top of page

ከ 8000 ኪሎ ሜትር ርቀት የተደረገው ቀዶ ጥገና

ወቅቱ መጋቢት 2026 ነው። በጂብራልታር!

አንድ ታካሚ የቀዶ ጥገና ጠረጴዛ ላይ ተኝቷል። ክፍሉ ውስጥ ያለው ሮቦት እጆች በሰውነቱ ውስጥ ያለውን የፕሮስቴት ካንሰር በከፍተኛ ጥንቃቄ እየለዩ ያወጣሉ።


ክፍሉ ውስጥ የሚሰማው የሞኒተሩ ድምፅ ብቻ ነው። የታካሚው ልብ ትርታ በዲጂታል ስክሪን ላይ ይታያል። በታካሚው ራስጌ ቆሞ መመሪያ የሚሰጥ ሐኪም የለም፤ የሐኪሙ እጆች እንደውም በሌላ አገር ናቸው።

እንደውም ቀዶ ጥገና ሐኪሙ ያለው ለንደን ውስጥ ባለ አንድ ክሊኒክ ውስጥ ነው።

በሐኪሙ ጣቶች እና በታካሚው ልብ ትርታ መካከል 1,500 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕርና የየብስ ርቀት ቢኖርም ፤ በለንደን የሚንቀሳቀሱት የሐኪሙ ጣቶች በጂብራልታር ካሉት የሮቦት እጆች ጋር በፍጹም ቅንጅት ይሰራሉ።


በዶክተሩ ጣቶች እና በሮቦቱ እጆች መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት አንድ ሰከንድ አንድ ሰከንድ እንኳን አይሞላም (ስድስት መቶኛ ስከንድ)።


ይህም ቴሌሰርጀሪ የቀዶ ጥገና ክፍልን ግድግዳ ማፍረሱን ያሳያል።


አዲሱ ዘመን

ለብዙ አስርት ዓመታት የቀዶ ጥገና ሕክምና የማይጣስ አንድ ሕግ ነበረው፦ ሐኪሙና ታካሚው በቀዶ ጥገና ክፍል መገናኘት አለባቸው። የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት እጥረት ባለበት አከባቢ ለሚኖር ታካሚ ፤ ይህ ሕግ ብዙውን ጊዜ የሞት ፍርድ ነበር። ዛሬ ግን ይህ ሕግ በቴሌ-ሰርጀሪ (Telesurgery) አማካኝነት ታሪክ መሆን ችሏል።


ፈጣን የፋይበር ኦፕቲክስ ግንኙነት ፤ የ5ጂ ቴክኖሎጂ እና የዘመናችን ሳይንስ ያገኛው ግኝቶች ተጣምረው በአለም ዙሪያ የዲጂታል የመረጃ መረብ ገንብተዋል። አሁን አንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም ልክ እንደ ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪ በመቆጣጠሪያ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኝን ታካሚን በስክሪን እያየ የቀዶ ጥገና ማከናወን ይችላል። ይህ ደግሞ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቱን ተደራሽነት ለአለም ህዝብ በሙሉ ያደርገዋል።


የሕክምና ዓለምን ያስገረሙ 4 ድንቅ የርቀት ቀዶ ጥገናዎች


1. ከለንደን እስከ ጂብራልታር (2026)

በቀዶ ጥገናው ጊዜ የተነሳ ምስ፡ ከቢቢሲ ድህረ ገጽ የተወሰደ
በቀዶ ጥገናው ጊዜ የተነሳ ምስ፡ ከቢቢሲ ድህረ ገጽ የተወሰደ

ይህ ተራ የሕክምና ሙከራ ሳይሆን የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ ምጥቀት የታየበት ታላቅ ድል ነበር። ፕሮፌሰር ፕሮካር ዳስጉፕታ በለንደን ክሊኒክ ሆነው "ቱማይ" (Toumai) የተባለውን የሮቦት ሥርዓት በመምራት በጂብራልታር የሚገኝን ታካሚ በስኬት አከሙ። የሚገርመው የመረጃ ልውውጥ መዘግየቱ (Latency) 0.06 ሰከንድ ብቻ መሆኑ ነው። ይህም ለሐኪሙ አእምሮ ምንም ዓይነት መዘግየት እንዳይሰማውና ልክ እዚያው ታካሚው አጠገብ እንዳለ ሆኖ በልበ ሙሉነት እንዲሠራ አስችሎታል።


2. ከሮም እስከ ቤጂንግ (8,000 ኪ.ሜ)

