ ከሰውነት ጋር ሲጋጭ
ሰውነትዎ ሞቆ ልብሶችን ቀዝቃዛ ቦታ ሲያወልቁ

"ይሄን ጊዜ ብርድ ይመታዎታል!" ተብሎ ይታሰባል።
ብርድ ሲመታዎትም ፤ አንገትዎ ጋር ፣ ጀርባዎ አልያም ደረትዎ ጋር ህመም ሊሰማዎት ይችላል። የ ሳል ምልክት ሊያዩ ይችላል። በአጠቃላይ ሰውነትዎ ላይ ደስ የማይል የህመም ስሜት ይሰማዎታል።
ይህ በባህላዊው ነው።
ግን ጥያቄው፦
❓ ይህ በሽታ እውነት ነውን? ቀዝቃዛ አየር በራሱ በሽታ ነው? ወይስ ከበስተጀርባ ሌላ የህክምና ምስጢር አለ?
🧠የህክምና ሳይንስ ምን ይላል?
ዘመናዊ ህክምና አንድ ነገር ላይ በደንብ ይስማማል፦
👉 ቀዝቃዛ አየር በራሱ በሽታ አያመጣም።
በህክምና ሳይንስ ውስጥ ነፋስ፣ ለቅዝቃዜ መጋለጥ ወይም የሙቀት መጠን መቀነስ ብቻውን ኢንፌክሽን ወይም በሽታ እንደሚፈጥር የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ የለም። ይልቁንም ሰዎች “የብርድ በሽታ” ብለው የሚጠሩዋቸው ምልክቶች በህክምናው እንደሚከተለው ይብራራሉ፦

1. የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን
ብዙውን ጊዜ የጉንፋን ምልክቶች የሚታዩብን ከቅዝቃዜ በኋላ ስለሚሆን፣ ተጠያቂው ብርዱ ይመስለናል። ነገር ግን እውነተኛው ወንጀለኛ ቫይረስ ነው። ብርድና ንፋስ ለቫይረሶች ስርጭት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ እንጂ ኢንፌክሽን አያመጡም። ቀዝቃዛ አየር የአፍንጫችንን የውስጥ እርጥበት ሲያደርቀው፣ ቫይረሶችን አጣብቆ የሚያስቀረውና የሚያጠፋው ተፈጥሯዊ “ንፍጥ” (Mucus) ስራውን ያቆማል። በዚህ ጊዜ ቫይረሶች/በሽታ አምጪ ተህዋሳት በቀላሉ ወደ ሰውነታችን ሰርገው ይገባሉ። ለዚህም የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ያስከትላሉ። እንዲሁም በብርድ ጊዜ ሰዎች ቤት ውስጥ ይቆያሉ፣ የቅርብ ንክኪ ይጨምራል። ይህ ደግሞ ቫይረሱ ከአንዱ ወደ ሌላው እንዲዘዋወር ሰፊ እድል ይሰጠዋል።
2. የጡንቻና የአጥንት ህመም
“ንፋስ ገባብኝ” ስንል የምንገልጸው የጀርባ ወይም የአንገት ህመም፣ የሰውነታችን የተፈጥሮ የመከላከያ ስልት ውጤት ነው። ሰውነት ቅዝቃዜ ሲሰማው ሙቀት ለማመንጨት ሲል ጡንቻዎችን በሃይል እንዲኮማተሩ ያደርጋል። ይህ ድንገተኛ መኮማተር (Spasm) ጡንቻው እንዲዝልና ከፍተኛ ህመም እንዲሰማን ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዝቃዜ የደም ስሮችን ስለሚያጠብ፣ ወደ ጡንቻዎች የሚደርሰው ደም ይቀንሳል። ለዚህም በብርድ ጊዜ ጡንቻዎች ይወጠራሉ፣ የደም ቧንቧዎች ይኮማተራሉ፤ ይህም ህመም በይበልጥ እንዲሰማን ያደርጋል። ችግሩ ያለው ከውጭ በመጣ ንፋስ ሳይሆን በሰውነታችን የውስጥ ምላሽ ላይ ነው።

3. ለቀዝቃዛ አየር ሳንባችን የሚሰጥ ስሜታዊ ምላሽ
አንዳንዴ ብርድ ራሱን የሚችል በሽታ ሳይሆን የሰውነት “ቁጣ” (Irritation) ሊሆን ይችላል። ቀዝቃዛና ደረቅ አየር በቀጥታ ወደ ሳንባ ሲገባ፣ የመተንፈሻ ቱቦዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ይጠብባሉ። ይህ ሁኔታ እንደ አስም ያሉ ችግሮች ባሉባቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ትንፋሽ ማጠርና ሳል ይፈጥራል።
ከዚህም ባሻገር አፍንጫችን ቀዝቃዛውን አየር ለማሞቅ ሲሞክር ተጨማሪ ፈሳሽ (ንፍጥ)ያመነጫል። ይህ ፈሳሽ በራሱ የኢንፌክሽን ምልክት ሳይሆን፣ አፍንጫችን ስራውን በትክክል እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።
🔍 ለዚህም ነው “የብርድ በሽታ” እውነት የሚመስለን!
📊ጥናቶች ምን ይጠቁማሉ?

