top of page

🌿 ሺ ህመም የሚፈራው ቅጠል - ሽፈራው

ሽፈራው ቅጠል ወስደው ያውቃሉ ? ስለ ጤና ጠቀሜታውስ በጥልቅ ያውቃሉ? ከደም ግፊት ባሻገር ለስኳር ህመምስ ያለውን ጠቀሜታ?

ከኢትዮጵያ ቆላ መሬት ጀምሮ እስከ ሂማልያ ተራሮች ግርጌ ባሉ ሀገራት ድረስ ይህ ተክል በደንብ ይታወቃል። በእንግሊዘኛ ስሙ ሞሪንጋ በአማርኛ ሽፈራው ተብሎ ይጠራል። ለዘመናት በአፍሪካ፣ በእስያ እና በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ ሀገራት ባህል ህክምና ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። አይዩሪቪዲክ ሜድሰን በመባል የሚታወቀው የህንድ የባህላዊ ህክምና ውስጥም ከ300 በላይ በሽታዎችን እንደሚያክም ይነገራል። በአፍሪካ ስነ እጽዋት እውቀት ደግሞ ፤ ይህ ቅጠል ኢንፌክሽኖችን ፣ የተለያዩ እብጠቶችን ለማከም ግልጋሎት ሲውል ቆይቷል።


ree

ነገር ግን የሽፈራው ቅጠል ጠቀሜታ በታሪክ እና በባህላዊ ህክምና ውስጥ ብቻ ተቀብሮ የቆየ አይደለም። በቅርብ አመታት የዘመናዊ ህክምና ትኩረትን ስለሳበ በቅጠሉ ዙሪያ ብዙ ጥናቶች/ ምርምሮች ተደርገዋል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሞሪንጋ በቫይታሚን ሲ፣ ካልሲየም፣ ፖታሲየም እና ፕሮቲን የበለፀገ ከመሆኑ ባሻገር የአንቲ አክሲዳንት ባህሪ ያላቸው ንጥረ ነገሮች (እንደ quercetin እና chlorogenic አሲድ) አሉት። በዚህም የተነሳ ጤና ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ሊኖረው ችሏል።


የጤና ጠቀሜታው


ይህ ተክል ጤና ላይ ባለው ጠቀሜታ "ተአምረኛው ዛፍ” ወይም “የሕይወት ዛፍ” የሚል ተቀጽላ ስያሜ ተሰጥቶታል። ዋና ዋና የጤና ጠቀሜታዎቹ የሚከተሉት ናቸው።


🌱 የላቀ የንጥረ ነገር ስብስብ አለው።


ree

የሽፈራው ቅጠሎች በውስጣቸው የሚከተሉት ንጥረ ነገሮች አሏቸው፡-


ቫይታሚን፡ የሰውነታችንን የበሽታ መከላከል አቅም የሚያጎለብቱና የቆዳ ጤንነትን የሚደግፉ በሆኑት በቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ሲ እና ቫይታሚን ኢ የበለፀገ ነው።


• ማዕድን፡ ከፍተኛ የካልሲየም፣ የፖታስየም እና የብረት መጠን ስላለው ፤ የአጥንት ጤናን ከመደገፍ ባሻገር ፤ የደም ግፊትን ለመቆጣጠር ያግዛል።


ፕሮቲኖች፡- ዋነኛ የሚባሉት አስፈላጊ ዘጠኙን አሚኖ አሲዶች አሟልቶ በውስጡ የያዘ በመሆኑ ፤ ከእጽዋት የተቀመመ ተመራጭ የፕሮቲን ምንጭ ያደርገዋል።


እነኝህ ንጥረ ነገሮች ስላሉት ፤ ጤናን ይደግፋል፣ የኃይል መጠን ይጨምራል፣ እና የበሽታ መከላከያ አቅምን ያጎለብታል።

💖 የልብ እና ደምስር ጤናን ይጠብቃል ።


የሽፈራው ውስጡ አንቲኦክሲዳንት ባህሪያት ያላቸው ንጥረ ነገሮች ስላሉት ፤ የኮሌስትሮል መጠንን ይቀንሳል። ይህም ኮሌስትሮል በደም ወሳጅ ቧንቧዎች ላይ እንዳይከማች ለመከላከል ይረዳል።


