“ይሰማኛል! ግን ቃላቱ አይለዩልኝም?” — በፍጹም ቸል ሊባሉ የማይገቡ የመስማት ችግር ምልክቶች
- Zebeaman Tibebu
- 2 days ago
- 7 min read
"እሰማሃለሁ... ግን የምትለውን ነገር መለየት አልቻልኩም።"
ይህች አጭር ዓረፍተ ነገር ብዙዎች እንደተራ የሚያዩት ቢሆንም፤ የመስማት ችግር እያጋጠመ መሆኑን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።

ብዙ ሰዎች የመስማት ችግር በዕድሜ በገፉ አዋቂዎች ላይ ብቻ የሚከሰት ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከከፍተኛ ፍንዳታ ወይም ከባድ ሕመም በኋላ በድንገት የሚመጣ ይመስላቸዋል። ሁለቱም ግን ሙሉ እውነት አይደሉም።
እውነታው በጣም የተለየ እና ረቂቅ ነው!
ለሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የመስማት ችግር በጣም ቀስ በቀስ ስለሚጀምር መጀመሪያ ላይ ጨርሶ ላያስተውሉት ይችላሉ። በጊዜ ሂደት ውስጥ እየባሰ የሚመጣ ነው። አእምሯቸው ድምፅ ሲቀንስ ራሱን በዝምታ ከሁኔታው ጋር ያስማማል።
ከዚያ ግን ምልክቶቹ በግልጽ መታየት ይጀምራሉ። የቤተሰብ አባላት የሚናገሩትን ነገር በተደጋጋሚ እንዲደግሙ ይገደዳሉ።
እንዲሰማን የቴሌቪዥን ድምጽ እንጨምራለን። በጫጫታ ቦታዎች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ከመደሰት ይልቅ በጣም አድካሚ ይሆናሉ።
ሰዎች "የመስማት ችግር የለብኝም፤ ሰዎች ግን በግልጽ አይናገሩም" ብለው ማሰብ ይጀምራሉ። ነገር ግን ወደ ሕክምና በሚሄዱበት ጊዜ፤ የተወሰነው የመስማት ችሎታቸው አስቀድሞ በቋሚነት ተጎድቶ ሊሆን ይችላል። እርስዎ ግን ይህንን ዋጋ መክፈል አይገባዎትም።
የመስማት ችግርን የሚያስከትሉ በርካታ ምክንያቶች፤ በተለይም ቀድመው ከተገኙ፤ ሊከላከሏቸው፤ ሊታከሙ ወይም በቀላሉ ሊታገሱ የሚችሉ ናቸው። ዓለምዎን በሙሉ ድምፅዋ መልሰው ማግኘት ይችላሉ።
ዛሬውኑ ጆሮዎ ሊነግሩዎት የሚሞክሩትን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች በዝርዝር እንመርምር።
መስማት ይህን ያህል ለምን አስፈላጊ ሆነ?

