ግማሽ አንጎሏን አጥታ ማስተር የያዘችው ሴት ታሪክ
የሰው ልጅ አንጎል አስደናቂ ነው። ለእያንዳንዱ የህይወት እንቅስቃሴያችን፣ ለምናስበው እያንዳንዱ ሃሳብ እና ለሚሰማን እያንዳንዱ ስሜት ዋነኛው መሪ እሱ ነው። በዚህ ስስ እና ውስብስብ አካል ላይ ጥቂት ጉዳት እንኳን ሲደርስ፤ የንግግር መቋረጥ፣ የእይታ መደብዘዝ፣ አልያም ድንገተኛ የባህሪ ለውጥ ሲከሰት በተደጋጋሚ አስተውለናል።

የአንጎል ጥቃቅን ክፍሎች እንኳ ሲጎዱ፤ ህይወት እንዲህ ከተመሰቃቀለች....
"ግማሽ አንጎል ባይኖር ምን ይፈጠራል?" "አንድ ሰው በህይወት ይኖር ይሆን? " "ቢኖርስ፤ ሙሉ እና የተሳካ ህይወት ሊመራ ይችላልን?”
እነዚህን ጥያቄዎች ስንሰማ ብዙዎቻችን ያለ ምንም ማወላወል “ፈጽሞ አይቻልም!” የሚል አጭር እና ቁርጥ ያለ ድምዳሜ እንሰጥ ይሆናል።
ዛሬ ግን ይህንን ድምዳሜያችንን ፍጹም የሚፈትነውን እና የህክምና ሳይንቲስቶችን ሳይቀር በአድናቆት አፍ ያስያዘውን የክሪስቲና ሳንታውዝ (Christina Santhouse) እውነተኛ እና አስደናቂ የሕይወት ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
የክሪስቲና ታሪክ

ታሪኩ የሚጀምረው ክሪስቲና ገና በልጅነት እድሜዋ ላይ እያለች ነበር። በወቅቱ የስምንት ዓመት ህጻን የነበረችው ክሪስቲና፤ ከቤተሰቦቿ ጋር በኒው ጀርዚ የባህር ዳርቻ አስደሳች የዕረፍት ጊዜዋን እያሳለፈች ሳለ፤ በድንገት ያልተጠበቀና እጅግ አስፈሪ አጋጣሚ የሕይወቷን አቅጣጫ ቀየረው።
ያለምንም ቅድመ-ምልክት እግሯ ቁጥጥር ባጣ መልኩ መንቀጥቀጥ ጀመረ። ቤተሰቦቿ በድንጋጤ ወደ ሆስፒታል ይዘዋት ቢሮጡም፤ በወቅቱ ለነበሩት ሐኪሞች ነገሩ ግራ አጋባቸው።
ከተከታታይ አድካሚ ምርመራዎች በኋላ ግን፤ ይፋ የሆነው የሕክምና ውጤት በቀላል የሚዋጥ አልነበረም።
ክሪስቲና ራስሙሰን ኢንሴፋላይተስ (Rasmussen's encephalitis) የሚባል የአንጎል በሽታ ተገኘባት። ይህ ከባድ እና ቀስ በቀስ የአንጎልን አንድ ጎን የሚያጠቃ እጅግ አልፎ አልፎ የሚከሰት የነርቭ ሕመም ነው።
ይህ በሽታ የአንጎልን አንዱን ጎን (ሂሚስፌር) ብቻ ለይቶ በማጥቃት፣ ከባድ መቆጣት ያመጣል። ለዚህም የአንጎል ህዋሳትን ቀስበቀስ የሚገድል ጨካኝ በሽታ ነው። በተለይ ደግሞ በሕፃናት ላይ ሲከሰት፤ በመድኃኒት በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስቸግሩ ፤ የሚከታተሉ የሰውነት መንቀጥቀጦችን (seizures) ያመጣል።
በቀን ከ150 ጊዜ በላይ የሚጥል በሽታ!

