የአስም ህመም በኢትዮጵያ
- Zebeaman Tibebu
- Jun 25
- 4 min read
ድንገት ቢታፈኑ ... ምን ይሰማዎታል? ለ እያንዳንዷ ቅንጣት አየር መታገል አይጨንቅም?!

በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ፤ በተለይም ለህጻናት ፤ ይህ ምናባዊ ጉዳይ አይደለም። ድንገት ሊያጋጥማቸው የሚችል እውነታ ነው። የትንፋሽ ቱቦአቸው ተዘግቶ አየር ለመሳብ ሲታገሉ ፤ የትንፋሽ ቱቦአቸውን የሚያረጋጋ መድሐኒት ከሌለ ፤ ጉዳቱ አይሎ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።
አስም የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ህመም ሲሆን ፤ ከህጻን እስከ አዋቂ ሁሉንም የእድሜ ክልል ያጠቃል። ህመሙ ያለባቸው ሰዎች የመተንፈሻ አካላቸው የውስጥ ስጋ (respiratory mucosa) እጅጉን ሰበበኛና ቁጡ ነው። ይህም ማለት በመደበኛ ነገር(የአስም ቀስቃሽ አካላት) ሊቆጣ እና ሊያብጥ ይችላል። ችግሩ ታድያ መቆጣቱ ብቻ ሳይሆን ፤ በማበጡ የመተንፈሻ ቱቦ ይጠባል። እዚህ ላይ የመተንፈሻ አካል የሚያመርታቸው ወፍራም ፈሳሾች (አክታ) ሲጨመር ፤ አየር መውጣት እና መግባት ያስቸግራል። ይታፈናል። የሚያረጋጋው መድሀኒት ካላገኘ እብጠቱ እያደገ ሂዶ ፤ አየር ቱቦን ሊደፍን ይችላል።

ህመሙ እንዲህ ሆኖ ሳለ በሀገር ደረጃ ለአስም በቂ አጽንኦት አልሰጠነውም። ባሉብን አንገብጋቢ ጉዳዮች ወደ ኋላ ከገፋናቸው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች አንዱ ነው። የአስም ብሔራው ቀን የለንም ፣ ብሔራዊ እቅድ አላወጣንም። በሕዝብ ተቋማት ውስጥ በቂ መሰረታዊ መድኃኒቶች የሉም። የህመሙ ስርጭት ግን እየተሰፋፋ ነው።
ታማሚም ግንዛቤ ኖሮት ህክምና እስኪመጣና ፤ መድሐኒቱ እስኪገኝ በጸጥታ ብዙ ኢትዮጵያውያን ይሞታሉ። በማይታይ አፋኝ ትንፋሻቸውን ይሰረቃሉ።
🌍 የአስም ስርጭት
እ.ኤ.አ. በ2019 በአለም ዙሪያ አስም ከነበረባቸው ከ262 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ሰዎች መሀል ፤ ከ455,000 በላይ በአስም የተነሳ መሞታቸውን የአለም ጤና ድርጅት በ2021 ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።
የአለምአቀፍ የአስም ሪፖርት ደግሞ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የአስም በሽታ ስርጭት እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ ከተሞችን ጠቅሶ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ከ ዘጠኝ አመት በፊት የተደረገ የዳሰሳ ጥናት በበኩሉ ፤ የአስም መጠን በከተማ ነዋሪዎች ላይ እየጨመረ መሆኑን አሳይቷል።
አገር አቀፍ መረጃ ባይኖረንም ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የአስም ህመም ተጠቂ ቁጥር ከ 8.7 እስከ 9.2 በመቶ እንደሚደርስ ይገመታል። ይህም በትንሹ 10 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የአስም ህመም እንዳለባቸው ያመላክታል።
በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የተደረገ ጥናት በበኩሉ እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ህጻናት መሀከል 13.3 በመቶ የሚሆኑት የአስም ምልክቶች እንደሚያሳዩ ይገልጻል።
በኢትዮጵያ ድንገትኛ ክፍል ከሚያመጡ 5ቱ ዋና ዋና ህመሞች መካከል አስም አንዱ ነው።
በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ያሉ የአስም ህመምተኞችስ?
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ብዙ የአስም ታማሚዎች በጭራሽ አይመረመሩም። ምልክታቸውን ችላ ብለው ያልፋሉ። ለዚህም ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው።
🔥የአስም ህመም ጠንሳሽ ምክንያቶች በኢትዮጵያ

