ስለ ነስር ማወቅ ያለብን እውነታዎች፦ መንስኤው፣ ስህተቶች እና ህይወት አድን እርምጃዎች
"ነስር አለብዎ!? ያለበት ሰውስ ያውቃሉ"

ይህ ብዙ ጊዜ የተለመደ ጥያቄ ነው። እስቲ ያስቡት... ድንገት እየተጫወቱ ፤ አንድ ሰው በድንገት ከአፍንጫው ደም መፍሰስ ቢጀምር ምን ይሰማዎታል? ይደነግጣሉ? ምንስ ያደርጋሉ?
"ጭንቅላትህን ወደ ኋላ አዘንብል!" ብለው የተለመደ ምክር ይሰጡ ይሆናል። ግን ይህ ምክር ትክክል ነውን!?
ጭንቅላትን ወደ ኋላ ማዘንበል ደሙን አያቆመውም!
ይልቁኑ ወደ ጉሮሮ እና ወደ ሆድ እንዲወርድ በማድረግ ትውከትና የመታፈን አደጋን ይጋብዛል። በቅንነት የምናደርጋት ይህች ድርጊት ነገሩን ይበልጥ ሊያወሳስበው ከቻለ ፤ ማድረግ ያለብንን እና የሌለብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል።
ስለ እርሱ በደንብ ለመረዳት ደግሞ፤ በመጀመሪያ ስለ ነስር ምንነት እንወቅ።
ነስር ምንድነው?የበሽታ ምልክት ወይስ በሽታ?

ነስር የምንለው በአፍንጫችን ውስጠኛው ክፍል ባሉ ጥቃቅንና ስስ የደም ስሮች መበጠስ ምክንያት የሚከሰት ድንገተኛ የደም መፍሰስ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ደሙ የሚፈሰው ከአፍንጫችን የፊት ለፊት ክፍል ሲሆን፤ ይህ ዓይነቱ ነስር በቀላሉ የሚቆምና ብዙም ስጋት የማይፈጥር ነው።
ነገር ግን ስለ ነስር ስናስብ ሁላችንም ልናስተካክለው የሚገባ አንድ ትልቅ የተሳሳተ አመለካከት አለ። ብዙ ጊዜ ሰዎች "ነስር አለብኝ" ሲሉ እንሰማለን እኛም "ነስር አለብዎ" ብለን እንጠይቃለን። ይህ አረዳድ ክፋት ያለው ባይመስልም ፤ ነስር በራሱ ራሱን የቻለ በሽታ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብናል።
ይልቁኑ ነስር የበሽታ ምልክት ነው።
ልክ እንደ ትኩሳት፣ ራስ ምታት ወይም ሳል ሁሉ፤ ነስርም በሰውነታችን ውስጥ የሆነ ነገር መለወጡን ወይም መነካቱን የሚጠቁምበት መንገድ ነው። ለምሳሌ የአየር መድረቅ፣ አፍንጫን በሃይል መጥረግ፣ የደም ግፊት መጨመር፣ ወይም አንዳንድ የጤና እክሎች ከአፍንጫችን ደም እንዲፈስ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ለነስር (ለአፍንጫ ደም መፍሰስ) ዋና ዋና መንስኤዎች
ቀደም ሲል እንዳየነው ነስር ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን የሌላ ነገር ምልክት ነው። ታዲያ ይህ ምልክት እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉት ዋና ዋና መንስኤዎች ምንድናቸው? ነገሩን ቀለል አድርገን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፦ አልፎ አልፎ የሚከሰት ነስርን የሚያመጡ በሽታዎች እና ለተደጋጋሚ ነስር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ብለን።
አልፎ አልፎ ለሚከሰት ድንገተኛ ነስር መንስኤዎች

