የኪንታሮት ህመም ፡ ምን ማድረግ ይኖርብዎታል?
- Zebeaman Tibebu
- May 4
- 4 min read
መጸዳጃ ቤት መሄድ ፈርተው ያውቃሉን? መጸዳጃ ቤት መሔድ እንዲፈሩ የሚያደርግ ህመም አጋጥሞት ያውቃልን?
እስቲ አስቡት ...
መጸዳጃ ቤት መሔድ ከመፍራቶት የተነሳ እየተሳቀቁ የሚመገቡ ቢሆንስ?

ይህ ብዙ ጎልማሳ ኢትዮጵያውያንን የሚያጠቃ በሽታ በተለምዶ ኪንታሮት ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ፤ በህክምና ደግሞ ሔሞሮይድስ ይባላል። በተለያየ ምክንያት የሚመጣ ፤ ብዙ የዘመናዊ ህክምና አማራጭ ያለው ቢሆንም ፤ ብዙዎች የባህል ህክምናን የሚመርጡለት ህመም ነው። በኢትዮጵያ ስለህመሙ መጠን ሀገር አቀፍ መረጃ ባይኖርም ፤ በጎንደር ዩንቨርስቲ ሆስፒታል ከታከሙ የቀዶ ህክምና ታካሚዎች 13 ፕርሰንት አከባቢ የሚሆኑት ፤ እንዲሁም በመቀሌ አይደር ሆስፒታል በአንጀት እና ጨጓራ ክፍል ከሚታዩት መካከል ደግሞ እሰከ 7 ፐርሰንት የሚሆኑት በኪንታሮት ይሰቃያሉ። ይህ ቁጥር የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ አያሳይም። ሆኖም ግን ፤ ሀገር አቀፍ መጠኑ ከዚህ እንደሚያልፍ መገመት ይቻላል።
ታድያ ይህ የኪንታሮት ህመም ምንድነው?
የኪንታሮት ሀመም በፊንጢጣ አከባቢ ያሉ የደም ስሮች (የደም መልስ ደምስሮች / veins) በተለያየ ምክንያት ሲወጠሩ/ሲታፈኑ የሚመጣ ህመም ነው። እነዚህ ደም መላሽ ደምስሮች ሰገራን ለመቆጣጠር በሚረዳ ፤ ተፈጥሮአዊ ስፖንጅ በሚመስል አካል የተደገፉ ናቸው። ሆኖም ግን በአንድ ሆነ በተለያየ ምክንያት እዛ አከባቢ ያሉ የደም ስሮች ጫና ሲያጋጥማቸው/ግፊት ሲጨምርባቸው/ ሲታፈኑ ፤ እንደፊኛ መወጠር ግድ ይሆንባቸዋል። ታድያ ይህ የተወጠሩ ደምስሮች ከጀርባቸው ቦታ ስለሌለ ፤ የሚወጠሩት ወደ ፊንጢጣ ቱቦ ነው። ለዚህም በአይናችን ስንመለከት የኪንታሮት እብጠት እናያለን።

መቼም በአንድ ምክንያት ይሁን በሌላ አብዛኞቻችን ደም ሰጥተን እናውቃለን። ስለዚህ እንዲህ ብላችሁ አስቡት...
ደም የሚወስደው ባለሙያ ደም ስር እንዲታይ ክንዳችን ላይ ከፍ ብሎ ሲያስር ፤ በሙሉ እጃችን መኖራቸውን እንኳን የማናቃቸው ደምስሮች አብጠው ወይም አፍጥጠው ይወጣሉ። ይህም ደም ስራችንን ወደቆዳችን ቅርብ ስለሚያደርገው ፤በቀላሉ ደም ለመቅዳት ይመቻል።
ታድያስ በበፊንጢጣ በኩል ያሉት ደምስሮች ጋር የሚያጋጥመው ይህ ነው። ከላይ በተለያየ ምክንያት የታሰሩ የደም ስሮች ያብጣሉ። እነኝህ ደምስሮች ግን የሚያብጡት ወደ ፊንጢጣ ውስጥ በመሆኑ ፤ ሰገራ ሲወጣ እብጠቱን እየተሻሸው ወይም እየፈተገው ይሆናል። ይህም ሲደጋገምም እብጠቱን ያቆስለዋል። የፊንጢጣን ስጋ አልፎ ደም ስር ጋር ቁስሉ ከደረሰ ደግሞ ፤ ለማቆም የሚያስቸግር ደም መፍሰስ ከፊንጢጣ አከባቢ ሊታይ ይችላል።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
በዚህም የተነሳ የኪንታሮት ምልክቶች ማየት ይጀምራሉ። ከሚያዩዋቸው ምልክቶች በጥቂቶቹ፡

