MRI ወይስ CT Scan? የትኛው የተሻለ ነው?
አንዲት ሴት ሰሞኑን እንዲህ ስትል ጠየቀች.... “ለመሆኑ ሙሉ ጤናዬን በደንብ ተመርምሬ፤ ያለብኝን የተደበቀ በሽታ ሁሉ ለማወቅ፤ CT ስካን ባደርግ ይሻላል ወይስ MRI? የቱ ነው የሚበልጠው?”

ይህ ጥያቄ የእሷ ብቻ አይደለም! በአሁኑ ጊዜ የሲቲ ስካን እና የኤም አር አይ አገልግሎቶች በየሆስፒታሉ እየተስፋፉ በመምጣታቸው፤ ብዙዎቻችን ተመሳሳይ ሀሳብ ይመላለስብናል። እንዲያውም እነዚህን ዘመናዊ መሣሪያዎች በሰውነታችን ውስጥ የተሸሸገን ማንኛውንም በሽታ ጠራርገው የሚያወጡ ‘የጭንቅ ቀን ደራሾች’ አድርገን የምናስብ ጥቂት አይደለንም።
የውስጥ አካል ችግርን ለመለየት ወይም እጢን ለመመልከት የትኛው እንደሚበልጥ ስንከራከርም እንሰማለን፤ አንዳንዶች MRI ከCT ይበልጥ “ዘመናዊና የላቀ” ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ CT ፈጣንና ቀልጣፋ ስለሆነ ይመርጡታል።
ነገር ግን ነገሩን በጥልቀት ለሚያውቁት የሕክምና ባለሙያዎች እውነቱ በጣም ቀላልና አስገራሚ ነው።

CT እና MRI በፍጹም ተፎካካሪዎች አይደሉም!
አንዱ ከሌላው አይበልጥም! ይልቁንም እንደ መዶሻና መጋዝ የተለያየ ተግባር ነው ያላቸው። አንዱ ሌላውን የሚደግፉ ብልህ መሣሪያዎች ናቸው። ዛሬ በሰውነታችን ውስጥ ያሉትን ምስጢሮች ፈልፍለው የሚያወጡትን የእነዚህን ሁለት መሣሪያዎች እውነተኛ ማንነት፣ ጥቅምና ልዩነት በግልጽ እንፈትሻለን።
ለመሆኑ CT እና MRI ምንድናቸው? እንዴትስ ይሰራሉ?
እነዚህን መሣሪያዎች ወደ ውስጥ ገብተን ስንመረምራቸው፤ በስተጀርባ ያሉት ሳይንሳዊ ምስጢሮችና አሰራራቸው ፍጹም የተለያዩ ሆነው እናገኛቸዋለን።

CT Scan (ኮምፒውተራይዝድ ቶሞግራፊ)፦ ይህ መሣሪያ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታከለበት የ ኤክስ ሬይ (X-ray) ስሪት ነው። ተራው የኤክስ ሬይ ምስል አንድ ባለ ሁለት ገጽ (2D) ምስል ብቻ የሚያሳይ ሲሆን፤ የሲቲ ስካን ግን በከፍተኛ ፍጥነት በሰውነታችን ዙሪያ በመሽከርከር ብዙ የኤክስ ሬይ ምስሎችን ያነሳል። እነኝህን በ ኤክስሬይ ጨረር የተነሱ ምስሎች ሰብስቦ፤ የሰውነታችንን የውስጥ አካላት ልክ እንደ ዳቦ ተቆራርጠው (cross-sectional images) በግልጽ እንዲታዩ ያደርጋቸዋል።

MRI (ማግኔቲክ ሬዞናንስ ኢሜጂንግ)፦ ይህ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው። MRI ምንም ዓይነት የኤክስሬይ ጨረር አይጠቀምም። ይልቁንም በውስጡ በጣም ኃይለኛ የሆነ የማግኔት እና የሬዲዮ ሞገዶችን ይዟል። መሣሪያው በሰውነታችን ውስጥ ያሉትን የሃይድሮጂን አተሞች በማንቀሳቀስ፤ በተለይ ለስላሳ የሆኑትን የሰውነት ክፍሎቻችንን እጅግ ጥራት ባለውና ዝርዝር በሆነ ምስል ይቀርጻቸዋል።
ብዙዎች የሚሳሳቱት እዚህ ጋ ነው፤ MRI ጨረር ስለማይጠቀም ብቻ ሁልጊዜ ከCT የተሻለ ምርመራ ነው ማለት በፍጹም አይደለም! እያንዳንዱ መሣሪያ የራሱ የሆነ የማይተካ ሚና አለው።
⚡ CT መቼ ይመረጣል?

