top of page

የጭንቀት ህመም ጉዳይስ?

ይህ ጽሁፍ ከዚህ በፊት ራስን ማጥፋት ዙሪያ ላዘጋጀነው ጽሁፍ በተሰጡ ምላሾች ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ምልክቶች ካለብዎ / ያለበት ሰው ካወቁ ይህ ጽሁፍ ለእርስዎ ነውና በጥልቀት ያንብቡ።

እስቲ እንጠይቅዎ?


ለአንዳንዶች እነኝህ ምልክቶች የተለመዱ ፣ የዕለት ተዕለት እውነታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ በእነኝህ የህመም ምልክቶች ለተሰናከለ ህይወታቸው ፤ እራሳቸውን እየወቀሱ የሚኖሩም አሉ። በባህላችን ውስጥ እነኝህን ምልክቶች ማስታመሚያ ስፍራ ስለሌለን ፤ እንዲሁም የአእምሮ ህመምን ከመንፈስ ጋር አያይዘን ስለምንረዳ ፤ ይህንን ህመም እንደደባል ይዘው ፤ ኑሮዋቸውን የሚገፉም ጥቂቶች አይደሉም።


እርስዎ ከላይ ከተዘረዘሩት ምልክቶች መሀል ምን ያህሉን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ አስተውለዋል? ታድያስ የስነ ልቦና ምክር ያስፈልገኛል ብለው ያስባሉን?

በተለይ በተለይ ከ ምልክቶቹ ውስጥ ቢያንስ አምስቱን (ከ1 እስከ 9 ተራ ቁጥር ያሉት መሀል) 'አዎ' ብለው ከመለሱ ፤ በአቅራቢያዎ ያለ የስነልቦና ሀኪም ቢያማክሩ ፤ እጅጉን ያተርፉበታል። ምላሾት 'አይ! አያስፈልገኝም። ' ከሆነ ብቻዎን አይደሉም። እንደ እርስዎ ብዙ ኢትዮጵያውያን ፤ የህክምና እርዳታ አያስፈልገንም ብለው በዝምታ ይታመማሉ።


ግን ያስተውሉ...የመንፈስ ጭንቀት አይ 'ከዚህ በኋላ አልጨነቅም' ብለው የሚፈቱት ፤ ራስዎን በመውቀስ የሚያክሙት ህመም አይደለም። ችግሩም እርስዎ ሳይሆኑ የአእምሮዎ ጤና መታወክ ነው።

መረጃዎች ምን ይላሉ?


ይህ ህመም በህክምና ቋንቋ ሜጀር ዲፕረሲቭ ዲስኦርደር(major depressive disorder) ወይም በተለምዶ የመንፈስ ጭንቀት ህመም ተብሎ ይጠራል። የመንፈስ ጭንቀት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ከባድ የአእምሮ ጤና ችግር ነው።



በአለማችን ከሚኖሩ 10 ግለሰቦች በአማካይ አንዱ የመንፈስ ጭንቀት ሊኖርበት እንደሚችል እ.ኤ.አ በ 2022 የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ ያሳያል። እንዲሁም ሆስፒታል ሄደው ከሚታከሙት መካከል ከ13 እስከ 22 ፐርሰንት የሚሆኑት የጭንቀት ህመም ምልክት ቢያሳዩም ፤ ህመሙ በስርአት ተገኝቶ የሚታከሙት ግን ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው።

 

በኢትዮጵያ ደግሞ በትንሹ 4.5 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በዚህ የመንፈስ ጭንቀት ህመም ይጠቃሉ።  የመንፈስ ጭንቀት በኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቀስ የአእምሮ ህመም ነው። እ.ኤ.አ በ 2023 በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ የተደረገ ጥናት በበኩሉ ከወላድ እናቶች መካከል 23.8 በመቶው ከወሊድ በኋላ በሚያጋጥም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት እንደሚጠቁ ያሳያል። ሆኖም ግን እስከ አሁን ባለው መረጃ ብዙዎቹ እናቶች ሆነ ሌሎች የአእምሮ ህመም ተጠቂዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እና ምርመራ አያገኙም።



ይህ የመንፈስ ጭንቀት ምንድነው?


