top of page

ሔፓታይተስ ሲ የጉበት ቫይረስ

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚገልጸው በአለማችን


ወደ 58 ሚሊዮን ሰዎች ሥር ከሰደደ ሄፓታይተስ ሲ ጋር ይኖራሉ።

ወደ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች  በየዓመቱ በቫይረሱ ይያዛሉ።

290,000 ሰዎች በየአመቱ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ይሞታሉ።


ከ 10 አመት በፊት የነበረ የሄፓታይተስ ሲ ስርጭት። ኢትዮጵያ መካከለኛ ስርጭት ካላቸው ሀገራት መሆኗን ያስተውሉ!  ጥናታዊ ጽሁፉን እዚህ ያገኙታል።
ከ 10 አመት በፊት የነበረ የሄፓታይተስ ሲ ስርጭት። ኢትዮጵያ መካከለኛ ስርጭት ካላቸው ሀገራት መሆኗን ያስተውሉ! ጥናታዊ ጽሁፉን እዚህ ያገኙታል።

ይህ ቫይረስ በሰውነትዎ ለዓመታት ወይም ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሊከርም ይችላል። በዝምታ ቀስ በቀስ ጉበትን እያጠቃ ይመሽጋል። የጉበት ጉዳት እስኪስተዋል ድረስ ምልክት አይኖረውም። ሞትም ሲያጋጥም በቀጥታ ከቫይረሱ ይልቅ፤ በሚያደርሰው ጉዳት የተነሳ ነው።


አሁን ህክምና በደረሰበት አቅም ከዚህ ቫይረስ ታክሞ መዳን የሚቻል ቢሆንም ፤ አሁንም ቫይረሱ የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል።


በኢትዮጵያም ሔፓታይተስ ሲ መዳን እየቻለ ፣ በዝምታ ብዙዎችን የከፋ ደረጃ ያደርሳል።

ለመሆኑ ሄፓታይተስ ሲ ቫይረስ ምንድን ነው?


ሄፓታይተስ ሲ ጉብትን በይበልጥ የሚያጠቃ ፤ በደም ንክኪ የሚተላለፍ ቫይረስ ነው። በህክምናው ፍላቪቫይሪዴ የሚባለው የቫይረስ ቤተሰብ አባል የሆነ አር ኤን ኤ ቫይረስ ነው።



ቫይረሱ ጉበትን በይበልጥ ያጥቃ እንጂ ፤ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ላይ ተጽእኖ አለው። ቫይረሱ አንዴ ከያዘ በኋላ ሰውነት ውስጥ ተደብቆ ፤ በቋሚነት ሰውነትን የማጥቃት ዝንባሌ አለው። ይህም በህክምናው ስር የመስደድ ባህሪ (chronic) በመባል ይታወቃል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ፤ በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች መካከል ከ70% በላይ የሚሆኑት ሥር በሰደደ የሔፓታይተስ ኢንፌክሽን ይያዛሉ። ቫይረሱም ካልታከመ በስተቀር በሰውነት ውስጥ ይቆያል።


ለዚህ ኢንፌክሽን አጋላጭ ምንድን ነው?


ሄፓታይተስ ሲ በምግብ፣ በመጠጥ፣ በትንፋሽ (በሳል)፣ እንዲሁም በአካል ንክኪ አይተለላፍም። በሻይረሱ ለተጠቃ ሰው ደም ጋር በሚኖር ንክኪ ብቻ ይተላለፋል። ለዚህም ዋነኛ መተላለፊያ መንገዶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡



  • ደህንነቱ ያባልተጠበቀ መርፌ በመወጋት / መርፌዎችን እንደገና መጠቀም

  • እንደ እንጥል መቁረጥ ጉሮሮ መቧጠጥ ያሉ ባህላዊ የህክምና አማራጮች

  • በደም ስር የሚወሰድ አደንዛዥ እጽ በመጠቀም

  • የጤና ባለሙያዎች ስራ ላይ በሚያጋጥማቸው ድንገተኛ በመርፌ መወጋት

  • በበሽታው ከተጠቃ ሰው ጋር በሚኖር ወሲባዊ ግንኙነት

  • እንዲሁም አንዳንዴ በእርግዝና ወራት በቫይረሱ አንድ እናት ከተያዘች ፣ ቫይረሱ ወደ ጽንስ ሊተላለፍ ይችላል።


ሄፓታይተስ ሲ በኢትዮጵያስ?


በኢትዮጵያ በቫይረሱ ዙሪያ ላይ የተደረጉ ጥናቶች የቫይረሱ ስርጭት ከ 1 እስከ 3 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ይገምታሉ። በቅርብ የወጡ ጥናቶች መጠኑ ከዚህም ሊቀንስ እንደሚችል ቢያመላክቱም ፤ ስርጭቱም እንደ ክልሉ እና አከባቢው የተለያየ ነው።



ከምእራቡ አንጻር በኢትዮጵያ በደም ስር የሚወሰድ አደንዛዥ እጽ ተጠቃሚ እምብዛም የለም። አብዛኛውን ጊዜ ንጽህናችው ባልተጠበቁ የባህላዊ ህክምናዎች፣ በህክምና ስፍራ በሚያጋጥም ተጋላጭነት እንዲሁም በግብረ ስጋ ግንኙነት በብዛት ይተላለፋል።


ይህ እንደዚህ እንዳለ ብዙ የሄፐታይተስ ሲ ታማሚዎች ዘግይተው ህክምና ስፍራ ይመጣሉ። ጤና ተቋም በመጡ ጊዜ ቫይረሱ ጉበት ላይ ቋሚ ጉዳት አድርሶ ይገኛል።