ብዙዎች MRIን “የበለጠ ዘመናዊ” አድርገው ስለሚቆጥሩት፤ ሲቲ ስካን ጥቅሙ ያነሰ ሊመስላቸው ይችላል። ነገር ግን በተግባራዊ የሕክምና ዓለም ውስጥ ሲቲ ስካን ወደር የሌለው የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝበት ሁለት ትልልቅ ሳይንሳዊ ምክንያቶች አሉት። እነሱም ፍጥነቱ እና ለአንዳንድ የሰውነት ክፍሎች ያለው ልዩ የምስል ጥራት (Resolution) ነው።
ፍጥነቱ!
አንድ የኤምአርአይ (MRI) ምርመራ ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ሊወስድ ሲችል፤ የሲቲ ስካን (CT) ምርመራ ግን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ይጠናቀቃል። ይህ የጊዜ ልዩነት በሕክምናው ዓለም በሕይወትና በሞት መካከል ያለ ልዩነት ሊሆን ይችላል።
ለዚህም በድንገተኛ አደጋ ጊዜ፤ በአፋጣኝ ህክምናዊ እርምጃ መውሰድ በሚያስፈልግበት ጊዜ ተመራጭ ይሆናል።

የምስል ጥራቱ!
ከፍጥነቱ በተጨማሪ፤ በሳይንሳዊው የሕክምና እይታ ሲቲ ስካን ለአጥንት (Bone structure) ያለው የምስል ጥራትና ንፅፅር ከኤም አር አይ ይልቅ እጅግ የላቀ ነው። ለዚህም ውስብስብና ጥቃቅን የሆኑ የአጥንት ስብራቶችን (በተለይ መገጣጠሚያዎች አካባቢ ያሉ) በግልጽ ያሳያል። አዲስ የፈሰሰ ደምም በሲቲ ስካን ላይ በነጭ ቀለም ፍንትው ብሎ ስለሚታይ ሐኪሞች በቀላሉ እንዲለዩት ይረዳል። ስለዚህም በአስቸኳይ እና በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሲቲ ስካን የመጀመሪያውና ተመራጩ መሣሪያ ነው።
ከዚህም ባሻገር ሲቲ ስካን በውስጣቸው አየር የያዙ አካላትን፣ ውስብስብ የሰውነት አካላትን እንዲሁም የደም ስሮችን በተሻለ ጥራት የማሳየት ብቃት አለው። በተለይ የሳንባ፣ የደረትና የሆድ ውስጥ አካላትን፣ አንዳንድ ካንሰሮችን ለመመርመርና ካንሰር ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች መሰራጨቱን ለማየት በስፋት ይጠቅማል። ግን የትኛው ምርመራ እንደሚመረጥ በካንሰሩ ዓይነትና በሚፈለገው መረጃ ይወሰናል።
ታድያ MRI መቼ ይበልጥ ይጠቅማል?

ሲቲ ስካን ለፍጥነትና ለአጥንት ምርመራ ቀዳሚ እንደሆነ ሁሉ፤ ኤም አር አይ (MRI) ደግሞ ለስላሳ የሰውነት ክፍሎችን ዘልቆ በመመልከት ረገድ ተወዳዳሪ አይገኝለትም።
እነኝህ ለስላሳ የሰውነት ክፍሎች (እንደ አንጎል፣ ነርቭና ጡንቻዎች)፤ በውስጣቸው ከፍተኛ የውሃ መጠን ስላላቸው፤ ኤም አር አይ ከፍተኛ በሆነ የምስል ጥራት ያሳያቸዋል። ለዚህም ሲቲ ስካን እንዲሁ በደብዛዛው የሚያልፋቸውን ረቂቅ የውስጥ አካላት መዋቅር፣ MRI ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ስለዚህ የአንጎል፣ የአከርካሪ አጥንት፣ የጡንቻ ወይም የጅማት ችግር ሲጠረጠር ኤም አር አይ በብዙ ሁኔታዎች ከሲቲ የበለጠ ዝርዝር መረጃ ይሰጣል። በተለይም ፦
ለአንጎል እጢዎች፣
ለጥቃቅን የአንጎል ጉዳቶች፣
ለአከርካሪ አጥንት ችግሮች፣
ለዲስክ መንሸራተት፣
የጉልበት እና ትከሻ ጅማቶች መጎዳት/ መበጠስ፣
ለጡንቻ እና ጅማት ችግሮች፣
ለአንዳንድ ከለስላሳ አካላት የሚነሱ ካንሰሮች ኤም አር አይ ይመረጣል።
ትልቁ ትርፍ፡ የደህንነት ስጋት አለመኖሩ!