ጭንቀት ተፈጥሮአዊ እና የተለመደ ነገር ቢሆንም ፤ ከቁጥጥራችን ውጭ ሲሆን ግን ፤ እጅጉን አሳሳቢ የጤና እክል ሊያመጣ ይችላል። ሀዘን ከመሰማት ወይም በከባድ ችግር ውስጥ በማለፍ ብቻ የሚመጣ ህመም አይደለም። ሲያጋጥም በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ጣልቃ ሊገባ የሚችል ፤ የማያቋርጥ የጤና ቀውስ ነው። ምልክቶቹን እና ያሉትን መፍትሄዎች መረዳት ቀደም ብሎ ለማወቅ እና ውጤታማ አስተዳደር ለማግኘት ወሳኝ ነው።


ከላይ የተጠቀሱት ዋነኛ ምልክቶቹ ቢሆኑም ፤ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ጭንቀት አካላዊ ምልክትም ጭምር ሊያሳይ ይችላል። ይህም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ራስን በነጻነት የመግለጽ ባህል የሌላቸው ማህበረሰቦች ላይ ይታያል። ለዚህም ጥቂት የማይባሉ፤ የጭንቀት ህመም ያለባቸው ሰዎች የ ስጋ ደዌ ሀኪሞች ጋር ክትትል ያደርጋሉ። ሆኖም ግን ለውጥ አያሳዩም።


ታድያ ግን ያስተውሉ የመንፈስ ህመም እንደሚታሰበው ፤ ሁልጊዜ ማልቀስ አይደለም። መጨነቅ አይደለም። በዝምታ፣ በብቸኝነት፣ በድካም፣ በድብርት ውስጥ የተደበቀም ሊሆን ይችላል። የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ መቅበዝበዝ፣ እንዲሁም የማይተው ራስ ምታትም ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው አንዳንዴ ህመሙን ለመለየት የሚያዳግተው። ህመሙ እንዳለባቸው ያወቁትም ደግሞ ፤ ህክምና ለማግኘት እጅጉን ያቅማማሉ።


አደገኛው መላምት፡ “ይህ ከባድ አይደለም”


በባህላችን የአእምሮ ህመምን እንደ እምነት ማነስ፣ የሰብእና ድክመት ፣ እንዲሁም ስንፍና አድርገን እንወስደዋለን። አማኝ ከሆንን ደግሞ ፤ የመንፈስ ጭንቀታችን አለመዳን ምክንያት በጸሎት አለመጽናታችንን አልያም የእምነታችን አለመበርታት ተደርጎ ይወስዳል። ያማከሩም " በቃ አትጨነቅ/ቂ! ከልኩ አያልፍም በሚሉ የሽንገላ ቃላት ይታከማሉ። ያልተሻላቸው ምክራችንን ስላልሰሙ አድርገን እናስባለን። ለዚህም ታማሚዎችም ራሳቸውን ለማጀገን ፤ ይህ ከባድ አይደለም ብለው እርዳታ አይፈልጉም።


ታድያስ ግን ከልኩ አልፎ ራሳቸውን ማጥፋት የደረሱትስ?

