ስኳር ማቆም ከ ስኳር በሽታ ይታደጋልን?
- Zebeaman Tibebu
- 3 days ago
- 3 min read
ጣፋጭ ፍራቻ እና ውስብስብ እውነታው
ብዙውን ጊዜ ማስጠንቀቂያው የሚጀምረው እንዲህ በሚል ነው፦
“ስኳር መብላትን አቁም፤ አለበለዚያ ስኳር ይይዝሃል።”
በብዙዎች ዘንድ ይህ መልዕክት በስፋት ይነገራል። ስኳር እንደ ዋነኛ ጠላት ይታያል። ያለ ስኳር የሚጠጣ ሻይ እንደ መድኃኒት ይቆጠራል። ዳቦ፣ ሩዝ እና ፍራፍሬዎች እንኳን ሳይቀር በጥርጣሬ ዓይን ይታያሉ።

ግን ነገሩ እንደዚህ ቀላል ነውን? ስኳርን ማቆም ብቻውን ከስኳር ህመም ይጠብቀናል? ወይስ እውነታው ከባዮሎጂ፣ ከአኗኗር ዘይቤ እና ከጊዜ ጋር የተቆራኘ ከዚህ የበለጠ ውስብስብ ነው?
ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ከፍርሃት ወጥተን ወደ ሳይንስ መግባት ይኖርብናል።
የሰውነታችን እና የስኳር ግንኙነት
እንደ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ፍራፍሬ ወይም ስኳር ያሉ ምግቦችን ስንመገብ ሁል ጊዜ ሰውነታችን ካርቦሃይድሬቱን ወደ ግሉኮስ (Glucose) ይቀይረዋል። ይህ ግሉኮስ ወደ ደም ዝውውራችን ይገባል።
በዚህ ጊዜ ኢንሱሊን (Insulin) የተባለ ሀይለኛ ሆርሞን ስራውን ይጀምራል። ኢንሱሊን እንደ ቁልፍ በማገልገል ግሉኮስ ወደ ህዋሳት ገብቶ ለኃይል ምንጭነት እንዲውል ያደርጋል።

ጤናማ በሆነ ሰውነት ውስጥ ይህ ሂደት ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል። ነገር ግን በስኳር ህመም (በተለይም ሁለትኛው አይነት ስኳር ውስጥ) ይህ ስርአት መታወክ ይጀምራል። ሰውነታችን በቂ ኢንሱሊን ማምረት ያቅተዋል ወይም ሴሎቻችን ለኢንሱሊኑ ምላሽ መስጠት ያቆማሉ። ይህም የኢንሱሊን መቋቋም (Insulin Resistance) ይባላል። እውነተኛው ችግር የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው።
ለምን ስኳር ያላቸው ምግቦች ከስኳር ህመም ጋር ይያያዛሉ?
ይህንን በግልጽ እንረዳው። ስኳር በቀጥታ በአንድ እርምጃ ብቻ የስኳር ህመምን አያመጣም። ነገር ግን የተጨመረ ስኳር የበዛባቸው ምግቦች (በተለይም ለስላሳ መጠጦች) ለበሽታው የመጋለጥ እድልን በእጅጉ ይጨምራሉ።

ለምን? ስኳር ያለባቸው ምግቦች በሚመገቡበት ጊዜ የሚከተሉትን ሂደቶች በሰውነትዎ ውስጥ ይፈጠራሉ።
ከመጠን በላይ ኃይል ያገኛሉ (ካሎሪ )→ይህም የክብደት መጨመር ያመጣል።
የክብደት መጨመር በበኩሉ → የኢንሱሊን መቋቋም መጨመርን ያስከትላል።
የኢንሱሊን መቋቋም ደግሞ → በጊዜ ሂደት የደም ስኳር መጠን ከፍ እንዲል ያደርጋል።
ስለዚህ ዋናው ችግር ስኳሩ ብቻ ሳይሆን፤የአመጋገብ ዘይቤው፣ ከፍተኛ የካሎሪ ፍጆታ፣ የቃጫ (Fiber) እጥረት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ድምር ውጤት ነው። ስኳር ብቻ ፈጽሞ አይደለም።
ችግሩ ስኳር ብቻ አይደለም
ብዙዎቻችን ትኩረታችን ያለው ሻይ ውስጥ በምንጨምረው ስኳር ወይም በምንጠጣው ለስላሳ መጠጥ ላይ ነው። እርግጥ ነው፣ እነሱን መጠንቀቅ መልካም ነው፤ ግን ችግሩ እዚህ ጋር ብቻ አያበቃም።

