ለረዥም ሰዓት ሲቀመጡ ወይም ሲቆሙ ወገብዎን ያምዎታል? ለምን?
“ወገቤን ያመኛል!”
ይሄን ቃል ስንሰማ ከእድሜ ጋር የምናያይዘው ጥቂቶች አይደለንም።

ለዚህም ድሮ ድሮ.... ወገብ ሲያም “አረጀህ” ተብሎ ማሾፍ የተለመደ ነበር። እንደ ማህበረሰቡ አረዳድ ከሆነ፤ የወገብ ሕመም ከእድሜና ከከባድ ሥራ ጋር ብቻ ይያያዝ ነበር።
አሁን ግን ተቀይሯል! የ20 ዓመት ጉብል ከአንድ ሰዓት በላይ ኮምፒውተር ፊት ተቀምጦ ሲያሳልፍ አልያም አንዲት ኮረዳ ለአንድ ሰአት ስትቆም “ወገቤን!” ሲሉ መስማት የተለመደ ክስተት ሆኗል።
ለመሆኑ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ? የዘመኑ ሰው ደካማ ሆኖ ነው? ወይስ አጠቃላይ አመጋገባችን ተበላሽቶ? ምንድነው ነገሩ?
በዛሬው ጽሁፍ ስለ ወገብ ህመም በጥልቀት እናነሳለን።
የወገብ ህመም አለም አቀፋዊ እውነታ

ይህ ችግር ምን ያህል ሰፊ መሰላችሁ? ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአንድ ሰው የሕይወት ዘመን ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ የወገብ ሕመም የማጋጠም ዕድሉ እስከ 84% ይደርሳል! ይህ ማለት በአጭሩ ከአስር ሰዎች ውስጥ ስምንቱ ይህ ሕመም በህይወታቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ያጋጥማቸዋል።
ይህ የኢትዮጵያ እውነታ ብቻ አይደለም!
በመላው ዓለምም ተመሳሳይ ነገር እየተስተዋለ ይገኛል። በ2020 በተደረጉ ዓለም አቀፍ ጥናቶች መሰረት ወደ 619 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በወገብ ሕመም ይሰቃያሉ። ይህም ለአካል ጉዳትና ለሥራ መስተጓጎል፤ እንዲሁም ለምርታማነት መጥፋት ዋነኛው ምክንያት ሆኗል።

በኢትዮጵያ የተደረገ ጥናትም፤ ወደ 54 በመቶ የሚጠጉ የወገብ ሕመምተኞች ከሥራ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይጠቁማል። በቢሮ ውስጥ ለረጅም ሰዓት በሚቀመጡ ሠራተኞች ላይ የተደረጉ ሌሎች የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ከቢሮ ሰራተኞች ውስጥ ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆኑት (እስከ 38.4%) የወገብ ሕመም ተጠቂ ናቸው። ይልቁንም በቀን ውስጥ ከ6 ሰዓት በላይ ሳይነሱ በተመሳሳይ ሁኔታ ተቀምጠው የሚሠሩ ሰዎች ላይ ይህ ሕመም በብዛት ይስተዋላል።
ነገር ግን እዚህ ላይ ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ጥናቶች በተወሰኑ የሥራ መደቦች ላይ የተደረጉ ናቸው። ለዚህም ይህንን ቀጥታ ከሁለት አንዱ ተብሎ አይተረጎምም። አንዳንዶችም ይህንን አይተው "የዘመኑ ትውልድ ደካማ ሆነ" ብለው ጣታቸውን ይቀስራሉ። ጥንካሬ ማጣትንም እንደ ምክንያት ያቀርባሉ።
ነገር ግን እውነታው ከዚህ በጣም የራቀ ነው! የወገብ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እና በሁሉም የዕድሜ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ወገብዎ ላይ የሚደርሰው ምንድነው?