መጸዳጃ ቤት ሲቀመጡ የሚብስ የህመም ስሜት
ፊንጢጣ አከባቢ ያለ እብጠት
ፊንጢጣ ጋር ማሳከክ
ደም የቀላቀለ ሰገራ
ከፊንጢጣ የሚወጣ ደም ሊኖር ይችላል።
አይነቶቹ ምን ምን ናቸው?
ታድያ ግን የሚታዩት ምልክቶች እንደአለብን የኪንታሮት ህመም አይነት ይለያያሉ። ኪንታሮት በአጠቃላይ ለሁለት ይከፍላል።
ውስጠኛው ኪንታሮት(Internal Hemorrhoid)-የፊንጢጣ ውስጠኛው ክፍል ያለ ሲሆን ከእይታም ከንክኪም የራቀ ነው። ከእብጠቱ ባሻገር ብዙ ጊዜህመም የለውም ። ነገር ግን ሰገራ ሲወጣ በጣም ስለሚፈትገው ፤ ይህንን ተከትሎ የደም መፍሰስ ምልክት ሊያሳይ ይችላል።
ውጫዊ ኪንታሮት(External Hemorrhoid)- ይህ ፊንጢጣ ውጭ ክፍል ላይ የሚገኝ የኪንታሮት አይነት ሲሆን ፤ቦታው በነርቮች የበለጸገ በመሆኑ ፤ ህመሙም ጠንከር ያለ ነው። ህመሙም እነኝህ ደም ስሮቹም በረጋ ደም ሲዘጉ ሊያይል ይችላል። የማሳከክ ምልክትም ሊያሳይ ይችላል።
ለምን ይከሰታል?
ከላይ እንደተወያየነው ኪንታሮት ህመም የእነኝህ ደምስሮችን መንገድ ሊያፍኑ በሚችሉ ምክንያቶች ሊክሰሰት ይችላል። ለዚህም የሚያጋልጡ የተለያዩ ልማዶች እና የጤና እክሎች እክሎች አሉ። ለምሳሌ

መጸዳጃ ቤት አብዝቶ መቀመጥ
ማማጥ
አሰር (fiber)የሌላቸውን ምግቦች ማዘውተር
ስር የሰደደ የሰገራ ድርቀት ወይም ተቀማጥ
ከመጠን ያለፈ ውፍረት
እርግዝና
ካንሰር
አብዘቶ መጸዳጃ ቤት መቀመጥ
የህክምና አማራጮቹ
ይህንን በሽታ ማከም የሚያስችሉ የተለያዩ የህክምና አማራጮች አሉ። የህክምናው ውጤታማነት ግን ፤ ህመሙ እንደ ተገኘበት ደረጃ እና እንደታካሚው የህክምና ክትትል ይለያያል። ታካሚው ዶክተሩ ያለውን በስርአት የሚፈጽም ከሆነ ፤ አመርቂ ለውጥ ማየት ይቻላል። ያሉት የህክምና አማራጮች የሚከተሉት ናቸው።

የህይወት ዘይቤን ማስተካከል
በአሰር የበለጸጉ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ(እንደ አትክልት፣ ጥራጥሬ እና ፍራፍሬ ያሉ)፤ ሰገራ በቀላሉ እንዲወርድ ከማገዝ ባሻገር ድርቀትንም ይከላከላሉ። ለዚህም የህመሙም ምልክት ይቀንሳል።
መጸዳጃ ቤትን ሁልጊዜ በተመሳሳይ ሰአት መጠቀም ፤ ጭንቅላታችን እንዲዘጋጅ ስለሚያደርገው ፤ ፊንጢጣችን ላይ ምንም ጫና ሳይኖር ፤ በቀላሉ መጠቀም እንድንችል ያደርገናል።
መጸዳጃ ቤት ሲጠቀሙ ብዙ አይቆዩ። የመጸዳጃ ሰአት ይገድቡ። እንዲህ ካደረጉ ፊንጢጣ አከባቢ ያለ ጫና ይቀንሳሉ።
ጭንቀትን መቀነስ ። በተለይ መጸዳጃ በሚቀመጡበት ሰአት ከራስዎ ጭንቀትን ያስወግዱ። ይህም የምግብ ቱቦ ዘና እንዲል በማድረጉ ፤ በቀላሉ ሰገራ እንዲወጣ ያግዛል።
በቂ ውሃ መጠጣት ሰገራ እንዳይደርቅ ስለሚያደርግ ፤ የኪንታሮት ህመም ምልክትን ይቀንሳል።
አዘውትረው የስፖርታዊ እንቅስቃሴን ያድርጉ።
ኪንታሮቱ ከቆሰለ፣ ከተቆጣ፣ ህመሙ ከባሰ ፤ ዶክተርዎን አማክረው ለብ ባለ ዉሀ (በመጠኑ ጨው መጨመር ይቻላል።) ውስጥ በመቀመጥ/በመዘፍዘፍ ህመምዎን በቤትዎም ማከም ይችላሉ። ይህም እነኝህ ደምስሮች እንዲያርፉ፣ የደም ዝውውር እንዲጨምር፣ የፊንጢጣ አከባቢ እንዲጸዳ ከማድረጉም ባሻገር የተቆጣው/ የቆሰለው ኪንታሮት እንዲጠግን ያግዘዋል።
መድሀኒቶች እና ቅባቶች
ከዚህም ባሻገር ፤ ፊንጢጣ አከባቢ የሚደረጉ ፤ ምልክቶቹን መቀነስ የሚችሉ የኪንታሮት ቅባቶች አሉ። እነኝህን ቅባቶች በቀላሉ በቅርብዎ ካለ ፋርማሲ ገዝተው መጠቀም ይችላሉ።
ህመሙን ለማስታገስ ፤ የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶችንም መውሰድ ይቻላሉ።
የሰገራ ድርቀትን ለመቀነስና የአንጀት እንቅስቃሴን ለማሻሻል ደግሞ ፤ የሰገራ ማለስለሻ መድሀኒቶችን መጠቀም ይችላሉ። ይህም የህመም ምልክቶችን ይቀንሳል።
የኪንታሮት ደምስሮችን የሚያኮመሽሹ ህክምና አማራጮች
ህመሙ ትንሽ ገፋ ያለ ከሆነ እና እላይ ላየናቸው አማራጮች የማይመለስ ከሆነ፡
ኪንታሮት የመቋጠር ህክምና ፡ በዚህ ህክምና የኪንታሮቱን እብጠት ከስር በመቋጠር ፤ መጋቢ ደምስሮችን በመዝጋት ፤ ኪንታሮቱ እንዲጠፋ ፤ ምልክቶቹ እንዲቀንሱ ማድረግ ይችላል።
ስክለሮቴራፒ፡ የኪንታሮቱን ደም ስር ማድረቂያ መድሀኒት በመውጋት ኪንታሮቱ እንዲጠፋ የሚያደርግ ህክምና ነው።
የኢንፍራሬድ ኮአጎሌሽ ወይም የጨረር ህክምና፡ ይህ ህክምና ኪንታሮቱን በጨረር በመምታት እንዲጠፋ ያደርጋል።