የቫይረሱን ስርጭት ለመቃወም የጤና ጥበቃ ሚኒስተር ስትራተጂ ነድፎ እየሰራ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር የደም ልገሳ ፕሮግራሞች ደም ውስጥ ቫይረሱ መኖሩን ይመረምራሉ። ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም እየሰራ ይገኛል።


ሆኖም ግን ቫይረሱ በመደበኛ ሁኔታ እየተመረመረ አየደለም። የፀረ-ቫይረስ መድሀኒቱ ተደራሽነት ውስን ነው። የጸረ ቫይረስ መድሀኒቱም ሲገኝ ሂሳቡ ብዙዎችን ይፈትናል።


የህመም ምልክቶቹ

ቫይረሱ ጸጥተኛ ነው። ብዙ ጊዜ ጉዳት እስኪያደርስ ድረስ ምልክት አያሳይም። ምልክት ካሳየ ይህንይመስላል።


ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲይዝ ፡

  • ፈጽሞ ምልክት ላይሳይ ይችላል።

  • አልያም መለስተኛ ድካም ፣ አነስተኛ ትኩሳት፣ ማቅለሽለሽ እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል።


አንዳንዶች ላይ ቆዳ እና አይን ቢጫ ሊሆኑ ይችላሉ።


ቫይረሱ ስር ከሰደደ

ቫይረስ ስር ሲሰድ፣ ታካሚዎች ምንም ላያስተውሉ ይችላሉ። አልያም ለዓመታት መለስተኛ ድካም ሊሰማቸው ይችላል።


ቫይረሱ ግን ከጀርባ ጉበት ላይ ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ ይቆያል። ይህንንም ተከትሎ ጉብት ቋሚ ጉዳት ይደርስበታል። ከመቁሰል አልፎ ጉበት ጠባሳ ይኖረዋል። ጉበት እንደደረሰበት ጉዳት የተለያዩ ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። እነኝህም ምልክቶች በቫይረሱ የተነሳ የሚመጡ አይደሉም።


ከጉበት ባሻገርስ?

ሔፓታይተስ ሲ ቫይረስ ቆዳ ላይ የሚያመጣቸው ለውጦች። ጥናታዊ ጽሁፉን እዚህ ያገኙታል።
ሔፓታይተስ ሲ ቫይረስ ቆዳ ላይ የሚያመጣቸው ለውጦች። ጥናታዊ ጽሁፉን እዚህ ያገኙታል።

ከጉበት ባሻገር ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ይጠቃሉ። የሚከተሉትን ሊጎዳ ይችላል-


  • የበሽታ መከላከያ ስርዓትን ያሰናክላል

  • ኩላሊት ያስቆጣል (membranoproliferative glomerulonephritis)

  • ቆዳንም ሲያጠቃ ቆዳ ላይ ጥቋቁር ምልክቶችን ያሳያል ( lichen planus, vasculitis)

  • የሆርሞን ስርአትንም አዛብቶ ለ ስኳር ህመም ሊያጋልጥ ይችላል (insulin resistance, type 2 diabetes)

  • ደም ላይ የፕሌትሌት መጠን ሊመነምን ይችላል።



ባይታከሙስ ምን ይፈጠር ይሆን?


ህክምና ከሌለ ሥር የሰደደ ሄፓታይተስ ሲ ወደሚከተሉት ሊያመራ ይችላል-

1️⃣ የጉበት መቁሰል /መከርቸች (Fibrosis)

2️⃣ የጉበት ጠባሳ (cirrhosis)

3️⃣ የጉበት ደም ስሮች ላይ የሚታይ ደም ግፊት (Portal hypertension)

4️⃣ የጉሮሮ ደም መፍሰስ (Variceal Bleeding)

5️⃣የሆድ መወጠር ወይም መነፋት (Ascites)

6️⃣ የጉበት ካንሰር


ህክምና ቢደረግም ፤ አንዴ የጉብት ጠባሳ ካጋጠመ የጉበት ካንሰር የማጋጠም እድል እጅጉን ከፍተኛ ነው። ለዚህም ቀድሞ ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው።


📌 ሄፓታይተስ ሲ ሙሉ በሙሉ ሊድን ከሚችሉ በጣም ጥቂት ሥር የሰደደ የቫይረስ ኢንፌክሽኖች አንዱ ነው።

ታሪኩ የሚቀየረው እዚህ ላይ ነው።

በአሁኑ ወቅት ያሉ የቫይረሱ መቃወሚያ ፀረ ቫይረሶች (DAA) በአፍ በሚዋጥ መልክ የሚሰጡ ሲሆን ፤ ከ ሁለት እስከ ሶስት ወር መድሀኒቶቹን መውሰድ ያስፈልጋል። እነኝህ መድሀኒቶች በአግባቡ ከተወሰዱ ከቫይረሱ ፈጽሞ ይፈውሳሉ።



ምን መደረግ አለበት?


የ ጉበት ቫይረስ አለብዎ ? እንዴት አወቁ? ዛሬውኑ ይመርመሩ።

በተለይ

  • የህክምና መርፌ ከወጋዎት

  • ጤና ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ከሆነ

  • ያልታወቀ የጉበት በሽታ ካለብዎ

  • ከደም ጋር የተያያዘ/አካል መቆረጥ/መቅደድ ያለበት ባህላዊ ህክምና ካደረጉ

በፍጥነት ይመርመሩ። ስር ሳይሰድ ፤ ቋሚ ጉዳት ሳያደርስ ቫይረሱን ይያዙት።



ዛሬውኑ ተግባራዊ ለውጥ ያምጡ!

ዛሬ ይመርመሩ!

እርስዎንም ቤተሰብዎንም ይጠብቁ!


 

Comments

Couldn’t Load Comments
It looks like there was a technical problem. Try reconnecting or refreshing the page.
bottom of page