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ሰፊ የሕክምና ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ቀዳሚ ምክንያቶች አንዱ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (CDC) መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአማካይ አንድ አዋቂ ሰው በዓመት ከ2 እስከ 4 ጊዜ በጉንፋን የሚጠቃ ሲሆን፣ ሕፃናት ደግሞ የመከላከል አቅማቸው ገና በማደግ ላይ በመሆኑና በትምህርት ቤቶች ባለው የቅርብ ንክኪ ምክንያት በዓመት ከ6 እስከ 8 ጊዜ ለዚህ ሕመም ይጋለጣሉ።
በሀገራችን ኢትዮጵያም በተለይ በክረምት ወቅት፣ በበጋው ቅዝቃዜ እና በደጋማ አካባቢዎች የመተንፈሻ አካላት ችግር ዋነኛው የጤና ስጋት ሆኖ ይታያል.
🤧 የብርድ በሽታ ምልክቶች

ሰዎች የሚከተሉትን ምልክቶች በሙሉ “የብርድ በሽታ” በሚል ስም ይሰበስቧቸዋል። "የብርድ በሽታ" ተብለው በአንድ ጥቅል ስም ቢጠሩም ፣ ምልክቶቹ እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ የተለየ ምክንያትና ትርጉም አላቸው። አንድ በአንድ እንመልከት፡
የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት (ምክንያቱ፦ የቫይረስ ኢንፌክሽን ምልክት)
የአንገት፣ የትከሻ ፣ የደረት/ጀርባ ህመም (ምክንያቱ፦ የጡንቻ መቆጣት ምልክት)
መንቀጥቀጥ /ብርድ ብርድ ማለት/ የትኩሳት (ምክንያቱ፦ የሰውነት መቆጣት/ የኢንፌክሽን ምልክት)
ሳል (ምክንያቱ፦ የመተንፈሻ አካል መቆጣት ምልክት)
የራስ ምታትና የድካም ስሜት (ምክንያቱ፦ የሰውነት መቆጣት/ የኢንፌክሽን ምልክት)
❄️ የ“ብርድ” እና “ብርድ ብርድ ማለት” ልዩነት

ይህ ብዙዎች የሚያሳስቱትት ነው። እላይ ያነሳነው ቢሆንም ፤ በይበልጥ እንዘርዝረው።
ብርድ ብርድ ማለት (Chills)፦ ይህ የኢንፌክሽን/የሰወነት መቆጣት ምልክት ነው። ይህ ብዙውን ጊዜ ትኩሳትን ያመለክታል። ሰውነታችን ሙቀቱን ለመጨመር የሚያደርገው ጥረት ነው። ጡንቻዎቻችንም ሙቀት ለማመንጨት ሲሉ ይንዘፈዘፋሉ። ይሄን ጊዜ የማንቀጥቀጥ ምልክት ይስተዋላል። እርስዎ “ብርድ አነቀጠቀጠኝ” ብለው ልብስ ይደርባሉ።
“የብርድ በሽታ”፦ ለቅዝቃዜ በመጋለጥ የሚመጣ ተብሎ የሚታመን ፤ በሕክምና የተለያዩ በሽታዎች ምልክት ነው።
🧣 በተለምዶ ምን ይመከራል?
ብዙ ጊዜ ሰው "ብርድ እንዳይመታው" የሚከተሉት ምክሮች ይሰጣሉ።
"ቅዝቃዜ ቦታ ልብስ አታውልቅ!"
"ወፍራም ልብስ ልበስ!"
"ትኩስ ነገር ጠጣ!"
"ቅዝቃዜ ቦታ ላይ አትውጣ!"
ለመሆኑ እነኝህ ምክሮች ትክክል ናቸው?
👉 አዎ! ነገር ግን የተሟሉ አይደሉም!

እንዴት?
እርግጥ ነው! ሙቅ ልብስ መልበስ ሰውነት ምቾት እንዲሰማው፣ ከመጠን በላይ መቀዝቀዝንና የጡንቻ መኮማተርን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ አለው። ነገር ግን በሽታን ለመከላከል ብቻውን በቂ አይደለም።
ትክክለኛው እና ሳይንሳዊው የመከላከያ መንገድ ትኩረት ማድረግ ያለበት ተላላፊ ተህዋሲያን ላይ ሲሆን፣ ይህም የእጅ ንፅህናን በመጠበቅ፣ ከታመሙ ሰዎች በመራቅ፣ በተዘጉ ክፍሎች ውስጥ በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር በማድረግ እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚገነቡ የተመጣጠነ ምግቦችን በመመገብ መተግበር አለበት።
ማስተዋል ያለብዎት ጉዳይ!

ሁሉንም የጤና መታወክ “ብርድ ነው” በሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ስር መሰብሰብ ደግሞ የራሱ የሆነ ከፍተኛ የጤና አደጋ አለው። ይህ አመለካከት ሰዎች ትክክለኛውን የህክምና እርዳታ እንዲያዘገዩ፣ እንደ የሳምባ ምች (Pneumonia) ያሉ ለህይወት አስጊ የሆኑ ከባድ ህመሞችን እንደ ተራ “የብርድ በሽታ” አይተው ቸል እንዲሉ እና ተገቢ ያልሆኑ መድኃኒቶችን እንዲጠቀሙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ስለዚህ ቅዝቃዜው ለበሽታው መንገድ የሚያመቻች “አጋዥ” እንጂ ዋናው “መንስኤ” አለመሆኑን ተገንዝቦ፣ ከጥንቃቄዎች ሁሉ የላቀውን ሳይንሳዊ ጥበቃ ማድረግ ለጤናችን ዋስትና ነው።
🧭 እንግዲህ… “የብርድ በሽታ” እውነት ነው?
👉 እንደ ስሜት — አዎ!
👉 እንደ ህክምና ምርመራ — አይደለም!





Comments