አፍንጫዎ ሁልጊዜ ተደፍኖ ይሰማዎታል? ጉንፋን ሳይሆን የአፍንጫ እጢ ቢሆንስ?
- Zebeaman Tibebu
- 5 days ago
- 3 min read
አፍንጫዎ ለወራት ተደፍኖ ይቆያል?
አፍንጫዎ ውስጥ ሁልጊዜ ንፍጥ እንዳለ ይሰማዎታል?
ሽታ የመለየት አቅምዎ ቀስ በቀስ ቀንሷል?
የጉንፋን መድሃኒት ቢወስዱም ለውጥ አላዩም?

ችግሩ ምንድነው?
ብዙዎች ይህንን ስቃይ እንደ ተራ ጉንፋን ይቆጥሩታል። ነገር ግን ከጀርባው በድብቅ የሚሰለጥን ሌላ ጠላት አለ። እርሱም ናዛል ፖሊፕ (Nasal Polyp) ይሰኛል። ይህ ስም ሲሰማ ብዙዎችን ካንሰር ቢያስፈራቸውም፤ እውነታው ግን ፈጽሞ የተለየ ነው።
ናዛል ፖሊፕ ምንድን ነው?

ናዛል ፖሊፕ ማለት በአፍንጫ ወይም በሳይነስ መተላለፊያዎች ሽፋን ላይ በሚፈጠር የረጅም ጊዜ እብጠት ምክንያት የሚከሰት ዕጢ ነው። ነገር ግን ፍጹም ካንሰር ያልሆነ፤ ህመም የሌለው፤ ልክ እንደ ተንጠለጠለ ወይን ለስላሳና ውኃ የሞላበት እብጠት ነው።
ችግሩ ግን አድጎ ፤ ሁለቱንም የአፍንጫ ቀዳዳዎች በአንድ ጊዜ ሲዘጋ ነው። ይህን ጊዜ ንጹህ አየር እንዳይገባ መንገድ ይከለክላል፤ ሕይወትንም ፈታኝ ያደርገዋል። ይህንን ስውር ስውር ችግር ለይቶ ማወቅና መፍትሔ መፈለግ ወደ ሙሉ ጤንነት የሚመልስ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
ፖሊፕ ለምን ይፈጠራል?

ትክክለኛው መንስኤ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ባይታወቅም፤ አንድ ነገር ግን በግልጽ እንረዳለን። የቆየ የአፍንጫ እና የሳይነስ መቆጣት የፖሊፕ መፈጠር ዋናው መሠረት ነው። ለዚህ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ የሚያደርጉ የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ። እነርሱም፦
ሥር የሰደደ የሳይነስ እብጠት (Chronic Rhinosinusitis)፣
አስም (Asthma)፣
የአፍንጫ አለርጂ (Allergic Rhinitis)፣
ለአስፕሪን ወይም ለአንዳንድ NSAIDs የሚኖር ከባድ ስሜታዊ ምላሽ፣
አንዳንድ የበሽታ መከላከያን የሚያጠቁ እና ከዘረመል ጋር የተያያዙ በሽታዎች፣
በተደጋጋሚ የሚከሰት የአፍንጫ መቆጣት ናቸው።
ምልክቶቹ ምንድናቸው?

ብዙ ጊዜ እነዚህን ምልክቶች "ጉንፋን ነው" ብለን ለወራት በቸልተኝነት ልናልፋቸው እንችላለን። ነገር ግን ፖሊፕ በውስጣችን ካለ፤ ምልክቶቹ ከ12 ሳምንት በላይ አብረውን ይቆያሉ። ከእነሱም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
አፍንጫ መደፈን፣ የማያቋርጥ ንፍጥ፣ ወደ ጉሮሮ የሚወርድ ንፍጥ፣
ሽታ የመለየት አቅም መቀነስ ወይም መጥፋት፣ ጣዕም የመለየት ችግር፣
አፍንጫ ተደፍኖ መተኛት፣ ሲተኙ ማንኮራፋት፣ እና
ፊት ላይ የሚሰማ የግፊት ስሜት ናቸው።
ምን ያህል አደገኛ ነው?

