top of page

አሳሳቢው የኮሌራ ወረርሽኝ

Updated: Mar 15

ለዘመናት ከሰው ልጅ ጋር የኖረው የኮሌራ ህመም በአሁኑ ጊዜም በአለም ላይ ብዙ ሰዎች እያጠቃ እንደሚገኝ ያውቃሉ?

በየአመቱ ክ1.3 እስከ 4 ሚሊየን ሰዎች በኮሌራ እንደሚጠቁ ፤ እንዲሁም ከ 21,000 እስከ 143,000 ሞት እንደሚያጋጥም መረጃዎች ያመላክታሉ። በያዝነውም አመትም በ አለም ዙሪያ  የኮሌራ ውረርሽኝ እያገረሽ ይገኛል። ባሳለፍነው የፈረንጆች ጥር ወር ውስጥ ብቻ በአለም ዙሪያ 34,799 ሰዎች በ ህመሙ የተጠቁ ሲሆን ፤ ከነኚህ ውስጥም 349 ሞተዋል።


ወረርሽኙ በአለም ዙሪያ መስፋፋቱ በአንድ በኩል ፤ በተፈጥሮ አደጋ እና በግጭት የተነሳ የሚፈናቀለው ሰው መብዛት ጋር ይያዛል። እንኝህ ግጭቶች በ ወረርሽኙ ዙሪያ በአንዳንድ ስፍራዎች የተሟላ ሪፖርት እንዳይቀርብ እንቅፋት ሆነዋል። ሆኖም ግን ባለው መረጃ አፍሪካ፣ ምስራቅ ሜዲትራንያንና ደቡብ ምስራቅ እስያ ክልሎች ወረርሽኙ በስፋት እየተስፋፋባቸው ይገኛል። ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ የአለም ጤና ድርጅት በአፍ የሚወሰድ የኮሌራ ክትባቶችን (ኦሲቪ) ምርትና ስርጭት ለማሳደግ ጥረቱን አጠናክሮ እየቀጠለ ቢገኝም ወረርሽኙን መቀልበስ ግን አልተቻለም።


በ ሀገራችን ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ካሉ የጤና እክሎች መካከል የኮሌራ እና የ አተት ወረርሽኝ አንዱ ነው። ይህ ወረርሽኝ ሀገሪቷ እያሳለፈቻቸው ካሉ ተግዳሮቶች ጋር ተደምሮ ከባድ ጫና እያሳደረ ይገኛል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ይህንን የኮሌራ ወረርሽኝ "በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ረዥሙ" ሲል ገልጾታል።


የኮሌራ ወረርሽኙ በዋነኝነት በአማራ እና በ ጋምቤላ ክልሎች እየተንሰራፋ ፤ በማህበረሰቡም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ወረርሽኙ በአማራ ክልል ውስጥ ብቻ ወደ 60 ወረዳዎችን ያጠቃ ሲሆን ፤ በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት 126 ገደማ ሰዎች መሞታቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ። በ ጋምቤላ ክልል ወረርሽኙ ከጀመረብት ጊዜ ጀምሮ 36,180 ሰዎች የታመሙ ሲሆን ፤ 600 ሰዎች ከ ወረርሽኙ ጋር በተያያዘ አርፈዋል።


ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል የሀገር በቀል ድርጅቶች፣ የአለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም መንግስት ተጣምረው እይሰሩ ይገኛል። ሆኖም ግን ፤ የኮሌራው ወረርሽኙን እስከአሁን ሙሉ በሙሉ መግታት አልተቻለም።


የኮሌራ ወረርሽኝ ለ ኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። በታሪክ በርካታ ጊዜ የኮሌራ ወረርሽኝ ያጋጠመ ቢሆንም ፤ የአሁኑ ወረርሽኝ ለረዥም ጊዜ መቆየቱ አሳሳቢ ያደርገዋል። 

ኮሌራ ሙሉበሙሉ አክሞ ማዳን መቆጣጠር የሚቻል ህመም ሆኖ ሳለ ታዳይ እንዴት እንዲህ ሊያጋጥም ቻለ? ይህንን ለመረዳት ስለ ኮሌራ ማውራት መልካም ይሆናል።


ኮሌራ ምንድነው?