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በነጭ ዱቄት የተጋገረ ዳቦ፣ የተቀነባበረ ነጭ ሩዝ እና የታሸጉ ፋብሪካ ስራ ምግቦች በደማችን ውስጥ የሚያስከትሉት ውጤት ልክ እንደ ስኳር ነው። እነዚህ ምግቦች በደም ውስጥ ያለ የስኳር መጠንን በፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራሉ። 'ከፍተኛ የሆነ ግላይሴሚክ ኢንዴክስ (Glycemic Index) አላቸው።
ስለዚህ 'ስኳር አቆምኩ' ብለን ፤ ነጭ ዳቦ ወይም ሩዝ ላይ ካልተጠነቀቅን፤ ግማሽ መንገድ ላይ ብቻ ነን ያለነው። ምክንያቱም ለሰውነታችን ስኳር ተመገብን ፤ ዳቦ ሆነ ሩዝ በሰውነትዎ ላይ የሚያሳድሩት ተጸእኖ ተቀራራቢ ነው።
በስኳር ህመምተኞች ላይ ስኳር ለምን ይከለከላል?

አንድ ሰው በስኳር ህመም ተያዘ ማለት ሰውነቱ በደሙ ውስጥ ያለውን ስኳር የማስተናገድ አቅሙ ተዳክሟል ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ ጣፋጭ ነገሮችን መመገብ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል። እንዴት ቢሉ?
በመጀመሪያ፣ ጣፋጩ ምግብ እንደተበላ በደማችን ውስጥ ያለው ስኳር በድንገት በጣም ይጨምራል። ይህ ደግሞ ቀድሞውኑ ዝልፍልፍ ላለውና ለተዳከመው የኢንሱሊን ስርአታችን የማይሸከመውን ተጨማሪ ጫና ይሳድራል።
ነገሩ እዚህ ላይ ብቻ አያበቃም፤ ይሄ በደም ውስጥ የበዛው ስኳር በጊዜ ሂደት ሰውነትን ይጎዳል። ቀስ እያለ የአይን ብርሃንን ይነጥቃል፤ ኩላሊትን ያዳክማል፤ እንዲሁም የነርቭ ስርአትን በማጥቃት ለከባድ መዘዞች ይዳርጋል።
ትልቁ ስህተት! “ስኳር ካቆምኩ በሽታው ይጠፋል”

ይህ በጣም የተለመደ እና አደገኛ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። ስኳርን ማቆም የደም ስኳርን ለመቆጣጠር ይረዳል፣ ክብደት ለመቀነስም ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ስኳር መቀነስ በራሱ በሽታውን ወዲያውኑ አያጠፋውም።
ምክንያቱም የስኳር ህመም የኢንሱሊን መቋቋምን፣ የጣፊያ ስራን እና የዘር ውርስን ጋር ቁርኝት ያለው ቋሚ የሰውነት ኡደት መዛባት ነው። አንዳንድ ሰዎች በአኗኗር ለውጥ የደም ስኳራቸውን ወደ ጤናማ ደረጃ ሊመልሱ ይችላሉ። ይህ ሪሚሽን (Remission) እንጂ ፈውስ (Cure) አይደለም፤ ምክንያቱም የአኗኗር ዘይቤው ከተቀየረ ምልክቶቹ ሊመለሱ ይችላሉ።
ስኳርን ለመቀነስ ፤ የታሸጉ ምግቦች ሲገዙ ምን ይዩ?
በሱፐርማርኬቶች ውስጥ “ጤናማ” ተብለው የሚሸጡ ብዙ ምግቦች የተደበቁ ስኳሮች ሊኖሯቸው ይችላል። ሰውነትዎን ለመጠበቅ የግድ የምርቱን ይዘት (Ingredients) እና የአመጋገብ መረጃ (Nutrition Facts) መመልከት አለብዎት።