🏙️ የከተማ አየር ብክለት
የአዲስ አበባ የአየር ጥራት መጠን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው። ባሉ መረጃዎች የከተማው አየር የአለም ጤና ድርጅት የደህንነት ወሰኖችን ይጥሳል ። የአየር ጥራቱም እየተባባሰ ይገኛል። ለዚህም የመኪና ጭስ፣ የመንገዶች አቧራ ፣ በግንባታ እና በኢንዱስትሪ የሚወጡ አየር በካይ ጋዞች እና ንጥረ ነገሮች ፣ እንዲሁም ከሚቃጠሉ ማገዶዎች እና ቆሻሻዎች የሚወጡ ውህዶች ተጠቃሽ ምክንያቶች ይሆናሉ።
እ.ኤ.አ. በ 2022 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ የአየር ብክለት ጥናት ፒኤም 2.5 ክምችት የዓለም ጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው ገደብ ከ 5-7 እጥፍ እንደሚደርስ እና ይህም አስም ላለባቸው ሰዎችች ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን አመላክቷል።
🔥 የቤት ውስጥ የአየር ብክለት
አዎ የቤት ውስጥ አየርም ይበከላል። ከ90% በላይ የሚሆኑት የገጠር አባወራዎች እና 60% የሚጠጉ የከተማ ቤቶች አሁንም ምግብ ለማብሰል ከሰል፣ማገዶና ኩበት ይጠቀማሉ። ይህንን ተከትሎ ለሚመጣ አየር መበከል ዋነኛ ተጋላጮች ፤ ቤት ውስጥ የሚውሉ ህጻናት እና ሴቶች ናቸው።
🧬 በቤተሰብ የሚመጣ ተጋላጭነት እና የድህነት ጥምር
ዝቅተኛ ግንዛቤና የዘገየ ምርመራ በዘር ከሚመጣ ተጋላጭነት ጋር ተጣምረው ፤ የአስም ታማሚዎችን ቁጥርን እየጨመሩ ይገኛሉ። እዚህ ላይ ያልተሟላ የመድሀኒት አቅርቦት ሲታከልበት ችግሩን ይባባሳል።
ለምሳሌ፡ ሳልቡታሞል እና ኮርቲኮስቴሮይድ መተንፈሻ መድሀኒቶች ህይወት አድን እና አስፈላጊ ቢሆኑም በተሟላ ሁኔታ የሉም።
መድህኒቶቹ በግል ፋርማሲዎችም ከተገኙ ዋጋቸው ከፍተኛ ነው። ይህም በደሀው የማህበረሰብ ክፍል ዘንድ ያለውን የአስም መድሀኒት ተደራሽነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። መድሐኒቱን ካልገዙ ህመሙ ይባባስባቸዋል። ከገዙ ደግሞ መሰረታዊ ፍላጎታቸው ላይ ተጽእኖ አለው። ይህ አሳዛኝ አዙሪት ነው።
ይብሱኑ መድሀኒቶቹ ሙሉ በሙሉ የሚጠፉበትም ጊዜዎች ጥቂት አይደሉም።
📚 አስም ህመም የሚያስከፍለው ክፍያ
ያልታከመ አስም ያለባቸው ልጆች ፤ በአመት በአማካይ 18 የትምህርት ቀናት ያመልጣቸዋል።
አስም ያለባቸው አዋቂዎች በህመሙ የተነሳ ፤ በአመት ከ10-15 የስራ ገበታቸው ላይ አይገኙም።
ለመድሃኒት፣ ለክሊኒክ ጉብኝት እና ለትራንስፖርት ብቻ ብዙዎች በሺዎች ያውጣሉ። ይህም ወደ የገንዘብ ችግር ይገፋቸዋል።
ሆኖም ከ80% በላይ የሚሆነው የአስም በሽታ ሞትን ፤ በጊዜው በሚደረግ ምርመራና በትክክለኛ መድሃኒት መከላከል ይቻላል።
⚠️ የአስም ህመም ቀስቃሾች⚠️

የአስም ምልክቶች በተለያዩ የአካባቢ እና አካላዊ ምክንያቶች ሊነሳሱ ወይም ሊባባሱ ይችላሉ። አብዛኞቹ ቀስቃሾች እለትተእለት ኑሮ ላይ የተለመዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ከእነኝህ መሀል ፡
የቤት ውስጥ ጭስ፡ ምግብ ስናበስል የምንጠቀማቸው ነዳጆች ጭስ (ከሰል፣ ማገዶ፣ ኩበት፣ ወ.ዘ.ተ...)
አቧራዎች ፡ ከመንገዶች፣ ከግንባታዎች እንዱሁም ከተለያዩ ምንጮች የሚመጡ አቧራዎች
ጠንካራ ጠረኖች/ሽታዎች ፡ከዕጣን፣ ከሰንደል ፣ ከሽቶዎች ፣ ጠረን ካላቸው ሳሙናዎች/ማጽጃዎች፣ ወ.ዘ.ተ... የሚመጡ ጠንካራ ሽታዎች
ቀዝቃዛ አየር - የሚተነፍሱት አየር ቀዝቃዛ ከሆነ
እንደ ጉንፋን ያሉ የላይኛው የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽኖች።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (በተለይ ስለ ህመማቸው የማያውቁ ልጆች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ስለማያደርጉ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያፍናቸዋል)
🌧️ በወቅት ተለዋዋጭ የሆኑ ቀስቃሽ ምክንያቶቹ
በበጋ፡- ከፍተኛ የአቧራ፣ ንፋስ እና የመተንፈሻ ኢንፌክሽኖች
በክረምት: ቀዝቃዛ እርጥብ አየር
በጸደይ : የአበባ ብናኝ ፣ በተለያዩ አካላት ላይ ያደጉ ሻጋታዎች ።
በዚህም የተነሳ በወቅቶች ላይ ተመስርቶ የሚዋዥቁ የአስም ህመም ምልክቶች ይታያሉ።
🚨 ምን ምልክቶች ያሳያል?
አስም ሁልጊዜ በደንብ የሚታዩ ምልክቶች ላያሳይ ይችላል። ህመሙ በዝምታ ሊያሰቃይ ይችላል።

