top of page

"ማንኮራፋት" የሰላማዊ እንቅልፍ መግለጫ ወይስ የጤና ጠንቅ?

ብዙዎቻችን አንድ ሰው ሲያንኮራፋ ስናይ «በሰላም ተኝቷል፣ ደክሞት ነው» በማለት ማለፍን እንመርጣለን። ይሁን እንጂ እውነታው ከዚህ በተገላቢጦሽ ነው። ማንኮራፋት የሰላማዊ እንቅልፍ ምልክት ሳይሆን፤ ይልቁኑ በሰውነታችን ውስጥ እየተካሄደ ያለ ስውር የጤና ቀውስ ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።

በተለይም «ስሊፕ አፕኒያ» (Sleep Apnea) ተብሎ የሚጠራው በእንቅልፍ ወቅት የሚከሰት የትንፋሽ መቆራረጥ እክል፤ በአንድ ምሽት ውስጥ ብቻ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ጊዜያት እየተደጋገመ ህይወትን ለከባድ አደጋ ያጋልጣል።


ስሊፕ አፕኒያ ምንድን ነው?

ይህ ችግር አንድ ሰው በተኛበት ቅጽበት የአየር መተላለፊያ ቱቦው በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ ምክንያት መተንፈስ የሚያቆምበት አደገኛ ክስተት ነው። በእነዚህ አስገራሚ ሰኮንዶች ውስጥ ወደ አንጎል የሚሄደው የኦክስጅን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ያንሳል።


በዚህ ጊዜ አደጋውን የተረዳው አንጎል ሰውነቱን ከመታፈን ለማዳን ሲል፤ ግለሰቡን ለጥቂት ሰኮንዶች ከእንቅልፉ እንዲባንን ያደርገዋል፤ ከዚያም እንደገና ወደ እንቅልፉ ይመለሳል። የሚገርመው ግን፤ ይህ አስፈሪ ዑደት በአንድ ምሽት ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት ሊደገም ቢችልም፤ አብዛኞቹ ተጎጂዎች ጠዋት ሲነቁ የደረሰባቸውን ስቃይ ፈጽሞ አያስታውሱትም።


የበሽታው ስርጭት በአለም

ይህ ችግር የጥቂቶች ብቻ አይደለም፤ በዓለም ዙሪያ ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጉ አዋቂዎች በዚህ አደገኛ አዙሪት ውስጥ እንደሚገኙ ይገመታል። ይሁን እንጂ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ሳይመረመሩና በሽታው እንዳለባቸው ሳያውቁ፤ ከከባድ የጤና ስጋት ጋር ይኖራሉ። በተለይ ደግሞ የሚከተሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው።

  • ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው ሰዎች

  • ወንዶች

  • እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ

  • ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው

  • ወፍራም ወይም ሰፊ አንገት ያላቸው ሰዎች


የችግሩ ሶስት ገፅታዎች

የጤነ ኛ ሰው(ግራ) እና ስሊፕ አፕኒያ ያለበት ሰው የአየር ፍሰት (ቀኝ)። በቀኝ በኩል አየር ፍሰት መቋረጡን ያስተውሉ!
የጤነ ኛ ሰው(ግራ) እና ስሊፕ አፕኒያ ያለበት ሰው የአየር ፍሰት (ቀኝ)። በቀኝ በኩል አየር ፍሰት መቋረጡን ያስተውሉ!

ይህ የእንቅልፍ ጠላት ሶስት ዋና ዋና አይነቶች አሉት። በሰውነት ላይ የሚሰነዝረውም ጥቃት እንዲሁ ይለያያል።


  • ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ (OSA): ይህ የጉሮሮ ጡንቻዎች ከመጠን በላይ በመዛላቸው ምክንያት፤ የአየር መንገዱ ሙሉ በሙሉ የሚዘጋበትና በብዛት የሚስተዋለው ዓይነት ነው።

  • ሴንትራል ስሊፕ አፕኒያ (Central Sleep Apnea): የአየር መንገዱ ክፍት ቢሆንም፣ አንጎል ለሳንባዎች መተንፈስ የሚያስችል ትክክለኛ የነርቭ ትዕዛዝ ሳይሰጥ ሲቀር የሚከሰት ነው።

