በሕፃናት ላይ የሚከሰቱ የጉበት ቫይረሶች
- Zebeaman Tibebu
- 3 days ago
- 5 min read
"ሲጀምር ተራ የሆድ ሕመም ይመስል ነበር።"
የስምንት ዓመቱ ሳሚ ከትምህርት ቤት ሲመለስ ደክሞት ነበር። ሁልጊዜ ምግብ የማይጠላው ልጅ ያን ዕለት እራት አልበላም አለ። በማግስቱ ጠዋት ደግሞ መጠነኛ ትኩሳትና የማቅለሽለሽ ስሜት ታየበት። ሁለት ጊዜም አስመለሰው። ወላጆቹ የበላው ነገር አልተስማማውም በሚል ግምት ለህመሙ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ነገሩ ይበልጥ አሳሳቢ ሆነ። የሽንቱ ቀለም ሲጠቁር፤ የዓይኑ ነጭ ክፍል ደግሞ ወደ ቢጫነት ተቀየረ። ቤተሰቡ በከፍተኛ ፍርሃት ሳሚን ወደ ሆስፒታል ወሰዱት። ዶክተሮቹም ፈጣን ምርመራ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከሰት በቫይረስ የሚመጣ የጉበት መቆጣት (Acute Viral Hepatitis) እንዳለበት አረጋገጡ። ቤተሰቡ በድንጋጤ "የጉበት ቫይረስ በሕፃንነት?" ሲሉ ጠየቁ።
በአገራችን ብዙዎች የሚያውቁት ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ የተባሉትን የጉበት ቫይረስ ዓይነቶች ቢሆንም፤ እንደ ሳሚ ዓይነት ታሪኮች ግን የተለመዱ ናቸው። በየዓመቱ በርካታ ሕፃናት በጉበት ቫይረስ ይጠቃሉ። በተለይም ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ደካማ በሆነባቸው አካባቢዎች ሄፓታይተስ ኤ (Hepatitis A) እና ሄፓታይተስ ኢ (Hepatitis E) ዋነኛ የሕዝብ ጤና ስጋቶች ናቸው።
ስለ ቫይረሶቹ ባህሪ እና ተያይዞ ስለሚመጣው የጉበት ሕመም በጥልቀት እንወያይ።
የልጅዎ የሰውነት ጠባቂ ጉበት

በቀኝ በኩል ከጎድን አጥንት በታች የሚገኘው ጉበት፤ በሰውነታችን ውስጥ ካሉ እጅግ በጣም ሥራ ከሚበዛባቸው አካላት አንዱ ነው። ይህ ድንቅ አካል በቀን 24 ሰዓት ሙሉ ያለማቋረጥ:- ከደም ውስጥ መርዛማና ጎጂ ነገሮችን ያጣራል፤ ምግብ እንዲፈጭ የሚያግዘውን ሐሞት (Bile) ያመነጫል፤ የምንወስዳቸውን መድኃኒቶችና መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ይሰባብራል፤ ለሰውነት የሚያስፈልገውን ኃይል ያከማቻል፤ ደም እንዲረጋ የሚያደርጉ ፕሮቲኖችንም ያመርታል።
ታዲያ ቫይረሶች ይህንን ወሳኝ አካል ሲያጠቁት፤ ጉበት ሥራውን በአግባቡ መሥራት አቅቶት ይቆጣል። ይህ የጉበት መቆጣት ሄፓታይተስ (Hepatitis) የሚባለው ሲሆን፤ ለዚህ መከሰት ምክንያት ከሚሆኑት ቫይረሶች መካከል ሄፓታይተስ ኤ (HAV) እና ሄፓታይተስ ኢ (HEV) በሕፃንነት ጊዜ በጣም የተለመዱ ናቸው።
የቫይረሶቹ የመተላለፊያ መንገድ

