🫁 ትንፋሽ ማጠር ሁሉ የሳንባ ችግር ነው?
ድንገት አንድ ቀን ደረጃ ሲወጡ ፤ ገና ጥቂት እርምጃዎችን እንደወጡ ያልተለመደ ነገር ተሰማዎት እንበል። ደረትዎ ላይ ጨነቅዎት፣ አየር አጠርዎ፣ ልብዎም በፍጥነት መምታት ጀመረ ።

በዚያ ቅጽበት በአእምሮዎ ውስጥ የሚመጣው የመጀመሪያው ሃሳብ ምንድን ነው?
“ሳንባዬ ላይ ችግር አለ መሰል” ብለው ያስባሉ?
ወይም ደግሞ በሌሊት በአልጋዎ ላይ በሰላም ተኝተው፤ በድንገት የታፈኑ ያህል ከእንቅልፍዎ የሚያባንን ያህል አየር ቢያጥርዎ፤ ተነስተው ቁጭ ይላሉ። ይህን ጊዜ
“አስም ይሆን? ወይስ የሳንባ ምች?” ብለው ይጨነቃሉ።
ይህ የብዙዎቻችን ቅጽበታዊ ድምዳሜ ነው። ነገር ግን እዚህ ላይ ቆም ብለን ልንጠይቀው የሚገባ አንድ እጅግ ወሳኝ የሕክምና እውነት አለ፦
🤔 ትንፋሽ ማጠር ሁሉ ከሳንባ የሚመጣ ነውን?

አጭሩ እና አስገራሚው መልስ፦ በፍጹም አይደለም።
እውነት ነው! ትንፋሽ ማጠር (Dyspnea) ሳንባ ላይ ከባድ ችግር ሲኖር ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን የሰውነታችን ውስብስብ መዋቅር የሚያሳየን ሳንባ የዚህ ታሪክ መጀመሪያ እና መጨረሻ አለመሆኑን ነው።
አንዳንድ ጊዜ ልብዎ፣ ደምዎ፣ ጡንቻዎችዎ፣ አጠቃላይ የሰውነትዎ የአካል ብቃት ወይም እንዲያውም ስውር የሆነ የጭንቀት ስሜት ከትንፋሽ ማጠሩ በስተጀርባ ሆነው ገመዱን የሚጎትቱ መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
በመጀመሪያ የሳንባን ሚናን እንይ

እርግጥ ነው፣ የመጀመሪያውን ጥርጣሬ ወደ ሳንባ ማድረጉ ስህተት አይደለም። ጥቂት የማይባሉ የትንፋሽ ማጠር ምልክቶች ከሳንባ ጤና መቃወስ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው።
ለአብነት ያህል፦
አስም (Asthma)፦ የአየር ቧንቧዎች መጥበብና መቆጣት የአየር ዝውውሩን ሲገቱት የሚፈጠር ሲሆን፤ ከአየር መለወጥ እንዲሁም ሳንባን የሚያስቆጡ ነገሮች በማጋጠማቸው የተነሳ፤ ከፍተኛ የአየር ማጠር ሊያስከትል ይችላል።
የሳንባ ኢንፌክሽን (Pneumonia)፦ ሳንባ ሲቆጣ፤ የአየር መተንፈሻ አካላት (alveoli) ስራቸውን በስርአት ለመፈጸም ስለሚቸገሩ ትንፋሽ ማጠር ሊያጋጥም ይችላል።
የረጅም የቆዩ የሳንባ በሽታዎች (COPD)፦ በተለይ በሲጋራ ጭስ ወይም በበካይ አየር ምክንያት የሚደርሱ ቋሚ የሳንባ ጉዳቶች ፤ የትንፋሽ ማጠር ስሜት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የሳንባ የደም ስር መዘጋት (Pulmonary Embolism)፦ በሳንባ የደም ቧንቧ ውስጥ ድንገተኛ የደም መዘጋት ሲፈጠር፤ በዚያ ደም ስር የሚመገቡ የሳንባ ክፍሎች ስራቸውን እንዳይሰሩ ይሰናከላሉ። ይህም ድንገተኛ ትንፋሽ ማጠርን ሊያስከትል ይችላል። ሆኖም ግን ይህ በጣም አስቸኳይ የሕክምና ክትትል የሚሻ ነው።

