top of page

ዝምተኛው የቆሽት ካንሰር

ስለ ቆሽት ካንሰር ሰምተው ያውቃሉ?

በተለይ የቆሽት ጫፍ ካንሰር በአለም ዙሪያ በጣም አደገኛ እና ገዳይ ከሚባሉ የካንሰር አይነቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ በሽታ አስፈሪ የሚያደርገው ዋናው ምክንያት «ዝምተኛ» መሆኑ ነው።

ምንም ዓይነት ግልጽ ምልክት ሳያሳይ ፤ በሰውነትዎ ውስጥ ለወራት ወይም ለዓመታት በዝምታ ሊያድግ ይችላል። ካንሰሩ ሲጀምር ብዙ ጊዜ ግልጽ የሕመም ምልክት አያሳይም፤ ትኩሳትም የለውም። በሰውነትም ላይ የሚታይ እብጠት ወይም እንግዳ ለውጥ አይኖርም። ካንሰሩ እያደገ መሆኑን የሚጠቁም አንዳችም ፍንጭ አይገኝም። ስለዚህም ብዙ ሰዎች ሳያውቁት ይኖራሉ።


ነገር ግን፤ በድንገት ሁሉም ነገር ይቀየራል። የታማሚው ዓይኖች ወደ ቢጫነት ይለወጣሉ። የምግብ ፍላጎት ጨርሶ ይጠፋል። በጀርባ ላይ ደግሞ የማይለቅ የማያቋርጥ ሕመም ይፈጠራል። ሰውነት በፍጥነት ስለሚቀንስ፤ ልብሶች እንኳ ሳይቀሩ በድንገት እየሰፉ ይሄዳሉ።


ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ታማሚ ደንግጦ ወደ ሕክምና ቦታ የሚሄደው። ሆኖም፣ ብዙ ሰዎች የሕክምና ዕርዳታ በሚፈልጉበት በዚያ ወሳኝ ወቅት፤ ካንሰሩ ተሰራጭቶ ይሆናል። ብዙዎች አርፍደው ነው የሚያውቁት።


ይህ በዘመናዊው ሕክምና ውስጥ ካሉት እጅግ በጣም አስፈሪ እና ፈታኝ ከሆኑ ሕመሞች አንዱ የሆነው የቆሽት ካንሰር (Pancreatic Cancer) እውነተኛ ገጽታ ነው። ዛሬ ስለ ቆሽት ካንሰር በጥልቀት እናነሳለን።

🧩 በመጀመሪያ ቆሽት ምንድን ነው?

ስለ ልብ፣ ስለ ጉበት፣ ስለ ኩላሊት እና ስለ ሳንባ ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ሲነሳ ሰምተው ይሆናል። ስለ ቆሽት ምንነትና ጥቅም የሚያውቁ ግን በጣም ጥቂት ናቸው። ቆሽት ከጨጓራ በስተጀርባ፣ በሆድ ዕቃ ጥልቅ ክፍል ውስጥ ተደብቆ የሚገኝ ረዥም እና ለስላሳ እጢ ነው። ይህ አካል በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ትንሽ ቢሆንም፤ በሰውነታችን ውስጥ ሁለት መሠረታዊ እና እጅግ ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን ያከናውናል።



የመጀመሪያው ዋና ተግባሩ የምግብ መፈጨት ሂደትን ማገዝ ነው። ቆሽት በየቀኑ ወደ ትንሹ አንጀት የሚፈሱ ኃይለኛ ኢንዛይሞችን ያመርታል። እነዚህ ኢንዛይሞች የምንመገበውን ስብ፣ ፕሮቲን፣ እና ካርቦሃይድሬት በመሰባበር ሰውነታችን አልሚ ንጥረ ነገሮችን በቀላሉ እንዲመጥ ያደርጉታል። እነዚህ ኢንዛይሞች ከሌሉ ግን ትክክለኛው የምግብ መፈጨት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ይስተጓጎላል።


