ስለ እምብርት ኸርኒያ ማወቅ ያለብዎ?
- Zebeaman Tibebu
- 13 minutes ago
- 4 min read
ድንገት በአዘቦት ቀን ፤ መስታወት ፊት ቆመው ሲያዩ እምብርትዎ አካባቢ እብጠት ቢያስተውሉስ ?
እብጠቱን ያዩት አራስ ሕፃን ልጅዎ ላይ ቢሆንስ ?
ምን ይሰማዎታል? መጨነቅ ይኖርቦት ይሆን ፤ ወይስ ጉዳዩ በፍጹም አያሳስብም ?

ዛሬ የምናነሳው ስለ የእምብርት ኸርኒያ ነው። የእምብርት ኸርኒያ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረት ከሚሹና፤ በተደጋጋሚ የቀዶ ጥገና ሕክምና ከሚያስፈልጋቸው የጤና እክሎች አንዱ ነው ። ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ብዙ ሰዎች ስለ ምንነቱ፣ ለምን እንደሚከሰት፣ እና መቼ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ የሆነ ግንዛቤ የላቸውም ።
የእምብርት ኸርኒያ (Umbilical Hernia) ምንድን ነው?
ይህ ዓይነቱ የኸርኒያ ችግር የሚከሰተው፤ በእምብርት አካባቢ ባለው የሆድ ዕቃ ግድግዳ ላይ ክፍተት ወይም መላላት ሲኖር ነው። በዚህም ክፍተት የተወሰነ የአንጀት ክፍል፣ የስብ ክምችት፣ ወይም ሌላ የሆድ ዕቃ ይዘት ሾልኮ ሊወጣ ይችላል ። ይህን ጊዜ የእምብርት ኸርኒያ ተከሰተ እንላለን።በሽታው በሕፃናትም ሆነ በአዋቂዎች ላይ የሚከሰት ቢሆንም፤ መንስኤው፣ ባህሪው እና የሕክምናው ሂደቱ ግን ፈጽሞ የተለያየ ነው።

ስለ ኸርኒያ ለመረዳት የሆድዎ ግድግዳን የውስጥ አካላትን በአግባቡ ጠብቆ የሚያቆይ ጠንካራ መከላከያ አጥር አድርገው ያስቡት። ምስሉ ላይ በቀኝ በኩል እንደሚታየው በዚህ አጥር ላይ ደካማ ቦታ ወይም ክፍተት ከተፈጠረ ግን፣ የሆድ ዕቃ አካላት በክፍተቱ አፈንግጠው/ ሾልከው ለመውጣት ይሞክራሉ። በግራ በኩል እንደሚታየው ወደ ውጭ በመግፋታቸውም እምብርት ላይ የሚታይ እብጠት ይፈጥራሉ ።በዚህም ምክንያት በእምብርት ላይ ወይም በአቅራቢያው፤ ግልጽ የሆነ እብጠት ይፈጠራል። ይህ እብጠት የሚከተሉት ባህሪያት አሉት፦
በሚያምጡ፣ በሚያስሉ፣ በሚያለቅሱ፣ በሚስቁ ወይም በሆድ ላይ ጫና በሚያደርጉበት ጊዜ ይበልጥ ይታያል።
በጀርባ በሚተኙበት ጊዜ መጠኑ ይቀንሳል ፤ ወይም ሙሉ በሙሉ ይሰወራል።
ይህም እብጠት ሲነካ ለስላሳ ነው። ብዙ ጊዜም ህመም የለውም።
አንዳንድ ጊዜ ግን ይህ ከፍተኛ ምቾት ማጣት ወይም ሕመም ያስከትላል።
እምብርትዎ ለምን ለዚህ ችግር ይጋለጣል?
ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ ለማግኘት ጉዟችንን የምንጀምረው ከውልደት በፊት ካለው አስደናቂ የተፈጥሮ ሂደት ነው ። በእርግዝና ወቅት ፅንስ ከእናቱ አካል ጋር የሚገናኝበት እትብት ፤ በልጂ የሆድ ግድግዳ ላይ ባለው ተፈጥሯዊ ክፍተት በኩል ያልፋል ። ሕፃኑ ተወልዶ እትብቱ ሲቆረጥ ግን ፤ ይህ ክፍተት በጊዜ ሂደት በተፈጥሮ ራሱን ይዘጋል ።

