top of page

የምሽት አይነስውርነት እና ቪታሚን ኤ

ለመሆኑ ዳፍንት ሲባል ሰምተው ያውቃሉ?

በማታ ሲሄዱ ከብዙ ነገሮች ጋር ይጋጫሉ?

ከብርሀን ጨለም ወዳለ ክፍል ሲገቡ አይኖት ለመላመድ ከሌላው ሰው የበለጠ ጊዜ ይወስዳልን?

የምሽት አይነስውርነት ቢኖርቦትስ?

👁️ ለመሆኑ የምሽት ዓይነ ስውርነት ምንድን ነው?

የምሽት ዓይነ ስውርነት በተለምዶ ስሙ ዳፍንት ሲባል ፤ በህክምና ስሙ ኒካታሎፒያ (ናይት ብላይንድነስ) ተብሎ ይጠራል። ይህም ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን ከስር ያለ ህመም ምልክት ነው። ይህ ምልክት መታየቱ ከስር የተደበቀ የምግብ አለመመጣጠን ችግር ማመላካቻ ሊሆን ይችላል።  ላስተዋለ አይናችን ላይ ቋሚ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ፤ አመጋገባችንን እንድናስተካክል የማስጠንቀቂያ ጥሪ ነው።። 

ዳፍንት ከቪታሚኢን ኤ እጥረት ባሻገር ከዘረመል ጋር በሚያይዙ የአይን ህመሞች ፣ በአይን ሞራ፣ በግላኮማ፣ በስኳር ህመም፣ በአንዳንድ መድሀኒቶች ፣ ወ.ዘ.ተ... ሊመጣ ይችላል። እንዲሁም ቪታሚን ኤ ወደ ደም የሚገባበት የጨጓራ ክፍል ቀዶ ህክምና ያደረጉ ሰዎችም ይህንን የህመም ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ።


ከእነኝህ መሀል ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋው ፤ ከቪታሚአን ኤ እጥረት ጋር የተያያዘው የምሽት አይነ ስውርነት ህመም ነው። ይህም በብዛት የሚስተዋለው ህጻናት እና እርጉዝ ሴቶች ላይ ነው።


ይሄ የምግብ መዛባትን አመላካች የሆነ የማንቂያ ጥሪ ነው።

ቪታሚን ኤ ለአይናችን ምን ጠቀሜታ አለው?

አይናችን ጀርባ ላይ የሚገኝ ፤ ብርሀንን የማንበብ አቅም ያለው ፤ ሬቲና የሚባል ሥሥ አካል አለ። ይህ አካል ስራውን በስርአት እንዲሰራ ቪታሚን ኤ ያስፈልገዋል።


ቪታሚአን ኤ ይህ አካል ካሉት ህዋሳት ውስጥ ሮድስ ለተባሉት ህዋሳት ቪታሚን ኤ አስፈላጊ ነው። እነኝህ ህዋሳት በጨለማ(በደበዘዘ ብርሀን) ውስጥ አጥርተን እንድናይ ያስችሉናል። ቪታሚን ኤ ሰውነታችን ውስጥ ሲያንስ ፤ እነኝ ህዋሳት በደበዘዘ/ደካማ ብርሀን ውስጥ ማየት ያዳግታቸዋል። ለዚህም የማታ/ምሽት ጊዜ እይታ ይሰናከላል።


በቂ የቪታሚን ኤ ካለ ፤ ሮድስ ስራቸውን መስራት ስለሚችሉ ፤ እይታዎ የጠራ ይሆናል።

👁️ ከምሽት ዓይነ ስውርነት ባሻገር


የቪታሚን ኤ እጥረት ዳፋ በምሽት አይነ ስውርነትና በአይን ብቻ አያበቃም። የበሽታ መከላከል ስርአታችን ይዳከማል። ለኢንፌክሽን ተጋላጨነት ይጨምራል።

ቪታሚን ኤ እጥረት አይን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት (በግራ ቢቶት ስፖትና በቀኝ የኮርኒያ ጠባሳ/ቁስለት)
ቪታሚን ኤ እጥረት አይን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት (በግራ ቢቶት ስፖትና በቀኝ የኮርኒያ ጠባሳ/ቁስለት)

አይን ላይ እራሱ እስከ ቋሚ አይነ ስውርነት የሚያደርስ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። አይን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በአራት ደረጃ ሊከፈል ይችላል።


  • የመጀመሪያው ደረጃ የምሽት ዓይነ ስውርነት ነው። ለዚህ ነው ማስጠንቀቂያ ነው የሚባለው)


  • ሁለተኛ ደረጃ ሲደርስ አይን ይደርቃል። ለዚህም አይን ያቃጥላል ፣ ያሳክካል ፣ በቀላሉም ይቆጣል።


  • ሶስተኛ ደረጃ ሲደርስ አይን ላይ እንግዳ የሆኑ ነጫጭ ስጋዎች ማደግ ይጀምራሉ። በህክምና ስማቸው የቢቶት ነጠብጣቦች (bitot spots) ይባላሉ።