የቀዶ ህክምና አማራጮች
ያበጡትን የኪንታሮት ደም ስሮች በ ቀዶ ህክምና ቆርጦ በማውጣት ለኪንታሮት ህመም ዘላቂ መፍትሔ ማማጣት ይቻላል።
ታድያ የታከምኩት ኪንታሮት ተመልሶ የሚመጣው ለምንድነው?
ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። ታክመው ከሄዱ በኋላ ኪንታሮት መልሶ እየመጣ የሚያስቸግራቸው ጥቂቶች አይደሉም። በዘመናዊ ህክምና አማራጭ ተስፋ ቆርጠው ባህላዊ መፍትሔም የሚፈልጉ አለ። ታድይ ለምን?
እላይ የጠቀስናቸው የህክምና አማራጮች በሙሉ በውጤታማነት ኪንታሮትን ሊያክሙ ይችላሉ። ይህ በአለም ዙሪያ በተደረጉ ጥናቶች የተደገፈ ነው። የኪንታሮት ህክምና የሚያኮመሽሸው ወይም ቆርጦ የሚያወጣው አሁን ያበጠውን የደም ስር ነው። ይህ የደም ስር ስለወጣ መልሶ ኪንታሮት አያመጣም። ነገርግን ለኪንታሮት አጋላጭ ምክንያቶች ከጀርባ እስካሉ ድረስ ፤ የተቀሩት በፊት ያላበጡት የደምስሮች በተመሳሳይ ሁኔታ አብጠው ፤ ኪንታሮት ማምጣታቸው አይቀርም።
የቅድሙ ምሳሌ ብንጠቀም ፤ ክንዳችን ላይ ያለው ማሰሪያ እስካልተነሳ ድረስ ፤ እጃችን ላይ ያሉ ደምስሮች ማበጣቸው አይቀርም። በጣም ያበጠውን የደም ስር ብናወጣም እንኳን ፤ የተቀሩት የደም ስሮች በተመሳሳይ ሁኔት ማበጣቸው አይቀርም።
ለዚህም እርሶ ከህክምናው በኋላ የኪንታሮት ህመም እንዳያጋጥምዎ መከላከል ይኖርብዎታል። ለመከላከል የሚከተሉትን ያድርጉ።
ለኪንታሮት አጋላጭ ህመሞች ካሉ ክትትል አድርጎ መቆጣጠር
ጭንቀት መቀነስ
መጸዳጃ ቤት ሁሌ በተመሳሳይ ሰአት መሄድ ፤ ሄደውም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መጠቀም
መጸዳጃ ቤት ሲጠቀሙ አለማማጥ
አሰር የበዛበት ምግብ ማዘውተር እና ውሀ አብዝቶ መጠጣት
ማሳረጊያ ሀሳብ
እንዲህ በቀላሉ በሚቆጣጠሩት ህመም ፤ ሲበሉ ሆነ መጸዳጃ ቤት ሲሄዱ ፤ መሳቀቅ አይገባዎትም።
የኪንታሮት ህመም ምልክት ካለብዎ ፤ አቅራቢያዎ ወዳለ ጤና ተቋም ሄደው ተገቢውን ህክምና ያድርጉ።
የኪንታሮት ህክምና የሚጀምረው ከቤትዎ መሆኑን ያስተውሉ።
የኑሮ ዘይቤዎን አስተካክለው ፤ ኪንታሮትን ማጥፋት ወይም መከላከል ይችላሉ።
ሁልጊዜም ለጤናዎ ቦት ይስጡ።
Comments