  • ኮምፕሌክስ ስሊፕ አፕኒያ (Complex Sleep Apnea): ከላይ የተጠቀሱትን የሁለቱንም ዓይነቶች አስከፊ ባህሪያት አጣምሮ የሚይዝ ድብልቅ እክል ነው።


በሽታው እንዳለብን እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ምልክቶቹ)

ብዙ ጊዜ ግለሰቡ ራሱ ባያውቀውም፤ አብረውት የሚተኙ የቤተሰብ አባላት በእንቅልፍ ወቅት የሚከተሉትን ዋና ዋና ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ፦

  • ከፍተኛ በሆነ የማንኮራፋት ድምጽ

  • በእንቅልፍ ጊዜ የትንፋሽ መቆራረጥ ወይም ሙሉ በሙሉ ትንፋሽ መቆም

  • በድንገት ከእንቅልፍ እየነቁ መተንፈስ (የመታፈን ስሜት)

  • ጠዋት ጠዋት የሚከሰት ራስ ምታት እና የአፍ መድረቅ

  • በቀን ውስጥ የሚሰማ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት እና የትኩረት መቀነስ፣ እንዲሁም

  • ያለምክንያት መበሳጨት ሊያስተውሉ ይችላሉ


ስሊፕ አፕኒያ ካልታከመ ምን ያህል አደገኛ ነው?


ይህንን በሽታ ችላ ማለት ቀላል የማይባል የጤና መቃወስን ያስከትላል። በጊዜ ሂደት ካልታከመ ወደሚከተሉት ከባድ ችግሮች ያመራል፦

  • የልብና የደም ዝውውር ችግር፡ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የልብ ድካም፣ የልብ ምት መዛባት እና የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ)

  • የስኳር በሽታ መባባስ

  • የአእምሮ ድካም እና አጠቃላይ የሕይወት ጥራት መቀነስ

  • በቀን ውስጥ በሚመጣ ድንገተኛ እንቅልፍ ምክንያት የሚከሰቱ አስፈሪ የመኪና አደጋዎች


በሽታው እንዴት ይመረመራል?

የችግሩን መኖር በትክክል ለማረጋገጥ ታካሚው የእንቅልፍ ምርመራ (Sleep Study) እንዲያደርግ ይደረጋል። ይህ ልዩ ምርመራ ግለሰቡ በተኛበት ጊዜ የሚከተሉትን ወሳኝ ጉዳዮች ይመረምራል።

  • በእንቅልፍ ወቅት ያለውን የትንፋሽ ሁኔታ

  • በእንቅልፍ ጊዜ በደም ውስጥ ያለውን የኦክሲጅን መጠን

  • የልብ ምትን ፍጥነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ይለካል።


የሕክምና አማራጮች

የስሊፕ አፕኒያ ሕክምና እንደ ችግሩ ክብደትና ዓይነት ይለያያል። ዋና ዋናዎቹ የሕክምና አማራጮች የሚከተሉት ናቸው፦

የመተንፈሻ ማሽን አድርጋ የተኛች ታካሚ ምስል። በጎኗ መተኛቷን ያስተውሉ
የመተንፈሻ ማሽን አድርጋ የተኛች ታካሚ ምስል። በጎኗ መተኛቷን ያስተውሉ
  1. የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ፦

ይህ ቀላል ለሆነው የስሊፕ አፕኒያ የሚውል ሲሆን፤ የሚከተሉትን የአኗናር ዘይቤ ለውጦች እንዲያመጡ ይመከራል።

  • የሰውነት ክብደትን መቀነስ

  • ከመኝታ በፊት አልኮል ከመጠጣት ሙሉ በሙሉ መቆጠብ

  • ሲጋራ ማቆም

  • በጎን የመተኛትን ልማድ ማዳበር(የአየር መንገድ እንዳይዘጋ ያደርጋል)