እስከዚህ ደረጃ አይን ላይ የደረሰው ጉዳት በህክምና እርዳታ/ በቪታሚን ኤ እገዛ ሊመለስ/ሊገለበጥ ይችላል።

  • ከዚህ ከባሰ የአይናችን ነጩ ክፍል (ኮርኒያ) ይቆስላል። ጠባሳ ያመጣል። የዚህን ጊዜ አይናችን ላይ ያለው ጉዳት ቋሚ ይሆናል። ህክምና ካልተደረገ እና ቪታሚን ኤ ካልተሰጠ ሙሉ ዓይነ ስውርነት ደረጃ ሊደርስ ይችላል።


አመጋገብን በማስተካከል ይህንን ሁሉ መከላከል ይቻላል።

🌑 የዳፍንት ምልክቶች ምንድን ናቸው?


  • ዝቅተኛ ብርሃን ባለባቸው ስፍራዎች ወይም ጨለም ሲል (ሲመሸ/ሲነጋ) ያለ የእይታ ችግር ።


  • ከደማቅ ብርሀን ወደ ደብዛዛ ስፍራ (ከጸሀይ ወደ ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል) ሲገቡ ፤ አይንዎ ለመላመድ ረዥም ጊዜ መውሰድ።


  • ደካማ ብርሃን ባለባቸው (ጨለም ባሉ) ቦታዎች ላይ ሲንቀሳቀሱ ፤ ከነገሮች ጋር መጋጨት ፣ መደናቀፍ እና መውደቅ።


  • ለዚህም ይህ ህመም ምልክት ያለባቸው ሰዎች መሸት ሲል ወይም ለሊት ላይ ለመንቀሳቀስ ይፈራሉ


ታድያ ላላስታዋለ ሰው እነኝህ ምልክቶች በቸልታ ይታለፋሉ። ይህም ደግሞ ከስር ያለው በሽታ ያለ ህክምና እርዳታ እንዲደረጅ እድል ይሰጣል።


📉 የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ

የቪታሚን ኤ እጥረት አለም አቀፍ ስርጭት (ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስርጭት ካላቸው ሀገራት ትታያለች)  ከዱቦክ 2024 የተወሰደ
የቪታሚን ኤ እጥረት አለም አቀፍ ስርጭት (ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስርጭት ካላቸው ሀገራት ትታያለች) ከዱቦክ 2024 የተወሰደ

ኢትዮጵያ ከ 5 አመት በታች ባሉ ህጻናት ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እጅጉን የተንሰራፋ ነው። ላለፉት አስርት አመታት የአለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ብዙ ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆንም ፤ የቫይታሚን ኤ እጥረት በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛ 3 ንጥረ ነገር እጥረቶች መሀል ይጠቀሳል። ለዚህም ብዙ ይቀረናል።


እ.ኤ.አ. በ 2022 የኢትዮጵያ የስነ-ሕዝብ እና ጤና ዳሰሳ እና የዓለም ጤና ድርጅት ባቀረቡት መረጃ መሠረት፡-


🚸 ከ5 ከ 5አመት በታች ከሆኑ ህጻናት መሀከል ቢያንስ አንዱ የቫይታሚን ኤ እጥረት አለበት።


👩‍🍼 ከ3 ነፍሰ ጡር እናቶች መካከል አንዷ ቪታሚን ኤ እጥረት ይኖርባታል። ይህም የልጇን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል።


⚰️ የቫይታሚን ኤ እጥረት በየአመቱ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ህጻናት ሞት ምክንያት ነው። ይህንን ሞት ግን መከላከል ይቻላል።


ቫይታሚን ኤ ያጠረው ህጻን የበሽታ የመከላከል አቅሙ ስለሚዳከም ፤ የእንደ ኩፍኝ፣ ተቅማጥ ወይም የሳምባ ምች ባሉ የተለመዱ ኢንፌክሽኖች የመሞት እድሉ በ20-30% የበለጠ ነው።


🚨 ይህ ለምን እየሆነ ነው?

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአመጋገብ ረገድ እድገት አሳይታለች። ሆኖም ግን የቪታሚን ኤ እጥረት በተለይ በገጠራማ አከባቢዎች እንዲሁም ግጭት ባለባቸው አከባቢዎች ፤ እየተንሰራፋ ይገኛል። ለምን?


