በጉሮሮ ህመም ምክንያት የሚመጣው የልብ ህመም ስጋት፡ የተግባር ጥሪ
- Zebeaman Tibebu
- Mar 31
- 3 min read

የጉሮሮ ህመምን ተከትሎ የሚመጣ የልብ ህመም እንዳለ ያውቁ ኖሯል?
ባብዛኞቻችን እንደቀላል የምናየው ፤ በህጻንነታችን ደግመን ደጋግመን የታመምነው የጉሮሮ መከርከር/መቆጣት ህመም ፤ በስርአት ካልታከመ ለልብ ህመም ይዳርጋል። ብዙጊዜ ቀለል እንዳለ ጉንፋን አድርገን የምናልፈው ህመም ፤ ከአመታት በኋላ ልባችንን ላይ መመለሻ የሌለው ጠንቅ ያመጣብናል።
እስቲ አስቡት...
አንድ ህጻን ልጅ በጉሮሮ ህመም ሲታመም የተመለከተ የቤተሰብ አባል ፤ "አይ! የተለመደ ጉንፋን ነው" ብሎ ፤ ብዙ ትኩረት አይሰጠውም። ልጁም ህመሙም ብሶበት በራሱ ጊዜ ይሻለዋል።
አሁን ወደፊት አንድ ወይም ሁለት አስርት አመት እንምጣ። ያ ጨቅላ አሁን አድጓል ፤ ትልቅ ሰው ሆኗል። ሆኖም ግን የድካም ስሜት አዘውትሮ መሰማት ይጀምረዋል። ቶሎ ይደክመዋል። ረዥም መንገድ ሲሄድ፣ ደረጃዎችን ሲወጣ፣ ከሱቅ እቃ ገዝቶ ሲመጣ ትንፋሽ ያጥረዋል። ከሰውነት ግዝፈት እንዲሁም እስፖርት ካለመስራት ጋር የተያያዘ ይመስለውና ፤ አሁንም ይዘናጋል። በጊዜ የህክምና ምርመራ አያደርግም።
እውነታው ያኔ በህጻንነቱ ጉሮሮውን ቢሻለውም ልቡ ግን አደጋ ላይ ነበረች። ላለፉት አስርት አመታት ልቡ ጥቃት ላይ ነበረች። በደንብ የተጎዳው ልቡም ስራዋን በትክክል መስራት ይሳናታል። የልብ ቧንቧዎቹም ይዳከማሉ። አሁን ይህ ወጣት የልብ ህመምተኛ ሆኗል። በህክምና ስሙ ክሮኒክ ሪዩማቲክ የልብ ህመም (CRVHD) ተይዟል።
አሳዛኙ እውነታ...
አብዛኛው የዚህ ህመም ታማሚዎች ሆስፒታል ለምርመራ የሚመጡት የልብ ድካም ሲያጋጥመው ነው።
ያስተውሉ...ይህ ታሪክ ብቻ አይደለም! ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ የሚያጋጥም እጅጉን አሳዛኝ እውነታ ነው። ይህንን በሚያነቡበት ጊዜ እራሱ የጉሮሮ ህመም ያለበትን ልጁን ቀላል ነው ብሎ እቤት አቆይቶታል።
በጸረ-ባክቴሪያ ታክሞ ፤ በቀናት ውስጥ የሚሻል ህመም ፤ ለምን ታክሞ የማይሽር የልብ ጠባሳ ለህይወት ያኖራል?
ይህ የልብ ህመም ምንድን ነው? ለምንስ ትኩረት መስጠት አለብዎ?
ይህ የልብ ህመም በህክምና ስሙ ክሮኒክ ሪዩማቲክ ቫልቩላር ኸርት ዲዚዝ ፤ ወይንም የልብ ቧንቧን የሚያጠቃ ለረዥም ጊዜ የቆየ የሪዩማቲክ ህመም ይባላል። ብዙ ጊዜ ይህ ህመም ከጉሮሮ እና ከቆዳ መቆጣት ጋር በሚነሳ ስትሬፕቶ ኮካስ (Streptococcus pyogenes) በሚባል ባክቴሪያ ጠንሳሽነት የሚመጣ ህመም ነው። ይህ ባክቴሪያ በቀላሉ እንደ አሞክሳሲሊን ባሉ የጸረ ባክቴሪያ ሊወገድ የሚችል ህመም ቢሆንም፤ ካልታከመ ጠንቁ እጅጉን ከባድ ነው።

