ደም ግፊት ህመም እና ጠንቁ፡ ምን ማወቅ ይኖርቦታል?
- Zebeaman Tibebu
- Mar 22
- 3 min read
የደም ግፊት እና የተባበሩት መንግስታት ታሪክ
የደም ግፊት ከ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ምን አገናኝቶት ይሆን ብለው አስበው ይሆናል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥንሥሥ ሀሳብ የተጣለበት የያልታ ኮንፍረንስ ተሳታፊዎች ፤ በስብሰባው ጊዜ የከፍተኛ ደም ግፊት ታማሚ እንደነበሩስ ያውቃሉ?
ታሪኩ እንዲህ ነው...
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ የመጣበት ጊዜ ነበር። የዓለም ዕጣ ፈንታ በያልታ ስብሰባ ላይ በ"ትልቁ ሦስት" ማለትም በሩዝቬልት፣ በስታሊንና በቸርችል ሊወሰን ግድ አለ። እነኝህ አውራዎች የአሜሪካ ፣ የ ሶቪየት ዩኒየን ፣ እንዲሁም የብሪታንያ መሪዎች ነበሩ። እነዚህ አይበገሬ መሪዎች የአውሮፓን ድንበር ክፍፍል በማሻሻል እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመመስረት ላይ ተጠምደው ሳሉ ፤ ድምጽ አልባ ጠላት ከውስጣቸው ተመሽጎ ነበር። እነኝህ ክንዳቸው ያየለ ብርቱ መሪዎች በደም ግፊት ህመም በጠና ተይዘው እያለ ነበር ፤ የተባበሩት መንግስታትን መሰረትን ያኖሩት።

የማይቋርጥ ጦርነትና እና የስልጣን ውጥረት ጤናቸውን እጅጉን አዳክሞት ስለነበር ፤ ከዚህ ታሪካዊ ስብሰባ በኋላ ሁሉም ብዙ አልቆዩም። ሲታይም ደክሞ የነበረው ሩዝቬልት ከስብሰባው ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፤ ደም ግፊት ጋር በተያይዘ ጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ አይነት) አስቀድሞ አረፈ። ከእርሱም ሞት በኋላ በአሜሪካ እና በሶቪየት ዩኒየን መካከል ያለው ግንኙነት እጅጉን ቆረፈደ። ከሁለቱ አለማት ጦርነት በላይ ሰው በላ የሆነው፤ የቀዝቃዛው ጦርነት በዚሁ ተጠንሥሦ ፤ የብዙህን ህይወት ቀጠፈ።
የማያመነታው ብርቱው ስታሊንም ከ 8 አመት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲያርፍ ፤ የተፈጠረው ሥርዓት አልበኝነት የሶቪየት ህብረት መፈረካከስ ምክንያት ሆነ። የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስተር ቸርችል ፤ የጤናው ማሽቆልቆሉን ተመልክቶ ከስልጣኑ ቀድሞ ለቀቀ። እሱ ከስልጣን መውረዱን ተከትሎ ፤ መልካም ደረጃ የነበረው የእንግሊዝ እና የግብጽ ግንኙነት ተበላሸ። የስዊዝ ካናል ውዝግብ አጋጠመ። ዊንስተን ቸርችልም በተዳጋጋሚ በስትሮክ ሲጠቃ ቆይቶ ከ12 አመት በኋላ ፤ ደም ግፊት ጋር በተያያዘ ስትሮክ አረፈ።
አሁን ያለንበትን ዓለምን የቀረጹ፤ የተባበሩት መንግስታትን ለመገንባት መሰረት የጣሉት፤ የሁለተኛው አለም ጦርነት ብርቱ እጆች፤ በ ቦንብ፣ በመትረየስ ወይም በኒዩክለር ሳይሆን ፤ ቦታ ባልሰጡት መቆጣጠር ባልተቻለ የደም ግፊት ተንበረከኩ። የሂትለር ዛቻ ሳያሸንፋቸው ፤ የደም ግፊት ዝምታ አፈር አለበሳችው !