ክሪስቲና በሽታውን የተጋፈጠችው በቀላሉ አልነበረም። ይህ በሽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቀኝ ክፍለ-አንጎሏን (Right hemisphere) ሙሉ በሙሉ ማውደም ጀመረ። ሁኔታዋ እየባሰ ሲሄድ፤ የሚጥል በሽታው በየደቂቃው እየተደጋገመ በቀን እስከ 150 ጊዜ ያጋጥም ጀመር።
እሲት ያስቡት.... አንድ የ8 ዓመት ሕፃን በቀን ውስጥ ይህን ያህል ጊዜ በሚጥል በሽታ ሲሰቃይ መመልከት፤ ለአንድ ወላጅ ምን ያህል ልብ የሚሰብር እና አቅም የሚያጣ ስቃይ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። እያንዳንዱ ሰከንድ ለቤተሰቦቿ ሲኦል ነበር።
በዓለም ላይ ያለው ምንም ዓይነት ዘመናዊ መድኃኒት፤ በሽታውን ከመስፋፋት ሊገታው አልቻለም። በሽታው በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ መላ አካሏን ሽባ ከማድረጉም በላይ ሕይወቷን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ሐኪሞች ተረዱ። ይህን ጊዜ የታወቁት የነርቭ ቀዶ ጥገና ሐኪም ዶ/ር ቤን ካርሰን (Dr. Ben Carson) እና የሕክምና ቡድናቸው፣ አንድ አስደንጋጭ እና የመጨረሻ አማራጭ ይዘው ቀረቡ፦
"ክሪስቲና እንድትኖር ከተፈለገ የቀኝ ክፍለ-አንጎሏ ሙሉ በሙሉ ተቆርጦ መውጣት አለበት!"

ይህ ቀዶ ጥገና ‘ሄሚስፌሬክቶሚ’ (Hemispherectomy) ይባላል። ዓላማውም የታመመውን የአንጎል ክፍል ከቀሪው ጤናማ ክፍል በመለየትና በማስወገድ፤ በየቀኑ የሚከሰተውንና መላ አካሏን የሚያንቀጠቅጠውን የሚጥል በሽታ፤ ማቆም ነው።
ማሰብ፣ ማስታወስና መኖር የሚቻለው በሙሉ አንጎል በሆነበት ዓለም፤ ግማሹን አንጎል ጥሎ መውጣት ምን ዓይነት ሕይወትን ሊያመጣ ይችላል? ሐኪሞቹ ሳይቀሩ “ከቀዶ ጥገናው በኋላ ክሪስቲና በተለምዶው መንገድ ልትራመድ፣ ልትናገር አልያም ራሷን ችላ መኖር ሊከበዳት እንደሚችል" ለቤተሰቦቿ ቀድመው አሳውቀው ነበር።
የ14 ሰዓታቱ አስገራሚ ቀዶ ሕክምና

እ.ኤ.አ. በ1996፣ ክሪስቲና ገና የ8 ዓመት ልጅ ሳለች፣ በዓለም ታዋቂው የጆንስ ሆፕኪንስ (Johns Hopkins) ሆስፒታል ውስጥ ይህ ታሪካዊ ቀዶ ሕክምና ተከናወነ። ቀዶ ሕክምናው ሙሉ 14 ሰዓታትን የፈጀ፣ እያንዳንዱ ስክንድ በጥንቃቄ የተሰላበት የሕይወትና የሞት ፍልሚያ ነበር።
በጆንስ ሆፕኪንስ ሆስፒታል የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በዚህ አስቸጋሪ የራስሙሰን በሽታ ለተጠቁ ሕፃናት ይህ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ሁለት ሦስተኛው (67%) የሚሆኑት ከሚጥል በሽታ ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሆናሉ፤ ወይም በሽታው በቀላሉ የሚቆጣጠሩት ደረጃ ላይ ይደርሳል። ነገር ግን ይህንን ነፃነት ለማግኘት የሚከፈለው ዋጋ እጅግ የከበደ ነበር።
ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የመጣው አዲስ ፈተና

ክሪስቲና ከቀዶ ሕክምናው ስትነቃ ያሰቃያት የነበረው የሚጥል በሽታ ሙሉ በሙሉ ቆሞ ነበር። ነገር ግን የቀኝ ክፍለ-አንጎሏ በመወገዱ ምክንያት፣ መላው የግራ የሰውነት ክፍሏ ላይ ሽባ ሆኖ (Paralysis) ነበር። የግራ እግሯን ለማንቀሳቀስና ለመራመድ ልዩ የድጋፍ መቆጣጠሪያ (Brace) መጠቀም ግድ አላት። የግራ እጇ ሙሉ በሙሉ ሥራ አቆመ። የእይታ መስኳም በከፊል ተጎድቶ ነበር።
ይህን ጊዜ "ክሪስቲና መቼም ቢሆን መኪና መንዳት ወይም ራሷን ችላ መኖር አትችልም" ተብሎ ተገምቶ ነበር።
ነገር ግን እዚህ ላይ ነው የሰው ልጅ የመጽናት አቅም እና የአንጎላችን አስደናቂ ምስጢር በአደባባይ የወጣው። የቀረው ግማሽ አንጎሏ ዓለምን የሚያስደንቅ ተአምር መስራት ጀመረ..
የአንጎል ተለዋዋጭነት ባህሪ (Neuroplasticity)

