የዓይን ግፊት (Glaucoma)፦ ምልክቶቹ፣ መንስኤዎቹ እና ሕክምናው
የዓይንዎን የጤና ምርመራ መቼ ነው ያደረጉት?

አይንዎ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንደሆነ እርግጠኛ ነዎት? ለመሆኑ እንዴት አወቁ?
በአለም ላይ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ልክ እንደ እርስዎ ነበሩ። ጠዋት ከእንቅልፋቸው ይነሳሉ፤ ቁርሳቸውን ይበላሉ። ቀናቸውን መጽሐፍ ሲያነቡ፣ ስልክ ሲጠቀሙና ቴሌቪዥን ሲያዩ ይውላሉ። በኮምፒውተር ላይ ያሉ ትናንሽ ጽሑፎችን በግልጽ እያነበቡ፤ መንገድ ላይ ያለምንም ችግር በነጻነት እየተንቀሳቀሱ ዓመታትን አሳልፈዋል።
ዓይናቸው ፈጽሞ ታሞ አያውቅም፤ ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት፣ መቅላት፣ ብዥታ ወይም ራስ ምታት አልነበረባቸውም። እንዲያውም ቢጠይቋቸው፤ የማየት ችሎታቸው ፍጹም አስተማማኝ እንደሆነ ይመሰክሩ ነበር።
ነገር ግን፤ እነዚህ ሰዎች ወደ ዓይን ሕክምና ለመሄድ የወሰኑት ፤ እይታቸው በድንገት መደበዝዝ ሲጀምር ነበር። ያኔ ግን ዘግይተው ነበር። ለዓመታት ሳይታወቅና ምንም ሕመም ሳይሰማ፤ የዓይናቸውን ነርቭ እየተጎዳ ነበር።

ይህ ግላኮማ (Glaucoma) የሚባለው የዓይን በሽታ አስፈሪ ገጽታ ነው።
እንደእርስዎ ብዙዎች “የዓይን ግፊት” ሲባል ዓይን ላይ የመውጋት፣ የመጫን፣ ወይም የመግፋት ስሜት መኖር እንዳለበት ያስባሉ። እውነታው ግን ፍጹም ተቃራኒ ነው። ግላኮማ ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ሳያሳይ፣ በጸጥታ የዓይንዎን ብርሃን የሚሰርቅ “የብርሃን ሌባ” ነው። እይታዎ ላይ ለውጥ መኖሩን ሲያስተውሉ፤ በሽታው ቀድሞውኑ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ማለት ነው።
ታዲያ ይህ በሽታ እንዴት ይከሰታል? የዓይን ብርሃንንስ ከመጥፋቱ በፊት ምን ማድረግ ይቻላል?
ግላኮማ (Glaucoma) ምንድን ነው?

ዓይናችን በውስጡ የዓይንን ቅርጽ እና ሥራ ለመጠበቅ የሚረዳ ፈሳሽ (Aqueous humor) ያመነጫል። ይህ ፈሳሽ ያለማቋረጥ እየተመረተ፤ በነጻነት እየተዘዋወረ፤ በተፈጥሮ በተዘጋጁ ትንንሽ ቱቦዎች ከዓይን ይወገዳል። ለዓይን ጤና የዚህ ፈሳሽ ዝውውር አስፈላጊ ነው።
ሆኖም የዚህ ፈሳሽ ዑደት ከተሰናከለና ፈሳሹ በትክክል ሳይወገድ ቀርቶ ዓይን ውስጥ መከማቸት ሲጀምር፤ የዓይን ውስጣዊ ግፊት ይጨምራል። ይህ የጨመረው ግፊት ደግሞ፤ ዓይናችን የሚያየውን ምስል ቀጥታ ወደ አእምሯችን የሚወስደውን የዓይን ነርቭ (Optic nerve) ይጫነዋል፤ ቀስ በቀስም ጉዳት ያደርስበታል። ይህም ግላኮማ ይሰኛል።
ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ጠቃሚ ልዩነት አለ።
ግላኮማ ማለት በቀላሉ የዓይን ግፊት መጨመር ማለት አይደለም። የዓይን ግፊት መጨመር ለግላኮማ ዋነኛ የተጋላጭነት ምክንያት ቢሆንም፤ ግፊታቸው መደበኛ በሆነ ሰዎች ላይም የዓይን ነርቭ ጉዳት ሊከሰት ይችላል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የዓይን ግፊታቸው ከፍ ያለ ሁሉም ሰዎች ግላኮማ ይይዛቸዋል ማለትም አይደለም። ስለዚህ የዓይን ግፊትን ብቻ መለካት ግላኮማ እንዳለ ወይም እንደሌለ ለማረጋገጥ በቂ አይደለም።የግላኮማ ዓይነቶች፦ አንዱ በዝግታ፣ ሌላው በድንገት ይመጣል!
ግላኮማ በርካታ ዓይነቶች ቢኖሩትም፤ ሁለቱ ዋና ዋና ዓይነቶች በሽታው ምን ያህል አታላይ እና አደገኛ ሊሆን እንደሚችል በግልጽ ያሳያሉ።
1. በዝግታ የሚመጣው ግላኮማ (Open-angle glaucoma)