ይህ ክንውን ልክ እንደ ሳይንስ ልብ-ወለድ ፊልሞች አስደናቂ ነው። ሐኪሙ ዣንግ ሹ ጣሊያን (ሮም) ተቀምጦ፣ በቻይና (ቤጂንግ) የሚገኝን ታካሚ የፕሮስቴት ቀዶ ጥገና አከናወነ። በመካከላቸው የ8,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ቢኖርም፤ የመረጃ ፍጥነቱ ግን 135 ሚሊ ሰከንድ ብቻ ነበር። ይህ ፍጥነት የሰው ልጅ ዓይኑን ከሚከድንበት ቅጽበት (300 ሚሊ ሰከንድ) በሁለት እጥፍ የፈጠነ በመሆኑ፣ የምድር ስፋት ሕይወት ለማዳን እንቅፋት አለመሆኑን በተግባር አረጋግጧል።


3. በሳተላይት የታገዘ ቀዶ ጥገና (2025)

"የኢንተርኔት ገመድ ባይኖር ወይም ቢቋረጥ ምን ይከሰታል?" ለሚለው ስጋት በ2025 ቻይናውያን ሐኪሞች በሰማይ ላይ መልስ አግኝተዋል። በምድር ላይ ካለ የኬብል መስመር ይልቅ በሳተላይት ግንኙነት በመታገዝ ከ5,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ ቀዶ ጥገና አደረጉ። ይህ ስኬት ወደፊት በጦር ሜዳ፣ በውቅያኖስ ላይ ወይም ገለልተኛ በሆኑ በረሃማ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች የሰለጠነ የሕክምና እርዳታን ከከተማ ሆኖ ለማድረስ ትልቅ ተስፋን ሰንቋል።


4. ከታይላንድ እስከ ቻይና፦ የሕክምና እኩልነት

 ዶክተሩ ከቻይና እስክሪን እያየ የሀሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና ሲያደርግ። ከባንጎክ ፖስት የተወሰደ
ዶክተሩ ከቻይና እስክሪን እያየ የሀሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና ሲያደርግ። ከባንጎክ ፖስት የተወሰደ

በሚያዝያ 2026 በባንኮክና በምዕራብ ቻይና መካከል በ2,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሐሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና ተከናወነ። ቴክኖሎጂው የሕክምና እውቀት ከሐኪሙ አእምሮ ወጥቶ በዲጂታል መስመር አማካኝነት ወደ ማንኛውም የዓለም ጥግ ማድረስ እንደሚቻል አሳይቷል።


 ታድያ ግን በቴክኖሎጂው ላይ ሕይወትን መጣል ይቻላል?

ቴሌ-ሰርጀሪ (Telesurgery) የሕክምናውን ዓለም ድንበር ቢሰብርም ፤ አንድ ትልቅ ጥያቄ ግን ያጭራል፦ ቴክኖሎጂው ችግር ቢያጋጥመው ፤ እንደተጠበቀው ባይሰራ ሕይወትስ ምን ይሆናል? ይህንን የቴክኖሎጂ እመርታን ጥያቄ ላይ የሚያሳድሩ አንዳንድ ፈተናዎች አሉ። ለምሳሌ፡-

መዳሰስ አለመቻል

አንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም የሚሠራው በአይኑ ብቻ ሳይሆን በጣቶቹም ጭምር ነው። የደም ሥር ትርታን፣ የስጋን መደደር እና መለስለስ በእጅ ዳስሶ የመለየት ጥበብ (Haptics) ለስኬታማ ቀዶ ጥገና ወሳኝ ነው። በቴሌ-ሰርጀሪ ግን ይህ የለም። የሐኪሙ ጣቶች ያዛሉ እንጂ መዳሰስ አይችሉም። ሐኪሙ የሰውን አካል የሚነካው በብረት እንጂ በጓንት አይደለም። ይህ የ መዳሰስ ስሜት መቋረጥ በሐኪሙና በታካሚው መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ወደ ቴክኒካዊ ትዕዛዝ ብቻ ይቀንሰዋል። ይህም ቀዶ ጥገናው ላይ ጫና ማሳደሩ የማይቀር ነው።

ግንኙነት ቢቋረጥ ተጠያቂው ማን ነው?

የሕግና የሞራል ፈተና ሌላ ትልቁ ጥያቄ ነው። በተለመደ ቪዲዮ ጥሪ ላይ የኢንተርኔት መቆራረጥ ቢያስከፋ ነው፤ ሆኖም ግን በቀዶ ጥገና መሃል ግን ሕይወት ሊያልፍ ይችላል። በቀዶ ጥገና ጊዜ የዶክተሩ ትእዛዝ ሮቦቱ ጋር ባይደርስ ፤ የኢንተርኔት መቆራረጥ ቢከሰት ወይም ግንኙነቱ ቢዘገይ (Lag) ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂው ማን ነው?


  • ኢንተርኔት አቅራቢው የቴሌኮም ድርጅት? የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ችግር ስላጋጠመ

  • ሆስፒታሉ? የቴክኖሎጂው ዝግጅት ስለሌለው

  • ወይንስ ሐኪሙ? ቀዶ ጥገናውን እያደረገው ያለው በመሆኑ ፤ በቅጽበት የሚደማ ደምስርን መቋጠር ባለመቻሉ።


ተጠያቂው ማን ነው?

