ስለ ሪህ ማወቅ ያለብዎ
- Zebeaman Tibebu
- May 3
- 5 min read
ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በዝምታ ነው!
ሪህ ያለበት ሰው ቀኑን ደህና ሆኖ ውሎ ፤ ሌሊት ሲሰቃይ ሊያሳልፍ ይችላል። አንሶላ ሲነካው እንኳን የሚያሳብድ ፤ የሚመዘምዝ/ የሚለበልብ/ የሚቆረጥም ከባድ ህመም አለው። ህመሙ እጅጉን ከባድ ነው። የሆነ ባዕድ ነገር መገጣጠሚያ ውስጥ ገብቶ የሚወጋና የሚቆረጥምም ይመስላል።

ከዘመናዊው ሕክምና ዕውቀት በፊት፤ ይህ ድንገተኛና ክፉ ስቃይ "በመገጣጠሚያ ውስጥ በሰፈረ ርኩስ መንፈስ" የሚመጣ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ይህም ሕመሙ ካለው ኃይል የተነሳ ነበር። በወቅቱም አንድ የማይታይ ክፉ ኃይል መገጣጠሚያን ቆንጥጦ ይዞ / እየቀጠቀጠ ያሳምማል ተብሎ ይታሰብ ነበር (እላይ ያለውን ምስል ይመልከቱ)። ለዚህም ብዙዎች መንፈሳዊ መፍትሔዎች ይፈልጉት ነበር።
ቆየት ብሎም በሽታው "የነገሥታት በሽታ" የሚል ስያሜ አገኘ። ይህ የሆነው በሽታው የላቀ ክብር ኖሮት ሳይሆን፤ ከቅንጦት አመጋገብ፣ ከሥጋ ብዛትና፣ ከመጠን ካለፈ መጠጥ ጋር ተያይዞ ስለሚከሰት፤ በወቅቱ ድሎት ያላቸው ወገኖች ብቻ የሚያስተናግዱት በመሆኑ ነበር።
ዛሬ ግን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ በሽታ ሆኗል። በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ የአኗኗር ዘይቤ መለወጥን ተከትሎ የሪህ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም፤ አሁንም ድረስ በበሽታው ዙሪያ ባለ የግንዛቤ ክፍተት ፤ እንደ ተራ ቁርጥማት ታይቶ በአግባቡ ሳይታከም ረዥም ጊዜ ይቆያል። ይህም በሽታው እንዲባባስ እድልን ይከፍታል።
በደንብ ለመረዳት ስለ ሪህ በጥልቀት እንመልከት...
ሪህ በትክክል ምንድን ነው?
ሪህ በዋናነት የመገጣጠሚያ ሕመም ብቻ ሳይሆን ፤ የሰውነት ባዮኬሚካላዊ ኡደት (Metabolism) መዛባት ውጤት ነው። ይህ ችግር የሚከሰተው ዩሪክ አሲድ (Uric acid) የተባለ ዝቃጭ በመገጣጠሚያዎች ውስጥ ሲከማች በሚፈጠር የመቆጣት (Inflammation) ዓይነት ነው። ዩሪክ አሲድ ደግሞ ሰውነታችን ፒዩሪን (Purines) የተባሉ ውህዶችን ሰባብሮ ወደ ጥቅም ሲቀይር የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ተረፈ ምርት ነው።

በጤናማ ሰውነት ውስጥ የተመረተው ዩሪክ አሲድ በደም ውስጥ ይሟሟል። ደም ውስጥ ያለው ዩሪክ አሲድም ኩላሊት ጋር ሲደርስ ተጣርቶ በሽንት መልክ ከሰውነት ይወገዳል። ይህ ኡድት ሲስተጓጎል ሪህ ይፈጠራል። ይህም የሚፈጠረው ሰውነታችን ከመጠን በላይ ዩሪክ አሲድ ሲያመርት (ስጋ በመብላት፣ ወ.ዘ.ተ....) ወይም ኩላሊታችን ዝቃጩን በአግባቡ ማስወገድ ሲያቅተው(የኩላሊት ችግር ሲኖር) በደማችን ውስጥ ያለው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
ዋናው ችግር የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው። በደም ውስጥ ያለው የዩሪክ አሲድ መጠን እጅጉን ሲበዛ ፤ የዩሪክ አሲድ ዝቃጩ ወደ ክምችት ይቀየራል። ይህም ክምችት እንደ መርፌ የሾሉ ክሪስታሎች በውስጡ ያሉት ሲሆን ፤ በመገጣጠሚያዎች ውስጥ ይሰበሰባል። ይህም መውጋትና መቆርጠም ይጀምራል። ይህም ለከፍተኛ ስቃይ፤ ለመገጣጠሚያ መቆጣትና ለድንገተኛ እብጠት ዋነኛው ምክንያት ይሆናል።
ሪህ ለምን በጣም ያማል?
ሪህ ዝምተኛ አይደለም።

