አደገኛው የጉበት ቫይረስ ፡ ሔፓታይተስ ቢ
- Zebeaman Tibebu
- Jun 2
- 3 min read

ይህ አዲስ አበባ ውስጥ ያለ አንድ ቤተሰብ ታሪክ ነው።
አባት ደጋግመው 'ቀኝ ሆዴ አሞኛል' ማለት ሲያበዙ፤ ልጆች ሀሳብ ገብቷቸው የጤና ተቋም ይዘዋቸው ይሄዳሉ። ምርመራም ሲደረግ ፤ የህመማቸው ምንጭ የጉበት ጠባሳ እንዲሁም የጉብት ካንሰር እንደሆነ ይነገራቸዋል። ይህን ጊዜ ልጆች እጅጉን ይደናገጣሉ። አባታቸው ጤነኛ እንደሆኑ ነበር የሚያውቁት። ታድያ የተደናገጡት ልጆችም እርግጠኛ ለመሆን የጉበት ስፔሻሊስት ጋር ይዘዋቸው ይሄዳሉ። ስፔሻሊስቷም ካንሰሩ የደረጀ መሆኑን እንዲሁም (Hepatocellular carcinoma BCLC stage C) ፤ ደማቸው ውስጥ የሄፕታይተስ ቢ የጉበት ቫይረስ እንደሚገኝ አስረድታቸው ፤ ህክምና ክትትል ይጀምራሉ።
ጉዳዩ ዱብዳ የሆነባቸው ልጆች ፤ አባታቸው መዳን የሚችልበትን መንገድ ለማወቅ ውጭ እስካሉ የህክምና ባለሙያዎች ድረስ ይሄዳሉ። ሆኖም ግን ካንሰሩ መጋቢ የደም ስርን ስለነካ ፤ ያለው የህክምና አማራጭ የተገደበ መሆኑንና ፤ ዋናው ህክምና የእገዛ ህክምና (palliative care) መሆኑን ያስረግጡላቸዋል።
ታድይ ይህ ዜና ቀላል አልነበረም። ያላቸውን ቅሪት ሸጠው ሆነ ፤ የስው ፊት አይተው ፤ አንድ አባታቸውን ለማሳከም የወሰኑት ልጆች ፤ ተስፋቸው ሟጨጨ። የሚያደርጉት ግራ ገባቸው። የእገዛ ህክምና ብቻ እንደ መፍትሔነት አልዋጥ ቢላቸውም ፤ ህክምና ክትትላቸውን አጥብቀው ቀጠሉ።
ባላቸው አቅም አባታቸውን ለማስታመም ቢሞክሩም ፤ እኝህ አባት ከቀን ወደ ቀን እየተዳከሙ መጡ። ምግብ አልበላ አላቸው። ከበሉም ምግብ ሆዳቸው አይረጋም። ሰውነታቸው እየመነመነ መጣ። ታድያ ድንገት አንድ ቀን በአፋቸው በኩል ደም ገንፍሎ መጣ ። ድንገተኛ ክፍል ይዘዋቸው ቢሄዱም ፤ ህይወታቸውን ግን ማዳን አልተቻለም ።
ይህ የአንድ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ቁንጽል ታሪክ ቢሆን ፤ እንዴት መልካም ነበር። የአንጀት እና ጉበት ክትትል ክፍል ለሳምንት ቢያሳልፉ ፤ ብዙ ተመሳሳይ ታሪኮችን ይሰማሉ።
ዛሬ የምናነሳው ስለ ካንሰር አይደለም። ካንሰር በማምጣታቸው ከሚታወቁ ቫይረሶች መሀከል ዋነኛ ተጠቃሽ ስለሆነው ፤ ሁሉንም የሰውነታችንን ክፍል ስለሚያጠቃው ፤ ሄፓታይተስ ቢ ስለሚባለው የጉበት ቫይረስ ነው። ይህ ቫይረስ ከ ኤች አይቪ ኤድስ ጋር ተመሳሳይነት ቢኖረውም ፤ በአንዳንድ ባህሪው ከ ኤች አይ ቪ ኤድስ ይብሳል። መልካሙ ነገር ግን ክትባት አለው።
ሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ በኢትዮጵያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህ የጉበት ቫይረስ ስርጭታቸው ከፍተኛ ከሆኑ ሀገራት ውስጥ ትመደባለች። ቫይረሱ ከ 8 እስከ 12 ፐርሰንት የማህበረሰቡን ክፍል እንደሚያጠቃ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ማለት በትንሹ አስር ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ይህ የጉበት ቫይረስ አለባቸው። ባብዛኞቹ የተያዙት በህጻንነት እድሜያቸው ቫይረሱ ካለበት የቤተሰብ አባል መሆኑ ፤ አሳዛኝ ያደርገዋል። ለዚህም የጎልማሳ እድሜ ላይ ሲደርሱ ፤ ቫይረሱ ከባድ የጉበት ጥቃት ያደርሳል።
ቫይረሱ የጉበት ጠባሳ (cirrhosis) ለማምጣት እስከ 20 አመት ፤ እንዲሁም የጉበት ካንሰር (hepatocellular carcinoma (HCC) ) ለማምጣት እሰክ 30 አመት የሚፈጅበት ቢሆንም ፤ ብዙ ታካሚዎች ሲመረመሩ ጉበታቸው የከፋ ጉዳት ደረጃ ደርሶበት ይገኛል። ቀድሞ የህክምና ምርመራ ተደርጎ ቢሆን ፤ ጉበት ጠንካራ ጉዳት ሳይደርስበት መቆጣጠር ይቻል ነበር።
እኝህ ባለታሪክ አባት ከአመታት በፊት ጉበታቸውን ተመርምረው ቢሆን ፤ የህይወታቸውን አቅጣጫ እንዴት መለወጥ ይቻል ነበር?
⚠️ የ ህመሙ ምልክቶች
ይህ ህመም ጉበት ላይ ጠንካራ ጉዳት እስኪያደርስ ድረስ ፤ ፈጽሞ ምልክት ላያሳይ ይችላል። በሽታው ሲጀምር የሚያሳያቸው ምልክቶች ፤ እንደ ተራ ኢንፌክሽን ችላ ተብለው ሊታለፉ ይችላሉ።

ህመሙ የጀመረ ሰሞን የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል።
ድካም
የምግብ ፍላጎት መቀነስ
ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ
ህመሙ ሲጀመር ጠንካራ ከሆነ የሚከተሉት ሊስተዋሉ ይችላሉ።
የሆድ ህመም
ሽንት መጥቆር
ቆዳ እና አይን ቢጫ መሆን
ለረዥም ጊዜ ቫይረሱ ሰውነታችን ውስጥ ቆይቶ ጉበታችንን ሲያቆስል ደግሞ ፤ እንደደረሰው የጉዳት መጠን የተለያዩ ተጨማሪ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ።
የሆድ እና የእግሮች እብጠት (እነኝህ ምልክቶች መታየት ሲጀምሩ ፤ በተለምዶ የወፍ በሽታ ተብሎ ይጠራል)
ምግብ ፍላጎት ፈጽሞ መጥፋት
ደም ማስታወክ
የሰገራ መንጣት
የባህሪ መለወጥ
ወደ ካንሰር ከተለወጠ ካንሰሩ እንደተሰራጨበት አካል ምልክቶቹ ይለያያል
ጉዳቱ ጠንካራ ከሆነ ጉበት እጅጉን ይደክማል ፣ ጭንቅላትን አጥቅቶ ባህሪ ይለውጣል፣ ኩላሊት ድካምም ሊያመጣ ይችላል።
⚠️ መተላለፊያ መንገዶቹ

የጉበት ቫይረስ በዋነኝነት የሚተላለፈው ፤ ከታመመ ሰው የወጣ የሰውነት ፈሳሽ ንክኪ ሲኖር ነው። ለዚህ የሚያጋልጡ ማንኛዎም አይነት ድርጊቶች ሆኑ ባህሪያት ፤ ለበሽታው የመጋለጥ እድልን ይጨምራሉ። እነኝህም፡