ይህ በዓለም ላይም ሆነ በአዋቂዎች ላይ በብዛት የሚታየው ዋነኛው የግላኮማ ዓይነት ነው። በዚህ ጊዜ የዓይን ፈሳሽ የሚወጣበት መንገድ ክፍት ቢመስልም፤ ፈሳሹ በተፈለገው ፍጥነት መውጣት ይሳነዋል።
በዚህም ምክንያት ፈሳሹ እየተከማቸ የዓይን ግፊትን ይጨምራል። የዓይን ነርቭንም በጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ ይጎዳዋል።
የዚህ በሽታ ዋናው አደገኛው ገጽታ፤ ሂደቱ እጅግ በጣም ቀርፋፋ መሆኑ ነው።
ምንም ዓይነት የዓይን ሕመም፣ መቅላት ወይም ግልጽ የሆነ የእይታ መለወጥ ስለማይታይ፤ ታካሚው በሽታው በውስጡ መኖሩን እንኳ ሳያውቅ ዓመታት ሊነጉዱ ይችላሉ።
በሽታው እየገፋ ሲሄድ ግን ታማሚው በጎን በኩል ያሉ ነገሮችን የማየት ችሎታው መቀነስ ሊጀምር ይችላል። ለምሳሌ፦ በቀጥታ ከፊት ያለውን ነገር በግልጽ እያየ ከጎኑ የሚመጣን ሰው/አካል ላያስተውል፤ አልያም በቀላሉ እንቅፋት ሊመታው ይችላል። በሽታው በጣም ከዚህ ከገፋ ደግሞ የመሃል እይታም ሊጎዳ ይችላል።
2. በድንገት የሚከሰተው ግላኮማ (Acute angle-closure glaucoma)

ይህኛው ዓይነት ደግሞ የዓይን ፈሳሽ የሚወጣበት መንገድ በድንገት ሲደፈን የሚከሰት ነው። ፈሳሹ መውጫ ሲያጣ የዓይን ግፊት በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
ከመጀመሪያው ዓይነት በተለየ መልኩ፤ ይህ በሽታ ሲጀምር ምልክቶቹ ከባድ እና አስደንጋጭ ናቸው።

ሰውየው በድንገት ኃይለኛ የዓይን ሕመም እና ከባድ ራስ ምታት ይሰማዋል። ዓይኑ ይቀላል፤ እይታው ይደበዝዛል፤ አልፎ ተርፎም ማቅለሽለሽና ማስታወክ ሊከተል ይችላል።
ይህ ፈጣን የሕክምና እርዳታ የሚሻ ድንገተኛ ሁኔታ (Medical emergency) ነው። እንዲህ ዓይነት ምልክቶች ሲታዩ፤ “እስኪሻለኝ ልጠብቅ” ብሎ ጊዜ ማጥፋት ፈጽሞ አይገባም። በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓይን ብርሃንን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ ስለሚችል፤ ፈጥኖ ወደ ዓይን ሕክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።
ለግላኮማ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች እነማን ናቸው?
ግላኮማ ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ይችላል። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

