የመመረዝ አደጋ በኢትዮጵያ፦ የሚያጋጥሙ መርዞች እና መፍትሔዎቻቸው
- Zebeaman Tibebu
- 2 days ago
- 6 min read
በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ያለ የ አንድ ገበሬ ቤትን በዓይነ ሕሊናዎ ይሳሉ።
እናቲቱ እራት በማዘጋጀት ተጠምዳለች። ገበሬ ባሏ፤ ቀኑን ሙሉ ማሳውን በተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ሲረጭ ውሎ፤ ወደ ቤት ተመልሷል። ረጅም እና አድካሚ ቀን ስለነበር፣ ሰውነቱ ዝሏል። ቤት ውስጥ የሚጫወተው አነስተኛው ህጻን ልጃቸው፤ በጥግ የተቀመጠውን፣ አባቱ ለሰብል መከላከያ ገዝቶ ያመጣውን ኬሚካል ያያል። በጉጉት ቀርቦ ሲነካው፤ በውስጡ ያለው መርዛማ ፈሳሽ ፈስሶ ቆዳውን ይነካዋል።

ህጻኑ ወዲያው አላቃጠለውም፤ አላለቀሰም፤ ወይም አልጮኸም። ጨዋታውን ዝም ብሎ ቀጠለ። ምንም ድምፅ ስላልተሰማም ፤ እናትና አባት አንዳች አደጋ መኖሩን አልጠረጠሩም።
ነገር ግን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በህጻኑ ላይ አስደንጋጭ ለውጥ ታየ። ትኩሳት መጣበት፤ ምራቅ በአፉ ይዝረበረብ ጀመር። ትውከትና ተቅማጥም ተያያዘው። ወላጆቹ ደነገጡ። እናትየው "የበላው ነገር አልተስማማው ይሆን?" በሚል ጥርጣሬ የምታውቀውን የጤና ባለሙያ በስልክ አናገረች። ሁኔታውን ከምግብ መመረዝ ጋር አያይዛ በመንገሯ፤ ባለሙያውም ሽሮፕ እንድትገዛ ነገራት።
እናትየው መድኃኒቱን ገዝታ ስትመለስ ግን ልጇ ፈጽሞ ደክሟል። የሚጥል በሽታ እንዳለበት ሰው መላ አካሉ ይንቀጠቀጥ ጀመር። በዚህች አስፈሪ ቅጽበት ነበር ፤ አባትየው በጥግ በኩል የተደፋውንና ሰማያዊ ምልክት ያለበትን የተባይ ማጥፊያ ብልቃጥ ያስተዋለው!
ተሯሩጠው አቅራቢያ ወዳለው የጤና ተቋም ወሰዱት። መርዙ ቆዳውን ከነካው ሰዓታት ተቆጥረው ነበር። እዚያ ያሉት የሕክምና ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነት ታማሚዎችን ማየት ስለለመዱ ፤ ወዲያው ስለ ተባይ ማጥፊያው ዓይነት ጠየቋቸው። አባትየው ግን ብልቃጡን ይዞ አልመጣም ነበር።
እናትየውም "ኧረ ወደ አፉ ጨርሶ አላስጠጋውም!" በማለት በጭንቀት መለሰች።
ዶክተሩም፦ "አደጋው ለመድረስ መርዙን በአፍ መውሰድ አያስፈልግም፤ እነዚህ የኬሚካል መርዞች ቆዳን በመንካት ብቻ ወደ ደም ውስጥ ገብተው ሰውን ሊገድሉ ይችላሉ።" ብሎ መለሰላት
ህጻኑ በድንገተኛ ክፍል የሕይወት አድን ሕክምና ተጀመረለት...

