top of page

የልጅዎ ጭንቅላት ከመጠን በላይ እያደገ ነው? ችላ አይበሉት!

15 hours ago
3 min read

አንድ ሕፃን ከተለመደው በላይ ትልቅ ጭንቅላት ሲኖረው፤ ብዙ ወላጆች ይህ የልጁ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንደሆነ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ በጊዜ ሂደት ይስተካከላል ብለው ሊጠብቁ ይችላሉ።


ነገር ግን የሕፃኑ ጭንቅላት መጠን በፍጥነት እየጨመረ ከሆነ፤ ከዚህ ጀርባ አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልገው የጤና ችግር ሊኖር ይችላል።


ይህ ችግር ምንድን ነው? ሌሎች ምን ምልክቶች አሉት? እንዴትስ ይታከማል?


ሃይድሮሴፋለስ (Hydrocephalus) ምንድን ነው?

ሃይድሮሴፋለስ በአንጎል ውስጥ ከመጠን በላይ ፈሳሽ በመከማቸቱ የሚከሰት የጤና ችግር ነው። በቀላሉ ለማስረዳት፤ አንጎላችን የራሱ የፈሳሽ ዝውውር ሥርዓት አለው።


ይህ ፈሳሽ ሴሬብሮስፓይናል ፍሉድ (Cerebrospinal fluid — CSF) ይባላል። ይህ ፈሳሽ አንጎልን አንሳፎ በውስጡ ይይዛል። አንጎልንና ህብለ-ሰረሰርን ከግጭት ለመጠበቅ፤ ንጥረ ነገሮችን ለማጓጓዝ እና ቆሻሻ ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድ ይረዳል።


ይህ ፈሳሽ ያለማቋረጥ ይመረታል፤ ይዘዋወራል፤ ከዚያም ወደ ደም ዝውውር ይመለሳል። የፈሳሹ ዝውውር ወይም መመጠጥ ሲዛባ፤ በአንጎል ውስጥ ሊከማችና ክፍተቶቹን ሊያሰፋ ይችላል። ይህም የአንጎል ክፍተቶችን በማስፋት በአንጎል ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል።


ይህ ሃይድሮሴፋለስ ይሰኛል።


በሕፃናት ላይ ምን ምልክቶች ይታያሉ?

ይህ ግፊት ገና ጨቅላ በሆኑ ህጻናት ላይ የጭንቅላቶቻቸው አጥንቶች ገና ስላልገጠሙ ፤ የጭንቅላት መጠን ከልክ በላይ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ለዚህም ልጅዎ ላይ የሚከተሉትን ምልክቶች ይጠንቀቁ፦

🔹 የጭንቅላት መጠን በፍጥነት መጨመር፤

🔹 የእርግብግቢት መወጠር፤

🔹 ዓይኖች ወደ ታች ማማተር፤

🔹 ማስታወክ፤

🔹 ጡት ወይም ምግብ በደንብ አለመቀበል፤

🔹 ከመጠን በላይ መነጫነጭ ወይም እንቅልፍ መብዛት፤

🔹 የእድገት መዘግየት ወይም የሚጥል በሽታ ምልክቶች።


ከእነዚህ ምልክቶች ውስጥ አንዱ መኖሩ ብቻ ሃይድሮሴፋለስ እንዳለ አያረጋግጥም። ነገር ግን በተለይ የጭንቅላት መጠን በፍጥነት ከጨመረ፤ ሕፃኑን ያለማዘግየት ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ፤ አስፈላጊው ምርምራ እንዲደረግ አድርጉ።


በትልልቅ ሕፃናትና በአዋቂዎችስ?

ሃይድሮሴፋለስ በሕፃናት ብቻ አይከሰትም። በኋለኛው የሕይወት ዘመንም ሊከሰት ይችላል። በዚህ ጊዜ የጭንቅላት መጠን በግልጽ ሁኔታ አይጨምርም፤ ምክንያቱም የጭንቅላት አጥንቶች በቋሚነት ተደፍነዋል። ለዚህም የሚታዩት ምልክቶች ይለያሉ። ለዚህም

🔹 በተለይ ጠዋት የሚበረታ የራስ ምታት፣

🔹 ማቅለሽለሽና ማስታወክ፣

🔹 የዓይን ብዥታ /ሁለት ነገር እንደሚታይ መሰማት፣

🔹 የመራመድ ችግርና ሚዛን ማጣት፣

🔹 የማስታወስ ችሎታ መቀነስ ወይም ግራ መጋባት፣

🔹 ሽንትን መቆጣጠር መቸገር፤ ሊያስተውሉ ይችላሉ።


በተለይም አዛውንቶች ላይ የመራመድ ችግር፣ የሽንት መቆጣጠር ችግርና የአስተሳሰብ ወይም የማስታወስ ለውጥ ቀስ በቀስ ሊታዩ ይችላሉ። በእነርሱም የሚታየው መደበኛ ግፊት ያለው ሃይድሮሴፋለስ (Normal Pressure Hydrocephalus) ይሰኛል። ይህ ሁኔታ በአንዳንድ ታካሚዎች ላይ በሕክምና ሊሻሻል ይችላል።


❓ ሃይድሮሴፋለስ ለምን ይከሰታል?

