top of page

መጸዳጃ ቤት ውስጥ ማማጥ በጤናችን ላይ የሚያስከትለው ከባድ መዘዝ

አብዛኞቻችን መጸዳጃ ቤት ውስጥ ረጅም ሰዓት የማሳለፍና የመማጥ ልማድ አለን። ነገር ግን ይህ ቀላል የሚመስለው ልማድ ከጀርባው ከባድ የጤና ጠንቅ ሊያስከትል እንደሚችል ያውቃሉ? ምክንያቱስ ምን እንደሆነ ያውቃሉ? ከዚህ ቀላል ከሚመስለው ውሳኔ ጀርባ ብዙ ሳይንሳዊ ምክንያቶች አሉ።


ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ አንድ እውነተኛ የሕክምና ታሪክ ላካፍላችሁ።


አንድ የ45 ዓመት ጎልማሳ በድንገት የሁለቱም ዓይኖቹ እይታ ሙሉ በሙሉ በመጋረዱ ወደ ዓይን ህክምና ክሊኒክ ይመጣል። ይህ ሰው ላለፉት ቀናት የሆድ ድርቀት ታሪክ የነበረው ሲሆን፤ ከመጣበት ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ሽንትቤት ሲጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ አምጦ ነበር።


ታዲያ ምን ተፈጠረ? ......ግንኙነት ይኖራቸው ይሆን?


ይህ ታሪክ አስደናቂ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን በአለም ዙሪያ ያሉ ሐኪሞች በሕክምና መጻሕፍት ላይ ተመሳሳይ የሆኑ በርካታ ክስተቶችን መዝግበዋል። ምንም እንኳን እንዲህ ያሉ ከባድ ጉዳቶች በተደጋጋሚ ባያጋጥሙም አንድ ትልቅ እውነታን ግን ያስገነዝቡናል፦

ሽንት ቤት ሲጠቀሙ ፈጽሞ ማማጥ አይመከርም!

የማማጥ እውነታ

መጸዳጃ ቤት ሲጠቀሙ ማማጥ፤ አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው ፈጽሞ ጉዳት የሌለው ተራ ነገር አይደለም! መጸዳጃ ቤት ምናልባትም ሰዎች ድንገተኛ የሕክምና አደጋ ይከሰታል ብለው ፈጽሞ የማይጠብቁት ቦታ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንዳንዴ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ የከፋው አደጋ እዚያው ይከሰታል።


በየቀኑ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች፤ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ረጅም ሰዓት ተቀምጠው በኃይል የማማጥ ልማድ አላቸው። አንዳንዶች ከ15 እስከ 30 ደቂቃ የሚሆን ጊዜያቸውን እዚያው በማማጥ ያሳልፋሉ። ብዙዎች ይህንን ከዕድሜ መግፋት ጋር ብቻ ያያይዙታል። ሆኖም እውነታው ከዚህ የተለየ ነው!


የሕክምና ጥናቶች ደጋግመው እንዳረጋገጡት፤ ከልክ በላይ ማማጥ በሰውነታችን ላይ ከፍተኛ የጤና ቀውስ ያስከትላል። ይህ ድርጊት በልብ፣ በደም ሥሮች፣ በአንጎል፣ በዓይኖች፣ በምግብ መፈጨት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።


ማማጥ ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድረው ለምንድን ነው?

ችግሩን በጥልቀት ለመረዳት፤ በመጀመሪያ በማማጥ ወቅት በሰውነታችን ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች እንደሚከሰቱ ማወቅ ያስፈልገናል።


አንድ ሰው ሰገራ ለማውጣት በኃይል ወደ ታች ሲያምጥ፤ በሕክምናው ዓለም "ቫልሳልቫ ማኑቨር" (Valsalva maneuver) የሚባለውን የሰውነት እንቅስቃሴ ያደርጋል። ይህም የአየር መተንፈሻ ቱቦን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት፤ በሆድ እና በደረት ጡንቻዎች ላይ በኃይል መግፋትን ያካትታል። ይህ ድርጊት በደረት እና በሆድ ውስጥ ያለውን የውስጥ ግፊት በአስገራሚ ሁኔታ ከፍ ያደርገዋል።