አብዛኛውን ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ አንዴ ወይም ሁለቴ ለሚያጋጥመን ተራ ነስር መንስኤ የሚሆኑት በአካባቢያችን ያሉ ወይም ቀላሉ የጤና ለውጦች ናቸው። እነሱም፦
የአየር መድረቅ፦ በተለይ በብርድ ወራት ወይም የአየር እርጥበት በጣም በሚቀንስበት ጊዜ፣ በአፍንጫችን ውስጥ ያለው ስስ ሽፋን ይደርቃል፣ ይሰነጠቃል፤ ከዚያም በቀላሉ ይደማል።
የአፍንጫ መጎርጎር ወይም በኃይል መጥረግ፦ በአፍንጫ ውስጥ ያሉትን በጣም ስስ የሆኑ የደም ስሮች በጣታችን ወይም በኃይል በመጥረግ በቀላሉ ልንጎዳቸው እንችላለን። ለዚህም ሊደሙ ይችላሉ።
ጉንፋን እና አለርጂ፦ በተደጋጋሚ አፍንጫን መጥረግ፣ ማስነጠስ እና የአፍንጫ መታፈን የደም ስሮቹ እንዲያብጡና በቀላሉ እንዲፈነዱ ያደርጋል።
ድንገተኛ አደጋ፦ በአፍንጫ ወይም በፊት ላይ የሚደርስ ማንኛውም ዓይነት መመታት ወይም መጋጨት ደም እንዲፈስ ያደርጋል።
በተደጋጋሚ ለሚከሰት ነስር መንስኤዎች

ነገር ግን ነስሩ እየቆየ፤ በተደጋጋሚ (ለምሳሌ በሳምንት ወይም በወር ውስጥ ብዙ ጊዜ) የሚመጣ ከሆነ፤ ነገሩን በቀላሉ ማየት የለብንም። ይህ አይነቱ ተደጋጋሚ ነስር በሰውነታችን ውስጥ ያለን የጤና እክል ሊጠቁም ይችላል። ለዚህም የሚያጋልጡ ዋነኞቹ መንስኤዎች የሚከተሉት ናቸው፦
የደም ማቅጠኛ መድኃኒቶች፦ እንደ አስፕሪን (Aspirin) ወይም ሌሎች ለልብና ለደም ሥር ህክምና የሚወሰዱ የደም ማቅጠኛዎች፣ ደም የመርጋት አቅምን ስለሚቀንሱ ተደጋጋሚ ነስር ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የደም ግፊት በሽታ፦ ቁጥጥሩ ያልተጠበቀ ከፍተኛ የደም ግፊት በሚኖርበት ጊዜ፤ በአፍንጫ ውስጥ ያሉት ደካማ የደም ስሮች ግፊቱን መቋቋም አቅቷቸው በተደጋጋሚ ሊፈነዱ ይችላሉ።
ደም የመርጋት እክሎች ፦ እንደ ሄሞፊሊያ (Hemophilia) ወይም ቮን ዊሊብራንድ (von Willebrand disease) ያሉ በደማችን ውስጥ ፕሌትሌትን አልያም ደም የሚያረጋጉ ፕሮቲኖች እንዲቀንሱ የሚያደርጉ በዘር የሚተላለፉ የጤና እክሎች ነስር ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የአፍንጫ ውስጥ መዋቅራዊ ችግሮች፦ የአፍንጫ አጥንት መጣመም (Deviated Septum) ወይም በአፍንጫ ውስጥ ያሉ እድገቶች (Nasal Polyps) የአየር ዝውውሩን በማስተጓጎል፤ አፍንጫ እንዲደርቅ በማድረግ ተደጋጋሚ ደም መፍሰስ ያመጣሉ።
የጉበት ወይም የኩላሊት በሽታዎች፦ ጉበታችን ደም እንዲረጋ የሚያደርጉ ፕሮቲኖችን የማምረት አቅሙ ሲዳከምም፤ ሰውነታችን በቀላሉ መደማት ይጀምራል።
አንዳንድ የደም ስር በሽታዎች እና ካንሰር፦ አንዳንድ የደም ስር በሽታዎች እንዲሁም አልፎ አልፎ እንደ ሌውኬሚያ (Leukemia) ያሉ የደም ካንሰሮች ተደጋጋሚ ነስርን እንደ መጀመሪያ ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ።

