ጉንፋን ብለው አትዘናጉ! ሳንባ ምች ቢሆንስ?
Updated: Aug 19
እያሳላፍን ባለነው የክረምት ወቅት ጉንፋን ይዞዎት ነበርን? በዙሪያዎ ስንት ሰው በጉንፋን ተይዞ አስተውለዋል? ቢይዝዎትም ሊደንቆት አይገባም። በሀገራችንም ሆነ በአለም ዙሪያ፤ በእንደዚህ ያሉ ወቅቶች የመተንፈሻ አካል ቫይረሶች ስርጭት ሊጨምር ይችላል።

ለዚህም ብዙዎቻችን ማሳል ስንጀምር “ተራ ጉንፋን ነው፤ ይሻላል” ብለን እናስባለን። ነገር ግን ሁልጊዜ ነገሮች በዚህ አያበቁም። አንዳንድ ጊዜ ጉንፋኑን ተከትሎ፤ ባክቴሪያዎች የሰውነታችንን መከላከያ ሰብረው ወደ ሳንባ ከወረዱ ግን፤ በቀላሉ ወደ ሳንባ ምች (Pneumonia) ይለወጣል። እኛ ተራ ጉንፋን መስሎን በዝምታ በምንጠብቅበት ሰዓት፤ በሽታው በጀርባ እየደረጀ ምልክቶቹ ከቀን ወደ ቀን እየጠነከሩ ይመጣሉ። ብዙዎችም ተኝተው ለመታከም ይገደዳሉ።
ታድያ ሳንባ ምች ምንድነው? እንዴት ከጉንፋን መለየት እንችላለን? እንዴትስ እንከላከል?
ሳንባ ምች ምንድነው?
ብዙዎቻችን የሳንባ ምች ሲባል፤ በአንድ ዓይነት ጀርም (በሽታ አምጪ ተሕዋስ) ብቻ የሚመጣ በሽታ ይመስለናል።
እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው!

የሳንባ ምች ሳንባችን በተለያየ ምክንያት ሲቆጣ የሚመጣ በሽታ ነው። ሳንባችን በበሽታ አምጪ ተሕዋሳት (ባክቴሪያ፣ ቫይረስ እና ፈንገስ)ሲጠቃም ሊፈጠር ይችላል። ከበሽታ አምጪ ተሕዋሳት ባሻገር ፤ በአጋጣሚ ምግብ፣ መጠጥ ወይም ትውከት ወደ ሳንባችን አምልጦ በሚገባበት ጊዜም (Aspiration) ሳንባ ምች ሊያጋጥም ይችላል። ስለዚህ በሽታው በአንድ ምክንያት ብቻ የሚመጣ ሳይሆን፣ በርካታ መንገዶች ያሉትና ጥንቃቄ የሚሻ የጤና ስጋት ነው።
ስርጭቱ ምን ይመስላል?

ሳንባ ምች በአለም ዙሪያ ካሉ በየዓመቱ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ይቀጥፋል። በተለይም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትንና አረጋውያንን ክፉኛ ያጠቃል። ለዚህም በገዳይነቱ ከተላላፊ በሽታዎች ቀዳሚ ነው።
ኢትዮጵያ በአለም ላይ በሳንባ ምች ከፍተኛ የህመም ስርጭት ካለባቸው ሀገራት አንዷ ናት። በቀደሙ ግሞቶች በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ህፃናት በዚህ በሽታ ይያዛሉ። ይህም ማለት በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶች ልጆቻቸውን ታቅፈው ወደ ህክምና ተቋማት ይሮጣሉ ማለት ነው። በአመት ወደ 40 ሺ የሚሆኑ ህጻናትም ይሞታሉ ተብሎ ይገመታል።
እውነቱን ለመናገር፤ ስለ ሳንባ ምች ስናስብ ብዙ ጊዜ አእምሯችን ውስጥ የሚመጡት ሕፃናት ናቸው። ነገር ግን በሽታው በአዋቂዎች ላይም እያደረሰ ያለው ጉዳት ቀላል አይደለም። በሀገራችን በአዋቂዎች ላይ ስላለው ትክክለኛ የበሽታው ስርጭት የተሟላ መረጃ ማግኘት አሁንም ፈታኝ ነው። ምክንያቱም አብዛኞቹ መረጃዎች የሚሰበሰቡት ታማሚዎች ተባብሶባቸው ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ነው።
በሽታው በቀላሉ መከላከል የሚቻል ቢሆንም፤ በቤት ውስጥ "ተራ ጉንፋን ነው" ብሎ መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል።
የሳንባ ምች ይተላለፋል?

