የሚጥል በሽታ በትኩሳት ይመጣልን? (Febrile Seizure)

መቼም አያድርገውና... ጤነኛው ልጅዎ በተለመደው ጉንፋን ወይም ትኩሳት ታሞ ተኝቷል እንበል። በድንገት ግን ያልጠበቁት አስደንጋጭ ነገር ይፈጠራል።
ልጅዎ ራሱን ስቶ ይወድቃል... ዓይኖቹ ወደ ላይ ይገለበጣሉ... እጆቹ እና እግሮቹ በኃይል መንቀጥቀጥ ይጀምራሉ።
በዚያች ቅጽበት ልብዎ በድንጋጤ ይቆማል። "ልጄን ኢፕለፕሲ (Epilepsy) ያዘው እንዴ?" የሚል ከባድ ፍርሃት ይወርስዎታል። በማህበረሰባችን ውስጥ የሚጥል በሽታ ብዙ ጊዜ ከመንፈስ እና ከተለያዩ እምነቶች ጋር ተያይዞ ስለሚታይም፤ ድንጋጤዎ እና ጭንቀትዎ እጥፍ ድርብ መሆኑ አይቀርም።
ግን ቆይ... እውነት ልጅዎን የሚጥል በሽታ ያዘው?
በዚያች አስፈሪ ቅጽበት ውስጥ በልጅዎ ሰውነት ላይ የተፈጠረው ትክክለኛው ነገር ምንድን ነው? ልጅዎን ለመታደግስ ምን ማድረግ ይኖርብዎታል?
ዛሬ ፍርሃትዎን የሚያቀል እና የልጅዎን ሕይወት የሚታደግ ወሳኝ እውነታ ይዘን ቀርበናል።
በትክክል የተፈጠረው ምንድን ነው?

አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ድንገተኛ መንቀጥቀጥ ኢፕለፕሲ አይደለም። በሕክምናው ዓለም 'በትኩሳት ምክንያት የሚመጣ መንቀጥቀጥ ወይም የሚጥል በሽታ' (Febrile Seizure) ይባላል።
ይህ ሁኔታ በብዛት የሚታየው ዕድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 5 ዓመት ባሉ ሕፃናት ላይ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ በተለመዱ የቫይረስ ወይም ሌሎች ኢንፌክሽኖች ምክንያት ትኩሳት ሲነሳ ይከሰታል።
ግን ለምን ይንቀጠቀጣሉ?

የሕፃናት አንጎል ገና በማደግ ላይ ስለሆነ ለድንገተኛ የሙቀት መጨመር በቀላሉ ተጋላጭ ነው። የሰውነታቸው ሙቀት በድንገት ሲጨምር፤ የአንጎላቸው የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ለጊዜው ሊዛባ ይችላል። ልክ በቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲጨምር ፊዩዝ እንደሚያቃጥል ሁሉ፤ የልጅዎ አንጎልም ለዚህ ድንገተኛ ትኩሳት ምላሽ ሲሰጥ የሚጥል በሽታ ምልክት ያሳያል።
አንድ ወሳኝ እውነታ ልብ ይበሉ!
አንድ ልጅ ትኩሳት ኖሮት ስለተንቀጠቀጠ ብቻ "በትኩሳት የመጣ ነው (Febrile Seizure)" ብሎ ዝም ማለት አይቻልም። ሐኪሞች ይህንን ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት፤ ሌሎች ሕመሞች አለመኖራቸውን በምርመራ ማረጋገጥ አለባቸው። ለዚህም ነው መንቀጥቀጡ ቢቆም እንኳ ልጅዎን ወደ ሐኪም መውሰድ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው።በትኩሳት የሚመጣ የሚጥል በሽታ ምልክቶች ምንድናቸው?