የተሟላ ህክምና ያላገኘ ጊዜ ፤ የሰውነታችን ጠባቂ ሰራዊት የሆኑት ነጭ የደም ሴሎች ባክቴሪያውን አጥቅተው በ ውጤታማነት ከአካላችን ያስወግዱታል። ህመሙ ይጠፋል። እላይ እንዳለው ጨቅላ ተሽሎታል ተብሎ ይታሰባል። እውን ነው የጉሮሮ ህመሙ ተሽሎታል። ሆኖም ግን ፤ እባብ ያየ በልጥ በረየ እንዲሉ ፤ እነኝህ ነጭ የደም ህዋሳት የልብ ቧንቧ ጋር ሲደርሱ ፤ የልብ ቧንቧችን ህዋሳት ባክቴሪያው ጋር ተመሳስለውባቸው የልባችን ህዋሳትን ያጠቃሉ። አጥፍተው የሚሄዱት ባክቴሪያ ሳይሆን ፤ መሰረታቸውም መኖሪያቸውም ከልብ የሆኑ የሰውነታችን ህዋሳትን ያጠቃሉ። ለዚህም ከልካይ የለሹ የማያቋርጠው የእራስን ማጥቃት ጦርነት ልብ ላይ ይታወጃል። ልብም ጥቃቱን ችሎ ለአመታት ምንም ለውጥ ሳያሳይ ቢቆይም ፤ ከጊዜ በኋላ ግን ቋሚ ጠባሳ ይይዛል። ስራውም መስተጓጎል ይጀምራል። ህክምና እርዳታ ካላገኘ ፤ ልብም እጅጉን እየተዳከመ ይመጣል።
ቀላሉ የጉሮሮ ህመም ወደ ከባድ የልብ ችግር ይለወጣል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታ

ኢትዮጵያ አለም ላይ ካሉ ይህ ህመም በከፍተኛ ደረጃ ከተንሰራፋባችው ሀገራት አንዷ ናት። ይህ የልብ ህመም በሀገሪቷ ለልብ ድካም የሚያጋልጥ ፤ ዋነኛ ተጠቃሽ መንስኤ ነው። በመላ አገሪቱ ያሉት ሆስፒታሎች በዚህ ህመም በሚሰቃዩ ታካሚዎች ተሞልተዋል።
ለምሳሌ ፡-
በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተደረገ ጥናት የልብ ድካም ችግር ካለባቸው ሰዎች ከፍተኛ የሚሆኑት ይህ ህመም እንዳለባቸው ያመላክታል።
ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥም ካሉ የልብ ድካም ታካሚዎች ውስጥ የዚህ ህመም ታማሚዎች 30 ፐርሰንቱን ይይዛሉ።
በምስራቅ ኢትዮጵያ ሀረር ከተማ የተደረገ ጥናትም ከባድ የልብ ህመም ካለባቸው ህሙማን ውስጥ ግማሽ ያህሉ ይህ ህመም ጋር የተያያዘ መሆኑን ያሳያል።
ይህ ህመም ሁሉንም የእድሜ ክልል ሊያጠቃ ይችላል። ሆኖም ግን ለበሽታው ተጋላጭነት ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ላይ ያመዝናል። ያለን የጤና ተደራሽነት ውስን በሆነበት ሀገር ላይ የበሽታው ተጽእኖ የቤተሰብ ተንከባካቢ የሆኑት ሴቶች ላይ ማየሉ አሉታዊ ተጽእኖው የከፋ እንዲሆን ያደርገዋል።
ቀደም ብሎ ማወቅ፡ ህይወትን የማዳን ቁልፉ

