ስለ ጭንቅላት ዕጢ ማወቅ ያለብዎ!
- Zebeaman Tibebu
- 19 hours ago
- 4 min read
ለመሆኑ ስለጭንቅላት ዕጢ ሰምተዋልን? ምንድነው የሰሙት?
በዚህ ሕመም የተጠቃ የቅርብ ሰው ያውቃሉ? ውጤቱስ እንዴት ሆነ? «ምናለ ቀድሞ ባወቀው!» ብለውስ ተቆጭተው ያውቃሉ?
የጭንቅላት ዕጢ በአለማችን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ እጅግ አሳሳቢ በሽታ ነው። ዕድሜ፣ ጾታ ወይም ዘር ሳይመርጥ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ወንዶችንና ሴቶችን ያጠቃል። ብዙዎች በጊዜ ባለመድረሳቸው ምክንያት የኋሊት የሚቆጩበት፤ ሕይወት በከንቱ የሚቀጠፍ አስፈሪ በሽታ ነው።

ጭንቅላት ውስጥ ያለ ዕጢ አደገኛ ለመሆን የግድ ካንሰር መሆን አያስፈልገውም!
እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ እንጠይቅ...
ሌላ የሰውነት ክፍል ላይ ችላ የምንለው ተራ ዕጢ፤ ጭንቅላት ውስጥ ሲሆን ለምን እንዲህ አሳሳቢ ጉዳይ ሆነ? ዛሬ ስለ የጭንቅላት ውስጥ ዕጢ በጥልቀት እናነሳለን።
በመጀመሪያ፦ የጭንቅላት ዕጢ ምንድን ነው?

የጭንቅላት ዕጢ ማለት በአንጎል ውስጥ አልያም በአንጎል ዙሪያ ያሉ ህዋሳት አለመጠን ሲያድጉ የሚፈጠር፤ ያልተለመደ እድገት ነው። ይህ የካንሰር ባህሪ ሊያሳይም ላያሳይም ይችላል። የጭንቅላት ዕጢ እንደመሰረቱ ሊለያይ ይችላል። አንጎል ውስጥ ባሉ ህዋሳት አለልክ ማደግ አልያም ሌላ አከባቢ ያለ ካንሰር ወደ አንጎል በመሰራጨት ሊከሰቱ ይችላሉ።
ሆኖም ግን እዚህ ጋር ለአፍታ ቆም ብለው ያስተውሉ..
ሁሉም የጭንቅላት ዕጢዎች ካንሰር አይደሉም።
ነገር ግን “ካንሰር አይደለም” ማለት “ምንም አደጋ የለውም” ማለት ፈጽሞ አይደለም። ይህንን ምስጢር ለመረዳት የራስ ቅላችንን የተፈጥሮ አወቃቀር በሚገባ ማወቅ አለብን።

የራስ ቅላችንን ውኃ ሙሉ በሙሉ ተሞልቶ እንደተዘጋ የሃይላንድ ላስቲክ አድርገው ያስቡት። ይህ ሃይላንድ መያዝ የሚችለውን ልክ ይዟል። ውስጡ ፍጹም የተሞላ በመሆኑ፤ አንድም ተጨማሪ ነገር ሊያስተናግድ አይችልም።
ጭንቅላታችንም ልክ እንደዚህ ሃይላንድ ነው። በራስ ቅላችን ውስጥ አንጎል፣ የደም ሥሮች፣ ነርቮች እና ፈሳሾች ተለክተው ተቀምጠዋል። ምንም ትርፍ ቦታ የለም!
በዚህ በውኃ የተሞላ ሃይላንድ ውስጥ ሌላ ተጨማሪ ነገር ለመጨመር ብንሞክር ምን የሚፈጠር ይመስልዎታል? ውኃው ይፈሳል፣ ወይም ላስቲኩ ሊፈነዳ ይደርሳል።
በበአንጎል ውስጥም የሚሆነው ልክ ይህ ነው። ዕጢ—ማደግ ሲጀምር፤ የራስቅላችን ሊለጠጥ ስለማይችል ውስጡ ያለው ግፊት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ይህ ግፊት ደግሞ አጠገብ ያሉ አካላትን በመጉዳት፤ ዘላቂ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር፤ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። ስለዚህ ጭንቅላት ውስጥ ያለ ዕጢ፤ ካንሰር ሳይሆን እራሱ ከባድ የሆነ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
ምናለ ቀድሜ ባወቅኩት የሚሏቸው ምልክቶች
ራስ ቅላችን ውስጥ ግፊቱ መጨመር ሲጀምር፤ ሰውነታችን አደጋ ላይ መሆኑን የሚነግሩን የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል። ከእነዚህም ውስጥ ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፦