ልጅዎ በትኩሳት ምክንያት የሚመጣ ማንቀጥቀጥ እና ራስ መሳት (Febrile Seizure) ሲያጋጥመው የሚከተሉትን ድንገተኛ ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል፦
የሰውነት ሙቀት መጨመር፦ የልጅዎ ሰውነት በጣም ይሞቃል ወይም ከፍተኛ ትኩሳት ይኖረዋል።
ራስን መሳት፦ ልጅዎ በድንገት ምላሽ መስጠት ማቆም አልያም ራሱን ሊስት ይችላል።
የሰውነት ግትር ማለት እና መንቀጥቀጥ፦ እጆቹ እና እግሮቹ መጀመሪያ ላይ ሊገትሩ (ሊወጠሩ) እና ወዲያውኑ በኃይል መንቀጥቀጥ ሊጀምሩ ይችላሉ።
የዓይን መገልበጥ፦ ዓይኖቹ ወደ ላይ ወይም ወደ ጎን ሊገለበጡ ይችላሉ።
የቆዳ ቀለም መለወጥ፦ በአፍና በአፍንጫ አካባቢ ያለው ቆዳ ሊገረጣ አልያም ሰማያዊ መልክ ሊይዝ ይችላል።
ከማንቀጥቀጡ በኋላ መዛል፦ መንቀጥቀጡ ካቆመ በኋላ ልጅዎ ግራ ሊጋባ፣ ሊዝል አልያም ወዲያውኑ እንቅልፍ ሊተኛ ይችላል።
ይህ ሁኔታ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል?
ብዙውን ጊዜ ይህ የትኩሳት ማንቀጥቀጥ ከጥቂት ሰከንዶች እስከ 2–3 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ በራሱ ይቆማል። ከዚያ በኋላ ልጅዎ ሰውነቱ ስለሚደክም ለተወሰነ ጊዜ ፈዞ ወይም እንቅልፍ ወስዶት ሊታይ ይችላል፤ ይህ የተለመደ ነው።
ሁሉም በትኩሳት የሚመጣ የሚጥል በሽታ አንድ ዓይነት ነው?

አይደለም። በትኩሳት ምክንያት የሚመጣ ማንቀጥቀጥ (Febrile Seizure) በዋናነት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባል።
1. ቀላሉ ዓይነት (Simple Febrile Seizure)
ይህ በሕፃናት ላይ በብዛት የሚታየውና ብዙም የማያሰጋው ዓይነት ነው። የሚከተሉት መገለጫዎች አሉት፦
መንቀጥቀጡ የልጁን መላ ሰውነት በሙሉ ያካትታል።
ቆይታው ከ15 ደቂቃ በታች ነው (አብዛኛውን ጊዜ ከ1 እስከ 4 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ ይቆማል)።
በ24 ሰዓት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ይከሰታል።
2. ውስብስብ ዓይነት (Complex Febrile Seizure)
ከሚከተሉት ምልክቶች ቢያንስ አንዱ ከታየ ሁኔታው "ውስብስብ የትኩሳት ማንቀጥቀጥ" ተብሎ ይመደባል፦
መንቀጥቀጡ ከ15 ደቂቃ በላይ ከቆየ።
መላ ሰውነቱ ሳይሆን የሰውነቱ አንድ ክፍል ብቻ (ለምሳሌ አንድ እጁ ወይም አንድ ጎኑ ብቻ) ወይም ከተንቀጠቀጠ።
በ24 ሰዓት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ተደጋግሞ ከተከሰተ።

💡 ለወላጆች ወሳኝ ማሳሰቢያ፦
እርስዎ በቤት ውስጥ ሆነው 15 ደቂቃ እስኪሞላ በፍጹም መጠበቅ የለብዎትም። የልጅዎ መንቀጥቀጥ ከ5 ደቂቃ በላይ ከቆየ ወዲያውኑ ወደ አስቸኳይ ሕክምና መውሰድ አለብዎት።
እርስዎ ምን ማድረግ አለብዎት?