ይህ ምናባዊ ታሪክ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን በየዓመቱ በተለያዩ አካባቢዎች ብዙ ወላጆች የሚጋፈጡት መራራ እውነት ነው ።
በጥቂት ሰከንዶች ፤ ሁልጊዜ ለሥራ የምንጠቀምባቸው ነገሮች ወደ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ። ሰብልን ከተባይ ለመጠበቅ የሚረጭ ኬሚካል፣ በቀላሉ ሊደረስበት በሚችል ቦታ የተቀመጠ መድኃኒት፣ ወይም ለጽዳት የምንጠቀመው በረኪና ወይም ማጽጃ ፈሳሾች ፤ በድንገት ሕይወትን የሚቀጥፉ ንጥረ ነገሮች ሆነው ይገኛሉ!
ዛሬ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ በብዛት የሚታዩ የመመረዝ ዓይነቶችን፣ ምልክቶቻቸውን እና እንዲህ ዓይነት አደጋ ሲያጋጥም መውሰድ ያለብንን የመጀመሪያ እርዳታ በዝርዝር እንመለከታለን።
ከአደጋው በስተጀርባ ያሉት ቁጥሮች?

በኢትዮጵያ በተለያዩ ሆስፒታሎች የተደረጉ ጥናቶች፣ ከዚህ ማኅበራዊ ቀውስ በስተጀርባ ያሉትን አሳሳቢ እውነታዎች በሚከተሉት ቁልፍ ነጥቦች ያሳያሉ፦
ወጣቶች ቀዳሚ ሰለባዎች ናቸው (ከ70% እስከ 88%)
በኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና ክፍሎች ውስጥ ከሚመዘገቡት የመርዝ ሰለባዎች መካከል ከ70% እስከ 88% የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ናቸው። አደጋው በሁለት መልክ ይከሰታል፤ ሕፃናት በወላጆች ቸልተኝነትና በአያያዝ ጉድለት ለድንገተኛ አደጋ ይጋለጣሉ። ወጣቶች ደግሞ ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ከሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች ጋር በተያያዘ ለከባድ ስሜታዊ ውሳኔዎች ይዳረጋሉ።
ሴቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ (ከ60% እስከ 78%)
በሆስፒታሎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ከተመዘገቡት የመመረዝ አደጋዎች ውስጥ ከአጋማሽ በላይ የሚሆኑት (ከ60% እስከ 78%) በሴቶች ላይ የደረሱ ናቸው። ተመራማሪዎች ይህንን አስከፊ ሁኔታ ከቤት ውስጥ እና ከማኅበራዊ ውጥረቶች፣ ከቤተሰብ ግጭቶች፤ እንዲሁም ተገቢውን ትኩረት ካላገኙ የአእምሮ ጤና ፈተናዎች (እንደ ድብርት ያሉ) ጋር ያያይዙታል።

አብዛኛው ሆን ተብሎ የሚደረግ ነው (80%)
