top of page

ጋንግሪን፦ ምልክቶች፣ መንስኤዎች እና መከላከያ መንገዶች

ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በዝምታ ነው። በድንገት ሳይታሰብ ፤ ያለምንም ማስጠንቀቂያ።


ሲጀምር ጥቃቅን ጥቁር ነጠብጣቦች በጣት ጫፍ ላይ ይታያሉ። ቀጥሎም የማይድን፤ እረፍት የማይሰጥ ቁስል ይከተላል። ቀጥሎም እጅግ የሚከብድ ፤ ነፍስን የሚረብሽ መጥፎ ሽታ ቤቱን ይሞላዋል።


ጋንግሪን የሰውነት ህዋሳት (tissues) ሲሞቱ የሚከሰት ሁኔታ ነው። በሰውነት ውስጥ የሚካሄድ የድብቅ ጦርነት ውጤት!


እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የስኳር በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባቸው እና የደም ስር ሕክምና ገና ባልተስፋፋባቸው አገራት ፤ ጋንግሪን ብርቅ አይደለም። አውዳሚ ነው፤ አካልን ይበላል ፤ ሕይወትን ያናጋል። ጋንግሪን ከጊዜ ጋር የሚደረግ ሩጫ ነው።


በሀገራችን ብዙዎች በትናንሽ ቁስሎች ይዘናጋሉ። "ይድናል" በሚል ተስፋ በባህላዊ መድኃኒቶች ወርቃማውን የሕክምና ጊዜ ያባክናሉ። "አካል ይቆረጣል" የሚለው ፍርሃት ራሱ ፤ ታካሚዎች ወደ ሆስፒታል ዘግይተው እንዲመጡ ያደርጋል።


መፈራት የነበረበት ቀዶ ጥገናውን ሳይሆን ፤ ዘግይቶ መድረስ የሚያስከትለውን የማይመለስ ጥፋት ነበር።


ዛሬ ስለ ጋንግሪን በግልጽ እንነጋገራለን።


ጋንግሪን ምንድን ነው?

በቀላል አነጋገር ጋንግሪን ማለት በበቂ የደም ዝውውር እጥረት ወይም በከባድ ባክቴሪያ ወረራ ምክንያት የሰውነት ህዋሳት (tissues) ሲሞቱ የሚከሰት ሁኔታ ነው።


ደም ለሰውነታችን የህልውና መሰረት ነው። ለእያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ኦክስጅንን ፤ አልሚ ምግቦችን እና በሽታን የሚከላከሉ ነጭ የደም ሴሎችን ያቀርባል። ልክ የአንድ ተክል የውሃ መስመር ሲዘጋ እንደሚጠወልገው ሁሉ ፤ የደም ዝውውር ሲቋረጥም የሰውነት ክፍሎቻችን መኖር አይችሉም።


ጋንግሪን አከሳሰት ደረጃዎች ፡ መጀመሪያ የቆዳ መልክ ይለወጣል (ግራ) ፤ ሲቀጥል ቁስል ይኖራል (መሀል) ፤ መጨረሻ ላይ ጋንግሪን ይከሰታል።
ጋንግሪን አከሳሰት ደረጃዎች ፡ መጀመሪያ የቆዳ መልክ ይለወጣል (ግራ) ፤ ሲቀጥል ቁስል ይኖራል (መሀል) ፤ መጨረሻ ላይ ጋንግሪን ይከሰታል።

ሕዋሳቱ አንዴ መሞት ከጀመሩ ደግሞ ሥጋው መበስበስ ይጀምራል። ያ የሚከረፋና ነፍስን የሚረብሽ ሽታ የሚመጣውም ከዚሁ የሞተ ሥጋ ነው።


ነገር ግን ትልቁ አደጋ ሞቱ መጀመሪያ በተጠቁት ሕዋሳት ላይ አለመቆሙ ነው። ለዚህ መበስበስ ምክንያት የሆነው ባክቴሪያ እንደ ሰደድ እሳት አጠገብ ወዳሉ ጤናማ አካላት በፍጥነት ይስፋፋል። እነሱንም እየገደለ ጉዞውን ይቀጥላል። ጋንግሪን "ተላላፊ" የሚመስለውም ለዚህ ነው፤ ሳይቆርጡት የማይቆም ፤ ሳይገቱት የማይገታ የጥፋት ጉዞ!


