የትራኮማ የዓይን በሽታ በኢትዮጵያ:- መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና መከላከያ መንገዶች
- Zebeaman Tibebu
- 17 minutes ago
- 4 min read
"ዕውርነት አንዳንድ ጊዜ ሕክምና ሊደረግለት ከሚችል እና በቀላሉ መከላከል ከሚቻል የዓይን ኢንፌክሽን ይጀምራል።"
በኢትዮጵያ ከሚገኝ አንድ ገጠራማ መንደር የምትኖር የ6 ዓመት ሕፃን ልጅን በዓይነ ሕሊናዎ ያስቡ። በየቀኑ ወደ ትምህርት ቤት የምትጓዝበት መንገድ በአቧራ የተሸፈነ ነው። በአካባቢዋ ንጹህ ውሃ በቀላሉ ስለማይገኝ ፤ ፊቷን በየቀኑ መታጠብ የቅንጦት ያህል ይከብዳታል። ዝንቦችም ሁልጊዜ በዓይኖቿና በፊቷ ዙሪያ ይሰበሰባሉ።

አንድ ቀን ዓይኖቿ በድንገት ቀሉ። ከባድ ማሳከክና እንባ ማፍሰስ ጀመሩ። ቤተሰቦቿ እንደ ማናቸውም ጊዜ "ቀላል የዓይን መቆጣት ነው፣ ውሎ አድሮም ይሻላታል" ብለው በቸልታ አለፉት። ህመሙ ግን ፈጽሞ አልጠፋም ነበር። ይልቁንም በየሳምንቱና በየወራቱ ደጋግሞ መመላለስ ጀመረ።
ዓመታት ነጎዱ። ያ ተደጋጋሚ የአይን ኢንፌክሽን በዓይኗ ውስጠኛ ሽፋን ላይ ጠባሳ መፍጠር ጀመረ። የዐይን ሽፋሽፍቶቿም ወደ ውስጥ ተገልብጠው ማደግ ጀመሩ። ለዚህም የአይኗ ሽፋሽፍት ዓይኗን በከደነች እና በከፈተች ቁጥር ፤ ዓይኗን መቧጨር ጀመሩ። ይህም በጊዜ ውስጥ የአይኗን መስታወት ፤ በጠባሳ ምክንያት ሸፈነው።
ሕፃኗም ሙሉ በሙሉ ብርሃኗን አጣች።
ይህ አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ የደረሰው ዘመናዊ ሕክምና ስለሌለ ሳይሆን፤ መፍትሔው በጊዜው ወደ እሷ ሊደርስ ስላልቻለ ብቻ ነበር!
ይህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀይረው ትራኮማ በሽታ ይባላል። በዓለማችን ላይ ለዕውርነት የሚዳርግ ዋነኛው ተላላፊ የዓይን በሽታ ነው። ባኢትዮጵያም ብዙዎችን ያጠቃል።
ዛሬ ስለ ትራኮማ በጥልቀት እናንሳ!
ትራኮማ ምንድን ነው? እንዴትስ ይሰራጫል?

ትራኮማ ክላሚዲያ ትራኮማቲስ (Chlamydia trachomatis) በተባለ ባክቴሪያ የሚከሰት ሲሆን፤ ተደጋጋሚ የአይን ኢንፌክሽንን ተከትሎ፤ ለዕውርነት የሚዳርግ አደገኛ የዓይን በሽታ ነው። ይህ ባክቴሪያ በሦስት መንገዶች ይተላለፋል።
በቀጥታ ንክኪ፦ በበሽታው ከተያዘ ሰው የሚወጣ እንባ ወይም የአፍንጫ ፈሳሽ ጋር በቀጥታ በሚኖር ግንኙነት ሊተላለፍ ይችላል።
ቁሳቁስ በመጋራት፦ የታመመ ሰው የተጠቀመበትን ፎጣ፣ አልባሳት፣ አንሶላ፣ ብርድልብስ ወይም ሌሎች የግል ዕቃዎችን በጋራ በመጠቀምም ሊተላለፍ ይችላል።
በዝንቦች ምክንያት፦ በዓይን ፈሳሽ ላይ የሚያርፉ ዝንቦች ፤ ባክቴሪያውን ከአንድ ታማሚ ሰው ተሸክመው፤ ወደ ጤናማ ሰው ፊት ላይ ሲያስተላልፉ ይችላሉ።
በዚህ ዑደት ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ ተጎጂዎች ሕጻናት እና እናቶች ናቸው። ሕፃናት የበሽታው ዋነኛ ምንጭ ሲሆኑ፤ እናቶች ደግሞ ለሕጻናት ባላቸው ቅርበት ወይም ከህጻናቱ ጋር በሚኖራቸው የማያቋርጥ ንክኪ፤ ምክንያት ለበሽታው የመጋለጥና ብርሃናቸውን የማጣት ዕድላቸውከፍተኛ ነው።
ትራኮማ እንዴት ወደ ዕውርነት ያደርሳል?
በሽታው በአንድ ጀምበር ብርሃንን አይሰርቅም። ዕውርነት ከማምጣቱ በፊት በአራት ደረጃዎች ማለፍ ይኖርበታል።