ከዚህም ባሻገር ሰውነታችን እንዳይቆጣ ስለሚያደርግ (anti-inflammatory) ፤ የደም ግፊትን ቁጥጥርን ያሻሽላል እንዲሁም የልብን ጤናን ይደግፋል።


🩸 የደም ስኳር ቁጥጥር ያሻሽላል።


ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሽፈራው በደም ውስጥ ያለውን የደም ላይ ያለ የስኳር መጠን ስለሚቀንስ ስኳር በሽታ ላለባቸው እንዲሁም ለስኳር ተጋላጭነት ላለባቸው ሰዎች ጠቀሜታ አለው።


ውስጡ ያሉት ንጥረነገሮች ለኢንሱሊን ሰውነታችን ያለውን ምላሽ (insulin sensitivity) ያሻሽላሉ። እንዲሁም ከአንጀት ውስጥ ወደ ደም የሚገባውን የግሉኮስ መጠን ይቀንሳሉ። ይህም የስኳር ቁጥጥርን እጅጉን ያግዛል።


🧠 የአዕምሮ ደህንነትን ይጠብቃል።


ሽፈራው ከ ፀረ-ኦክሲዳንት ባሻገር ፤ ነርቮቻችንን የሚጠብቁ ንጥረ ነገሮች በውስጡ ስላሉ የአዕምሮ ጤናን ያግዛል። ለዚህም ስሜታችንን ፣ የማስታወስ ችሎታችንን እና አስተሳሰባችንን ያሻሽላል ። ከዚህም አልፎ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ድብርት እና ጭንቀትንም ይቆጣጠራል።


🛡️ የበሽታ መከላከያ ስርዓትን ይደግፋል።


እላይ በተዘረዘሩት ንጥረነገሮች የተነሳ ፤ ሽፈራው የሰውነታችን የበሽታ የመከላከል አቅምን የበለጠ ያጠናክራል። ባክቴሪያን ስለሚቃወም ፤ እንዲሁም ሰውነታችን እንዳይቆጣ ስለሚከላከል ፤ ስውነታችን በሽታ አምጪ ተህዋሳትን የሚቃወምበትን አቅም ያበረታል።


🌿 ሽፈራውን ወደ አመጋገብዎ እንዴት ማካተት ይችላሉ።


ree

  1. አድርቀው ከፈጩት በኋላ ፤ ዱቄቱን በ ሻይ ሾርባ እና ጁሶች ውስጥ መደባለቅ ይችላሉ።


  2. አንዳንድ እንደ መድሀኒት የተዘጋጁ ፤ የሽፈራው እንክብሎችን መውሰድ ይችላሉ።


  3. እንዲሁም ቅጠሉን በማብሰል፣ በማፍላት፣ እንደሰላጣም በማድረግ መጠቀም ይችላሉ።


ታድያ ግን ሽፈራውን ሲወስዱ ፤ ሰውነትዎት ከቅጠሉ ጋር መስማማቱን ለማስተዋል እንዲቻልዎ ፤ በአንድ ጊዜ ብዙ በመውሰድ አይጀምሩ።


በመጠኑ እያደረጉ ደጋግመው ይውሰዱ።


ያስተውሉ ይህ የህክምና መተኪያ አይደለም። የሚወስዱትን መድሀኒት ቅያሪም አይደለም።


ይህ የእርሶን ጤና መደገፊያ ፣ ህክምናዎን ማገዣ ነው።


የሚወስዱትን መድሀኒት ለማቆምም ዶክተርዎን ያማክሩ።


ማጠቃለያ


ሽፈራው በአያቶቻችን ጥበብ ላይ የተመሠረተ ፤ በዘመናዊ ሳይንስ የተረጋገጠ ፤ ጠቀሜታ ያለው ተአምረኛ ቅጠል ነው። እንዳሻዎት አድርገው ሊመገቡት የሚችሉት ፤ ትልቅ የጤና ጥቅም ያለው ተክል ነው።


ስለዚህ በሚቀጥለው ጊዜ በሽፈራው ዛፍ አጠገብ ሲያልፉ ፤



ያለውን የላቀ የጤና ጠቀሜታ ያስታውሱ።



Comments


bottom of page