የሕዋሳት መሞት ሂደት ጀርባ ያለው ባዮሎጂ

ነገሩን በቀላል ቀመር እንመልከተው። የሰውነታችን ጤንነት በዚህ ሚዛን ላይ የተመሰረተ ነው፦


ደም = ኦክስጅን + አልሚ ምግብ + የበሽታ መከላከያ

ይህ የሕይወት መስመር ከአንድ የሰውነት ክፍል ላይ ለረጅም ጊዜ ሲርቅ ፤ ያ አካል ቀስ በቀስ ወደ ሞት ይጓዛል። ሂደቱም እንዲህ ነው፦

  1. የኃይል መቋረጥ፦ መጀመሪያ ሕዋሳቱ ነዳጅ እንደጨረሰ ሞተር ኃይል ማመንጨት ያቆማሉ።

  2. የመዋቅር መፈራረስ፦ ቀጥሎም የሕዋሳቱ ሽፋን ጥንካሬውን ያጣና መፈራረስ ይጀምራል።

  3. የማይመለስ ጥፋት (Necrosis)፦ በመጨረሻም ሕዋሳቱ ሙሉ በሙሉ ይሞታሉ። ይህ "ኔክሮሲስ" ወይም የማይመለስ የሥጋ መበስበስ የምንለው አስፈሪ ደረጃ ነው።


ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም። ባክቴሪያዎች ይህንን የሞተ ሥጋ እንደ መራቢያ ካገኙት ጥፋቱ እንደ ሰደድ እሳት ይፋጠናል! ውጤቱም የሚታይና የሚሰማ ይሆናል። የጠቆረ ፤ የሰለለ ፤ ያበጠ ወይም የሚገማ ሥጋ።


ይህ የማይታይ ጦርነት ውጤት ነው። ደም ለሕዋሳቱ መድረስ ሲያቅተው ፤ ባክቴሪያዎች በሞተው ሥጋ ላይ አስፍተው ይሰፍራሉ።


አራቱ ዋና ዋና የጋንግሪን ዓይነቶች

ጋንግሪን እንደየመጣበት መንገድ እና እንደ ጥፋት ፍጥነቱ በአራት ዋና ዋና ዓይነቶች ይከፈላል። እያንዳንዱ ዓይነት የራሱ የሆነ የጥፋት ምልክት አለው፦

እርጥብ ጋንግሪን ያለባት ግለሰብ የመጀመሪያ ደረጃ
እርጥብ ጋንግሪን ያለባት ግለሰብ የመጀመሪያ ደረጃ
  1. ደረቅ ጋንግሪን (Dry Gangrene) — "ዝምተኛው ገዳይ"


    ይህ በአብዛኛው ያለ ኢንፌክሽን ፤ በደም ዝውውር እጥረት ብቻ የሚከሰት ነው። በስኳር በሽተኞች እና በደም ስር በሽታ ተጠቂዎች ላይ በብዛት ይታያል። ሥጋው ቀስ በቀስ ይደርቃል። ይጠቁራል። በመጨረሻም ልክ እንደ ደረቅ እንጨት ይረግፋል። ሂደቱ ዝግተኛ በመሆኑ ብዙዎች ሳይረዱት ጊዜ ያባክናሉ።


  2. እርጥብ ጋንግሪን (Wet Gangrene) — "ድንገተኛው ወራሪ"