የመጀመሪያው ደረጃ ኢንፌክሽን ነው።
በዚህ ደረጃ ዓይን ይቀላል፣ ያብጣል፣ እንባ ይፈሳል፣ ማሳከክ ይኖራል፣ እናም ታማሚዎች ብርሃን ይፈራሉ። የአይን ሽፋሽቶች ስርም ትናንሽ እብጠቶች ይታያሉ።
ቀጣዩ ደረጃ የጠባሳ መፈጠር ነው።
እያንዳንዱ ኢንፌክሽን በዓይን ውስጥ ቁስል ይፈጥራል። ሲደጋገም በዓመታት ውስጥ ይህ ቁስል ጠባሳ ሆኖ፤ የዐይን ሽፋሽፍት ቆዳ እንዲጠብ/እንዲያጥር ያደርጋል።

ቀጥሎም የዐይን ሽፋሽፍት ወደ ውስጥ ይታጠፋል (Trichiasis)
የውስጠኛው ጠባሳ ሲጠብቅና ሲሸበሸብ፤ የዐይን ሽፋሽፍቶች ወደ ውስጥ ተገልብጠው ወደ ዓይን ያድጋሉ። እያንዳንዱ የዓይን መከደን የዓይንን መስታወትን ይቧጭራል። ታካሚዎች ህመሙን "ዓይንን በመርፌ እንደመወጋት ፤አልያም አይን ውስጥ አሸዋ እንዳለ" አይነት ስሜት አድርገው ይገልጹታል። ሕመሙ እጅግ ከባድ ሊሆን ይችላል።
በቋሚነት ኮርኒያ ይጎዳል(Corneal Opacity)
ደጋግሞ መቧጨር የዓይንን መስታወት (ኮርኒያ) በነጭ ጠባሳ እንዲሸፈን ያደርገዋል። አይን ይታወራል። በዚህ ደረጃ የጠፋውን እይታ መልሶ ማግኘት አይቻልም።
የበሽታው ስርጭት በኢትዮጵያ ምን ይመስላል?
ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የትራኮማ ከፍተኛ ጫና ካለባቸው አገሮች መካከል አንዷ ሆና ትጠቀሳለች። ይባስ ብሎም በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙት አጠቃላይ የትራኮማ ተጠቂዎች መካከል፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚኖሩት እዚሁ ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ፤ እውነታው ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ያሳየናል። በአሁኑ ወቅት ከ61 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በሽታው በስፋት በሚገኝባቸው አደገኛ አካባቢዎች የሚኖሩ ሲሆን፤ በተለይም በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል (የቀድሞው) ገጠር አካባቢዎች በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለመሆኑ ይሄ በሽታ በአሁኑም ዘመን የኢትዮጵያን ማህበረሰብ እያጠቃ ያለው ለምንድን ነው?
ምክንያቱም ይህ በሽታ የሚኖረው በድህነትና በንጽህና ጉድለት ጥላ ስር ነው። ንጹህ ውሃ በቀላሉ በማይገኝበት የገጠር አካባቢ፤ ፊትን በየቀኑ መታጠብ አስቸጋሪ ይሆናል(በተለይ ለህጻናት)። ደካማ የአካባቢ ንጽህና ደግሞ ፤ባክቴሪያውን ተሸክመው የሚበሩትንና በሽታውን የሚያስፋፉትን ዝንቦች እንዲባዙ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በዚያ ላይ ሰዎች በጠባብ ቤቶች ውስጥ በብዛት በሚኖሩበት ሁኔታ፤ በተለይም ብዙ ሕፃናት በአንድ ላይ በሚተኙበትና በሚጫወቱበት ወቅት፤ ባክቴሪያው ከአንዱ ወደ ሌላው ሳይታወቅ በዝምታና በፍጥነት ይሰራጫል። ለዚህ ነው በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የበሽታው ስርጭት አሁንም ድረስ አሳሳቢና ከፍተኛ ሆኖ የቀጠለው።
💊 ሕክምና አለው?

