🌿ጤና አዳም ጀርባ ያለው ሳይንስ
- Zebeaman Tibebu
- Jun 22
- 4 min read
ብዙ ኢትዮጵያዋያን ሲታመሙ ፤ አልያም ጤናቸውን ለመጠበቅ ጤና አዳም ይጠቀማሉ። ለትኩሳት ፣ ለሆድ ህመም ወ.ዘ.ተ የሚጠጣው ውስጥ ጤና አዳም ቅጠል ተደርጎ ይመጣል። ህመም ሳይኖር እራሱ ፤ ቡና፣ ሻይ እና ወተት ላይ እንደ ልማድ ጤና አዳም የሚከቱ ብዙዎች ናቸው።
ለምን? ለቃናው ወይስ ጤናን ለማጎልበት።
ስንታመም እናቶቻችን/አያቶቻችን ምግብ ውስጥ አድርገው የሚሰጡን ጤና አዳም የሚያሽለው በእናት/አያት ፍቅር ታጅሎ መቅረቡ ነው ? ወይስ መድሐኒትነት ኖሮት ?

ጤና አዳም ታሪክ በአለም ዙሪያ
ኢትዮጵያ ውስጥ ጤና አዳም እንበለው እንጅ ፤ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ። በአለም ዙሪያ ይታወቃል።
የሰው ልጅ ጤና አዳምን እንደመድሐኒትነት መጠቀም ከጀመረ ፤ ሺ አመታት ተቆጥረዋል። ግሪካዊው ሐኪም በአንደኛው መቶ ክፍለዘመን በጻፈው የሕክምና መጽሐፍ ላይ ፤ ጤና አዳአም ለነርቭ ሕመሞች ፣ ለምግብ መፈጨት ችግር እንዲሁም ለመርዛማ ንክሻ መድሐኒትነት እንዳለው አስፍሯል። የጥንት የሮም ወታደሮችም ራሳቸውን ከበሽታ እና ከክፉ መናፍስት ለመከላከል ፤ ጤናዳም ይይዙ ነበር። በሌሎች ማህበረሰቦች ጤና አዳም ለወር አበባ ህመም ማስታገሻ ፤ እንዲሁም ለ ምግብ መፈጨት ችግሮች ይውል ነበር።
በሜዲትራንያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ፤ ጤና አዳምን ከቤት አጠገብ መትከል ፤ መጥፎ እድልን ያርቃል ብለው ይታመን ነበር። በቀኝ ግዛት ዘመን የተዋወቀ ቢሆንም ፤ በደቡብ አሜሪካ (ላቲን አሜሪካ) ደግሞ ፤ ለሆድ ሕመም እንዲሁም ክፉ መንፈስ ለማባረር ፤ጤና አዳም ይውል ነበር።
እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሞሮኮ፣ ግብፅ ባሉ አረብ አገራት በሻይ እና በምግቦች ውስጥ ተደርጎ ፤ ኢንፌክሽን ህመሞችን ለማከም እና ህመም ለማስታገስ ይጠቀሙት ነበር።
ኢትዮጵያም ጤና አዳም ከዘመን ዘመን ሲሸጋገር የመጣ ፤ ለብዙ ህመሞች ፍቱን የሆነ ባህላዊ ህክምና ነው። በባህላዊ ህክምና ባለውም የጤና ጠቀሜታ ፤ የአዳም ጤና (የሰው ልጅ ጤና) በመባል ይጠራል። በባህላዊ ህክምና ለ ኢንፌክሽን ህመሞች ፣ ለትኩሳት ፣ ለራስ ምታት ፣ ለሆድ ህመም ፣ ለምግብ መፈጨት ችግር ፣ ለደም ግፊት፣ ለ ድኅረ ወሊድ እንክብካቤ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አብዝቶ ከሚጠቀማቸው ባህላዊ መድሐኒትነት ካላቸው ቅጠሎች ይካተታል። ከመድሐኒትነቱ ባሻገር ፤ ከማንነታችን ጋርም ቁርኝነት አለው። ከ ጤና አዳም ጋር ብዙዎቻችን ትውስታ አለን።
አንድ ጥያቄ እንጠይቅ እስቲ...
እነኝህ በዘመናት ፣ በኪሎ ሜትሮች ፣ በባህል እና በእምነት የተራራቁ ማህበረሰቦች ውስጥ ፤ ጤና አዳም እንዴት ተቀራራቢ የጤና ጠቀሜታ ሊኖረው ቻለ?