የመስማት ችሎታችን ከምናስበው በላይ ለሕይወታችን ወሳኝ ነው። ጆሮዎቻችን ድምፅን ማጣት ሲጀምሩ፤ አእምሯችን ጠንክሮ ለመሥራት ስለሚገደድ ከፍተኛ ለአእምሮ ድካም ከማጋለጡ ባሻገር፤ ከመርሳት በሽታ ጋር ይያዛል። በተጨማሪም ውይይቶችን መከታተል ባለመቻላችን፤ ራሳችንን ከሰዎች እንድናገልልና ለድብርት እንድንጋለጥ ያደርገናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ የውስጠኛው ጆሮ የሰውነታችንን ሚዛን ስለሚጠብቅ፤ የመስማት ችግር ሲኖር በአካባቢያችን ያሉትን አደጋዎች አስቀድሞ የመለየት አቅማችን ይቀንሳል። የመውደቅ አደጋም ይጨምራል።ለዚህም የመስማት ችሎታ በሚቀንስበት ጊዜ፤ የዕለት ተዕለት ሕይወትን እያንዳንዱን ገጽታ ይነካል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚያስቀምጠው፤ በዓለም ዙሪያ ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ የመስማት ችግር አለባቸው። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ፤ ማገገሚያ (rehabilitation) የሚያስፈልገው ከፍተኛ የመስማት ችግር ይገጥማቸዋል። ይህ ቁጥር ዝም ብሎ ስታቲስቲክስ አይደለም። ከጀርባው የብዙ ሰዎች ሕይወት ግንኙነት እና ደስታ አለ።
የመስማት ችግርን መረዳት
የመስማት ችግር የሚከሰተው ድምፅን ከአካባቢያችን ተቀብሎ ወደ አእምሯችን የሚያስተላልፈው አስደናቂው የተፈጥሮ መስመር በትክክል ሳይሠራ ሲቀር ነው። ልክ እንደ ስልክ መስመር መቆራረጥ፤ ችግሩ ከየትኛው የጆሮ ክፍል እንደሚነሳ በመነሳት በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ይገለጻል፦

1. ድምጽን የማስተላለፍ ችግር (Conductive Hearing Loss)
በዚህ ጊዜ ድምጽ ወደ ውስጠኛው ጆሮ በብቃት መድረስ አይችልም። ልክ በሩ በጥብቅ ተዘግቶ ድምፅ ከውጭ እንደሚሰማው ሁሉ፤ በዙሪያዎ ያለው ዓለም በሙሉ ደብዝዞና ርቆ ይሰማዎታል። ይህ የሚሆነው በድምፅ ማስተላለፊያ መንገዱ ላይ እንቅፋት ሲኖር ነው። ለዚህም የተለመዱ ምክንያቶችም የሚከተሉት ናቸው፦
የጆሮ ኩክ በከፍተኛ ሁኔታ መከማቸት
በጆሮ ውስጥ የሚፈጠር አስቸጋሪ ኢንፌክሽን
ከታምቡር ጀርባ ፈሳሽ መኖር
የጆሮ ታምቡር መበሳት ወይም መቀደድ
የመካከለኛው ጆሮ አጥንቶች ላይ የሚከሰቱ የእንቅስቃሴ ችግሮች
ትልቁ ተስፋ ግን እዚህ ላይ ነው። እነዚህ አብዛኛዎቹ ሁኔታዎች በሕክምና ወይም በቀላል ቀዶ ጥገና ሙሉ በሙሉ ሊታከሙና ሊስተካከሉ የሚችሉ ናቸው።