በአዋቂዎች ላይ ከሚከሰቱት አስር የመመረዝ አደጋዎች ውስጥ ስምንቱ (80%) ሆን ተብሎ በራስ ላይ የሚደረግ ጉዳት ነው። ይህ መርዞች በአካባቢያችን በቀላሉ መገኘታቸው፤ ሰዎች በጭንቀት ቅጽበት ሕይወታቸውን ለማጥፋት ቀላሉን መንገድ እንዲመርጡ ዕድል እየሰጠ መሆኑን ያሳያል።
ሕክምና ለማግኘት ሰዓታት ይፈጃል (በአማካይ 4.2 ሰዓታት)
አንድ የተመረዘ ሰው አደጋው ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሕክምና ተቋም ለመድረስ በአማካይ 4.2 ሰዓታት ይፈጅበታል። ይህ መዘግየት በሕይወት የመትረፍ ዕድል ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው። ሰዓታት ባለፉ ቁጥር መርዙ እንደ ልብ፣ ኩላሊትና ሳንባ ያሉ ወሳኝ የሰውነት ክፍሎችን ለማጥቃት ሰፊ ዕድል ያገኛል። በተለይም እንደ ኦርጋኖፎስፌት (የተባይ ማጥፊያ) ባሉ መርዞች ላይ፤ ይህ መዘግየት ሕይወትን ለማዳን የሚረዳውን የመርዝ ማርከሻ (Antidote) ለመስጠት ያለውን ወርቃማ ጊዜ ይሰርቃል።
በኢትዮጵያ በብዛት የሚታዩ መርዞች እና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች
በኢትዮጵያ የሕክምና ማዕከላት መረጃ መሠረት፣ አራት ዋና ዋና መርዞች የጉዳቱን ስፋት በቀዳሚነት ይይዛሉ። እነኝህም፦
1. የኦርጋኖፎስፌት ተባይ ማጥፊያዎች (የእርሻ ኬሚካሎች)

ግብርና የብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን የኑሮ መሠረት ቢሆንም፤ አንዳንድ የእርሻ ኬሚካሎች (እንደ ማላቲን ያሉ) በአግባቡ ካልተያዙ ገዳይ ይሆናሉ።። እነዚህ ኬሚካሎች የነርቭ ሥርዓትን ያዛባሉ። ኮሊነርጂክ የነርቭ መግባቢያዎችን ስለሚያጠቁ፤ የነርቭ መልእክት ልውውጥን ያበላሻሉ።
ይህም ለህይወት አስጊ ደረጃ ነው።
መመረዝን የሚያሳዩ ምልክቶች፦
ከፍተኛ ላብ፣ ዕንባ እና የምራቅ መብዛት/መዝረብረብ፣
ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና ማስቀመጥ፣
የመተንፈስ ችግር ፣
የዓይን ብሌን መጥበብ፣
የጡንቻ መንቀጥቀጥ አልያም መዛል፣
ግራ መጋባት፣
የሰውነት መንቀጥቀጥ (seizures)፣
እራስን መሳት ናቸው።
ምን ማድረግ አለብዎት?
✅ ተጎጂውን ወዲያውኑ ኬሚካሉ ካለበት አካባቢ ያርቁ።
✅ በኬሚካሉ የተበከሉ ልብሶችን በጥንቃቄ ያውልቁ።
✅ የተነካውን ቆዳ አብዝተው በ ንጹህ ውሃ እና ሳሙና በፍጥነት ይጠቡ።
✅ ተጎጂውን በአስቸኳይ ወደ ሕክምና ተቋም ይውሰዱ። (ሆስፒታሎች አተነፋፈስን ለማስተካከልና በሽተኛውን ለማረጋጋት እንደ አትሮፒን ያሉ መርዙን መቃወሚያ መድኃኒቶችን ሊሰጥዎ ይችላሉ።)
ማድረግ የሌለብዎ!