አብዛኛውን ጊዜ በተለይ በሕፃናትና በወጣቶች ላይ የሚከሰተው ተደጋጋሚ ነስር "ምክንያቱ የማይታወቅና ጉዳት የሌለው" ነው።
ነስሩ ምንም ዓይነት የጤና አደጋ ሳይፈጥር ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ በራሱ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል። ስለዚህ ወደ ሕክምና ሄዶ መመርመር የሚያስፈልገው ከበድ ያሉ የጤና እክሎች አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ እንጂ፤ ነስሩ በራሱ ሁልጊዜ አስፈሪ በመሆኑ እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል።
❌ ነስር ሲነሳ በፍጹም ማድረግ የሌለብን ስህተቶች

ነስር ድንገት ሲነሳ በቤት ውስጥ የምናደርገው የመጀመሪያ እርዳታ የሁኔታውን ክብደት በእጅጉ ይወስነዋል። አብዛኛውን ጊዜ ደሙን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ማቆም የምንችለው ትክክለኛውን እርምጃ ስንከተል ብቻ ነው። ለዚህም ነስር ሲያጋጥምዎ የሚከተሉትን ባያደርጉ ይመረጣል!
ጭንቅላትን ወደ ኋላ ማዘንበል፦ ይህ የለመድነው ትልቁ ስህተት ነው። ጭንቅላትን ወደ ኋላ ማዘንበል ደሙን አያቆመውም። ይልቁኑ ደሙ ወደ ሳንባ እና ወደ ሆድ እንዲወርድ በማድረግ ለትውከት፣ ለሳል ወይም ለመታፈን አደጋ ይጋብዛል።
መተኛት ወይም ጋደም ማለት፦ ልክ ጭንቅላትን ወደ ኋላ እንደማዘንበል ሁሉ፤ መተኛትም የደም ግፊትን በአፍንጫ አካባቢ ስለሚጨምር፤ ደሙ ይበልጥ እንዲፈስ እና ወደ ጉሮሮ እንዲወርድ ያደርጋል።

አፍንጫን በሶፍት ወይም በጨርቅ መድፈን፦ ደሙን ለመከላከል በሚል ጥቅልል ሶፍትን/ጨርቅን አፍንጫ ውስጥ መክተት አይገባም። እነዚህም ለጊዜው ደሙን ቢያስቆሙት እንኳን፤ ሲወጡ የረጋውን ደም አብረው ስለሚያነሱት፤ ነስሩ ዳግመኛ እንዲቀሰቀስ ያደርጋሉ።
ነስሩ ከቆመ በኋላ አፍንጫን መንካት ወይም መጎርጎር፦ ደሙ ከቆመ በኋላ ባሉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ አፍንጫን በኃይል መጥረግ፤ መጎርጎር ወይም በኃይል መተንፈስ የቆሰሉትን የደም ስሮች መልሶ ሊያደማቸው ይችላል።
ማድረግ ያለብን ትክክለኛ እርምጃዎች

1️⃣ ቀጥ ብለው ቁጭ ይበሉ እና ጭንቅላትዎን ወደ ፊት ትንሽ ያዘንብሉ።
ለምን? ጭንቅላትን ወደ ፊት ማዘንበል ደሙ ወደ ጉሮሮዎ እንዳይፈስ ያደርጋል። ደም ወደ ሆድዎ ከገባ ማቅለሽለሽና ማስታወክ ሊያስከትል ስለሚችል ወደ አፍዎ የመጣውን ደም በሙሉ ይትፉት እንጂ በፍጹም አይዋጡት።
2️⃣ የአፍንጫዎን ለስላሳ ክፍል ይጫኑ።
እንዴት? ከአፍንጫው ጠንካራ አጥንት በታች ያለውን ለስላሳ ክፍል በአውራ ጣትና በጠቋሚ ጣትዎ አጥብቀው ይያዙ።
ዋናው ሚስጥር፦ ሁለቱንም የአፍንጫ ቀዳዳዎች ዘግተው ለ10–15 ደቂቃ ሳይለቁ (ሰዓት እያዩ) ተጭነው መያዝ አለብዎት። በዚህ ጊዜ በአፍዎ ይተንፍሱ። ደሙ ቆሟል ወይ ለማየት በየደቂቃው እጅዎን እየለቀቁ አይዩ። ይህ ቶሎ እንዳይረጋ ያደርጋል።