በአለም ባለው የህክምና ጣራ መታከም ቢቻል እንኳን ፤ አንዴ ጉዳት ካደረሰ መሉ ጤናን መመለስ እንደማይቻል ፤ ከዚህ በላይ ምን አስረጂ ታሪክ ሊኖር ይችላል?
በኢትዮጵያስ?
የደም ግፊት በኢትዮጵያ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የማህበረሰብ ገጽታ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የሚያመላክት መረጃ ማግኘት ያዳግታል። ሆኖም ግን ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ አምስት ግለሰቦች ውስጥ በአማካይ አንዱ ከፍተኛ የደም ግፊት እንደሚኖርበት ጥናቶች ያሳያሉ። አብዛኛው የደም ግፊት ታማሚዎች ህመሙ እንዳለባቸው አለማወቃቸው አሳዛኝ እውነታ ነው። ወንዶች ከሴቶች ይልቅ ተጋላጭነት ስላለባቸው ፤ የወንድ ታማሚ ቁጥር ይበዛል። ከገጠሩ ማህበረስብ አንጻር ደግሞ ፤ የ ህመሙ ስርጭት በከተሞች ያይላል።
ታድያ እርሶስ ተመርምረዋል? ካልተመረመሩ ታማሚ አለመሆኑዎን እንዴት ያውቃሉ?
ከደም ግፊት ጋር ተይያዥነት ያላቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ፤ በኢትዮጵያ በዋነኝነት የሚጠቀሱት የሚከተሉት ናቸው።
· ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጡ የሰውነት ለውጦች
· ከ መጠን ያለፈ ውፍረት
· ጫት መቃም ፣ አልኮል መጠጣት ፣ ሲጋራ ማጨስ
· በቤተሰብ የሚተላለፍ የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ተጋላጭነት
ከ እነኝህ ባሻገር አኗኗራችን ወይም የኑሮ ዘይቤያችን ለደም ግፊት መሰራጨት ከፍተኛ አስተዋእጾ እንደሚያደርግ ይታሰባል። ለምሳሌ ጨው የበዛበት ምግብን ፣ እንደ ቡና ያሉ የደም ቱቦ ላይ ጫና የሚያሳድሩ መጠጦችን እንዲሁም ቅባት እጅጉን የበዛባቸው ምግቦችን ማዘውተር ለዚህ ተጠቃሽ ይሆናሉ። የስራ ይሁን ፣ የማህበረሰባዊም ጫና ፣ እንዲሁም ጭንቀት ለዚህ ቀንደኛ መንስኤ ነው።
ለዚህስ ይሆን እንዴ ፤ የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስተር ቸርችል ለጤናው ቦታ ሰጥቶ ፤ በጊዜ የስራ ጫና በመቀነሱ ፤የህይወት ዘመኑ ከ እነ ሩዘቬልት እና ስታሊን የረዘመው?
ታድያ የደም ግፊት መጨመር ምንድነው?

የደም ግፊት አንዳንዴ በተለምዶ የደም ብዛት ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ለዚህም አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎች የደም ህዋሳት ቁጥርን መብዛትን እንደደም ግፊት አርገው ወስደው ፤ የደም ብዛት የለብኝም ሲሉ ማየት የተለመደ ነው። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። የደም ግፊት የደም ህዋስ መጨመር አይደለም።
የደም ግፊት በደም ስር (በደም ወሳጅ ቱቦ) ግድግዳዎች ላይ ያለው የግፊት ኃይል ሲጨምር የሚመጣ ህመም ነው። ይህም ደግሞ
1. የደም ቱቦዎቹ መጥበብ
2. የልብ ደምን የሚገፋበት ኃይል መጨመር ወይም፤
3. በደም ቱቦዎች ውስጥ የሚጓዘው የደም መጠን ሲበዛ ሊፈጠር ይችላል።
ለዚህም ክንድ ላይ በሚደረግ ፤ ግፊት በሚለካ የደም ግፊት መሳሪያ ፤ በቀላሉ ሊለካ ይችላል።
ደም ግፊት ጨመረ የምንለው መቼ ነው? ምንስ ያሰጋናል?