ፖሊፕ በራሱ ካንሰር ባይሆንም፤ በሕይወታችን ላይ ግን ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል። ካልታከመና እያደገ ከመጣ ሁለቱንም የአፍንጫ ቀዳዳዎቻችንን በአንድ ጊዜ ይዘጋል። ንጹህ አየር እንዳናገኝ መንገድ በመከልከልም ፤ ለተደጋጋሚ የሳይነስ ኢንፌክሽን ያጋልጣል። ሽታ የመለየት አቅምንም ከማዳከም አልፎ እንቅልፍን ያስተጓጉላል። ለአስም በሽተኞች ደግሞ የአስም ህመሙ እንዲባባስ እድል ይፈጥራል።
ስርጭቱ ምን ይመስላል?

የናዛል ፖሊፕ 1% እስከ 4% የሚደርሰውን የአለም ህዝብ ላይ የሚታይ ሲሆን ፤ የሳይንሳይተስ በሽታ ካለባቸው ሰዎች መካከል ደግሞ ከ20% እስከ 30% የሚሆኑትን ያጠቃል። ይህ ሕመም በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ ጎልማሶች ላይ ይታያል። ወንዶች ከሴቶች ከ2 እጥፍ እስከ 3 እጥፍ በበሽታው ይጠቃሉ።
ህጻናት ላይ ግን ናዛል ፖሊፕ እጅግ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት እንግዳ ሕመም ነው። ለዚህም አንድ ሕፃን ላይ ይህ ችግር ከተገኘ ሐኪሞች ከጀርባው ያሉ ሌሎች ከባድ የጤና እክሎችን በጥልቀት ይመረምራሉ። ከእነዚህም መካከል ሲስቲክ ፋይብሮሲስ (Cystic Fibrosis)፣ ፕራይመሪ ሲሊያሪ ዳይስኪኔዥያ (Primary Ciliary Dyskinesia)፣ እንዲሁም የተለያዩ ከባድ የአለርጂና የሳይነስ በሽታዎች አለመኖራቸውን ማረጋገጥ ዋነኛው የሕክምና ትኩረት ይሆናል።
የአፍንጫ ፖሊፕ እንዴት ይመረመራል?

ሐኪምዎ የአፍንጫ ፖሊፕ መኖር አለመኖሩን፤ መጠኑን እና የተፈጠረበትን ምክንያት ለማወቅ ፤ ልዩ የእጅ ባትሪና መመልከቻ መሣሪያ በመጠቀም የአፍንጫዎን ውስጠኛ ክፍል ይመረምራል። በይበልጥ ለመመልከት ናዛል ኢንዶስኮፒ (Nasal Endoscopy) ሊያዝ ይችላል።
ይህ በሳይነስና በአፍንጫ ጥልቅ ክፍሎች ውስጥ ያሉትን ፖሊፖች በግልጽ በስክሪን ለማየት ይረዳል። ሲቲ ስካን ምርመራ ደግሞ በሳይነስ አካባቢ ያለውን የመቆጣት መጠንና የፖሊፑን ትክክለኛ ስፍራ ለማወቅ ይረዳል። ፖሊፑ የተከሰተው በአለርጂ ምክንያት መሆኑ ከተጠረጠረ ፤ ዋናውን መንስኤ ለማወቅ የአለርጂ የቆዳ ምርመራ ሊደረግ ይችላል። እንዲሁም ደጋፊ የሆኑ የደም ምርመራዎች ይታዘዛሉ።
ፖሊፕ ሙሉ በሙሉ ይድናል?
አዎ፤ ይድናል።
የሕክምናው ዋና ዓላማ የፖሊፑን መጠን ማሳነስ፣ በአፍንጫ ውስጥ ያለውን መቆጣት መቀነስ እና የታካሚውን የአፍንጫ አተነፋፈስ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ማሻሻል ነው።
ያሉት የህክምና አማራጮች ይህን ይመስላሉ።