በተለይ በእኛ ኢትዮጵያውያን ላይ (አፍሪካውያን ስለሆንን)፤ በሽታው በወጣትነት ዕድሜ ቀድሞ ሊጀምር እና በፍጥነት እይታን ሊያሳጣ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ የሚከተሉት ሁኔታዎች የግላኮማ ተጋላጭነትን ይጨምራሉ፦
1. ዕድሜ መጨመር፦ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ በሽታው የመከሰት ዕድሉም አብሮ ያድጋል። በተለይ ዕድሜዎ ከ40 ዓመት በላይ ከሆነ፤ ስለ ዓይንዎ ጤና የበለጠ መጠንቀቅ መጀመር አለብዎት።
2. በቤተሰብ ውስጥ የግላኮማ ታሪክ ካለ፦ ግላኮማ በዘር ሊተላለፍ ይችላል። ወላጅዎ፣ ወንድምዎ ወይም እህትዎ በዚህ በሽታ ከተያዙ፤ እርስዎም የመያዝ ዕድልዎ በብዙ እጥፍ ይጨምራል። ስለዚህ በቤተሰብ ውስጥ ግላኮማ ካለ፣ ምንም ምልክት ባይሰማዎትም እንኳ መመርመር ግድ ይላል።
3. የዓይን ግፊት መጨመር ፦ ከፍተኛ የዓይን ግፊት መኖር ለዓይን ነርቭ መጎዳት መንስኤ ነው።
4. የስኳር በሽታ፦ የስኳር በሽታ ለግላኮማ ተጋላጭነትን ሊጨምር ይችላል። በተለይም የስኳር በሽታ በዓይን ውስጥ ያሉ የደም ሥሮችን በሚጎዳበት ጊዜ፤ አንዳንድ ሰዎች ከባድ የግላኮማ ዓይነት ሊያጋጥማቸው ይችላል።

5. የዓይን አደጋና ጉዳት፦ ቀደም ሲል በአደጋ፣ በስፖርት ወይም በማንኛውም ግጭት ምክንያት የዓይን ጉዳት ደርሶብዎት የሚያውቅ ከሆነ፤ ቱቦዎቹ በሂደት ሊደፈኑና ከዓመታት በኋላ ለግላኮማ ሊዳርጉ ይችላሉ።
6. የስቴሮይድ መድኃኒቶችን መጠቀም፦ አንዳንድ የስቴሮይድ (Steroid) ይዘት ያላቸው መድኃኒቶች፣ በተለይም የዓይን ጠብታዎች ለረጅም ጊዜ ሲወሰዱ የዓይንን ግፊት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራሉ።
ለዚህ ነው ማንኛውንም የዓይን ጠብታ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ እና ክትትል ለረጅም ጊዜ መጠቀም አይመከርም!
ግላኮማ እንዴት ይመረመራል?

እዚህ ላይ አንድ ጠቃሚ ጥያቄ አለ...
" በሽታው ምንም ምልክት ካላሳየ ታዲያ ሰው እንዴት ሊያውቅ ይችላል?"
መልሱ "በተገቢው የዓይን ምርመራ" ነው።
ግላኮማን በቀላሉ በዓይን ግፊት መለኪያ ብቻ መለየት አይቻልም። ሙሉ የዓይን ምርመራ ያስፈልጋል።
በምርመራው ወቅት የዓይን ሐኪሙ የሚከተሉትን ሊያደርግ ይችላል፦
የዓይን ግፊት መለካት (Tonometry): የዓይን ውስጣዊ ግፊት የሚለካ ምርመራ ሊደረግ ይችላል።
የዓይን ነርቭ ምርመራ: የዓይን ነርቭ ቅርጽን እና የጉዳት ምልክቶችን ይመለከታል።

የእይታ ምህዳር ምርመራ (Visual field test): በቀጥታ የሚያዩትን ነገር ብቻ ሳይሆን በጎን በኩል ያሉ ነገሮችን የማየት ችሎታዎን ይመረመራሉ።
የዓይን ፈሳሽ መውጫ መንገድ ምርመራ (Gonioscopy): የዓይን ፈሳሽ የሚወጣበት መንገድ ክፍት ወይም የተዘጋ መሆኑን በዚህ ምርመራ መመልከት ይቻላል።
እነዚህ ምርመራዎች በግላኮማ የተነሳ የዓይን ነርቭ ጉዳት መኖሩን፣ የበሽታውን ደረጃ እና የሕክምና አማራጮቹን ለመወሰን ይረዳሉ።
ሕክምናው ምንድን ነው?