የታችኛው የጀርባ አካባቢ አጥንቶች፣ ጡንቻዎች፣ ጅማቶች፣ ዲስኮች እና ነርቮች የሚገናኙበት በተፈጥሮ ውስብስብ አካባቢ ነው።
ስለሆነም “ወገቤን ያመኛል” ማለት የወገብዎ አጥንት፣ ጅማት አልያም ዲስክ ላይ ትልቅ ችግር አለ ማለት አይደለም። የነርቭ ብቻ ሊሆን ይችላል።
በሕክምናው አለም የሚታየው እውነታም ይህንን ይደግፋል። ከ90% በላይ የሚሆነው የወገብ ሕመም የተለየ ነጠላ መንስኤው በውል አይታወቅም (Nonspecific)። ለዚህም አንድ ሰው “ኤምአርአይ (MRI) ተነስቶ ዲስክ ተንሸራቷል ቢባል እንኳን፤ የወገብ ሕመሙ ዋነኛ መንስኤ ዲስኩ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ወገብ የሚያመው በእነዚህ አወቃቀሮች ላይ በሚፈጠር “የጡንቻ መዛባትና የድካም ጫና” እንጂ በአጥንት ችግር ብቻ አይደለም።
ታድያ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ወይም መቆም ወገብን ለምን ያሳምማል?

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ትልቅ ምስጢር አለ፦ጡንቻዎቻችን ዕረፍት ይፈልጋሉ! ሆኖም ግን :-
ሲቀመጡ፦ በተለይ ለረጅም ሰዓት ሳይንቀሳቀሱ ሲቀመጡ ወገብን ደግፈው የሚይዙት የሆድና የጀርባ ጡንቻዎች (Core muscles) ይዝላሉ፤ ይደክማሉ። ጡንቻዎቹ ሲዝሉ ደግሞ የሰውነታችን ሙሉ ክብደትና ጫና በቀጥታ በጀርባ አጥንትና በጅማቶች ላይ ያርፋል። ይህ “የማይንቀሳቀስ የማያቋርጥ ጫና” (Static Overload) ጡንቻው ደም እንዳያገኝና እንዲሸማቀቅ በማድረግ ሕመም ይፈጥራል። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ በተሰሩ የቢሮ ጥናቶች ላይ ለረዥም ጊዜ በሚቀመጡ ሰዎች ላይ በብዛት የጀርባ ህመም የተስተዋለው።

ሲቆሙ፦ ለረጅም ሰዓት በአንድ ቦታ መቆምም በተመሳሳይ ሁኔታ የጀርባ ጡንቻዎችን (Extensor muscles) ከመጠን በላይ በማስጨነቅና የደም ዝውውርን በማዛባት የወገብ መገጣጠሚያዎች ላይ ድካም ይፈጥራል። ይህም ድካምና ጫና የወገብ ህመም ያስከትላል።
ታዲያ የሚመከረው ምንድነው?
እዚህ ላይ ነው የዘመኑ የሕክምና ሳይንስ አስገራሚ ነገር የሚነግረን።

ብዙዎች “ቀጥ ብዬ ካልተቀመጥኩ ወገቤ ይታመማል” ብለው ይጨነቃሉ። ነገር ግን ሳይንሳዊ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት “ይህ አቀማመጥ ትክክል ነው" የሚል ፍጹም አቀማመጥ የለም። ዋናው ነገር አቀማመጣችን አልያም አቋቋማችን ሳይሆን፤ በአንድ ቁመና ላይ “የቆየንበት የሰዓት ርዝማኔ” ነው!
ለምን?
የጀርባ አጥንታችን የተፈጠረው ለመንቀሳቀስ ነው። ለዚህም ለረዥም ሰአት ሳይንቀስቀስ መቆየት የለበትም። የጀርባ ሕመምን የሚቀንስ ፍጹም አቀማመጥ ከመፈለግ ይልቅ፤ የሚመከረውም በየመካከሉ አቀማመጥን መቀየርና መንቀሳቀስ ነው!
ይህ በተለይ በየቀኑ በኮምፒውተር ፊት የሚሠሩ፣ ረዥም ሰዓት መኪና የሚያሽከረክሩ፣ ወይም በአንድ ቦታ ቆመው የሚውሉ ሰዎች ሊያስታውሱት የሚገባ ወርቃማ ሕግ ነው።
ታዲያ መፍትሔው ምንድነው?

