top of page

የማሕበራዊ ሚዲያ አብዝቶ መጠቀም ጭንቅላት ላይ ያለው ተጽእኖ

አንድ መልእክት ለመፈተሽ ስልክዎን ያበራሉ። ስከንዶች በደቂቃዎች ፤ ደቂቃዎች በሰዓታት ይተካሉ። አውራ ጣትዎ ግን ማለቂያ በሌለው የሞባይል ስክሪን ላይ እንደ ማሽን መንቀሳቀሱን ይቀጥላል። ያለ አንዳች እረፍት፣ ለረዥም ጊዜ ከስልክዎ ውስጥ ይጠፋሉ።


እውነቱን ለመናገር..... እርስዎ ፈልገውት ወይም አስበውበት ባይመርጡትም ፤ አእምሮዎ ሳያውቁት ያንን አስገዳጅ ምርጫ በራሱ አድርጓል።

ለዚህም ሳያስቡት ቀጣዩን ምስል ወይም ፖስት ያያሉ። ቀጥሎም ሌላ.... ቀጥሎም ሌላ ለሰአታት ማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም ይቀጥላሉ።


ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ይህ የዕለት ተዕለት እውነታ ሆኗል። ተማሪዎች ደብተራቸውን ዘግተዋል፤ ባለሙያዎች ስራቸውን አቁመዋል፤ ቤተሰቦችም በአንድ ማዕድ ተቀምጠው እርስ በርስ ሳይነጋገሩ በየስልካቸው ባለው ዲጂታል ዓለም ተውጠዋል። ለመሆኑ ግን፦

ደጋግሞ ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም ፤ የሰውን ልጅ አንጎል መዋቅር ሊለውጠው ይችላል?

አዕምሮአችን እና ማህበራዊ ሚድያ


የሰው ልጅ አእምሮ ለሺህ ዓመታት በዝግመተ-ለውጥ ሂደት ውስጥ ተሻሽሎ የመጣው ለተወሰኑ፤ ጥረት ለሚጠይቁ እና ትርጉም ላላቸው ስራዎች ፤ ሽልማት/ምላሽ ለመስጠት ብቻ ነው። በጥንታዊው ታሪካችን ውስጥ አንጎላችን ዶፓሚን (Dopamine) የተባለውን የደስታ ሆርሞን እንደ ሽልማት የሚያመነጨው በከባድ ዋጋ ነበር። ለምሳሌ፦

  • ከረሃብ እና ከአደን በኋላ ምግብ ሲገኝ የሚሰማ ጥልቅ የእርካታ ስሜት፤

  • ከማህበራዊ ጥረት በኋላ ከጎሳ ወይም ከማህበረሰቡ የሚገኝ እውቅና እና ክብር ጊዜ፤

  • እንዲሁም ከላብ እና ከከባድ ሥራ በኋላ የሚገኝ ሰላማዊ እረፍት ለአእምሯችን ትልቅ ዋጋ ነበራቸው።

ባጭሩ፡ በጥንቱ ዓለም ሽልማት ለማግኘት ፤ ግዴታ መስራትና መልፋት ነበረብን።

ማህበራዊ ሚዲያ ግን ይህንን በጥንቃቄ የተገነባ የተፈጥሮ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ገለበጠው። አሁን ምንም አይነት ጉልበትና ጥረት ሳናወጣ፤ አእምሯችንን በሰው ሰራሽ የሽልማት ጋጋታ ማጥለቅለቅ ችለናል። መተግበሪያዎቹ አንጎላችን የሚጠማውን አዲስ መረጃ በየሰከንዱ፤ በነጻ እና ያለ ገደብ ያቀርቡለታል። በቅጽበት የምናገኛቸው የ"ላይክ" እና የአስተያየቶች ናዳ ደግሞ በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዳለን እንዲሰማን የሚያደርግ የሀሰት ስሜት ይፈጥራሉ። ይባስ ብሎም፤ ገጹን ወደ ታች በሳብን ቁጥር የሚመጣው አዲስ ይዘት አእምሯችን "በቃኝ" የሚልበትን የተፈጥሮ ማቆሚያ ነጥብ ሙሉ በሙሉ ያሳጣዋል።