2. የነርቭ መስማት ችግር (Sensorineural Hearing Loss)
ይህ ዓይነቱ ችግር የሚከሰተው ድምፅን ተቀብሎ ወደ አእምሮ በሚያስተላልፈው ዋናው መዋቅር ላይ ጉዳት ሲደርስ ነው። ይህም
በኮክሊያ (cochlea) ውስጥ ባሉ ረቂቅ እና ስስ የፀጉር ህዋሳት ላይ፤ አልያም ድምፅን ወደ አእምሮ በቀጥታ በሚወስደው በመስማት ነርቭ ላይ ጉዳት ሲደርስ ይህ ያጋጥማል።
ይህንን ጉዳት የሚያስከትሉ ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
ከዕድሜ ጋር ተያይዞ
ለረጅም ጊዜ ለከፍተኛ ጫጫታ መጋለጥ (ለምሳሌ፦ በሥራ ቦታ ወይም በጆሮ ማዳመጫ)
ለጆሮ ነርቭ መርዛማ የሆኑ አንዳንድ መድኃኒቶች መውሰድ
የውስጠኛውን ጆሮ የሚያጠቁ ከባድ ኢንፌክሽኖች
በቤተሰብ የሚዋረዱ የዘር (የጄኔቲክ) ችግሮች
ይህ ዓይነቱ የመስማት ችግር አብዛኛውን ጊዜ ዘላቂ (የማይመለስ) ነው። አንዴ ከጠፋ መልሶ ማግኘት ስለማይቻል፤ ጆሮን አስቀድሞ መከላከል እና ልዩ ትኩረት መስጠት የህልውና ጉዳይ ነው።
3. ሁለቱንም ያጣመረ የመስማት ችግር (Mixed Hearing Loss)
ይህ ከላይ የጠቀስናቸውን ሁለቱንም የመስማት ችግሮች የሚያካትት ነው። ይህ ደግሞ ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል። ለምሳሌ ፦ በዕድሜ መግፋት ምክንያት የነርቭ መስማት ችግር ያለበት ሰው፤ በተጨማሪ የጆሮ ኩክ ቢከማችበት ወይም ኢንፌክሽን ቢይዘው የዚህ ችግር ሰለባ ይሆናል።
በፍጹም ቸል ሊሏቸው የማይገቡ 10 የቀደሙ ምልክቶች
የመስማት ችሎታችን በአንድ ጀንበር አይጠፋም። ይልቁንም ቀስ እያለ በስውር ነው የሚሰርቀን። አእምሯችንም ድምፅ ሲቀንስ ራሱን በዝምታ ለማስማማት ስለሚሞክር ፤ብዙ ጊዜ ምልክቶቹን ሳናስተውላቸው እንቀራለን። ነገር ግን ጆሯችን እርዳታ ሲሻ፤ የሚከተሉትን 10 ግልጽ ምልክቶች ያሳየናል፦

1. ሰዎች የሚያወሩት ቃላት በግልጽ አይሰሙም።
ይህ ብዙውን ጊዜ የመጀመሪያው እና ዋነኛው ምልክት ነው። ድምጾች ይሰሙዎታል... ግን ቃላቱን ለይቶ ለመረዳት ይቸገራሉ። ንግግሮች በቀላሉ ድምፃቸው ከማነስ ይልቅ፤ ግልጽነታቸው ጠፍቶ ድምፅ ብቻ ይሆኑብዎታል።
2. ሰዎችን በተደጋጋሚ "ምን አልህ/ሽ?" ብሎ መጠየቅ
በዕለት ተዕለት ውይይቶች ወቅት "ምን?" ፤ "ልትደግምልኝ ትችላለህ?" ወይም "እባክህ ድገመው" የሚሉ ቃላትን በተደጋጋሚ መጠቀም ከጀመሩ ያስተውሉ! ይህ በቀላሉ በትኩረት ማጣት ሳይሆን፤ ጆሮዎ የመስማት አቅሙ እየቀነሰ ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
3. የቲቪ ወይም የራዲዮ ድምጽን ሌሎች ከሚፈልጉት በላይ ከፍ ማድረግ
የቤተሰብ አባላት "የቲቪው ድምጽ በጣም ይጮኻል!" ብለው በተደጋጋሚ ያማርራሉ? የድምጹ መጠን ለእርስዎ ፍጹም መደበኛ ሆኖ ሳለ ለሌሎች ግን የሚረብሽ ከሆነ፤ የመስማት አቅምዎን ለመመርመር ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው።