መፍትሔውን ስናስብ፤ ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን፤ አንድ ወርቃማ ምስጢር ላይ ነው፦ እንቅስቃሴ!
የቢሮ ውሏችንን እና የአኗኗር ዘይቤያችንን ሳንቀይር፤ የወገብ ሕመምን ማከም ሆነ ማስታገስ አንችልም።
ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ!
በየ 30- 60 ደቂቃ ይንቀሳቀሱ፦ በወንበር ላይ ተጣብቆ ለሰዓታት መቀመጥን ያቁሙ። በየ30-60 ደቂቃው ስልክዎ ላይ አጭር ማስታወሻ (Alarm) በመሙላት ለ1 ወይም ለ2 ደቂቃ ብቻ ተነስቶ ይቁሙ፤ ቢሮ ውስጥ ይራመዱ፤ ሰውነትዎን ያሳስቡ። ይህ በጡንቻዎችዎ ላይ የተከማቸውን ጫና ሙሉ በሙሉ ያቀልልዎታል።
የስራ ቦታዎን ከቻሉ ለእርሶ ምቹ ያድርጉ (Office Ergonomics)፦ ኮምፒውተር ሲጠቀሙ የኮምፒዩተሩ ስክሪን ጫፍ የቅንድብዎ የላይኛው ክፍል ጋር እኩል መሆን አለበት። ክንድዎ እና ጭንዎ ደግሞ ከወለሉ ጋር 90 ዲግሪ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህ አንገትዎን እንዳይደፉ፤ ከወገብዎ እንዳይታጠፉ በማድረግ ወገብዎ ላይ አካላዊ ጫና እንዳይፈጥሩ ያግዛል።

የሆድና የጀርባ ጡንቻዎችን በስፖርት ማጠንከር፦ ወገብዎ ጠንካራ እንዲሆን ከተፈለገ ደጋፊ ጡንቻዎቹ (Core muscles) መጎልበት አለባቸው። በሳምንት ለጥቂት ቀናት ቀለል ያሉ የእግር ጉዞዎችን ያድርጉ። የጀርባ ማሳሳብ እንቅስቃሴዎችን ያዘውትሩ። ከቻሉ ዋና ይዋኙ።እነኝህም ወገብን ከማስታገስ ባለፈ፤ ወደፊት መልሶ እንዳይቀሰቀስ የመከላከል ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው ሳይንሳዊ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።
ወገብዎ ሲያም አልጋ ላይ ተኝቶ መቆየት ይሻላል?
ለአብዛኛው ተራ የወገብ ሕመም ረዥም ጊዜ እረፍት ከመስጠት ይልቅ በተቻለ መጠን ቀላል የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን መቀጠል ይመከራል።
እዚህ ጋር አንድ ደስ የሚል እውነታ አለ!

አዲስ የጀመረ የወገብ ሕመም ብዙ ጊዜ ፤በራሱ ጊዜ ይሻሻላል። ሀኪም ቤት ሳይሄዱ የሕይወት ዘይቤዎን በማስተካከል ቭቻ ሊሻልዎ ይችላል። አንድ የቅርብ ጊዜ ሰፊ ጥናትም፤ ይህንን አረጋግጧል። አዲስ የወገብ ሕመም ከጀመራቸው ሰዎች መካከል፤ አብዛኛዎቹ ሕመማቸው በመጀመሪያዎች 6 ሳምንታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
ለዚህም አንድ ቀን የወገብ ሕመም ስላጋጠምዎ ብቻ የዲስክ ችግር ነው ብለው አይደንግጡ!
ታድያ መቼ ነው ሐኪም ቤት መሄድ ያለብዎ?
እዚህ ላይ ትኩረት ይስጡ!