ለዚህም ነው ለጥቂት ቅጽበታት የሚከተሉት ለውጦች የሚከሰቱት፦

ወደ ልብ የሚመለሰው የደም ዝውውር በጊዜያዊነት ይቀንሳል፤

የልብ ምት በድንገት ሊዛባ ይችላል፤

የደም ግፊት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል፤

በሆድ፣ በራስ፣ በዓይኖች ውስጥ ያለው ግፊት በአንድ ጊዜ ይጨምራል።


በእርግጥም ጤናማ በሆኑ ሰዎች ላይ ፤ ሰውነታቸው እነዚህን ፈጣን ለውጦች አብዛኛውን ጊዜ በቀላሉ ይቋቋመዋል። ነገር ግን አስቀድሞ የጤና ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ፤ አልያም ማማጡ በጣም ጠንካራ እና ተደጋጋሚ በሚሆንበት ጊዜ መዘዙ ከባድ ሊሆን ይችላል።


የማማጥ መዘዙ

1️⃣ ኪንታሮት (Hemorrhoids)

ብዙ ኢትዮጵያውያን አስቀድመው የሚያውቁት አንድ የተለመደ የጤና ችግር ካለ፤ እርሱ ኪንታሮት ነው። ኪንታሮት ማለት በፊንጢጣ አካባቢ ያሉ ስስ የደም ሥሮች ማበጥና መቆጣት ማለት ነው። አንድ ሰው መጸዳጃ ቤት ውስጥ ደጋግሞ በሚያምጥበት ጊዜ፤ በእነዚህ የደም ሥሮች ላይ ያለው የውስጥ ግፊት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ይህ ግፊት ደግሞ በጊዜ ሂደት የደም ሥሮቹ እንዲሰፉ፣ እንዲያብጡ፣ ውጥረት እንዲፈጥሩ ያደርጋቸዋል።


በዚህ ምክንያት የሚከሰቱት የተለመዱ የኪንታሮት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦

🔴በሰገራ ወቅት ደማቅ ቀይ ደም መፍሰስ፤

🔴የሕመም ወይም የምቾት ማጣት ስሜት፤

🔴የፊንጢጣ ማሳከክ፣ መቅላት፣ ማበጥ፤

🔴በሰገራ መውጫ አካባቢ የሚወጣ የሚዳሰስ እብጠት።


ብዙ ሕመምተኞች ለዚህ ችግር፤ ቅመም የበዛበትን ምግብ ብቻ ተጠያቂ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ነገር ግን መጸዳጃ ቤት ውስጥ የሚደረግ የማያቋርጥ ማማጥ፤ ብዙውን ጊዜ ለበሽታው መባባስ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። የሕክምና መጽሐፍትም ደጋግመው እንደሚያረጋግጡት፤ የረጅም ጊዜ የሆድ ድርቀትን ተከትሎ የሚመጣ ብርቱ ማማጥ ለኪንታሮት በሽታ መከሰት ዋነኛው መንስኤ ነው።


2️⃣ የፊንጢጣ መገልበጥ (Rectal Prolapse)

ፊንጢጣ መውጣት የሚባለው የጤና ችግር፤ የፊንጢጣ ውስጠኛው ክፍል ከቦታው ተንሸራቶ ፤ በፊንጢጣ ቀዳዳ በኩል ወደ ውጭ ብቅ ሲል ነው።


ይህ አስከፊ ችግር ይበልጥ በተለመደ ሁኔታ የሚከሰተው፤ በዕድሜ በገፉ አዋቂዎች ላይ፣ በተደጋጋሚ በወለዱ ሴቶች ላይ፣ ሥር የሰደደ የሆድ ድርቀት ባለባቸው ሰዎች ላይ፣ እና መጸዳጃ ቤት ሲጠቀሙ በተደጋጋሚ በሚያምጡ ሰዎች ላይ ነው።


በዚህ በሽታ የተጠቁ ሕመምተኞች የሚከተሉትን አስቸጋሪ ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ፦

  • ከፊንጢጣ ቀዳዳ የሚወጣ ቀላ ያለ ሥጋ መሰል ነገር፤

  • ሰገራን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ችግር፤

  • የፊንጢጣ ደም መፍሰስ፣ መቅላት፣ ማሳከክ፤

  • ሲቀመጡ፣ ሲራመዱ፣ ሲንቀሳቀሱ ከፍተኛ ምቾት ማጣት።

ይህ የጤና እክል እየባሰ በሚሄድበት ጊዜ፤ ችግሩን ለማስተካከል ብዙውን ጊዜ አስገዳጅ የሆነ የቀዶ ጥገና ሕክምና ያስፈልገዋል።


3️⃣ መጸዳጃ ቤት ላይ ራስን መሳት (Defecation Syncope)