❌ መርዙን በአፍ ከተወሰደ፤ ከሆድ ለማውጣት ፤ በግድ ለማስመለስ አይሞክሩ። ይህን ጊዜመርዙ ወደ ሳንባ ውስጥ ገብቶ የመተንፈሻ አካልን ሊጎዳ ይችላል።
❌ ወተት፣ ውሃ፣ ወይም ባህላዊ መፍትሔዎችን በአፍ ለማጠጣት አይሞክሩ። ተጎጂው ራሱን ከሳተ ፈሳሹ በቀጥታ ወደ ሳንባው ሊሄድ ይችላል።
❌ "ምልክቶቹ እስኪሻሻሉ" አይጠብቁ። በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ስፍራ ይሂዱ። ማርከሻውን በጊዜ ውስጥ መሰጠት አለበት።
2. የቤት ውስጥ ማጽጃ ኬሚካሎች

በቤታችን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ንጥረ ነገሮች ከተዋጡ ወይም በአግባቡ ካልተያዙ ከባድ ጉዳት ያመጣሉ። ለምሳሌ፦ በረኪና፣ የተለያዩ ቤዝና አሲድ ያላቸው የቤት ውስጥማጽጃዎች፣ ነዳጆች። እነዚህ አፍን፣ ጉሮሮን፣ ጨጓራንና አንጀትን ወይም ሊበሉ ይችላሉ። ነጭ ጋዝ እና ሌሎች የነዳጅ ምሮቶችም በበኩላቸው ከተጠጡ አልያም በብዛት ከተተነፈሱ የትንፋሽ አካላት ላይ ችግር ይፈጥራሉ። መመረዝን የሚያሳዩ ምልክቶች፦
በአፍ፣ በከንፈርና በጉሮሮ አካባቢ ከባድ የማቃጠል ስሜት፣ መቅላት አልያም መገርጣት፣
ለመዋጥ መቸገር፣ የደረት እና የሆድ አካባቢ አጣዳፊ ሕመም፣
የምራቅ መብዛት እና ደም የቀላቀለ ትውከት፣
የድምፅ መጎርነን፣ ሳል እና የትንፋሽ ማጠር ናቸው።
የተመረዙት በጋዝ/በነዳጅ ከሆነ የሚታዩ ምልክቶች፦
ከባድና ተከታታይነት ያለው ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥ እና ማፈን፣
ከትንፋሽ ወይም ከዓይነ ምድር የሚወጣ የጋዝ/የነዳጅ ሽታ፣
ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ እና የሆድ መቃጠል፣
መደበት፣ አልያም ራስን መሳት (ነዳጁ ወደ ደም ውስጥ ከገባ) ናቸው።
ምን ማድረግ አለብዎት?
✅ ተጎጂውን ከኬሚካሉ ያርቁ። መርዙ ነዳጅ ከሆነ ፤ተጎጂውን ወዲያውኑ ነዳጁ ከተደፋበት ዝግ ክፍል አውጥተው ንጹሕ አየር እንዲተነፍስ ያድርጉ።
✅ ኬሚካሉ ቆዳን ወይም ዓይንን ከነካ፣ ወዲያውኑ በበረዶ ሳይሆን ፤ ንጹህ ውሃ ቢያንስ ለ15-20 ደቂቃዎች ያፍስሱበት።
✅ኬሚካሉ የነካውን ልብስ በፍጥነት ይቀይሩ። ልቡሱን አውልቀው፤ ኬሚካል የነካውን ቆዳ በውሃና በሳሙና ይጠቡ (ነዳጅ በቆዳ በኩል በቀላሉ ሊመጠጥ ይችላል)
✅ ምልክቶቹ ቀላል ቢመስሉም እንኳን፤ ሳይዘገዩ ወደ ሕክምና ተቋም ይሂዱ።
ምን ማስወገድ አለብዎት?
❌ ፈጽሞ አያስመልሱ! ይህ ጥብቅ መመሪያ ነው። የሚያቃጥሉ ኬሚካሎችን አልያም ነዳጅ የጠጣ ሰው ማስመለስ አይመከርም። መርዙ ተመልሶ በሚወጣበት ጊዜ ጉሮሮንና አፍን በድጋሚ ያቃጥላል። ነዳጅም ተመልሶ በሚተፋበት ቅጽበት በቀላሉ ተንኖ ወደ ሳንባ ውስጥ ይገባል። ይህም ሳንባን ሙሉ በሙሉ በማቃጠል ለመታፈንና ለሞት ይዳርጋል።
❌ሌላ ፈሳሽ በመስጠት መርዙን በሆድ ውስጥ ለማሙዋትም ሆነ ለማክሸፍ አይሞክሩ! ለምን?