    የደም ዝውውር መቋረጥ ከባክቴሪያ ኢንፌክሽን ጋር ሲቀላቀል የሚፈጠር እጅግ አደገኛ ሁኔታ ነው። እዚህ ጋር ሥጋው አይደርቅም። ይልቁንም ያብጣል ፤ ይረጥባል። እንዲሁም የሚረብሽ የመበስበስ ጠረን ያመጣል። ይህ ዓይነቱ ጋንግሪን በሰዓታት ውስጥ ስለሚስፋፋ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ይሻል።


  3. የጋዝ ጋንግሪን (Gas Gangrene) — "ውስጣዊው ቦምብ"


    ይህ ዓይነቱ ጋንግሪን መርዛማ ጋዝ በሚያመነጩ ባክቴሪያዎች የሚመጣ ሲሆን ፤ በብዛት ከባድ ቁስል ባለባቸው ሰዎች ላይ ይታያል። ባክቴሪያዎቹ በቆዳ ስር አየር ስለሚረጩ ፤ ሲነካ አየር እንዳለ ሆኖ "ጠር-ጠር" የሚል ድምፅ ይሰማል። በፍጥነት ወደ ደም በመቀላቀል ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ገዳይ ዓይነት ነው።


  4. ፎርኒየርስ ጋንግሪን (Fournier’s Gangrene) — "ፈጣኑ አጥፊ"


    በብልት እና አካባቢው ላይ የሚከሰት ፤ እጅግ ፈጣን እና አስከፊ ኢንፌክሽን ነው። ይህ ዓይነቱ ጋንግሪን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ጤናማ ሕዋሳትን የማውደም አቅም ስላለው ፤ከፍተኛ ትኩረትና ፈጣን ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል።


ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው?

ጋንግሪን በድንገት የሚከሰት ክስተት ሳይሆን ፤ የሰውነታችን የተፈጥሮ ጥበቃ መስመሮች ሲዳከሙ የሚመጣ የጤና ቀውስ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ፤ በተለይም በኢትዮጵያ ለዚህ አደገኛ ሕመም ዋነኛ መንስኤ የሚሆኑት የሚከተሉት ናቸው፦


  • የስኳር በሽታ ፦ በኢትዮጵያ የጋንግሪን ቁጥር እንዲጨምር ያደረገው ቀዳሚ ምክንያት ነው ይህ ነው። በኢትዮጵያ ካሉ የስኳር በሽተኞች ውስጥ ከ15% እስከ 25% የሚሆኑት በእድሜ ዘመናቸው የከፋ የእግር ቁስል (Foot Ulcer) ያጋጥማቸዋል። ይህ ቁስል በወቅቱ ካልታከመ በቀጥታ ወደ ጋንግሪንና ወደ አካል መቆረጥ (Amputation) ያመራል።

  • የደም ስር መጥበብ (PAD)፦ የደም ስሮች በስብ ወይም በሌላ ምክንያት ሲጠቡ ፤ ሕዋሳቱ የሚፈልጉትን ኦክስጅን አያገኙም። ይህም ለጋንግሪን ያጋልጣል።


  • ከባድ አደጋዎችና ቁስሎች፦ ድንገተኛ አደጋዎች፣ ቃጠሎዎች ፣ ወይም ጥልቅ የሆኑ የመኪና አደጋ ቁስሎች ለባክቴሪያዎች መግቢያ በር በመሆን የጋዝ ጋንግሪን (Gas Gangrene) ሊያስከትሉ ይችላሉ።


  • የሰውነት በሽታ መከላከያ አቅም መቀነስ፦ እንደ ኤች.አይ.ቪ (HIV) ፤ ካንሰር ወይም በኬሞቴራፒ ምክንያት የመከላከል አቅማቸው የደከመ ሰዎች ፤ ትናንሽ ኢንፌክሽኖችን እንኳ መቋቋም ስለማይችሉ ለጋንግሪን ተጋላጭ ናቸው።


በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አሳሳቢ የሚያደርገው ምንድነው?

