top of page

ካንሰር የሚያመጣው ቫይረስ! ብዙዎች የማያውቁት ስለ የማህጸን ጫፍ ካንሰር እውነታ

4 minutes ago
4 min read
ለመሆኑ የማህጸን ጫፍ ካንሰር (Cervical Cancer) ከቫይረስ ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ያውቃሉ?

የማህጸን ጫፍ ካንሰር (Cervical Cancer) ከሌሎች ካንሰሮች በተለየ መልኩ ዋነኛ መንስኤው ቫይረስ ነው። ቫይረሱ በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንዶችም ላይ ይገኛል።


አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት ምልክት ስለማያሳይ ብዙ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም። ደስ የሚለው ነገር በአብዛኛው ጊዜ የሰውነታችን የተፈጥሮ የመከላከያ አቅም ቫይረሱን በራሱ ያስወግደዋል። ነገር ግን በአንዳንድ ሰዎች ላይ ቫይረሱ ለረዥም ጊዜ ሲቆይ ሕዋሳትን በመለወጥ ወደ ካንሰር ሊያመራ ይችላል።


ይህ ቫይረስ Human Papillomavirus (HPV) ይባላል።

ታዲያ HPV ምንድነው? እንዴት ይተላለፋል? ሁሉም HPV ካንሰር ያመጣል? ከዚህ አደጋ ራሳችንንና ልጆቻችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን? እነዚህን አስፈላጊ ጥያቄዎች እንመልስ።


HPV ምንድነው? ሁሉም ካንሰር ያመጣልን?


HPV ወይም Human Papillomavirus ከ200 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችን የሚያካትት ትልቅ የቫይረስ ቤተሰብ ነው። እነዚህ ቫይረሶች ቆዳን፣ የብልት አካባቢን እና የጉሮሮ አካባቢን ጨምሮ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ሊያጠቁ ይችላሉ። ይህ ቫይረስ በግንኙነት ወቅት በሚኖር አካላዊ ንክኪ ሊተላለፍ ይችላል።


ቫይረሱን በአጠቃላይ በሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ከፍሎ ማየት ይቻላል፦

  1. ዝቅተኛ የካንሰር አደጋ ያላቸው (Low-risk HPV):

እነዚህ የቫይረስ ዓይነቶች በብዛት በብልት አካባቢ የሚወጡ ትናንሽ እብጠቶች ወይም ኪንታሮቶች (Genital Warts) ያስከትላሉ።


  1. ከፍተኛ የካንሰር አደጋ ያላቸው (High-risk HPV):

እነዚህ ደግሞ በሰውነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ ከቆዩ የሕዋሳትን መደበኛ እድገት በማዛባት ወደ ካንሰር ሊያመሩ ይችላሉ። ከእነዚህ መካከል በተለይ HPV 16 እና HPV 18 ዝርያዎች ብቻ ወደ 70% የማህጸን ጫፍ ካንሰርን ያስከትላሉ።


አስፈላጊ መረጃ ፦ የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከሚያጋጥማቸው ሴቶች መካከል ከ95% በላይ የሚሆነው ከእነኝህ አደገኛ የባይረስ ዝርያዎች ጋር ይገናኛል።


HPV ከያዘ በኋላ ምን ይፈጠራል? እያንዳንዱ ኢንፌክሽን ወደ ካንሰር ይቀየራል?

ሁሉም HPV የያዘው ሰው ካንሰር ይይዘዋል ማለት አይደለም። ሂደቱ በሦስት ደረጃ ሊታይ ይችላል፦

  1. በራሱ ይወገዳል፦ በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መረጃ መሠረት 90% የሚሆኑ ሰዎች በ1 ወይም በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ቫይረሱን በራሳቸው የሰውነት መከላከያ ያስወግዱታል።


  2. ለረዥም ጊዜ ይቆያል፦ በቀሪዎቹ 10% ሰዎች ላይ ቫይረሱ ሳይወገድ ለዓመታት ይቆያል።


  3. ወደ ካንሰር ይሸጋገራል፦ ለረዥም ጊዜ የቆየው ቫይረስ በማህጸን ጫፍ ሕዋሳት ላይ "ቅድመ-ካንሰር ለውጥ" ይፈጥራል። ይህ ለውጥ ካልታከመ ወደ ካንሰር ያድጋል።


ይህ ሂደት በአንድ ጀምበር አይከሰትም!

የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከHPV ኢንፌክሽን በኋላ ለመፈጠር ከ15–20 ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ነገር ግን የሰውነት የመከላከያ አቅም በተዳከመባቸው ሁኔታዎች፦ ለምሳሌ በኤች.አይ.ቪ (HIV) ኢንፌክሽን ያለባቸውና ሕክምና በቂ ያላገኙ ሰዎች ላይ ይህ ሂደት ከ5–10 ዓመታት በአጭር ጊዜ ሊከሰት ይችላል።



HPV ምን ዓይነት ካንሰሮችን ያስከትላል?

ብዙዎች HPV የሚያመጣው የማህጸን ጫፍ ካንሰርን ብቻ እንደሆነ ያስባሉ። ይህ ግን ከእውነታው የራቀ ነው ። ይህ ቫይረስ የሚከተሉት ካንሰሮችንም ያስከትላል፦


  • የማህጸን ጫፍ ካንሰር (Cervical Cancer)

  • የሴት ብልት ካንሰሮች (Vaginal Cancer & Vulvar Cancer)

  • የወንድ ብልት ካንሰር (Penile Cancer)

  • የፊንጢጣ ካንሰር (Anal Cancer)

  • የአፍና የጉሮሮ አካባቢ ካንሰሮች (Oropharyngeal Cancers)


በተለይም የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከHPV ጋር በጣም ጠንካራ የሆነ ግንኙነት አለው።


HPV ምልክት ያሳያል?

እዚህ ላይ አንድ አስገራሚ እውነታ አለ።

HPV በአብዛኛው ጊዜ ምንም ዓይነት ምልክት አያሳይም!

በቅድመ-ካንሰር ደረጃ ያሉ ለውጦችም ብዙውን ጊዜ ምልክት አያሳዩም። ስለዚህ ሴቶች ምንም ሕመም ባይሰማቸውም መደበኛ የማህጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ (Cervical Cancer Screening) ማድረግ አስፈላጊ ነው።


ካንሰሩ ግን ደርጅቶ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሲሸጋገር ግን የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፦


  • ከወር አበባ ውጭ፣ ከጾታዊ ግንኙነት በኋላ ወይም ከማረጥ (Menopause) በኋላ የሚከሰት ደም መፍሰስ፣

  • ያልተለመደ ወይም መጥፎ ሽታ ያለው የሴት ብልት ፈሳሽ፣

  • በዳሌ አካባቢ የሚሰማ ሕመምና፣

  • በጾታዊ ግንኙነት ወቅት ሕመም።


እነዚህ ምልክቶች በሌሎች በሽታዎችም ሊከሰቱ ይችላሉ። ለዚህም በራስዎ ላይ ካንሰር እንዳለ መደምደም የለብዎትም። ነገር ግን  ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።

ቀድሞ ለማወቅ ምን ማድረግ ይቻላል?

የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከመፈጠሩ በፊት የሚከሰቱ የሕዋሳት ለውጦችን ቀድሞ ማወቅና ማከም ይቻላል። ይህንን ለማድረግ የተለያዩ የምርመራ ዘዴዎች ሊኖሩ ይችላሉ።


  1. የፓፕ ስሚር ምርመራ Pap Smear (Pap Test) ፡ በማህጸን ስፔሻሊስት የማህጸን ምርመራ ከተደረገልዎ በኋላ፤ የማህጸን ጫፍ ናሙና ተወስዶ፤ ባህሪያቸው የተቀየሩ ሕዋሳት መኖራቸው በማይክሮስክፕ ይታያል።

  2. VIA (Visual Inspection with Acetic Acid)፦ ይህ ደግሞ የጤና ባለሙያው የአሴቲክ አሲድ ፈሳሽን ተጠቅሞ የባህሪ ለውጥ ያለባቸውን አከባቢዎች ይመለከታል።

  3. የዘረመል (HPV DNA) ምርመራ፦ ይህ በማህጸን ጫፍ ናሙና ውስጥ ከፍተኛ የካንሰር አደጋ ያላቸው የHPV ዓይነቶች ይመረምራል።

መቼ መመርመር ይገባል?