አእምሯችን ለሺህ ዓመታት ከተለማመደው የተፈጥሮ ሕግ ውጪ፤ ይህንን በሰከንዶች ውስጥ የሚፈስ የዶፓሚን ጎርፍ መቋቋም አይችልም።

ውጤቱም ግልጽ ነው። እኛ የስልካችንን አጠቃቀም ለመቆጣጠር ሙሉ በሙሉ ተስኖናል።

ለምንድነው ስልክ አጠቃቀማችንን መቆጣጠር ያቃተን?


ዶፓሚን የተባለው ሆርሞን "ጉጉትን እና መሻትን" ይፈጥራል። ስልክዎን በከፈቱ ቁጥር እያንዳንዱ የደረሰዎት መልዕክት ወይም አዲስ ቪዲዮ እርካታን ሳይሆን ፤ "ቀጥሎ ምን አስደሳች ነገር ይኖር ይሆን?" የሚል መጠባበቅን ይወልዳል። የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎችም (ቲክቶክ፣ ፌስቡክ፣ ወ.ዘ.ተ) እኛን በቁጥጥራቸው ስር የሚያደርጉት ፤ ይህንን የስነልቦና ሳይንስ ተጠቅመው ነው። ድረ-ገጾቹን መጠቀም ሰልችቶን እንኳ ስልኩን ማስቀመጥ የሚያቅተን ለዚህ ነው። አእምሯችን እየፈለገ ያለው ያገኘውን እርካታ ሳይሆን፣ "ቀጥሎ ምን ይመጣል?" የሚለውን አዲስ ጉጉት ነው።


ይህ የማያቋርጥ ጉጉት ደግሞ በጊዜ ሂደት በአእምሯችን ላይ አካላዊ ለውጥ ማምጣት ይጀምራል። የሰው ልጅ አእምሮ በተፈጥሮው የመለዋወጥ እና እራሱን ከአዲስ ነገር ጋር የማላመድ ብቃት አለው። ይህን በህክምናው ኒውሮ ፕላስቲሲቲ (Neuroplasticity) እንለዋለን።



ለረዥም ጊዜ እነኝህን ማህበራዊ ድህረገጾች ስንጠቀም አእምሯችን የነርቭ አቀማመጡ ላይ አዲስ ለውጥ ያመጣል። በዚህም ምክንያት ስልኩን በፍጥነት የመፈተሽ ፍላጎታችን ሲጨምር፤ በተቃራኒው ደግሞ በአንድ ነገር ላይ ትኩረትን የመሰብሰብ እና ራስን የመግታት/የመቆጣጠር አቅማችን እየዛለ ይሄዳል። ከጊዜ በኋላ አእምሯችን አዳዲስ ማነቃቂያዎችን በፍጥነት የሚፈልግ፣ እምቢ ለማለት ግን የሚቸገር ይሆናል።