በእነዚህ ሁኔታዎች የሰውነታችን የኦክስጅን ፍላጎትና የአተነፋፈስ ስርዓት ይዛባል። አንጎላችንም ይህንን ለውጥ እንደ ‘ትንፋሽ እያጠረኝ ነው’ ሊያስሰማን ይችላል። ግን ይህ ስሜት የሚፈጠርበት መንገድ እንደ መንስኤው ይለያያል።
ለምሳሌ፦ ሳንባ ወደ ደም ውስጥ የሚያስገባው የኦክስጅን መጠንና የሚያስወጣው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ይዛባል። በዚህ ጊዜ አንጎላችን ፈጣን መልዕክት በመላክ ሰውነታችን የበለጠ አየር እንዲወስድ ያዝዛል። ይህ ትዕዛዝ በኛ ስሜት ውስጥ “አየር እያጣሁ ነው” ወይም “ትንፋሽ አጠረኝ” የሚል የመድረስ ስሜት ይፈጥራል።
ነገር ግን የትንፋሽ እጥረት ምስጢር እዚህ ላይ ብቻ አያበቃም።
❤️ አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ልብ ነው!

ልብ እና ሳንባ የማይነጣጠሉ የሰውነት ክፍሎች ናቸው። ሳንባ አየር ሲቀበል፤ ልብ ደግሞ ያንን አየር (ኦክስጅን) በደም አማካኝነት ወደ መላው የሰውነት ክፍል የሚያሰራጭ ዋናው ፓምፕ ነው።
ልብዎ በተለያዩ ምክንያቶች (ለምሳሌ በደም ግፊት፣ በልብ ቧንቧ ችግር ወይም በልብ ጡንቻ መዳከም ምክንያት) ደምን በአግባቡ መርጨት ካልቻለ ምን የሚፈጠር ይመስልዎታል?
ደም ወደ ኋላ ይመለሳል። ይህ ወደ ኋላ የሚመለሰው ፈሳሽ ደግሞ በቀጥታ በሳንባ አካባቢ መከማቸት ይጀምራል።

ይህ ክስተት የሳንባን የአየር ልውውጥ ስለሚረብሸው ከባድ የትንፋሽ እጥረት ያስከትላል። በተለይም የሚከተሉትን ምልክቶች ካስተዋሉ ችግሩ ከሳንባ ይልቅ ከልብ የመነጨ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፦
በተለመደው እንቅስቃሴ (ለምሳሌ እርምጃዎች) ላይ እንኳን ሳይቀር ትንፋሽ መቆራረጥ።
ደረጃ ሲወጡ ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ መድከም።
በጀርባዎ በሚተኙበት ጊዜ ትንፋሽ ማጠር (ትራስ ደግፈው ቁጭ ሲሉ ግን መሻል።)
በሌሊት በከባድ የትንፋሽ ማጠር ስሜት ደንግጦ መንቃት።
ከትንፋሽ ማጠሩ ጋር አብሮ የእግር ወይም የቁርጭምጭሚት እብጠት መታየት።
ስለዚህ “ትንፋሽ አጠረኝ ማለት የሳንባ ችግር ብቻ ነው” ብሎ መደምደም የልብን ጤና ችላ ማለት ሊሆን ይችላል።
እንግዲህ ደምስ?

ይህ እውነታ ለብዙ ሰዎች አዲስና አስገራሚ ሊሆን ይችላል። ኦክስጅንን ተሸክሞ ከመላው ሰውነት የሚያደርሰው የደማችን ክፍል (ሄሞግሎቢን) ነው።
በሰውነትዎ ውስጥ የደም ማነስ (Anemia) ካለ፤ በደማችሁ ውስጥ ያለው የኦክስጅን ተሸካሚ አካል ቁጥር ያንሳል። በዚህ ጊዜ ሳንባዎ ምንም ያህል ጤናማ ቢሆንና በቂ ኦክስጅን ቢስብም፤ ያንን ኦክስጅን ወደ ህዋሳት የሚያደርሰው የደም አቅም ይዳከማል።
ህዋሳትም የኦክስጅን ረሃብ ሲያጋጥማቸው ለልብና ለሳንባ የጭንቀት ጥሪ ያስተላልፋሉ።ሰውነታችንም ይህንን ለመካካስ የልብ ምትንና አተነፋፈስን ሊያፋጥን ይችላል።
ይህ ሁኔታ በተለይ ሰውየው ሲራመድ፣ ደረጃ ሲወጣ ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በጉልህ ይታያል። ከትንፋሽ ማጠሩ በተጨማሪ ከፍተኛ ድካም፣ የልብ ምት መፍጠን፣ ራስ ምታት፣ አይን ብዥ ማለት፣ ጆሮ ላይ የሚያቃጭል ድምጽ መስማት፣ እንዲሁም የቆዳ እና የከንፈር መገርጣት ካለ፤ ምክንያቱ የደም ማነስ ሊሆን ይችላል።
“ጭንቀት ብቻ ” ቢሆንስ?