የኤም አር አይ ሌላው ትልቅ ጥቅሙ ምንም ዓይነት የኤክስሬይ ጨረር (Ionizing radiation) የሌለው መሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ ምርመራ ለሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞችና ለነፍሰ ጡር እናቶች (በተለይ ሶስት ወር ጀምሮ ) ይበልጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ምርጫ ያደርገዋል።
ነገር ግን CT አስፈላጊ ከሆነ በእርግዝና ምክንያት ብቻ አይከለከልም።
ኤም አር አይ የራሱ የሆኑ ጥንቃቄዎች አሉት። መሣሪያው እጅግ ኃይለኛ ማግኔት በመሆኑ፦
በሰውነታቸው ውስጥ የልብ ማስተካከያ (Pacemaker) ያላቸው፣
በአጥንት ቀዶ ጥገና ሰው ሰራሽ የብረት መገጣጠሚያዎች የተደረገላቸው፣
የብረት ስብርባሪ ውስጣቸው ያለ ታካሚዎች፤ ኤም አር አይ ማሽን ውስጥ ከመግባታቸው በፊት፤ ባለሙያ ማማከር ይኖባቸዋል። ለእነርሱ ማግኔቱ ውስጣቸው ያለውን ብረት ስለሚስብና ከፍተኛ ሙቀት ስለሚፈጥር አደገኛ ሊሆን ይችላል።
☢️ የሲቲ ስካን የጨረር ስጋትስ እንዴት ይታያል?

ይህ እንግዲህ በሁለቱ መሣሪያዎች መካከል ያለው እጅግ መሠረታዊና ጥቅምን ከጉዳት ጋር አገናዝቦ የመወሰኛ ትልቁ ነጥብ ነው።
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሲቲ ስካን የኤክስሬይ (Ionizing radiation) ጨረርን ይጠቀማል። ይህ ጨረር ደግሞ በብዛትና ያለ አግባብ ሲደጋገም በሰውነት ህዋሳት ላይ ጉዳት የማድረስ እምቅ አቅም አለው። በዚህም ምክንያት አስፈላጊ ያልሆነ የሲቲ ስካን ምርመራን ያለምክንያት መደጋገም በፍጹም አይመከርም። በተለይም ሕፃናት ለአዋቂዎች ከተዘጋጀ የጨረር መጠን ጋር እንዳይጋለጡና ለወደፊት የጤና ስጋት እንዳይዳረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄና የባለሙያ ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል።
ነገር ግን እዚህ ጋ ሊሰመርበት የሚገባ ትልቅ እውነት አለ፦ “ሲቲ ስካን ጨረር ስላለው ብቻ ሁልጊዜ ኤምአርአይ (MRI) መምረጥ አለብን” ብሎ ማሰብ ፍጹም ስህተት ነው!

ዋናው ሳይንሳዊ ዓላማ፦ ለትክክለኛው ታካሚ፣ ትክክለኛውን ምርመራ፣ በትክክለኛው ምክንያት እና በትክክለኛው ሰዓት ማድረግ ነው!
ያለ ሕክምና ባለሙያ ትዕዛዝ እንዲሁ “ሰውነቴን ሙሉ ለሙሉ ላረጋግጥ” በሚል ሀሳብ ብቻ ወደ እነዚህ መሣሪያዎች መሮጥ ግን ለከፍተኛ የገንዘብ ብክነት፣ አላስፈላጊ የጨረር ተጋላጭነት እና የሥነ-ልቦና ጭንቀት ይዳርጋል። ስለዚህ የትኛው ምርመራ እንደሚያስፈልግዎት ሁልጊዜም ቢሆን ውሳኔውን ለሚያምኑት የሕክምና ባለሙያ ይተው።
ይህ ለምን አስፈለገ?
በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በተለያዩ የጤና ተቋማት የሲቲ ስካን እና የኤምአርአይ አገልግሎቶች በሰፊው እየተስፋፉ በመምጣታቸው፣ “ገንዘቡ ካለኝና አቅሙ ካለኝ ለምን ሰውነቴን በየጊዜው ሙሉ በሙሉ አላስመርምርም?” ብሎ ማሰብ በጣም ቀላልና የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
ነገር ግን ጥሩ ሕክምና ማለት ማሽኖች ውስጥ እየገቡ ሁሉንም ምርመራ ማድረግ አይደለም።
እውነተኛ ጤና የሚጀምረው፤ በትክክለኛው ጊዜ፣ በትክክለኛው ምክንያት፣ ትክክለኛውን ምርመራ ብቻ በማድረግ ነው።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ለአብዛኛዎቹ ገዳይ ለሆኑ የጤና ችግሮች ዋነኛው መከላከያ የሚጀምረው፤ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመተግበር ነው።




Comments