ህጻን በእርግጥም አዛውንት መስሎ ሊወለድ ይችላልን? ከማህበራዊ ሚዲያ ወሬ ጀርባ ያለው እውነት
- Zebeaman Tibebu
- 19 hours ago
- 3 min read
“አንዳንዴ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ እጅግ አስገራሚ ወሬዎች፤ ስለ ህክምና ሳይንስ ድንቅ እውነታዎችን የምንማርባቸው መልካም አጋጣሚዎች ይሆናሉ።”

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ “ወጣት የሚመስል ህጻን በጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ ተወለደ” የሚሉ መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ ታይተዋል። ከወሬው ጋር የተያያዙ ምስሎች፤ አዲስ የተወለደ ጨቅላ ህጻን በጥቁር ጺም የተሞላ ፊት እንዳለው ያሳያሉ። “በወጣትነቱ የተወለደ ህጻን” የሚሉ መግለጫዎችም ተጨምረውባቸዋል።
ነገር ግን ጉዳዩ የተከሰተበትን የጤና ተቋም በስም የጠቀሰ መረጃ የለም። እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች የሰጡት የምርመራ ውጤት (Diagnosis) ወይም ይፋዊ የህክምና ግምገማ አልቀረበም። ይህ የብዙ ሰዎችን ጉጉት ከመሳቡም ባሻገር፤ ብዙ ጥያቄዎችን አጭሯል።
“ህጻን በእርግጥም አዛውንት መስሎ ሊወለድ ይችላልን?” የሚለው ጥያቄ አስነስቷል። የህክምና ሳይንስ ለዚህ የሚሰጠው መልስ ደግሞ ከምናስበው በላይ አስደናቂ ነው።
ከልብ-ወለድ ወደ ህክምና ሳይንስ
ይህ ወሬ የብዙዎችን ቀልብ የሳበውን ታዋቂ የልብ-ወለድ ታሪክ ያስታውሳል።

እ.ኤ.አ. በ1922 አሜሪካዊው ጸሐፊ ፊትዝጀራልድ ( F. Scott Fitzgerald) የቤንጃሚን በተን አጓጒ ታሪክ( "The Curious Case of Benjamin Button") የተሰኘውን አጭር ልብ-ወለድ አሳተመ። በታሪኩ ውስጥ ቤንጃሚን በተን ሲወለድ የ80 ዓመት አዛውንት ቁመና ነበረው። በታሪኩ መሰረት ፤ ቤንጃሚን ከ እርጅና፣ ወደ ጉልምስና፣ ከጉልምስና ወደ ወጣትነት፤ ከወጣትነት ወደ ልጅነት እድሜውን ሲገፋ ይታያል። በመጨረሻም የጨቅላ ሰውነት ይዞ ያርፋል። ይህ ታሪክ በኋላ በተመሳሳይ ወደ ፊልምነት ተቀይሮ ፤ ታዋቂው አርቲስት ብራድ ፒት ሊተውንበት ችሏል። ከላይ የሚታየውም ምስል ከ ፊልሙ የተቀነጨበ ነው።
ግን ይህ እውነታ አይደለም። ፍጹም ልብ-ወለድ ነው። በእውነተኛው ዓለም ሰዎች ከአዛውንትነት ወደ ጨቅላነት አይመለሱም። ሆኖም የህክምና ሳይንስ አንዳንድ ጊዜ አስደናቂ ሁኔታዎች ያጋጥሙታል።
ታድያ ህጻን እድሜው የገፋ መልክ ሊኖረው ይችላልን?
አጭሩ መልስ "አዎ! ሊኖረው ይችላል።" ነው።
ሆኖም ግን በጽሑፉ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው፤ አልያም በዚህ ምስል እንደሚታየውም አይደለም።

በነባራዊ አለም ሲያጋጥም ፤ ብዙ ጊዜ የሚታየው ይህን ይመስላል።

ነገር ግን ይህ “በማህጸን ውስጥ ማርጀት” ማለት አይደለም። በአብዛኛው ጊዜ ይህን ገጽታ የሚፈጠረው በቆዳ፣ በሰውነት ስብ ወይም በዘረመል ላይ በሚያጋጥሙ የጤና እክሎች የተነሳ ነው። እነዚህ እክሎች እጅግ አናሳ ናቸው። አንዳንዶቹ በዓለም ዙሪያ በጥቂት ቤተሰቦች ላይ ብቻ የሚታዩ ናቸው።
የአዛውንት ገጽታ ሊፈጥሩ የሚችሉ ዋና የጤና እክሎች፦

ኒዮናታል ፕሮጄሮይድ ሲንድሮም (Neonatal Progeroid Syndrome): በዚህ እክል የተጠቁ ህጻናት ከቆዳቸው በታች ያለው የስብ መጠን በጣም አነስተኛ ነው። ለዚህም የፊት አጥንቶቻቸው ጎልተው ስለሚታዩ እና ቆዳቸው የላላ እና የተሸበሸበ ስለሚሆን የአዛውንት ገጽታ ይኖራቸዋል። ይህ ሁኔታ በዘረመል ለውጦች የሚከሰት ነው።