4. በተጨናነቁ ቦታዎች ለመስማት መቸገር
ምግብ ቤቶች፣ ገበያዎች፣ የሃይማኖት ቦታዎች ወይም የቤተሰብ ስብሰባዎች ላይ ንግግርን ከጀርባ ካለው ጫጫታ ለይቶ ማዳመጥ ያቅትዎታል። ብዙ ሰዎች ችግሩ እንዳለባቸው መጀመሪያ የሚያስተውሉት እዚህ ላይ ሲሆን፤ ይህ ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የመስማት ችግር የመጀመሪያው ምልክት ነው።
5. ቀጫጭን (ከፍተኛ ፍሪኩዌንሲ ያላቸው) ድምጾችን ማጣት
አንዳንድ ድምጾችን ቀስ በቀስ መስማት ያቆማሉ። የወፎች ጫጫታ፣ የልጆች የለሰለሰ ድምጽ፣ የስልክ መልዕክት ድምጾች፣ የበር ደወል ወይም የማንቂያ ድምጾች ማስተዋል ካቆሙ፤ ከፍተኛ ፍሪኩዌንሲ (high-frequency) ያላቸውን ድምጾች የመስማት አቅምዎ መቀነሱን ያሳያል።
6. በጆሮ ውስጥ የሚጮህ ድምጽ (Tinnitus)
አካባቢው ሙሉ በሙሉ ጸጥ ባለበት ጊዜ እንኳ፤ በጆሮዎ ውስጥ ቴሌቭዝን ሲዘጋ አይነት አልያም፤ የሚጮህ ድምጽ ይሰማዎታል? የጆሮ መጮህ (tinnitus) ሌላም የጤና ምክንያት ሊኖረው ቢችልም፤ አብዛኛውን ጊዜ ከመስማት ችግር ጋር አብሮ የሚመጣ መንታ ምልክት ነው።

7. በስልክ ለመነጋገር መቸገር
በአካል ሲነጋገሩ የፊት ገጽታን ወይም የከንፈር እንቅስቃሴን አይተው የሚረዱት ነገር፤ በስልክ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ይጠፋል። ብዙ ሰዎች ይህን ጊዜ የሚያጋጥም የመስማት ችግር፤ በስህተት "የስልክ መስመር መቆራረጥ ነው" ብለው ያስባሉ። ከተደጋገመ የመስማት ችግር ስለሚሆን፤ የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
8. ከንግግሮች በኋላ የድካም ስሜት መሰማት
ማዳመጥ ራሱ እንደ ትልቅ ጉልበት የሚጠይቅ ሥራ ይሆንብዎታል። አእምሮዎ ያልሰማቸውን የንግግር ክፍሎች በግምት "ለመሙላት" ከባድ ሥራ መሥራት ስላለበት፤ ከጥቂት ውይይት በኋላ የአእምሮ ድካም፣ በትኩረት ለመስራት መቸገር፣ እና ብስጭት ይስተዋላል።
9. ማኅበራዊ ስብሰባዎችን መሸሽ
እነኝህ ግለሰቦች ውይይቶች አስጨናቂ ሲሆኑባቸው፤ ቀስ በቀስ ከቤተሰብ ፕሮግራሞች፣ ከሃይማኖታዊና፣ ከማኅበረሰብ ስብሰባዎች መራቅ ይጀምራሉ። ያልታከመ የመስማት ችግር ሰዎችን ለብቻኝነት እና ለሕይወት ጥራት መበላሸት ይዳርጋል።
10. እርስዎ ሳያስተውሉ ቤተሰብዎ አስቀድሞ ያስተውላል
የሚያስገርመው ነገር፤ የቅርብ ዘመዶች እና ጓደኞች የመስማት ችግርን ከተጎጂው ሰው በፊት ቀድመው ይረዳሉ። የሚወዷቸው ሰዎች ስለ መስማትዎ በተደጋጋሚ ስጋታቸውን እና አስተያየታቸውን ከገለጹ፤ ጉዳዩን በቀላሉ ሳይሆን በትኩረት ይመልከቱት።
ይበልጥ የተጋለጡት እነማን ናቸው?