ሃይድሮሴፋለስን የሚያመጡ የተለያዩ መንስኤዎቹ ናቸው።

  • ከወሊድ ጋር የተያያዙ ችግሮች፦ ጽንስ በማህጸን ውስጥ እያለ በአንጎል እድገት ወቅት የሚከሰቱ መዋቅራዊ ችግሮች ምክንያት ሊመጣ ይችላል።

  • የፈሳሽ መንገድ መዘጋት፦ በአንጎል ውስጥ ያሉ የፈሳሽ መተላለፊያዎች ሲዘጉም በሽታው ይስተዋላል።

  • ኢንፌክሽን፦ እንደ ማጅራት ደግፍ (Meningitis) ያሉ በአንጎልና በሽፋኑ ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችም ሊያመጡች ይችላሉ።

  • የጭንቅላት ጉዳት ወይም የደም መፍሰስ፦ በአንጎል ውስጥ ያለውን ተፈጥሮአዊ የፈሳሽ ዝውውርን ሊያውኩ ይችላሉ።

  • የአንጎል እጢ፦ በአንዳንድ ሁኔታዎች የአንጎል ውስጥ እጢም፤ የፈሳሽ መንገድን ሲዘጋ ችግሩ ሊከሰት ይችላል።

በብዙ ሁኔታዎች ግን ትክክለኛው መንስኤ ላይታወቅ ይችላል።


እንዴት ይመረመራል?

የጤና ባለሙያ ጋር ሲሄዱ፤ ሐኪሙ አካላዊ ምርመራ ካደረገ በኋላ፤ አጥንቱ ያልደፈነ ጨቅላ ላይ እንደ ሁኔታውም የአንጎል አልትራሳውንድ ሊታዘዝ ይችላል። በአዋቂዎች እና ትልልቅ ህጻናት ላይ ሲቲ ስካን ወይም ኤም አር አይ ሊያዝልዎ ይችላል።


 ሕክምናውስ ምንድን ነው?


የሕክምና አማራጮቹ እንደ መንስኤውና እንደ ታካሚው ሁኔታ ይለያያሉ። ብዙ ጊዜ ቀዶ ጥገና ያስፈልጋል።


ከተለመዱት የሕክምና ዘዴዎች አንዱ ሸንት (Shunt) የተባለ ቀጭን ቱቦ በመጠቀም ትርፍ ፈሳሹን ከአንጎል ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል(ብዙውን ጊዜ ወደ ሆድ ዕቃ)፤ እንዲፈስ ማድረግ ነው።


ሕክምናው በጊዜው ካልተደረገ ግን፤ በአንጎል ላይ የሚደርሰው ጫና ዘላቂ የአእምሮ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።



መከላከያ መንገዶች አሉትን?

ሃይድሮሴፋለስን በሁሉም ሁኔታዎች መከላከል አይቻልም። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በማህፀን ውስጥ በሚከሰቱ የአንጎል እድገት ችግሮች ሊመጣ ይችላል። ሆኖም አንዳንድ መንስኤዎችንና የጉዳት አደጋዎችን መቀነስ ይቻላል።


  1. በእርግዝና ወቅት የቅድመ ወሊድ ክትትል ያድርጉ። እርግዝና እንዳለ ከታወቀ ጀምሮ የጤና ባለሙያን በማማከር በየጊዜው የቅድመ ወሊድ ክትትል ያድርጉ። ፎሊክ አሲድ (Folic acid) በተመከረው መጠን መውሰድም አንዳንድ የአንጎልና የአከርካሪ እድገት ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል። ይህ ግን ሁሉንም የሃይድሮሴፋለስ ዓይነቶች አይከላከልም።


  2. ኢንፌክሽኖችን ችላ አይበሉ። እንደ ማጅራት ገትር ያሉ አንዳንድ ኢንፌክሽኖች ሃይድሮሴፋለስን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህንን ለመከላከላ ልጅዎን ክትባት በስርአት ያስከትቡ። ከባድ ሕመም ወይም የማጅራት ገትር ምልክቶች ሲታዩም ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ።


  1. ጭንቅላትን ከጉዳት ይጠብቁ። ልጆችን ከመውደቅ ይጠብቁ። ጥንቃቄ ያድርጉ።


  1. የልጅዎን የጭንቅላት እድገት ይከታተሉ። በተለይም በጨቅላ ሕፃናት የጭንቅላት ዙሪያ መጠን በመደበኛ የጤና ክትትል ወቅት መለካት አስፈላጊ ነው። የጭንቅላት መጠን በፍጥነት እየጨመረ ከሆነ፤ እርግብግቢቱ ካበጠ/ከተወጠረ ወይም ሌሎች አሳሳቢ ምልክቶች ከታዩ፤ ምርመራ ለማድረግ ወደ ጤና ተቋም ይውሰዱት።


ምን ማድረግ አለብዎት?

የልጅዎ ጭንቅላት መጠን በፍጥነት እየጨመረ ከሆነ፤ ወይም ከተለመደው በላይ ትልቅ ከሆነ፤ በጤና ባለሙያ ያስመርምሩት። በተለይ ማስታወክ፣ ከመጠን በላይ እንቅልፍ፣ የሚጥል በሽታ ወይም የንቃተ ህሊና ለውጥ ካለ፣ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ይውሰዱት።


በተመሳሳይ፣ በአዋቂ ሰው ላይ ድንገተኛና ከባድ የራስ ምታት፣ ተደጋጋሚ ማስታወክ፣ የንቃተ ህሊና መቀየር ወይም የሚጥል በሽታ ከታየ፣ አስቸኳይ ሕክምና ያግኙ።


ያስታውሱ!

 የልጅ ጭንቅላት ትልቅ መሆኑ ብቻ ሃይድሮሴፋለስ አለ ማለት አይደለም። ነገር ግን የጭንቅላት መጠን በፍጥነት መጨመር ሊታለፍ የማይገባው ምልክት ነው። ቀድሞ መመርመርና ተገቢውን ሕክምና ማግኘት የአንጎልን ጉዳት ለመከላከል ወሳኝ ነው።




Comments


bottom of page