አእምሯችን እና አካላችን እጅግ የተሳሰሩ ናቸው። ከፍተኛ የጭንቀት ስሜት፣ ስጋት ወይም ድንገተኛ የፍርሃት ስሜት (Panic Attack) በሚያጋጥምበት ጊዜ ሰውነታችን አደጋ ውስጥ እንዳለ በማሰብ "ለመዋጋት ወይም ለመሸሽ" (Fight or Flight) ይዘጋጃል።
በዚህ ጊዜ የልብ ምት ይጨምራል። የደረት ጡንቻዎች ይወጠራሉ። እናም ሳናስተውለው ጥልቀት የሌለው ፈጣን አተነፋፈስ (Hyperventilation) ይኖረናል። ይህም አየር እንዳጠረን እንዲሰማን ያደርገናል።
ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስተዋል አለብዎ!
“ይህማ የጭንቀት ስሜት ነው” ብሎ በራስ መወሰን እጅግ አደገኛ ነው።
በተለይ የትንፋሽ ማጠሩ አዲስ ከሆነ፣ ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት ከሄደ፣ ወይም ከጭንቀት ስሜቱ ውጭ ባሉ ጊዜያትም የሚከሰት ከሆነ ፤ ጭንቀት ነው ከማለት በፊት ፤ ሌሎች አሳሳቢ የጤና እክሎች አለመኖራቸው በሕክምና ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
መቼ ነው አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልገው?

ትንፋሽ ማጠር ተራ ምቾት ማጣት ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ የህይወትና የሞት ጉዳይ ምልክት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በቤት ውስጥ ተቀምጠው፤ ትንፋሽ ማጠር ካጋጠምዎ ችላ አይበሉ። በተለይም መታገስ የሌለብዎ እና ወዲያውኑ ወደ አስቸኳይ ህክምና መሄድ የሚገባዎት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦
በድንገት እና ያለምንም ምክንያት ከባድ የትንፋሽ ማጠር ከተከሰተ፤
ከትንፋሽ ማጠሩ ጋር የደረት ህመም፣ ደረት ላይ የመጫን ስሜት ወይም ወደ ትከሻና መንጋጋ የሚሄድ ህመም ካለ፤
ከንፈርዎ፣ ምላስዎ ወይም ጥፍርዎ ሰማያዊ/ግራጫ መልክ ከያዙ (ከፍተኛ የኦክስጅን እጥረትን ያሳያል)፤
አብርዎት ከፍተኛ የመደናገር፣ የመቅበዝበዝ ወይም የመሳት ስሜት ከተከተለ፤
ሳል ሲስሉ ደም የተቀላቀለበት አክታ የሚወጣ ከሆነ፤
እነዚህ ምልክቶች ከታዩ የትኛውንም ሰዓት ሳይጠብቁ አቅራቢያዎ ወዳለ ጤና ተቋም ይሂዱ!
በአጭሩ…
ትንፋሽ ማጠር ማለት የሳንባ ችግር ብቻ ማለት አይደለም። ከዚህ ምልክት በስተጀርባ፦ ሳንባ፣ ልብ፣ ደም፣ የአእምሮ ጭንቀት፣ የአካል ብቃት ማነስ እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

ስለዚህ ትንፋሽዎ በተደጋጋሚ እያጠረዎት ከሆነ፣ በቀድሞ ጊዜ በቀላሉ የሚያከናውኑት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አሁን እያደከመዎት ከመጣ፤ በራስዎ መድሐኒት ከመውሰድ፤ የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
ፈጽመው አይዘናጉ! ጤናዎን ይጠብቁ!




Comments