ሄፓታይተስ ኤ እና ሄፓታይተስ ኢ በተለያዩ ቫይረሶች የሚመጡ ቢሆንም፤ የሚሰራጩበት መንገድ ግን አንድ ነው። እንደ ሄፓታይተስ ቢ (B) ወይም ሲ (C) በዋነኝነት በደም ወይም በሰውነት ፈሳሽ አይተላለፉም። እነኝህ ቫይረሶች በዋነኝነት በተበከለ ምግብና ውኃ የሚተላለፉ ሲሆን፤ ዶክተሮች ይህንን ከአይነምድር ጋር በሚኖር ንክኪ በአፍ በኩል ወደ ሰውነት የመግባት ሂደት (Fecal-Oral Route) ይሉታል።
ይህ ማለት በቀላል አነጋገር፤ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ሰገራ የሚወጡ በጣም ጥቃቅንና በዓይን የማይታዩ ቫይረሶች ውኃን፣ ምግብን ወይም እጅን ይበክላሉ። ሌላ ሰው ይህንን የተበከለ ነገር ሳያውቅ በአፉ ሲያስገባ ቫይረሱ በቀጥታ ወደ ሰውነቱ ይገባል።
ይህ አደጋ ያልተፈላ ውኃ በመጠጣት፣ ንጽህናው ባልተጠበቀ ሁኔታ የተዘጋጀ ምግብ በመመገብ፣ በቆሸሸ ውኃ የታጠቡ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመብላት፣ ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጅን በሳሙና በሚገባ ባለመታጠብ፣ እንዲሁም የደረቅ ቆሻሻና የሽንት ቤት አወጋገድ ሥርዓት ደካማ በሆነበት አካባቢ በመኖር በቀላሉ ሊከሰት ይችላል። ሕፃናት ደግሞ ውጭ መሬት ላይ መጫወት ስለሚወዱ፤ ምግብ ስለሚጋሩ፤ እጃቸውን መታጠብ ስለሚረሱ እና ስለ ንጽሕና ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ለዚህ ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ።
እነዚህ ኢንፌክሽኖች በኢትዮጵያ ለምን ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል?

ከኢትዮጵያ የሕዝብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በውኃ አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎች ለሕፃናት ወቅታዊ መታመም ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው። በተለይም በክረምት ወቅት በሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ወይም የንጹሕ ውኃ አቅርቦት መቆራረጥ በሚኖርበት ጊዜ በውኃ የሚተላለፉ በሽታዎች፤ ሄፓታይተስ ኤ እና ኢ ጨምሮ፤ የመሰራጨት ዕድላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። የጎርፍ ውኃ የፍሳሽ ማስወገጃዎችን በማጥለቅ ቆሻሻን በቀጥታ ወደ ግል ክፍት ጉድጓዶች፣ የሰፈር ጉድጓድ ውኃዎችና የከተማ የውኃ መስመሮች ውስጥ ያቀላቅላል።
ትምህርት ቤቶች፣ የተጨናነቁ መኖሪያ ቤቶች እና የንጽሕና አጠባበቅ ውስን የሆነባቸው ማኅበረሰቦች ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ ቫይረሱ በፍጥነት እንዲሰራጭ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ። ለዚህ ነው የውኃ ጥራትን ማሻሻልና የእጅ ንጽሕናን መጠበቅ የኢትዮጵያን ሕፃናት ለመጠበቅ ዋነኛው መፍትሔ የሚሆነው።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ አዲስ አበባ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ የከተማ አካባቢዎች አንድ ለየት ያለ ነገር ይስተዋላል።
የተሻለ ኑሮና ንጽሕና ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚያድጉ ሕፃናት በልጅነታቸው ከሄፓታይተስ ኤ ቫይረስ ጋር የመገናኘት ዕድላቸው ጠባብ ነው። እነዚህ ሕፃናት በልጅነታቸው ቫይረሱን ስላላገኙ በሰውነታቸው ውስጥ የቫይረሱ መከላከያ (Antibodies) ሳይገነባ ይቀራል። እነዚህ መከላከያ የሌላቸው ሕፃናት አድገው በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ወይም በወጣትነት ጊዜ ሄፓታይተስ ኤ ሲይዛቸው፤ የጎለመሰው የሰውነት መከላከል አቅማቸው ከባድ የሆነ የተቃውሞ ምላሽ ይሰጣል። በዚህም ምክንያት በትናንሽ ሕፃናት ላይ ከሚታየው ቀለል ያለ ሕመም በተለየ፤ በትላልቅ ልጆች ላይ ሕመሙ በጣም ይበረታል፤ ዓይናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይቢጫል፤ አልጋ ላይ ያውላል፤ እንዲሁም ለሆስፒታል መተኛት ይዳርጋል።የሕመሙ ምልክቶች

