top of page

የማጅራት ገትር ህመም ምልክቶች እና መከላከያዎቹ 


ለመሆኑ ስለ ማጅራት ገትር ምን ያህል ያውቃሉ?


ለምንስ ማጅራት ገትር ተባለ?


ብዙውን ጊዜ በህጻናት የሚታወቅ ህመም ቢሆንም ፤ ሁሉንም የእድሜ ክልል እንደሚያጠቃ ያውቃሉ?


📍 ማጅራት ገትር ምንድን ነው?


ማጅራት ገትር በእንግሊዘኛ ስሙ ሜኒንጃይተስ(meningitis) ሲባል ፤ በአንጎልና በአከርካሪ ዙሪያ ያሉ ጠባቂ ሽፋኖች ወይንም ልባሶች(meninges) ፤ በተለያዩ በሽታ አምጪ ተህዋሶች ሲጠቁ የሚያጋጥም ኢንፌክሽን ነው። ይህም ኢንፌክሽን በባክቴሪያ፣ በቫይረስ፣ በፈንገስ፣ አልፎ ተርፎም ጥገኛ ተውሳኮች ምክንያት ሊመጣ ይችላል።

ከሁሉም ግን በአደገኝነቱ በባክቴሪያ የሚመጣው ይብሳል። ይህ በሽታ ከደረጀ በሰዓታት ውስጥ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል። ከበሽታው የተረፉት ሰዎችም ዘላቂ የአካል ጉዳት ሊኖርባቸው ይችላል።

በሽታውን የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም የሕመም  ምልክቶቹን  መለየት  ይኖርብዎታል።-

ዋነኛ ምልክቶቹ

  • ትኩሳት

  • ከባድ ራስ ምታት

  • የአንገት ግትርነት/ ማጅራት መገተር

  • ግራ መጋባት ወይም እንቅልፍ ማጣት ወይም እንቅልፍ ማብዛት

  • በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ የህመም ምልክቶች ስውር ሊሆኑ ይችላሉ።

 

📍 የማጅራት ገትር በኢትዮጵያ


ኢትዮጵያ የማጅራት ገትር ሕመም ከተንሰራፋባቸው ሀገራት መሀል ትጠቀሳላች። ለዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የማጅራት ገትር ሰንሰለት አገራት ውስጥ ትገኛለች። ይህም ሰንሰለት ከሴኔጋል ጀምሮ የተዘረጋ ሲሆን ፤ የማጅራት ገትር ወረርሽኝ በብዛት ያጋጥምበታል። ወረርሽኙ በብዛት የሚስፋፋው በደረቅ ወራት (ከ ታህሳስ እስከ ሰኔ) ባሉት ነው። አቧራ ፣ ነፋስና የተጣበበ መኖሪያ ለኢንፌክሽኑ ስርጭት ተስማሚ እድልን ይፈጥራሉ።

የማጅራት ገትር ሰንሰለት (በቀይ ያሉት ወረርሽኙ የተስፋፋባቸው ሀገራት ሲሆኑ ፤ ኢትዮጵያም ተካታለች)
የማጅራት ገትር ሰንሰለት (በቀይ ያሉት ወረርሽኙ የተስፋፋባቸው ሀገራት ሲሆኑ ፤ ኢትዮጵያም ተካታለች)

ከዛሬ 3 አመት በፊት (እ.ኤ.አ በ2022 መጀመሪያ ላይ) የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ ወረርሽኝ መከሰቱን ዘግቦ ነበር። በዚህም ጊዜ


  • በኢትዮጵያ 11 ክልሎች የተጠረጠሩ 1,398 ታማሚዎች ሲገኙ

  • 13 ሰዎች መሞታቸው ተረጋገጧል

  • ወረርሽኙ በኦሮሚያ፣ ሶማሊና ደቡብ ክልል በይበልጥ ተስፋፍቶ ነበር።


ይህ ብቸኛው ወረርሽኝ አልነበረም። በየጥቂት ዓመታት ደጋግሞ ፈጽሞ አለመጥፋቱን የሚያሳይ ወረርሽኝ ይከሰታል።


ምንም እንኳን በብዛት  ወረርሽኝ  የሚያመጣው ሴሮ ግሩፕ ኤ የተባለው የሚኒንጆኮከስ (serogroup A meningococcus ) ባክቴሪያ ዝርያ ነው። ሆኖም ግን በቅርብ አመታት ሴሮ ግሩፕ ሲ( C), ደብሊው( W), እና ኤክስ (X) የሚባሉት ዝርያዎች በብዛት ወረርሽኝ እያመጡ ይገኛሉ።


ከሚያጋጥሙ ተላላፊ በሽታዎች አንጻር ፤ የማጅራት ገትር ህመም መጠን አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ፤ በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በበሽታው ይያዛሉ።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፤ በኢትዮጵያ ስርጭቱ ከወቅት እና ከመልክአምድራዊ ሁኔታ ጋር ይያዛል። ለምሳሌ ስርጭቱ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል በ ታህሳስ ወር ሲያይል ፤ በኦሮሚያና በ ሲደማ በህዳር ወር ያይላል። በአፋር ፣ በደቡብ ክልል እና ትግራይ ደግሞ ፤ ወደ ሰኔ አከባቢ ስርጭቱ ይጨምራል።