ዋናው መለያው በድንገት የሚመጣ ከፍተኛ ህመም ነው። ህመሙ ከባድ ከሆኑ የመገጣጠሚያ ህመሞች ተርታ ይመደባል። የሚሰማውም ብዙውን ጊዜ በሌሊት ወይም በማለዳ ላይ ነው።
ብዙውን ጊዜ የሚጠቃው መገጣጠሚያ የእግር ትልቁ ጣት ስርን(ኳሱን)ነው። ይህም ህመም ፖዳግራ/Podagra ይባላል። ይህ የተለመደው ቦታ ይሆን እንጂ ፤ ሪህ ቁርጭምጭሚትን፣ ጉልበትን፣ የእጅ ጣቶችን እና ክርንን ሊያጠቃ ይችላል።
ታድያ ህመሙ ለምን ይበረታል?
የሕመሙ ግዝፈትና የጥቃቱ ድንገተኛነት የሚያያዘው ፤ የሰውነታችን የበሽታ መከላከል ሥርዓት ከሚሰጠው ምላሽ ነው። የሰውነታችን መከላከያ ሰራዊት እነዚህን በመገጣጠሚያ ውስጥ የተከማቹ መርፌ መሰል ክሪስታሎች እንደ ባዕድ ወራሪ ይመለከታቸዋል። ለዚህም ነጭ የደም ህዋሳት ወደ ተጠቂው ቦታ በከፍተኛ ሁኔታ ይዘምታሉ። እነኝህ ህዋሳት በሚያደርጉት ጥቃት (የሰውነታችን የተጋነነ ምላሽ) የሪህ ምልክቶች ይታያሉ። መገጣጠሚያው ያብጣል ፤ ይቀላል ፤ሙቀት ይኖረዋል/ለንክኪ ያተኩሳል እንዲሁም ሥሥ ነገር እንኳን ሲነካው እጅጉን ያማል።
ይህ ሂደት ሰውነታችን ራሱን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ቢሆንም፤ ውጤቱ ግን ልብስ ሲነካው የሚብስ ጽኑ ስቃይ ይሆናል።

💡 ያስተውሉ፦ ድንገተኛ የሆነ የመገጣጠሚያ ሙቀት እና እብጠት ለመጀመሪያ ጊዜ ካጋጠመዎት ወደ ሕክምና ባለሙያ መሄድ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ምልክቶቹ ከሪህ ጋር የሚመሳሰል ግን አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልገው ሌላ የመገጣጠሚያ ኢንፌክሽን (septic arthritis) ሊሆን ስለሚችል ነው። ለዚህም በቤት ውስጥ በሚደረግ ህክምና ብቻ ማለፍ አደጋ አለው።
የሪህ በሽታ ለምን እየጨመረ መጣ?
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሪህ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ይህ ለውጥ በግልጽ እየታየ ይገኛል።

ለዚህ መባባስ ዋነኛው ምክንያት የከተማ ነዋሪ መሆን ያስከተለው የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ነው። በተለይም የስጋ፣ የለስላሳ ስኳር መጠጦች እና የተቀነባበሩ ምግቦች ፍጆታ መጨመር፤ ከሰውነት እንቅስቃሴ መቀነስ ጋር ተዳምሮ ለዩሪክ አሲድ መከማቸት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።በመሆኑም ሪህ የአንድ መገጣጠሚያ ሕመም ብቻ ሳይሆን፤ አጠቃላይ የጤና ሁኔታችንና የአኗኗር ዘይቤያችን ነጸብራቅ ነው።
ለሪህ ተጋላጭ ማነው?
ከአኗኗር ዘይቤ ባሻገር፤ ለሪህ በሽታ ተጋላጭነትን የሚጨምሩ የተፈጥሮ እና የግል ሁኔታዎች አሉ። እነዚህም በሽታው በማን ላይ በብዛት ሊከሰት እንደሚችል ፍንጭ ይሰጡናል።