ለምሳሌ ፡ አሲድ ለዋጠ ሰው ለማክሸፍ ሌላ ቤዝ መስጠት ፤ ሆድ ውስጥ ኃይለኛ የኬሚካል ሙቀት የሚፈጥር ኬሚካላዊ ኡደት እንዲካሄድ ያደርጋል። ይህም ጨጓራን ሊበሳው ይችላል።
ነዳጅ ቢሆን እንኳን ፤ አይመከርም። ለምሳሌ፡ ወተት ወይም ዘይት ማጠጣት ነዳጁ በሆድ ውስጥ ይበልጥ እንዲሟሟና ወደ ሰውነት እንዲሰራጭ ያደርጋል።
በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም ይውሰዱ!
3. መድኃኒቶች

መድኃኒቶች ሕይወትን ያድናሉ። ነገር ግን በብዛት ሲወሰዱ፤ አልያም የተሳሳተ አጠቃቀም ሲኖር መርዛማ ሊሆኑ ይችላሉ። ከእዚህ መሃል የህመም ማስታገሻዎች፣ የእንቅልፍ ክኒኖችና ለአእምሮ ጤና የሚሰጡ መድኃኒቶች ተጠቃሽ ናቸው። ምልክቶቹ እንደተወሰደው መድሐኒት ፈጽሞ የሚለያዩ ቢሆኑም፤ ማስታገሻ መድሐኒት አብዝቶ ሲወሰድ ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች፦
ከፍተኛ ማንቀላፋት ወይም ድብርት፣
ግራ መጋባትና የንግግር መዛባት፣
የመተንፈስ መቸገር፣
እራስን መሳት ወይም መንቀጥቀጥ ናቸው።
ምን ማድረግ አለብዎት?
✅ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ። እቤትዎ እርዳታ ለማድረግ አይሞክሩ!
✅ ተጎጂውን ወደ ሀኪም ቤት ይዘው ሲሄዱ፤ የወሰደውን የመድኃኒት አቃፊ፣ ጠርሙስ ወይም ሽፋን አብረው ይውሰዱ።
✅ ከባድ ምልክቶች እስኪታዩ ድረስ በፍጹም አይጠብቁ።
4. የአይጥ መርዞች (Rodenticides)

በየገበያዎች ለተባይ መከላከያ ተብለው በብዛት የሚሸጡ አንዳንድ የአይጥ ማጥፊያ ውህዶች (በተለይም የአሉሚኒየም ፎስፋይድ/Aluminum Phosphide ያለባችው) ከፍተኛ መርዛማነት አላቸው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ከተዋጡ በኋላ፤ በሆድ ውስጥ ካለው እርጥበት እና አሲድ ጋር ሲገናኙ፤ "ፎስፊን" (Phosphine Gas) የተባለ ጋዝ ይለቃሉ። ይህ ጋዝ ፈጣን፣ አደገኛ ለነርቭና ሳንባ ገዳይ የሆነ ኋይለኛ መርዝ ነው።
በውስጣቸው ስትሪችኒን (Strychnine)የሚባለው ውህድ ያለባቸው የአይጥ መርዞች ደግሞ በቀጥታ ነርቭን ያጠቃሉ። ይህ መርዝ በሰውነታችን ውስጥ ጡንቻዎች እንዲላሉ የሚያደርገውን "ግላይሲን" (Glycine) የተባለውን የነርቭ መግባቢያ ሙሉ በሙሉ ይዘጋል። በዚህም ምክንያት የሰውነት ጡንቻዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ በኃይል እንዲሸማቀቁና እንዲገተሩ አድርጎ ይገድላል።
መመረዝን የሚያሳዩ ምልክቶች፦
አሉምኒየም ፎስፋይድ ከሆነ፦
የነጭ ሽንኩርት መሰል የትንፋሽ ሽታ፣
በአፍና በጉሮሮ አካባቢ ኃይለኛ የማቃጠል ስሜት፣
ከባድና የማያቋርጥ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ እና የሆድ መጮህ (ቁርጠት)፣
የትንፋሽ ማጠር፣ የደረት መወጠር እና ከባድ ሳል፣
የልብ ምት መዛባት እና የደም ግፊት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ፣
መቅበጥበጥ፣ ራስ ምታት፣ ድካም አልያም በአጭር ሰዓት ውስጥ ራስን መሳት ያሳያል።
ስትሪችኒን ከሆነ
ከባድ የጡንቻ መገተር፣
መላ አካልን ላይ ያለ ብርቱ መሸማቀቅ (Opisthotonus)፣
መንጋጋ መቆለፍ፣
መጠነኛ ድምፅ ወይም ብርሃን ሲኖር የሚቀሰቀስ ኃይለኛ እረፍት ማጣት እና
በመጨረሻም የመተንፈሻ ጡንቻዎች በመገታተራቸው ምክንያት የሚመጣ መታፈን ይኖራል።
ምን ማድረግ አለብዎት?