የመስማት ችግር በማንኛውም ሰው ላይ፤ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን ለአንዳንዶቻችን የዕለት ተዕለት ውሳኔዎቻችን፤ የሥራ አካባቢያችን ወይም የጤና ሁኔታችን ለዚህ አደጋ ይበልጥ ተጋላጭ ያደርጉናል።ለዚህም እነኝህ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ ፤ የመስማት ጤናቸውን በልዩ ሁኔታ ሊጠብቁና ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል።
የዕድሜ ባለጸጎች ፦ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ በጆሮ ውስጥ ያሉ ረቂቅ የፀጉር ሕዋሳት በተፈጥሮ የመዛል እና የመሞት ዕድላቸው ስለሚጨምር፤ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ይሆናል።
በጫጫታ ድምፅ ውስጥ የሚሠሩ፦ እንደ ኮንስትራክሽን፣ ፋብሪካ፣ የምሽት ክበብ (ክለቦች)፣ አውሮፕላን ማረፊያ ወይም በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በከፍተኛ ጫጫታ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች፤ ጆሯቸው በየቀኑ ለአደጋ ይጋለጣል።
የጆሮ ማዳመጫ (Earphones/Headphones) አዘውታሪዎች፦ በጆሮ ማዳመጫ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ሙዚቃ የሚያዳምጡ፤ በተለይም ወጣቶች፣ የጆሮአቸውን ሕዋሳትን ሳያውቁት ቀስ በቀስ ይጎዳሉ።
ሥር የሰደደ የጤና እክል ያለባቸው፦ የደም ግፊት ወይም የስኳር ሕመም ያለባቸው ሰዎች የደም ዝውውር መዛባት ስለሚኖርባቸው፤ ወደ ውስጠኛው ጆሮ የሚሄደው የደም ፍሰት ቀንሶ ለነርቭ መጎዳት ይዳረጋሉ።
ተደጋጋሚ የጆሮ ኢንፌክሽን የሚገጥማቸው፦ በልጅነትም ሆነ በአዋቂነት ዕድሜ የጆሮ ኢንፌክሽንን በአግባቡ ሳይታከሙ ከቆየ፤ ታምቡርንና የመካከለኛውን ጆሮ አጥንቶች በቋሚነት ሊያበላሽ ይችላል።
የዘር ውርስ (የጄኔቲክ) ታሪክ ያላቸው፦ በቤተሰብ ውስጥ ቀድሞ የመስማት ችግር ያጋጠመው የቅርብ ዘመድ ካለ፤ በተፈጥሮ ለችግሩ የመጋለጥ ዕድል ከፍ ይላል።
መስማትን የሚጎዱ መድኃኒቶችን (Ototoxic) የሚወስዱ፦ ለአንዳንድ ከባድ ሕመሞች የሚታዘዙ አንቲባዮቲክስ፣ የካንሰር መድኃኒቶች ወይም በብዛት የሚወሰዱ የሕመም ማስታገሻዎች፤ ጆሮን የመጉዳት ስውር የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው። ስለዚህም ሐኪምዎን ያማክሩ።
ሌሎች የአኗኗር ዘይቤና ድንገተኛ አደጋዎች፦ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ( ወደ ጆሮ የሚሄደውን ኦክስጅን ስለሚቀንሱ)፤ እንዲሁም በድንገተኛ አደጋ የራስ ቅል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የመስማት ችሎታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።
በሕፃናት ላይስ?

ሕፃናት የመስማት ችግር እንዳለባቸው ራሳቸው አውቀው ሊናገሩ ስለማይችሉ፤ ወላጆች የሚከተሉትን ስውር ምልክቶች በንቃት መከታተል አለባቸው። የመስማት ችሎታ በቋንቋ እድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና ስላለው፤ ልጁ እንደ ዕድሜው መናገር ካልጀመረ ወይም የንግግር እድገት መዘግየት ካሳየ፤ ጆሮውን ማስመርመር ያስፈልጋል። እንዲሁም ልጁ በተደጋጋሚ "ምን?" የሚል ከሆነ፣ ሲጠሩት ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ ወይም ካርቱን ሲያይ የቲቪ ድምጽን ከልክ በላይ የሚጨምር ከሆነ ሳይሰማ ቀርቶ ሊሆን ይችላል። ይህ ችግር ክፍል ውስጥ መምህራን የሚናገሩት ነገር እንዳይሰማው በማድረግ፤ በትምህርት ቤት ደካማ ውጤት እንዲያመጣ ያደርገዋል።
ልጅዎ ላይ እነዚህን ምልክቶች ካስተዋሉ፤ ወደ ሕክምና ባለሙያ በመውሰድ አስቀድሞ መመርመር ወሳኝ ነው።
የመስማት ችግር መቼ ነው አስቸኳይ የሕክምና ጉዳይ የሚሆነው?