የአንድ ጤነኛ ሰው የደም ግፊት የላይኛው(ሲስቶሊክ) ከ120 ፤ እንዲሁም የታችኛው ደግሞ (ዳያስቶሊክ) ከ 80 መብለጥ የለበትም። ከዚህ አልፎ ከተገኘ የደም ግፊቱ ጨምሯል ይባላል። የደም ግፊት ህመም ለመባል ግን ፤ ተደጋግሞ በተለያየ ጊዜ ከፍ ያለ የደም ግፊት መታየት ይኖርበታል። ይህ የጨመረ የደም ግፊት መቆጣጠር ካልቻልን ፤ የሰውነት አካላችን ላይ ቋሚ የሆነ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እነኝህም ደግሞ
• የልብ ሕመም፡- የደም ግፊት መጨመር ለልብ ድካምና ልብ ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
• ስትሮክ፡- ከፍተኛ የደም ግፊት በአንጎል ውስጥ ያሉ የደም ስሮች ላይ በሚያደርገው ጫና ለስትሮክ ይዳርጋል።
• የኩላሊት መጎዳት፡- ረዥም ጊዜ የቆየ የደም ግፊት ጥቃቅን የኩላሊት ደም ስሮች ላይ በሚያደርሰው ቋሚ ጉዳት ለኩላሊት በሽታ ወይም ድክመት ያስከትላል።
• አይን ላይ የሚደርስ ጉዳት፡- ከደም ግፊት የተነሳ ጥቃቅን የአይናችን የደም ስሮች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ፤ እይታችንን ከማስተጓጎል አልፎ ፈጽሞ ማየት እንዳንችል ሊያደርገን ይችላል።
እንዴት እንቆጣጠረው?፡ ቀላል የአኗኗር ለውጦች

ከታሸጉ ምግቦች ይልቅ እቤትዎ አብስሎ የሚሰሩትን ምግብ ይምረጡ። የሚመገቡት ምግብ ላይ አትክልት እና ፍራፍሬ ያዘውትሩ። የሚመጉብት ምግብ ውስጥ ያለው የጨው መጠን እጅጉን የተገደበ ይሁን።
በ ሳምንት 2 እስከ 3 ቀን ለ30 ደቂቃ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። የግድ ስፖርት ቤት ገብተው መስራት አይጠበቅቦትም፣ እንደ ፈጣን የእግር ጉዞ ቀላል የሆነ እንቅስቃሴ በቂ ሊሆን ይችላል።
አልኮል መገደብ፣ ጫት እና ማጨስን ማቆም፡ ሁሉም የደም ግፊትን ይጨምራሉ። በልብዎ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ አልኮልን መቀነስ ፤ ጫት ፈጽሞ አለመቃም እና ማጨስን ለማስወገድ ይሞክሩ።
ውጥረትን ያስወግዱ፡- ሥር የሰደደ ውጥረት የደም ግፊትን ያባብሳል። ስለዚህምጭንቀትዎን ለመቆጣጠር ይሞክሩ።
መደበኛ ምርመራዎችን ያድርጉ፡ የደም ግፊትዎን ይከታተሉ። ህመሙ ከተገኘቦት የዶክተርዎን ምክር በደንብ ይከተሉ።
ዛሬውኑ የመጀመሪያውን እርምጃ ይውሰዱ
ጤናዎ በእጅዎ ነው! የደም ግፊትዎን በመመርመር ይጀምሩ!
በቶሎ እርምጃ ሲወስዱ ፤ ራስዎን ከከፉ የጤና እክሎች ይታደጋሉ።
コメント