ኩቲስ ላክሳ (Cutis Laxa): ይህ በሽታ ቆዳ የመለጠጥ ባህሪውን እንዲያጣ ያደርገዋል። ለዚህም ቆዳው ስለሚንጠለጠል ፤ አብዝቶ ይሸበሽባል። ይህም ህጻኑን ከእድሜው በላይ ያረጀ እንዲመስል ያደርገዋል። ይህ አንዳንድ ህጻናት ላይ የቆዳ ችግር ብቻ ሲሆን፣ ለሌሎች ግን በሳንባ፣ በልብ ወይም በምግብ መፈጨት ሥርዓት ላይ ተጨማሪ ችግሮች ያመጣል።

ኮንጄኒታል ጄኔራላይዝድ ሊፖዲስትሮፊ (Congenital Generalized Lipodystrophy): ይህ እክል ኖሮባቸው የሚወለዱ ህጻናት፤ በሰውነታቸው ውስጥ እጅግ አነስተኛ ወይም ምንም ስብ አይኖራቸውም። ስለዚህ የፊት አጥንቶቻቸው እና ጡንቻዎቻቸው ጎልተው ይታያሉ። ከገጽታው በተጨማሪ ለስኳር በሽታ፣ ለኢንሱሊን መቋቋም እና ለጉበት ችግሮች ስለሚያጋልጥ፤ የዕድሜ ልክ ክትትል ያስፈልጋል።

ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናት (Severe Prematurity): እየተሸበሸበ ቆዳ ያለው እያንዳንዱ ህጻን ብርቅዬ የዘረመል እክል አለበት ማለት አይደለም። ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናት ም፤ ከቆዳቸው በታች በቂ ስብ ስላልተከማቸ ቆዳቸው ቀጭን እና የተሸበሸበ ሊመስል ይችላል። ይህ ገጽታ ግን ህጻኑ እያደገ ሲሄድ በአብዛኛው ጊዜ በተፈጥሮ ይስተካከላል።
ታድያ በኢትዮጵያው የተፈጠረው ክስተት ምንድነው?
እስከ አሁን ያለው በጣም ታማኝ የህክምና መልስ ይህ ነው። "እውነቱን አናውቅም።"
እስካሁን ድረስ የህጻኑን ገጽታ የሚያብራራ ይፋዊ የህክምና ሪፖርት፤ ከተወለደበት ሆስፒታል የተሰጠ መግለጫ ወይም የተረጋገጠ የምርመራ ውጤት አልቀረበም። ስለዚህ ህጻኑ ምን ዓይነት የጤና እክል እንዳለበት፤ ወይም ምንም ችግር እንዳልነበረው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

ምስሉ ለምን ጥያቄ ያስነሳል?
በምስሉ ላይ ትኩረት የሚስበው የተሸበሸበ ቆዳ ሳይሆን የአዋቂ ሰው የሚመስል የፊት ጺም መኖሩ ነው። ይህ ከህክምና አንጻር ከእውነታ የራቀ ያስመስለዋል። እንደዚህ አይነት ጺም ለማደግ በጉርምስና ጊዜ የሚያጋጥም ሆርሞን ያስፈልጋል። ከዚህም ባሻገር ህጻን ልጅ ይዞት የሚወለደው ጸግሩ ለስላሳ የጸጉር አይነት ሲሆን፤ በህክምናው ላኑጎ (Lanugo) ይሰኛል። እንጂ እንደ አዋቂ ሰው የተስተካከለ የፊት ጺም አይኖረውም።
ከላይ የተጠቀሱት ብርቅዬ የጤና እክሎች እንዲህ ያለ የጺም አቀማመጥ አያሳዩም። እንኳን ከመጠን በላይ የጸጉር እድገት (Hypertrichosis) የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም፤ እነርሱም በሙሉ ሰውነት የተሰራጨ ጸጉር ይኖራችቸዋል። ለዚህም በዋቢነት ከታች በሚታየው ምስል ያለችውን ሴት ህጻን መመልከት ይችላሉ። ይህች ህጻን በቅጽል ስሙ ዌርዎልፍ ሲንድረም የሚባል፤ አለልክ ጸግሩ የማደግ ተፈጥሮአዊ ችግር አለባት።

ስለዚህ በማህበራዊ ድህረገጽ የተሰራጨው ምስል እና ታሪክ ትኩረትን ለመሳብ የተደረገ ፤ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተቀነባበረ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው።
ተጨማሪ ማስረጃ
ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ከመሰራጨቱ በፊት ፤ ይሄው ምስል በሌሎች ሀገራትም እንዳጋጠመ ተደርጎ መዘገቡን ፤ አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ የለቀቀችውን መመልከት ይችላሉ።
ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን?
ይህ ክስተት አንድ አስፈላጊ ትምህርት ይሰጠናል። የጤና መረጃዎችን ከማጋራታችን በፊት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ያልተረጋገጡ የህክምና ወሬዎች ፍርሃት፣ ግራ መጋባት ከመፍጠራቸውም ባሻገር፤ በተመሳሳይ የጤና እክል ውስጥ ያሉ ቤተሰቦችን ለማህበራዊ መገለል (Stigma) ሊዳርጉ ይችላሉ።




Comments