  • የ አመጋገብ ባህላችን አንድ ወጥ በመሆኑ፡ ብዙ ጊዜ የምንመገበው ምግብ ተመሳሳይ ነው። የተለያየ የምግብ አይነቶችን ደባልቀን አንመገብም። ለዚህም ዝቅተኛ የ ቫይታሚን ኤ መጠን ያላቸው ምግቦችን (እንጀራ፣ምስር ፣ ሽሮ ፣ ወ.ዘ.ተ) አዘውተረን እንመገባለን።


  • ረሃብና ድርቅ፡ በሀገራችን በተለያዩ ስፍራዎች እየተነሱ ያሉት ድርቅ እና ረሀብ የምግብ ዋስትናችንን እያዳከሙት ይገኛሉ። በዚህም አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች የቪታሚን ኤ እጥረት ቢኖርባቸው አይደንቅም።


  • የአስተሳሰብ ክፍተት ፡- ህጻናት ሲመገቡ እንቁላል፣ ጉበት ወይም አትክልት ቅድሚያ አይሰጥም።


  • ዝቅተኛ ግንዛቤ፡ የዳፍንት ህመም ምልክት ብዙ ጊዜ በቸልተኝነት ይታለፋል።


  • እንዲሁም የተለያየ ጊዜ እየተነሳ ያለው የኩፍኝ ወረርሽን በበኩሉ ይህንን የቪታሚን ኤ እጥረት እያባባሰ ይገኛል።


🥕 ቫይታሚን ኤ ከየት ማግኘት እንችላለን?


ቪታሚን ኤን በተፈጥሮ ከብዙ አይነት ምግቦች ማግኘት እንችላለን። ከእንሰሳት እንዲሁም ከእጽዋት ምንጮች ልናገኘው እንችላለን። እንደ ጉበት፣ እንቁላል አስኳል፣ ወተት፣ አሳ አይነት የእንሰሳት ተዋጽኦዎች በሬቲኖል በሚባለው የቪታሚን ኤ የበለጸጉ ናቸው። አረንጓዴ ቅጠላማ ተክሎች (ስፒናች፣ የአበሻ ጎመን፣ ጥቅል ጎመን) እና ቢጫ/ቡርትካናማ ተክሎች (ዱባ፣ካሮት፣ ማንጎ፣ ስኳር ድንች) ካሮቲኖይድ የተባለው ቅድመ ቪታሚን ኤ በውስጣቸው አለ።


ታድያ የእርስዎ እና የቤተሰብዎ አመጋገብ ላይ እነኝህን ምግቦች ቢደባልቁስ? የግድ እለት ተእለት መጠቀም የለብዎትም።

በየሁለት ቀኑ የተቀቀለ እንቁላል ወይም የተቀቀለ ጎመን እንኳን ከሰጡ ፤ በልጅዎ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል።



💉 በሀገራችን ምን እየተደረገ ነው? ምንስ ይጎድላል ?

የቫይታሚን ኤ ዘመቻ፡- የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ዩኒሴፍ ለልጆች ከፍተኛ መጠን ያለው የቫይታሚን ኤ ተጨማሪ ምግቦችን በአመት ሁለት ጊዜ ይሰጣሉ። ይህ ህይወትን ቢያድንም ፤ በቂ አይደለም።.


የስነ-ምግብ ምክር፡- እናቶችን በአመጋገብ ዙሪያ በጤና ባለሙያዎች ትምህርት እየተሰጣቸው ይገኛል። ሆኖም ግን የዚህ ትምህርት የማህበረሰብ ተደራሽነት ውስን ነው።


✅ የበለፀጉ ምግቦች፡- በቫይታሚን ኤ የበለፀጉ ምግቦች ለማህበረሰብ እየቀረቡ ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ ለገጠሩ ማህበረሰብ በቀላሉ የማይገኙ ወይም የማይገዙ ናቸው።


የአደጋ ጊዜ የኩፍኝ ምላሽ፡ የኩፍኝ ወረርሽኝ የሚያክሙ ቡድኖች ፤ አሁን የቫይታሚን እንክብሎችን እንደ ድንገተኛ መድህኒቶች አካተው ይይዛሉ።


ሆኖም ግን እንደሀገር የሚያስፈልገን ክኒን ብቻ አይደለም። የባህልና የባህሪ ለውጥ ነው።

🌱 እርስዎስ ምን ያድርጉ?


👩‍🌾 በቤትዎ ዙሪያ ባለ የአትክልት ስፍራ በቫይታሚን ኤ የበለጸጉ እጽዋትን ይትከሉ።


🐓ለልጅዎ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ እንቁላል ፣ አሳ አልያም ጉበትን ይመግቡ።


🍼 የጡት ወተት የሕፃን የመጀመሪያ የቫይታሚን ኤ ምንጭ ስለሆነ ፤ ጡት ማጥባትን ይደግፉ።


💉 ልጅዎ የኩፍኝ ክትባት መውሰዱን ያረጋግጡ። ማንኛውም ልጅ ኩፍኝ በሽታን ፈጽሞ ያለ መከላከያ ሊገጥመው አይገባም።


🗣️ የመጨረሻ ቃል፡


ማንኛውም ልጅ በቪታሚን ኤ እጥረት ፤ አይኑን ሆነ ህይወቱን ማጣት የለበትም።


የቫይታሚን ኤ እጥረት እጣ ፈንታ አይደለም.።


በልጅዎ አመጋገብ ላይ ዛሬውኑ ተግባራዊ ለውጥ ያምጡ። የልጅዎን ጤና ያድሱ።


Comments


bottom of page