አዲስ የሆነ ወይም እየተባባሰ የሚሄድ ራስ ምታት
አዎ! ራስ ምታት ለብዙ ህመሞች በጣም የተለመደ ምልክት ነው። አብዛኛው ራስ ምታትም የጭንቅላት ዕጢ ምክንያት አይደለም። የራስ ምታት አሳስቢ የሚሆነው የሚከተሉትን ባህሪያት ካሳየ ነው፦
ከዚህ በፊት ያልነበረ አዲስ የራስ ምታት ከሆነ፤
ቀስ በቀስ እየባሰ የሚሄድ ከሆነ፤
ከዚህ በፊት ከሚያምዎት/ከለመዱት ራስ ምታት በጣም የተለየ ከሆነ፤
እንዲሁም ከሌሎች ምልክቶች ጋር (ማስታወክ፣ ማንቀጥቀጥ፣ ድካም፣ የእይታ ለውጥ ወይም ሌሎች የነርቭ ለውጦች) አብሮ ከታየ፤
የራስ ምታቱ ሊያሳስብዎ ይገባል።

የሚጥል በሽታ / ማንቀጥቀጥ
አንዳንድ ጊዜ የጭንቅላት ዕጢ የመጀመሪያው ግልጽ ምልክት የሚጥል በሽታ ሊሆን ይችላል። አንጎል ውስጥ ያለው ዕጢ የአንጎልን መደበኛ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ሊያውክ ስለሚችል ፤ የማንቀጥቀጥ በሽታ ሊያስከትል ይችላል።
ለዚህም በአዋቂ ሰው ላይ ከዚህ በፊት ያልነበረ ማንቀጥቀጥ ከተከሰተ፤ የጤና ባለሙያን ማምከር ያስፈልጋል።

የእይታ ለውጥ
ከአንጎል ዕጢ ጋር ተያይዞ አንድ ሰው፤ ዓይኑ ሊደበዝዝ፣ ሁለት ምስል ሊያይ፣ የተወሰነ እይታውን ሊያጣ፣ አልያም ሌላ ያልተለመደ የእይታ ለውጥ ሊያስተውል ይችላል።
የንግግር ችግር
በፊት ጤነኛ የነበረ ግለሰብ፤ ቃላት ሊጠፉበት፣ በትክክል ለመናገር ሊቸገር፣ የሌሎችን ንግግር ለመረዳት ሊቸገር፣ አልያም ማንበብ/መጻፍ ሊያስቸግረው ይችላል።
እዚህ ጋር ያስተውሉ! በድንገት የሚከሰት የንግግር ችግር በአንጎል ዕጢ ብቻ አይመጣም። ስትሮክም እንዲህ ያለ ምልክት ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም ወዲያውኑ አቅራቢያዎ ወዳለ የጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።

የእጅ ወይም የእግር ድካም
የጭንቅላት ዕጢ ያጋጠመው፤ የእጅ እና እግር እንቅስቃሴን በሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ላይ ከሆነ፤ ተያያዥነት ያለው የሰውነት ክፍል (እጅ/እግር) ሊደክም ወይም ስሜቱ ሊለወጥ ይችላል።
ይህም ምልክት ከስትሮክ ጋር ሊያያዝ ስለሚችል፤ አስቸኳይ ሕክምና ያስፈልጋል።
የሚዛን እና የመራመድ ችግር
አንድ ጤነኛ ሰው ሚዛን መጠበቅ ሊሳነው፣ በቀላሉ አብዝቶ ሊደናቀፍ አልያም መራመድ ሊቸገር ይችላል። በተለይም ዕጢው የሚዛንንና የእንቅስቃሴ ቅንጅትን በሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ከሆነ ይህ ሊታይ ይችላል።

7. ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
ራስ ውስጥ ግፊት ከጨመረ ማቅለሽለሽና ማስታወክ ሊከሰት ይችላል። አንዳንድ ሰዎች በተለይ ጠዋት ጠዋት አዘውትረው ሊያቅለሸልሻቸው አልያም ሊያስመልሳቸው ይችላል።
የባህሪ፣ የማስታወስ ወይም የአስተሳሰብ ለውጥ
አንዳንድ ጊዜ የጭንቅላት ዕጢ የሚያሳየው የመጀመሪያ ምልክት፤ በባህሪ ላይ የሚታይ ለውጥ ሊሆን ይችላል። የታማሚው ቤተሰቦችም በቀላሉ መርሳት እና ትኩረት ማድረግ መቸገር፣ ያልተለመደ የባህሪ መለወጥ (ያልተለመደ ቁጣ ወይም ግዴለሽነት ማሳየት)፣ እና ውሳኔ መስጠት መቸገርን ልያስተውሉ ይችላሉ።
ይህም ዕጢው የማስታወስ፣ የአስተሳሰብ ወይም የባህሪ ቁጥጥር ጋር የተያያዙ የአንጎል ክፍሎችን ሲያጠቃ ሊከሰት ይችላል።

እዚህ ጋ ግን ያስተውሉ!
እነኝህን ምልክቶች በሰውነትዎ ላይ አዩ ማለት፤ በእርግጠኝነት የአእምሮ ዕጢ አለ ማለት አይደለም። ስትሮክን ጨምሮ የተለያዩ የውስጥ ደዌ ሕመሞች እነኝህን ምልክቶች በተመሳሳይ ሁኔታ ሊያሳዩ ይችላሉ። ተደናግጦና ተጨንቆ ቤት ውስጥ መቀመጥ ፍርሀትን እንጂ መፍትሔን አይወልድም።
ዋናውና ትልቁ ነገር! እነዚህን አጠራጣሪ ምልክቶች ሲያዩ ጊዜ ሳይሰጡና ሳይጠብቁ፤ ፈጥነው በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን የሕክምና ምርመራ ማድረግ ነው።
ምርመራዎቹ ምንድናቸው?