ጾታ እና እድሜ፦ ሪህ በብዛት በወንዶች ላይ የሚታይ በሽታ ሲሆን፤ በተለይም ከ30 እስከ 50 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ በስፋት ይከሰታል። ሴቶች ደግሞ የመውለጃ እድሜያቸው እስኪያልፍ (Menopause) ድረስ ባለው ጊዜ በሰውነታቸው ውስጥ በሚመነጨው የኢስትሮጅን ሆርሞን ጥበቃ ስለሚያገኙ ተጋላጭነታቸው አነስተኛ ነው። ነገር ግን ከዚያ በኋላ በሴቶች ላይም ተጋላጭነቱ እየጨመረ ይሄዳል።
የቤተሰብ ታሪክ (ዘረመል)፦ በቤተሰብዎ ውስጥ የሪህ ተጠቂ ካለ፤ እርስዎም የመያዝ ዕድልዎ ከፍተኛ ነው። ይህም የሰውነታችን የሜታቦሊዝም ኡደትና ዩሪክ አሲድን የማስወገድ ብቃት በከፊል በዘር የሚወረስ በመሆኑ ነው።
የጤና ሁኔታዎች፦ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የደም ግፊት፣ ስኳር፣ የልብ እና የኩላሊት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ለሪህ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም አንዳንድ የደም ግፊት መድኃኒቶች በደማችን ውስጥ የዩሪክ አሲድ መጠንን ሊጨምሩ ይችላሉ። የበሽታውም መጭመር በአንድ በኩል ከዚህ ጋር ተያያዥነት አለው።
የምግብ ጥያቄ፦ ሪህን በትክክል የሚያመጣው ምንድን ነው?
ሪህ የሚመጣው "ብዙ ስጋ በመብላት" ብቻ ነው የሚል የተሳሳተ እምነት በማህበረሰባችን ውስጥ ይታያል። ይህ አመለካከት በከፊል እውነት ቢሆንም፤ ሙሉውን ምስል ግን አይገልጽም።

እርግጥ ነው፤ እንደ ጥሬ ስጋ (ክትፎ ወይም ቁርጥ)፤ እንደ ጉበት እና ኩላሊት ያሉ አካላትን መመገብ እና የተወሰኑ የባህር ምግቦች በውስጣቸው ባለው ከፍተኛ የፒዩሪን መጠን አላቸው። ለዚህም የዩሪክ አሲድን ክምችት ይጨምራሉ።
በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ቢራ እና ጠጅ ያሉ የአልኮል መጠጦች በሰውነታችን ውስጥ ዩሪክ አሲድ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመረት በማድረግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኩላሊት ዝቃጩን እንዳያስወግድ በማሰናከል ለሕመሙ መባባስ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።
ከስጋ ባልተናነሰ ሁኔታ የስኳር መጠጦችም (በተለይም ፍሩክቶስ ያላቸው ለስላሳዎችና የታሸጉ ጭማቂዎች) ለሪህ ተጋላጭነትን በእጅጉ ይጨምራሉ።
በአንጻሩ ደግሞ እንደ ወተትና እርጎ ያሉ የምግብ አይነቶች የዩሪክ አሲድ መጠንን የመቀነስ ባህሪ አላቸው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የጾም ምግቦች (አትክልትና ጥራጥሬዎች) ለሪህ ህመምተኞች እጅግ ተስማሚና ጤናማ አማራጮች ናቸው።
ህመሙ ከመጀመሩ በፊት
አንድ ሰው ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ሳይታይበት ለዓመታት በደሙ ውስጥ ከፍተኛ የዩሪክ አሲድ መጠን (Hyperuricemia) ሊኖረው ይችላል። ይህ ወቅት በሽታው በሰውነት ውስጥ ጫና የሚያሳድርበት ፤ ነገር ግን ገና ያልጀመረበት ረቂቅ ምዕራፍ ነው።

እዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ ፤ የሕመም ምልክቶች እስካልታዩ ወይም ሌሎች ለከፋ ችግር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እስካልኖሩ ድረስ ወዲያውኑ መድኃኒት ላለመጀመር ይመከራል። ይሁን እንጂ ምልክቶቹ አንዴ ከታዩና ሕመሙ ከቀሰቀሰ፤ በሽታው ወደ አዲስና አስቸጋሪ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ማለት ነው።
ይህም ማለት ሰውነታችን ውስጥ ያሉት ክሪስታሎች መከማቸት ብቻ ሳይሆን፤ መገጣጠሚያችንን ማጥቃት መጀመራቸውን የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ ምልክት ነው። በመሆኑም በዚህ ወቅት ወደ ሕክምና በመሄድ ተገቢውን ክትትል ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
የሕክምና ዘዴዎች
የሪህ ሕክምና ዋና ግብ ሕመምን ማስታገስ ብቻ ሳይሆን፤ መሠረታዊ የሆነውን የሰውነት ባዮኬሚካላዊ ኡደት (Metabolism) መቆጣጠር ነው። ሕክምናው እና የመከላከያ እርምጃዎቹ በሚከተሉት ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ይጠቃለላሉ፦