የ አጋጣሚ ጉዳይ ፣ የባህል ትስስር ወይስ እውነተኛ የጤና ጠቀሜታ ኖሮት?
ይህን ጥያቄ ለመመለስና የጤና ጠቀሜታውን ለመለየት፤ ሳይንቲስቶች በጤና አዳም መድሐኒታዊ ባህሪ ዙሪያ ላይ ብዙ ጥናቶችን አካሂደዋል። ሙሉ ጠቀሜታውን ለመረዳት እና ወደ ዘመናዊ ህክምና ለማምጣት አሁንም ጥናቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
የጤና አዳም ተክል ሳይንሳዊ ግንዛቤ

ጤና አዳም ተክል በሳይንሳዊ ስሙ ሩታ ቻልፕንሲስ (Ruta chalepensis) ይባላል። ሳይንስ አሁን በተረዳው ደረጃ ፤ ይህ ቅጠል በውስጡ ብዙ የፈውስ አቅም ያላቸው ውህዶች አሉት። ከእነኝህ ውህዶች የጤና ጠቀሜታቸውን ሳይንስ ለይቶ የተረዳው የሚከተሉትን ነው።
ጤና አዳም በውስጡ ጸረ ኦክሲዳንት ባህሪ ያላቸው ውህዶች አሉት። እነኝህ ፍላቭኖይድስ የሚባሉት ውህዶች ፤ ሰውነታችንን ይደግፋሉ። የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም ይደግፋሉ።
የፀረ-ባክቴሪያ፣ ፀረ-ፈንገስ እና ፀረ-ተባይ ባህሪያትን ያላቸው ዘይቶች በውስጡ አሉት። እነኝህ ዘይቶች (2-undecanone & methyl-nonyl-ketone) በተለያዩ ባክቴሪያዎች ላይ ( E. Coli, Staphylococcus Aureus) ላይ አሉታዊ ተጸእኖ እንዳላቸው ጥናቶች ያሳያሉ።
የህመም ማስታገሻ ባህሪ ያላቸው ውህዶችም (Alkaloids, furocoumarins chalepensin) ተገኝተዋል። እነኝህ ውህዶች ህመምን ከመቀነስ ባሻገር ፤ በፀረ-ተሕዋስያን ( antibiotics) ባህሪ አላቸው።
ከዚህም ባሻገር ውስጡ ያሉ ውህዶች የደም ስር ግድግዳዎችን ያላላሉ (ያሰፋሉ)። ይህም የደም ግፊት መጠንን ይቀንሳሉ። ይህ ባህሪያቸው በእንሰሳት ላይ በተደረጉ ጥናቶች ተረጋግጧል።
ሙሉ በሙሉ ያልተረጋገጡ ፤ ገና በጥናት ላይ ያሉ ባህሪያቶቹ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።
የደም ቅጥነትን/ውፍረትን የሚለውጡ ውህዶች በውስጡ ተገኝትዋል። ሆኖም ግን የእነኝህ ውህዶች ልዩ ባህሪ ፤ ደምን ማቅጠን ይሆን ማወፈር ገና አልተረጋገጠም።
ነርቭ ላይም ተጽእኖ ያላቸውም ውህዶች ተገኝተዋል። እነኝህም ውህዶች ነርቭን ያደንዝዙ ያነቃቁ ገና እየተጠና ነው።
ከዚህም ባሻገር ውስጡ ያሉ አንዳንድ ውህዶች የካንሰር ህዋሳት ላይ ያለው ተጽእኖም በጥናት ላይ ነው።
ይህ አፈ ታሪክ፣ትውፊት ወይም መላምት አይደለም። በዘመናዊ መንገድ ሲጠና የተገኙ የጤና አዳም አስደናቂ መድሐኒታዊ ባህሪያቱ ናቸው።
የቅድሙን ጥያቄ ስንመልስ ... "አዎ ጤና አዳም እውነተኛ ብዙ የጤና ጠቀሜታ አለው።"
እንደውም ይህ እጽዋት የባክቴሪያዎችን እድገት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚገታ እንደውም አቅሙ ከአንዳንድ መድሐኒቶች ጋር ሊወዳደር እንደሚችል ሁሉ ያሳየ የላብራቶሪ ጥናት አለ።
⚠️ ጥንቃቄ