ስኳር ብዙ ጊዜ ስሙን ቀይሮ ይደበቃል። በሚገዙት ዕቃ ላይ ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ይዘቶች ውስጥ እነዚህን ስሞች ካዩ፣ ዕቃውን መልሰው ያስቀምጡት!
ሀይ ፍሩክቶስ ኮርን ሲረፕ (High Fructose Corn Syrup)
ማልቶዴክስትሪን ወይም ዴክስትሮስ (Maltodextrin/Dextrose)
ኢንቨርት ሹገር ወይም ሞላሰስ (Invert Sugar/Molasses)
የፍራፍሬ ጭማቂ ክምችት (Fruit Juice Concentrates)
እነዚህ ስሞች ካሉ ስኳር መኖሩን ይወቁ።
የ"4-ግራም" ህግ
በምርቱ ማሸጊያ ላይ "Total Sugars" የሚለውን ይመልከቱ። ይህንን ቀመር ሁልጊዜ ያስታውሱ፦ 4 ግራም ስኳር = 1 የሻይ ማንኪያ ስኳር።
ለምን ይሄ አስፈላጊ ሆነ?
ምክንያቱም በፋብሪካ በተዘጋጁ ምግቦች ውስጥ ያለው ስኳር እንደ ፍራፍሬ ካሉ ተፈጥሯዊ ነገሮች የሚገኝ ሳይሆን "ፈጣን ስኳር" በመሆኑ ነው። በፋብሪካ የሚጨመር ስኳር በውስጡ ምንም አይነት ቃጫ (Fiber) ስለሌለው፣ እንደተመገብነው በቀጥታ ወደ ደም በመግባት የስኳር መጠንን በድንገት ያንራል።

ለምሳሌ የምትበሉት አንድ ትንሽ እርጎ 20 ግራም ስኳር ካለው ፤ በአንድ ጊዜ 5 የሻይ ማንኪያ ስኳር እየበላችሁ ነው ማለት ነው። ይህም ጣፊያዎ (Pancreas) ድንገት ለሚመጣበት ከፍተኛ ስኳር ተብሎ ያልተዘጋጀ ኢንሱሊን እንዲያመርት በማስገደድ ለከፍተኛ ድካም እና ለኢንሱሊን መቋቋም (Insulin Resistance) ይዳርጋል።
ለዚህም በማሸጊያው ላይ 4 ግራም ስኳር ካዩና በይዘቱ (Ingredients) ዝርዝር ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት ቃላት ከመጀመሪያዎቹ ሶስት ዝርዝሮች ውስጥ ከሉ ፤ ያ ምግብ ለጤናዎ ምንም ፋይዳ የሌለውና ለስኳር ህመም ተጋላጭ የሚያደርግ መሆኑን ይረዱ።
እነኝህን ካዩ ከመግዛት ቢቆጠቡ ይመከራል!
ከፍርሃት ወደ ግንዛቤ
የስኳር ህመም በአንድ ማንኪያ ስኳር የሚመጣ ሳይሆን የረጅም ጊዜ የአኗኗር ዘይቤ እና የሰውነት ኡደት መዛባት ውጤት ነው።
ስኳርን ማቆም ትልቅ እርምጃ ነው፤ ነገር ግን መፍትሄው እዛ ላይ አያበቃም። እውነተኛ ጥበቃ የሚመጣው ሰውነታችንን በማዳመጥ፣ ፋይበር (ቃጫ) ያላቸውን እንደ እንጀራ እና ጥራጥሬ ያሉ ምግቦችን በማዘውተር እና እንቅስቃሴ በማድረግ ነው።
ጤና በአንድ ውሳኔ የሚገነባ ሳይሆን፣ በየቀኑ በምናደርጋቸው ጥቃቅን ምርጫዎች ድምር ውጤት የሚገኝ ስጦታ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ስኳርን ብቻ ሳይሆን አኗኗርዎን ይቀይሩ!




Comments