ይህ ለወላጆች በጣም ወሳኙ ክፍል ነው። በዚያች አስደንጋጭ ቅጽበት ተረጋግተው ትክክለኛውን የመጀመሪያ እርዳታ መስጠትዎ የልጅዎን ሕይወትና ደህንነት ለመጠበቅ ይረዳል።
1. የማንቀጥቀጡን ሰዓት ይመዝግቡ
መንቀጥቀጡ የጀመረበትን ትክክለኛ ሰዓት ይመልከቱ። በድንጋጤ ውስጥ ሆነው ጊዜውን መገመት በጣም ከባድ ስለሚሆን፤ ሰዓትዎን ወይም የስልክዎን ሰዓት መቁጠሪያ (Timer) ይጠቀሙ።
2. ልጅዎን ከጉዳት ይጠብቁ
ቀስ ብለው ምቹና ጠፍጣፋ ቦታ (ለምሳሌ ምንጣፍ ወይም ፍራሽ ላይ) ያስተኙት። በአቅራቢያው ያሉ ሹል ነገሮችን፣ ጠንካራ ዕቃዎችን እና ሊጎዱት የሚችሉ ነገሮችን ያርቁ። ከራሱ ሥር ለስላሳ ልብስ ወይም ትራስ ያድርጉለት።
3. እንቅስቃሴውን ለማስቆም በኃይል አይያዙት
መንቀጥቀጡን ለማስቆም እጆቹንና እግሮቹን በኃይል አጥብቀው አይያዙ ወይም አይጫኑት። ይህ መንቀጥቀጡን አያስቆመውም፤ ይልቁንም በልጅዎ አካል ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

4. በአፉ ውስጥ ምንም ነገር አያስገቡ
ምላሱን እንዳይነክስ ወይም እንዳይውጥ በሚል ስጋት ማንኪያ፣ ጨርቅ፣ ጣት፣ ውኃ ወይም መድኃኒት በአፉ ውስጥ በፍጹም አያስገቡ። ነገር ግን አፉ ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን መክተት የልጅዎን ጥርስ ሊሰብር፤ አፉን ሊያቆስል ወይም እንዲታነቅ ሊያደርገው ይችላል።
5. ልጅዎን በጎኑ ያስተኙት
በተቻለ መጠን ልጅዎን ቀስ አድርገው በአንድ ጎኑ (Recovery Position) ዘንበል አድርገው ያስተኙት (በተለይም መንቀጥቀጡ ሲቆም)። ይህም ምራቅ ወይም ትውከት ወደ ሳንባው ገብቶ እንዳያፍነው ይረዳዋል። አተነፋፈሱንም በቅርበት ይከታተሉ።
6. የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ
ይህ ሁኔታ ለልጅዎ የመጀመሪያ ጊዜው ከሆነ፤ መንቀጥቀጡ ቢቆምም እንኳ የትኩሳቱን መንስኤ ለማወቅ ወደ ጤና ተቋም ይውሰዱት። ነገር ግን መንቀጥቀጡ ከ5 ደቂቃ በላይ ከቆየ ሳይዘገዩ ወደ አስቸኳይ ሕክምና ክፍል ያድርሱት።

ልጄ እንደገና ሊያጋጥመው ይችላል?
አዎ!
አንድ ጊዜ የትኩሳት ማንቀጥቀጥ ያጋጠመው ከሦስቱ ሕፃናት አንዱ ያህል በተለየ የትኩሳት ሕመም ወቅት እንደገና ሊያጋጥመው ይችላል። ይህ ዕድል የመጀመሪያው ማንቀጥቀጥ ልጁ ከ18 ወር በታች እያለ ከተከሰተ የበለጠ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን እንደገና መከሰቱ ልጅዎ ኢፕለፕሲ (Epilepsy) ያዘው ማለት አይደለም።
በትኩሳት የሚመጣ የሚጥል በሽታን መከላከል ይቻላል?

