ቤተሰብዎን ከአየር ብክለት እንዴት ይጠብቃሉ?
- Zebeaman Tibebu
- 5 days ago
- 4 min read
አዲስ አበባ ነቅታለች!
እንደወትሮው ሁሉ የትራፊክ ጫጫታው ከተማዋን ሞልቶታል። የሞተሮች ድምፅ ይነሳል፤ የመኪና ጥሩምባዎች በህንፃዎች መካከል ይስተጋባሉ። ሰዎች ወደ ስራ፤ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ይጣደፋሉ። ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ከፍተው ደንበኛ ይጠብቃሉ።
ሁሉም ነገር የተለመደ ይመስላል።

ሆኖም ግን አንድ ችላ የሚባል ስጋት አለ.... በእያንዳንዱ ትንፋሻችን ውስጥ በዝምታ የሚገባ ጠላት እርሱም የአየር ብክለት ነው።
ይህ ጠላት ወዲያውኑ አያስደነግጥም። ነገር ግን ቀስ እያለ በጤናችን ላይ ጥቃት ይሰነዝራል።
የሚያስደነግጠው እውነታ ግን ይሄ ነው፦
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2021 ብቻ በአየር ብክለት ምክንያት ከ 76,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል።
በተለይም እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት፤ የአየር ብክለት ከምግብ እጥረት ቀጥሎ ዋነኛው የሞት መንስኤ ነው።
እናስ በቀላሉ የምንተነፍሰው አየር፤ በዝምታ ህይወታችንን እያሳጠረው ይሆን?
ይሄ ጉዳይ "ለነገ" የሚባል አይደለም፤ ዛሬውኑ ልናስብበት የሚገባ የህልውና ጉዳይ ነው።
🏙️ የማይታየው የከተማ እውነታ

እንደ አለም ጤና ድርጅት (WHO) መረጃ፤ የአየር ብክለት የሚፈጠረው ከተሽከርካሪ ጭስ፣ ከፋብሪካዎች እና ከከሰል ወይም ከቆሻሻ መቃጠል በሚወጡ መርዛማ ቁሶች ነው።
አደገኛ የሚያደርገው ይዘቱ ብቻ ሳይሆን አለመታየቱ ነው።
የአየር ብክለት ከሚያመጡት ውህዶች ውስጥ እጅጉን ጥቃቅን የሆኑ ቅንጣቶች ይገኙበታል። እነዚህ በተለይ መጠናቸው አንድ አንድሚሊየነኛ አከባቢ ያሉት(በተለይ PM2.5 ተብለው የሚጠሩ እጅግ ጥቃቅን ቅንጣቶች) በሰውነታችን የተፈጥሮ መከላከያን በቀላሉ አልፈው ወደ ሳምባ በቀላሉ ይገባሉ። አልፎ ተርፎም ወደ ደም ዝውውር ይገባሉ። እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የነዚህ ቅንጣቶች መጠን ከአለም ጤና ድርጅት የደህንነት መስፈርት ከ4 እስከ 7 እጥፍ ብልጫ እንዳለው ተመዝግቧል።
🫁 የአየር ብክለት በሰውነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት
የመተንፈሻ አካላት የዚህ ስውር ጥቃት የመጀመሪያ ሰለባዎች ናቸው። ለተበከለ አየር መጋለጥ የአስም በሽታን ያባብሳል፤ ለከባድ የሳምባ መቆጣት (Bronchitis) ያጋልጣል እንዲሁም የሳምባን ኦክስጅን የመቀበል አቅም በእጅጉ ያዳክማል።