3️⃣በረዶ መጠቀም።
በረዶ በጨርቅ ጠቅልለው ወይም ቀዝቃዛ ጨርቅ ከአፍንጫዎ በላይ፤ በግንባርዎ ወይም በአንገትዎ ጀርባ ላይ ማድረግ፤ የደም ሥሮቹ እንዲኮማተሩ ያደርጋል። ይህም ደሙ ቶሎ እንዲቆም ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
ደሙ ከቆመ በኋላስ?
ደሙ ከቆመ በኋላ ቢያንስ ለጥቂት ሰዓታት ከባድ ዕቃዎችን ከማንሳት፣ ጎንበስ ቀና ከማለት ወይም ኃይለኛ ስፖርት ከመሥራት መቆጠብ ያስፈልጋል።
🚨 አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አደገኛ ምልክቶች)
ምንም እንኳን አብዛኛው ጊዜ ነስር ቀላልና በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥንቃቄ ሊቆም የሚችል ቢሆንም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አደገኛ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ።

የሚከተሉት ምልክቶች ካጋጠሙዎት በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የሕክምና ተቋም በአስቸኳይ መሄድ ይኖርብዎታል፦
ከ20 ደቂቃ በላይ ከቀጠለ፦ ከላይ የተጠቀሱትን ትክክለኛ እርምጃዎች ተከትለው፤ አፍንጫዎን ሳይለቁ ለሁለት ጊዜያት (ለተከታታይ 10-15 ደቂቃዎች) ተጭነው ይዘውት አሁንም ደሙ መቆም ካልቻለ፤
ከባድ የደም መፍሰስ ካለ፦ የሚፈሰው የደም መጠን በጣም ከፍተኛ ከሆነና ለመተንፈስ አስቸጋሪ እየሆነ ከመጣ፤

ከአደጋ በኋላ የመጣ ከሆነ፦ ነስሩ የተከሰተው በጭንቅላት ወይም በፊት ላይ በደረሰ ከባድ ድንገተኛ አደጋ (መኪና ግጭት፣ መውደቅ ወይም መመታት) ምክንያት ከሆነ፤
ተጓዳኝ አስፈሪ ምልክቶች ካሉ፦ ከነስሩ ጋር አብሮ ራስን መሳት፣ ማዞር፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ የልብ ምት መዛባት፣ የትንፋሽ ማጠር ወይም በጣም መገርጣት ከታየ፤
ደም ከሌላ የሰውነት ክፍል ጋር የሚወጣ ከሆነ፦ ከአፍንጫ በተጨማሪ ደም ከሌላ የሰውነት ክፍል የሚወጣ ከሆነ፤
አቅራቢያዎ ያለ የጤና ተቋም ይሂዱ።
📌 ዋናው ነገር...
ነስር ሲያጋጥምዎ አይደናገጡ!
ሁልጊዜ እነዚህን ሦስት ነገሮች ያስታውሱ፦ ቁጭ ይበሉ፣ ጭንቅላትዎን ወደ ፊት ያዘንብሉ፣ የአፍንጫዎን ለስላሳ ክፍል ለ15 ደቂቃ ሳያቋርጡ ይጫኑ!
ጤናዎን ይጠብቁ። ለሌሎችም ያካፍሉ!




Comments