መልሱ አጭርና ግልጽ ነው—አዎ!
ትራኮማ ገና በጊዜ ከደረሱበት በቀላሉ ሊሸነፍ የሚችል በሽታ ነው። ነገር ግን ሕክምናው እንደ በሽታው ደረጃ ይለያያል፦
በመጀመሪያው ደረጃ ከሆነ ያለው ፤ ባክቴሪያውን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የባክቴሪያ መቃወሚያ የሆነው የአዚትሮማይሲን (Azithromycin) አንቲባዮቲክ መድኃኒት ይሰጣል። ይህ መድኃኒት ባክቴሪያውን በመግደል፤ ለበሽታው ፈውስ ይሰጣል።
በሽታው ያለው በላቀ ደረጃ ከሆነ፤ የዐይን ሽፋሽፍቶቹ ወደ ውስጥ ተገልብጠው የዓይንን ብሌን መቧጨር ሲጀምሩ፤ መፍትሔው ቀላል ቀዶ ጥገና ማድረግ ነው። ይህ ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ የሚወስድ ቀላል ቀዶ ጥገና ፤ የዐይን ሽፋኑን ወደ ነበረበት በማስተካከል ሕፃናትንና እናቶችን ከዕውርነት ይታደጋል።
ሆኖም ግን የዓይን መስታወት (ኮርኒያው) በተከታታይ ጭረት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከቆሰለና በነጭ ጠባሳ ከተሸፈነ ፤ የጠፋውን እይታ መልሶ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል።
🛡️ ትራኮማን እንዴት መከላከል ይቻላል? የአለም ጤና ድርጅት መፍትሔ
ትራኮማን ከሀገራችን ምድር ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት፤ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) SAFE የተባለ አራት መዓዘናትን ያቀፈ ፤ እጅግ ስኬታማ ስልት እንድንጠቀም ይመክራል። ከእነኝህ ስልቶች መሃከል ከፊሉን ከላይ አንስተናል። ስልቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

S – Surgery (የዐይን ሽፋሽፍት ቀዶ ጥገና)፦ በሽታው ጸንቶባቸው ሽፋሽፍቶቻቸው ወደ ውስጥ ለታጠፈባቸው ወገኖች፤ እንደ አስፈላጊነቱ ፈጣንና ቀላል ቀዶ ጥገና በማድረግ የዓይን መስታወት ከመቆሰሉና ለዕውርነት ከመጋለጡ በፊት እንድንታደግ ይመክራል።
A – Antibiotics (የአንቲባዮቲክ መድኃኒት መስጠት)፦ ይህ በመድሐኒት ባክቴሪያውን በሰውነት ውስጥ ማጥፋት ነው። በሽታው ባለባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ማህበረሰቦች መድኃኒቱን በጅምላ በመስጠት፤ ኢንፌክሽኑን መፈወስና ስርጭቱን በእጅጉ መቀነስ ይመክራል።
F – Facial Cleanliness (የፊት ንጽህና መጠበቅ)፦ ዝንቦች ወደ ፊት እንዳይጠጉና ባክቴሪያው እንዳይጋባ ማድረግ ይመክራል። ለዚህም በተለይ የሕፃናትን ፊት በየቀኑ በንጹህ ውሃና በሳሙና ማጠብ ቁልፍ ተግባር ነው።
E – Environmental Improvement (የአካባቢ ንጽህና መጠበቅ)፦ የበሽታውን መሸጋገሪያ መንገዶችን መዝጋትም ይመከራል ። ይህንን ለማሳካት የሚከተሉት ሦስት ተግባራት ወሳኝ ናቸው፦
ንጹህ ውሃን ለዕለት ተዕለት ፍጆታና ለንጽህና በአግባቡ መጠቀም፣
የመጸዳጃ ቤት ንጽህናን መጠበቅና ሁልጊዜም ቢሆን በመጸዳጃ ቤት ብቻ መጸዳዳት፣
የአካባቢን ቆሻሻ በአግባቡ በማስወገድ በሽታ አምጪ ዝንቦችን መቀነስና እንዳይራቡ ማድረግ ይመከራል።
🚨 ያስተውሉ!
ትራኮማ ቀላል የዓይን መቅላት ወይም ተራ መቆጣት ብቻ አይደለም። ለዓመታት ሳይታወቅ ቆይቶ ፤ በዝምታ እይታን የሚሰርቅ በሽታ ነው።
ነገር ግን መከላከል ይቻላል። የግል እና አከባቢ ንጽህናን ይጠብቁ። ምልክቶቹን እንዳዩ አቅራቢያ ወዳለ ጤና ተቋም ይሂዱ።




Comments