ከ አንድ በላይ ሰው ጋር የ ፍቅር ግንኙነት መኖር
ክታመመ ሰው ጋር ግብረ ስጋ ግንኝነት መኖር
ከታመመ ሰው ጋር ስለት ያላቸው እቃዎችን በመጋራት
በስርአቱ ያልተመረመረ ደምን መቀበል
በቀዶ ጥገና ወቅትም (ይህ ደግሞ በዋነኝነት ጤና ባለሙያዎችን ይመለከታል)
እናት ቫይረሱ ካለባት ፤ በወሊድ ጊዜ በሚኖር የደም እና የሰውነት ፈሳሽ ንክኪ ሊተላለፍ ይችላል።
ስቴራላይዝ ባልተደረጉ መገልገያዎች ድድን መነቀስ፣ ጆሮን መበሳትና ንቅሳት መነቀስ
አሳዛኙ እውነታ ! ብዙ የቫይረሱ ተጠቂዎች መሉ በሙሉ ጤናማ እንደሆኑ ስለሚሰማቸው ፤ ሳያውቁ ያሰራጫሉ ።
🛡️ መከላከያ መንገዶች
ክትባት
ቫይረሱን መከላከል የሚያስችል ክትባት አለው። ክትባት መውሰድ ይኖርብዎታል። እንደ ፈረንጆች ከ 2007 ዓ.ም ጀምሮ የጨቅላ ህጻናት ክትባት ጋር ተደባልቆ ስለሚሰጥ ተጋላጭነቱ ከፍተኛ የሆነው ከዛ በፊት ለተወለዱ ግለሰቦች ነው። ስለዚህም ልጅዎን ክትባት ያስከትቡ። እርስዎም ክትባት ከጀመሩ ፤ አንድ ክትባት ብቻ በቂ አይደለም። ሙሉ ክትባት ይውሰዱ።
ክትባቱን አሟልተው ከወሰዱ ፤ ከአስር አመት በኋላ የደም ምርመራ ያድርጉ። የቫይረሱ መከላከያ መጠን ከተመናመነ ፤ ማጠናከሪያ ክትባት መከተብ ይኖርቦታል።

ከክትባት ባሻገርስ
እላይ ከተጠቀሱት አደገኛ ባህሪያት እራስዎን ይጠብቁ።
በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶም ይጠቀሙ።
ስለት ያለው መገልገያ እቃ አይጋሩ።
ድድዎን ሲነቀሱ፣ ጆሮ ሲበሱ እንዲሁም ንቅሳት ሲነቀሱ ይጠንቀቁ። የሚነቀሱበት ስፍራ ህክምናዊ ጥንቃቄ (እቃዎቹን ስቴራላይዝ) እንደሚደርግ ያረጋግጡ ። ካልሆነ ለጤናዎ ቅድሚያ ይስጡ።
ቫይረሱ ያለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ከወሊድ በኋላ ባሉ 3 ቀናት ውስጥ ፤ ለልጆቻቸው የ ቫይረሱን መቃወምያ መሰጠት ይኖርባቸዋል።
ታመው እስኪሄድ አይጠብቁ። በመደብኛ ሁኔታ ጉበትዎን ይመርመሩ።
ስለቫይረሱ የተሟላ ግንዛቤ ይኑርዎ።
💊 ቫይረሱ ካለብዎስ ምን ያድርጉ?
በሕክምና ለቫይረሱ ፈውስ ባይኖረውም ፤ ቫይረሱን ተከትሎ የሚመጣ ጉዳትን መቆጣጠር ይቻላል። ስለዚህም ከጉበት ስፔሻሊስት ጋር ተነጋግረው ፤ የፀረ-ቫይረስ መድሐኒቶችን ይውሰዱ።
ምንም ቢሆን ቀድም ህክምና ለመጀመር አያመንቱ። ማመንታቶት ዋጋ ያስከፍልቶታል።
ወደሌላ ሰው እንዳያስተላልፉ ይጠንቀቁ። በተለይ የዚህ አንደኛ ተጠቂ ቤተሰብዎ ናቸውና ያስከትቧቸው።
የቅድሙ ባለታሪክ ልጆችስ እጣ ፈንታ ምን ይሆን? ተከትበው ይሆን!?
Berut leager teqami t/t new