  1. የመተንፈሻ መሣሪያመጠቀም፦

ለመካከለኛና ለከባድ የኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ (OSA) ታካሚዎች የሚሰጥ የመጀመሪያና ዋነኛ ሕክምና ነው። ይህ የመተንፈሻ መሣሪያ ሲፓፕ (CPAP) ይሰኛል። በምሽት የአየር መንገዱ ተዘግቶ እንዳይቀር ቀጣይነት ያለው የአየር ግፊት በመስጠት፤ ከመታፈን ይታደጋል።


3. የአፍ ውስጥ መሣሪያዎች (Oral Appliances)፦

ለአንዳንድ ቀላል ወይም መካከለኛ ደረጃ ላይ ላሉ ታካሚዎች የሚጠቅሙ ሲሆን፤ የታችኛውን መንጋጋ ወደ ፊት በመግፋት የአየር መንገዱ ክፍት ሆኖ እንዲቆይ ያደርጋሉ።


4. የቀዶ ሕክምና፦

የአየር መተላለፊያ መንገዱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚዘጉ የአካል መዋቅሮች (ለምሳሌ ያበጠ እንጥል ወይም የላንቃ ስጋ) ካሉ፤ በተመረጡ ታካሚዎች ላይ የቀዶ ህክምና ሊያስፈልግ ይችላል።


ልዩ ጥንቃቄ፡ በሕፃናት ላይስ?

ብዙዎች ባያውቁትም ስሊፕ አፕኒያ በሕፃናትም ላይ ሊከሰት ይችላል። በልጆች ላይ የሚታዩት ምልክቶች ከአዋቂዎች ጥቂት ለየት ይላሉ። እነኝህ ምልክቶች የሚከተሉትን ይመስላሉ፦

  • ከፍተኛ የሆነ ማንኮራፋት እና በእንቅልፍ ወቅት የትንፋሽ መቆራረጥ

  • በትምህርት ላይ ከፍተኛ የትኩረት መቀነስ ማሳየት

  • በቀን ከመድከም ይልቅ፣ ከመጠን በላይ ንቁ (Hyperactive) ሊሆኑ ይችላሉ።


ማንኮራፋት ቀልድ ወይም የጥሩ እንቅልፍ መግለጫ አይደለም። የሰውነትዎን የጭንቀት ጥሪ በጥንቃቄ በማዳመጥና በጊዜ በመመርመር ጤናዎንና ህይወትዎን ይታደጉ።

❗ መቼ ሐኪም ማየት አለብዎት?


ከሚከተሉት ምልክቶች መካከል ቢያንስ አንዱ እንኳን፤ በእርስዎ ወይም በቅርብ ሰውዎ ላይ ከተስተዋለ ሳይዘገዩ የሕክምና ምክር ያግኙ፦

  • በጣም የሚያንኮራፉ ከሆነ

  • በእንቅልፍ ጊዜ መተንፈስ እንደሚያቆሙ፤ በትዳር አጋር ወይም በቤተሰብ ከተነገረዎት

  • በቂ እንቅልፍ ተኝተው እንኳ፤ በቀን ሙሉ እንቅልፍ እንቅልፍ የሚልዎት ከሆነ

  • ጠዋት ሲነቁ ፤ ሁልጊዜ የሚደጋገም ራስ ምታት ካለዎት

  • እንዲሁም ከፍተኛ የደም ግፊትዎ በመድኃኒትና በሕክምና ሊስተካከል ካልቻለ፤ የጤና ባለሙያ በዚህ ዙሪያ ማማከርዎት ይመረጣል።


ያስተውሉ!

 ጤናማ እንቅልፍ የጤናማ ሕይወት መሠረት ነው! ከፍተኛ ማንኮራፋትን በቀላሉ አይመልከቱ። ራሱን የቻለ የጭንቀት ጥሪ መሆኑን ተረድተው ጤናዎን ይጠብቁ።

1 Comment


Guest
10 hours ago

관리가 체계적으로 진행되어 처음 이용하는 사람도 편안하게 받을 수 있었어요. 서비스를 경험한 뒤 몸이 한결 가벼워졌고, 전반적인 출장마사지 만족감도 높았습니다.

Like
bottom of page