ሁለተኛው እና ሌላኛው ትልቅ ተግባሩ ደግሞ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር ነው። ይህንን የሚያደርገው በቀጥታ ወደ ደም ዝውውር የሚገቡ ሁለት ተቃራኒ ሆርሞኖችን በማምረት ነው። ኢንሱሊን የተሰኘው ሆርሞን በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በጣም እንዳይጨምር ሲያደርግ፣ ግሉካጎን ደግሞ በተቃራኒው ስኳር በጣም እንዳይቀንስ ይከላከላል። እነዚህ ሆርሞኖች በጋራ በመሥራት የስኳር እና የስብ ቁጥጥርን ይከታተላሉ።


ለዚህም ነው ቆሽት ላይ የሚያጋጥሙ በሽታዎች የምግብ መፈጨትን የሚናጉት ፤ አልፎ ተርፎም የስኳር ቁጥጥር ላይ እክል የሚፈጥሩት።


🚨 የቆሽት ካንሰር ምንድን ነው?

የቆሽት ካንሰር የሚከሰተው በቆሽት ውስጥ ያሉ ሴሎች ከቁጥጥር ውጪ ማደግ ሲጀምሩ እና አደገኛ እብጠት ወይም እጢ ሲፈጥሩ ነው። ከዘጠኝ አስረኛ በላይ የሚሆኑት የቆሽት ካንሰር አይነቶች የሚጀምሩት የምግብ መፈጨት ኢንዛይሞችን ከሚያስተላልፉት ቱቦዎች ውስጥ ሲሆን፤ እነዚህም በሕክምናው ዓለም ፓንክሪያቲክ ደክታል አዴኖካርሲኖማ (Pancreatic Ductal Adenocarcinoma) በመባል ይታወቃሉ።



የቆሽት ካንሰር በተለይ አደገኛ የሚያደርጉት በርካታ ተፈጥሯዊ ባህሪያት አሉት። በሽታው በመጀመሪያ ደረጃው ላይ ምንም ዓይነት ግልጽ ምልክት አያሳይም። በተጨማሪም ቆሽት በሆድ ዕቃ ውስጥ በጣም ጥልቅ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ትናንሽ እብጠቶችን በተለመደው የሕክምና ምርመራ ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው። በዚህም ምክንያት ካንሰሩ በሰውነት ውስጥ መኖሩ ሳይታወቅ በፊት በአቅራቢያው ወደሚገኙ የሰውነት ክፍሎች የመሰራጨት ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል። በሽታው አንዴ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከተሸጋገረ በኋላ ደግሞ ውጤታማ ሕክምና ለመስጠት ይበልጥ ፈታኝ ይሆናል። ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ታካሚዎች የሚሰጡ የህክምና አማራጮችም ውስን ናቸው።


የቆሽት ካንሰር በዓለም ዙሪያ በብዛት ከሚከሰቱት የካንሰር አይነቶች ተርታ ባይመደብም፤ ከካንሰር ጋር በተያያዘ ለሞት ከሚያደርሱ ግንባር ቀደም ምክንያቶች አንዱ ሆኖ የሚጠቀሰው በዚህ ባህሪው ነው። ለዚህም በሽታውን አስቀድሞ መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህም ለሕይወት መትረፍ ወሳኝ ነው።


⚠️ ፈጽሞ ችላ ሊባሉ የማይገቡ 8 የማስጠንቀቂያ ምልክቶች

የበሽታው አንዱ ትልቅ ፈተና የሕመም ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ በሂደት እና ደረጃ በደረጃ ብቅ ማለታቸው ነው። የሚከተሉት ምልክቶች፣ በተለይም ሳይጠፉ ለረዥም ጊዜ ሲቆዩ ወይም በአንድ ላይ ተያይዘው ሲከሰቱ ፈጣን የሕክምና ምርመራ ያስፈልጋቸዋል።


  1. የዓይን ወይም የቆዳ ቢጫ መሆን (Jaundice)