የመስማት ችግሩ የሚከተሉትን ካሳየ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ይሂዱ፦
በሰዓታት ወይም በጥቂት ቀናት ውስጥ በድንገት ከተከሰተ
ከራስ ቅል ጉዳት በኋላ ከተከሰተ
ከከፍተኛ የማዞር ስሜት ጋር ከተያያዘ
ከፊት ጡንቻዎች መድከም (ሽባ መሆን) ጋር ከመጣ
ከከፍተኛ የጆሮ ሕመም፣ በጆሮ ደም መፍሰስ ወይም ፈሳሽ መውጣት ጋር ከተያያዘ
በድንገት የሚከሰት የነርቭ መስማት ችግር (Sudden sensorineural hearing loss) በፍጥነት ከታከመ፤ የመስማት አቅምን መልሶ ለማግኘት የተሻለ ዕድል ይሰጣል።
ሐኪሞች የመስማት ችግርን እንዴት ይመረምራሉ?

የመስማት ችግርን በትክክል ለማከም መነሻ ምክንያቱን ጠንቅቆ ማወቅ ቀዳሚው ተግባር ነው። ምርመራው አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው የሕክምና ታሪክን በመጠየቅ እና በልዩ መሣሪያ የጆሮን ውስጣዊ ክፍል በመመልከት (Otoscopy) ነው። ይህም በኩክ መዘጋቱን ወይም ኢንፌክሽን መኖሩን ለመለየት ይረዳል።
በመቀጠልም የተለያዩ ድምፆችን በማሰማት የመስማት ፈተናዎች (Audiometry) ይደረጋሉ። እንደ አስፈላጊነቱም የድምፅ ሞገዶች በአጥንት በኩል እንዴት እንደሚተላለፉ በቲዩኒንግ ፎርክ (Tuning fork) ይመረመራል። ከዚህ በተጨማሪም የመካከለኛው ጆሮ እና የታምቡር ሥራን ለመገምገም የሚደረግ ምርመራ (Tympanometry)፣ የራጅ (Imaging) ወይም የላቦራቶሪ ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ።
የመስማት ችግር ሊታከም ይችላል?

አዎ! የመስማት ችግር ሊታከም ይችላል። ሕክምናው ግን ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው፤ በችግሩ መሠረታዊ ምክንያት ላይ ነው። ለምሳሌ፦ ለጆሮ ኢንፌክሽኖች፣ ለጆሮ እብጠት ወይም በጥቂት ቀናት ውስጥ በድንገት ለሚከሰቱ የመስማት ችግሮች በመድኃኒት የሚደረግ ሕክምና ፍቱን መፍትሔ ይሰጣል።
ችግሩ የጆሮ ኩክ መከማቸት ከሆነ ደግሞ፤ በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት በደኅንነት እንዲወገድ ይደረጋል። ዘላቂ የነርቭ የመስማት ችግር ላለባቸው በርካታ ሰዎች ደግሞ ዘመናዊ የመስሚያ መርጃ መሣሪያዎች (Hearing aids) ማድረግ፤ የሕይወት ጥራትን በሚያስደንቅ ሁኔታ ያሻሽላል። እነዚህ መሣሪያዎች ብዙም ለማይረዷቸው እና ከፍተኛ የነርቭ መስማት ችግር ላለባቸው ሰዎች ደግሞ፤ የቀዶ ጥገና መፍትሔ ይሰጣል።
የመስማት ችሎታዎን የሚጠብቁባቸው 7 መንገዶች
ዓለምን በሙሉ ድምፅ ለማጣጣም እና ጆሮዎን ከአደጋ ለመጠበቅ፤ እነዚህን 7 ቀላል ግን ወሳኝ የዕለት ተዕለት ልማዶች ይተግብሩ፦