የአፍንጫ ፖሊፕን ለማከም የሚከተሉት የሕክምና አማራጮች አሉ።
የአፍንጫ ስቴሮይድ ስፕሬይ (Nasal Steroid Sprays): ይህ የመጀመሪያውና ዋነኛው ሕክምና ሲሆን፤ አፍንጫ ውስጥ ያለውን መቆጣት በመቀነስ የፖሊፑን መጠን ያሳንሰዋል። ይህም የተዘጋው የአፍንጫ ቀዳዳ እንዲከፈት ፤ እንዲሁም ምልክቶቹ እንዲሻሻሉ ያደርጋል።
የሚዋጡ ስቴሮይድ መድኃኒቶች (Oral Corticosteroids): ስፕሬዩ በቂ ካልሆነ ፤ ሐኪሙ ለአጭር ጊዜ የሚዋጥ የስቴሮይድ መድኃኒት ሊያዝልዎት ይችላል።
ከዚህም ባሻገር በቤትዎ በጨው ውኃ አፍንጫን እንዲያጥቡ ሊመክርዎት ይችላል (Saline Nasal Rinse)። ይህ ደግሞ አፍንጫ ውስጥ የተከማቸ ቆሻሻን በማጽዳት ፤ መተንፈስን ያቀላል።
ለከባድ እና በተደጋጋሚ ለሚመጡ የፖሊፕ ዓይነቶች የሚሰጡ የመርፌ አማራጮችም አሉ።
ከእዚህም ባሻገር የባክቴሪያ ኢንፌክሽን አለ ተብሎ ሲታሰብ ፤ አንቲባዮቲኮች ሊሰጡ ይችላሉ።
ቀዶ ጥገናስ?

ይህ ሌላው የህክምና አማራጭ ነው። ሆኖም ግን፤ እያንዳንዱ ፖሊፕ ቀዶ ጥገና አያስፈልገውም። በካሜራ የታገዘ ቀዶ ጥገና በማድረግ (Endoscopic Sinus Surgery) ፖሊፑን ሙሉ በሙሉ ማንሳትና ሳይነሱን ማፅዳት ይቻላል። ይህ የሚመከረው ፤ ታካሚ ፦
✅ መድሃኒት ቢወስዱም ምልክቶቹ ካልተሻሻሉ
✅ አፍንጫው ሙሉ በሙሉ ከተዘጋ
✅ ሽታ የመለየት አቅሙ በጣም ከቀነሰ
✅ በተደጋጋሚ የሳይነስ ኢንፌክሽን ካጋጠመ
✅ ፖሊፑ የሳይንሱን መተላለፊያ ከዘጋ
✅ የአፍንጫ ውስጥ ሌላ አደገኛ እጢ መኖሩ ሲጠረጠር ነው
የቀዶ ጥገናው ዓላማ ፖሊፑን ማስወገድ፣ የሳይነስ መተላለፊያን መክፈት እና መድሃኒቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲሰሩ ማድረግ ነው።
ከቀዶ ጥገና በኋላ ይመለሳል?
ይህ በታካሚዎች የሚጠየቅ በጣም የተለመደ ጥያቄ ነው።
ምላሹ "አዎ "ነው።
ናዛል ፖሊፕ ዳግመኛ ሊያድግ ይችላል። ምክንያቱም ቀዶ ጥገናው ፖሊፑን ቢያስወግድም፤ ለእርሱ መሰረት የሆነው መቆጣት ሊያጠፋ ባለመቻሉ ነው።
ስለዚህ ከቀዶ ጥገና በኋላም የአፍንጫ ስቴሮይድ ስፕሬይ መጠቀም፣ የአለርጂ ችግርን መቆጣጠር፣ እና መደበኛ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በቤት ውስጥ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ቀላል መፍትሔዎች

ምልክቶቹን ካስተዋሉ በቤትዎ ውስጥ እነዚህን በማድረግ ፤ እፎይታ ማግኘት ይችላሉ፦
የጨው ውኃ አፍንጫን ማጠብ፤ የተዘጋውን ቀዳዳ ለመክፈትና ንፍጥን ለማስወገድ ይረዳል።
ሞቅ ባለ ውኃ እንፋሎት መታጠን ፤ የአፍንጫ ውስጥ ሽፋንንን በማርጠብ እና በማጽዳት መተንፈስን ያቃልላል።
በሰውነት ውስጥ ፈሳሽ መብዛቱ በአፍንጫ ውስጥ የሚገኘው ንፍጥ እንዲቀጥን ያደርገዋል።




Comments