ስለ ሄፓታይተስ ኤ እና ሄፓታይተስ ኢ አስቸጋሪው ነገር ፤ ሕመሙ ሲጀምር ራሱን በግልጽ ለይቶ አለማሳወቁ ነው። የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ግራ የሚያጋቡና፤ ከሌሎች የትኩሳት ህመሞች ጋር በቀላሉ የሚመሳሰሉ ናቸው። በዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ አንድ ልጅ የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል፡-
መጠነኛ ትኩሳት
ከፍተኛ ድካምና መዛል
የምግብ ፍላጎት መቀነስ
የማቅለሽለሽ ስሜትና ማስመለስ
በሆድ ላይ መጠነኛ ህመም (በተለይ በስተቀኝ በኩል ከጎድን በታች)
ብዙ ወላጆች መጀመሪያ ላይ ልጃቸው "የምግብ መመረዝ" ወይም የሆድ ኢንፌክሽን የያዘው ይመስላቸዋል። ትክክለኛው የጉበት በሽታ ምልክት የሚታየው ከቆይታ በኋላ ነው።
ሰዎች ሁሉ የሚያስተውሉት የዓይን ቢጫ መሆን ዘግይቶ ይመጣል

አብዛኛው ሰው ከጉበት በሽታ ጋር የሚያያይዘው ዋና ምልክት ጃንዲስ (Jaundice) ወይም የዓይንና የቆዳ ቢጫ መሆን ነው።
ነገር ግን ቢጫ መሆን አብዛኛውን ጊዜ የመጀመሪያው ምልክት አይደለም።
የጉበት እየተቆጣ ሲሄድ፤ በሕፃናት ላይ የሚከተሉት ምልክቶች ይታያሉ፡-
የዓይን ነጭ ክፍልና የቆዳ ቢጫ መሆን
የሽንት ቀለም መጥቆር (እንደ ሻይ መልክ)
የሰገራ ቀለም መቅላት ወይም የሸክላ አፈር መምሰል
የማያቋርጥ ማቅለሽለሽ
ከፍተኛ የድካም ስሜት
ይሁን እንጂ አንዳንድ ትናንሽ ሕፃናት ምንም ዓይነት የዓይን ቢጫ መሆን ምልክት ሳያሳዩ ሊያገግሙ ይችላሉ። እንዲያውም በትናንሽ ልጆች ላይ የሄፓታይተስ ኤ ህመም በጣም ቀሊል ከመሆኑ የተነሳ፤ በሽታው መኖሩ ሳይታወቅ ሊድኑ ይችላሉ።
ሄፓታይተስ ኤ እና ሄፓታይተስ ኢ አደገኛ ናቸው?