ነገር ግን በአንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት ይህ ክፍተት ሙሉ በሙሉ ሳይዘጋ ሊቀር ይችላል። ይህም በአከባቢው ላይ ደካማ ስፍራን ይፈጥራል። ሕፃናት ላይ የእምብርት ኸርኒያ በብዛት የሚስተዋለውም በትክክል በዚህ ምክንያት ነው ።
አብዛኛው የሕፃናት እምብርት ኸርኒያ አደገኛ እንዳልሆነ የሕክምና ሳይንስ ያረጋግጣል ። የሕፃኑ የሆድ ጡንቻዎች እያደገና እየጠነከረ ሲሄድ ፤ አብዛኞቹ ኸርኒያዎች ያለምንም ሕክምና በራሳቸው ጊዜ ይጠፋሉ ። መቼ?
በሕፃናት ላይ የሚከሰቱ አብዛኞቹ የእምብርት ኸርኒያዎች እስከ 4–5 ዓመት ዕድሜ ድረስ በራሳቸው ይዘጋሉ።
ይህ ኸርኒያ ይበልጥ ትልቅ ሆኖ ሊታይ የሚችለው፤ ህጻኑ ፦
ሲያለቅስ፣
ሲያስል፣
ሲያምጥ፣
ሲስቅ ነው።
በብዙ ሕፃናት ላይ ይህ ክፍተት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የዕድሜ ዓመታት ውስጥ በተፈጥሮ ስለሚዘጋ ፤ ሐኪሞች ለቀዶ ጥገና ሕክምና አይቸኩሉም። ይልቁንም ሁኔታውን በቅርብ ክትትል ብቻ መቆጣጠር ይመርጣሉ ።
አዋቂዎች ላይ የሚከሰት የእምብርት ኸርኒያ
በአንጻሩ በአዋቂዎች ላይ የሚከሰተው የኸርኒያ ችግር መነሻው የተለየ ነው። የአዋቂዎች የእምብርት ኸርኒያ የሚከሰተው በሆድ ውስጥ ያለው ተከታታይ ግፊት የሆድ ግድግዳ ጡንቻን አቅም አሸንፎ ሲወጣ ነው። ለዚህም ይህንን ጫና በተከታታይ የሚፈጥሩ ምክንያቶች ለዚህ ያጋልጣሉ።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አዋቂዎችን ለዚህ የጤና እክል የሚያጋልጡ ዋነኛ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
ከመጠን በላይ ውፍረት፦ ከባድ የሰውነት ክብደት በሆድ ግድግዳ ላይ የማያቋርጥ ጫና ስለሚፈጥር ለዚህ ያጋልጣል።
እርግዝና፦ ተደጋጋሚ እርግዝና ሆድ ላይ በሚያሳድረው ተጽእኖ ፤ ጡንቻዎችን ያዳክማል።
ከባድ ዕቃ ማንሳት፦ በተደጋጋሚና ያለ ጥንቃቄ ከባድ ዕቃዎችን ማንሳት በሆድ ውስጥ ድንገተኛ ግፊት ይፈጥራል።
የቆየ ወይም ሥር የሰደደ ሳል፦ በተደጋጋሚ መሳል በሆድ ግድግዳ ላይ የማያቋርጥ ተያያዥ ጫና ያሳርፋል። ይሄም አደጋ አለው።
በሆድ ውስጥ የተቋጠረ ፈሳሽ መቋጠር ፦ በተለይ በጉበት በሽታ ምክንያት በሆድ ውስጥ የሚከማች ፈሳሽ የውስጥ ጫናን በእጅጉ ስለሚጨምር ለኸርኒያ ያጋልጣል።
ቀደም ሲል የተደረገ የሆድ ቀዶ ጥገናም ለዚህ በሽታ አጋላጭ ነው።
የዕድሜ መግፋት፦ ዕድሜ ጋር ተያያዞ የሰውነት ጡንቻዎች ስለሚዳከሙ/ስለሚላሉ ለኸርኒያ ያጋልጣሉ።
የእምብርት ኸርኒያ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የእምብርት ኸርኒያ በሁሉም ሰው ላይ ተመሳሳይ የሕመም ስሜት ላያሳይ ይችላል። እንደውም ብዙዎች ህመም አይሰማቸውም። እነርሱ የሚያስተውሉት እምብርት አከባቢ የሚታይ እብጠት ብቻ ነው። ሆኖም ግን ችግሩ እየቆየ ሲሄድ ብዙዎች የሚከተሉትን አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ስሜቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ፦