የማዳመጫ መሣሪያዎችን ድምፅ ይቀንሱ፦ የጆሮ ማዳመጫ (Earphones) ሲጠቀሙ ድምፁን ሁልጊዜ ደኅንነቱ በተጠበቀና መጠነኛ በሆነ ደረጃ ላይ ያድርጉ። ጆሮዎን በገዛ እጅዎ ለከፍተኛ ጫጫታ አያጋልጡ።
በሥራ ቦታዎ ጆሮዎን ይሸፍኑ፦ ፋብሪካ፣ ኮንስትራክሽን ወይም ማሽኖች ባሉበት ጫጫታ በሚበዛበት የሥራ አካባቢ የሚውሉ ከሆነ፤ የጆሮ መከላከያዎችን (Earplugs) የማድረጉን ነገር በፍጹም ቸል አይበሉ።
ለኢንፌክሽን ፈጣን እርምጃ ይውሰዱ፦ የጆሮ ሕመም ወይም ፈሳሽ ሲያጋጥምዎት፤ ሳይዘገዩ አስቀድመው ሕክምና ያግኙ። ትናንሽ ኢንፌክሽኖች ሳይታከሙ ከቆዩ ታምቡርን ሊያበላሹ ይችላሉ።
የጥጥ እንጨቶችን (ኩክ መውጫ) ያስወግዱ፦ የጥጥ እንጨቶችን ወይም ማንኛውንም ስለታም ነገር ወደ ጆሮ በፍጹም አያስገቡ። ጆሮ ራሱን በራሱ የማጽዳት ተፈጥሮ አለው። እርስዎ የሚያስገቡት እንጨት ግን ኩኩን ወደ ውስጥ በመግፋት መንገድ ሊዘጋ፤ እንዲሁም ታምቡርዎን ሊቀደው ይችላል።
ሥር የሰደዱ በሽታዎችን ይቆጣጠሩ፦ እንደ ስኳር እና ደም ግፊት ያሉ ሕመሞችን በአግባቡ መከታተልና መቆጣጠር ወደ ጆሮ የሚሄደውን የደም ዝውውር፤ ጤናማ በማድረግ የነርቭ መጎዳትን ይከላከላል።
የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን አይናቁ፦ በጆሮዎ ውስጥ ጥቂት የመጮህ፣ የቃላት መደባለቅ፣ ወይም ሌላ ማንኛውንም ለውጥ ካስተዋሉ፤ ሳይቆዩ የመስማት አቅምዎን በባለሙያ ያስመርምሩ።
ወላጆችን እና አረጋውያንን ይደግፉ፦ መግባባት አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ፤ በዕድሜ የገፉ የቤተሰብ አባላት "ዕድሜው ስለገፋ ነው" ብለው ከመተው ይልቅ፤ የጆሮ ምርመራ እንዲያደርጉ በፍቅር ያበረታቷቸው።
ማጠቃለያ
የመስማት ችግር በድንገት በአንድ ሌሊት አይከሰትም። ይልቁንም ተራ በሚመስሉ የቀን ልማዶች ይጀምራል። እነዚህ ትናንሽ ለውጦች ጉዳት የሌላቸው ቢመስሉም፤ ከባድ የጤና ችግር ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ።
እርስዎ ወይም የሚወዱት ሰው ላይ ከእነዚህ ምልክቶች አንዱን ካስተዋሉ ቸል አይበሉት። በጊዜው የሚደረግ ምርመራ ዘላቂ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።




Comments