ይህ ብዙ ወላጆች የሚጠይቁት ወሳኝ ጥያቄ ነው። ልጅዎ ትኩሳት ሲይዘው ፓራሲታሞል (Paracetamol) ወይም ኢቡፕሮፌን (Ibuprofen) መስጠት ትኩሳቱን በመቀነስ ለልጅዎ ምቾትና እፎይታ ሊሰጥ ይችላል። ነገር ግን እነዚህ የትኩሳት መድኃኒቶች የትኩሳት ማንቀጥቀጥን እንዳይከሰት ሙሉ በሙሉ ይከላከላሉ የሚል በቂ የሕክምና ማስረጃ የለም።
ስለዚህ ልጅዎ ትኩሳት ሲይዘው የሚከተሉትን ያድርጉ፦
በቂ ፈሳሽ ይስጡት፦ ሰውነቱ ውኃ እንዳያንሰው በቂ ውኃ፣ ጡት ወተት ወይም ሌሎች ፈሳሾችን እንዲወስድ ያድርጉ።
ቀላል ልብስ ያልብሱት፦ ሙቀቱን እንዳይብስ፤ በምቾት የሚያስተኛ ቀላልና ስስ ልብስ ያልብሱት።
በሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒት ይስጡት፦ በጤና ባለሙያ በተመከረው መጠን ብቻ የትኩሳት ማስታገሻ መድኃኒት ይስጡት።
የትኩሳቱን ምክንያት ይወቁ፦ ትኩሳቱን ያስከተለውን ኢንፌክሽን፤ ለመለየት እና ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
ቋሚ መድኃኒት ያስፈልጋል?
ልጅዎ በድጋሚ እንዳያንቀጠቅጠው በሚል ስጋት፤ ቋሚ የሚጥል በሽታ መድኃኒት መስጠት በአብዛኛው አይመከርም።
መቼ ወደ ሆስፒታል መሄድ አለብዎት?

የሚከተሉት አደገኛ ምልክቶች ከታዩ ሳይዘገዩ የአስቸኳይ ሕክምና እርዳታ ይፈልጉ፦
ማንቀጥቀጡ ከ5 ደቂቃ በላይ ከቆየ።
ልጁ በመተንፈስ ላይ ችግር ካለበት ወይም ከንፈሩና ፊቱ ወደ ሰማያዊነት ከተቀየረ።
ማንቀጥቀጡ ከቆመ በኋላ ልጁ ቶሎ ካልነቃ ወይም ንቃተ ህሊናው ካልተመለሰ።
በሰውነቱ አንድ ክፍል ብቻ (ለምሳሌ አንድ እጁ ወይም አንድ ጎኑ ብቻ) የሚንቀጠቀጥ ከሆነ።
በ24 ሰዓት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ተደጋግሞ ካንቀጠቀጠው።
አንገቱ ከደረቀ፣ ከባድ የራስ ምታት ካለው ወይም በሰውነቱ ላይ ሲጫኑት የማይጠፋ ሽፍታ ከታየ።
በተለይም ይህ ሁኔታ ለልጅዎ የመጀመሪያ ጊዜው ከሆነ፣ ማንቀጥቀጡ በራሱ ቢቆምም እንኳ የትኩሳቱን መንስኤ ለማረጋገጥ ወደ ጤና ተቋም ሄዶ የሕክምና ምርመራ ማድረግ አለበት።
ወላጆች ሊያስታውሱት የሚገባ አንድ አስፈላጊ ነገር

የትኩሳት ማንቀጥቀጥ ለማየት እጅግ አስፈሪና ልብ የሚያስደነግጥ ቢሆንም፤ በአብዛኛው ጊዜ ልጅዎ ያለምንም ተጓዳኝ ጉዳት ሙሉ በሙሉ ያገግማል።
ቀላል ከትኩሳት ጋር የተያያዘ ማንቀጥቀጥ (Simple Febrile Seizure) በልጅዎ ላይ የአንጎል ጉዳት፣ የዕድገት መዘግየት ወይም የአእምሮ ችሎታ መቀነስ አያስከትልም። ወደፊት የሚጥል በሽታ (Epilepsy) የመከሰት ዕድሉም እጅግ ዝቅተኛ ነው።
ዋናው ወሳኝ ነገር ልጅዎ የትኩሳት ማንቀጥቀጥ ሲያጋጥመው በድንጋጤ የተሳሳተ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ፦
ትክክለኛውን የመጀመሪያ እርዳታ ማወቅ፣
የማንቀጥቀጡን ሰዓት መመዝገብ እና
በጊዜው የሕክምና እርዳታ መፈለግ ነው።
ትክክለኛ እውቀት የልጅዎን ሕይወት ይታደጋል!
ይህንን ወሳኝ መረጃ ለሌሎች ወላጆችና ቤተሰቦች ያጋሩ!




Comments