WHO በአጠቃላይ ሴቶች ከ30 ዓመት ጀምሮ በየ5–10 ዓመቱ ከፍተኛ የምርመራ አቅም ባለው ዘዴ እንዲመረመሩ ይመክራል።

በHIV ኢንፌክሽን የሚኖሩ ሴቶች ግን ከ25 ዓመት ጀምሮ በየ3–5 ዓመቱ እንዲመረመሩ ይመከራል።


ሴቶች የHPV ክትባት ቢወስዱም የማህጸን ጫፍ ምርመራ ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው።


የማህጸን ካንሰር ክትባት

ከሁሉም በላይ አስደሳቹ ዜና መከላከል መቻላችን ነው!

ክትባቱ ግን የሚከላከለው ለማህጸን ጫፍ ካንሰር መንስኤ የሆነውን ቫይረሱን መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ይህ ክትባት የሚከተሉትን ጥቅሞች አሉት፦

  • ከከፍተኛ የካንሰር አደጋ ያላቸው የHPV ዓይነቶች ኢንፌክሽን ይከላከላል።

  • የማህጸን ጫፍ ቅድመ-ካንሰር ለውጦችን ይቀንሳል።

  • ከHPV ጋር የተያያዙ ሌሎች ካንሰሮችንም ለመከላከል ይረዳል።

ክትባቱ ለማን ይሰጣል?

WHO በዋናነት ከ9–14 ዓመት ዕድሜ ላይ ላሉ ሴት ልጆች ጾታዊ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት ክትባቱን እንዲወስዱ ይመክራል።


ለምን?

ምክንያቱም ክትባቱ ለቫይረሱ ከመጋለጣቸው በፊት ሲሰጥ ውጤታማነቱ ይጨምራል።


የHPV ክትባት በተለያዩ አገራት እንደ ብሔራዊ የክትባት ፕሮግራም አንድ ወይም ሁለት ዶዝ ሊሰጥ ይችላል። የመከላከያ አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች፣ በተለይም በHIV የሚኖሩ ሰዎች፣ ተጨማሪ ዶዝ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።


በኢትዮጵያ የHPV ክትባት በመደበኛ የክትባት ፕሮግራም በ9 ዓመት ዕድሜ ለሚገኙ ሴት ልጆች ይሰጣል። በተጨማሪም በ2024 ከ9–14 ዓመት ዕድሜ ላይ ላሉ ሴት ልጆች ሰፊ የክትባት ዘመቻ ተካሂዷል።


ያስተውሉ!

ክትባቱን የወሰዱ ሴቶችም የማህጸን ጫፍ ምርመራቸውን መቀጠል አለባቸው።


እንዴት እንከላከል?

ክትባትና ቅድመ ምርመራ ከሁሉም በላይ ወሳኝ ቢሆኑም ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎችም አሉ።

  1. ኮንዶም ይጠቀሙ፦በግንኙነት ጊዜ ኮንዶም የቫይረሱ የመተላለፍ እድልን ይቀንሳል። ግን በኮንዶም ያልተሸፈኑ አከባቢዎች ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ ሙሉ በሙሉ አይከላከልም።

  2. ሲጋራ አያጭሱ፦ ሲጋራ ማጨስ የHPV ኢንፌክሽን በቀጣይነት የመቆየትና ወደ ካንሰር የመሸጋገር አደጋን ያሳድጋል።

  3. የHIV ምርመራ ያድርጉ። ከተገኘብዎ አስፈላጊውን ሕክምና ያድርጉ፦ የሰውነት መከላከያ አቅም መዳከም የቫይረሱ ኢንፌክሽን ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ እና ወደ ካንሰር እንዲሸጋገር ሊያግዝ ይችላል።


ወላጆች ማወቅ ያለባቸው እውነታ!

የማህጸን ጫፍ ካንሰርን ከመታከሙ በፊት መከላከል እንችላለን! ሴት ልጆቻችሁ ከ9–14 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሆኑ ዛሬውኑ በአቅራቢያችሁ ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ በመሄድ ስለ HPV ክትባት ይጠይቁ።


ይህ ዛሬ የምትወስዱት እርምጃ ነገ ከከባድ የጤና ችግር ሊጠብቃቸው ይችላል።


ካንሰርን ከመታከሙ በፊት መከላከል እንችላለን!

Comments


bottom of page