ነገር ግን ጉዳቱ እዚህ ላይ አያበቃም።
ረጅም ጊዜ ለብክለት መጋለጥ ከልብ እና የደም ዝውውር በሽታዎች፣ ከደም ግፊት እና ከስትሮክ (Stroke) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ። ሳይንሳዊ እውነታው እንደሚጠቁመው፤ ጥቃቅን የብክለት ቅንጣቶች ወደ ደም ዝውውር በመግባት የደም ቧንቧዎችን ያጠባሉ። ይህም ልብን ለከፍተኛ ጫና ይዳርገዋል።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት
በአዲስ አበባ ከተማዋ የጤና ጣቢያዎች የሚመዘገቡ የሳምባ ምች ታካሚዎች ቁጥር በአምስት ዓመት ውስጥ ብቻ ከ500 ወደ 29,000 በላይ ማደጉ ተመዝግቧል። ይህ አስገራሚ ጭማሪ ከከተማዋ የአየር ብክለት መጠን መጨመር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በአየር ውስጥ የጥቃቅን ቅንጣቶች መጠን በጨመረ ቁጥር (በተለይ መጠናቸው ከ2.5 ማይክሮሜትር በታች) ፤ በድንገተኛ ክፍል የሚታከሙ የልብ ህመምተኞች ቁጥርም አብሮ ይጨምራል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በሲጋራ ማጨስ የማያውቁ ሰዎችን ጨምሮ፤ በሳምባ መጥበብና መዘጋት (COPD) የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
ይህ ማለት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ስንጓዝ የምንተነፍሰው አየር፤ በውስጣችን የማይታይ የጤና ቀውስ እየፈጠረ ነው ማለት ነው። እያንዳንዱ ትንፋሽ ሳምባችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም ጭምር አደጋ ላይ እየጣለው ይገኛል።
🌍 የአየር ብክለት ምንጮች ምንድን ናቸው?
የአዲስ አበባን አየር የሚበክሉ ምክንያቶች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም፤ በዋናነት ግን የሚከተሉት አምስት ዋነኛ መንስኤዎች እንመለከታለን።

1. አሮጌ ተሽከርካሪዎች "ወረራ"
በከተማ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች መካከል ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑት የሚተፉት ጥቁር ጪስ ከዘመናዊ መኪኖች በብዙ እጥፍ ይበልጣል። በተለይ በከባድ ጭነት መኪኖችና በአሮጌ ታክሲዎች የሚወጣው የተሽከርካሪ ጪስ (28%) ዋነኛው የአየር መመረዝ ምክንያት እንደሆነ የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ።
2. የቤት ውስጥ የባዮማስ ቃጠሎ (18%)
የአየር ብክለት ከቤት ውጭ ብቻ ሳይሆን በቤታችን ውስጥም አለ። አብዛኛው ነዋሪ ለምግብ ማብሰያነት የሚጠቀመው እንጨት፣ ከሰል እና ኩበት ከፍተኛ የሆነ መርዛማ ጭስ ይፈጥራሉ። በተለይ ደካማ የአየር ዝውውር ባለባቸው ቤቶች ውስጥ ምግብ ማብሰል እና እንጀራ መጋገር የቤት ውስጥ አየርን እጅጉን እንዲበከል ያደርጉታል። ለዚህም ብዙ እናቶችን ለሳንባ ካንሰር እና ለትንፋሽ ቧንቧ ህመሞች እየዳረገ ይገኛል። በዚህም ዙሪያ የጻፍነውን ጽሁፍ ይመልከቱ።
3. የመንገድና የህንፃ ግንባታ አቧራ (17%)
አዲስ አበባ በግንባታ ላይ ያለች ከተማ እንደመሆኗ፤ ያልተጠረጉ መንገዶችና የግንባታ ቦታዎች የሚፈጥሩት አቧራ ሌላኛው የብክለት ምንጭ ነው። መኪኖች ባልተጠረጉ መንገዶች ላይ ሲጓዙ የሚነሳው ደቃቅ ብናኝ በቀጥታ ወደ መተንፈሻ አካላችን በመግባት ሳንባን ያቆስላል።

4. በክፍት ቆሻሻ ማቃጠል
ቆሻሻን በሜዳ ላይ የማቃጠል ልምድ ፤ በተለይም ፕላስቲኮችንና ጎማዎችን ማቃጠል እጅግ መርዛማ የሆኑ ኬሚካሎችን ወደ አየር ይለቀቃል። እንደ "ህዳር ሲታጠን" ያሉ ባህላዊ ድርጊቶች በአንድ ጀምበር የከተማዋን የአየር ብክለት መጠን እንዲጨምር ሊያድርጉ ይችላሉ።
5. የኢንዱስትሪ ልቀቶች
ፋብሪካዎች (ለምሳሌ የጨርቃጨርቅ፣ የሲሚንቶና የምግብ ማቀነባበሪያዎች) ለአየር ብክለት የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚለቁት ሰልፈር ዳይኦክሳይድ እና ናይትሮጅን ኦክሳይድ የአየሩን ጥራት ይበልጥ ያበላሹታል።
በይበልጥ ተጎጂ ማነው?