በሽታውን መከላከል የሚቻል ቢሆንስ? ወደ ልብ ከመድረሱ በፊት መግታት ቢችሉ ምን ያደርጋሉ?
ከዚህ ህመም እና ጠንቁ ለመዳን ቁልፉ ቀድሞ እርምጃ መውሰድ ነው። የጉሮሮ ህመም ካልታከመ የሚያመጣው ጠንቅ መገንዘብ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህንን ግንዛቤ ማስጨበጥ ከቻልን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ህይወት ማዳን እንችላለን።
እራስዎን እና የሚወዷቸውን ሰዎች ለመጠበቅ ማድረግ የሚገባዎት ሶስት ነገሮች
የጉሮሮ በሽታን በፍጥነት ማከም፡- የጉሮሮ ህመም ቀላል የሆነ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ሲሆን በፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒት ሊታከም ይችላል። ነገር ግን ያለ ተገቢ እንክብካቤ ህመሙ ከቆየ የልብ ህመም ሊያመጣ ይችላል። ይህም በጊዜ ሂደት የልብ ቧንቧን እንዳይሰራ ያደርጋል። ስለዚህም ማንኛውም የጉሮሮ ህመም በትክክል ተመርምሮ በሙሉ መታከምን ያረጋግጡ።
መደበኛ ምርመራዎችን ያድርጉ፡- የልብ ህመሙ የከፋ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ምንም ምልክት አይሳይም። ማስጠንቀቂያ የለውም። ለዚህም የሪዩማቲክ የደም ምርመራ አድርገው ለበሽታው ተጋላጭነት እንዳለብዎት ማወቅ ይችላሉ። አዘውትሮ የልብ ምርመራ ማድረግም አስፈላጊ ነው።
ማህበረሰብህን ያስተምሩ፡- እውቀት ሃይል ነው። ብዙ ሰዎች የጉሮሮ በሽታዎችን ማከም የሚያስከትለውን አደጋ እና አስፈላጊነት በተረዱ መጠን ብዙ ህይወትን ማዳን እንችላለን። ስለዚህም በዙሪያዎት ያሉ ሰዎችን ግንዛቤ አስጭብጧቸው።
መደምደሚያ ሐሳብ፡
እንደተመለከትነው በሽታው ቀላል አይደለም። በሀገራችን ያለው እውነታ በጣም አሳሳቢ ነው። መፍትሄው ግን ግልጽ ነው።

ድርጅታችን ተግባር ኤድ ይህንን የበሽታውን አስከፊነት ተረድቶ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሁም በውጭ ካሉ አጋሮች ጋር በመተባበር ለውጥ ለማምጣት እየሰራ ይገኛል። ድርጅቱ በበሽታው ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ እንደ ሂሊንግ ቫልቭ ኢትዮጵያ ካሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ፣ እንዲሁም በዚህ የተጠቁ ታካሚዎችን በማገዝ ህይወትን ለማዳን እየሰራ ይገኛል።
እርስዎ ታድያ አሁን ምን ያደርጋሉ? እውቀት ወደ ተግባር ካልተለወጠ ምን ፋይዳ አለው?
ከዚህ ልብ ህመም (CRVHD) ጋር የሚደረገው ትግል ከእርስዎ ጋር ይጀምራል። ይህን መልእክት ሼር በማድረግ እውቀቱን አስፋፉ እና ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ። የኢትዮጵያን ልብ እንጠብቅ - አንድ ህይወት በአንድ ጊዜ እናድን።
አስበውታል .... ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን ቢያውቅ ኖሮ....ይህንን በሽታ ከኢትዮጵያ ምድር ይጠፋ ነበር። ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ጤና ደርጃ ላይ ይሆን ነበር።
Comments