የ ኢንተርኔት መረብ ደህንነት

ሕይወት በዳታ መልክ በኢንተርኔት ሲጓዝ፤ ሌላው ስጋት የሳይበር ጠለፋ ነው። አንድ ታካሚ በቀዶ ጥገና ጠረጴዛ ላይ እንዳለ ፤ የግንኙነት መረቡ ቢጠለፍ ውጤቱ አስከፊ ነው። በመሆኑም ሆስፒታሎች አሁን የቀዶ ጥገና ክፍሉን ብቻ ሳይሆን፣ መረጃው የሚጓዝበትን የዲጂታል መስመርም መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ጋዜጣ ላይ የማይወጣው የማይታየው ቡድን


በሺዎች ኪሎ ሜትሮች ርቆ ያለው ሐኪም ላይ ብናተኩርም፤ የታካሚው ሕይወት ግን በእርግጥ ያለው በቅርቡ ያሉ የቀዶ ጥገና ህክምና ቡድን ላይ ነው። ኢንተርኔት ቢቋረጥ ወይም ሮቦቱ ሥራ ቢያቆም፣ የክፍሉ የሕክምና ቡድን በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ቀዶ ጥገናውን ተረክበው ለማስቀጠል ዝግጁ መሆን አለባቸው።

ቴሌ-ሰርጀሪ ስኬታማ የሚሆነው ሮቦቱ ሲሠራ ብቻ ሳይሆን፤ ሮቦቱ ሲበላሽ የሰው ልጅ ተክቶት ለመሥራት ሲችል ነው።

ተግባራዊነቱ ለኢትዮጵያ ምን ያህል ነው?

ዓለም ለንደንና ሮም ያሉ ሐኪሞችን በአድናቆት ሲመለከት፤ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ የራቀ ነው። የሐኪምና የሕዝብ ብዛት ጥምርታ ከ100,000 ሰው ከአንድ ስፔሻሊስት በታች በሆነበት አገራችን ፤ ርቀት ችግር የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። ለዚህ እውነት ተግባራዊ ቢሆን ፤ ቴሌ ሰርጀሪ የሚያመጣቸው መልካም ጎኖች አሉ። ሆኖም ግን የሚከተሉት መታሰብ አለባቸው።


ትልቁ ፈተና "የሁለትዮሽ ቡድን" ወጪና ድካም ነው። ቴሌ-ሰርጀሪ "አንድ ታካሚ ግን ሁለት የሕክምና ቡድን" ይጠይቃል፤ አንደኛው ከሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በስክሪን የሚያክም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሽተኛው አጠገብ ሆኖ የኢንተርኔት መቆራረጥን ወይም የመብራት መጥፋትን በተጠንቀቅ የሚጠብቅ ነው። የሰው ኃይል እጥረት ባለባት አገር፤ አንድን ሙሉ የባለሙያ ቡድን ለጥንቃቄ ብቻ "ተጠባባቂ" አድርጎ ማስቀመጥ የሰው ኃይል ብክነትን ብቻ ሳይሆን፤ ለሆስፒታሎችና ለታካሚዎች የማይቀመስ የሕክምና ወጪን ይዞ ይመጣል።


ከዚህም በላይ የመበራት መጥፋት በተለመደበትና የኔትወርክ መቆራረጥ እጅጉን አስቸጋሪ በሆነበት በሀገራችን ፤ ቀዶ ጥገና መሃል የሮቦት እጅ መቆሙ አልያም አርፍዶ መስራቱ፤ የምናልባት ጉዳይ ሳይሆን ፤ የሚያጋጥም አደጋ ነው ።

እንደ ሀገርስ፦

በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በአንድ የሮቦት ሲስተም ላይ ማዋል ይሻላል ወይስ ያንን ገንዘብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሐኪሞችን ለማሰልጠንና የገጠር ክሊኒኮችን ለማጠናከር?

ለጊዜው በኢትዮጵያ ያለው እውነተኛ "ዲጂታል አብዮት" በሮቦቱ ቀዶ ጥገና ማድረጉ ሳይሆን ቴሌ-ሜንቶሪንግ (Telementoring) ሊሆን ይችላል። ይህም የዓለም ስፔሻሊስቶች በኢንተርኔት አማካኝነት የኢትዮጵያ ሐኪሞችን "በጆሮአቸው" እየመከሩ ቀዶ ጥገናው ላይ ማገዙ ነው። እንደ ሀገር እያደግን ስንሄድ ግን በሙሉ ደረጃ መተግበር ይችላል።


ባጠቃላይ ሲታይ፤ ቴሌ-ሰርጀሪ ለኢትዮጵያ የሕክምና ዘርፍ ብሩህ ተስፋን ሰንቆ የመጣ "የነገ ተአምር" መሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ፣ ያለንበት ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ቴክኖሎጂውን ዛሬውኑ በሙሉ አቅም ለመተግበር ገና መሆናችንን ያሳየናል።

Comments


bottom of page