ይህ በሽታ ሳይሆን፤ አእምሮ ለቀረበለት አዲስ የዲጂታል ዓለም የሰጠው ተፈጥሯዊ ምላሽ ነው።

የሕክምና ሳይንስ ግን እዚህ ላይ ግልጽ የሆነ ልዩነት ያስቀምጣል።

ማህበራዊ ሚዲያን አዘውትሮ መጠቀም ብቻውን እንደ በሽታ አይቆጠርም።

ይህንን መረዳት አስፈላጊ ነው። ስጋት የሚፈጠረው አጠቃቀማችን ቁጥጥር ሳይኖረው ሲቀር ነው። ይህም የሚሆነው

  • በራስ ፈቃድ ለማቆም ፈልገው ስልኩን ማስቀመጥ ሲያቅትዎት፣

  • ስልኩ በእንቅልፍዎ፣ በስራዎ ወይም በትምህርትዎ ላይ እንቅፋት ሲሆን፣

  • እንዲሁም እንደ አይን እና የአንገት ህመም ያሉ ግልጽ ጉዳቶች እያጋጠሙዎት እንኳን ማቆም ሲሳንዎት ነው።


ችግሩ ቴክኖሎጂውን መጠቀም ላይ ሳይሆን፤ አጠቃቀማችንን መቆጣጠር ማቃቱ ላይ ነው።


የሚያመጣው ችግር


አጠቃቀማችንን ተከትሎ የሚመጣው የትኩረት መበታተን ደግሞ ፤ የአእምሯችን "ዋና ስራ አስኪያጅ" ተብሎ የሚታወቀውን የፊት ለፊቱን የአንጎል ክፍል (Prefrontal Cortex) በቀጥታ ይጎዳዋል። ይህ ክፍል ውሳኔ የመስጠት፣ ስሜትን የመቆጣጠር እና "አሁን ይበቃሃል፣ ስልክህን አስቀምጥ" የሚለውን የውስጥ መገደቢያ ድምፅ የሚያመነጭ ነው። ማለቂያ የሌለው የዲጂታል አጠቃቀም ፤ የዚህን መሪ ክፍል የማስተዳደር አቅም ያዝላል።


ለዚህ ነው አሁን አሁን መጽሐፍ ማንበብ፣ በጥልቀት ማጥናት፣ ወይም ረጅም ንግግሮችን መከታተል እጅግ እየከበደን የመጣው። ይህ የሚሆነው የማሰብ ችሎታችን ስለቀነሰ ሳይሆን፤ አእምሯችን ትኩረቱን በየሰከንዱ መቀያየር ስለለመደ ነው።


አእምሯችን ሌላ የሚከፍለው ትልቁ ዋጋ እንቅልፍ ነው። ሳይንስ እንደሚያስረዳው፤ በምሽት ከስልክ ስክሪን የሚወጣው ብርሃን ለሰውነታችን "የመተኛት ጊዜ ደርሷል" የሚል ምልክት እንዲሰጥ የሚያደርገውን ሜላቶኒን የተባለውን ሆርሞን ያግዳል። ይህ ሲሆን የሰውነት የተፈጥሮ የጊዜ ሰሌዳ ይናጋና እንቅልፍ ቢወስደንም እንኳ አእምሮ በትክክል ማረፍ ይሳነዋል።


ሊዚህም እረፍት የሚስጥ ጥሩ እንቅልፍ አንተኛም። ደካማ እንቅልፍ ደግሞ ፤ በነጋታው ትኩረትን ይበታትናል፤ ጭንቀትን የመቋቋም አቅምን ያዳክማል፤ ስሜታዊ ቁጥጥርንም ያሳጣል። ይህ በበኩሉ አብዝተን ስልክ እንድንጠቀም የሚያደርግ ሌላ አደገኛ አዙሪት ይፈጥራል።


ይህ አደገኛ አዙሪት በተለይ ገና እየተቀረጸ ባለው የህፃናት እና የወጣቶች አእምሮ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የከፋ ነው። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ አእምሮ ደግሞ ገና ተሰርቶ አላለቀም። ራስን የመግዛት ኃላፊነት ያለባቸው የአንጎል ክፍሎች ፤ እስከ 20ዎቹ አጋማሽ ድረስ እድገታቸውን አይጨርሱም። ለዚህም የስልክ አጠቃቀማችንን ማስተካከል፤ ለረጅም ጊዜ የነርቭ እድገት ወሳኝ ነው።


ይህ መላምት ብቻ አይደለም!


ዓለም አቀፍ ክሊኒካዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፦

  • በቀን ከሶስት ሰዓት በላይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፉ ታዳጊዎች፤ ለአእምሮ ጤና መታወክ፤ በተለይም ለድብርት እና ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው ፤ በሁለት እጥፍ የጨመረ ነው።

  • በተደጋጋሚ ለዲጂታል ማነቃቂያዎች በሚጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ፤ በትንሹ ከአስሩ አራቱ ላይ የጭንቀት እና የድብርት በሽታ ይታይባቸዋል

  • የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች (እንደ ፌስቡክ ያሉ) በስፋት ተደራሽ መሆን ብቻ በወጣቶች ላይ ከባድ የድብርት ስሜትን በ7%፤ እንዲሁም የጭንቀት መታወክ በሽታን (Anxiety Disorder) በ20% ከፍ እንዲል ምክንያት ሆነዋል።

  • በምሽት ለሚወጣው የስክሪን ሰማያዊ ብርሃን በመጋለጣቸው ምክንያት ከ16 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ፤ 91% ወጣቶች ለከፍተኛ የእንቅልፍ እጥረት (Insomnia) እና ለድካም ተዳርገዋል።


....... ዝርዝሩ በዚህ አያበቃም፤ ይቀጥላል!