ኮሌራ  ቫይብሮ ኮሌራ (Vibrio cholerae) በተባለው ባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የ ኢንፌክሽን ህመም ሲሆን፤ ህክምና ካላገኘ ባጭር ጊዜ ውስጥ እስከሞት ድረስ ሊያደርስ የሚችል በሽታ ነው። ታማሚዎች በዋነኝነት አጣዳፊ የሆነ ተቅማጥ ይኖራቸዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የትውከት እና ድካም ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ።  በአጭር ጊዜ ሰውነታቸው በተቅማጥ መልክ የሚያጣው ፈሳሽ ፤ ሰውነትን ለውሀ እጥረት ይዳርገዋል።  


ሁሉም የ ህመሙ ተጠቂዎች እነኝህን ምልክቶች ላያሳዩ ይችላሉ። እንደውም ባብዛኛው የኮሌራ ታማሚዎች ምንም ምልክት ላይሳዩ

፤ አልያም ቀለል ያሉ የህመም ምልክቶችን ብቻ ሊያሳዩ ይችላሉ። እነኚህ በጠና ያልታመሙ ታማሚዎች መታመማቸውን ስለማያቁ በዙሪያቸው ወድሚገኙ ሰዎች በሽታው እንዲተላለፍ ያደርጋሉ። ለበሽታው ስርጭት እና መንሰራፋት ትልቁን አስተዋእጾም ይጫወታሉ።


ኮሌራ እንዴት ይተላለፋል?

ኮሌራን የሚያስከትሉት አካላት፦


🚱 የተበከለ /ንጽህናው የተጓደለ የመጠጥ ውሃ ዋነኛው መንስኤው ነው።

🍽️ አንዳንዴ ከተበከለ ምግብ በተለይም አሳን የመሳሰሉ የባህር ምግቦች ጋር ሊያይዝ ይችላል።


ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ


✅ ከንጽህና ጉድለት ይመጣል።

✅ ከወንዝ ጋር የሚገናኙ አልያም በስርአት ያልተወገዱ መጸዳጃ ቤቶች ጋር ሊያያዝ ይችላል።

✅ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም ግጭቶች የተጣራ የዉሀ ስርጭትን ስለሚያስተጓጉሉ፤ እንዲሁም የመጸዳጃ ቤቶች አወጋገድ ሆነ አጠቃቀም ላይ እክል ስለሚፈጥሩ፤ ለ ኮሌራ ኢንፌክሽን ያጋልጣሉ።

 

መንስኤው ቀላል ቢመስልም ፤ መፍትሔው ግን ብዙ አካላትን ያጣመረ ነው።

ከቤታችን የሚመጣው የመጠጥ ውሃ አማራጭ በኛ ፈቃድ የሚወሰን ጉዳይ አይደለም። የ አስተዳደር አካላት የተጣራ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሻሻል ይህንን ችግር ለመፍታት  ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። ድርቅ፣ የተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም ግጭት ባለባቸው ስፍራዎች ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች ይህንን አቅርቦት ማሻሻል እጅጉን አዳጋች ነው። ለዚህም ከመንግስት ባሻገር የተለያዩ ሀገር ውስጥ ያሉ እንዲሁም የአለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ተቋማት የሰብዓዊ እርዳታ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል።


እንደግለሰብስ ምን ማድረግ ይቻላል?