ለአብዛኞቹ ጤናማ ሕፃናት በሽታው አሳሳቢ አይደለም። በእነዚህ ቫይረሶች ከሚመጡ ድንገተኛ (Acute) የኢንፌክሽን ዓይነቶችም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሙሉ በሙሉ ያገግማሉ።
እንደ ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ ሳይሆን፣ ሄፓታይተስ ኤ እና ኢ በሽታ የመከላከል አቅማቸው ጠንካራ በሆኑ ሕፃናት ላይ ስር አይሰዱም(Chronic) ። ቫይረሱ አንዴ ከተሸነፈ በኋላ በሰውነት ውስጥ ተደብቆም አይቆዩም። ጉበትንም ለዓመታት ቀስ በቀስ የመጉዳት አቅም የላቸውም። በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ ሕፃናት ያለምንም ዘላቂ የጉበት ጉዳት ሙሉ ጤንነታቸውን ይመልሳሉ።
ይሁን እንጂ ይህ መረጋጋት በሽታውን ሙሉ በሙሉ አቅልለን እንድንመለከት ሊያደርገን አይገባም።
አንዳንድ ሕፃናት በማስመለስና ምግብ መብላት በመተው ምክንያት ለከባድ የሰውነት ፈሳሽ ማጣት (Dehydration) ሊጋለጡ ይችላሉ። ይባስ ብሎም ሕመሙ ሲበረታ(ከስንት አንዴ ቢሆንም) በድንገተኝነት ጉበት ሥራ ሊያቆም (Acute Liver Failure) ይችላል። ይህም አስቸኳይ የሕክምና ክትትል የሚሻ የሕይወት አደጋ ነው።
ሁሉም ሰው ሊያውቀው የሚገባ የሄፓታይተስ ኢ ባህሪ

ምንም እንኳን ሄፓታይተስ ኢ በሕፃናት ላይ ቀለል ያለ ትኩሳትና ድካም ብቻ አስከትሎ ቢያልፍም፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ ሊያውቀው የሚገባ አንድ ድብቅና አደገኛ ባሕሪ አለው።
አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት በዚህ ቫይረስ ከተያዘች—በተለይም ከሦስት ወር እርግዝና በኋላ ( 2nd/3rd Trimester)፤ በሽታው የጉበትን መዋቅር በከፍተኛ ፍጥነት ሊያሰናክል ይችላል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መረጃ እንደሚያሳየው፤ በቫይረሱ ከተያዙ ነፍሰ ጡር እናቶች መካከል እስከ 25 በመቶ (ከ20% እስከ 25%) የሚደርሱት ለህልፈተ ሕይወት ሊዳረጉ ይችላሉ።
በመሆኑም ሄፓታይተስ ኢ እንዳይሰራጭ መከላከል ከሕጻናት ባሻገርል የነፍሰጡር እናቶችን እና ጽንሶቻቸውንም መታደግ ነው።
እንዴት ይመረመራል?

ዶክተሮች በመጀመሪያ ስለ ልጁ ምልክቶች፤ ከተበከለ ውሃ ወይም ምግብ ጋር ስለመገናኘቱ እና በአካባቢው ተመሳሳይ ወረርሽኝ መኖር አለመኖሩን ይጠይቃሉ። ይሁን እንጂ በሽታው መኖሩ ሙሉ በሙሉ የሚረጋገጠው በደም ምርመራ ብቻ ነው።
ተመሳሳይ ምልክት ከሚያመጡ በሽታዎች ለመለየት የቫይረሱ ምርመራ (Viral Serology or Antibody Tests) ይደረጋል። ጉበት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ የጉበት ኢንዛይሞች (Liver Function Tests) ምርመራ ይታዘዛል። ከዚህም ባሻገር የደም ሕዋሳት ምርመራም (Complete Blood Count) የሰውነት መቆጣትን ለማየት ሊታዘዝ ይችላል።
ሕክምናው ምንድን ነው?