ይህ የሚሆነው በቆሽት ራስ ላይ የሚገኝ እብጠት የጉበት ፈሳሽ ማለፊያ ቱቦን በሚዘጋበት ጊዜ ሲሆን፤ ይህም የዓይንና የቆዳ ቀለም መለወጥን ብቻ ሳይሆን፣ የሽንት ቀለም በጣም መጥቆርንና የሰገራ ቀለም ነጣ ብሎ የሸክላ አፈር መልክ መያዝን ያስከትላል። ብዙ ሕመምተኞች መጀመሪያ ወደ ሕክምና ቦታ የሚሄዱትም፣ የቤተሰብ አባላት የዓይናቸው ቀለም መለወጡን ቀድመው ካስተዋሉላቸው በኋላ ነው።

  1. ያለ ምክንያት የሰውነት ክብደት መቀነስ

ምንም ዓይነት የምግብ ቁጥጥር ሳይደረግ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሳይጨምሩ፣ ያለ ምክንያት የሰውነት ክብደት በፍጥነት መቀነስ ሁልጊዜም ትልቅ አሳስቢ ምልክት ነው። ካንሰሩ የሰውነትን መደበኛ አሠራር ስለሚያስተጓጉል እና በምግብ መፈጨት ሂደት ላይ ጣልቃ ስለሚገባ፤ ለክብደት መቀነስ ይዳርጋል።

  1. የማያቋርጥ የሆድ ሕመም

ሌላው አስቸጋሪ ምልክት ብዙውን ጊዜ በሆድ የላይኛው ክፍል ላይ የሚፈጠር የማያቋርጥ የሆድ ሕመም ነው። አንዳንድ ሕመምተኞች ይህንን ስሜት በሆድ ውስጥ ጥልቅ የሆነ ምቾት ማጣት፣ ከመውጫ የጎድን አጥንቶች በታች የመጫን ስሜት፣ ወይም ደግሞ የማያቋርጥ የደነዘዘ ሕመም አድርገው ይገልጹታል።


  1. የጀርባ ሕመም

 የሆድ ሕመሙ ወደ ጀርባ ሊሰራጭ ይችላል። ይሁን እንጂ የጀርባ ሕመም በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በጣም የተለመደ በመሆኑ፤ ይህ ምልክት ብዙ ጊዜ ትኩረት ሳይሰጠውና ከቆሽት በሽታ ጋር ሳይያያዝ ይታለፋል።

  1. የምግብ ፍላጎት መጥፋት

ከዚህ ጋር ተያይዞ በጥቂት ምግብ ወዲያውኑ የመጥገብ ስሜት፣ ለምግብ ያለው ፍላጎት መቀነስ፣ እና ምግብን ጨርሶ የመመገብ መቸገርን የመሰሉ ከፍተኛ የምግብ ፍላጎት መጥፋት ምልክቶች ይታያሉ።

  1. የማቅለሽለሽ ስሜት እና የምግብ መፈጨት ችግሮች

በተጨማሪም በሽታው በተለመደው የምግብ መፈጨት እና ሆድ ባዶ በሚሆንበት ተፈጥሯዊ ሂደት ላይ ጣልቃ ስለሚገባ ፤ የማቅለሽለሽ ስሜት፣ የሆድ መነፋት፣ እና ከፍተኛ የምግብ አለመፈጨት ችግሮች በታማሚው ላይ በተደጋጋሚ ይስተዋላሉ።


  1. አዲስ የተከሰተ የስኳር በሽታ

 በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ የቆሽት ካንሰር መጀመሪያ የሚታወቀው አዲስ በሚከሰት የስኳር በሽታ አማካኝነት ነው። ተመራማሪዎች እንዳስተዋሉት፤ ካንሰሩ ሌሎች ምልክቶች በግልጽ ከመታየታቸው በፊት የቆሽትን የኢንሱሊን ምርት ሊያስተጓጉል ይችላል። ይህ በተለይ በዕድሜ የገፉ አዋቂዎች ላይ፣ ቤተሰብ ታሪክ ወይም ግልጽ የስኳር መንስኤዎች ሳይኖሩ በድንገት የስኳር በሽታ ሲከሰት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ለዚህ ነው።

  1. ከፍተኛ የድካም ስሜት

በመጨረሻም፣ በእረፍት ጨርሶ የማይሻሻል እና ቀጣይነት ያለው ከፍተኛ የድካም ስሜት መታየት ነው፤ ይህ ዓይነቱ ድካም የቆሽት ካንሰርን ጨምሮ ከብዙ የካንሰር ዓይነቶች ጋር አብሮ የሚከሰት ሌላው ምልክት ነው።


ይበልጥ ተጋላጭነት ያላቸው እነማን ናቸው?