በአገራችን የስኳር በሽታ ስርጭት እየጨመረ እየመጣ ነው።  በቅርብ የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የደም ግፊትና ስኳር ባለባቸው ታካሚዎች ላይ የደም ስር መጥበብ (Peripheral Arterial Disease) በከፍተኛ ሁኔታ እየታየ ይገኛል። ከዚህም በላይ ፤ ብዙ ታካሚዎች የሕመሙ ምልክት ሳይታይባቸው ለረጅም ጊዜ ስለሚቆዩ ፤ ሆስፒታል የሚደርሱት ጋንግሪኑ ሥር ሰዶ አካል መቆረጥ የግድ በሚሆንበት ደረጃ ላይ ነው።


የጋንግሪን ምልክቶች


ያስተውሉ መደንዘዝ የመሻል ምልክት አይደለም
ያስተውሉ መደንዘዝ የመሻል ምልክት አይደለም
  • የቆዳ ቀለም መለወጥ (ከቀይ → ወደ ሐምራዊ/ጥቁር ሰማያዊ → ወደ ጥቁር (ሕዋሳቶቹ ሲሞቱ) )


  • መጀመሪያ ላይ  የማይታገስ ከፍተኛ ህመም ይሰማል።


  • ሕዋሳቱና ነርቮቹ መሞት ሲጀምሩ ሕመሙ ይጠፋና አካባቢው ይደነዝዛል።(ሕመሙ መጥፋቱ "ዳኑ" ማለት ሳይሆን ፤ አደገኛ ምልክት መሆኑን ልብ ይበሉ)


  • በተለይ በእርጥብ ጋንግሪን ወቅት ፤ ቆዳው ይወጥራል ፤ ያብጣል እንዲሁም መግል ወይም ደም የቀላቀለ ፈሳሽ ይወጣል።


  • ሕዋሳቱ/ስጋው ሲሞት ከባድ ሽታ ይኖረዋል።


  • ኢንፌክሽኑ ወደ ደም ከተቀላቀለ ከፍተኛ ትኩሳት ፤

    ብርድ ብርድ ማለት እና የልብ ምት መጨመር ይከሰታል። (ይህ አደገኛ ነው)


ደገኛ ምልክቶች (አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው)

ጋንግሪን ጊዜ አይሰጥም። "ነገ እሄዳለሁ" የሚባልለት ሕመምም አይደለም። የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩዎት ፤ ሕይወት የመጥፋት አደጋ ስለተጋረጥዎ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል መሄድ ይኖርብዎታል፦



  • የጣት መጥቆር ፦ የእግር ወይም የእጅ ጣትዎ ቀለሙን ቀይሮ ወደ ጥቁርነት ካዘነበለ ፤ ያ አካል ኦክስጅን አጥቶ እየሞተ መሆኑን የሚያሳይ የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ ነው።

  • የሰደድ እሳት ስርጭት፦ የቆዳ መቅላትና እብጠቱ በዓይንዎ እያዩት በፈጣን ሁኔታ ወደ ላይ የሚሰራጭ ከሆነ ፤ ባክቴሪያው በከፍተኛ ፍጥነት ጤናማ ሕዋሳትን እየወረረ መሆኑን ያሳያል።

  • የበሰበሰ ሥጋ ሽታ፦ ከቁስልዎ የሚወጣው ሽታ የሚረብሽ ከሆነ ፤ በሰውነትዎ ውስጥ የሞቱ/እየበሰበሱ ያሉ ሕዋሳት መኖራቸውን ይጠቁማል።

  • ድንገተኛ ግራ መጋባት፣ የሰውነት መዛል፣ ወይም ከፍተኛ ድካም ከተሰማዎት፣ ኢንፌክሽኑ ወደ ደምዎ ውስጥ ገብቶ ሊሆን ይችላል። ይህ በሰዓታት ውስጥ ለሞት ሊያደርስ የሚችል አደገኛ ደረጃ ነው።


እነዚህን ምልክቶች ሲያዩ ፈጽሞ የባህል ሐኪም ጋር እንዳይሄዱ። በሕይወትዎ ይፈርዳሉ!