፩. አፋጣኝ ሕክምና ማድረግ፦
ድንገተኛ ሕመም በሚቀሰቅስበት ወቅት ዋነኛው ግብ እብጠትንና ስቃይን መቀነስ ነው። ለዚህም የሕክምና ባለሙያዎች የተለያዩ መድሐኒቶችን ያዝዛሉ።
፪. የአኗኗር ዘይቤና የምግብ ምርጫ፦
ሪህን ለመከላከልና የዩሪክ አሲድ መጠንን ለማመጣጠን የሚከተሉት እርምጃዎች ወሳኝ ናቸው፦
ውህ አብዝቶ መጠጣት ይመከራል። በቂ ውኃ መጠጣት ኩላሊታችን ዩሪክ አሲድን በቀላሉ አጥልቶ እንዲያስወግድ ይረዳዋል።
የምግብ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርብዎታል። ከፍተኛ ፒዩሪን ያላቸውን ምግቦች (ቀይ ሥጋና የውስጥ አካላት) መቀነስ፤ እንዲሁም በስኳር የበለፀጉ ለስላሳዎችንና አልኮልን ማስወገድ።
ክብደትን ይቆጣጠሩ። ከልክ ያለፈ ውፍረት ለሪህ ተጋላጭነትን ስለሚጨምር፤ ጤናማ የሰውነት ክብደትን መጠበቅና መጠነኛ እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

፫. የረዥም ጊዜ ክትትል
ሪህ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ በየጊዜው የሚመላለስ በሽታ ነው። በመሆኑም የሕመሙ ጥቃት ተደጋጋሚ ከሆነ፤ የዩሪክ አሲድ መጠንን በቋሚነት የሚቀንሱ መድኃኒቶችን መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል። በየጊዜው የዩሪክ አሲድ መጠንን በደም ምርመራ መከታተልና ከሐኪም ጋር መመካከር በሽታው ወደ ከፋ ደረጃ (የመገጣጠሚያ እብጠትና የኩላሊት ጠጠር) እንዳይሸጋገር ይረዳል።ረጅም ጊዜ ህክምና ደግሞ የዩሪክ አሲድ መጠንን የሚቀንሱ መድሃኒቶችን መውሰድን ያካትታል።
⚠️ ጠቃሚ ጥንቃቄ፦ የረጅም ጊዜ መድሃኒቶች ከፍተኛ ህመም ባለበት ወቅት መጀመር የለባቸውም! ምክንያቱም ድንገተኛ የዩሪክ አሲድ መጠን ለውጥ ፤ ህመሙን ሊያባብሰው ይችላል። ህመሙ ጋብ ሲል መጀመር ይመረጣል።
ሪህ ችላ ቢባል ምን ይከሰታል?
ሪህ የ"ህመም" ጉዳይ ብቻ አይደለም። ካልታከመ ወደ ስር የሰደደ እና ከባድ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል።

ሪህ የ"ሕመም" ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ካልታከመ ወደ ስር የሰደደ እና አውዳሚ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል። በሽታው በወቅቱ ካልተገታ መገጣጠሚያን ደጋግሞ ያጠቃል። ይህም በጊዜ ውስጥ ብዙ የዩሪክ አሲድ ክምችት መጋጠሚያ ላይ እንዲኖር ከማድረጉ ባሻገር ፤ እላይ በምስሉ እንደሚታየው የመገጣጠሚያን ቅርጽ በቋሚነት ሊለውጥ ይችላል። ይህ ክምችት በህክምናው ቶፋይ (Tophi) ይባላል። በመገጣጠሚያዎች ዙሪያ ስለሚገኝ ከመልክ ባሻገር ፤ የመገጣጠሚያን እንቅስቃሴ ይገድባሉ።
ኩላሊት ላይም ዩሪክ አሲድ ከተከማቸ ፤ ለኩላሊት ጠጠር እንዲሁም ለኩላሊት ችግር ሊያጋልጥ ይችላል።
ያስተውሉ!
ሪህ የመገጣጠሚያ ህመም ብቻ አይደለም። የበሽታው ስቃይ እጃችን ላይ እንደሆነው ሁሉ መፍትሄውም በእጃችን ላይ ይገኛል።
ዛሬ የምናደርገው የአመጋገብ ምርጫ፤ የምንወስደው የውሃ መጠን እና ለጤናችን የምንሰጠው ትኩረት የነገውን ጤንነት ይወስነዋል።
ሕመሙ እስኪቀሰቅስ አይጠብቁ።
ምልክቱ ከታየዎት ወደ ሕክምና በመሄድ ተገቢውን ምርመራ ያድርጉ፤ የአኗኗር ዘይቤዎን ያስተካክሉ፤ ጤናዎን በንቃት ይጠብቁ።




Comments