አብዛኛዎቹ የቆሽት ካንሰሮች የሚከሰቱት በዘረመል (ጄኔቲክ)፣ በአካባቢ፣ እና በአኗኗር ዘይቤዎች ጥምረት ምክንያት ነው። ለበሽታው መከሰት ዋና ዋና መንስኤዎች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ሲጋራ ማጨስ ዋነኛው ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ጨርሶ ከማያጨሱት ይልቅ በቆሽት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው በእጅጉ የላቀ ነው። 


ከዚህ በተጨማሪ ከመጠን በላይ የሰውነት ክብደት መጨመር ወይም ውፍረት እና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ ለበሽታው መጋለጥ እድልን ይጨምራሉ። እነዚህ ጤናማ ያልሆኑ የአመጋገብ ዘይቤዎች የሰውነት ኃይልና ምግብ አጠቃቀም ሂደትን በማስተጓጉል፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ለካንሰሩ ያጋልጣሉ።


ከአኗኗር ዘይቤ ባሻገር ደግሞ በበሽታው የተያዘ የቤተሰብ አባል መኖሩ የመጋለጥ እድሉን ይጨምራሉ። አንዳንድ የዘረመል በሽታዎች (የጄኔቲክ ሲንድሮሞች) የአደጋውን መጠን ከፍ ያደርጉታል። ለረዥም ጊዜ የቆየ የቆሽት መቆጣትም (Chronic Pancreatitis)፤ ለቆሽት ካንሰር ያጋልጣል።

እድሜም ለዚህ በሽታ አጋላጭ ነው። አብዛኛዎቹ የቆሽት ካንሰር ተጠቂዎች በሽታው የሚከሰትባቸው ከ60 ዓመት ዕድሜያቸው በኋላ እንደሆነ የሕክምና ጥናቶች ይጠቁማሉ።


የቆሽት ካንሰር ምርመራዎች?



ዶክተሮች የቆሽት ካንሰር መኖሩን በእርግጠኝነት ለመለየት በርካታ የሕክምና ምርመራዎችን በጥምረት ይጠቀማሉ። ለምሳሌ፦

  1. የደም ምርመራዎች

ይህ የደም ህዋሳት ያሉበትን ሁኔታ እንዲሁም የጉበትን የሥራ ሁኔታ ለመገምገም እና እንደ ጉበት ፈሳሽ ቱቦ መዘጋት ያሉ ተያያዥ ችግሮችን ቀድሞ ለመለየት ይረዳል።

  1. የሲቲ ስካን (CT Scan) ምርመራ

በሽታውን ይበልጥ በትክክል ለማረጋገጥ ይህ ምርመራ ተመራጭ ነው። ይህ ዘመናዊ መሣሪያ የካንሰሩን ትክክለኛ መጠን፣ የሚገኝበትን ቦታ፣ እና ካንሰሩ ወደ አቅራቢያ አካላት መሰራጨቱን ወይም አለመሰራጨቱን በግልጽ ሊያሳይ ያስችላል። በአንዳንድ ታካሚዎች ላይ በይበልጥ በዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት ኤምአርአይ (MRI) ሊታዘዝ ይችላል።

  1. በአንጀት በኩል የሚሰራ አልትራሳውንድ (EUS)