ግላኮማ መኖሩ በጊዜ ከታወቀ እና ተገቢው ሕክምና ከተጀመረ የዓይን ብርሃንን ከተጨማሪ ጉዳት መጠበቅ ይቻላል። ነገር ግን አንድ አስፈላጊ እውነታ አለ...በግላኮማ ምክንያት የጠፋውን የማየት ችሎታ በአሁኑ ጊዜ ወደ ቀድሞው ሁኔታ የሚመልስ የታወቀ ሕክምና የለም። ስለዚህ የሕክምናው ዋና ዓላማ ፤ የተጎዳውን መመለስ ሳይሆን ፤ በሽታው የበለጠ እንዳይጎዳ መቆጣጠር ነው።
የሕክምና አማራጮቹ እንደ በሽታው ዓይነት፣ ደረጃ እና የታካሚው ሁኔታ ይለያያሉ። ያሉት ዋነኛ የህክምና አማራጮች የሚከተሉት ናቸው።
1. የዓይን ግፊትን የሚቀንሱ ጠብታ መድኃኒቶች፦ ይህ ከተለመዱት የሕክምና ዘዴዎች አንዱ ነው። መድኃኒቶቹ የዓይን ፈሳሽ ምርትን በመቀነስ ወይም ፈሳሹ በቀላሉ እንዲወጣ በማድረግ የዓይን ግፊትን ይቀንሳሉ።
2. የሌዘር ሕክምና (Laser treatment)፦ በሌዘር በመታገዝ የዓይን ፈሳሽ የሚወጣበትን መንገድ ማሻሻል ይቻላል። ይህ ግን ለተወሰኑ የግላኮማ ዓይነቶች ነው ጥቅም ላይ የሚውለው።
3. ቀዶ ሕክምና (Surgery)
የዓይን ግፊትን በመድኃኒት ወይም በሌዘር መቆጣጠር ካልተቻለ ፤ አልያም የበሽታው ሁኔታ አስፈላጊ ካደረገው ቀዶ ሕክምና ሊደረግ ይችላል።
ምልክት ካልተሰማኝ መድኃኒቴን ማቆም እችላለሁ?

ይህ በግላኮማ ለተያዙ ሰዎች በጣም አስፈላጊ ጥያቄ ነው። አንድ ሰው ለብዙ ወራት የዓይን ጠብታ ከተጠቀመ በኋላ፤ ዓይኑ ምንም ህመም ሳይሰማው፤ እይታው እንደድሮው ከተመለሰ ይህን ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል።
ነገር ግን ግላኮማ ብዙውን ጊዜ ሕመም የማያሳይ በሽታ ነው። መድኃኒቱ እየሰራ ስለሆነ የዓይን ግፊቱ ተቆጣጥሮት ሊሆን ይችላል። ምልክት አለመኖሩ ግን፤ በሽታው ተወግዷል ማለት አይደለም። ለዚህም መድኃኒቱን መቀጠል፣ መቀየር ወይም ማቆም የሚለውን ውሳኔ የሚደረገው በእርስዎ ሳይሆን በዓይን ሐኪምዎ ነው።
ግላኮማን መከላከልስ ይቻላል?
እዚህ ላይ እውነቱን መናገር ያስፈልጋል። ግላኮማን ሙሉ በሙሉ የሚከላከል የተረጋገጠ የህክምና ዘዴ በአሁኑ ጊዜ የለም። ሆኖም በሽታውን ቀድሞ በመለየት እና በተገቢው ሕክምና በመቆጣጠር የዓይን ብርሃንን መጠበቅ ይቻላል።

ለዚህም ለግላኮማ ያልዎትን ተጋላጭነት ለምቀነስ እነኝህ ሁለት ነገሮች ያድርጉ።
1.የዓይን ምርመራን ፈጽሞ አይዘንጉ።
በሽታው አስቀድሞ ምልክት ስለማያሳይ፤ ብቸኛው መከላከያ መንገድ አስቀድሞ መመርመር ብቻ ነው። በተለይ ዕድሜዎ ከ40 ዓመት በላይ ከሆነ፤ የቤተሰብዎ አባል በግላኮማ ከታመመ ወይም ሌሎች የተጋላጭነት ምክንያቶች ካሉዎት፤ ሙሉ የዓይን ምርመራ ያድርጉ። ምርመራው በየምን ያህል ጊዜ መደገም እንዳለበት የዓይን ሐኪምዎ ከመረመርዎ በኋላ ይወስናል።
2.የዓይን ጠብታዎችን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ፈጽሞ አይጠቀሙ። እላይ እንደገለጽነው ስቴሮይድ ያላቸው ጠብታዎች የዓይን ግፊትን ሊጨምሩ ይችላሉ። ስለዚህ ማንኛውንም የዓይን ጠብታ መድኃኒት ያለ ባለሙያ ምክርና ክትትል ለረጅም ጊዜ መጠቀም እይታዎን እንዲያጡ እድል ሊከፍት ይችላል።
ለዓይንዎ ጤና ቦታ ይስጡ! በጊዜ ይመርመሩ፤ ያለዎትን የዓይን ብርሃን ይጠብቁ!




Comments