በኮሌራ እንዳንጠቃ የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግ አጥብቆ ይመከራል።

 

  1. የግል እንዲሁም የአከባቢ ንጽህናን ይጠብቁ። ቆሻሻን በአግባቡ ያስወግዱ።ከጽዳት በኋላ እጃችሁን ታጠቡ።

  2. ኮሌራ ወዳጠቃው ስፍራ እየሄዱ ከሆነ ፤ የኮሌራ ክትባት አማራጭ ማግኘት የሚቻሉ ከሆነ ወይም ምን ማድረግ እንዳለቦት የጤና ባለሙያ ያማክሩ

  3. የታሸገ፣ በክሎሪን የታከመ ውሀ ይጠቀሙ።

  4. የተጣራ ውሀ አማራጭ ከሌለ የሚጠጡትን ውሃ ማፍላት ይኖርቦታል።

  5. የሚኖርበት አከባቢ በኮሌራ ከተጠቃ የ ቧንቧ ውሀን ከመጠቀም መቆጠብ።

  6. የሚጠቀሙት ውሀ ንጽህናው በተጠበቀ እና በተሽፈነ ስፍራ ያኑሩት።

  7. ምግብ ሲበሉ፣ ምግብ ሲያበስሉ ወይም መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ  በኋላ  እጆትን  በሳሙና እና በውሃ  አዘውትረው  ይታጠቡ።  ሳሙና የማይገኝ ከሆነ የአልኮል መጠኑ ከፍ ያለ ሳኒታይዘር ይጠቀሙ።

  8. የተፈጥሮ ግዳጅ ሲመጣ ሁል ጊዜ የመጸዳጃ ቤትን ይጠቀሙ። የመጸዳጃ ቤቱን ንጽህና በተገቢ ሁኔታ ይጠብቁ። 

  9. የመጸዳጃ ቤት የማይገኝ ከሆነ ከ ማንኛውም የውሃ አካል ቢያንስ 30 ሜትር ርቀው ይጠቀሙአጠባበቅ ይጠቀሙ።

  10. ሁሉንም ምግቦትን በስርአት አብስለው ይመገቡ። ያልበሰሉ የምግብ አማራጮችን ፍራፍሬ/ አትክልትን ከምጠቀም ይቆጠቡ። የሚመገቡትን ምግብ ንጽህናው ከተጠበቅ ሽፋን ካለው ስፍራ ያቆዩ።

 

🏥ተቅማጥ በተለይም ከባድ የተቅማጥ ህመም ምልክት ካለቦት ወዲያውኑ ወደ አቅራቢያ የሕክምና ተቋም ሄደው ህክምና ያግኙ። በሰአታት ውስጥ የከፋ ደረጃ የማድረስ አቅም ስላለው፤ ወደ አቅራቢያ የሕክምና ተቋም ለመሄድ በማመንታት ጊዜዎን አያባክኑ።

 

የተለያዩ አካላት ወረርሽኙን ለመግታት በጥምረት እይሰሩ ይገኛል።  በሽታውን ለመከላከል በተጎጂ ስፍራዎች የኮሌራ ክትባት እየተሰጠ ይገኛል። በእነኝህ ስፍራዎች ላሉ ስዎች የውሃ ስርጭት ለማሻሻል ከመሞከር ባሻገር የጽዳት መጠበቂያ አካላት እይተሰጡ ይገኛሉ። ይህንንም እንዲከታተል የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ጤና ድርጅት የጤና ባለሙያዎች ያካተተ የፈጣን ምላሽ ቡድኖችን ልኮ እየሰራ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር ማህበረሰብን ለማስተማር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ይገኛል።



እርሶም የመፍትሔው አካል ነዎት!


አሁን የደረሶትን መረጃ አቀልለው አይዩት። መከላከል ምርጡ የህክምና አማራጭ ነው። ስለዚህም በዙሪያዎት ላሉ ቤተሰብ፣ ጓድኛ፣ እንዲሁም ባልደረባዎች መረጃውን ያጋሩ። እነሱም ስለ ኮሌራ እና እራሳቸውን ከኮሌራ እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው አጥርተው ይወቁ።


ኮሌራን በአንድነት እንከላከል!


መረጃውን ያዳርሱ የሰው ህይወት ያድኑ።

Commenti


bottom of page