የጭንቅላት ዕጢ ሲጠረጠር፤ ለማረጋገጥ የጤና ባለሙያው የሚከተሉትን ምርመራዎች ሊያደርግልዎ ይችላል።
አካላዊ የነርቭ ምርመራ ፦ በነገሩት ታሪክ ላይ ተመስርቶ ሐኪሙ የጡንቻዎን ጉልበት፣ የቆዳዎን ስሜት፣ የእጅና እግርዎን ፈጣን ምላሽ (reflex)፣ ሚዛን መጠበቅ መቻልዎን፣ የዓይን እንቅስቃሴዎትን እና ማስታወስ መቻልዎትን ለማየት አካላዊ ምርመራ ያደርጋል። ይህ ምርመራም ችግሩ በአንጎል የትኛው ክፍል ላይ እንዳለ ፍንጭ ይሰጣል።
የምስል ምርመራ፦ የራስ ቅልና አንጎልን ለመመልከት ሐኪምዎ ኤክስ ሬይ፣ ሲት ስካን፣ ወይም ኤም አር አይ ምርመራዎችን፤ ባገኘው የአካላዊ ምርመራ ተመስርቶ ሊያዝልዎ ይችላል። እነኝህም የምስል ምርመራዎች ዕጢው የት እንዳለ፣ መጠኑን እና በዙሪያው ያሉትን አካላት በግልጽ ያመላክታሉ።
የናሙና ምርመራ፦ የምስል ምርመራ ዕጢ መኖሩን ከጠቆመ፤ ዶክተርዎ እንደአስፈላጊነቱ የናሙና ምርመራ ሊያዝልዎ ይችላል። ይህም ምርመራ ዕጢው በትክክል ምን ዓይነት እንደሆነ ያረጋግጣል። ነገር ግን ሁልጊዜ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል።
የጭንቅላት ዕጢ ከተገኘ ሕክምናው ምንድን ነው?

በራስ ቅል ውስጥ ለሚገኝ ዕጢ «አንድ ዓይነት ሕክምና» የሚባል ነገር የለም! ህክምናው በዕጢው ዓይነት፣ ደረጃ፣ ቦታ፣ መጠን፣ ፍጥነት፣ በታካሚው ዕድሜና አጠቃላይ ጤና ላይ ይወሰናል።
ዕጢው በደኅና ሊወገድ የሚችል ከሆነ ቀዶ ጥገና ሊደረግ ይችላል። ዕጢው ወሳኝ የአንጎል ተግባራትን (ንግግር፣ እይታ) ከሚቆጣጠሩ ክፍሎች አጠገብ ከሆነ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አደገኛ ሊሆን ይችላል። የዕጢ ህዋሳትን ለማዳከም እና ለመግደል የጨረር እና የኬሞቴራፕ ህክምና ሊያስፈልግ ይችላል። ይህ የሚወሰነው በዕጢው ተፈጥሮአዊ ባህሪ ላይ ተወስኖ ነው።
በተመረጡ አንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ክትትል ብቻ ሊደረግ ይችላል።
አንዳንድ ትንንሽ፣ ቀስ ብለው የሚያድጉ፣ እና ከባድ ምልክት የማያስከትሉ ዕጢዎች በመደበኛ ክትትልና ተደጋጋሚ ኤም አር አይ ምርመራ ሊደረግላቸው ይችላል። ይህም የሚደረገው ዕጢው እያደገ ከመጣ በጊዜ ሕክምና ለመጀመር ፤ በጥንቃቄ ለመከታተል ነው።
ታዲያ ምን ያስታውሱ?
እያንዳንዱን ራስ ምታት መፍራት አያስፈልግም። ምልክቶቹን ሲያስተውሉ ችላ ማለትም አይገባም።
ምልክቱ አዲስ ከሆነ፣ እየተባባሰ ከሄደ፣ ምክንያቱ ካልታወቀ ወይም ከሌሎች የነርቭ ምልክቶች ጋር ከተያያዘ፤ አቅራቢያዎ ወዳለ የጤና ተቋም ይሂዱ።
የጭንቅላት ዕጢ ከተጠረጠረም፤ ወዲያውኑ “ካንሰር ነው” ብሎ አይደምድሙ።
ካንሰር አለመሆኑም ፤ ሊያዘናጋዎ አይገባም! ሐኪምዎን ያማክሩ




Comments