✅ ይሄ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ የድንገተኛ አደጋ ነው። ተጎጂውም ሆነ አጠገቡ ያሉ ሰዎች ተጨማሪ መርዛማ ጋዝ እንዳይተነፍሱ (አልሙኒየም ፎስፋይድ ከሆነ) ወዲያውኑ ወደ ግልጽና አየር ወደሚገኝበት ቦታ መወሰድ አለባቸው።
✅ተጎጂው ስትሪችኒን የዋጠ ከሆነ፣ ንክኪ፣ ጫጫታ እና ብርሃን የጡንቻ መሸማቀቁን ስለሚያባብሱት ተጎጂውን በተቻለ መጠን ጸጥ ባለና ጨለምለም ባለ ስፍራ ማቆየት ያስፈልጋል።
✅ በአፋጣኝ ጤና አቅራቢያ ወዳለ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ይውሰዱ።
ማድረግ የሌለብዎት!
❌ የአይጥ መርዝ ለዋጠ ሰው ውሃ ወይም ማንኛውንም ፈሳሽ በአፍ በፍጹም አይስጡ። ውሃ ወይም ሌሎች ፈሳሾች በሆድ ውስጥ ያለውን የፎስፊን መፈጠር ሊጨምሩ ስለሚችሉ ፤ መርዛማ ጋዙ ይበልጥ እንዲለቀቅና ጉዳቱ እንዲባባስ ያደርጋል።
❌በስትሪችኒን መመረዝ ላይ ማስመለስን ለመቀስቀስ መሞከር ገዳይ የሆነ የሰውነት መሸማቀቅ/መንቀጥቀጥ (Seizures) ወዲያውኑ ሊቀሰቅስ ይችላል።ለዚህም ለማስመለስ እንዳይሞክሩ።
ከሁሉ የተሻለው ሕክምና፤ መከላከል!

አብዛኛዎቹ የመመረዝ አደጋዎች ቀላል በሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች መከላከል የሚቻሉ ናቸው፦
✅ የእርሻ ኬሚካሎችንና ተባይ ማጥፊያዎችን ከምግብና ከሕፃናት እጅ ሙሉ በሙሉ ያርቁ።
✅ ኬሚካሎችን ሁልጊዜም በነበሩበት /በተመረቱበት (ኦሪጅናል) መያዣ ላይ ብቻ ያስቀምጡ።
✅ በፍጹም ኬሚካሎችን በውሃ ጠርሙስ፣ በለስላሳ፣ ወይም በጭማቂ መያዣዎች ውስጥ አያስቀምጡ። ሕፃናት ውሃ መስሏቸው ሊጠጡት ይችላሉ።
✅ መድኃኒቶችን ቁልፍ ባለው ሳጥን ወይም ከፍ ባለ ቦታ ላይ ያስቀምጡ።
✅ ከባድ የስነ-ልቦና እና የስሜት ጭንቀት ለሚገጥማቸው ወዳጅ ዘመዶችዎ ፤ አለኝታ ይሁኗቸው። የባለሙያ የአእምሮ ጤና ድጋፍ እንዲያገኙ ያግዟቸው።




Comments