አንድ ሰው መጸዳጃ ቤት ውስጥ እንዳለ በድንገት እንዳዞረው፤ ወይም እዚያው ወድቆ እንደተገኘ ፤ የሚያወሩ አስደንጋጭ ታሪኮችን ሰምተው ሊሆን ይችላል።

ይህ ክስተት እውነተኛ ነው!

በህክምናው "ዲፌኬሽን ሲንኮፒ" (Defecation syncope) ተብሎ ይጠራል። ይህ ችግር፤ ሂደቱ ውስብስብ ቢሆንም መነሻው ግን መጸዳጃ ቤት ውስጥ ከሚደረግ ከልክ ያለፈ ማማጥ ጋር የተያያዘ ነው።  በኃይል በሚማጥበት ጊዜ፤ በልብ ምት እና በደም ግፊት ላይ ድንገተኛ ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ። በተለይም ለዚህ ችግር ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ላይ፤ ወደ አንጎል የሚሄደው የደም ፍሰት ለጥቂት ቅጽበታት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።

በዚህ ምክንያት ድንገተኛና ከባድ የራስ ማዞር ስሜት፣ ከልክ ያለፈ ማላብ፣ ለጥቂት ሰከንዶች ራስን መሳት፣ ሚዛንን ስቶ መውደቅና፣ ከባድ የአካል ጉዳት ሊያጋጥም ይችላል። የጉዳቱ ዋነኛ አደጋ ብዙውን ጊዜ ራስ ከመሳቱ ብቻ ሳይሆን፤ ሰውየው መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሲወድቅ ከግድግዳ፣ ከሴራሚክ፣ ከጠንካራ ዕቃዎች ጋር በመጋጨቱ ምክንያት ከሚደርስበት የጭንቅላትና የአካል ጉዳት ነው።


4️⃣  የልብ ድካም እና ድንገተኛ አደጋዎች

ማማጥ በልብና በደም ሥር ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ፤ ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት ጀምሮ በሕክምናው ዓለም በደንብ የታወቀ እውነታ ነው።


አንድ ሰው መጸዳጃ ቤት ውስጥ በኃይል በሚገፋበት ወይም በሚያምጥበት ጊዜ፤ የደም ግፊት በአስገራሚ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል። የልብ የሥራ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ይከብዳል። የልብ የኦክስጅን ፍላጎትም አብሮ ሊጨምር ይችላል። በእርግጥ ጤናማ ልብ ላላቸው ሰዎች ይህ ሁኔታ ምናልባት ጎልቶ የሚታይ ፈጣን ችግር ላይፈጥር ይችላል። ነገር ግን የልብ የደም ሥር በሽታ (Coronary artery disease)፣ የልብ ድካም (Heart failure)፣ ከባድ የልብ ምት መዛባት (Arrhythmias)፣ ቁጥጥር ያልተደረገበት የደም ግፊት ያሉባቸው ሰዎች ላይ ግን ድርጊቱ ከፍተኛ የሕይወት አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል።


በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ የልብ ሕመም ባለባቸው ታካሚዎች ላይ፤ ሽንትቤት በሚጠቀሙበት ጊዜ ያጋጠሙ በርካታ ከባድ የልብ አደጋዎች አሉ። ሐኪሞች በሆስፒታል ውስጥ ለሚገኙ የልብ ሕመምተኞች የሆድ ድርቀት እንዳይኖራቸው፤ እና ፈጽሞ እንዳያምጡ ልዩ ትኩረት የሚያደርጉትም ለዚህ ነው።


5️⃣ ስትሮክ እና በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ

ጉዳዩን ግልጽ እናድርገው!