ምርመራ እና ሕክምና


ጋንግሪንንን ለመለየት ዶክተሮች በአካላዊ ምርመራ ብቻ አይወሰኑም። ሐኪሞች የኢንፌክሽኑን ጥልቅነት በደም ምርመራ ፤ የደም ስሮችን ስራ በዶፕለር (Doppler) አልትራሳውንድ እና የጋዝ መኖርን በራጅ (X-ray) ያረጋግጣሉ።


በሽታው ከተረጋገጠ በኋላ የመጀመሪያውና ዋናው ተግባር የጠፋውን የደም ዝውውር መመለስ ነው። የሞተ ሥጋ ለባክቴሪያዎች ምርጥ መራቢያ ስለሆነ ፤ ሐኪሞች የሞተውንና የተበከለውን ሥጋ በጥንቃቄ ያስወግዳሉ። አንዳንዴ ኢንፌክሽኑ ወደ መላ ሰውነት ተሰራጭቶ ሕይወትን እንዳይቀጥፍ ሲባል "አካልን መቁረጥ" (Amputation) እንደ የመጨረሻ አማራጭ ሊወሰድ ይችላል።


ታድያ ለምንድነው ኢትዮጵያ ላይ አብዛኛውን ጊዜ አካል የሚቆረጠው?

ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ታካሚዎች ሆስፒታል የሚደርሱት ጋንግሪኑ አጥንት ደርሶና ሥጋው በስብሶ ካበቃ በኋላ ነው። ቀድሞ ምልክቶቹን እንዳዩ አይመጡም። የታካሚን ሕይወት በትንሹ አካል ለመለወጥ ሲባል፤ ዶክተሮች ይህን መራራ ግን አስፈላጊ ውሳኔ ይወስናሉ።


ኢንፌክሽኑንም ለመቆጣጠር የኢንፌክሽን መቃወሚያ አንቲባዮቲክ ይሰጣል። ከዚህም ባሻገር ከጀርባ ያለ ህመም (ደምግፊት ወይም ስኳር) ለመቆጣጠር ይሞከራል። ህመሙን ለማስታገስም የህመም ማስታገሻ ይሰጣል።


ጋንግሪን ዕጣ ፈንታ አይደለም፦ መከላከል ይችላሉ!

ትልቁ የምስራች ይህ ነው፦ አብዛኛው ጋንግሪን መከላከል ይቻላል! በተለይ የስኳር ሕመም ያለባችሁ ወገኖቻችን ፤ ጥቂት ቀላል ጥንቃቄዎችን በማድረግ አካልንና ሕይወትን መታደግ ይቻላል። ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ።

  • በየቀኑ እግርን መመርመር

  • ትክክለኛ ጫማ ማድረግ

  • የስኳር መጠንን በጥብቅ መቆጣጠር

  • ሲጋራ አለማጨስ

  • ቁስል ሲፈጠር ወዲያው መታከም


የጋንግሪን ህክምና ከጊዜ ጋር የሚደረግ ሩጫ ነው።


ጋንግሪን አንድ ከባድ እውነት ያስተምረናል፦ ሕይወት በደም ዝውውር ላይ የተመሰረተች ናት።


ደም ቀይ ፈሳሽ ብቻ አይደለም። ኦክስጅን ነው፤ መከላከያ ነው፤ ፈውስ ነው ፤ ሕልውና ነው።


ጋንግሪን ከመጮኹ በፊት በለሆሳስ ምልክት ያሳያል። በጊዜ መታከም ማለት ጣትን ከማጣትና እግርን ከማጣት መካከል ያለው ልዩነት ነው።


በጋንግሪን ውስጥ ጊዜ ማለት አካል ነው፤ አካል ደግሞ ሕይወት ነው።


ምን ይጠብቃሉ!?

ዛሬውኑ እግርዎን ይመርምሩ!

ዛሬውኑ ስኳርዎን ይቆጣጠሩ!

ዛሬውኑ ለጤናዎ ይቁሙ!



Comments


bottom of page