በተለይም በልጅነት ዕድሜ፣ የሰው ልጅ አንጎል እጅግ አስገራሚ የሆነ የማገገም እና ራሱን መልሶ የማደራጀት አቅም አለው። ይህ አስደናቂ ሳይንሳዊ ክስተት ኒውሮፕላስቲሲቲ (Neuroplasticity) ይባላል። አንጎል አንዱ ክፍሉ ሲወገድ፤ የተረፈው ሌላኛው ግማሽ ክፍል (በክሪስቲና ሁኔታ የግራው አንጎሏ) ልክ እንደማስቲካ የመለጠጥ አቅም አለው። የቀረው አንጎልም አዳዲስ የነርቭ መስመሮችን (Neural pathways) ይዘረጋል። በዚህም የጠፋውን የቀኝ አንጎል ሥራዎች በከፊል መደገፍና መረከብ ይጀምራል። የግራ አንጎሏ የራሱን ስራ ብቻ ሳይሆን፤ የቀኙን አንጎሏን ስራ ለማገዝ ራሱን አዘጋጀ!
እዚህ ጋር ያስተውሉ!
ኒውሮፕላስቲሲቲ ማለት አንጎል የጠፋውን ክፍል በቀጥታ እንደገና ይገነባል ማለት አይደለም። የቀረው አንጎል ከተለመደው በተለየ መንገድ ራሱን ማደራጀትና አንዳንድ የጠፉ ተግባራትን በከፊል መደገፍ ይችላል።
ይህ ማለት ግን ሂደቱ አልጋ በአልጋ ነበር ማለት አይደለም። ክሪስቲና ከባድ፣ አታካችና አድካሚ የሆኑ የአካልና የንግግር ማገገሚያ (Rehabilitation) ሕክምናዎችን ለዓመታት በጽናት መከታተል ነበረባት። እያንዳንዱን እርምጃ ለመራመድ እና እያንዳንዱን ቃል ለመናገር ከአንጎሏ ጋር በየቀኑ በብርቱ ትታገል ነበር።
ወላጆቿም ክሪስቲናን እንደ በሽተኛ ሳይሆን እንደ ሙሉ ጤነኛ ልጅ ነበር ያሳደጓት። በትምህርት ቤት የቦውሊንግ (Bowling) ቡድን ውስጥ እንድትሳተፍ እና እንደማንኛውም ልጅ እንድትጫወት በማበረታታት ከማህበረሰቡ እንዳትገለል አደረጉ።
ከሆስፒታል አልጋ እስከ ማስተርስ ዲግሪ
ክሪስቲናም የሰዎችን ግምት እና ፍርዶች ሁሉ አንድ በአንድ መናድ ጀመረች።

ገና በ17 ዓመቷ፤ በግራ በኩል ያለውን የሰውነት እንቅስቃሴ ገደብ የሚደግፍ ልዩ ማሻሻያ የተደረገበትን መኪና መንዳት ተለማምዳ የመንጃ ፈቃድ አወጣች።
ትምህርቷን በከፍተኛ ብርታትና ተነሳሽነት ቀጥላ ሚዜሪኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ (Misericordia University) ገባች። በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ በንግግር ሕክምና (Speech-Language Pathology) የመጀመሪያ እና የማስተርስ ዲግሪዋን በከፍተኛ ውጤት አጠናቀቀች።

ከሁሉም በላይ የሚያስደንቀው፤ ግማሽ አንጎሏን ያጣችው ይህች ቆራጥ ሴት፤ ዛሬ ሌሎችን መናገር ለተሳናቸው ሕፃናት ድምፅ ለመሆን በንግግር ሕክምና ባለሙያነት (Speech Therapist) ተቀጥራ በቁርጠኝነት መስራት ጀመረች! ለእነዚያ ህጻናት እሷ ከመምህርም በላይ ህያው ምስክር ናት።

እ.ኤ.አ በ2016 በወጣው የፊላዴልፊያ ኢንኩዊረር (Philadelphia Inquirer) ዘገባ መሠረት፤ ክሪስቲና የራሷን ቤት ገዝታ፣ ትዳር መሥርታ፣ አልፎ ተርፎም ሁለት ሴት ልጆችን ወልዳ ህይወትን እየመራች ትገኛለች።
ከክሪስቲና ሕይወት ምን እንማራለን?
ክሪስቲና ያሳየችን ነገር ግማሽ አንጎል ካለ ሁሉም ሰው ሙሉ በሙሉ መደበኛ ሕይወት ይኖራል ማለት አይደለም። ያሳየችን ግን የሰው አንጎል እና የሰው ልጅ የመላመድ አቅም ከምናስበው በላይ ሊሆን እንደሚችል ነው።




Comments