መጸዳጃ ቤት ውስጥ የሚያምጡ አብዛኞቹ ሰዎች በቀጥታ በስትሮክ አይጠቁም። ሆኖም ግን ጠንከር ያለ ማማጥ በደም ግፊት ላይ ከፍተኛ መለዋወጥ ሊያስከትል ይችላል። ይህም ወዲያውኑ ስትሮክ እና በአንጎል ውስጥ ደም የመፍሰስ (intracranial hemorrhage) አደጋዎች ሊያስከትል ይችላል።


እነዚህ አስከፊ ክስተቶች በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በጣም የተለመዱ ባይሆኑም፤ ማማጥ በልብና በደም ሥር ሥርዓት ላይ የሚያሳድረውን ከፍተኛ አካላዊ ጫና በግልጽ ያሳያሉ። በተለይም አስቀድሞ በጭንቅላታቸው ውስጥ ስስ የደም ሥር  (aneurysm) እብጠት ያለባቸው፤ ወይም ቁጥጥር ያልተደረገበት ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ላይ ይህ ድንገተኛ ጫና ለአስከፊ የሕይወት አደጋ መንስኤ ሊሆን ይችላል።

6️⃣ ኸርኒያ (Hernia) ሊባባስ ይችላል።

ሄርኒያ (Hernia) የሚከሰተው የሰውነታችን የውስጥ ክፍል (ብዙውን ጊዜ አንጀት) በጡንቻዎች መላላትና ድክመት ምክንያት ተገፍቶ በቆዳ ላይ ወደ ውጭ ብቅ ሲል ነው።

በመጸዳጃ ቤት ውስጥ በኃይል በሚማጥበት ጊዜ፤ በሆድ ዕቃ ውስጥ ያለው የውስጥ ግፊት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ይህ በተደጋጋሚ በሆድ ውስጥ ያለውን ግፊት በመጨመር ፤ አስቀድመው ያሉትን የሄርኒያ ዓይነቶች ሊያባብስ፤ አልፎ ተርፎም ለአዳዲስ ሄርኒያ መፈጠር ዋነኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል።


በዚህ ምክንያት ዘወትር በኃይል የሚያምጡ ሰዎች በሰውነታቸው ላይ በብሽሽት አካባቢ እያደገ የሚሄድ እብጠት፣ ከባድ ዕቃ ሲያነሱ ከፍተኛ ምቾት ማጣት፣ በሚያስሉበት ወይም በኃይል በሚገፉበት ጊዜ የሕመም ስሜት ሊያስተውሉ ይችላሉ።


7️⃣ ዓይኖችም ቢሆኑ አደጋ ላይ ናቸው።

መጸዳጃ ቤት ውስጥ በኃይል በሚማጥበት ጊዜ፤ ዓይነቶቻችንም ቢሆኑ ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ ናቸው። በኃይል ማማጥ በዓይኖች ውስጥ ያለውን የውስጥ ግፊት ለጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር የሚያውቁት ግን በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው።

በእርግጥ ለአብዛኞቹ ጤናማ ሰዎች ይህ ጊዜያዊ ግፊት ዘላቂ ጉዳት አያመጣም። ነገር ግን ተጋላጭ በሆኑ ታካሚዎች ላይ፤ በተለይም የላቀ የዓይን ግፊት በሽታ (ለምሳሌ፦ ግላኮማ) ባለባቸው ሰዎች ላይ ይህ ተደጋጋሚ የግፊት መለዋወጥ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራል። የዓይን ሐኪሞች የተወሰኑ የዓይን ችግሮች ያሉባቸው ታካሚዎች፤ በተቻለ መጠን ከልክ በላይ ማማጥን እንዲያስወግዱ አጥብቀው የሚመክሩት ለዚህ ነው።


በመጀመሪያው ላይ ያነሳነው የ45 ዓመቱ ጎልማሳ ታሪክም የተከሰተው በዚህ ምክንያት ነው። ሰውየው መጸዳጃ ቤት ውስጥ በኃይል በማማጡ ምክንያት፤ በደረትና በሆድ አካባቢ የጨመረው ከፍተኛ ግፊት በደም ሥሮች በኩል በቀጥታ ወደ ላይ ተጓዘ። ይህ ጫና በዓይኖቹ ውስጥ የሚገኙትን እጅግ ስስ የሆኑ የደም ሥሮች እንዲፈነዱ በማድረጉ፤ "ማኩላ" (Macula) በተሰኘው የዓይናችን ዋና የዕይታ ማዕከል ላይ ከፍተኛ የደም መፍሰስ አስከተለ። ለዚህም ነው ...ያ ሰው ያለምንም ቅድመ ምልክት በድንገት የሁለቱም ዓይኖቹ እይታ ሙሉ በሙሉ የተጋረደው።  


እንደ እድል ሆኖ፤ ታካሚው የሆድ ድርቀቱ ከታከመለት ከሦስት ወራት በኋላ ዓይኖቹ ሙሉ በሙሉ ድነው ፤ እይታቸው ተመልሷል።

ይህ ጉዳይ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ትኩረት የሚሻው ለምንድን ነው?


በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ የሆድ ድርቀት በተለያዩ ማኅበራዊና አካላዊ ምክንያቶች የተነሳ እጅግ የተለመደ የጤና ችግር ነው። ለአብነት ያህል በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ የአሰር (Fiber) ይዘት ያላቸው ምግቦች አጠቃቀም አነስተኛ መሆን፣ በቀን ውስጥ በቂ ውኃ አለመጠጣት፣ የከተማ ኑሮ ዘይቤ እየጨመረ መምጣቱና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማነስ ተጠቃሽ ናቸው። እንዲሁም ክእድሜ ጋር የተያይዘ የሆድ ድርቀትም አንዱ ምክንያት ነው።


ብዙ ሰዎችም የሆድ ድርቀትን እንደ ተራና ቀላል ነገር በመቁጠር፤ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ለረጅም ሰዓት የመቀመጥ እና በኃይል የመማጥ መጥፎ ልማድ አዳብረዋል። ነገር ግን በየቀኑ የሚደረግና ቀላል የሚመስል የማማጥ ድርጊት፤ በጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ እላይ ለዘረዘርናቸው ከባድና አስከፊ የጤና እክሎች ይዳርጋል።


ማማጥን የሚያስወግዱበት 7 ተግባራዊ መንገዶች

መልካሙ ዜና፤ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ማማጥንና መከላከል በአብዛኛው በጣም ቀላል መሆኑ ነው። ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ፦

1. በቂ ውኃ ይጠጡ። በቂ ውኃ መጠጣት ሰገራ እንዲለሰልስና በቀላሉ እንዲወጣ ይረዳል።

2. የአሰር (fiber) ይዘት ያላቸውን ምግቦች ያብዙ። እንደ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ጥራጥሬዎች እና ሙሉ እህል ያሉ ምግቦችን መመገብ የሰገራ እንቅስቃሴን ያሻሽላል።

3. አካላዊ እንቅስቃሴ ያዘወትሩ። የዘወትር አካላዊ እንቅስቃሴ የአንጀት ሥራን ያነቃቃል።

4. ሽንት ቤት የመሄድ ፍላጎትን ማዘግየት ብዙውን ጊዜ የሆድ ድርቀትን ያባብሳል። . የሰገራ መምጣት ስሜትን ችላ አይበሉ።

5. በመጸዳጃ ቤት ላይ ከመጠን በላይ ሰዓት ማሳለፍን ያስወግዱ። ረጅም ሰዓት መቀመጥ በፊንጢጣ የደም ሥሮች ላይ ያለውን ጫና ይጨምራል።

6. የሚወስዷቸውን መድኃኒቶች ይፈትሹ። አንዳንድ መድኃኒቶች ለሆድ ድርቀት መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። ምልክቶቹ ከቀጠሉ የሕክምና ባለሙያ ያማክሩ።

7. ለሥር የሰደደ የሆድ ድርቀት የሕክምና ምርመራ ያድርጉ። የማያቋርጥ የሆድ ድርቀት ፈጽሞ እንደ መደበኛ ነገር ተደርጎ መወሰድ የለበትም።


ያስተውሉ!

በሰገራ ወቅት ማማጥ ከተራ ምቾት ማጣት ያለፈ ጉዳይ ነው። በመላው ሰውነት ላይ ግፊትን በመጨመር ለኪንታሮት፣ ለፊንጢጣ መውጣት፣ ለሄርኒያ፣ ለራስ መሳት፣ ለልብ ጫና እና አልፎ ተርፎም ለከባድ የሕክምና አደጋዎች ሊዳርግ ይችላል።


ሰገራ ለመውጣት ተደጋጋሚ ማማጥ ካስፈለገ፤ መፍትሄው በኃይል መግፋት አይደለም። መፍትሄው የሆድ ድርቀቱን ማከም ነው።


Comments


bottom of page