ይህ ኢንዶስኮፒ ከሚባል ምርመራ ጋር ተያይዞ የሚሰራ ነው። አልትራሳውንድ መሳሪያው ከኢንዶስኮፒ መመርመሪያው ጋር ሆኖ በአፍ እና በጉሮሮ በኩል አድርጎ ጨጓራን አልፎ አንጀት ጋር ይደርሳል። በትንሹ አንጀት ግድግዳ በኩል አድርጎም ቆሽትን ይመረምራል። ይህ ዘዴ ምርመራ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ለላቦራቶሪ የሚሆን ናሙና ለመውሰድም ጭምር ያገለግላል።

  1. የናሙና ምርመራ (Biopsy)

ከቆሽት የተወሰደው ናሙና በላብራቶሪ የካንሰር ባህሪ እንዳለውና ደረጃው ይረጋገጣል።


ሊታከም ይችላል?

አዎ፤ የቆሽት ካንሰር ሊታከም ይችላል!

ይሁን እንጂ የሚሰጠው የሕክምና ዓይነት እንደ እብጠቱ ቦታ፣ እንደ በሽታው ደረጃ፣ እና እንደ ሕመምተኛው አጠቃላይ ጤናማነት ሁኔታ ይወሰናል።


በሽታው ቀድሞ ሲታወቅና በቆሽት ላይ ብቻ ተወስኖ በሚገኝበት ወቅት፤ አማራጩ ህክምና ቀዶ ጥገና ሊሆን ይችላል። ይህ ለረጅም ጊዜ የመኖር የተሻለ ዕድል የሚሰጥ ዋነኛ የሕክምና መንገድ ነው። ይህ የቀዶ ጥገና ሥራ የቆሽትን የተወሰነ ክፍል፣ በአቅራቢያ ያሉ ንፍፊቶችን፣ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በአቅራቢያ ያሉ ተያያዥ አካላትን ማስወገድን ሊያስፈልግ ይችላል።


በተጨማሪ የኬሞቴራፒ መድኃኒት ከቀዶ ጥገና በፊት እብጠቱን ለማሳነስ፤ ከቀዶ ጥገና በኋላ የቀሩ የካንሰር ሴሎችን ለማጥፋት፤ እንዲሁም በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለደረሰባቸው ታካሚዎች ዕድሜን ለማራዘም ሊያገለግል ይችላል።


ለተወሰኑ ታካሚዎች የጨረር ሕክምና ሊሰጥ ይችላል።


ከእነዚህ ሕክምናዎች ጎን ለጎን ግን የእንክብካቤ ሕክምና አስፈላጊ (Palliative Care) ነው። ይህ እንክብካቤ የታማሚውን ሕመም መቆጣጠርን፣ የአመጋገብ ሁኔታን ማስተካከልን፣ የምግብ መፈጨት ችግሮችን መፍታትን፣ እና የስሜት ደኅንነትን መንከባከብን ያካትታል።

ይህም ታካሚው በሕክምናው ሂደት ውስጥ የተሻለ እና ምቹ ሕይወት እንዲመራ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

መከላከያ መንገዶቹ?

ለቆሽት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚከተሉትን እርምጃዎች ይውሰዱ።

✅ ሲጋራ አያጭሱ።

✅ ጤናማ የሰውነት ክብደትን ይጠብቁ።

✅ አዘውትረው አካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።

✅ የስኳር በሽታዎትን በአግባቡ ይቆጣጠሩ።

✅ በፍራፍሬ፣ በአትክልት፣ በጥራጥሬ እና በሙሉ እህል የበለጸገ የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ።

✅ የምግብ መፈጨት ችግሮች ወይም ያለ ምክንያት ክብደት መቀነስ ምልክቶች ካስተዋሉ ተገቢውን የሕክምና ክትትል ያድርጉ።

ማስታወስ ያለብዎ ዋና ጉዳይ

እላይ የዘረዝርናቸውን ምልክቶችን አዩ ማለት ቆሽት ካንሰር አለብዎ ማለት አይደለም! መኖሩን ለማረጋገጥ የሕክምና ምርመራ ያስፈልጋል። ለዚህም ተገቢውን የሕክምና ምርመራ በአፋጣኝ ያድርጉ።


Comments


bottom of page