ለሄፓታይተስ ኤ እና ኢ ቫይረሱን በቀጥታ የሚያጠፋ የተለየ የፀረ-ቫይረስ መድኃኒት ወይም አንቲባዮቲክ የለም።
ይልቁንም የሕክምናው ዋና ትኩረት የልጁ የመከላከል አቅም ቫይረሱን በራሱ ጊዜ አስወግዶ እስኪጨርስ ድረስ ድጋፍ ማድረግ (Supportive Care) ላይ ነው። ይህም የሰውነት ፈሳሽ እንዳይደርቅ በቂ ፈሳሽ መስጠትን፣ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብን፣ በቂ እረፍት መፍቀድን እና የሕመም ማስታገሻዎችን በጤና ባለሙያ ትዕዛዝ ብቻ መጠቀምን ያጠቃልላል።
በዚህ ወቅት ወላጆች ያለ ዶክተር ምክር ማንኛውንም መድኃኒት ወይም ባሕላዊ የዕፅዋት ውህዶችን ከመስጠት በጥብቅ መቆጠብ አለባቸው። ቀድሞውኑ የቆሰለና ያበጠ ጉበት በጣም ደካማ ስለሚሆን፤ መድሐኒትን ባህሪ ያላቸውን ነገሮች ጨምሮ መስጠት ፤ ጉበት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ሊያባብስ ይችላል። አልፎ ተርፎም ጉበት ሥራ እንዲያቆም ሊያደርግ ይችላል። አብዛኞቹ ሕፃናት ግን በዚህ ተገቢ እንክብካቤ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያገግማሉ።
ዋነኛው ህክምና መከላከል ነው!

አብዛኛውን የሄፓታይተስ ኤ እና ኢ ኢንፌክሽኖችን በቀላሉ መከላከል ይቻላል።
ቀላል የሚመስሉ የዕለት ተዕለት ልማዶች በልጆቻችን ጤና ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ። የቧንቧም ሆነ የኮንዶሚኒየም ውሃ ንጹህ ቢመስሉም፤ አስተማማኝ ላይሆኑ ስለሚችሉ ሁልጊዜም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
በሽታውን በልጅዎ ላይ እንዳያጋጥም ለመከላከል ፤ የሚከተሉትን ዋና ዋና መንገዶች መተግበር ይገባል፦
የመጠጥ ውሃን ማፍላት፦ ለመጠጥና ለምግብ ማዘጋጃነት የሚውል ውሃን ማፍላት፤ በውስጡ ያሉ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን ሙሉ በሙሉ ይገድላል።
እጅን በሳሙና መታጠብ፦ ልጆች ከመጸዳጃ ቤት ከተመለሱ በኋላ፤ እጃቸውን በሳሙናና በፈሳሽ ውሃ ቢያንስ ለ20 ሰከንድ በሚገባ እንዲታጠቡ ማድረግ።
ከምግብ በፊት መታጠብ፦ ልጆች ማንኛውንም ምግብ ከመንካታቸውና ከመመገባቸው በፊት፤ እጃቸውን የመታጠብ ልማድ እንዲያዘወትሩ ማስለመድ።
የምግብ ንጽሕናን መጠበቅ፦ ጥሬ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በንጹህ ውሃ በሚገባ ማጠብ፤ ከተቻለ ልጣጩን ማንሳት ወይም አብስሎ መመገብ።
የአካባቢ ንጽሕናን መጠበቅ፦ የሽንት ቤትና የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓትን ንጽሕና መጠበቅ፤ እንዲሁም የመጸዳጃ ጉድጓዶች ከውሃ ምንጮች የራቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ።
በትምህርት ቤት ጥንቃቄ ማድረግ፦ ልጆች በትምህርት ቤት የውሃ መጠጫዎችን እንዳይጋሩና የራሳቸውን መጠጫ እንዲይዙ ማስተማር።
ከእነዚህ የንጽሕና ልማዶች በተጨማሪ፤ በሕፃንነት ዕድሜ የሄፓታይተስ ኤ ክትባትን መውሰድ ወደፊት ከሚከሰተው በሽታ ዘላቂና አስተማማኝ ጥበቃን ይሰጣል።
ለልጅዎ ጤና ቦታ ይስጡ!
ልጅዎ በጉበት ቫይረስ ከመያዙ በፊት ዛሬውኑ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ ይውሰዱ። የሕመም ምልክቶቹን ካዩም ሳይዘገዩ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም ይዘው በመሄድ፤ የባለሙያ እገዛ ያግኙ።




Comments