መጠነኛ ምቾት ማጣት፣
በእምብርት ዙሪያ የማያቋርጥ ጫና/የሚጫን ስሜት፣
ዕቃ በሚያነሱበት ጊዜ የሚሰማ ሕመምና፣
ሆድ ላይ የሚሰማ ስሜት ናችው።
ብዙዎቹ የእምብርት ኸርኒያዎች ለዓመታት ያህል ምንም ዓይነት ከባድ ሕመም ሳይፈጥሩ ሊቆዩ ይችላሉ ።
ይህ ማለት ግን ፤ ቸል ማለት አለብን ማለት አይደለም ።
አሳስቢ የሚሆነው መቼ ነው?
የእምብርት ኸርኒያ አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። አንዳንዴ እብጠቶቹ በቀላሉ ወደ ውስጥ ይመለሳሉ። ይህም የመጀመሪያው ደረጃ ነው። ይህም ወደ ውስጥ የሚመለስ ኸርኒያ (Reducible Hernia) ይባላል ።
ይህ አሳሳቢ አይደለም።
እብጠቱ ሲያምጡ/ ሲያስሉ ወደ ውጭ የሚወጣ ቢሆንም ፤ በጀርባ ሲተኙ ወይም ቀስ አድርገን ሲጫኑት በቀላሉ ወደ ሆድ ዕቃ ይመለሳል ።
በሽታው አሳሳቢ የሚሆነው ፤ በክፍተቱ ሾልኮ የወጣው አንጀት ወደ ቦታው መመለስ ሲያቅተው ነው።
ይህም ሁሉት አደገኛ አይነቶች አሉት።
የመጀመሪያው አንጀት በክፍተቱ ውስጥ ተቀርቅሮ ሲቀር እና ወደ ሆድ ዕቃ መልሶ መግፋት ሳይቻል ሲቀር ነው። ይህንንም ደረጃ የሚጠቁሙ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦
የማይጠፋ እምብርት ጋር ያለ ቋሚ እብጠት፣
እየጨመረ የሚሄድ ምቾት ማጣት፣
ሲነካ የሚሰማ ህመምና (Tenderness)፣
እብጠቱን ወደ ውስጥ ለመመለስ መቸገር ናቸው ።

ህክምና ካላገኘ ግን ፤ ወደ መጨረሻውና አደገኛ ደረጃ ይሸጋገራል። ተቀርቅሮ የቀረው የአንጀት ክፍል የደም ዝውውር ይቋረጣል። በቂ ደም ያላገኘው የተያዘው የአንጀት ክፍል ደግሞ ሊሞት ወይም ሊበሰብስ ይችላል ።
ይህ ለህይወት አስጊ ደረጃ ነው።
ይህንን የሚጠቁሙ አሳሳቢ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦
ከፍተኛ /ኃይለኛ ሕመም፣
የእብጠቱ አካባቢ መቅላት ወይም ቀለም መለወጥ (መጥቆር)፣
ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ፣
ከፍተኛ ትኩሳት፣
የሆድ መነፋት፣
ለመንካት በጣም የሚከብድና የማይመለስ ሕመም ያላቸው እብጠት ናቸው።
ይህ አፋጣኝ ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል።
ታድያ ሁሉም ኸርኒያ ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል?
አያስፈልገውም!

ሕክምናው የሚወሰነው በዕድሜ፣ በምልክቶች፣ በእብጠቱ መጠን እና ሊያስከትል በሚችለው የውስብስብ ችግር ስጋት ላይ ነው።
ለሕፃናት፦ ብዙዎቹ ትናንሽ የእምብርት ኸርኒያዎች በራሳቸው ጊዜ ይዘጋሉ። ቀዶ ጥገና የሚታሰበው፦ ክፍተቱ ከሕፃንነት ዕድሜ በኋላ ሳይዘጋ ሲቀር፣ እብጠቱ በጣም ትልቅ ከሆነ፣ ውስብስብ ችግሮች ከተፈጠሩ እና የሕመም ምልክቶች ከታዩ ብቻ ነው።
ለአዋቂዎች፦ ከሕፃናት በተለየ መልኩ፣ የአዋቂዎች እምብርት ኸርኒያ በራሱ ጊዜ የመዘጋት ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው። በጊዜ ሂደት መጠናቸው እየጨመረ ስለሚሄድ እና ለውስብስብ ችግር ሊዳርጉ ስለሚችሉ፣ ምልክት ላላቸው ኸርኒያዎች ቀዶ ጥገና ማድረግ በብዛት ይመረጣል።
መከላከል ይቻላል?
ሁሉንም አይነት የእምብርት ኸርኒያ መከላከል ባይቻልም፤ በአዋቂዎች ላይ ተጋላጭነት መቀነስ ይቻላል።ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ።
የሰውነት ክብደትዎን ይቀንሱ።
ለረዥም ጊዜ የቆየ ሳልን ያክሙ።
ከባድ ዕቃዎችን ሲያነሱ ጥንቃቄ ያድርጉ።
የሆድ ድርቀትዎን በጊዜ ያክሙ። ሽንትቤት ሲጠቀሙ አይምጡ!
ያስተውሉ!
በእምብርቱ ላይ ሳንቲም ማስቀመጥ፣ በጨርቅ አጥብቆ ማሰር ወይም ሌላ ቁሳቁሶችን እምብርት ላይ ማድረግ አያድነውም። ይልቁኑ እብጠቱን ሊያቆስሉ ፤ ላልታሰበ ህመም ራስዎን ሊያጋልጡ ይችላሉ።
በእምብርት ዙሪያ የሚታይ እብጠት ሁልጊዜ አደገኛ ባይሆንም፤ ችላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አይደለም። በተለይ እብጠቱ ሕመም፣ መቅላት፣ መጥቆር ወይም ማስታወክ ጋር ከተያያዘ አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ። ቀደም ብሎ መታየት ቀላል የሆነ ሕክምናን ከማስቻሉም በላይ ከከባድ ውስብስብ ችግሮች ሕይወትን ሊታደግ ይችላል።




Comments