ብክለቱ ሁሉንም ቢነካም፤ በስራ መደባቸው የተነሳ በይበልጥ ተጋላጭ ነት ያላቸው አሉ። ለምሳሌ፦
የመንገድ ዳር ነጋዴዎች፦ ቀኑን ሙሉ በመኪና ጪስና በአቧራ ታፍነው የሚውሉ እናቶችና ወጣቶች።
አሽከርካሪዎችና ትራፊክ ፖሊሶች፦ በትራፊክ መጨናነቅ ውስጥ ረጅም ሰዓት የሚያሳልፉና አየሩን በቀጥታ የሚጋፈጡ የከተማዋ ዘብ ጠባቂዎች።
🏠 እርስዎ ምን ማድረግ ይቻላሉ?
የአየር ብክለትን ለመከላከል የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልገው ፤ ሳይታለም የተፈታ ነው። ሆኖም ግን እርስዎ እንደ ግለሰብ በቤትዎ የሚከተሉትን ቢያደርጉ ተጋላጭነትዎን መቀነስ ይችላሉ።

በአከባቢዎ ትራፊክ የሚበዛበት ፤ብዙ ጎረቤቶዎችዎ ምግብ የሚያበስሉበት ሰዓታት ላይ መስኮቶችውን ይዝጉ። ይህም የአየር ብክለቱ ወደቤትዎ እንዳይገባ ይከላከልልዎታል።
ግድ ካልሆነብዎ በቀር በእግር ሲጓዙ ከዋና ዋና መንገዶች የቻሉትን ያህል ቢርቁ ፤ ለብክለት የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል።
ቤትዎ ውስጥ እንጨት ወይም ከሰል የሚጠቀሙ ከሆነ ፤ የጭስ ማውጫ መጠቀም ወይም ማብሰያ ቤትዎ በቂ አየር እንዲያገኝ ያድርጉ።
በተለይ በተለይ የህፃናት የመተንፈሻ አካላት ገና በማደግ ላይ ስለሆኑ ለብክለት እጅጉን ተጋላጭ ነው። ገና በልጅነት ለብክለት መጋለጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የሳምባ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም ልጆችዎ ከፍተኛ ብክለት ባለባቸው ሰዓታት ከቤት ባይወጡና ንጹህ አየር ባለባቸው ቦታዎች ቢጫወቱ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።
የአመለካከት ለውጥ ያስፈልግዎታል!
ምናልባትም ከሁሉ በላይ አስፈላጊው ለውጥ የተግባር ብቻ ሳይሆን የሐሳብም ጭምር ነው። የአየር ብክለት ብዙ ጊዜ ከቁጥጥርዎ ውጭ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ነገር ግን የሕዝብ ጤና ሳይንስ በተለየ መንገድ ይተረጉመዋል፦
የአየር ብክለት መሻሻል እንደሚችል የጤና ስጋት (Modifiable Risk Factor) እንደሆነ ይገልጻል።
ይህ ማለት ግለሰቦች የብክለቱን ምንጭ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይችሉም፤ ግንዛቤ በመያዝ ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እና ጤናቸውን መጠበቅ ይችላሉ ማለት ነው።
አዎ! ከእርሶዎ ግንዛቤ ጋር ተያይዞ ፤ የተሻሉ የከተማ ፖሊሲዎች ፤ ንፁህ የትራንስፖርት ሥርዓቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ደንቦች መኖራቸው ያስፈልጋል።
እርስዎ ግን እስከዛ የድርሻዎን ይወጡ። ጤናዎን ይጠብቁ!




Comments