አዎ!
ሆኖም ግን ያስተውሉ! ሳንባ ምች የሚያስከትሉት አንዳንድ ኢንፌክሽኖች ሊተላለፉ ቢችሉም፤ ሁሉም የሳንባ ምች ዓይነቶች ተላላፊ አይደሉም።
በሽታውን የሚያመጡ ተሕዋስያን ፤ ወደ ሰውነታችን ሰርገው የሚገቡት በጣም ቀላል በሆኑ፤ በተለምዶ ሕይወታችን የማናስተውላቸው ናቸው። እነኝህም
አንድ የሳንባ ምች ሕመምተኛ በአቅራቢያችን ሆኖ ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጀርሞችን ወደ አየር ይበትናል። እኛም በዚያ ቅጽበት ከአጠገቡ ስላለን ፤ የምንተነፍሰው አየር ውስጥ ሳናውቀው እነዚህን ጀርሞች ቀጥታ ወደ ሳንባችን እናስገባለን።
ከዚህም ባሻገር ከታመመ ሰው ጋር በሚኖር የቅርብ ንክኪ (ስንጨባበጥ፣ ስንተቃቀፍ ወይም እርሱ የተጠቀመበትን ስልክ ስንነካ፣ አብረን ስንመገብ)፤ ታማሚ ጋር ያሉት ጀርሞቹ በቀላሉ ወደ እጃችን ይሻገራሉ። ከዚያም በዚያው ባልታጠበ እጃችን አፋችንን ወይም አፍንጫችንን ስንንካ፤ በሽታ አምጪ ተሕዋሳቱ ወደ ሰውነታችን ይገባሉ።
እንደ ጉንፋን ጀምሮ ወደ ሳንባ ምች ሊለወጥ ይችላልን?

እዚህ ጋር በጣም አስገራሚው ነገር፤አንዳንድ የሳንባ ምች ዓይነቶች በመጀመሪያ እንደ ተራ ጉንፋን በሚመስሉ ምልክቶች ሊጀምሩ ይችላሉ።
ሲጀምር ቫይረሱ አፍንጫችንና ጉሮሯችንን በማጥቃት እንደ አፍንጫ መዘጋትና የጉሮሮ መቆጣት ያሉ የተለመዱ የጉንፋን ምልክቶችን ያሳያል። በዚህ ወቅት የሰውነታችን መከላከያ ስርአት በቫይረሱ ስለሚዳከም፤ በአፍና በጉሮሮ ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኙ አንዳንድ ባክቴሪያዎች፣ ከቫይረስ ኢንፌክሽን በኋላ የሳንባን ኢንፌክሽን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህን ጊዜ የሳንባ ምች ይከሰታል።
ለዚህም በመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ የአፍንጫ መዘጋት፣ የጉሮሮ መቅጣት፣ መጠነኛ ትኩሳት፣ የሰውነት ድካም እና ሳል ሊኖር ይችላል።
እነዚህ ምልክቶች ታዩ ማለት፤ በሽታው የሳንባ ምች ነው ማለት አይደለም።

አሳሳቢውና ትኩረት የሚሻው የሚሆነው፤ ቀናቶች እያለፉ ሲሄዱ ምልክቶቹ መሻሻል ሲገባቸው ይበልጥ እየባሱ ሲሄዱ ነው። ምልክቶቹም የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ፦
ሳሉ እየበረታ ሄዶ ፤ አክታ መደባለቅ ይጀመራል።
ትኩሳቱ ከመጥፋት ይልቅ፤ እየባሰ ሊሄድ አልያም፤ ጠፍቶ ተመልሶ ሊመጣ ይችላል።
ትንፋሽ ማጠር ይጋጥማል። መተንፈስ ሊከብድ ይችላል።
ሲተነፍሱ የሚሰማ የደረት ሕመም ሊኖር ይችላል።
ድካሙም ሊብስ፤ ሊጫጫንዎት ይችላል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ምልክቶች በሁሉም ሰው ላይ አንድ ዓይነት ላይሆኑ ይችላሉ። በተለይ ዕድሜያቸው በገፉ አረጋውያን ላይ እንደ ትኩሳት ያሉ የተለመዱ ምልክቶች ላይታዩ ይችላሉ። ይልቁንም እነርሱ ላይ ድንገተኛ የሆነ የሃሳብ መዘበራረቅና የማስታወስ ችግር (ግራ መጋባት) ዋነኛ የሳንባ ምች ምልክት ሆኖ ሊመጣ ይችላል። ስለዚህ የሰውነታችንን ለውጥ በትዕግስት መከታተልና ምልክቶቹ ሲፈጠሩ ፈጥኖ መታከም ያስፈልጋል።
በተለይ በጣም ከባድ የመተንፈስ ችግር፣ ከንፈር ሰማያዊ መሆን አልያም ግራ መጋባት ካለ አስቸኳይ ሕክምና ይፈልጉ። ሳይውሉ ሳያድሩ የጤና ተቋም ይሂዱ!
ታድያ ሕመሙ ሲጀምር ምን ማድረግ ይችላሉ?