 የልጆች ብቻ ህመም አይደለም ም። ሁሉንም እድሜ ክልል ያጠቃል። 


👶በሽታው የሚበረታባቸው ልጆች 


የማጅራት ገትር ህመም በብዛት በህጻናት ነው የሚታወቀው። ለማጅራት ገትር ህመም ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በከፍተኛ  የተጋለጡ ናቸው ። በሽታ የመከላከል አቅማቸው በደንብ ጎልብቶ አልጨረሰም። በትምህርት ቤቶች በተለይም በተጨናነቁ ክፍሎች ውስጥ የማጅራት ገትር የሚያመጡ ባክቴሪያዎች በቀላሉ ይሰራጫሉ።


ከሁለት አመት በፊት(እ.ኤ.አ 2023) በጥበበ ጊዮን፣ በደብረ ታቦር ፣ እና በደብረ ማርቆስ ኮምፕሪኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው ፡ 


  • 85.8% ማጅራት ገትር የነበራቸው ህጻናት ትኩሳት ነበራቸው

  • 71.2% የአንገት ወይም ማጅራት ግትርነት ነበረባቸው

  • ከ4 ልጆች መሀል በአማካይ አንዱ ሞቷል አልያም ሆስፒታል ለረዥም ጊዜ ቆይቷል።


ብዙ ጊዜ ወላጆች የልጆች ህመም በቀናት ውስጥ ሊባባስ እንደሚችል አይገነዘቡም። ህመሙ ፈጽሞ ጊዜ አይሰጥም። በቀናት ውስጥ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።


👨 🦱 ችላ የሚባሉት ጎልማሶች

የማጅራት ገትር ህመም በአዋቂዎች ዘንድ እምብዛም አይነሳም። ጎልማሶች የበሽታ የመከላከል አቅማቸው የተሻለ በመሆኑ ፤ ተጋላጭነታቸው ይቀንሳል። ተጋላጭነታቸው ቢያንስም በማጅራት ገትር ይጠቃሉ። በእነርሱም ዘንድ የማጅራት ገትር ህመም መጠን እየጨመረ ይገኛል።


በጎንደር ዩንቨርስቲ ሆስፒታልም የተደረገ የ 10 ዓመት ዳሰሳ ጥናት(2011- 2020)  ይህንን ጠቁሟል። ጥናቱ እንደሚያሳየው ፡

  

  • ከታከሙ 3,683 አዋቂዎች መካከል 1.3 ፐርሰንቱ በባክቴሪያ ምክንያት የመጣ የማጅራት ገትር አሳይተዋል።

  • ብዙ ታማሚዎች ከተለመዱት ትኩሳት እና ማጅራት ገትር ምልክት ይልቅ ፤ ለየት ያሉ እንደ ግራ መጋባት አይነት ምልክቶችን አሳይተዋል።  

  • ከህጻናት አንጻር አዋቂዎች ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ያመነታሉ። ህመሙንም እንደ ጉንፋን አድርገው ፤ እስኪብስ ቸል ሊሉት ይችላሉ።


ታድያ ይህ ዋጋ ያስከፍላል።  እያንዳንዷ ሰአት ትርጉም አላት።  


👴 የሚረሱ ሰለባዎች  አዛውንቶች


በዕድሜ የገፉ ሰዎች የበሽታ የመከላከል አቅማቸው እየተዳከመ ስለሚመጣ ፤ የማጅራት ገትር የመያዝ እድላቸው የሰፋ ነው። የህመሙም ዳፋ በእነርሱ ያይላል። እድሜያቸው ከ 65 ዓመት በላይ ከሆኑ የማጅራት ገትር ካለባቸው አዛውንቶች ውስጥ እሰከ 30 በመቶ የሚሆኑት ፤ በህመሙ የተነሳ ሊሞቱ ይችላሉ።


እዚህ ጋር አሳሳቢው ጉዳይ፤ በአዛውንቶች ላይ ህመሙን መለየት ሊከብድ ይችላል። አዛውንቶች የተለመዱትን የትኩሳት እና የአንገት መገተር ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። በእነኝህ ምልክቶች ፈንታ አንደበታቸው ሊንተባተብ ፣ ግራ ሊጋቡ ፣ የማስታወስ ችግር ሊያሳዩ ፣ ንቃት ሊቀንሱ ይችላሉ።


አዛውንቶች የሌላ ሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ስለሚሆኑ ፤ ለተንከባካቢያቸው እነኝህን ምልክቶች ከእርጅና ይልቅ በ ኢንፌክሽን ህመም የመጡ መሆናቸውን ላይረዳ ይችላል።


ይህም የሚንከባከባቸው ሰው በቀላሉ ህመሞቹን ለይቶ ፤ ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል።


በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ድግሞ የህክምናው ተደራሽነት ውስን በመሆኑ ፤ ጤና ተቋም በሚደርሱበት ጊዜ ዘግይተው ሊሆን ይችላል።

ሆኖም ግን በጊዜ ከተገኘ እና አስፈላጊ ህክምና ከተደረገ ፤ ህመሙ ጉዳት ሳያደርስ ሊድን ይችላል።


🧪 አስፈላጊው ህክምና

ይህ በሽታ ከተጠረጠረ ለማረጋገጥ ፤ ከደም ምርመራ ባሻገር ከአከርካሪ አጥንት የሚወሰድ የፈሳሽ ምርመራ ያስፈልጋል። ይህም በሽታ አምጪ ተህዋሱ መኖሩን ሊያመላክት ይችላል። ነገር ግን ህክምናው ይህ ምርመራ እስኪደርስ አይጠበቅም። ለታካሚ የሚሰጠውም የፀረ ተህዋስ መድሐኒት ፤ እንደተጠረጠረው ህመም አምጪ ተህዋስ በመጠኑ ሊለያይ ይችላል።


ታድያ ይህ ህክምና በጊዜ ካልተደረገ ፤ በሽታው እስከ ሞት ሊያደርስ ይቻላል። እንደ አንዳንድ ጥናቶች ከሆነ ከታመሙት መሀከል ከ 20 እስከ 30 ፐርሰንት የሚሆኑት ሊሞቱ ይችላሉ።


በሕይወት የተረፉት ሰዎች እራሱ ፤ ቋሚ ጉዳት ሊኖርባቸው ይችላል። ሞቱም ሆነ ዘላቂ ጉዳቱ እድሜያቸው በገፋ ታማሚዎች ላይ ያይላል።

በእነኝህ ታካሚዎች ላይ ቋሚ የመስማት ችግር ፣ የማሰብ ችሎታ መዛባት ፣ የእንቅስቃሴ እና የመናገር እክልም ሊያጋጥማቸው ይችላል።


🛡️እንዴት እንከላከለው?

  • በክትባት መከላከል ይቻላል። ኢትዮጵያ ላይ በታየው ዋነኛ ባክቴሪያ የሆነ የሴሮ ግሩፕ ኤን የሚከላከለው ክትባት በመሰጠቱ፤ አመርቂ ውጤት ታይቷል። ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ፤ በሌሎች ዝርያዎች የሚመጣው ወረርሽኝ እያየለ መጥቷል። ለዚህም እነኝን ተደራሽ የሚያደርጉ ክትባቶች መሰጠት ይኖባቸዋል። በዚህም ዙሪያ እየተሰራ ይገኛል።


  • እንደ ግለሰብ እና እንደ ማህበረሰብ ስለ በሽታው እና ምልክቶቹ የተሟላ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። ለዚህም ማንኛውም ታማሚ ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ካሳየ ፤ በ48 ሰዓታት ውስጥ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ማገዝ አለብን


  • ጸረ ተህዋሳት (አንቲባዮቲክ) የለመዱ ተህዋሳት የማጅራት ገትር እያመጡ እንደሆነ ፤ታማሚዎችም ላይ የከፉ ጉዳት እያመጡ መሆኑን የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ። የምንወስደውንም አንቲባዮቲክ ፤ በህክምና ባለሙያ የታዘዘ ብቻ መሆን አለበት።


⚠️ ለማጠቃልያ እነኝህን ምልክቶች ያስተውሉ

ምልክት

ልጆች

አዋቂዎች

በዕድሜ የገፉ ሰዎች

ከፍተኛ ትኩሳት

🔄 አንዳንዴ

የአንገት ግትርነት

🔄 እምብዛም አይታይም

ማስመለስ

🔄 እምብዛም አይታይም

ግራ መጋባት

መንዘፍዘፍ

🔄 አንዳንዴ

🔄 አንዳንዴ

ብርሀን አለመቻል/ መመጥላት

🔄 እምብዛም አይታይም

 

🛑 እርሶም ሆነ በዙሪያዎ ያሉ ሰዎች እነኝህን ምልክቶች ካሳዩ ፤ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል መሄድ ይኖርባቸዋል።

ያስተውሉ


ማጅራት ገትር በፍጥነት የሚገድል ከመሆኑም በላይ ፤ ዘላቂ ጉዳት ያስከትላል።

 

ሁሉንም የ እድሜ ክልል ቢያጠቃም ፤ የበሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ አዛውንቶች እና ህጻናቶች ላይ ያይላል።

 

መከተብ ፣ የተሟላ ግንዛቤ መኖር ፣ እንዲሁም ቀደም ብሎ የሆስፒታል ምርመራ ማድረግ እጅጉን ጠቃሚ ነው።


በሽታው እስኪደረጅ አንጠብቅ። መከላከል ይቻላል። እርሱም አሁኑኑ እርምጃ የምንወስድ ከሆነ ብቻ ነው ።

Comments


bottom of page