የመድሐኒትነት ጥቅሙን ከተረዳን ፤ ውስጡ ያሉት ውህዶች ያላቸው የመድሐኒትነት ባህሪ ኃይለኛ መሆኑን መገንዘብ አለብን። ባህላዊ ህክምና ብዙ ጊዜ ተግዳሮቱ ፤ የመድሐኒቶችን ውህድ መጠን መለየቱ ላይ ነው። ውስጡ ያሉ ውህዶች ሲበዙ ጉዳት ሊያመጡ ፤ አልያም ህመም ሊያባብሱ ወይም መድሐኒት ጋር ሊቃረኑ ይችላሉ። ስለዚህ መጠኑን ሁሌ መጠንቀቅ አግባብ ነው። በዋነኝነት መጠንቀቅ ያለብን፡
እርግዝና ጊዜ መጠንቀቅ አለብን። የማህጽን ጡንቻ እንዲኮማተር የሚያደርጉ ውህዶች ስላሉት፤ በእርግዝና ጊዜ አይመከርም። በእንሰሳቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች ይህንን አረጋግጠዋል። ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት ከሆነ መጠኑ በበዛ ቁጥር ማህጸን የመኮማተር ኃይሉ ይጠነክራል። ይህ ደግሞ እርግዝና እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል። ለዚህም ይሆናል አንዳንድ ማህበረሰቦች በባህላዊ ህክምና ጽንስ ለማቋረጥ የሚጠቀሙት።
ቅድም በመድሐኒትነት የጠቀስናቸው ውህዶች (furancoumairns, alkaloids and flavonois) ሲበዙ ፤ ጉበትን ሊጎዱ ይችላሉ። ለዚህ አብዝቶ ጤና አዳም መውሰድ አይመከርም። ይህ በጥናቶች ተረጋግጧል።
ካሉት ውህዶች አንዱ (furanocoumarin) የጉበት የመድሐኒት ማርከሻ ኤንዛይም (CYP3A4) ያከሽፋል። በዚህም የተነሳ የተለያዩ መድሐኒቶችን ስራ ለውጦ ፤ መርዛማ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ መድሐኒት ለሚወስድ ሰው ጥንቃቄ ማደረጉ መልካም ነው። በተለይ ጤና አዳም በብዛት ከተወሰደ።
"እስከዛሬ ስወስድ ምንም አልሆንኩም!"ብለው ካሰቡ ይህንን ያስታውሉ፤ ቁልፉ ያለው ከመጠኑ ጋር ነው።
ጤና አዳም ብዙ በሳይንስ የተረጋገጠ ጥቅም ያለው ተክል ቢሆንም ፤ ሲወስዱ ጥንቃቄ ያድርጉ። አብዝቶ መውሰድ ከደህንነቱ ፤ ጉዳቱ እንዲያይል ሊያደርግ ይችላል።
ከዘመናዊ ህክምና ይጠቃለል ይሆን?
ይህ ቅጠል ከባህላዊ ህክምና የመጣ ስለሆነ ፤ ወደ ዘመናዊ ህክምና እስኪጠቃለል ብዙ ጥናቶች ያስፈልጋሉ። ውስጡ መድሐኒትነት ያላቸው ንጥረ ነገሮች ፤ ለሚያዱኑት ህመም ብቻ እንዲሆኑ ተደርገው ተለይተው መመረት አለባቸው። ይህ ደግሞ ረዥም ጊዜ ይፈጃል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጥናት እያካሂዱ ያሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ራሱ ትኩረት ሰጥተው ማጥናት የጀመሩት በቅርብ ጊዜ ነው። በአለም ዙሪያ ያሉ ተመራማሪዎች የመድኃኒትነቱን መጠንን፣ የመርዛማነት ገደቦችን እና የውህዶችን መለየት ዙሪያ እየሰሩ ነው።
ከሱ አንጥረን ያወጣነው ውህድ ሆነ ጤናዳም ቅጠሉ ፤ በዘመናዊ መንገድ ተዘጋጅቶ ፤ የብዙ ሰዎች ጤና በዘመናዊ መልክ ማከሙ የማይቀር ነው።
ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ... ጤናዎን እንዲያግዝ ጤና አዳምን ይጠቀሙ።
Comments