ይህ አስተሳሰብ አደገኝነት አለው። ታማሚዎች ህክምና እርዳታ እንዳያገኙ ፤ ከራሳቸው ጋር ያልተገባ ፍልሚያ እንዲጀምሩ ፤ ህመሙን እንዲደብቁ ያደርጋቸዋል። እምነት፣ ማህበራዊ ቁርኝት እንዲሁም ምክር የመንፈስ ጭንቀትን ለመፍታት ትልቅ ሚና ቢጫውቱም ፤ የመንፈስ ጭንቀት ግን የህክምና እርዳታ የሚያስፈልገው የጤና ችግር መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው። እንደሚታሰበውም ራስን በማጀገን ብቻ የሚታለፍ ፤ የሞራል ወይም የስብእና ውድቀት አይደለም።


የመንፈስ ጭንቀትን እንደዚህ አድርጎ ማሰብ ሆነ ችላ ማለት ፤ የሚያቃጥል ቁስልን ችላ እንደማለት ነው። ህመሙ ህክምና ካላገኘ ቤተሰብ ያፈርሳል ፤ ስራንና ትምህርትን ያሰናክላል ፤ ማህበራዊ ቁርኝትን ያናጋል ፤ ወደ አደንዛዥ እጽ ሱሰኝነትም ያመራል። መፍትሔ ካላገኘ መጨረሻው አሳዛኝ ይሆናል።


በዚህም የተነሳ ራስን ማጥፋት በመላው ኢትዮጵያ ከወጣቶች መሀከል እየተበራከተ መጥቷል።


ሆኖም ግን ተስፋ አለ!


መጀመሪያ በማስተዋል ይጀምራል። እላይ ያሉትን ምልክቶች ካለብዎ ፣ የስነልቦና ሀኪም ጋር መታየት፣ የስነ ልቦና ምክር መወሰድ ፤ እንዲሁም የሰነልቦና ችግሮችን መፍትሄዎችን ማንበብ ህይወትዎን ያተርፋል።


የመንፈስ ጭንቀት መታከም የሚችል ነው። የግድ በመድሀኒት ብቻ ሳይሆን ፣ በስነ ልቦና ምክር ፣ በማህበረሰብ ድጋፍና ፣ የአኗኗር ዘይቤ ላይ በሚደረጉ ለውጦች ፤ ታማሚዎች ከህመሙ እንዲያገግሙ ማድረግ ይቻላል።

 

እርስዎስ ምን ያድርጉ?



  • የመጀመሪያውን እርምጃ ከዚህ ጽሁፍ ጀምረዋል። አንብብዋል። ስለዚህ የመጀመሪያውን እርምጃ ወስደዋል።


  • ምልክቶቹ ካለብዎ ፤ አደራ! ይህ ከባድ አይደለም ብለው እንዳያስቡ።


  • ህመምዎን ሊረዳዎ ለሚችል ሰው ይናገሩ/ ያዋዩ። የጤና ባለሙያ አማክረው ስነ ልቦናም ምክር ይውሰዱ። የሚያሳፍር ጉዳይ ስላልሆነ አይፍሩ። ብቻዎትን አይደሉም። ብዙዎች እንደርስዎ በዝምታ ውስጥ ሆነው ፤ የመንፈስ ጭንቀት ገፈት ቀማሽ እየሆኑ ነው።


  • ሌሎችንም ይደግፉ። ህመማቸውን ጭንቀታቸውን ሲያዋይዎት፤ ያለትዝብት ያዳምጧቸው። አንዳንድ ጊዜ የሚሰማ ጆሮ ከባድ የፈውስ ኃይል አለው።



እናስተውል!!


ወገናችን በዝምታ ውስጥ ሆኖ በመንፈስ ጭንቀት መሰቃየትም ፤ ሆነ መሞትም የለበትም። ማውራት፣ መነጋገር ከጀመርን ፈውሱ በእጃችን ነው።

 

ስለዚህ የሚወዱት የሚያውቁት ሰው በድንገት የራቀ ከመሰልዎ ፤ ከተለምዶ ሰላምታ አልፈው ከልብ ይጠይቁት ፤ ችግሩን ሲያዋይዎት ሳይታዘቡ ጆሮ ይስጡ።

 

የመንፈስ ጭንቀት እውነተኛ ህመም ነው። ማገገምም ይቻላል። በኢትዮጵያም ስለጉዳዩ ለመነጋገሪያ ጊዜ አሁን ነው።

Comments


bottom of page