👀 የተለመዱ ምልክቶች:
ሲተነፍሱ (አየር ሲያስወጡ) እንደ ፉጨት የሚመስል(ወይም ሲር የሚል) ተደራቢ ድምጽ።
ሲነጋ ወይም ሲመሽ ማሳል / አየር ማነስ።
የደረት መጭነቅ ወይም የደረት ህመም
ትንፋሽ ማጠር ወይም በፍጥነት መተንፈስ
ለትንሽ ስራ አብዝቶ መድከም
🛑 አሳሳቢ ምልክቶቹ (የህክምና ድንገተኛ አደጋ)
ቃላት ለማውጣት መቸገር። ሙሉ ዓረፍተ ነገር መናገር አለመቻል።
በሚተነፍሱበት ጊዜ የአፍንጫ ቀዳዳ መስፋት ወይም የጎድን አጥንት መሰርጎድ
ከንፈር ወይም ጣቶች ወደ ሰማያዊነት መለወጥ
ለአስም በሚሳቡ የመተንፈሻ መድሐኒቶችም ወስደው የአስም ምልክቶቹ አለመጥፋት።
እነኝህን ምልክቶች ካዩ ፤ አፋጣኝ ድንገተኛ ህክምና ያስፈልጋልና ፈጽሞ አይዘናጉ። አቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በፍጥነት ይሂዱ።
💡በአስም ዙሪያ ምን ሊደረግ ይችላል?

✅ 1. ብሔራዊ እውቅና
በኢትዮጵያ አሁን አስም ቀዳሚ ስፍራ አልተሰጠውም። ለዚህም እውቅና ተሰጥቶት በአገር አቀፍ ደረጃ የአስም ህመም እንክብካቤ እና ስልጠና ያስፈልጋል። በህመሙ ዙሪያ በተሟላ ደረጃ መረጃ መሰብሰብ ይኖርበታል።
✅ 2. የህዝብ ግንዛቤ ዘመቻዎች
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ50% በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ፤ በአስም ዙሪያ የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው። ለዚህም ለማህበረሰቡ ስለ አስም ህመም ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ፤ መሰራት ይኖርበታል። ለዚህም በሬዲዮ፣ በቲቪ፣ በትምህርት ቤቶች እና በሃይማኖታዊ መድረኮች ላይ ፤ ግንዛቤን የሚያሳድጉ ትምህርታዊ ዘመቻዎች ያስፈልጋሉ።
የአስም ህመም ተላላፊ አለመሆኑም መታወቅ ይኖርበታል።
✅ 3. የአስም መድሐኒቶች ተደራሽነት መጨመር አለበት።
አስፈላጊ የአስም መድሃኒቶች በነጻ የሚቀርቡ የህዝብ አስፈላጊ መድሃኒት ጥቅል ውስጥ ተካተው ፤ ተመጣጣኝና ያልተቋረጠ አቅርቦትን መረጋገጥ የሚችልበት መንገድ መዘጋጀት ይኖርበታል።
የሳልቡታሞልን እና የኮርቲሲቶሮይድ መተንፈሻ መድሀኒቶች ህይወት አዳኝ ናቸውና ፤ ሀገር ውስጥ ያላቸው አቅርቦት ፈጽም መቋረጥ የለበትም።
✅ 4. ንጹህ አየር እና የአካባቢ ጥበቃ
ቆሻሻ ማቃጠል በማህበረሰብ ደረጃ መቆም አለበት። ቤቶች በደንብ መናፈስ አለባቸው። ቤት ውስጥ ካበሰሉ በካይ ጭስ የሌላቸውን የማብሰያ ነዳጆች ይጠቀሙ። ኤሌክትሪክ ይጠቀሙ።
🧒 ለወላጆች እና አስተማሪዎች

ምልክቶቹን ይወቁ።
የአስም ህይወት አድን መድሀኒቶችን (inhalers) በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያስቀምጡ።
አስም ያለባቸው ልጆች አካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ፤ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መከናወኑን ያ ረጋግጡ። (ለምሳሌ፣ አስፈላጊ ከሆነ ከቅድመ-ልምምድ በፊት inhaler አጠቃቀምን ይወቁ)
ልጆች ከመለስተኛ እንቅስቃሴ በኋላ ድካም ከተሰማቸው እንዲናገሩ አበረታቷቸው።
🗣️ ስለ አስም መነጋገር ይኖርብናል። መቆጣጠር በሚቻል ህመም ወገናችን መሰቃየት የለበትም።
ንግግራቸው ሳይገድብ ቃላቸውን ሳይሰናክል፣ እስትንፋሳቸውን ሳይሰርቅ በፊት እንከላከለው።
በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ተግባራዊ ለውጥ ማምጫ ጊዜው አሁን ነው።
Comments