በቤትዎ ሕመሙ ገና ሲጀምርዎት የሚወስዷቸው እርምጃዎች የበሽታውን ጥንካሬ ይወስናሉ። በመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ ትኩረት ሰጥተው የሰውነትዎን የመከላከል አቅም ካጠናከሩ፤ በሽታው በቀላሉ ይለቃል።
ነገር ግን በሽታው እስኪከፋና ሳንባን አጥቅቶ እስኪያዳክም ከጠበቁ፤ ማገገሙ ከባድና ፈታኝ ይሆናል። ስለዚህ እርምጃ መውሰድዎ ብቻ ሳይሆን፤ ያንን እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ ትልቅ ቦታ አለው።
ገና በመጀመሪያው ደረጃ ላይ እያሉ የሚከተሉትን ወሳኝ ነገሮች ያድርጉ፦
“ተራ ጉንፋን ነው” ብለው አይገምቱ፦ ትኩሳት፣ ሳል እና የሰውነት ድካም እየባሱ ከሄዱ ወይም አዲስ የመተንፈስ ችግር ከተጨመረ፤ ነገሩን አቅልለው ሳይመለከቱት በአቅራቢያዎ ያለ የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
የበሽታ መከላከል አቅምዎን በምግብ ይገንቡ፦ ምግብዎን በደንብ እና በሰዓቱ ይመገቡ። ምክንያቱም የምግብ ማነስ ሰውነትን ስለሚያዳክም፤ በሽታው እንዲባባስ ዕድል ይከፍታል። በተለይም የመተንፈሻ አካላትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚገነባውን ቪታሚን ሲ የያዙ፤ እንደ ብርቱካንና መንደሪን ያሉ ፍራፍሬዎችን በየቀኑ ይመገቡ።
በቂ ፈሳሽ ይውሰዱና በሚገባ ይረፉ፦ ውሃና ሞቅ ያሉ ፈሳሾችን አብዝተው ይጠጡ። “በቂ ፈሳሽ መውሰድ የውሃ እጥረትን ለመከላከልና በሕመም ወቅት ሰውነትዎን ለማገዝ ይረዳል በሽታው ሰውነትዎን እያዳከመው ስለሚሆን፤ ሙሉ እረፍት በማድረግ ሰውነትዎ ራሱን እንዲጠግን ዕድል ይስጡት።
ትኩሳትና ሕመም ካለ ፓራሲታሞል ሊወሰድ ይችላል።
አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን በራስዎ ፈቃድ አይጀምሩ፦ ቀደም ሲል እንዳየነው ሁሉም የሳንባ ምች በባክቴሪያ አይከሰትም። ቫይረስ ለፈጠረው ሕመም አንቲባዮቲክ መውሰድ ምንም ጥቅም የለውም። ይልቁኑ አላግባብ መውሰዱ ለመድሐኒት መላመድ ያጋልጣል።
ሳንባ ምችን እንዴት እንከላከል?

ታሞ ከመማቀቅ ...እንደሚባለው፤ ጥቂት ቀላል የዕለት ተዕለት ልምዶችን በማድረግ ሳንባችንን ከዚህ አስከፊ በሽታ መከላከል ይቻላል። ለዚህም የሚከተሉትን መንገዶች ይተግብሩ፦
እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና ይታጠቡ። ይህ በሽታ አምጪ ተሕዋሳት፤ ከእጅዎ ተነስተው ወደ አፍና አፍንጫዎ እንዳይገቡ የሚከላከል ቀዳሚውና ቀላሉ መከላከያ መንገድ ነው።
የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን ሲኖርብዎት፤ ከእርስዎ አልፈው ለሌሎች ያስቡ። የጉንፋን ስሜት ካለብዎት ሲስሉ ወይም ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫዎን በመሸፈን፤ በሽታው ወደ ቤተሰብዎና ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይሰራጭ ጥንቃቄ ያድርጉ።
ሳንባዎን ከጭስ ይጠብቁ። ሲጋራ ማጨስን በፍጹም ያቁሙ። በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ የሚኖርን የጭስ ተጋላጭነት ይቀንሱ። በተለይ በእንጨትና በከሰል ማብሰያ በሚጠቀሙባቸው ቤቶች ውስጥ አየር በነፃነት እንዲዘዋወር መስኮቶችን መክፈት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው።
ተገቢ የሆኑ ክትባቶችን ይውሰዱ። የኢንፍሉዌንዛ (የጉንፋን) እና የፕኒውሞኮካል ክትባቶች በሳንባ ምች የመያዝ አደጋን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳሉ። የትኛው ክትባት ለእርስዎ ወይም ለልጅዎ እንደሚያስፈልግ የጤና ባለሙያዎን ይጠይቁ።
የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ ሰውነትዎን ያጠናክሩ። ሁልጊዜ በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የሰውነትዎን የተፈጥሮ በሽታ መከላከል አቅም ስለሚገነባ፣ ሳንባዎ ማንኛውንም መጪ ወራሪ ጀርም በቀላሉ እንዲዋጋ ይረዳዋል።
ሳልን ችላ አይበሉ። ምልክቶቹን ይከታተሉ። በጊዜ ይመርመሩ።




Comments