ችግሩ በጊዜያዊነት የሚጠፋ የስሜት መለዋወጥ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ማህበራዊ ሚዲያ በአግባቡ ካልተመራ ትውልዱን ለአካላዊና ለአእምሯዊ በሽታዎች እያጋለጠ ይገኛል።


የሕክምና ዕርዳታ መቼ ያስፈልጋል?

አጠቃቀሙ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ የሚከተሉት ሲያዩ የባለሙያ ምክር ማግኘት ተገቢ ነው፦

  • በትምህርት ወይም በሥራ አፈጻጸም ላይ ግልጽ የሆነ መቀነስ ሲታይ፤

  • የእንቅልፍ መዛባት ቋሚ ችግር ሲሆን፤

  • የጭንቀት ወይም የድብርት ምልክቶች አብረው ሲከሰቱ፤


ይህን ጊዜ የጤና ባለሙያ ያማክሩ።

መፍትሔው ምንድነው?


እውነታውን ለመናገር... የሕክምና ሳይንስ ትኩረት የሚያደርገው ስልኩ ክፍት በሆነባቸው ደቂቃዎች ወይም “በስክሪን ሰዓት” ላይ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ስልኩን ስንጠቀም በሚሰማን ስሜት ላይ ነው። ሰዓት ከመቁጠር ይልቅ በውስጣችን የሚታዩትን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ማስተዋል ለጤናችን ይበልጥ ይጠቅማል።


ታድያ ግን ምን ያድርጉ?
  • የመጀመሪያው ስራ በየሰከንዱ እየጮኹ ትኩረትን የሚሰርቁትን አላስፈላጊ የስልክ መልዕክት ማሳወቂያዎችን (Notifications) ማጥፋት ነው። ይህ ሲሆን ስልኩ እኛን መረበሽ ያቆማል።

  • ቀጥሎም፤ ማህበራዊ ሚዲያን ያለ ምንም ዓላማ ዝም ብሎ ከመጎርጎር ይልቅ፤ ለተወሰነ ነገር ብቻ (ለምሳሌ መረጃ ለመለዋወጥ ወይም የተወሰነ ስራ ለመስራት) ብቻ ተጠቅሞ ፤ ወዲያውኑ ስልካችንን ማስቀመጥን መልመድ አለብን። ይህ ልምምድ አእምሯችን በስልኩ እንዳይሰረቅ በማድረግ ፤ የግል ፈቃዳችንን እንድንቆጣጠር ይረዳናል።

  • ከዚህ በተጨማሪ፤ ስልኩን አስቀምጠን የምናሳልፋቸው ጸጥ ያሉ ጊዜያት ለአእምሯችን ትልቅ እረፍት ይሰጡታል። በሕክምናው ዓለም ስልክን ዘግቶ መቀመጥ ስንፍና አይደለም። ይልቁንም አእምሮ ራሱን የሚያድስበት ወሳኝ ጊዜ ነው። ጸጥ ብሎ ማረፍ፤ መጽሐፍ ማንበብ እና አልፎ ተርፎም ከተለመደው የስልክ ጫና ወጥቶ ትንሽ መሰላቸት እንኳን በአእምሯችን ውስጥ ያለውን መወጠር ይቀንሳል። ይህም በነገሮች ላይ ትኩረት የመስጠት አቅማችንን በደንብ ያሳድገዋል።

ታድያ ውሳኔዎት ምንድነው?

ግንዛቤ ምርጫን ያመጣል፤ ምርጫ ደግሞ ሚዛናዊ ሕይወትን ይመልሳል።

Comments


bottom of page