የወገብ ሕመም በአብዛኛው ከባድ ባይሆንም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ቤት ውስጥ ማስታመም አይመከርም። ለዚህም የሚከተሉትን ምልክቶች ካዩ አስቸኳይ የሕክምና ምርመራ ያስፈልግዎታል፦
ከጉዳት በኋላ የመጣ ሕመም ከሆነ፦ ሕመሙ ከከባድ መውደቅ፣ ከአደጋ ወይም ከሌላ አካላዊ ጉዳት በኋላ ወዲያውኑ ከጀመረ፣
የእግር መዳከም ካለ፦ ከወገብ ህመሙ ጋር ተያይዞ እግር ላይ ከፍተኛ ድካም ወይም ከቀን ወደ ቀን የሚጨምር ሕመም ከተሰማዎት፣
መደንዘዝ ካለ ፦ ሕመሙ ከከፍተኛ መደንዘዝ ጋር ከተያያዘ እና ከወገብ ጀምሮ ወደ እግርዎ ከተሰራጨ፣
የስሜት መቀነስ ካለ፦ ከወገብ ህመሙ ባሻገር በብልት ወይም በመቀመጫ አካባቢ የንክኪ ስሜት ከቀነሰ ወይንም ሲነኩ አልያም ልብስ ሲለብሱ ስሜት ካልተሰማዎት
አካላዊ ቁጥጥር ማጣት ካለ፦ ከወገብ ህመሙ ጋር ተያይዞ ሽንትን ወይም ሰገራን የመቆጣጠር ችግር ድንገት ከተከሰተ፣
ትኩሳት ካለ፦ ከወገብ ሕመሙ ጋር ከፍተኛ የሰውነት ትኩሳት አብሮ ካለ፣
የክብደት መቀነስ ካለ ፦ ያለምንም ምክንያት ድንገተኛና ያልታሰበ የሰውነት ክብደት መቀነስ ካዩ፣
የካንሰር ታሪክ፦ ከዚህ በፊት በሕክምና የታወቀ የካንሰር ታሪክ ካለዎት፣
በአቅራቢያዎ ያለ የጤና ተቋም ይሂዱ። የጤና ባለሙያ ያማክሩ። በእነኝህ ሁኔታዎች ውስጥ ከቤትዎ መቆየት አደጋ አለው።
ወደ ተነሳንበት ጥያቄ እንመለስ
ይህ የዘመናችን ትውልድ ብቻ የመጣ አዲስ ጣጣ ነው? የዘመኑ ሰው ደካማ ሆኖ ነው?

የወገብ ሕመም ድሮም የነበረ የሰው ልጅ የጤና ፈተና ነው። ነገር ግን በዘመናችን በአሳሳቢ መልኩ መጨመሩ በሁለት ምክንያቶች ሊገለጽ ይችላል።
የእንቅስቃሴያችን መዳከም ፦የዘመናችን ቴክኖሎች እድገት ውሏችንን ሙሉ በሙሉ በቢሮ ወንበሮች፣ በመኪና ውስጥ አልያም በምቹ ሶፋዎች ላይ እንድናሳልፍ አድርጎናል። ስልኮቻችን ላይ አንገት ደፍተን ለሰአታት እናሳልፋለን። ይህም ሰውነታችን ለረዥም ሰዓት እንዳይንቀስቀስ አድርጎታል። ይህም ለወገብ ህመም ያጋልጠናል።
ከዚህም ባሻገር ለጤናችን የምንጠውው ትኩረት ጨምሮአል። ድሮ ወገብ ሲያም “እድሜ ነው” ተብሎ በዝምታ ይታለፍ ነበር። ዛሬ ግን ወጣቱ ትውልድ ስለ ጤናው በግልጽ መናገርና መፍትሔ መፈለግ በመጀመሩ እሮሮው ይበልጥ ጎልቶ እንዲሰማ አድርጎታል።
ስለዚህ የወገብ ሕመም የዕድሜ መግፋት መለኪያ ወይም የትውልድ ድካም ምልክት አይደለም። ይልቁንም ሰውነታችን “ለረጅም ሰዓት በአንድ ቦታ አስረኸኛል፤ እባክህን ተነሳና አንቀሳቅሰኝ!” እያለ የሚያሰማው፤ ተፈጥሯዊ ጥሪ ነው።
ዛሬውኑ እንቅስቃሴ በማድረግ ወገባችንን እንታደገው!




Comments